የኮ/መ/ቁ 170468 - እነ ቢም አይቲ ሶሉሽን ኃ/የተ/የግ/ማ እና አቶ በረከት ታደገኝ

የመ/ቁጥር 170468

ቀን 10/4/2012 ዓ/ም

 

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሾች፡- 1. ቢም አይቲ ሶሉሽን ኃ/የተ/የግ/ማ    አልቀረቡም

2. አቶ ሳሙኤል አርከበ

ተከሳሽ፡- አቶ በረከት ታደገኝ ወኪል ማንያህልሻል ንቦ ፡- ቀረቡ

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰቷል፡፡

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነው ከሳሾች የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ.ም አሻሽለው ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም በአጭሩ እንደሚከተለው ነው፡፡

ተከሳሽ እና ከሳሽ በ10/03/2001 ዓ/ም በፈረምነው የመመስረቻ ጽሁፍ ቢም አይቲ ሶሉሽን ኃ/የተ/የግ/ማን አቋቁመናል፤ ማህበሩም የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን የማማከር አገልግሎት እና የመረጃ ቋት ማደራጀትና የማቀናበር ስራዎችን የሚሰራ የንግድ ማህበር ነው፤ ማህበሩንም ከ25/4/2001 ዓ/ም ጀምሮ 2ኛ ከሳሽ እና ተከሳሽ ተስማምተን በጣምራ ሥራ አስኪያጅነት ስንመራ ቆይተናል፡፡ ነገር ግን ተከሳሽ ያለከሳሾች ፈቃድ የ1ኛን ከሳሽ ድህረ ገጾች እንዲስተጓጎል አድርጓል፤ 1ኛ ከሳሽ ማህበር ውል ተዋውሎ የጀመረውን የድህረገጽና የሶፍትዌር ሲስተም ዝግጅት ስራ ሳይጨርስ እንዲቋረጥና የይለፍ ኮዶችን ይዞ በመሰወር ማህበሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል የ1ኛ ከሳሽ ደንበኞች ያለደንበኞቹ ፈቃድ ራሱ አዲስ ወደከፈተው ተመሳሳይ ድርጅት ሰርቨር በማዞር ህግን የሚቃረን ድርጊት ፈጽሟል እንዲሁም የ1ኛ ከሳሽን ገንዘብ አባክኗል፡፡ ተከሳሽ የማህበሩ ጣምራ ሥራ ሰስኪያጅ ሆኖ ሲያገለግል ይጠቀምባቸው የነበሩ የድርጅቱ ንብረቶች ማለትም ግምቱ ብር የሆነ 18,645 /አስራ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ አርባ አምስት ብር / አዲስ ላብቶፕ እና ግምቱ ብር 7130/ሰባት ሺህ አንድ መቶ ሰላሳ ብር/ ያገለገለ ላብቶፕ ተመላሽ አላደረገም እንዲሁም 1ኛ ከሳሽ ማህበር በብድር የወሰደዉን ብር 369,000.00(ሶስት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺህ ) ተመላሽ ሳያደርግ ቀርቷል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሽ የማህበሩ የባንክ አካውንት አንደኛው ፈራሚ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከሀላፊነታቸው የተነሱ ሆኖ እያለ ፈራሚነታቸውን ለሌላ ሰው ለማስተላለፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የማህበሩን ሂሳብ ማንቀሳቀስ አልተቻለም፡፡ይህ የተከሳሽ ድርጊት 1ኛ ከሳሽ ማህበርን ችግር ላይ ጥሏል ለሠራተኞች የሚከፍለውንም ክፍያ እንዲቋረጥባቸው ሆኗል፡፡ ስለሆነም ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር አባልነት እንዲወጣ ድርሻውንም ለ2ኛ ከሳሽ ወይም 2ኛ ከሳሽ ለሚመርጣቸው ግለሰቦች እንዲያስተላልፍ ፤የ1ኛ ከሳሽ ንብረት የሆኑትና በክሱ ላይ የተጠቀሱትን ላብቶፓች ለ1ኛ ከሳሽ እንዲያስረክብ ፤ በብድር የወሰደዉን ብር 369,000/ሦስት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺህ ብር/እንዲከፈል፤የ1ኛ ከሳሽ ማህበርን ሰነዶች በሙሉ እንዲመልስ፤ተከሳሽ ከጣምራ ስራ አስኪያጅነት ስልጣኑ እንዲነሳ የባንክ አካውንት ከማንቀሳቀስ ስልጣኑ እንዲታገድ እና ከባንክ ፈራሚነቱ እንዲነሳ፤ተከሳሽ ጣምራ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሲያገለግል ያወቃቸውን የ1ኛ ከሳሽን ደንበኞችን ራሱ በግሉ ወዳቋቋመው ድህረገጽ/ website/ውስጥ እንዳያስገባ እንዲሁም የይለፍ ቁልፍ/pass word/ መረጃዎች እንዳይጠቀም እንዲከለከል እንዲሁም ተከሳሽ በማህበሩ ላይ የሥራ አስኪያጅ ስልጣኑን አላግባብ በመጠቀም በማህበሩ ላይ ያደረሰውን ጉዳት መጠን ተለይቶ በታወቀ ጊዜ ወደፊት ክስ የማቅረብ መብታቸው እንዲጠበቅላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ከሳሾች ክሱን ያስረዱልኛል ያሏቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ከክሱ ጋር አያይዘዉ አቅርበዋል የሰዉ ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡

