ፍርድ                

           ከሣሽ በሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም በአጭር ስነ ስርአት በተፃፈ ባቀረበው የክስ አቤቱታ ከተጠሪ ጋር በሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ/ም በተፈረመ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ኪራይ ውል መሰረት ተጠሪ የአመልካች ንብረት የሆኑትን አትላስ ካፕኮ ስሪት ሞዴሉ ኤየር አር ኦ ሲ ቲ 35 ዋገን ድሪል ኤክስ ኤ 316 የሆነ ሞዴል ካለው ኮምፕሬሰር ጋር ተ.እ.ታን ሳይጨምር በሜትር በብር 120 ሂሳብ ለመከራየትና የሚሰራው አጠቃላይ  ስራ ሜትርም 10,000 እንዲሆን አጠቃላይ ዋጋውም ብር 1,380,000 እንዲሆን ተስማምቶ ብር 250,000 እንደከፈለ፡፡ አመልካችም እንደ ውሉ የፈፀመ ቢሆንም ተጠሪ በውሉ መሰረት ክፍያውን እንዳልከፈለ በዚህም ምክንያት አለመግባባት የተፈጠረ በመሆኑ በውሉ አንቀፅ 9 መሰረትም አለመግባባት ሲፈጠር በግልግል ዳኞች እንደሚታይ እንደተመለከተ አመልካች የራሱን ግልግል ዳኛ የመረጠ መሆኑን ለተጠሪ ያሳወቀ ቢሆንም ተጠሪ የበኩሉን የግልግል ዳኛ በመምረጥ ለአመልካች ምንም ምላሽ አለመስጠቱን በዚህም ተጠሪ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የራሱን የግልግል ዳኛ ያልመረጠ በመሆኑ በፍ/ቤቱ በኩል እንዲመረጥና ወጪና ኪሳራ በቁርጥ ተጠሪ እንዲከፍል እንዲወሰንለት በመጠየቅ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡

 

   ተከሣሽ የመከላከያ ማስፈቀጃ እንዲያቀርብ ክሱ የደረሰው ቢሆንም በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የመከላከያ ማስፈቀጃውን ያላቀረበ በመሆኑ መብቱ ታልፏል፡፡    

     ፍ/ቤቱም በአመልካችና በተጠሪ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አይቶ የሚወስን የግልግል ዳኞች ጉባኤ ሊቋቋም ይገባል ወይስ አይገባም? በተጠሪ በኩል የግልግል ዳኛ በፍ/ቤቱ ሊሰየም ይገባል ወይስ አይገባም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን ከቀረበው ማስረጃ እና አግባብ ካለው ህግ ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምሯል፡፡

    አመልካች ክስ ያቀረበው ከተጠሪ ጋር ባደረግነው ውል መሠረት በመካከላችን አለመግባባት የተፈጠረ ስለሆነ እና በውሉ ላይ ደግሞ ይህን አለመግባባት አይቶ የመጨረሻ ውሣኔ የመስጠት ስልጣን ያለው የግልግል ዳኞች ጉባኤ መሆኑን የተስማማን በመሆኑ አመልካች የራሱን ግልግል ዳኛ እንደመረጠና ይህንንም ለተጠሪ ያሳወቀ ቢሆንም ተጠሪ የበኩሉን የግልግል ዳኛ በመምረጥ ለአመልካች ምንም ምላሽ አለመስጠቱን በዚህም ተጠሪ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የራሱን የግልግል ዳኛ ያልመረጠ በመሆኑ በፍ/ቤቱ በኩል እንዲመረጥ ውሳኔ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡

     በህግ አግባብ የተደረጉ ውሎች በህግ ፊት የሚፀና ህጋዊ ውጤትን የሚያስከትሉና  በተዋዋይ ወገኖች ላይ ህግ ስለመሆናቸው በፍ/ብ/ህ/ቁ 1678  እና 1731/1 ስር የተመለከተ ሲሆን ተዋዋይ ወገኖችም በገቡት የውል ግዴታ መሰረት መፈፀም ያለባቸውን ግዴታ የመፈፀም ሀላፊነት ያለባቸው ናቸው፡፡ በዚህም በውሉ ላይ አስቀድመው ውሉን ተከትሎ በመካከላቸው አለመግባባት ቢፈጠር ይህ አለመግባባት በምን መልኩ ታይቶ መፈታት እና መወሠን እንዳለበት ካስቀመጡት በኃላ በመካከላቸው አለመግባባት ከተፈጠረ ይህ አለመግባባት መፈታት ያለበት በውሉ ላይ በተቀመጠው የሙግት ወይም አለመግባባት መፍቻ መንገድ ሊሆን የሚገባ ሲሆን ይህንንም ከፍ/ብ/ህ/ቁ 3325 ÷ 3331  እና 3332 ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህም አንደኛው ተዋዋይ ወገን አለመግባባት ተፈጥሯል የሚል ከሆነ ይህን ጥያቄ ማቅረብ ያለበት ውሉን መሠረት በማድረግ ሊሆን የሚገባ መሆኑን የሚያስረዳ ሲሆን በውሉ ላይ አለመግባባቱ ከአማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶች አንዱ በሆነው በግልግል ዳኝነት ታይቶ መወሠን እንዳለበት ከተቀመጠ አለመግባባቱ በግልግል ዳኝነት ታይቶ መወሠን ያለበት፡፡ በውሉ ላይ ገላጋይ ዳኛው ተመርጦ በግልጽ ካልተቀመጠ እና አንደኛው ተዋዋይ ወገን አለመግባባቱ በውሉ መሠረት በግልግል ዳኝነት ታይቶ እንዲወሠን ለማድረግ የበኩሉን የግልግል ዳኛ ካልመረጠ ሌላኛው ተዋዋይ ወገን የግልግል ዳኞች ጉባኤ እንዲሠየም ለፍ/ቤቱ ጥያቄውን ማቅረብ ይችላል፡፡

