የሕክምና ስህተት ሕግ ምን ማለት ነው?

የሕክምና ስህተት ሕግ (Medical Malpractice Law) ዶክተሮች ወይም ሌላ የሕክምና አገልግሎት ሰጪ አካላት የሕክምና አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት በታማሚው ላይ በችልተኝነት ለሚያደርሱት ጉዳት ያለባቸውን ተጠያቂነት የሚገዛ ሕግ ነው፡፡ ይህ የሕግ ዘርፍ ከሀገር ሀገር የተለያየ ይዘት ቢኖረውም በአብዛኛው ሀገር ግን በሕክምና ስህተት ግለሰቦች ለሚደርስባቸው ጉዳት ጉዳቱን ያደረሰው አካል ተጠያቂ የሚሆንበት የአሠራር ሥነ ሥርዓት አላቸው፡፡ አንድ የሕክምና ባለሙያ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ በተመሳሳይ ጉዳይ ሌሎች የሕክማና ባለሙያዎች ሊያከብራቸው ወይም ሊፈጽሟቸው የሚገባውን መደበኛ ጥንቃቄ (“standard of care”) ሊያከናውን ወይም ሊከተል ባለመቻሉ ምክንያት በታማሚው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ የሕክምና ባለሙያው ለጥፋቱ ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር የሕክምና ስህተት ሕግ ይባላል፡፡

ሁሉም ስህተቶች የሕክምና ስህተት አይባሉም፡፡ አንድ ታካሚ የሚጠብቀውን የሕክምና ውጤት አላገኘሁም በማለት የሕክምና ባለሙያን ለመክሰስ አይችልም፡፡ በአጭሩ የሙያ ስህተት የሚባለው በአንድ የሙያ ዘርፍ የተሠማራ ባለሙያ ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ሊከተላቸው ወይም ሊመራባቸው የሚገባውን የሙያ ደንቦችና መመሪያዎች አውቆ ወይም በቸልተኝነት ሳያከብር መቅረት ወይም የሙያ ደንቦችን ባለማክበሩ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ እንደሆነ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2031 እና 2035 ይደነግጋል፡፡

በመሆኑም አንድ የሕክምና ባለሙያ የሕክምና ስህተት ፈጽሟል ለማለት የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ መሟላታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

1.     የአካሚና ታካሚ ሕጋዊ ግንኙት መኖሩን ማረጋገጥ

የሕክምና ስህተት አለ ብሎ ክስ ለመመሥረት የአካሚና ታካሚ ሕጋዊ ግንኙነት መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በሕክምና ባለሙያ እና በታካሚ መካከል ለሚኖረው ግንኙነት መሠረቱ የሕክምና አገልግሎት ውል ነው፡፡ ታካሚው ከሕክምና ባለሙያው ወይም ከሕክምና ተቋሙ ጋር የሚኖረው የሕክምና ግንኙነት የሚመሠረተው በውል እንደሚሆን የፍትሐብሔር ሕግ ከቁጥር 2639-2652 ያስረዳል፡፡ በአንድ የመዝናኛ ሥፍራ አንድ ዶክተር በሰጠዎት መድኃኒት ምክንያት ጉዳት ደርሶብኛል ለማለት አይቻልም፡፡ በሕክምና ተቋሙ ካርድ አውጥተው የሕክማ ባለሙያውን አግኝተውት እንደሆነ ግን የአካሚ ታካሚ ሕጋዊ ግንኙነት እንዳለ ማስረጃ ይሆናል፡፡

