ተከሳሾች፡- 1ኛ. አቶ አብዲሳ በየነ ያደታ

         2ኛ. ፍቅር ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማ

መዝገቡ የተቀጠረው መርምሮ ተገቢውን ለመስራት ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ብይን ተሠጥቷል፡፡

ብ ይ ን

     ከሳሾች በሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ከሳሾች 2ኛተከሳሽን በጥቅምት 30 ቀን 2008 ዓ/ም በብር 300,000 እንደመሰረቱ ማህበሩ የተቋቋመበት አላማም የእንስሳት መድሀኒት ከውጪ አገር አስመጥቶ ማከፋፈልና መሸጥ መሆኑን 1ኛተከሳሽም ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ/ም በተደረገ ቃለ ጉባኤ አባል ሆነው እንዲገቡ እንዲሁም በምክትል ስራ አስኪያጅነት እንዲሰሩ ተደርጎ ሲሰሩ እንደቆዩ ነገር ግን 1ኛተከሳሽ በቃለ ጉባኤው በተጠቀሰው መሰረት የማህበሩን ስራ በተሻለ ያስኬዳሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ወደ ማህበሩ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ የማህበር አባል ሊፈፅም የሚገባውን የማይፈፅሙና ሀላፊነት የማይወስዱ ከ1ኛተከሳሽ ስራ አስኪያጅ ጋር በየጊዜው በፍ/ቤት ጭምር የሚካሰሱ መሆኑን በከፋ ጭቅጭቅ ውስጥ እንዳሉ ማህበሩ እንዲፈርስም ከሳሾች በሌላ ችሎት ክስ ያቀረቡ መሆኑን በሌላ በኩል ተከሳሽ በፌ/መ/ደ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 7ኛ ፍ/ብ እሎት የማህበሩን መስራችና መሪ ባለሙያ ከ1ኛከሳሽ ስራ አስኪያጅ ሊሆኑ አይገባም በማለት በመ/ቁ 171480 ክስ አቅርበው ውሳኔ እንደተሰጠ ይህ በመሆኑም ዋና ስራ አስኪያጅ በሌለ ጊዜ አስተዳደሪ ሆኜ ልሾም ይገባኛል በማለት የአስተዳዳሪነቱን ቦታ በአሁኑ ሰአት ይዘው እንደሚገኙ ከሳሾች በማህበሩ 67% 1ኛተከሳሽ ደግሞ 33% ድርሻ እንዳላቸው 1ኛተከሳሽ አነስተኛ ባለመብት ሆኖ ማህበሩን ለማስተዳደር የሚያስችል የሙያ ብቃት የሌላቸው እንዲሁም በቃለ ጉባኤ ብቻ አባል በመሆናቸው ስራ አስኪያጅ ሆነው መሾማቸው የዋና ባለመብቶችን መብትና ጥቅም እጎዳ እንደሆነ 1ኛተከሳሽና ሌሎች አባላት በተለያዩ ፍ/ቤቶች በክርክር ላይ የሚገኙ ሲሆን 1ኛተከሳሽ ከዚህ ቀደም የ2ኛተከሳሽ ቴክኒካል ማናጀር ሆነው ከፍተኛ የሆነ የዲሲፕሊን ጥፋት ፈፅመው መስከረም ወር 2010 ዓ/ም ከድርጅቱ ሀላፊነት እንዲነሱ የሆነ መሆኑን፤

      1ኛተከሳሽ ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በሀላፊነት በነበሩበት ጊዜ በወጋገን ባንክ ለኢ/ት ንግድ መርከብ የትራንስፖርት አገልግሎት ሊከፈል የሚገባ ቼክ ብር 108,307.30 በቼክ እንዲከፈል ተጠይቆ የነበረ ሲሆን ተከሳሽ ግን ክፍያውን በቼክ ሳይሆን በቀጥታ በባንኩ እንዲከፈል በማድረግ የቼኩን ገንዘብ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል ጥረት እንዳደረጉ ቼኩን በተመለከተም የወንጀልና የፍ/ብ ክስ አቅርበው ውደቅ እንደተደረገ በዚህም 1ኛተከሳሽ አሁን ባላቸው ስልጣን ማህበሩን ማስተዳደራቸው በማህበሩም ሆነ በከሳሾች መብት ላይ የማይተካ ጉዳትን የሚያደርስ በመሆኑ 1ኛተከሳሽ ከማህበሩ ስራ አስኪያጅነታቸው እንዲነሱ ውሳኔ እንዲሰጥላቸው  ጠይቀው የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርበዋል፡፡

