የሕግ አገልግሎትን ለመቆጣጠር የወጣ ረቂቅ አዋጅ

Jun 17 2019

 

 

አዋጅ ቁጥር ........./2011

የሕግ አገልግሎትን ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ

 

ሉላዊነት በጥበቅና ሙያ ቁጥጥር እና በተቆጣጣሪው አካል ላይ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት በመደቀኑ፤ ተቆጣጣሪ አካላቱ ለእነዚህ ተግዳሮቶች የሚሰጡት ግብረ መልስ የተለያየ በመሆኑ እና አብዛኛውን ጊዜ በአንድ አገር የሚደረገው ቁጥጥር በሌላ አገር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ፤

 

የኢትዮጵያ የሕግ መሠረተ ልማት ከአገሪቱ ፈጣን የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሥርነቀል ለውጥ አንጻር ኋላ ቀር መሆኑን በተገቢው ሁኔታ በመገንዘብ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎች እና የሕግ ተቋማት መልሶ ለማዋቀር እና ለማሻሻል መሠረታዊና መጠነ ሰፊ ጥረት በማድረግ ላይ በመሆኑ፤

 

በሌሎች የሕግ ዘርፎች እንደሚስተዋለው ሁሉ፣ በአገራችን በሥራ ላይ ያሉት የጥበቅና ሙያ ቁጥጥር ሥርዓት በኢትየጵያ የሚስተዋሉት አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ነባራዊ ሐቆች ለፈጠሯቸው ወቅታዊ ተግዳሮቶች በቂ ምላሽ የማይሰጡ በመሆናቸው፣

 

በሕግ አገልግሎት ገበያና የሕግ አገልግሎቱን በሚመራበት የሕግ ማዕቀፍ መካከል ያለውን ነባራዊ ሐቅ የሚያጣጥም ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ፤

 

የተለያየ የሕግ ባህል ባላቸው አገሮች ውስጥ ከሚገኙ ተሞክሮዎችን በመቅሰም በሕግ አገልግሎት መስክ ለሚነሱ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ የሕግ መሠረት መጣል በማስፈለጉ፤

 

በመላ አገሪቱ የሕግ የበላይነት፣ ተመሳሳይ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ የፍትህ ተደራሽነት ይሰፍን ዘንድ የፍትሕ አስተዳደሩ አንድ አካል የሆነ፣ ጠንካራና ነጻ የቁጥጥር ተቋማት ያሉት የተረጋጋ የጥብቅና ሙያን የሚሻ የሕዝብ ፍላጎት በመኖሩ፤

 

በሕግ የበላይነት የሚመራ ማኅበረሰብ በሕግ በተደነገገ ማዕቀፍ ውስጥ ራሱን በራሱ የመቆጣጠር ሥልጣን ያለው የጥብቅና ሙያ ያለው መሆኑ ቁልፍ የላቀ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ፤

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐበሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 (1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

 

ክፍል አንድ

ጠቅላላ ድንጋጌዎች

አንቀጽ 1 - አጭር ርዕስ

 

ይህ አዋጅ “የሕግ አገልግሎትን ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር ……../2011” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 2 - ትርጉም

 

የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፣

1· “ጠበቃ” ማለት በዚህ አዋጅ መሠረት በነጻነት የግል የሕግ አገልግሎት ሥራ ለመሠማራት ፍቃድ የተሰጠው ግለሰብ ነው፡፡

 

2· “ሕገ-መንግስት” ማለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ሕገ መንግስት ነው፡፡

 

3· “ሸማች” ማለት የህግ አገልግሎት ተቀባይ ሰው ነው፡፡

4· “ጉባዔ” ማለት የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አካል ሆኖ የፌዴራል ጠበቆችን ማኅበር ፖሊሲዎች የሚያወጣና የሚያስፈጽመው አካል ነው፡፡

 

5· “የሥነ ምግባር ጉባዔ” ማለት በፌዴራሉ የጠበቆች ማኅበር ሥር ተቋቁሞ የሙያ ሥነ- ምግባር ጥሰቶችን የሚመለከቱ አቤቱታዎችን ለመቀበል እና ውሳኔ ለመስጠት የሚችል አካል ነው፡፡

 

6· “የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ” ማለት በሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 922/2008 መሠረት የተቋቋመው መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡

 

7· “የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ” ማለት በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቃቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 መሠረት የተቋቋመው መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡

 

8· “የሕግ አገልግሎት ድርጅት” ማለት የሕግ አግልግሎት ለመስጠት በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የሕግ ባለሙያዎች የተመሠረት ድርጅት ነው፡፡

9 “የሕግ አገልግሎት” ማለት በጠበቃ ሊሰጥ የሚችል ማናቸውም አገልግሎት ሲሆን የሚከተሉትንም ያጠቃልላል፤

 

ሀ)  ለደንበኛ በሕግ ጉዳዮች ላይ ምክር መስጠት፣

ለ)  የሕግ ሰነድ ማርቀቅ ወይም በደንበኛው ስም ሰነድን ማቅረብ

 

ሐ) እንደ ፍርድ ቤቶች፣ አስተዳዳራዊ ጉባዔዎች, በፍርድ ቤት መሰል ተቋማት፣ በግልግል ዳኝነት ጉባዔዎች እና ሌሎች አማራጭ የሙግት መፍቻ መድረኮች ባሉ ማናቸውም የመንግስት ወይም መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ደንበኛን ወክሎ መቅረብ

መ) የተለየ ፍቃድ የሚያስፈልገው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሰነድን ማረጋገጥ፣

10· “ሥራን በአግባቡ ያለመወጣት ማለት” ማለት የሥነ ምግባር ደንብን የሚቃረን ማንኛውም ባህርይ ሲሆን በደንበኛ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ተገቢ ያልሆነ፣ ሕገ ወጥ ወይም ቸልተኛ ባህርይን ያጠቃልላል፤

 

11· “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 47 የተመለከተው ማንኛውም ክልል ሲሆን የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ አስተዳደሮችን አይጨምርም፤

12· “የሥነ ምግባር ደንብ” ማለት   በዚህ አዋጅ የተመለከቱ ሙያዊ መብትና ግዴታዎች በዝርዝር ለመቆጣጠር በፌዴራል ጠበቆች ማኀበር የሚወጡ ደንቦች ስብስብ ነው፤

13. “ሕገ ደንብ” ማለት የራስ-ገዝ ተቋማትን ስራዎች ለመመራት በፌዴራል ጠበቆች ማኀበር የሚወጡ ደንቦች ስብስብ ነው፤

14 “መመሪያ” ማለት በዚህ አዋጅ መሰረት ሙያውን በተመለከተ በፌዴራል መንግስት የሚወጡ ደንቦች ናቸው፡፡

15.“የተከታታይ ህግ መመሪያ” ማለት የተከታታይ ትምህርትን በተመለከተ የሚወጡ የደንብ ድነጋጌዎች ስብብስቦች ናቸው፡፡

16 በቃሉ አገባብ የተለየ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር በዚህ አንቀጽ በወንድ ጾታ የተደነገገው የሴትንም ጾታ ያካትታል፡፡

 

አንቀጽ 3 - የተፈፃሚነት ወሰን

 

ይህ አዋጅ የጠበቆችና የሕግ አገልግሎት ድርጅቶች አስተዳደርን በተመለከቱ ጉዳዩች   ሁሉ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች እንዲሁም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

 

አንቀጽ 4 - የቁጥጥር ዓላማዎችና መርኆዎች

 

1. ተቆጣጣሪው የጠበቆችን የቁጥጥር ሥራ በሚያከናውንበት ጊዜ በተቻለ መጠን ሁሉ የሚከተሉትን የቁጥጥር ዓላማዎች ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡

ሀ)  የሕግ የበላይነትን መጠበቅና ማሳደግ፣ ለ) የሸማቾችን ጥቅም መጠበቅና ማሳደግ፣

ሐ)  በሕግ አገልግሎት መስክ ሚዛናዊነትን ማረጋገጥ፣

መ) ነጻ፣ ጠንካራ፣ ንቁ፣ ዘርፈ ብዙ እና ውጤታማ የሆነ የሕግ አገልግሎት ልማትን ማበረታታት፣

ሠ)  ለሙያ መርኆዎች እና ደንቦች ተገዢ መሆንን ማሳደግና ጠብቆ ማቆየት

2. ተቆጣጣሪው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የመለከቱትን የቁጥጥር ዓላማዎች ለማሳካት አስቦ ሥራውን ሲያከናውን በሚከተሉት መርኆወፐች መመራት አለበት፡፡

ሀ) ወጪ ቆጣቢ፣

ለ) የሥራው ውጤት ሥራው ከሚሠራበት መንገድ ጋር ተመጣጣኝ መሆን፣ ሐ) የባለድርሻ አካላት ሚዛናዊና ውጤታማ ተሳትፎ መኖር፣

መ) ለህግ ተግዢነትን በማስቀደም የህግ ማስከበር ስራ መስራት ሠ) ነጻነት፣

ረ) ግልጽነት፣ እና

ሰ) ወጥነትና እና እኩልነት

 

ክፍል ሁለት

የቁጥጥር ተቋማት

ንዑስ ክፍል አንድ

የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር

 

አንቀጽ 5 -  መቋቋም

 

1. የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር (ከዚህ በኋላ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በመባል የሚጠራ) ነጻ አካል ሆኖ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡

2. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት አለው፡፡

3. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ወደ ማኀብሩ እንዲገቡ የተፈቀደላቸውን ጠበቆች እና የተመዘገቡ የሕግ አገልግሎት ድርጅትች በሙሉ ያካትታል፡፡

 

አንቀጽ 6 - ዋና መሥሪያ ቤት

የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ ሲሆን በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ሊኖሩት ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 7 - ዓላማዎች

1. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው

ሀ) በሕግ አገልግሎት መስክ አግባብነት ያለው የቁጥጥር ሥርዓት መኖሩን ማረጋገጥ፣

ለ) በጠበቆችና በሕግ አገልግሎት ድርጅቶች ለሚሰጡ የሕግ አገልግሎቶች መለኪያዎችን ማስቀመጥ፣

ሐ) የሸማቾች ጥቅም መጠበቁን ማረጋገጥ፣

መ)  የሸማቾችን   ጥቅም  ለማስጠበቅ  ጠቀሜታ  ያላቸውን  የሕግ  ባለሙያዎች   መብቶች መፈጸማቸው መከታተል፣

ሠ)  የጥብቅና  ሙያ  እና  የኢትዮጵያ  የሕግ  ሥርዓት  እንዲለማ  እንዲያድግ  አስተዋጽዖ ማድረግ፣

ረ)  አባላቱ  የሕግ  አገልግሎትን   የሚሰጡት   በዚህ  አዋጅና  በሌሎች  አግባብነት   ባላቸው ሕግጋት መሠረት መሆኑን ማረጋገጥ፣

ሰ) በአገሪቱ ያሉት የቁጥጥር ሥርዓቶች የተጣጣሙ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ

 

2. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በሚወስዳቸው ማናቸውም እርምጃዎችና ውሳኔዎች የሕዝብ ጥቅም ማስፈን እና ማክበር አለበት፡፡

 

አንቀጽ 8 - የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በጀት

 

የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በጀት የሚገኘው ከሚከተሉት ምንጮች መሆን አለበት፡፡ ሀ. በዚህ አዋጅ መሠረት የሚያገኛቸው ገቢዎች፣

ለ. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ዓላማውን እንዲያሳካ ለማስቻል ከመንግስት የሚመደብ የድጋፍ በጀት፣

ሐ. ሌሎች ምንጮች

 

አንቀጽ 9 - ሕገ ደንብ

የፌዴራል  ጠበቆች  ማኅበር  ይህንን   አዋጅ  ለማስፈጸም  የሚረዱትን  ሕገ  ደንቦች ማውጣት አለበት፡፡

 

አንቀጽ 10 - ከመንግስት ጋር ስለሚኖር ግንኙነት

 

1. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በኩል ከመንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ጠብቆ ማቆየት አለበት፡፡

2. ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የፌዴራል ጠበቆች ማኀበር ውሳኔ ወይም እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ብሎ ሲያምን ጉዳዩን ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት በማቅረብ ውሳኔው ወይም እርምጃው እንዲሻር ማመልከት ይችላል፡፡

3. የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ያወጣው መመሪያ፣ የወሰደው እርምጃ ወይ የሠጠው ውሳኔ ሕገ ወጥ ነው ብሎ ሲያምን ሥልጣን ላላው ፍርድ ቤት ጉዳዩን በማቅረብ እንዲሻር ወይም እንዲከለስ መጠየቅ አለበት፡፡

 

4. መንግስት አስፈላጊውን     የገንዘብ ወይም   ሌሎች     ድጋፎች   በማድረግ          የፌዴራል   ጠበቆች ማኅበርን መደገፍ አለበት፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሁለት

የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የሥራ ክፍሎች

 

አንቀጽ 11 - 

 

1. በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የሚከተሉት የሥራ ክፎሎች መኖር አለባቸው፡፡

ሀ) ጠቅላላ ጉባኤ

ለ) ምክር ቤት

ሐ) ኮሚቴዎች

መ) ኦዲተሮች

ሠ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ረ) አስፈላጊው ሠራተኞች

 

አንቀጽ 12 - የአባላቱ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ

 

1. የአባላቱ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ከፍተኛው የሥልጣን አካል ነው፡፡

2. የአባላቱ ጠቅላላ ጉባዔ በዚህ አዋጅ መሠረት ፍቃድ ያላቸውን ሁሉም ጠበቆች ማካተት አለበት፡፡

3. በዚህ አዋጅ መሰረት ድንገተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የሚያስጠራ ምክንያት ከሌለ በቀር የአባላቱ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ በዓመት አንድ ጊዜ መካሄድ አለበት፡፡

4. አባላት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ የመገኘትና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካላጋጠማቸው በስተቀር ሲመረጡም ማገልግል አለባቸው፡፡

 

አንቀጽ 13 - የጠቅላላ ጉባዔ ሥልጣን

 

ጠቅላላ ጉባዔ የሚከተሉት ሥልጣኖች አሉት፡-

ሀ) የምክር ቤት እና የኮሚቴዎች አባላትን ይመርጣል፣

ለ) የአባላትነት መዋጮን ጨምሮ ክፍያዎችን ይወስናል፣

ሐ) በዚህ አዋጅ የተገለጸውን ሕገ ደንብ እና የሥነ ሥርዓት ደንቦች ማድደቅ፣

መ) የፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ስታራቴጂክ ዕቅድ፣ ዓመታዊ ዕቅድና በጀት ማጽደቅ፣

ሠ) ምክር ቤቱ ከተጠያቂነት ነጻ እንዲሆን ውሳኔ ማስተላለፍ፣

ረ) የምክር ቤቱን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና የውጪ ኤዲተሮችን ሪፖርት ማጽደቅ፣

ሰ) ለአባላቱ ጠቅላላ ጥቅም እና ለፍትህ ተደራሽነት ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ መወያየት፣

ሸ) ለፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ማንኛውም አካል በግልጽ ባልተሰጡ ጉዳዮች ላይ መወሰን፣

ቀ) የውጭ ኤዲተሮችን መሾም

 

አንቀጽ 14 - ስብሰባ እና ሥነ ሥርዓት

 

1. ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ መካሄድ ያለበት የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ጠቅላላ አባላት በጉባዔው እንዲሳተፉ ጥሪ መደረጉን ማወቃቸውን በሚያረጋግጥ መንገድ መሆን አለበት፡፡