ተከሳሽ በከሳሾች የቀረበዉ የክስ አቤቱታ ከነአባሪዎቹ ድርሶት የመከላከያ መልሱን መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ/ም ያቀረበ ሲሆን ባቀረበዉ የመከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መልስ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሽ ያቀረበዉን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ብይን የሰጠበት በመሆኑ ከዚህ ማስፈር ሳያስፈልግ ታልፏል፡፡

ተከሳሽ በፍሬ ነገሩ ላይ የሰጠዉ የመከላከያ መልስ በአጭሩ 1ኛ ከሳሽ በዋነኝነት ገቢ የሚገኘበትን ኢቲዮ ቴንደር የተባለዉ ዌብሳይት ሀሳብ አመንጪ እና ዴቨሎፐር መሆናቸዉን 1ኛ ከሳሽም በዚህ የሰራ ዘርፍ ከፍተኛ ተዋቂነት ማገኘቱን ተከትሎ 1ኛ ከሳሽ ለሚሰጠው አገልግሎት የአገልግሎት ክፍያ ዋጋ ጭማሪ በማደረጋቸዉ ከ2ኛ ከሳሽ ጋር አለመገባባት ዉስጥ የገቡ መሆኑን ይህን አለመግባባት ምክንያት በማድረግ 2ኛ ከሳሽ አንድ ጊዜ በራሱ ስም ሌላ ጊዜ በአንደኛ ከሳሽ ስም እንዲሁም በማህበሩ ጠበቃ አማካኝነት ማቆሚያ የሌለው ማስፈራሪያና ዛቻ በመላኩ ተከሳሽ በፍርሀት እና በመገደድ በማህበሩ ዉስጥ ያለዉን የአክሲዮን ድርሻ በፈቃደኝነት ለመሸጥ ገልጾ የነበረ ቢሆንም በድርድር ሂደት መስማማት ላይ መድረስ ባለመቻላቸዉ ሀሳባቸዉን የቀየሩ መሆኑን፤ከሳሾች በአንድ በኩል ተከሳሽ የጣምራ ሥራ አስኪያጅነቱን በፈቃዱ ትቶ ሄዷል እያሉ በሌላ በኩል ከሥራ አስኪያጅነቱ ሊነሳ ይገባል በሚል ያቀረቡት ክርክር እርስበርሱ የሚጣርስ መሆኑን፤ተከሳሽ ከሥራ አስኪያጅነቱ እንዲነሳ የሚጠይቀውን ክስ ያቀረቡት ማህበሩና የማህበሩ ሌላኛው ሥራ አስኪያጅ እንጂ ባለአክሲዮን ባለመሆኑ በንግድ ሕጉ ቁጥር 527/5/ መሰረት ክሱ ተቀባይነት ሊኖረው የማይገባ መሆኑን በማህበሩ መመስረቻና መተዳደሪያ ደንብ ሁለቱም ባለአክሲዮኖች ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ የተደረገው ለቁጥጥር አላማ በመሆኑ አንደኛው ሥራ አስኪያጅ ብቻዬን ሥራውን ልመራ ይገባል በሚል ሌላኛው ሥራ አስኪያጅ እንዲነሳለት ጥያቄ ሊያቀርብ የማይችል መሆኑን ከሳሾች ተከሳሽ ከሥራ አስኪያጅነቱ እንዲነሳ ላቀረቡት ክስ የሰጡት ምክንያት የሌለ መሆኑን ይህ ደግሞ ከንግድ ሕጉ ቁጥር 527/3/ ውጪ መሆኑን ከሳሾች ተከሳሽ ፈጽሟቸዋል ያሉትን ድርጊቶች መቼ እንዴት እንደተፈጸመ በክሱ ላይ ያልተገለጹ እና በማስረጃ ያላስደገፈ መሆኑን 2ኛ ከሳሽ ተከሳሽ ሥራውን እንዳይሰራ ይከፈለው የነበረውንም ደሞዝ እንዲቆም በማድረጉ ተከሳሽ ተገዶ የመሰረተው ኩባንያ የጨረታ መረጃ ሥራዎች ላይ ያልተሰማራ እና  የመሰማራት ሀሳብ የሌለው በመሆኑ የጥቅም ግጭት የሌለ መሆኑን፤የይለፍ ቃሉን/ pass word/ በተመለከተ 2ኛ ከሳሽ ስለቀየራቸው ተከሳሽ በድህረገፁ/website/ላይ ለመጠቀም የሚችልበት ሁኔታ የሌለ መሆኑን፤1ኛ ከሳሽ ጥሬ ገንዘብን በተመለከተ ያቀረበው ክስ የትርፍ ክፍፍል በአግባቡና በስርዓቱ ተከናውኖ የማያውቅ ስለሆነ በማህበሩ መመስረቻና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የትርፍ ክፍፍል እስኪካሄድ ድረስ ባለአክሲዮኖች ከትርፍ ላይ የሚታሰብ ገንዘብ እንዲወስዱ ሁለቱም ባለአክሲዮኖች ባደረጉት ስምምነት የወሰዱት ገንዘብ እንጂ የብድር ገንዘብ አለመሆኑን ብድር ተብሎ የተመዘገበዉም ለሂሳብ አያያዝ ተብሎ መሆኑን፤ብር 230,000/ሁለት መቶ ሠላሣ ሺህ ብር/የወሰዱትም ከማህበሩ ትርፍ ታሳቢ የሚደረግ መሆኑን፤ላብቶፖቹ ተከሳሽ ባለአክሲዮን በመሆኑ ለግል አግልግሎት እንዲጠቀምባቸው ተገዝተው የተሰጡት ንብረት እንጂ ተመላሽ የሚሆኑ አለመሆናቸዉን፤የማህበሩ 50/100 ባለድርሻ በመሆናቸዉ የባንክ አካውንት የማንቀሳቀስ ወይም ፈራሚነት ሥራውን ሊያቆሙ የማይገባ መሆኑን የ1ኛ ከሳሽ ምንም ሰነድ በእጃቸዉ የሌለ መሆኑን  ገልጸዉ የከሳሾች ክስ ውድቅ እንዲደረግ ዳኝነት ጠይቋል፡፡