2.     የሕክምና ባለሙያው ቸልተኛ መሆኑን ማረጋገጥ

የሕክምና ጥፋቱን ፈጽሟል የተባለው የህክምና ባለሙያ ጥፋቱን የፈጸመው ቸልተኛ ሆኖ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ቸልተኛ የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ በሕግ የራሱ የሆነ የአተረጓጎም ስልት ያለው ሲሆን አንድ የሕክምና ባለሙያ ቸልተኛ ነው የሚባለው የፈጸመው ድርጊት አንድ የሕክምና ባለሙያ አንድን የተወሰነ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ ሊያከብራቸው ወይም ሊፈፅማቸው ይገባል ተብለው የተቀመጡን ዝቅተኛ የሕክምና አገልግሎት ደረጃን (minimum standard of care) ሊጥስ እንደሚችል ማወቅ እያለበት ወይም እየቻለ፣ ባለመገመት ወይም ባለማሰብ ድርጊቱን የፈጸመ እና ጉዳቱን ያደረሰ እንደሆነ ነው፡፡ በተለይም በሕክምናው ዓለም ሲመዘን በጉዳዩ ዙሪያ ሊደረጉ ይገባል ተብሎ በአግባቡ የሚጠበቁትን ጥንታቄዎች ያላደረገ እንደሆነ ድርጊቱ በቸልተኝነት ተፈጽሟል ያስብላል፡፡ ይህንንም ለማስረዳት በሙያው የተሠማሩ ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎች እንደ አዋቂ ምስክርነት (expert witness) መጠቀም ይግድ ይላል፤ ምክንያቱም የሕክምና ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ድርጊቱን ፈጸመ በተባለው ባለሙያ ልክ የትምህርት ደረጃው፣ የአካባቢ ሁኔታው፣ ልምድ ከግምት በማስገባት የሕክምና ሙያ ስህተት ተፈፅሟል ወይስ አልተፈፀመም የሚለውን ለማስረዳት መጠቀም ይቻላል፡፡

3.     የሕክምና ባለሙያው ቸልተኝነት ጉዳቱን ያደረሰው መሆኑን ማረጋገጥ

አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሕክምና ቦታ የሚመጡ ታማሚዎች ጉዳት የደረሰባቸው በሕመሙ ምክንያት ነው ወይስ የሕክምና ባሙያው በሠራው ስህተት የሚለውን ነጥብ ማስረዳት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የሕክምና ባለሙያው ቸልተኝነት ጉዳቱን ያደረሰው መሆኑን በግልጽ ማመለካት አለበት፡፡ ለምሳሌ በካንሰር የተያዘ አንድ ታካሚ ሕክምና ሲያገኝ ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይና ሰውዬው የሞተው የሕክምና ባለሙያው በፈጸመው ስህተት ነው ቢባል ሰውየው የሞተው በካንሰሩ ምክንያት ነው ወይስ የሕክምና ባለሙያው በፈጸመው ስህተት ነው የሚለው በግልጽ መለየትና መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

4.     በታካሚው ላይ የደረሰው ጉዳት ወደሚታወቅ ሌላ ጉዳት ያጋለጠው መሆንን ማረጋገጥ

ምንም እንኳን የሕክምና ባለሙያው የሕክምና ስህተት ቢፈጽምም ወይም የፈጸመው ድርጊት በተመሳሳይ የሕክምና ባለሙያ መስፈርት ከደረጃ በታች ቢሆንም ስህተት የተፈጸመበት ታማሚ ጉዳት እንደደረሰበት እስካላረጋገጠ ድረስ ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት ይዞ ለመሔድ አይችልም፡፡

ምን ዓይነት ስህተቶች ናቸው የሕክምና ስህተት የሚባሉት

ስህተቶች የሕክምና ስህተት የሚባሉት በተለያዩ ዘርፍ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-

·        የታማሚውን ሁኔታ አለመመርመር ወይም የታማሚውን ሁኔታ ለመመርመር መዘግየት፣

·        የኤክስ ሬይ ወጤቶችን አሳስቶ ማንበብ ወይም መረዳት፣

·        ትክክል ያልሆነ ወይም የተሳሳተ የመድኃኒት ትዕዛዝ መስጠት፣

·        አንድ የሕክምና ሥነ ሥርዓት ያለውን ጉዳት ወይም ሥጋት ለታማሚው አለመንገር፣ አለማስረዳት ወይም አለማስጠንቀቅ፣

·        ታማሚው በግልጽ ፈቃዱን ሳይሰጥ በታማሚው ላይ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን መፈጸም፣ እና

·        በቀዶ ጥገና ወቀት ወይም ልጅ በማስወለድ ጊዜ ስህተት መፈጸም

 

ይገኙበታል፡፡