2. የጠቅላላ ጉባዔው ጥሪ ከጠቅላላ ጉባዔው ቢያንስ ከሃያ ቀናት በፊት በስፋት በሚሰራጭ ጋዜጣ እና በማኅበሩ ድረገጽ ታትሞ መውጣት አለበት፡፡

3. የጠቅላላ ጉባዔው አጀንዳ ከጠቅላላ ጉባዔው ጥሪ ጋር አብሮ መታተም አለበት፡፡

4. ቀድሞ ተገቢው ማስታወቂያ ባልተነገረበት ማናቸውም ጉዳይ ላይ ውሳ መወሰን አይቻልም፡፡

5. ምክር ቤቱ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 20(ሐ) መሠረት ድንገተኛ መደበኛ ጉባዔ እንዲጠራ ጥያቄ በቀረበለት በአሥር ቀናት ውስጥ ድንገተኛ መደበኛ ጉባዔው እንዲከናወን ካላደረገ ስብሰባው እዲካሄድ ጥያቄ ያቀረቡት አባላት ምክር ቤቱ ጥያቄውን በተቀበለ በሁለት ወር ውስጥ ስብሰባ ማካሄድ ይችላሉ፡፡

6. በማናቸውም ስሰባዎች ላይ እያንዳንዱ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አባል አንድ ድምጽ ብቻ ይኖረዋል፡፡

7. የሚጻና ውሳኔ መወሰን የሚቻለው ከአባቱ ሃምሳ በመቶው በስብሰባ ላይ ከተገኙ እና በስብሰባ ከተገኙት አባላት መካከል አብላጫው ከደገፉት ነው፡፡ ምልዓተ ጉባኤ ባለመሟላቱ ለሁለተኛ ጊዜ በተጠራ ስብሰባ ላይ ከተገኙት አባላት የአብዛኛዎቹን ድምጽ ያገኘው ውሳኔ ሊተላለፍ ይቻላል፡፡

8. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ሕገ ደንብ ስብሰባ የሚራበትን እና የሚመራበትን ዝርዝር ሁኔታ ማውጣት ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 15 - ምርጫ

 

1. ከምርጫ ዘመን አንድ ዓመት በፊት ጠቅላላ ጉባዔው አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሜቴ ይሰይማል፡፡

2. ኮሚቴው ከጠቅላላ ጉባዔው ሦስት ወራት ቀደም ብሎ የዕጩዎችን ጥቆማ ይቀበላል፡፡

3. በጠቅላላ ጉባዔው በጸደቀው  ሕገ  ደንብ  በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት  የዕጩዎች ዝርዝር ይዘጋጃል፡፡

4. ምርጫው በሚስጥር በሚሰጥ ድምጽ መከናወን አለበት፡፡

5. የተጓደሉ አባላትን ለመተካት የሚደረግ ምርጫ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ሥነ ሥርዓቶችን ሳይከተል ሊካናወን ይችላል፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሦስት

ምክር ቤቱ

 

አንቀጽ 16 - አባላት

 

የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ሰባት ድምጽ የሚሰጡ አባላት ያለው ምክር ቤት ይኖረዋል፡፡

 

አንቀጽ 17 - የአገልግሎት ዘመን

 

1. የምክር ቤቱ አባላት የሥራ ዘመን ሦስት ዓመት ነው፡፡ አባላቱ ለሁለተኛ የሥራ ዘመን መመረጥ ይችላሉ፡፡

2. ከምክር ቤቱ አባላት መካከል በሞት፣ በሥራ መልቀቅ፣ መሥፈርቱን ባለማሟላት፣ ወይም በሌላ ማናቸውም ተመሳሳይ ምክንያት የጎደሉ ካሉ ምክር ቤቱ በቀድሞ ምርጫ ዕጩ ከነበሩ ሰዎች መካከል መርጦ መተካት አለበት፡፡

 

አንቀጽ 18 - ተገቢነት

1. ቢያንስ ለሦስት ዓመታት አባል የነበረ ጠበቃ ለምክር ቤት አባልነት ለመመረጥ ብቁ ነው፡፡

2. ከምርጫ ዘመኑ በፊት በነበሩት ሁለት ተከታታይ የሥራ ዘመናት የምክር ቤቱ አባል ያልነበረ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አባል ለምክር ቤት አባልነት ዕጩ ሆኖ ለመቅረብ ብቁ ነው፡፡

 

አንቀጽ 19 - ድምጽ የማይሰጡ የምክር ቤቱ አባላት

 

1. የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እያንዳንዳቸው አንዳንድ የምክር ቤት አባላት መመደብ አለባቸው፡፡

2. ተወካዮቹ በስብሰበው ላይ የውይይት አጀንዳ ማስያዝና በምክር ቤቱ ውይይት ላይ መሳተፍ ቢችሉም ድምጽ የመስጠት ሥልጣን የላቸውም፡፡

3. ከአሁኑ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ፕሬዚዳንት በፊት የነበረው ፕሬዚዳንት የምክር ቤቱ አባል ተደርጎ ባይመረጥም እንኳን ድምጽ የማይሰጥ የምክር ቤቱ አባል ሆኖ በምክር ቤቱ ስሰባዎች ላይ የመገኘትመብት አለው፡፡

4. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ድምጽ የማይሰጥ የምክር ቤቱ አባል ነው፡፡

 

አንቀጽ 2 - የምክር ቤቱ ሥልጣን

 

ምክር ቤቱ የሚከተሉት ሥልጣኖች ይኖሩታል፡፡

ሀ)    የፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ማስተዳደር፣

ለ)  የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔን መጥራት፣

ሐ) የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አንድ ሦስተኛ አባላት በአንድ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራላቸው በጽሑፍ ጥያቄ ካቀረቡ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት፣

መ) በጠቅላላ ጉባዔ በአብላጫ ድምጽ የተላለፉ ውሳኔዎችን መፈጸም፣

ሠ) በጠቅላላ ጉባዔ እንዲጸድቁ የሚቀርቡ የፖሊሲ እና የፕሮግራም ሰነዶችን ማዘጋጀት፣

ሰ) ለጠቅላላ ጉበዔ የሚቀርብ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ወቅታዊ የሠራ አፈጻጸም እና የሒሳብ ሪፖርቶች ማዘጋጀት ወይም እንዲዘጋጁ ማድረግ፣

ረ) የፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና በሥራ አስፈጻሚው የሚቀርቡ የበላይ አመራሮችን መሾም፣

ሸ)  ዋና  ሥራ  አስፈጻሚው   ከሌሎች  ሠራተኞች  ጋር  በመሆን የማኅበሩን  የባንክ  ሒሳብ እንዲከፍትና ውል እንዲዋዋል ሥልጣን መሥጠት፣

ቀ)  የምክር ቤቱን ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ማቋቋም፣ በ) የኮሚቴ አባላትን መሾም ወይም ለሹመት ማቅረብ፣

ተ) በዚህ አዋጅ በተሰጡት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማስተላለፍ፣ ቸ) የኮሚቴዎችን የሥራ አፈጻጻም መከታተል፣

ነ)  ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶችን መክፈት፣

ኘ) በዚህ አንቀጽ ከተሰጡት ሥልጣኖች መካከል የተወሰኑትን ለሌሎች የማኅበሩ ሠራተኞች መወከል እና

ኀ) በጠቅላላ ጉባዔ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ማከናወን፡፡

 

አንቀጽ 21 - የምክር ቤቱ ሠራተኞች

 

1. ምክር ቤቱ ፕሬዚደንት፣ ምክትል ፕሬዚደንት እና ገንዘብ ያዥ ይኖሩታል፡፡

2. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ፕሬዚደንት፣ ወይም እሱ በሌለ ጊዜ ምክትል ፕሬዚደንቱ በምክር ቤቱ እና በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ሁሉም ስብሰባዎች ላይ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆነው ይሠራሉ፡፡

3. ገንዘብ ያዡ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን አጠቃላይ የገንዘብ መዋዕለ ንዋዮችና ሐብቶችን የማስተዳደርና ለጠቅላላ ጉባዔው የማኅበሩን ዓመታዊ የሂሳብ ሪፖርት የማቅረብ ኃላፊነት አለበት፡፡

 

ንዑስ ክፍል አራት

የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ኮሚቴዎች

 

አንቀጽ 22 - ኮሚቴዎች

1. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ቋሚና ጊዜያዊ ልዩ ኮሚቴዎች ይኖርታል፡፡

2. የማኅበሩ ቋሚ ኮሚቴዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ) የቅበላ ኮሚቴ፣

ለ) ተከታታይ የሕግ ትምህርት ኮሚቴ፣

ሐ) የሥነ ምግባር ኮሚቴ፣ እና

መ) የአደራ ሂሳብ ኮሚቴ

3. የምክር ቤቱ ኮሚቴዎች የሥራ ዘመን ሁለት ዓመት ነው፡፡

4. ጠቅላላ ጉባዔው እንደአስፈላጊነቱ ተጨማሪ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ሊወስን ይችላል፡፡

5. የኮሚቴዎች ተጠሪነት ለምክር ቤቱ ነው፡፡

6. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 (ሀ)፣ (ለ) እና (መ) የተጠቀሱት ኮሚቴዎች ከአባላቶቸቸው አንድ ሦስተኛው የሚሾሙት በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡

 

አንቀጽ 23 - የወል ድንጋጌዎች

 

እያንዳንዱ ኮሚቴ

1. ከተሰጠው የስር ዘርፍ ጋር ተያያዥ የሆኑ በዚህ አዋጅና አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕግጋት የተደነገጉ ደንቦችን መፈጸም፣

2. ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚረዱትን መመሪያዎችና ሥነ ሥርዓቶችን ማዘጋጀት፣

3. በዓመት አንድ ጊዜ ወይም ምክር ቤቱ በጠየቀ ማናቸውም ጊዜ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ማድረግ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 24 - የቅበላ ኮሚቴ

 

1. የቅበላ ኮሚቴ ቅበላን የሚመለከቱ የሕጉን ድንጋጌዎች ያስተዳድራል፡፡

2. በተለይም ልዩ አዋቂ አባላት ባሉት ጊዜያዊ ኮሚቴ የቅበላ ፈተና እንዲወጣ ያደርጋል፡፡

3. ፍቃድ ከመሰጠቱ በፊት በሕግ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ያረጋግጣል፡፡

4. የጥብቅና ፍቃድ  ለማግኘት  የሚቀርቡ  ማመልከቻዎችን ሒደት  ያካነውናል፣  ፍቃድም ይሰጣል፡፡

 

አንቀጽ 25 - የተከታታይ የሕግ ትምህርት ኮሚቴ

 

1. የተከታታይ የሕግ ትምህርት ኮሚቴ የተከታታይ የሕግ ትምህርትን የሚመለከቱ የሕጉን ድንጋጌዎች ያስተዳድራል፡፡

2. ኮሚቴው ከጠበቆች፣ ከሕግ ትምህርት ቤቶች፣ ከሕግ አውጪዎች፣ ከፍርድ ቤቶች እና ከሌሎች አግባብነት ያላቸው ተቋማት የተወከሉ በፌዴራል የጠበቆች ማኅበር በቀጥታ የሚሾሙ አምስት አባላት ይኖሩታል፡፡

3. ምክር ቤቱ ሰብሳቢውን እና ምክትል ሰብሳቢውን ይሾማል፡፡

 

አንቀጽ 26 - የተከታታይ የሕግ ትምህርት ኮሚቴ ሥልጣንና ተግባራት

 

ኮሚቴው የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይሩታል፡-

1. በምክር ቤቱ ዕውቅና የተሰጣቸውን መሥፈርች መሠረት አድርጎ የተከታታይ የሕግ ትምህርት ሰጪዎችን ተቀብሎ ይወስናል፣

2. የተከታታይ የሕግ ትምህርት ላይ ስለሚሰጡ የትምህርት ዘርፎች ሊይዙት ስለሚገባቸው የስልጠና ጊዜ መጠን ይወስናል፡፡

3. ከዚህ ደንብና በኮሚቴው ከተወሰኑ ሌሎች ደንቦች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሥልጠና ሰጪዎችን፣ የሥልጠና ክፍሎችን፣ የሥልጠና ስርዓተ ትምህርትን፣ የትምህርት መሣሪያዎችን፣ ግብዓቶችን፣ ከተከታታይ የሕግ ተምህርት የተገኘ ገቢን ጨምሮ ሥልጠና አገልግሎትን ክንውኖች ኤዲት ያደርጋል፣ ይፈትሻል፣ ይመረምራል፣ ይከልሳል፣

4. በተከታታይ የሕግ ትምህርት መመሪያ መሠረት ይህንን አዋጅ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ሕግጋትን በሚጥሱ የተከታታይ የሕግ ትምህርት ሰጪዎች ላይ በምክር ቤቱ አጸድቆ ተገቢውን ቅጣት ይጥላል፡፡ ሆኖም ቅጣቱ የተጣለበት ሰው የቅጣት ውሳኔው በተላለፈ በ15 ቀናት ውስጥ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ከተፈጸመ ብቻ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት ይችላል፡፡

5. ከተከታታይ የሕግ ትምህርት ጋር በተያያዘ የሚወጡ ወጪዎችን ለመተካት በጠበቆችና በተከታታይ የሕግ ትምህርት ሰጪዎች ላይ የሚጣል የክፍያ መጠንን በተመለከተ የውሳኔ ሐሳብ ይጠቁማል፡፡

 

አንቀጽ 27 - የሥነ ምግባር ኮሚቴ

 

1. የሥነ ምግባር ኮሚቴ የጠበቆች የሥራ አፈጻጸም ከሙያ ሥነ ምግባር ደንብ ጋር የተጣጠመ መሆኑን ይከታተላል፣

2. ምክር ቤቱ ማስጠንቀቂያን በተመለከተ የሚወስዳቸውን እርምጃዎችና ውሳኔዎች ያዘጋጃል፣

3. የሙያ ሥነ ምግባር ደንቡን በሚጥሱ ጠበቆች ላይ ክሥ እንዲመሠረት ሊያደርግ ይችላል ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 28 - የጠበቆች ትረስት ሂሳብ ኮሚቴ

 

የጠበቆች  ትረስት  አካውንት  ኮሚቴ  ምክር ቤቱ  የጠበቆች  ሃብት አስተዳደር  እና  የገንዝብ አደላደልን በሚመለከት የሚወስዳቸውን እርምጃዎችና ውሳኔዎች ያዘጋጃል፡፡

 

ንዑስ ክፍል አምስት

 

አንቀጽ 29 - ዋና ሥራ አስፈጻሚ

1. ዋና ሥራ አስፈጻሚው የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው፡፡ በምክር ቤቱ በሚሰጠው ጠቅላላ መመሪያ መሠረትም የፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ተግባራት ያከናውናል፡፡

2. ዋና ሥራ አስፈጻሚው በተለየም የሚከተሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች አሉት፡-

ሀ. በምክር ቤቱ መመሪያ መሠረት የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ሠራተኞችን ይቀጥራል ያስተዳድራል፣

ለ.  የፌዴራል   ጠበቆች   ማኅበርን  የባንክ  ሒሳቦች  በሒሳብ   መመሪያው   መሠረት ያንቀሳቅሳል፣

ሐ. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ዓመታዊ ዕቅድ፣ በጀት እና የሥራ ሒደት ሪፖርት አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ያቀርባል፣

መ. ውል ይዋዋላል፡፡ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ከሦስተኛ ወገኖች ጋር ባለው ግንኙነትን ማኅበሩን ይወክላል፣