   1ኛተከሳሽ በሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ/ም በተፃፈ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ ላይ ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከሳሾች 1ኛተከሳሽ ከማህበሩ ስራ አስኪያጅነት ስልጣን እንዲሻር  ዳኝነት የጠየቁ ቢሆንም 1ኛተከሳሽ ስራ አስኪያጅ ስለመሆናቸው ያቀረቡት ማስረጃ አለመኖሩን ይልቁንም ከሳሾች ይህንን አቤቱታ ያቀረቡት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ የነበሩት 1ኛ ከሳሽ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 7ኛ ንግድ ችሎት በመ/ቁ 171480 በሆነው በነበረው ክርክር ከፍተኛ የሆነ ጥፋት በመፈፀማቸው ከስራ አስኪያጅነት ስልጣናቸው እንዲነሱ እና በእጃቸው የሚገኙ ማህተሞች እና ሌሎች ንብረቶችን እንዲያስረክቡ የአፈፃፀም ትዕዛዝ በመሰጠቱ በዚህ ውሳኔ ቅሬታ ተሰምቷቸው ይግባኝ አቅርበው ውድቅ በመደረጉ አፈፃፀሙን ለማሰናከል በማሰብ ያቀረቡት ክስ መሆኑን ተገቢ ያልሆነ ክስ ያቀረቡ በመሆኑ በማህበሩ ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ዋስትና ሊያሲዙ እንደሚገባ፤

      ከሳሾች በማስረጃነት ካቀረቡት መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 8/8.1/ ለመመልከት እንደሚቻለው የማህበሩ ስራ አስኪያጅ 1ኛ ከሳሽ እንደሆኑ ከሳሾች በክስ አቤቱታቸው ላይ 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅ መሆናቸውን እንደገለፁ ይህም የሚያሳየው 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አለመሆናቸውን መሆኑን ከሳሾች 1ኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ ስለመሆናቸው ያቀረቡት ምንም አይነት ማስረጃ የለም፡፡ ከሳሾች 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ስለመሆናቸው ያቀረቡት ማስረጃ ሳይኖር እና በክስ አቤቱታቸው ጭምር የ1ኛ ተከሳሽ የስራ ድርሻ ም/ስራ አስኪያጅነት እንደሆነ እየገለፁ ባለበት 1ኛ ተከሳሽ ከስራ አስኪያጅነት ስልጣን ይነሱ በማለት የጠየቁት ዳኝነት መብትና ጥቅም እንዲሁም የክስ ምክንያት እንደሌላቸው፤

    ከሳሾች  ስራ አስኪያጅ እንዲሻር በጠየቁት ዳኝነት ላይ ቀደም ብሎ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 7ኛ ንግድ ችሎት በመ/ቁ 171480 በሆነው ተመሳሳይ የሆነ እና አሁን በቀረበው እና በቀድሞ ክርክር መካከል የተነሳው የስረ ነገር ክርክር እንዲሁም የተያዘው ጭብጥ አንድ አይነት በመሆኑ ከሳሾች የመጨረሻ ውሳኔ ባገኘ ጉዳይ ላይ በድጋሚ የጠየቁት ዳኝነት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 5 መሰረት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የገለፁ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በቃል ክርክር ጊዜ 1ኛተከሳሽ የቀረበውን ክስ ለማየት ስልጣን ያለው የፌ/መ/ደ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

     ከሳሾች በበኩላቸው ለተነሱት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች በሰጡት መልስ 1ኛተከሳሽ 1ኛከሳሽ ከስራ አስኪያጅነት ከተሻሩበት ከየካቲት 21 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ስራ አስኪያጅ መሆናቸውን ይህም በመ/ደንቡ አንቀፅ 9 መሰረት መሆኑን 1ኛተከሳሸ የጠቀሱት መዝገብ በዚህ ክርክር ላይ የሚነሳ አለመሆኑን ዋስትና ለማስያዝም የሚገደዱበት አግባብ እንደሌለ ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ለማየት ስልጣን ያለው መሆኑንና ይህንን መከራከሪያም 1ኛተከሳሽ በፅሁፍ ያላቀረቡት መሆኑን ገልፀው ተከራክረዋል፡፡

     የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ለማየት ስልጣን አለው ወይ? ከሳሾች ክስ ለማቅረብ መብት ወይም ጥቅም እንዲሁም የክስ ምክንያት ያላቸዉ መሆኑን በማረጋገጥ ክስ አቅርበዋል ወይ? የቀረበው ክስስ አስቀድሞ ውሳኔ የተሰጠበት ነው ወይ? የሚሉትን ጭብጦች በመያዝ መዝገቡን መርምሯል፡፡

   በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 37/1 ላይ እንደተመለከተው ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ዉሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን ፍ/ቤቶችም የቀረበላቸውን ክስ ለማየት ስልጣን ያላቸው መሆኑን አለመሆኑን ማረጋገጥ ያለባቸው መሆኑን ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 9/1/፣ 231/1/ለ ፣ 244/2/ሀ ፣ 245/2/ ድንጋጌዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ በተያዘው ጉዳይ ከሳሾች ክስ ያቀረቡት 1ኛተከሳሽ ከማህበሩ ስራ አስኪያጅነታቸው እንዲነሱ ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ሲሆን በዚህ አግባብ የቀረበን ክስ ለማየት ስልጣን ያለው የፌ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት መሆኑን በፌ/ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 14 ስር ተመልክቷል፡፡ 1ኛተከሳሽ ክሱ መቅረብ ያለበት በፌ/መ/ደ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው በማለት ነው መከራከሪያቸውን ያቀረቡት፡፡ ሆኖም የፌ/መ/ደ ፍ/ቤቶች በየክፍለ ከተማው የተቋቋሙት ተደራሽነታቸውን ለማስፋት ሲሆን በአንድ ከተማ ላይ ያሉ ፍ/ቤቶችም የግዛት ስልጣንን በተመለከተ ክርክር ሊቀርብባቸው የሚችልበት የህግ አግባብ የለም፡፡ በዚህም ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለውም በማለት ያቀረቡትን መከራከሪያ ፍ/ቤቱ አልተቀበለውም፡፡  

    በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 33/2 እና 3 እንዲሁም በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 244/2/መ ላይ እንደተመለከተዉ ከሳሽ ክስ ባቀረበበት ነገር (ሀብት) ላይ መብት ወይም ጥቅም ያለዉ መሆኑን ፤ ከተከሳሽ የሚጠይቀዉ መብት ወይም ጥቅም ያለ መሆኑንና የክስ ምክንያት ያለው መሆኑን  በማረጋገጥ ክስ ማቅረብ ያለበት መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን በተያዘው ጉዳይ ከሳሾች ክስ ያቀረቡት 1ኛተከሳሸ ከ2ኛተከሳሽ ስራ አስኪያጅነታቸው እንዲነሱ ሲሆን 1ኛተከሳሽ በበኩላቸው ስራ አስኪያጅ ባለመሆናቸው ከሳሽ ባቀረቡት ክስ ላይ መብትና ጥቅም እንዲሁም የክስ ምክንያት የላቸውም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የአንድ ማህበር ስራ አስኪያጅ ሆኖ በማህበሩ መመስረቻ ጽሑፍ ወይም በማህበርተኞች ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጠ ሠው ማህበርተኞች በአብላጫ ድምጽ ከስራ አስኪያጅነት ስልጣኑ እንዲሻር ሲወስኑ ወይም በፍ/ቤት ውሣኔ አማካኝነት እንደሚሻር በን/ህ/ቁ 527/2/ /5/ የተመለከተ ሲሆን በፍ/ቤት ውሳኔ ስራ አስኪያጅ እንዲሻር ክስ ሊቀርብ የሚችለውም ከሳሽ የሆነው ወገን በቅድሚያ ስራ አስኪያጅ ነው የተባለው ሰው ስራ አሰኪያጅ መሆኑን በማረጋገጥ ክስ ያቀረበ እንደሆነ ነው፡፡ በያዝነው ጉዳይ የግራ ቀኙን ማስረጃዎች ፍ/ቤቱ እንደመረመረው በ2ኛተከሳሽ የመ/ደንብ መሰረት ስራ አስኪያጅ ሆነው የተመረጡት 1ኛከሳሽ የነበሩ ሲሆን 2ኛከሳሽ ደግሞ ምክትል ስራ አስኪያጅ የነበሩ ናቸው፡፡ በሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ/ም በተደረገ የ2ኛተከሳሽ ቃለ ጉባኤም 1ኛተከሳሽ የ2ኛተከሳሽ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙ ሲሆን በፍ/ቤት የመ/ቁ 171480 በሆነው መዝገብ ላይ በነበረ ክርክር በየካቲት 21 ቀን 2011 ዓ/ም በተሰጠ ውሳኔ 1ኛከሳሽ ከስራ አስኪያጅነታቸው ተሽረዋል፡፡ ከሳሾች 1ኛተከሳሽ በየካቲት 21 ቀን 2011 ዓ/ም ፍ/ቤቱ 1ኛከሳሽን ከስራ አስኪያጅነታቸው ከሻራቸው ጊዜ ጀምሮ ስራ አስኪያጅ ሆነው እየሰሩ ነው በማለት የተከራከሩ ቢሆንም ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ መሰረት 1ኛተከሳሽ በጠቅላላ ጉባኤ ስራ አስኪያጅ ሆነው የተመረጡበት ሁኔታ የሌለ ሲሆን ከሳሾች በክሳቸው ላይ እንደገለፁትም ሆነ የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች እንደሚያስረዱት 1ኛተከሳሽ ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ መሰረት በምክትል ስራ አስኪያጅነታቸው ስራቸውን እየሰሩ ያሉ ናቸው፡፡ በዚህም 1ኛተከሳሽ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አለመሆናቸውን ፍ/ቤቱ  የተገነዘበ ሲሆን 1ኛተከሳሽ ስራ አስኪያጅ ባልሆኑበት ሁኔታም ከስራ አስኪያጅነት እንዲነሱ ከሳሾች ያቀረቡት ክስ የክስ ምክንያትም ሆነ የህግ መሰረት የሌለው በመሆኑ ፍ/ቤቱ ክሱን ባለመቀበል ውድቅ አድርጎታል፡፡ 3ኛውን ጭብጥ መመርመር ሳያስፈልግ በዚሁ ታልፏል፡፡

 

ት እ ዛ ዝ

  1. 1ኛተከሳሽ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው ተጠብቋል፡፡
  2. ይግባኝ መብት ነዉ ተብሏል፡፡
  3. መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