     አመልካች በግራቀኙ መካከል በሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ/ም የተደረገውን የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ኪራይ ውልን ተከትሎ አለመግባባት የተፈጠረ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ተጠሪ ያቀረበው መከራከሪያ የለም፡፡ ግራቀኙ ያደረጉትን የውል ስምምነት ፍ/ቤቱ እንደመረመረው  በውሉ አንቀፅ 9.1 ላይ በግራ ቀኙ መካከል ዉሉን በተመለከተ አለመግባባት ቢፈጠር በድርድር በቅድሚያ እንዲፈታ ጥረት እንደሚደረግ በዚህ መሰረትም መፍትሄ ካልተገኘ በግልግል ጉባኤ እንደሚፈታ የተመለከተ ሲሆን የግልግል ዳኞች በውሉ ላይ ማን እንደሆኑ ተመርጠው የተሰየሙበት አግባብ የለም፡፡ ስለሆነም በግራቀኙ መካከል የተደረገውን ውል ተከትሎ የተፈጠረውን አለመግባባት የሚፈታ የግልግል ዳኞች ጉባኤ ሊሠየም የሚገባው ነው፡፡ አመልካች በሰኔ 1 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ የራሱን የግልግል ዳኛ የመረጠ መሆኑን በመግለፅ በሶስት ቀን ውስጥ ተጠሪ የራሱን የግልግል ዳኛ በመምረጥ ለአመልካች እንዲያሳውቅ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ በግልግል ዳኝነት ጉዳዩ እንዲታይ ከመደረጉ በፊት የራሱን ገላጋይ የሾመው ወገን ሌላኛው እንዲመርጥ ማሳወቅ እንዳለበት እና ሌላኛውም ወገንም የራሱን የመምረጥ መብት ያለው ሲሆን በግራቀኙ የሚመረጡት ገላጋይ ዳኞች ደግሞ ሰባሳቢ ዳኛውን እንደሚመርጡ በቅድሚያ እድሉ ሊሰጣቸው የሚገባ ነው፡፡ በያዝነው ጉዳይ አመልካች የራሱን የግልግል ዳኛ የመረጠ ሲሆን በውሉ ላይ የግልግል ዳኛ አንደኛው ወገን ከመረጠና ለሌላኛው ወገን ካሳወቀ ይህ ማስታወቂያ የደረውና ያልመረጠው ወገን ማስታወቂያ በደረሰው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ የግልግል ዳኛ  መምረጥ እንዳለበት ያልተመለከተ ሲሆን በዚህም ተጠሪ አመልካች በገለፀው የሶስት ቀን ጊዜ ውስጥ የግልግል ዳኛ ባለመምረጡ የተነሳ ብቻ በውሉ እና በህግ ያገኘውን የግልግል ዳኛ በቅድሚያ የመምረጥ መብት ሊያጣ የሚችልበት የህግ አግባብ የለም፡፡

በመሆኑም በቅድሚያ ግራቀኙ የየበኩላቸውን ገላጋይ ዳኛ እንዲመርጡ፤ ሰባሳቢውንም በስምምነት እንዲመርጡ እድል በመስጠት በውሉ መሠረት እንዲፈፀም እንጂ ግራቀኙ ገላጋይ ዳኛ የመምረጥ መብታቸው ቀሪ ሊሆን የማይገባ በመሆኑ ተጠሪ ገላጋይ ዳኛ በቅድሚያ በራሱ ሊሾም ይገባል  ተብሏል፡፡   

                        ውሳኔ

  1. በአመልካችና በተጠሪ መካከል በሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ/ም የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት አይቶ የሚወሰን የግልግል ዳኞች ጉባኤ ሊሠየም ይገባል፡፡
  2. ግራቀኙ የየበኩላቸውን የግልግል ዳኛ በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ይምረጡ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ መርጠው የማይቀርቡ ከሆነ በፍ/ቤቱ ሬጅስትራር በኩል ገላጋይ ዳኞች ይሾሙ፡፡
  3. በግራቀኙ በኩል የሚመረጡት /የሚሾሙት/ ገላጋይ ዳኞች በስምምነት ሠብሣቢ ዳኛውን ይምረጡ፡፡ ሠብሣቢ ዳኛውን በስምምነት መመረጥ ካልቻሉ በአንደኛው ወገን አመልካችነት ሠብሳቢው ዳኛ በፍ/ቤቱ ሬጅስትራር በኩል ይሾም፡፡
  4. ወጪና ኪሣራን ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ፡፡

ትዕዛዝ

  • ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡
  • መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