ሠ.በሚያስፈልገው  መጠን  በውክልና  ለሾማቸው   ወኪሎቹ   ሥልጣኖቹን  በውክልና ይሰጣል፣

ረ.የሂሳብ  ሥርዓት  በአግባቡ   መዘርጋቱን  እና  የሒሳብ  ሰነዶች  በአግባቡ  መያዛቸውን ያረጋግጣል፣

3. የዋና ሥራ አስፈጻሚ ተጠሪነት ለምክር ቤቱ ነው፡፡

 

አንቀጽ 30 - ሠራተኞች

በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር እና የአስተዳደር ሥራ መደብ ባልያዙ ሠራተኞቹ መካከል ያለው ግንኙነት በአሠሪና ሠራተኛ ሕግ መሠረት ይገዛል፡፡

 

ክፍል ሦስት

ቅበላ እና ፍቃድ

ንዑስ ክፍል አንድ

ቅበላ

 

አንቀጽ 31 - መርኅ

 

1. በፌዴራል የጠበቆች   ማኅበር  ፍቃድ  ሳያገኝ   ማንም  ሰው  በሕግ  አገልግሎት   ላይ መሠማራት አይችልም፡፡

2. በዚህ ክፍል የተቀመጡትን መስመርቶች የሚያሟላ ማንኛውም ሰው በጠበቃናት ጠበቃ ሆኖ በሕግ አገልግሎት እንዲሰማራ ተቀባይነት ያገኛል፡፡

 

3. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አንድ የተገለጸው መብት እንደ ጾታን፣ ኃይማኖትን፣ ዘሩን ወይም ማኅበራዊ አመጣጡን፣ የፖለቲካ አመለካከቱን፣ ንብረቱን፣ ትውልዱን ወይም የአካል ጉዳቱን ወይም ማንኛውንም አመለካከቱን መሠረት ተድርጎ ሊከለከል አይችልም፡፡

 

አንቀጽ 32 - የብቁነት መሥፈርት

 

የሚከተሉትን መሥፈርች የሚያሟላ ማንኛውም ሰው በጠበቃነት ለመሥራት ተገቢነት አለው፡-

ሀ) ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው፣

ለ) በኢትዮጵያው ዕውቅና ከተሰጠው የሕግ ትምህርት ቤት በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው፣

ሐ) በዚህ ክፍል በተገለጸው መሠረት የሁለት ዓመት ልምምዱን በስኬት ያጠናቀቀ፣

መ) በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በሚወሰነው መሠረት የቅበላ ፈተናውን ማለፉን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ማቅረብ የሚችል፣

ሠ) ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው፣ እና

ረ) በሕግ አገለግሎት አንዳይሠማራ በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ያልተከለከለ፡፡

 

አንቀጽ 33 - ብቁ አለመሆን

1. ማንኛውም ሰው በሚከተሉት ምክንያቶች በጠበቃነት ለመሥረት ብቁ አይሆንም፡-

ሀ) ዕምነት ማጉደልን ወይም ማታለልን መሠረት ባደረገ ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ ከተባለ፣ ወይም

ለ) ባለፉት አምስት ዓመታት መክሰሩ ከታወጀበበት፣ ወይም

ሐ) በዚህ አዋጅ እና አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጡ ደንቦች መሠረት ከጠበቆች ማኅበር ከታገደ እና ዕግዱ ከሚጸናበት ጊዜ ጀምሮ ሁለት ዓመት ካለለፈ፣ ወይም

መ) ከቅጥር ሥራው ከተባረረ ወይም ከመንግስት መሥሪያ ቤት ወይም ከተነሳ ወይም ዕምነት ማጉደልን ወይም ማታለልን መሠረት ባደረገ ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ ከተባለ፣ ወይም

ሠ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሕግ መምህርነት የሥራ መደብ ተቀጥረው ከሚሠሩ በስተቀር በማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል መሥሪያ ቤት የሙሉ ሠዓት ሥራ ያለው

2. አንድ ጠበቃ በተደራቢነት የመንግስት የሕግ አውጪ ወይም የአስፈጻሚው አካል አባል መሆን አይችልም፡፡

 

አንቀጽ 34 - የውጭ ሐገር ዜጋ የሆኑ ጠበቆች

 

በሚከተሉት  መሥፈርቶች   ብቻ  ካልሆነ  በስተቀር  ማንኛውም  የውጭ   አገር   ዜጋ በኢትዮጵያ ውስጥ በጥብቅና ለመሥራት አይፈቀድለትም፡-

ሀ) ትውልደ ኢትዮጵያዊ መሆኑን የሚገልጽ መዋቂያ ያለው፣

ለ) በውጭ አገር የሕግ አገልግሎት ለመስጠት ብቁ የሆነ፣ እና

 ሐ) በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በሚወሰነው መሠረት የቅበላ ፈተናውን ማለፉን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ማቅረብ የሚችል፣

 

አንቀጽ 35 - ፈተና

 

1. በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ጠበቃ ለመሆን የቅበላ የጽሑፍ ፈተና መዘጋጀት አለበት፡፡ የቅበላ ፈተናው ሥነሥርዓት እና ጊዜ በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ይወሰናል የተዳደራል፡፡

2. የቅበላ የጽሑፍ ፈተናው በፌዴራል መንግስት የሥራ ቋንቋ መሠረት መዘጋጀት አለበት፡፡

3. የቅበላ የጽሑፍ ፈተናውን በስኬት ያጠናቀቀ ሰው ፈታናውን ማለፉን የሚያረጋግጥ ማሥረጃ ይሰጠዋል፡፡

4. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት የተሰጠ ማረጋገጫ የተቀበለው ሰው ፈተናውን ካለፈ በኋላ በአንድ ዓመት ውስጥ የሕግ አገልገሎት ሥራውን ካልጀመረ ማረጋገጫው ተቀባይነቱን ያጣል፡፡

 

አንቀጽ 36 - ሥልጠና

 

1. አንድ አመልካች ለቅበላ አስፈላጊ የሆነው የልምምድ መሥፈርት አሟልቷል የሚባለው በዳኛ፣ በጠበቃ ወይም በሕግ አገልግሎት ድርጅት ተቆጣጣሪነት ለሁለት ዓመት የህግ አገልግሎት ስራ መሥራቱን ወይም ሁለት ዓመት የሥራ ላይ ሥልጠና የሠለጠነ መሆኑን ማረጋገጥ ከቻለ ነው፡፡

2. ለቅበላ ዓላማ ከምርቃት በኋላ የተከናወነ የመስክ ልምምድ እንደ ልምምድ ይቆጠራል፡፡ የመሥክ ልምምዱ ሁለት ዓመት መሙላት አለበት፡፡ ተለመማጁ ከተቆጣጣሪው ደሞዝ/ክፍያ መቀበል አይከለከለም፡፡

3. ተለማማጅ ከልመምምድ ጊዜው ጎን ለጎን ትምህርቱን እየተከታተለ ከነበረ ለልምምዱ ዓላማ ትምህርቱን የተከታተለባቸው ጊዜያት በልምምድ ጊዜው ውስጥ ተካተተው አይቆጠሩም፡፡

 

አንቀጽ 37 - የቅበላ ማመልከቻ

 

1. በጠበቃነት ለመሥራት የሚፈልግ ሰው የጽሑፍ ማመልከቻ ለፌዴራል የጠበቆች ማኅበር በማቅረብ የቅበላ ፍጎቱን መግለጽ ይችላል፡፡

2. ከቅበላ ማመልከቻው ጋር በዚህ አዋጅ የተመለከቱት የቅበላ መስፍረቶች መሟላታቸውን የሚያረጋግጡ ማሥረጃዎች ተያይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡

3. አመልካቹ የተሟላ የቅበላ ማመልከቻ በቀረበ በአንድ ወር ውስጥ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በቅበላ ማመልከቻው ላይ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

4. የቅበላ ማመልከቻ ታግዶ ሊቆይ የሚችለው የቅበላ ማመልከቻውን ውድቅ ሊያደርገው የሚችል ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ከሆነ ብቻ ነው፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሁለት

ፍቃድ

አንቀጽ 38 - ፍቃድ

 

1. ቅበላ በሕግ ፊት የጸና የሚሆነው በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ፍቃድ በተሰጠ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

2. በሕግ የተቀመጡትን መሥፈርቶች የሚያሟላና በዚህ አዋጅ የተቀመጠውን መሥፈርት የሚያሟላ የሙያ ኃላፊነት መድን እንዳለው ማሥረጃ ማቅረብ የሚችል ሰው ፍቃድ ይሰጠዋል፡፡

3. ፍቃድ ከመሰጡ በፊት አመልካቹ የጽሑፍ መግጫ መስጠት አለበት፡፡ ከአመልካቹ ዕምነት ጋር የተጣጣመ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ለውጦች እንደተጠበቁ ሆነው የጽሑፍ መግለጫው የሚሰጠው በሚመለከተው ቅርጽ ነው፡-

“እኔ [የአመልካቹ ሥም]፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴራል ጠበቃነት ሳገለግል ሥራዬን በእውነትና በሐቀኝነት፤ ሕገ መንግስቱን፣ ሥራ ላይ ያሉ ሕጐችን፣ ያለኝን እውቀት እና ችሎታ መሠረት አድርጌ እንደማከናውን በፈጣሪ ስም እምላለሁ”

4. የቅበላ ኮሚቴ የቅበላ መሥፈርቶች መሟላታቸውን ሲያረጋግጥ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ለአመልካቹ ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡

5. የሚሰጠው ፍቃድ ውስን ወይም ጠቅላላ የሕግ አገልግሎትን የሚመለከት ሊሆን ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 39 - ልዩ የጥብቅና ፍቃድ

 

1. የሕብረተሰቡን ጠቅላላ መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ በነጻ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ወይም ተቋም ልዩ የጠብቅና ፍቃድ ይሰጠዋል፡፡

2. ለተቋም ልዩ የጥብቅና ፍቃድ ሲሰጥ ተቋሙ አገልግሎቱ የጥብቅና ፍቃድ ባለው ሰው ወይም የጥብቅና ፍቃድ ባለው ሰው ቁጥጥር ሥር እየተሰጠ መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት፡፡

3. ተቋሙ እና ሥራውን የሚከታተለው ጠበቃ የሚሰጡት የሕግ አገልግሎት ሕጋዊና የሥነ ምግባር ደንብን የተከተለ እና በሕግ መሠረት እየተከናነ መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡

4. ማንኛውም የጥብቅና ፍቃድ ያለው እና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተገለጸውን መስፈርት የሚያሟላ ማንኛውም ሰው ልዩ የጥብቅና ፍቃድ ሳያስፈልገው የጥብቅና ሥራ ለመሥራት ይችላል፡፡ ሆኖም ይህንን አገልግሎት ከመስጠቱ በፊት የፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ማሳወቅ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 40 - የተወሰነ የጥብቅና ፍቃድ

 

የሚከተሉት መሥርቶች ተሟልተው ሲገኙ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በክልል ፍርድ ቤት ለመቅረብ የሚያስችል ፈቃድ ላላቸው ሰዎች የተወሰነ የጥብቅና ፍቃድ ሊሰጥ ይችላል፡-

ሀ)    የክልሉ ከፍተኛ የጥበቅና ፍቃድ ካለው፣

ለ) ተገቢ ያልሆነ ባኅርይን በሚያሳይ ወንጀል ተጠርጥሮና ተከሶ ለማያውቅና በሚሠራበት ክልል የጥብቅና ፍቃዱ ያልተሠረዘ ወይም ያልተሻረ፣

ሐ) በዚህ አዋጅና በፌዴራል ጠበቆች የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት ሥራውን ለማከናወን እና ተገቢ ያልሆነ ሥነ ምግባር በሚያሳይበት ወቅት በሕግ መሠረት ተጠያቂ ለመሆን ለሚስማማ፡፡

 

አንቀጽ 41 - ሙያ መጠሪያ

 

1. አመልካቹ ከቅበላ በኋላ “ጠበቃ” በሚል የሙያ መጠሪያ የሕግ አገልግሎት ላይ መሠማራት ይችላል፡፡

2. “ጠበቃ” የሚለው የሙያ መጠሪያ በዚህ አዋጅ መሠረት የህግ አገልግሎት ለመስጠት ቅበላ ለተደረገላቸው ሰዎች የተተወ ነው፡፡

 

አንቀጽ 42 - የቅበላ እና ፍቃድ ሥረዛ

 

1. ቅበላ የተደረገለት ጠበቃ ፍቃድ ሊሰጣው የማይገባ መሆኑን የሚያሳዩ ፍሬ ነገሮች በሒደት ከተገኙ ለጠበቃው የተደረገው ቅበላ ይሠረዛል፡፡

2. የጥቅና ፍቃድ በሚከተሉት ምክንያቶች ይሠረዛል፡-

ሀ) ፍቃዱ የተገኘው በማታለል ከሆነ ወይም ፈቃዱ የተሰጠው ብቁ ላልሆነ ሰው ከሆነ ወይም ጠበቃው ፍቃድ ከተሰጠው በኋላ ብቁ አይደለም ከተባለ፣

ለ) ጠበቃው ከፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አባልነቱ ከተሰረዘ፡፡

3. ጠበቃው በዚህ አዋጅ እና በሥነ ምግባር ደንብ መሠረት የተጣሉበትን የተወሰኑ የሙያ ግዴታዎችን ሳያሟላ ከቀረ የሥነ ምግባር ጉባዔው ለጠበቃው የተደረገው ቅበላ ይሠረዛል፡፡

 

አንቀጽ 43 - ጊዜያዊ ዕግድ

 

1. በዚህ አንቀጽ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሲሟሉ ጠበቃ ወይም የሕግ አገልግሎት ድርጅት ሊታገድ ይችላል፡፡

2. ጠበቃ በሚታሠርበት ወቅት የሕግ አገልግሎት ከመሥራት ታግዶ ይቆያል፡፡

3. ግዴታውን በጽኑ ሁኔታ ባለመወጣቱ እና መልካም ስሙን በጽኑ በሚጎዳ ድርጊት ምክንያት ባለመወጣቱ የሥነ ምግባር ክስ ከቀረበበት ምክር ቤቱ ፍቃዱን ሊያግደው ይችላል፡፡

4. ጠበቃው በክፍያ ለሚሠራው የመንግስት ሥራ ከተመረጠ ወይም ከተሾመ የሕግ አገልግሎቱ በሥራ ላይ ለሚቆይባቸው ጊዜያት የሕግ አገልግሎት እንዳይሰጥ ይደረጋል፡፡

5. በቂ በሆኑ ምክንያቶች አንድ ጠበቃ ለረጅም ጊዜ የሕግ አገልግሎት መስጠት ካልቻለ የሕግ አግልግሎቱ ለአንድ ዓመት አገልግሎት እንዳይሰጥ ይደረጋል፡፡

6. ጊዜያዊ የዕግድ ትዕዛዝ ወይም ለጊዜው የሕግ አገልግሎት እንዳይሰጥ የመደረግ ውሳኔ የሚሠጠው በምክር ቤቱ ነው፡፡

7. ለጊዜው የሕግ አገልግሎት እንዳይሰጥ የተወሰነበት ጊዜ ሲያበቃ ወይም የጊዜያዊ ዕግዱ ጊዜ ሲያበቃ ጠበቃው የሕግ ሙያውን መቀጠል ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 44 - እድሳት

 

