የመሸሸግ ወንጀልን የሚደነግገው የተሻሻለው የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 682 የወንጀል ፍሬ ወይም ውጤት የሆኑ ንብረቶችን መያዝ፣ መደበቅ፣ ማስቀመጥ ሊያስከትል የሚችለውን ኃላፊነት ይዘረዝራል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ወንጀለኞችን ለመረዳት ወይም ከወንጀል ድርጊቶች ጥቅም ለማግኘት ታስቦ/ታውቆ ከሚደረግ የመሸሸግ ድርጊት በተጨማሪ ግለሰቦች በቸልተኝነት ማለትም የተጠቀሰው ንብረት የወንጀል ፍሬ መሆኑን ማወቅ እየተገባቸው በግድ የለሽነት ወይም በሌላ ምክንያት ይዘው የሚገኙ ሰዎች የሚቀጡበትን አግባብ ያስቀምጣል፡፡ በዚህም መሠረት ግለሰቦች በተለያየ አጋጣሚ እጃቸው የገቡ ንብረቶች በወንጀል ምክንያት ከትክክለኛ ባለቤቶቻቸው የተወሰዱ መሆኑ ሲረጋገጥ እስከ 1 ዓመት በሚደርስ እሥራት ሊያስቀጡ ይችላሉ፡፡

በመሆኑም ጎጃም በረንዳ ወይም ከሰፈር ወጠምሾች መንገድ ላይ የገዙ ሞባይል የስርቆት ወይም ሌላ የወንጀል ፍሬ መሆኑ ከተረጋገጠ እርሶንም ሊያስጠይቆት ይችላል፡፡ የተሰረቀ መሆኑን አላውቅም ነበር ብለው የሚያቀርቡት መከላከያም ከገዙበት ዋጋና ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይና የሚመዘን በመሆኑ ለምሳሌ በመደበኛ ሁኔታ ሊያወጣ ከሚችለው ዋጋ በጣም ዝቅ ባለ መጠን ንብረቱን መሸመትዎ፣ ግብይቱን ሲያካሒዱ በጨለማ ከሰው ተደብቀው መሆኑ …ወዘተ በርግጥም የተሰረቀ ንብረት መሆኑን ያውቁ እንደነበር የሚያመላክቱ ፍሬ ነገሮች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

ስለሆነም የተገዛው ዕቃ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች ከትክክለኛ ባለቤት መገዛቱ ካልተረጋገጠ ርስዎን ሊያስወነጅልዎት ስለሚችል ዕቃን በርካሽ ዋጋ አገኘሁ ብሎው ለመግዛት እንዳይቻኮሉ አጥብቀን ልንመክርዎ እንወዳለን፡፡