1. የጥብቅና ፍቃድ በየዓመቱ አንድ ጊዜ ፍቃዱ ጸንቶ ከሚቆይበት የመጨረሻ ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ መታደስ አለበት፡፡

2. በአንድ ወር ውስጥ ሳያስድሱ መቅረት በምክር ቤቱ የሚወሰን ቅጣት ያስቀጣል፡፡

3. ፍቃድ ለማደስ የሚከተሉት ማሥረጃዎች መቅረብ አለባቸው፡-

ሀ) የጠበቃው የታክስ ክሊራንስ፣

ለ) የሙያ አገልግሎት ኃላፊነት መድን ዕድሳት እና፣

ሐ) ጠበቃው ለተከታታይ የሕግ ትምህርት የተመደበውን አነስተኛውን የትምህርት ሠዓት ማጠናቀቁን የሚገለጽ ማሥረጃ፣

መ) ጠበቃው ፍቃዱን ከማሳደስ የሚከለክለው ጽኑ ችግር ከገጠመው ለምክር ቤቱ በማመልከት የእድሳት ጊዜውን ለተጨማሪ አንድ ወር ማራዘም ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 45 - የጠበቆች መዝገብ

 

1. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የጠበቆች መዝገብ ማዘጋጀት አለበት፡፡

2. የእያዳንዱ ጠበቃ ስም፣ አካላዊ እና የኤሌክትሮኒክ አድራሻ፣ የቅበላ ቀን፣ በቅበላ ቅደም ተከተል በመዝገቡ ላይ መመዝገብ አለበት፡፡

3. የተመዘገቡ የሕግ  አገልግሎት  ድርጅቶች  ስም፣  አድራሻ  እና  የአስተዳዳሪ ሸሪኮቹና የጠበቆቹ ስምና አድራሻም በመዝገቡ ላይ መካተት አለበት፡፡

4. መዝገቡ በበይነ መረብ ላይም መገኘት አለበት፡፡

 

አንቀጽ 46 - የሕግ አግልገሎት የመስጠት መብት መቋረጥ

 

1. የአንድ ጠበቃ  በሕግ  አገልግሎት  የመሠማራት  መብቱ   በሚከተሉት  ምክንያቶች ይቋረጣል፡-

ሀ)    ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊነቱን ካጣ፣

ለ) ችሎታ ያጣ መሆኑ ከተፈረደበት፣

ሐ) የሕግ  አገልግሎት  እንዳይሰጥ  የሚያደርገው  ቋሚ  የአካል  ጉዳት  ከገጠመው ወይም፣

መ) በተወሰደበት የሥነ ምግባር እርምጃ መነሻነት የሕግ አገልግሎት ለመስጠት ብቁ አይደለም ከተባለ፣

ሠ) በፍቃደኝነት ከሕግ አገልግሎት ራሱን ካገለለ፣

ረ) ከስድስት ወር በላይ ያለበቂ ምክንያት የሕግ አገልግሎት ሥራውን ካቋረጠ፣

ሰ) በቋሚነት ተቀጥሮ መሥራት ከጀመረ ሥራ

ሸ) ከስድስት ወር ለሚበልጥ ጊዜ ያልተገደበ የእሥራት ቅጣት ከተጣለበት፡፡

2. የአንድ ጠበቃ ፍቃድ ከተቋረጠ በኋላ ፍቃዱ ተሠርዞ ከጠበቆች መዝገብ ላይ ስሙ ይሠረዛል፡፡

 

ክፍል አራት

የጠበቆች የሙያ ግዴታ

ንዑስ ክፍል አንድ

ጠቅላላ ግዴታዎች

አንቀጽ 47 - ብቁ መሆንና ትጋት

 

ማንኛውም ጠበቃ የሕግ አገልግሎቱን ሙያዊ በሆነ መልኩ በተሟላ ሁኔታ እና በትጋት ማከናወን አለበት፡፡

 

አንቀጽ 48 - ነጻነት

 

1. ማንኛውም ጠበቃ የሕግ አገልግሎቱን ሲሰጥ ነጻ መሆን አለበት፡፡

2. የሕግ አገልግሎቱን በነጻነት የመስጠት ችሎታውን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶች ራሱን ማቀብ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 49 - የጥቅም ግጭትን ማስወገድ

 

ማንኛውም ጠበቃ የጥቅም ግጭት በሚፈጥር ወይም የመፍጠር ዕድል ባለበት ሑኔታ የሕግ አገልግሎት ከመስጠት መታቀብ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 50 - ሙያዊ ምሥጢር ጠባቂነት

 

1. ማንኛውም ጠበቃ ሙያዊ ምሥጢሮችን መጠበቅ አለበት፡፡

2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተገለጸው ሙያዊ ምሥጢር ግልጽ የሆኑ ፍሬነገሮችን፣ በይፋ የታወቁ ፍሬ ነገሮችን እና በተፈጥሯቸው በምሥጢርነት የማይጠበቁ መረጃዎችን ሳይጨምር ጠበቃው ከሙያ ተግባሩ ጋር ተያይዞ ያገኛቸውን ማናቸውምን መረጃዎች ያጠቃልላል፡፡

 

አንቀጽ 51 - ለጠበቃ የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎች

 

1. በጠበቃው እና በደንበኛው መካከል የተለየ ሥምምነት ከሌለ በቀር ወይም አገልግሎቱ የሚሰጠው በነጻ ካልሆነ በቀር ጠበቃ ለሚሰጠው አገልግሎት ክፍያ የማግኘት እና ከሥራው ጋር በተያያዘ ያወጣቸው ወጪዎች እንዲተኩለት መብት አለው፡፡

2. የአገልገሎት ክፍያን በተመለከተ በጠበቃ እና በደንበኛው መካከል የሚደረግ ስምምነት በጽሑፍ መሆን እና የክፍያው መጠን ወይም የአሰላልና የአከፋፈል ሁኔታ፣ የክፍያ አይነት እና የአገልግሎቱ አይነት መካተት አለበት፡፡

3. የተለየ ስምምነት ከሌለ በቀር በደንበኛውና በጠበቃው ስምምነት ላይ የተጠቀሰ የክፍያ መጠን የሙያ ክፍያ እና ለደንበኛው አገልግሎቱን ሲሰጥ የሚያወጣቸውን ወጪዎች ያጠቃልላል፡፡

4. የጽሑፍ ስምምነት ከሌለ ደንበኛው የሚከፍለው ክፍያ እና የሚተካው ወጪ የሚወሰነው በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በሚወሰኑ ፍሬነገሮች መሠረት ነው፡፡

5. ፍርድ ቤት በውሉ የተጠቀሰውን የክፍያ መጠን መቀነስ የሚችሉት ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው ከሆነ እና ደንበኛው በክፍያው መጠን የተስማማው በሕግ ጉዳዮቸ ላይ ግልጽ ሆኖ የሚታይ የልምድ ማነስ ያለበት በመሆኑ ወይም ልዩ የሆነ ፍላጎት ያለው በመሆኑ ከነገሩ ሁኔታ ሲረዱ ብቻ ነው፡፡

6. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 በተደነገጉት ነገሮች ላይ የፍትሃ ብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ አይሆኑም፡፡

7. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ጠበቆች በተሰወኑ የሕግ አገልግሎቶች ላይ የሚያስከፍሉትን የክፍያ መጠን ሊወስን ይችላል፡፡

8. የተወሰኑ የሕግ ጉደዮችን ልዩ ባኅርይ እና የቁጥጥር ዓላማዎችን ከግምት በማስገባት የፌዴራል የጠበቆች ማኅበር ጠበቃው የመጠባበቂያ ክፍያ እና ሌሎች የአከፋፈል ሁኔታዎችን የሚጠቀምበትን ሁኔታዎች ሊወሰን ይችላል፡፡

9. ጠበቃው የአገልግሎት ክፍያውን ከማን ጋር እና በምን አይነት ሁኔታ መጋራት እንደሚችል የፌዴራል የጠበቆች ማኅበር መወሰን አለበት፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሁለት

ተከታታይ የሕግ ትምህርት

 

አንቀጽ 52 - ዓላማ

 

የተከታታይ የሕግ ትምህርት ዓላማዎች፡-

1. ጠበቆች የሙያ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ይኖራቸው ዘንድ ትምህርታቸውን መቀጠላቸውን ማረጋገጥ፣ እና

2. የሕግ ጉዳዮችን፣ ግዴታዎቻቸውን፣ የሙያውን ደረጃ እና የሥራቸውን ስተዳደር በተመለከተ በሙያ ዘመናቸው በሙሉ ጠበቆች ወቅታዊ መረጃ እንዲኖራቸው ማረጋገጥ ነው፡፡

 

አንቀጽ 53 - የግዴታ ተከታታይ የሕግ ትምህርት

 

 1. ማንኛውም ጠበቃ በዓመት ቢያንስ ለ24 ሠዓታት የተከታታይ የሕግ ትምህርት መውሰድ አለበት፡፡

 2. ተከታታይ የሕግ ትምህርት በሚከተሉት የትምህርት ዓይነቶች ሳይወሰን፡-

        ሀ) የመሠረታዊ  እና  ሥነሥርዓታዊ  ሕግጋትን ተግባራዊ  እና  የንድፈ ሐሳብ ትምህርቶችን፣ እና

        ለ)   የጠበቆች  ሥነ   ምግባር  እና   የሙያ   ሥነ  ምግባር  ደንብ   ትምህርቶችን ያጠቃልላል፡፡

 

 

አንቀጽ 54 - ዕውቅና የተሰጣቸው የተከታታይ ሕግ ትምህርት ሠጪዎች

 

1. ማመልክቸውን ከማቅረቡ በፊት ባሉት ተከታታይ ሁለት ዓመታት ውስጥ በተከታታይ የሕግ ትምህርት ሥልጠና ሲሰጥ የነበረ ተቋም የተከታታይ የሕግ ትምህርት ሥልጠና ሰጪ ሆኖ ዕውቅና እንዲሰጠው ለቦርዱ ማመልከት ይችላል፡፡

2. ኮሚቴው የሚሰጠው ዕውቅና በተከታታይ ሕግ ትምህርት አሠልጣኙ አካል ወደፊት የሚሰጡ የሥልጠና ዓይነቶችን ቀድሞ የሚያጸድቅ መሆን አለበት፡፡ ሆኖም በቅድሚያ የጸደቁት የሥልጠና ዓይነቶች በኮሚቴው ወደፊት ሊሻሽሉ፣ ሊታገዱ፣ ወይም ሊሠረዙ ይችላሉ፡፡

3. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገው የሁለት ዓመት መሥፈርት ይህ አዋጅ የጸደቀበት አራተኛ ዓመት ክብረ በዓል ድረስ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡

4. የተከታታይ የሕግ ትምህርት ሰጪዎች ዕውቅና የሚያገኙበትን ሥነ ሥርዓት እና መሥፈርቶች እንዲሁም በዚሁ ንዑስ ክፍልን በመጣስ የሚጣለውን ቅጣት ኮሚቴው በሚያወጣው የተከታታይ የሕግ ትምህርት መመሪያ መወሰን አለበት፡፡

 

አንቀጽ 55 - ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነቶች

 

1. የተከታታይ የሕግ ትምህርት ሰቺዎች ሥልጣኞችን ተቀብለው ኮሚቴው ጋር የሚቀመጥ ቅጽ ማኖር ወይም በዚህ አዋጅ የተቀመጠውን የሥልጠና መሥፈርት ለሟሟላት ተካታታይ የሕግ ሥልጠና የወሰዱትን ተሳታፊዎች ዝርዝር የያዘ በቦርዱ በጸደቀ ኤሌክትሮኒክ ቅጽ ሥልጠናው በተሰጠ በሰላሳ ቀናት ውስጥ ለቦርዱ መላክ አለባቸው፡፡

2. ኮሚቴው ከተከታታይ የሕግ ትምህርት ሰጪዎቹ የሚቀበለውን ሪፖርት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የተረጋገጠ መግለጫ መጠየቅ አለበት፡፡

3. ኮሚቴው እያንዳንዱ ጠበቃ የጥብቅና ፍቃዱ ጸንቶ ከሚቆይበት ጊዜ ፺ ቀናት በፊት ስለሚጠበቅበት የተከታታይ የሕግ ትምህርት ለጠበቃው ማሳወቅ እና የተቀመጠው ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ የመጨረሻ ማስጠንቀቅያ መስጠት አለበት፡፡

4. የጠበቃ የጥብቅና ፍቃዱ ጸንቶ ክሚቆይበት ጊዜ የሚባለው የጠበቃው ፍቃድ በተሰጠበት ቀን እና ፍቃዱ በሚያበቃበት ቀን መካከል ያለው የአንድ ዓመት ጊዜ ነው፡፡

5. የቦርድ ሪፖርቱ የሚጠበቅበትን ተከታታይ የሕግ ትምህርት መውሰዱን የሚያሳይለት ጠበቃ የሚጠበቅበትን መሠፈርት እንዳሟላ ሊቆጥረው ይችላል፡፡

 

6. አንድ ጠበቃ በተከታታይ የሕግ ትምህርት ሥልጠና ምዝገባው ወይም በዓመታዊ የሪፖርት ቅጾቹ ላይ ካልተስማማ ያልተስማማበትን ምክንያት በመግልጽ በሰላሳ ቀናት ውስጥ በጽሑፍ ለኮሚቴው ማሳወቅ አለበት፡፡

7. ኮሚቴው አንድ ጠበቃ የተከተታይ የሕግ ትምህርት ወስዶ ያመጣውን  ነጥብ በተመለከተ የሚያቀርበው ቅሬታ የሚፈታበትን መንገድ እና ውጤቱ በድጋሚ የሚታይት መንገድ በተመለከተ ኮሜቴው የተከታታይ የሕግ ትምህርት መመሪያ ማውጣት አለበት፡፡

 

አንቀጽ 56 - የተከታታይ የሕግ ትምህርትን አለመከታተል

 

1. አንድ ጠበቃ በዚህ ንዑስ ክፍል የተከታታይ የሕግ ትምህርትን በተመለከተ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ሳያሟላ የቀረ እንደሆነ ወይም ቦርዱ የተከታታይ የህግ ትምህርትን በተመለከተ ጉድለት ያለበት መሆኑን ከወሰነ ኮሚቴው ጠበቃው ትምህርት አለመከታተሉን የሚመለከት እና በስልሳ ቀናት ውስጥ ትምህርቱን እንዲከታተል የሚገልጽ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት አለበት፡፡

2. ኮሚቴው አንድ ጠበቃ የዚህን ንዑስ ክፍል መሥፈርት ወይም የኮሚቴውን ደንብ ካላሟላ ለፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ሪፖርት ማድረግ እና ጠበቃው ከጥብቅና ስራቸው ታግዶ ከሚቆዩት መካከል እንዲሆን ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 57 - ከስልጠና ግዴታ ነጻ መሆን እና ማራዘም

 

1. የዚህ ንዑስ ክፍል ድንጋጌዎች በጥብቅ መፈጸም አለባቸው፡፡

2. ጠበቃው የተከታታይ የሕግ ትምህርት መሥፈርቱን ያላሟላው ሊቆጣጠረው በማይችል ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ከሆነ እና በማናቸውም ምክንያታዊ መንገድ በማንኛውም የሪፖርት ዓመት የተከታታይ የሕግ ትምህርት መሥፈርቱን ማሟላት ካልቻለ ኮሚቴው የተከታተይ የሕግ ትምህርት መሥፈርት በሙሉ ወይም በከፊል እንዲነሳ ሊወስን ይችላል፡፡

3. ከስልጠና ግዴታ ነጻ ለመሆን የሚቀርብ ማመልከቻ ጠበቃው አነስተኛውን መስፈርት ማሟላት እንዳይችል ያደረገውን ምክንያት፣ መሥፈርቱን ለማሟላት ያደረገውን ጥረት እና የስልጠና ግዴታው በተነሳበት ወቅት ቀሪ ጊዜ ውስጥ ሥልጠናውን ለመውሰድ ያለውን ዕቅድ የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡

4. ኮሚቴው ከስልጠና ግዴታ ነጻ የሚኮንበት ጊዜ ኮሚቴው ሊወስን ይችላል፡፡ ከስልጠና ግዴታ ነጻ የሚኮንበት ጊዜ ሲጠናቀቅ ኮሚቴው አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምንባቸውን ተጨማሪ የትምህርት መሥፈርቶችን ሊወስን ይችላል፡፡

5. አንድ ጠበቃ የተከታታይ የሕግ ትምህርት መስፈርቱን ለሟሟላት ትምህርቱን ወስዶ የሚያጠናቅቅበተን ጊዜ እንደአስፈላጊነቱ እንዲራዘም ሊወስን ይችላል፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሦስት

ነጻ የሕግ አገልግሎት

 

አንቀጽ 58 - ለሕዝብ ነጻ የሕግ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ

 

1. ማንኛውም ጠበቃ ለአገልግሎቱ መክፈል ላልቻሉ ሰዎች ለሕዝብ ነጻ የሕግ አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡

2. ማንኛውም ጠበቃ ቢያንስ በየዓመቱ ለሃምሳ ሰዓት ለሕዝብ ነጻ የሕግ አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡

3. ለሕዝብ ነጻ የሕግ አገልግሎት መስጠት የሕግ ምክር፣ ወክሎ መከራከር እና ፍትሕ የማግኘት መብትን የሚያረጋግጥ እና የሕግ የበላይነትን እና የጠበቃውን ሙያ የሚያሻሽሉ ማናቸውንም ድርጊቶች ያጠቃልላል፡፡

4. ማንኛውም ጠበቃ ለሕዝብ ነጻ የሕግ አገልግሎት የሰጠበትን ቀን፣ አይነት እና አገልግሎቱን ለምን ያህል ሰዓት እንደሰጠ ያካተተ ለሕዝብ ነጻ የሕግ አገልግሎት የመስጠት ግዴታውን መወጣቱን የሚገልጽ ማህደር መያዝ አለበት፡፡

 

ክፍል አምስት

የሕግ አገልግሎት ድርጅቶች የሕግ አገልግሎት

 

አንቀጽ 59 - የሕግ አገልግሎት ድርጅት

 

1. ፍቃድ ያለው ጠበቃ ከአንድ ወይም ከዛ በላይ ከሆኑ ፍቃድ ካላቸው ሌሎች ጠበቆች ጋር በመተባር የሕግ አገልግሎት ድርጅት የማቋቋም መብት አለው፡፡

2. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ለማቋቋም ቢያንስ ሁለት ፍቃድ ያላቸው ጠበቆች መኖር አለባቸው፡፡

 

አንቀጽ 60 - ቅርጽ እና ኃላፊነት

 

1. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር ቅርጽ ይኖረዋል፡፡

2. የሕግ አገልግሎት ድርጅት የራሱ የሕግ ሠውነት አለው፡፡

3. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 እንደተጠበቀ ሆኖ የሕግ አገልግሎት ድርጅት፡-

ሀ) ውል መዋዋል እና

ለ)    የንብረት ባለቤት መሆን ይችላል፡፡

4. የሕግ አገልግሎት  ድርጅት   ሸሪኮች   በግላቸው  በሚይዙት   የደንበኞቻቸው  ጉዳይ የሚመጣን ኃላፊነት ሳይጨምር ለሦስተኛ ወገኖች የተወሰነ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

5. የሕግ አገልግሎት ድርጅት አባላት በተመለከተ ለውጥ ቢመጣም የሕግ አገልግሎት ድርጅት ህልውና ይቀጥላል፡፡

6. በሕግ አግልግሎት ድርጅት የሕግ አገልግሎት መስጠቱ በኢትዮጵያ የንገድ እና የኢንቨስትመንት ሕግጋት መሠረት የሕግ ሙያን የንግድ ወይም የኢንቨስትመንት ሥራ አያሰኘውም፡፡

 

አንቀጽ 61 - የአገልግሎት ወሰን

 

1. የሕግ አገልግሎት ድርጅት አንድ ጠበቃ በዚህ አዋጅ እና አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕግጋት መሠረት እንደሚያከናውናቸው የሕግ አገልግሎት ሥራዎች ተመሳሳይ በሆነ መንገድ በሕግ አገልግሎት ሥራ ላይ መሳተፍ ይችላል፡፡

2. የሕግ አገልግሎት ድርጅት በዋነኝነት በሕግ አገልግሎት ሥራ ላይ መሳተፍ አለበት፡፡

3. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ሥር የተደነገገው እደተጠበቀ ሆኖ የሕግ አገልግሎት ድርጅት ከሕግ አገልግሎት ጋር ተያያዥነት እና ተደጋጋፊነት ያላቸውን ሌሎች አገልግሎቶች መስጠት ይችላል፡፡ የዚህ ንዑስ አንቀጽ ዝርዝር አፈጻጸም ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በሚያወጣው የሥነ ምግባር ደንብ ይወሰናል፡፡

 

አንቀጽ 62 - ስም እና ሰነዶች

 

1. የሕግ አገልግሎት ድርጅት አባላት ማንኛውንም ቃል ወይም ቃላት የሕግ አገልግሎት ድርጅታቸው መጠሪያ እንዲሆን መምረጥ እና መወሰን ይችላሉ፡፡

2. በሚከተሉት ምክንያቶች በሸሪኮች ለሕግ አገልግሎት ድርጅቱ መጠሪያነት የተመረጠው ስም በፌዴራል የጠበቆች ማኅበር ሊከለከል ይችላል፡-

ሀ)    ከሌላ የጸነ የሕግ አገልግሎት ድርጅት ስም ጋር በሚያደናግር መልኩ ተመሳሳይ ከሆነ፣ ወይም

ለ)    ለሕግ ወይም ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ ከሆነ፡፡

3. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ስም የሕግ አገልግሎት ድርጅት መሆኑን የሚያመለክትና ከስሙ በስተመጨረሻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር ወይም (ኃ.የተ.የሽ.ማ) የሚል ሐረግ ያለው መሆን አለበት፡፡

4. በሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ስም የሚወጡ ሰነዶች በሙሉ በግልጽ ስሙን እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር የሚለውን ሐረግ መያዝ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 63 - የመቋቋሚያ መሥፈርቶችና ሥነ ሥርዓቶች

 

1. የሕግ አገልግሎት ድርጅት በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በመመዝገብ ይቋቋማል፡፡

2. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ለማቋቋም የሚከተሉት ሰነዶች ለፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ከማመልከቻ ጋር ተያይዘው መቅረብ አለባቸው፡-

ሀ)    በሸሪኮቹ የተሞላ ማመልከቻ፣

ለ)    በሸሪኮቹ የተፈረመ የመመሥረቻ ጽሑፈ፣ ሐ)    የሸሪኮቹ የጥብቅና ፍቃድ ቅጂ፣ እና

መ)   ለሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ስምት የተመረጠው ስም፡፡

3. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የቀረቡለት ሰነዶች ከዚህ አዋጅና አግባብነት ካላቸው ሌሎች ሕግጋት ጋር የተጣጣሙ ከሆኑ ማመልከቻውን በተቀበለ በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ማመልከቻው ተቀብሎ የሕግ አገልግለት ድርጅቱን መመዝብ አለበት፡፡

 

4. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የቀረቡለት ሰነዶች ከዚህ አዋጅና አግባብነት ካላቸው ሌሎች ሕግጋት ጋር የሚጣረሱ ናቸው ብሎ ከደመደመ ማመልከቻውን በተቀበለ በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ማመልከቻው ውድቅ ማድረግና ማመልከቻው ውድቅ እንዲሆን ምክንያት የሆነውን ጥሰት በመግለጽ ለአመልካቹ ማሳወቅ አለበት፡፡

5. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 4 መሠረት ያቀረበው ማመልከቻ ውድቅ የተደረገበት አመልካች ማመልከቻው ውድቅ የተደረገበትን ምክንያት በማረም ወይም የተባለው ምክነያ አለመኖሩን በማብራራት ወይም ውድቅ ቀድ ያቀረበውን ማመልከቻ ውድቅ ለማስድረግ የሚበቃ ምክንያት አይደለም በማለት ማመልቻውን ለፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በድጋሚ የማቅረብ መብ አለው፡፡

6. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት በድጋሚ የቀረበ ማመልከቻ በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ውድቅ ከተደረገ ውሳኔው በተሰጠ በ3 ቃናት ውስጥ ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይለት ጉዳዩን ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወይም ሥልጣን ላላው የክልል ፍርድ ቤት የማቅረብ መብት አለው፡፡

 

አንቀጽ 64 - የመመሥረቻ ጽሑፍ

 

1. የሕግ አገልግለት ድርጅት የመመሥረቻ ጽሑፍ የሚከተሉትን መረጃዎች መያዝ አለበት፡-

ሀ)    የሁሉንም ሸሪኮች ስም፣ አድራሻ እና ዜግነት፣ ለ) የሕግ አገልግሎት ድርጅቱን ስም፣

ሐ)    የሕግ አገልግሎት ድርጅቱን ዋና መሥሪያ ቤት እና ቅርንጫፍ ካለ ቅርንጫፉን፣ መ)  የሕግ አገልግሎት ድርጅቱን ዓላማ፣

ሠ)    የሸሪኮችን መዋጮ ዓይነት፣ መጠን እና ዋጋቸው የተሰላበትን ዘዴ፣

ረ)    ከሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ትርፍና ኪሣራ ላይ የእያዳንዱን ሸሪክ ድርሻ፣

ሰ)    የሕግ አገልግለት ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የሚሾምበትን መንገድ እና ሥልጣንና ኃላፊነቶቹን፣

ሸ)    የሽርክና ማኅበሩን ዘመን፣

ቀ)    በሕግ  ወይ  በስምምነት  መሠረት  በመመሥቻ  ጽሑፍ   ውስጥ   እንዲካተቱ የተወሰኑ ሌሎች ነገሮችን፡፡

2. የዚህን አዋጅና አግባብን ያቸው ሌሎች ሕግጋትን አስገዳጅ ድንጋጌዎች የሚጥስ የመመሥረቻ ጽሑፍ ድንጋጌ ውጤት አይኖረውም፡፡

 

አንቀጽ 65 - የመዋጮ ዓይትና መጠን

 

1. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ሸሪኮች ክህሎት ዋናኛው መዋጮ መሆን አለበት፡፡

2. ሸሪኮች ሌሎች መዋጮችዎን በገንዘብ ወይም ማኅበሩን ለማቋቋም ዓላማ በሚዋጣ ማናቸውም የንብረት ዓይነት ማዋጣት ይችላሉ፡፡

3. የሕግ አገልግሎት  ድርጅት  ሸሪኮች  የመዋጮ   መጠን   የድርጅቱን   ዓላማ   ለማሳካት የሚበቃ መሆን አለበት፡፡

4. ገንዘብ ባልሆነ ማቸውም መንገድ በሕግ አገልግሎት ድርጅት ሸሪክ የሚደረግ መዋጮ ዋጋ በሁሉም ሸሪኮች ስምምነት እና አግባብነት ባላቸው ሕግጋትና ደንቦች ይወሰናል፡፡

 

አንቀጽ 66 - የሸሪኮች መብትና ግዴታ

 

1. የሕግ አገልግለት ድርጅት ሸሪክ የሚከተሉት መብቶች አሉት፡-

ሀ)    በሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ስብሰባዎች የመካፈል እና ድምጽ የመስጠት፣

ለ) በድርሻው መጠን በዚህ አዋጅ ወይም በመመሥረቻ ጽሑፉ በተወሰነው መሠረት ከድርጅቱ ትርፍ ወይም የሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ሲከስም ከተጣራው የማኅበሩ ሐብት የሚተርፈውን ሐብት የመውሰድ፣

ሐ) የሕግ አገልግሎት ድርጅቱን ሥራዎች እና ሌሎች ሰነዶች መፈተሸ እና መመርመር፣ እና

መ) በዚህ አዋጅ፣ አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕግጋት፣ በመመሥረቻ ጽሑፉ የተመለከቱ ወይም ከሽርክና ማኅበሩ ተፈጥሮ የሚመነጩ ሌሎች መብቶችና ጥቅሞች የመጠቀም፡፡

2. የሕግ አገልግለት ድርጅት ሸሪክ የሚከተሉት ግዴታዎች አሉት፡-

ሀ) ከርሱ የሚጠበቀውን መዋጮ በወቅቱ መክፈል፣

ለ) በማናቸውም ጊዜ የሕግ አገልግሎት ድርጅቱን ዓላማ ለማሳካት  በትጋት የመሥራት፣

ሐ) ለራሱ ጥቅም የሚያስገኝ ይሁንም አይሁንም የሕግ አገልግሎት ድርጅቱን ጥቅም ከሚጻረሩ ድርጊቶች ወይም አለማድረጎች መታቀብ፣ እና

መ) በዚህ አዋጅ፣ አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕግጋት፣ በመመሥረቻ ጽሑፉ የተመለከቱ ወይም ከሽርክና ማኅበሩ ተፈጥሮ የሚመነጩ ሌሎች ግዴታወችን የመወጣት፡፡

 

አንቀጽ 67 - ትርፍ እና ኪሠራ ክፍፍል

 

በሕግ አገልግሎት ድርጅቱ የመመሥረቻ ጽሑፉ በተለየ ሁኔተ ካልተገለጽ በስተቀር የማኅበሩ ሸሪኮች የድርጅቱን ትርፍ እና ኪሳራ ወይም የሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ሲከስም ከተጣራው የማኅበሩ ሐብት የሚተርፈውን ሐብት እኩል የመካፈል መብት አላቸው፡፡

 

አንቀጽ 68 - የሸሪኮች ለውጥ

 

1. አግባብነት ባለው ሌላ ሕግ የተጣለው ክልከላ እንደተጠበቀ ሆኖ የሕግ አገልግሎት ድርጅቱን ለሚለቅ ሸሪክ የድርሻው ዋጋ መከፈል አለበት፡፡

2. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ሸሪክ በሚሞት ወይም ችሎታ በሚያጣ ጊዜ ከድርሻው የሚመነጩ ጥቅሞቹ ለወራሾቹ ወይም ለሞግዚቱ የተላለፋሉ፡፡ በሌሎች ሸሪኮች በግልጽ ካተፈቀደላቸው በቀር የሸሪኩ ወራሾች ወይም ሞግዚቱ የሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ሸሪክ ሆነው ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡

 

አንቀጽ 69 - ባለቤትነት እና መዋቅር

 

1. የጥብቅና ፍቃድ ያላቸው ጠበቆች የሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ሦስት አራተኛ ካፒታል ባለቤት መሆን አለባቸው፡፡ ፡

2. ጠበቃ ያልሆኑ ሰዎች የሕግ አገልግሎት ድርጅቱ አንድ አራተኛ ካፒታል ባለቤት መሆን ይችላሉ፡፡ የዚህ ንዑስ አንቀጽ አፈጻጸም የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በሚያወጣው የሥነ ምግባር ደንብ ይወሰናል፡፡

3. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ዝርዝር መዋቅር እና በድርጅቱ የሚሠሩት ጠበቆች መብት እና ግዴታ በማኀበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ እና በድርጅቱ ውስጠ ደንብ ይወሰናል፡፡

 

አንቀጽ 70 - በሕግ አገልግሎት ድርጅት የሚሠሩ ጠበቆች ክልከላ

 

በሕግ አገልግሎት ድርጅት እንደ ሸሪክ የሚሠራ ማንኛውም ጠበቃ ወይም ሠራተኛ የሽርክና ወይም የሥራ ቅጥር ዘመኑ ጸንቶ ባለበት ወቅት የሚከተሉት ድርጊቶች ውስጥ ከመሳተፍ ተከልክሏል፡-

ሀ) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሌላ የሕግ አገልግሎት ድርጀት ሸሪክ ወይም ሠራተኛ መሆን፣

ለ) በሚሠራበት የሕግ አገልግሎት ድርጅት ውስጥ የተጣለበትን ግዴታ ለመወጣት አስፈላጊ መሆኑ በድርጅቱ ቀደም ብሎ ካልጸደቀ በስተቀር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሌላ የሕግ አገልግሎት ድርጀትን መርዳት ወይም መተባበር፣

ሐ) በግሉ ጠበቃ ሆኖ የሕግ አገልግሎት መስጠት፡፡

 

አንቀጽ 71 - አስተዳደር

 

1. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ሸሪኮች በመመሥረቻ ጽሑፍ ወይም ከዛን በኋላ በተሾሙ አንድ ወይም ከዛ በላይ ቁጥር ባላቸው ሥራ አስኪያጆች ይተዳደራል፡፡

2. ሥራ አስኪያጁ የሕግ ባለሙያ መሆን አለበት፡፡

3. የሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በሱ ስህተት ምክንያት በሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ለሦስተኛ ወገኖቹ ኃላፊነት አለበት፡፡

4. የሕግ አገለልግሎት ድርጅቱ ጣምራ ሥራ አስኪያጆች በዚህ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር 3

ለተገለጸው ግዴታ በአንድነት እና በተናጥል ኃላፊነት አለባቸው፡፡

 

አንቀጽ 72 - የሥራ አስኪያጅ ግዴታዎች

 

የሕግ አገልግሎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የድርጅቱ ሠራተኞች ጠቅላላ እና ድርጅቱ ራሱ ግዴታቸውን በድርጅቱ መመሥረቻ ጽሑፍ፣ በድርጅቱ ውስጠ ደንቦች፣ በዚህ አዋጅ እና አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕጎች መሠረት መወጣታቸውን ማረጋገጥ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 73 - የሽርክና ማኅበሩ ውሳኔዎች

 

በሕግ አገልግሎት ድርጅቱ መመሥረቻ ጽሑፍ ወይም ተፈጻሚነት ባለው ሌላ ሕግ በማናቸውም ሌላ ሕግ በተለየ ሁኔታ ካልተሰወነ በስተቀር የሕግ አገልግሎት ድርጅት ቢያንስ ሃምሳ ሲደመር አንድ አባላቱ በተገኙበት ስብሰባ ላይ ውሳኔዎች የሚተላለፉት ውሳኔው ስብሰባ ላይ ከተሳተፉት አባላት የሦስት አራተኛው ድምጽ ሲያገኝ ነው፡፡

 

አንቀጽ 74 - ግብር

 

1. የሕግ አገልግሎት  ድርጅት  እንደ  ኩባንያ  ተቆጥሮ   የኩባንያ   ግብር   እንዲከፍል አይገደድም፡፡

2. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ግብሩን ለሺሪኮቹ ያስተላልፋል፡፡ እያንዳንዱ ሸሪክ ከድርጅቱ ያገኘውን ትርፍም ሆነ ኪሳራ ማሳወቅ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 75 - ዘላቄታ እና መፍረስ

 

1. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ህልውና በሸሪኮቹ ሞት፣ መልቀቅ፣ ችሎታ ማጣት፣ መክሰር ወይም ሸሪኮቹን በሚያውክ ማናቸውም ለውጥ አይነካም፡፡

2. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ከሚከተሉት ምክንያቶች በአንዱ ለፈርስ ይችላል፡-

ሀ) የሽርክና ማኅበሩን ለማፍረስ ሸሪኮች ሲስማሙ፣

ለ) የሕግ አገልግሎት ድርጅት መክሰሩ ሲታወጅ፣

ሐ) የሁሉም ሸሪኮቹ ፍቃድ ሲሰረዝ፣

መ) የጥብቅና ፍቃድ ያላቸው ሺረኮቹ ቁጥር አንድ ሲሆንና ፍቃድ ያላቸው ጠበቆች ቁጥር በጎደለ በሦስት ወር ውስጥ ካልተሟላ፡፡

3. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ሲፈርስ በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ከነበረው መዝገብ ይሰረዛል፡፡

 

አንቀጽ 76 - የሕግ አገልግሎት ድርጅት እና ሸሪኮች ለደንበኞቻቸው ያለባቸው ኃላፊነት

 

1. የሕግ አገልግሎት ድርጅት ሸሪኮች በግላቸው በያዙት ጉዳይ ላይ ለደንበኞቻቸው ካላቸው ኃላፊነት ወይም ሥራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው፣ በማታለል ወይም አውቀው ባደረሱት ጉዳት ካልሆነ በስተቀር ሦስተኛ ወገኖችን በተመለከተ የተወሰነ ኃለፊነት አለባቸው፡፡

2. ለዚህ ሥራን በአግባቡ አለመወጣት ከሸሪኩ በተጨማሪ ሸሪክ የሆነበት  የሕግ አገልግሎት ድርጅትም ኃላፊነት አለበት፡፡

3. ኃላፊነት ያስከተለውን አገልግሊ በጋራ ካልሰጡ በስተቀር አንድ ሸሪክ ሥራውን በአግባቡ ባለመወጣቱ ለሚመጣበት ኃላፊነት ሌሎች ሸሪኮች ኃላፊ አይሆኑም፡፡

4. ጠበቃ ባለሆነ የሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ሠራተኛ በደንበኞች ላይ ለደረሰ ጉዳት የሕግ አገልግሎት ድርጅቱ በጋራ ኃላፊነት አለበት፡፡

 

አንቀጽ 77 - ገንዘብ ጠያቂዎች

 

1. ከሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ላይ ገንዘብ ጠያቂዎች ከድርጅቱ ማናቸውም ሐብት ላይ ገንዘብ መጠየቅ ይችላሉ፡፡

2. ከሕግ አገልግሎት ድርጅቱ ላይ ገንዘብ ጠያቂዎች ከሸሪኮች የግል ንብረት ላይ ገንዘብ መጠየቅ አይችሉም፡፡

 

አንቀጽ 78 - የሕግ አገልግሎት ድርጅት ግዴታዎች

 

በሌሎች ሕጎች የተቀመጡ ግዴታዎች እንደተጠበቁ ሆኖ የሕግ አገልግሎት ድርጅት የሚከተሉት ግዴታዎች አሉበት፡-

ሀ) ከሸሪኮቹ  የሙያ  ኃላፊነት  መድን  በተጨማሪ  የጸና  የሙያ  ኃላፊነት  መድን መግዛትና ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት ይዞ መገኘት፣

ለ) ተገቢውን የሒሳብ ሰነድ መያዝ፣

ሐ) የደንበኞቹን ምሥጢር በጥብቅ መጠበቅ፣

መ) በውጭ ኦዲተር በየዓመቱ ኦዲት መደረግ፣

ሠ) በማቸውም ጊዜ ይህንን አዋጅ፣ አግባብነት ያላቸውን ሌሎች ሕግጋትና የሙያ ሥነ ምግባር ደንቦችን ማክበር፣ እና

ረ)  የመመሥረቻ  ጽሑፉ  ላይ  ማሻሻያዎች  ሲያደርግ  ማሻሻያው  በተፈረመ በ15 ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ግልባጩን ማቅረብ፡፡

 

አንቀጽ 79 - የሌሎች ሕግጋት ተፈጻሚነት

 

ኃላፊነቱ ለተወሰነ ማኅበር አግባብነት ያላቸው ሌሎች ሕግጋት ከዚህ አዋጅ ጋር አስካልተቃረኑ ድረስ በዚህ አዋጅ መሠረት ለተቋቋሙ የሕግ አገልግሎት ድርጅቶች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡

 

ክፍል ስድስት

መድን እና የደንበኞች ንብረት

ንዑስ ክፍል አንድ

የሙያ ኃላፊነት መድን

 

አንቀጽ 80 - የሙያ ኃላፊነት መድን የመያዝ ግዴታ

 

1. ማንኛውም ጠበቃ ሥራውን በአግባቡ ሳይወጣ በመቅረቱ ምክንያት በደንበኛው ላይ ሊደርስ ለሚችል ጉዳት ካሳ የሚሆን የሙያ ኃላፊነት መድን መያዝ አለበት፡፡

2. ማንኛውም የሕግ አገልግሎት ድርጅት ሸሪኩ ሥራውን በአግባቡ ሳይወጣ በመቅረቱ ምክንያት በደንበኛው ላይ ሊደርስ ለሚችል ጉዳት ካሳ የሚሆን የሙያ ኃላፊነት መድን መያዝ አለበት፡፡

3. የሙያ ኃላፊነት መድኑ መጠን በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የሚወሰን ቢሆንም በማናቸውም መንገድ ከ510 ብር ሊበልጥ አይችልም፡፡

4. ጠበቆች እና የሕግ አገልግሎት ድርጅቶች ሊይዙት የሚገባውን የሙያ ኃላፊነት መድን መጠን የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በየጊዜው ይከልሳል፡፡

 

አንቀጽ 81 - የመድን ሰጪው ግዴታዎች

 

1. ለጠበቃ ወይም ለሕግ አገልግሎት ድርጅት የሙያ ኃለፊነት መድን የሰጠ መድን ሰጪ የመድን ውሉ የሚቋረጥበትን ቀን እና መድኑ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊፈጥር የሚችል ለውጥ ሲደረግ በፍጥነት ለፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ማሳወቅ አለበት፡፡

2. መድን ሰጪው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተቀመጠውን ግዴታውን ባለመወጣቱ በሰው ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ኃላፊነት አለበት፡፡

 

አንቀጽ 82 - ከኃላፊነት ነጻ መሆን

 

በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ደንብ ከፍተኛው አነስተኛ የመድን ሽፋን ከመድን ሽፋን ነጻ ሰለመደረግ፣ እና ደንበኞች ከጠበቃ ካሳ ለመጠየቅ ያላቸውን መብት ስለመገደብ ሊወሰን ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 83 - ልዩ ሁኔታ

 

በሕግ  አገልግሎት  ድርጅት  ተቀጥሮ  የሚሠራ  ጠበቃ  በድርጅቱ  በኩል  ሊገኝ  ከቻለ የራሱን ቢሮ ለመክፈት አይገደደም፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሁለት

የደንበኛን ንብረት መያዝ

 

አንቀጽ 84 - ጠቅላላ ድንጋጌ

 

1. ጠበቃ ከሙያ ሥራው ጋር በተገናኘ በይዞታው ወይም በአስተዳደሩ ሥር የሚገኝን የደንበኛውን ወይም የሦስተኛ ወገንን ንብረት ከራሱ ንብረት ለይቶ መያዝ አለበት፡፡

2. የእነዚህን ንብረቶች መረጃ ዝርዝር መያዝ እና  ንብረቱን ቢበዛ  ለ1 ዓመት መያዝ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 85 - ከገንዘብ ውጪ ያለ ንብረት

 

በጠበቃው ይዞታ ወይም አስተዳደር ሥር የሚገኝ የደንበኛው ወይም የሦስተኛ ወገን ከገንዘብ ውጪ የሆነ ንብረት እንደንብረት ተቆጥሮ በአግባቡ መጠበቅ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 86 - የደንበኛ የአደራ ሒሳብ

 

1. በጠበቃው ይዞታ ወይም አስተዳደር ሥር የሚገኝ የደንበኛው ወይም የሦስተኛ ወገን ገንዘብ በተለየ ሒሳብ ውስጥ መቀመጥ አለበት፡፡

2. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ጠበቆች የደንበኞች ትረስት ሒሳብ እንዲኖራቸው መጠየቅ ይችላል፡፡

3. ክፍያዎቹ መፈጸም ሲገባቸው ወይም ወጪ ሲኖር ጠበቃው ወጪ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን በቅድሚያ የተከፈሉ ሕጋዊ ክፍያዎችን እና ወጪዎችን በደንበኞች ትረስት ሒሳብ ማጠራቀም ይችላል፡፡

4. ጠበቃው የደንበኛ ወይም ሦስተኛ ወገን ጥቅም ያለበት ገንዘብ ወይም ሌላ ንብረት ሲቀበል ደንበኛውን ወይም ሦስተኛ ወገኑን ወዲያው ማሳወቅ አለበት፡፡

5. በዚህ አዋጅ ከተመለከተው በስተቀር ወይም በሕግ ወይም ከደንበኛው ጋር በተደረገ ስምምነት ካልተፈቀደ በስተቀር ደንበኛው ወይም ሦስተኛ ወገን የመቀበል መብት ያላቸውን ገንዘብ ወይም ሌላ ንብረት ደንበኛው ወይም ሦስተኛ ወገን ሲጠይቀው ገንዘቡን ወይም ንብረቱን ወዲያው ማስረከብ እና ንብረቱን በተመለከተ ወድያውኑ መግልጫ የመስጠት ሃላፊንት አለበት፡፡

 

ክፍል ሰባት

የሥነ ምግባር ደንብ

ንዑስ ክፍል አንድ የሥነ ምግባር ደንብ

 

አንቀጽ 87 - ዓላማ

 

1. በዚህ አዋጅ የተመለከቱ የሙያዊ መብትና ግዴታዎች የተመለከቱ አጠቃላይ ደንቦች ዝርዝር በሥነ ምግባር ደንቡ የሚወሰን ይሆናል፡፡  

2. የዚህ የጠበቆች ሥነ ምግባር ደንብ ዓላማ የሕግ የበላይነትን እና የሰብዓዊ መብትን መነሻዎችን ለማሳደግ፣ የፍትህ አስተዳደር ሥርዓቱ የሚከናንበትን መንገድ  ለማሻሻል፣ የፍትህን ተደራሽት ለማረጋገጥ እና የጠበቆችን እና የሕግ አገልግሎት ድርጅቶችን አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ የሕበረተሰቡ አባላት ለመጠበቅ በማሰብ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አባላትን የሙያ ሥነ ምግባር መቆጣጠር ነው፡፡

 

አንቀጽ 88 - የጠበቆች ሥነ ምግባር ደንብ ይዘት

 

1. የጠበቆች እና የሕግ አገልግሎት ድርጅቶች ሥነ ምግባር ደንብ ይዘት የሚከተሉትን ጉዳዮች ማካተት አለበት፡-

ሀ) ወደ ጥብቅና ሙያ ቅበላ ለማመልከት ስለሚሹ ተለማማጅ ጠበቆች የተግባር ሥልጠና፣ የንድፈ ሐሳብ ትምህርት እና ፈተና፣

ለ) ስለ ጠበቃ እና ደንበኛ ግንኙነትን፣

ሐ) ስለ ክፍያዎች፣

መ) ስለ መዝገብ አያያዝ፣

ሠ) ስለጠበቃ እና የቀድሞ ደንበኞቹ ግንኙነት፣

ረ) ስለ ጠበቃ እና ደንበኞቹ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች ግንኙነት፣ ሰ)  ስለ ጠበቃ እና የተከራካሪዉና የተከራካሪው ጠበቃ ግንኙነት፣ ሸ)    ልዩ ድጋፍ ስለሚሻቸው ደንበኞች፣

ቀ) በጠበቃ ካልተወከሉ ሰዎች ጋር ስለመከራከር፣

በ) የጠበቃ-ደንበኛ ግንኙነትን ስለመተው ወይም ስለማቋረጥ፣ ተ)   የሕግ አገልግሎትን ስለመሸጥ፣

ቸ) የሕግ አገልግሎት ድርጅት ባለቤት ስለመሆን እና ስለአደረጃጀቱ፣ ነ)    የጠበቃ አገልግሎቶች ግንኙነት በተመለከተ፣

ኘ) የሥነ ምግባር ጥሰትን ማሳወቅን በተመለከተ፡፡

2. የሥነ ምግባር ደንቡ ዝርዝር በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ወጥቶ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጸድቆ በሚወጣው የሥነ ምግባር ደንብ ይወሰነል፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሁለት

የሥነ ምግባር ደንብ ቦርድ

 

አንቀጽ 89 - ዓላማ

 

የፌዴራል  ጠበቆች  ማኅበር  በግል  የጥብቅና  አገልግሎት   ለሚሣተፉ  ጠበቆች  የሥነ ምግባር ደንብ ለማውጣትና ለማሻሻል ጊዜያዊ የሥነ ምግባር ደንብ ቦርድ ይኖረዋል፡፡

 

አንቀጽ 90 - የአባሎች ጥንቅር፣ ምርጫ እና የአገልግሎት ዘመን

 

1. የሥነ ምግባር ደንብ ቦርድ 11 አባላት አሉት፡፡ ከጠቅላላ አባላቱ 6ቱ ስብዕናቸውን፣ ብቃታቸውን፣ የሥራ ልምዳቸውን የጾታ ስብጥራቸውን መሠረት በማድረግ ከፌዴራል ጠበቆች መካከል ድምጽ በምሥጢር በሚሰጥበት ምርጫ ይመረጣሉ፡፡

2. የሥነ ምግር ደንብ ቦርድ አባላት የሥራ ዘመን ሦስት ዓመት ነው፡፡ ለሌላ ተመሳሳይ የሥራ ዘመን በድጋሚ መመረጥ ይችላሉ፡፡ የሥነ ምግር ደንብ ቦርድ አራት አባላት በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሾም አለባቸው፡፡

3. የቀድሞ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ሊቀመንበር የቦርዱ ሰብሳቢ መሆን አለበት፡፡

 

አንቀጽ 91 - ብቁነት

 

1. ማንኛውም የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አባል የሥነ ምግባር ደንብ  ቦርድ  ሆኖ ለመመረጥ ብቁ ነው፡፡

2. በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚሾሙ የሥነ ምግባር ደንብ ቦርድ አባላት ቢያንስ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

 

ክፍል ስምንት

የሥነ ምግባር ደንብ ጥሰት

ንዑስ ክፍል አንድ

የደንብ ጥሰቶችና እና ቅጣቶች

 

አንቀጽ 92 - የሥነ ምግባር እርምጃ የሚወሰድባቸው ምክንያቶች

 

የሚከተሉት ምክንያቶች በጠበቃ ላይ የሥነ ምግባር እርምጃ ለመውሰድ በቂ ናቸው፡-  

ሀ) ይህንን አዋጅ ወይም የሥነ ምግባር ደንብን የሚመለከት ማንኛውንም ደንብ መጣስ ወይም ለመጣስ መሞከር፣

ለ) ጠበቃው ቅበላ ባገኘበት ሌላ የሥልጣን ክልል ውስጥ ያለን የጥብቅና ሙያ ሕግጋት በሚጥስ ተግባር ውስጥ መገኘት፣

ሐ) የሥነ ምግባር ጉባዔ ያሳለፈውን የጸና የሥነ ምግባር እርምጃ በሙሉ ፍቃዱ መጣስ ወይም ማስጠንቀቂያ ለመቀበል የሥነ ምግባር ሸንጎው ጋር በሙሉ ፍቃዱ አለመቅረብ ወይም በሙሉ ፍቃዱ በአግባቡ ወጪ የተደረጉ መጥሪያዎችን አለመቀበል ወይም አለማክበር ወይም ደንቡ መረጃ መስጠትን ካልከለ ወይም ምሥጢር መጠበቅን በተመለከተ አግባብነት ባላቸው ሕግጋት ጥበቃ የተሰጠው ካልሆነ በቀር ከሥነ ምግባር ባለሥልጣኖች ላቀረቡት ሕጋዊ ጥያቄ በሙሉ ፍቃዱ መልስ አለመስጠት፡፡

 

አንቀጽ 93 - ቀላል ጥፋት

 

1. ቀላል ጥፋት የሚባለው የሕግ አገልግሎት የሚሰጠው ሰውን ፍቃድ እንዲታገድ የማያደርግ ጥፋት ነው፡፡

2. ከሚከተሉት አንዱን የሚመለከት ጥፋት ቀላል ጥፋት አይባልም፡-

 

ሀ) ገንዘብን አለአግባብ መጠቀም፣

ለ)    ደንበኛ  ወይም  ሌላ  ሰው  ላይ  ከፍተኛ  ጉዳት  የሚያደርስ  ወይም  ሊያደርስ የሚችልን ድርጊት ማድረግ ወይም አለማድረግ፣

ሐ)    መልስ  ሰጪው  ባለፉት   ሦስት  ዓመታት   በይፋ   የሥነ  ምግባር  እርምጃ ተወስዶበት ከነበረ፣

መ)   ባለፉት  አምስት  ዓመታት   ውስጥ  መልስ  ሰጪው   የሥነ  ምግባር  እርምጃ ከተወሰደበት ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ ድርጊት ከሆነ፣

ሠ)    ድርጊቱ  የመልስ  ሰጪውን   ዕምነት  ማጉደል፣  ውሸት፣  ማጭበርበር  ወይም ማታለልን የሚመለከት ከሆነ፣

ረ)    በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፺6 የተጠቀሰውን “ከባድ ወንጀል” የሚያቋቁም ከሆነ ወይም ሰ)      ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጥፋት አካል ከሆነ፡፡

 

አንቀጽ 94 - ተግሳጽ

 

1. ጉባዔው በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፻108 በተሰጠው ትርጓሜ መሠረት “ቀላል ጥፋት” የሚያቋቁም የሙያ ደንቦችን የጣሰ ጠበቃን መገሰጽ ይችላል፡፡

2. በጠበቃው ላይ የተከፈተ እና በመካሄደ ላይ የሥነ ምግባር ወይም የወንጀል ክስ ካለ ወይም ጥሰቱ ከተፈጸመ ከሁለት ዓመት በላይ ከሆነው ጉባዔው ተግሳጽ መስጠት አይችልም፡፡

3. የተገሳጽ ማስታወቂያ የተቀበለ ጠበቃ ተግሳጹ በደረሰው በ1 ወር ውሰጥ ውሳኔውን በመቃወም ለጉባዔው ማቅረብ ይችላል፡፡

4. ተግሳጽ መሰጠቱን የሥነ ምግባር ጉባዔው ሊያውቀው ይገባል፡፡

 

አንቀጽ 95 - ይግባኝ

ተገሳጹን  በመቃወም   የቀረበ  ማመልከቻ  ውድቅ  ከተደረገ  ጠበቃው   ለሥነ  ምግባር ጉባዔው ይግባኝ ማቅረብ ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 96 - ከባድ ወንጀል አንቀጽ

“ከባድ ወንጀል” ማለት ጠበቃው ለጥብቅና ሙያ ያለውን ሐቀኝነት፣ ታማኝነት እና ብቃት ጋር መቃረኑን የሚያሳይ ወይም በሕግ በተሰጠው ትርጉም መሠረት የወንጀሉ መሠረታዊ ማቋቋሚያ ወንጀሉ በፍትሕ አስተዳደር ላይ ጣልቃ መግባት፣ ሐሰተኛ መኃላ፣ ማታለል፣ ማጭበርበር፣ ውሸት፣ ጉቦ፣ ማስገደድ፣ ምዝበራ፣ ስርቆት፣ ሌላ ሰው ከባድ ወንጀል እንዲሠራ መሞከር፣ ማሤር ወይም መገፋፋት ነው፡፡

 

አንቀጽ 97 - ቅጣት

 

1. ጥፋት ከሚከተሉት አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ቅጣት ያስከትላል፡፡

ሀ) በሥነ ምግባር ጉባዔው ከጠበቆች ማኅበር አባላት መሠረዝ፣

ለ) ከሦስት ዓመት ላልበለጠ ተገቢ ጊዜ መታገድ፣

ሐ) በአመክሮ ማቆየት ውይም

መ) ተግሳጽ፡፡

2. በጽሐፍ የተቀመጡ ሆኔታዎች ከማስጠንቅቂያ እና ተግሰጽ ጋር ሊሠጡ ይችላል፡፡

3. በጽሑፍ የተቀመጡትን ሀኔታዎች አለማክበር ጉዳዩ በድጋሚ እንዲጤን ወይም በመልስ ሰጪው ላይ መደበኛ ክስ ለማቅረብ ምክንያት ነው፡፡

4. የጠበቃን ጥፋት ለይቶ ቅጣት ለመጣል የሚከተሉት ምክያቶች ማጤን አለባቸው፡-

ሀ)    ጠበቃው  የጣሰው  ለደንበኛው፣   ለሕዝብ፣  ለሕግ  ሥርዓቱ   ወይም  ለሙያው ሊወጣ የሚገባውን ግዴታ መሆኑን፣

ለ)    ጠበቃው ድርጊቱን የፈጸመው ሆነ ብሎ፣ እያወቀ ወይም በቸልተኝነት መሆኑን፣

ሐ)  በጠበቃው ጥፋት ምክንያት በእርግጥ የደረሰው ወይም ሊደርስ ሚችለው ጉዳት መጠን፣ እና

መ)   ቅጣቱን የሚያቀሉ ወይም የሚያከብዱ ማናቸውም ነገሮች መኖራቸው፡፡

5. የተወሰደው ጠበቃውን   ከጠበቆች   ማኅበር  የመሠረዝ፣  የማገድ  እና  የመገሰጽ  የሥነ ምግባር እርምጃ ከሆነ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል፡፡

6. የሥነ ምግባር ጉባዔ በወሰዳቸው ለሕዝብ ይፋ የሆኑ የሥነ ምግባር እርምጃዎች ሁሉ ጉባዔው በጉዳዩ ላይ ያንን ቅጣት የጣለበትን ምክንያት በጽሑፍ መግለጽ አለበት፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሁለት

የፌዴራል የሥነ ምግባር ጉባዔ

አንቀጽ 98 - መቋቋም

 

1. ነጻ የሆነ የፌዴራል የጠበቆች ሥነ ምግባር ጉባዔ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡

2. የሥነ ምግባር ጉባዔው በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ይተዳደራል፡፡

 

አንቀጽ 99 - ዓላማ እና ሥልጣን

 

1. የሥነ ምግባር ጉባዔው ዓላማ ይህንን አዋጅ ወይም ሌሎች የሙያ ደንቦችን የሚጥሱ ጠበቆችን እና የሕግ አገልግሎት ድርጅቶችን ሰምቶ አከራክሮ መወሰን ነው፡፡

2. የሥነ ምግባር ጉባዔው በፍርድ ቤት በድጋሚ የሚታዩ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ሆው ይቆጠራሉ፡፡

 

አንቀጽ 100 - አባላት

 

1. የሥነ ምግባር ጉባኤው 9 አባላት ይኖሩታል፡፡

2. ከሥነ ምግባር ጉባዔው አባላት 5ቱ በምሥጢር በሚሰጥ ድምጽ ከፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በብቃታቸው፣ በስብዕናቸው እና በልማዳቸው ላይ በመመሥረት የሚመረጡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 4ቱ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሚከተለው ጥንቅር የሚሾሙ ናቸው፡-

ሀ) ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት 1 አባል፣

ለ) ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምክር ቤት 1 አባል፣

ሐ) ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች  1 አባል፣ እና

መ) ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ  1 አባል፡፡

 

ንዑስ ክፍል ሶስት

የፌዴራል የደንበኞች ቅሬታ ጽህፈት ቤት

 

አንቀጽ 101 - መቋቋም

1. በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር የፌዴራል የደንበኞች ቅሬታ ጽህፈት ቤት በዚህ አዋጅ መሠረት ተቋቁሟል፡፡

2. የፌዴራል የደንበኞች ቅሬታ ጽህፈት ቤት የሚከተሉት ሥልጣኖች አሉት፡-

ሀ) የጠበቆችን ምግባር በተመለከተ መረጃ እና ቅሬታ መቀበል፤፣

ለ)    አቤቱታ አቅራቢዎች አቤተታቸውን እንዲያቀርቡ መርዳት፣

ሐ)    ለአቤቱታ አቅራቢዎች ስላሉት ሕጋዊ መፍትሔዎች መረጃ መስጠት፣ እና

መ)   የጠበቃውን ምግባርን በተመለከተ በአቤቱታው የተገለጹት ፍሬ ነገሮች በጠበቃው ላይ ሌሎች እርምጃዎች ለመውሰድ ምክንያት መሆን አለመሆኑ መወሰን፡፡

 

አንቀጽ 102 - መመሪያ

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል የደንበኞች ቅሬታ ጽህፈት ቤት የሥነ ሥርዓት መመሪያ ማውጣት አለበት፡፡

 

አንቀጽ 103 - ሥነ ሥርዓታዊና የማሥረጃ ደንቦች

 

1. የሥነ ምግባር ሥነ ሥርዓት ክርክር ሒደት የፍትሃብሔርም ሆነ የወንጀል ክርክር ያልሆነ የተለየ ክርክር ሒደት ነው፡፡

2. በዚህ አዋጅ በልዩ ሁኔታ ካልተደነገገ በቀር የተከራካሪዎቹን በሕግ አግባብ የመዳኘት መብት ከግምት በማስገባት የፍትሃ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ እና የፍትሃ ብሔር ጉዳይ የማሥረጃ ደንቦች ለሥነ ምግባር ክርክሮችም ተፈጻሚ ናቸው፡፡

3. የመደበኛ የጥፋት ወይም የአነስተኛ ጥፋት ክስ፣ ወደነበረበት ለመመለስ ወይም ለዳግም ቅበላ ማመልከቻ እና ወደ ለመዘዋወር እና አገልግሎት እንዳይሰጥ ለማድረግ የሚቀርብ ማመልከቻ በግልጽ እና አሳማኝ ማሥረጃ መደገፍ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 104 - በፈቃድ የሚወሰድ የሥነ ምግባር እርምጃ

 

1. መደበኛ ክስ የተመሠረተበት ጠበቃ አቤቱታውን ወይም የተለየ ክስን በተመለከተ በቅድመ ሁኔታ የእምነት ቃል በመስጠት የተወሰነ የሥነ ሥርዓት እርምጃ እንዲወሰድበት ሐሳብ ማቅረብ ይችላል፡፡

2. የሥነ ምግባር ጉባዔው የቀረበለትን በቅድመ ሁኔታ የተሰጠ የዕምነት ቃል ሐሳብ ያጸድቃል ወይም ውድቅ ያደርጋል፡፡

3. የተወሰነ የሥነ ሥርዓት እርምጃ እንዲወሰድበት የቀረበው ሐሳብ በሥነ ምግባር ጉባዔው ውድቅ ከተደረገ ጠበቃው በቅደመ ሁኔታ የሠጠውን የዕምነት ቃል ቀሪ መደረግ አለበት፡፡ በቀጣይ የክርክር ሒደት ውስጥ በጠበቃው ላይ ሊቀርብብት አይችልም፡፡

4. የሚጣለው የሥነ ምግባር እርምጃ መጠን በድጋሚ ሊታይ ይችላል፡፡

5. መደበኛ ክስ ከመቅረቡ በፊት ማስጠንቀቂያ ወይም በአመክሮ ማቆየት ስምምነት ላይ ከተደረሰ በሥነ ምግባር ጉባዔው ሰብሳቢ መጽደቅ አለበት፡፡

6. የተወሰነ የሥነ ሥርዓት እርምጃ እንዲወሰድበት የተስማማ ጠበቃ በሥነ ሥርዓት እርምጃው የሚስማማ መሆኑን የሚገልጽ ቃለ መኃላ ለሥነ ምግባር ጉባዔው ማቅረብ እና፡-

ሀ) ጠበቃው ፍቃዱን የሠጠው በነጻነት እና በበጎ ፍቃዱ መሆኑን፣ ማንኛውም ማስፈራራት ወይም ማስገደድ ሳይደርስበት እና ፍቃዱን የመስጠቱን ውጤት በአግባቡ የተረዳ መሆኑን፣

ለ) ጠበቃው በመከናወን ላይ ያለ ምርመራ ወይም  ጠባዩ  በትክክል  ወደፊት የሚታወቅ የሥነ ምግባር እርምጃ ሊያስወሰድ ይችላል የተባለ ክስን የተመለከተ ክርክር መኖሩን የሚያውቅ መሆኑን፣

ሐ) ጠበቃው የተባሉት የድርጊቱ ፍሬ ነገሮች እውነት መሆናቸውን እውቅና እንደሚሰጥ፣

መ) ጠበቃው ፍቃዱን የሠጠው በምርመራ ላይ ያለውን ድርጊት መሠረት አድርጎ ክሥ ቢመሠረት ወይም በክርክር ላይ ያለው ጉዳይ ራሱን ውጤታማ በሆነ መልኩ መከላከል እንደማይችል በማወቁ እንደሆነ፡፡

7. የቀረበው የሥነ ሥርዓት እርምጃ ሐሳብ ተቀባይነት በሚያገኝባቸው ሌሎች ሁኔታዎች የሥነ ምግባር ጉባዔው በጠበቃው ፍቃድ የሚወስደውን እርምጃ ያዛል፡፡

 

አንቀጽ 105 -  ከአጭር ጊዜ በኋላ ወደነበረበት መመለስ

 

በሥነ ምግባር እርምጃ ምክንያት ለስድስት ወር ወይም ከዛ በታች ለሆነ ጊዜ ታግዶ የነበረ ጠበቃ የእገዳው ጊዜው ሲያልቅ በእገዳ ጊዜው የተሰጡ ትዕዛዞችን እንዳከበረ እና ተገቢውን ክፍያ እና ወጪ መክፈሉን የሚገልጽ በቃለ መኃላ የተደገፈ አቤቱታ በማቅረብ ወደ ነበረበት መመለስ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 106 - ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደነበረበት መመለስ

 

1. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የሥነ ምግባር ቦርድ ከስድስት ወር በላይ ታግዶ ስለቆየ ጠበቃ፣ ከጠበቃ ማኅበሩ አባልነት የተሰረዘ ጠበቃ አቤቱታ ስለሚያቀርብብት መንገድ፣ ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ለዳግም ቅበላ የተቀመጡ መሥፈርቶች፣ ስለ ማመልከቻዎች ዳግም መታየት፣ ክስ ስለሚሰማበት ቀን እና በሥነ ምግባር ጉባዔው ውሳኔ ስለሚሰጥበት እና ወደነበረበት ለመመለስ ወይም ለዳግም ቅበላ ሁኔታዎችን የሚመለከት ደንብ ማውጣት አለበት፡፡

2. በሥነ ምግባር ጉባኤው የተሰጠ ውሳ በፍርድ ቤት በድጋሚ ሊታይ ይችላል፡፡

3. ወደነበረበት ለመመለስ ወይም ለዳግም ቅበላ ማመልከቻ አቅርቦ ተቀባይት ያላገኘ ጠበቃ ማመልከቻው ውድቅ በተደረገ በአንድ ዓመት ውስጥ በድጋሚ ወደነበረበት ለመመለስ ወይም ለዳግም ቅበላ በድጋሚ ለማመልከት አይፈቀድለትም፡፡

 

አንቀጽ 107 - በፍርድ ቤት በድጋሚ ስለመታየት

 

1. የሥነ ምግር ጉባዔው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወገን ውሳኔው በተገጸ በ ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡

2. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታው ተገቢነት ከሌለው ውድቅ ሊያደርገው መልስ ሰጪውን ከሰማ በኋላ በማናቸውም የሕግ ወይም የፍሬ ነገር ጥያቄ ላይ ሊወስን ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 108 -  ማስታወቂያ

 

1. የሥነ ምግባር ጉባዔው የሥነ ምግባር እርምጃ በወሰደ በ1 ቀናት ውስጥ ከፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አባልነቱ የተሠረዘው፣ በጊዜያዊ ዕግድ ውስጥ ያለው ወይም ከስድስት ወር በላይ የታገደው መልስ ሰጪ በተመዘገበ ወይም ማረጋገጫ በተመሰከረለት ደብዳቤ

 

ሀ)    በሂደት ላይ ባሉ ጉዳዮች የተወከሉ ደንበኞችን፣

ለ)    በሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮች አብሮ ለሚሰራ ጠበቃ እና

ሐ) በሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮች የተቃራኒ ወገን ጠበቃ ወይም የተቃራኒ ጠበቃ በሌለ ጊዜ ተቃራኒ ወገኖች፣ ጠብቃው ስለመታገዱ እንዲያውቁት ይደረጋል:: ለተቃራኒ ወገን ጠበቃ ወይም የተቃራኒ ጠበቃ በሌለ ጊዜ ተቃራኒ ወገኖች፣ በሚሰጠውም ማስታወቅያ ለይ የመልስ ሰጪ ደንብኛ አድራሻ መገለፅ አለበት::

2. የሥነ ምግር ጉባዔው ደንበኞችን ወይም ሌሎች የህብረተሰቡን አባል ጥቅም ለመጠበቅ ለገንዘብ ተቋማት እና ሌሎች አስፈላጊ ተቋማት ማስታወቂያ እንዲሰጥ ሊያዝ ይችላል፡፡

3. መልስ ሰጪ ለሁሉም ደንብኞቹ ማንኛውንም በእጁ የሚገኙ ሰነዶችን ወይም ንብረቶችን ያስረክባል ወይም አስቸኳይነቱን በመግልፅ ሰነዶቹ ወይም ንብረቶቹ የሚረከቡበት አመቺ ቦታ እና ጊዜን ማሳወቅ አለበት::

4. የሥነ ምግር ጉባዔው ጠበቃውን ከማኅበር አባልነቱ የሠረዘው፣ በጊዜያዊ ዕግድ ውስጥ ያስገባው ወይም ያገደው ወይም አገልግሎት እንዳይሰጥ ማድረግ የሰጠው ውሳኔ ለህዝቡ ጥቅም ሲባል ወድያው የሚፀና መሆኑ ካልተገለፀ በስተቀር ውሳኔው የሚፀናው ከ15 ቀናት ቡኋላ ብቻ ነው::.

5. መልስ ሰጪ የተሰጠበት ውሳኔ ብፀና በ1 ቀናት ውስጥ ከተቀበለው ቅድመ ክፍያ ላይ የልስራበትን መጠን ለደንብኛው ተመላሽ ያደርጋል::

6 እገዳው ወይም የሥነ ምግር ጉባዔው ጠበቃውን ከማኅበር አባልነቱ የመሠረዝ ውሳኔው ከመፅናቱ በፊት ደንብኛው ሌላ ጠበቃ ማግኘት ያልቻለ እንደሆነ መልስ ሰጪው ወደ ጉዳዩ የሚታይበት አካል ዘንድ ቀርቦ የማስፈቀድ ኃላፊነት አለበት:: ይህ ሁኔታ ሲከሰት መልስ ሰጪ ጉዳዩ እየታየ ለሚገኝበት አካል ለተቃራኒ ጠበቃ ወይም ለተቃራኒ ወገን ስለማሳወቁ ማመልከት አለበት::

 

ንዑስ ክፍል አራት

የክርክር ክፍያዎች እና ወጪዎች

 

አንቀጽ 109 - የአስተዳደራዊ ክፍያዎች

የፌዴራል ጠበቆች ማኀበር የአስተዳደራዊ ወጪዎቹን ለመሸፈን በተለይም ወደ ጥብቅና ሙያ ለመግባት የሚቀርቡ ማመልከቻዎችን ለማከናወን አስተዳደራዊ ክፍያዎችን ማስከፈል ይችላል፡፡

 

አንቀጽ 110 - የሥነ ምግባር ክርክሮች ወጪ

 

በአዋጁ በዚህ ክፍል ውስጥ የተገለጹት የሥነ ምግባር ክፍሎች በዝርዝር ሕገ ድንባቸው እና የሥነ ሥርዓት ደንቦች በተወሰነው መሠረት ክፍያ ያስከፍላል፡፡

 

ክፍል ዘጠኝ

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

 

አንቀጽ 111 - ሰነድ የማረጋገጥ ሥራ

 

1. የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተገለጹትን ማናቸውም ሰነዶች በቅርጽ እንከን እና ይዘት ምክንያት አልመዘግብም ማለት አይችልም፡፡

2. ጠበቃው ያዘጋጃቸው ሰነዶች ቅርጽና ይዘት የጸና መሆንን አስመለክቶ ጠበቃው ሙሉ ኃለፊነት ይወሰዳል፡፡

3. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሰ ሰነድ ያዘጋጀው ጠበቃ ሙሉ ስም እና ሌላ መለያ መረጃ መያዝ አለበት፡፡

4. ጠበቃ ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ልዩ ፍቃድ በማግኘት የሰነዶች ማረጋገጥ ሥራ ሊሠራ ይችላል፡፡

5. የሰነድ ማረጋገጥ ሥራ ለመሥራት የፌዴራል ጠበቆች ማኀበር አባል መሆን ብቻ በዚ አይደለም፡፡

6. የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሰነድ ማረጋገጥ አገልግሎት የሚሰጡ ጠበቆችን ለመቆጣጠር መመሪያ ማውጣት አለበት፡፡

 

አንቀጽ 112 - ምትክ ሕግጋት

 

ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ይህንን አዋጅ ሳይቃረን የዚህ አዋጅ ደንቦችን ለማስፈጸም የሥነ ምግባር ደንብ እና ሕገ ደንቦች የማውጣት ሥልጣን አለው፡፡

 

አንቀጽ 113 - መሸጋገሪያ ድንጋጌዎች

 

1. በዚህ አዋጅ መሠረት የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ኃላፊነተን እስኪረከብ ድረስ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር በነባር ሕጎች መሠረት የጠበቆችን ቁጥጥር ይቀጥላል፡፡

2. በፌዴራል ጠበቆች ማኅበር የቀረቡ ይህ ሕግ በሥራ ላይ ከመግባቱ በፊት በመታየት ላይ ያሉ ጉዳዮች በወቅቱ ጸንተው በነበሩት ድንጋጌዎች መሠረት ይቀጥላሉ፡፡

3. ምክር ቤቱ ሥራውን አስኪረከብ ድረስ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበርን ጸሐፊ ያስተዳድራል፡፡

4. የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እና ከሕግ የሙያ ማኅበራት የተውጣጡ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ማዋቀር አለበት፡፡

5. ኮሚቴው የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት እና በዚህ ዘዋጅ መሠረት እንደ አሥመራጭ ኮሚቴ ሆኖ ማገልገል አለበት፡፡

6. የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባዔ ይህ አዋጅ በሥራ ላይ ከዋለበት ቀን ጀምሮ በሦስት ወር ውሰጥ መደረግ አለበት፡፡

 

አንቀጽ 114 - የሕግ ትምህርት ቤቶች ወይም የሕግ ፋካሊቲዎች ዕውቅና

 

1. የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር እስከ ታህሳስ 21 ቀን 2116 ድረስ የሕግ ትምህርት ቤቶችን ዕውቅና ሥርዓት መጀመር የለበትም፡፡

2. እስከ ታህሳስ 21 ቀን 2127 ወደ ጥቅና ሙያ ለቅበላ የሚመለክት አመልካች በሕ የመጀመሪያ ደረጃ ዲግሪውን ዕውቅና ከተሰጠው የሕግ ትምህርት ቤት ማግኘት አለበት የሚለውን መሥፈርት ለሟሟላት አይጠበቅበትም፡፡

3. በሕግ የመጀመሪያ ደረጃ ዲግሪያቸውን ዕውቅና ከተሰጠው የሕግ ትምህርት ቤት ወይም የሕግ ፋካሊቲ ለማግኘት ዕድሉ ያልነበራቸው አመልካቾች ከዚህ መሥፈርት ነጻ ሊደረጉ ይችላሉ፡፡

 

አንቀጽ 115 - ዳግም ምዝገባ

 

1. ይህ አዋጅ ተፈጻሚ በሚሆንበት ቀን የጸና ፍቃድ ያላቸው ጠበቆች የዚህን አዋጅ መሥፈርቶች እንዳሟሉ ይቆጠራሉ፡፡

2. የዚህን አዋጅ የትምህርት መሥፈርቶች የማያሟሉ ጠበቆች ፍቃድ ባገኙበት ሕግ መሠረት ሥራቸውን የመቀጠል መብት አላቸው፡፡

3. ይህ አዋጅ ተፈጻሚ ከሆነበት ቀን በፊት ፍቃድ ያወጡ ጠበቆች የምክር ቤት አባላት በተመረጡ አንድ ዓመት ውስጥ በድጋሚ መመዝገብ አለባቸው፡፡

 

አንቀጽ 116 - የተሻሩና ተፈጻሚነት የሌላቸው ሕግጋት

 

1. የሚከተሉት ሕግጋት በዚህ አዋጅ ተሸረዋል፡-

ሀ)    የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፍቃደ እና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር  199/2ሺ

ለ)    የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፈተና፣ ምዝገባ እና የ … ክፍያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 65/2ሺ እና

2. የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች የሥነ ምግባር ደንብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 57/1999 በዚህ አዋጅ መሠረት በሚወጣ የስነ ምግባር ደንብ እስኪተካ ድረስ በሥራ ላይ ይቆያል፡፡

3. ከዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች ጋር የሚቃረን ማናቸውም ሕግ በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

 

አንቀጽ 117 - አዋጁ የሚጸናበት ቀን

 

ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ከታተመበት ቀን ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡

 

አዲስ አበባ ….. ቀን ….. ዓ.ም

 

ሳህለወርቅ ዘውዴ

የኢትዮጵ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት

Read 8192 times Last modified on Jun 19 2019
Abyssinia Law | Making Law Accessible!

Abyssinia Law is  a legal resource portal providing open access to primary and secondary legal materials for Ethiopia, such as laws, court decisions, articles, contact guidance and Lawyers Directory - with texts supplemented by online videos, a discussion forum and user blog. The service gives free access to Federal and State consolidated laws of Ethiopia (with status information whether the law is amended, repealed or effective)

Leave a comment