ተከሳሽ ክሱን ይከላከልልኛል ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎች ከመልሱ ጋር አይይዞ አቅርቧል የሰዉ ምስክሮች ቆጥሯል፡፡

ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሾች ባቀረቡት ክርክር የንግድ ህጉ አንቀጽ 261 እና 279 ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ ተፈጻሚነት ያላቸዉ ድንጋጌዎች በመሆናቸዉ ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር አባልነት ሊሰናበት የሚገባ መሆኑን የማህበሩን ሒሣብ ማንቀሳቀስ ያልተቻለ በመሆኑ፤2ኛ ከሳሽ እና ተከሳሽ አብረዉ መስራት የማይችሉ በመሆኑ፤ተከሳሽ ተመሳሳይ ድርጅት ከፍተዉ ከ1ኛ ከሳሽ ጋር የጥቅም ግጭት የፈጠሩ በመሆኑ፤1ኛ ከሳሽ የሚሰራዉን ስራ በድብቅ ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ ሲሰራ የነበረ በመሆኑ የ1ኛ ከሳሽን ደንበኞች እራሳቸዉ ወደ አቋቋሙት ድርጅት በመውሰዳቸዉን የ1ኛ ከሳሽ ማህብር ደንበኞች መረጃ ከሰርቨር ላይ እንዲጠፋ ያደረጉ በመሆኑ፤የማህበሩንም ፓስወርድ በመደበቅ ድንበኞች እንዲሻሹ ያደረገ በመሆኑ ተከሳሽ ከጣምራ ስራ እኪያጅነት ሊሻሩ የሚገባ መሆኑን በመግልጽ ክሳቸዉን አጠናክረዉ ሲከራክሩ ተከሳሽ በበኩላቸዉ 2ኛ ከሳሽ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር ወጪ ያደረጉት ክፍተኛ ገንዘብ እንዳይታወቅባቸዉ በማሰብ መሆኑን፤ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህብር አባል የሆነ ሌላኛዉ አባል ከማህበሩ እንዲወጣለት ክስ ማቅርብ የማይችል መሆኑን የንግድ ህጉ አንቀጽ 261 እና 279 ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ ተፈጻሚነት የሌላቸዉ መሆኑን እነዚህ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት አላቸዉ ቢባል ሊተገበሩ የሚችሉት ማህበር ይፈረስ በሚል የተጠየቀ ዳኝነት ሲኖር መሆኑን ነገር ግን ማህበር ይፈረስ የሚል ዳኝነት በዚህ መዝገብ ያልተጠየቀ መሆኑን፤በማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍም ሆነ በመተዳደሪያ ደንቡ አንድ አባል ተገዶ ሊወጣ የሚገባበት አግባብ ያልተቀመጠ መሆኑን ከ2ኛ ከሳሽ ጋር የጋራ ሥራ አስኪያጅ ሆነዉ የተሰየሙ በመሆኑ ከሥራ አስኪጅነት ከተሻሩ ሁለቱም ሊሻሩ የሚገባ መሆኑን የ1ኛ ከሳሽ ዌብሳይት የተፈጠረዉ በተከሳሽ መሆኑን፤ድርጅት ያቋቋሙት ሥራ ከአቆሙ ከአንድ ዓመት በኃላ መሆኑን ይህ የተቋቋመዉ ድርጅትም የኢትዮ ቴንደር ሥራ የማይሰራ መሆኑን የሚሰራዉም የዌብሳይ ዴቨሎፕመንት መሆኑን ድርጅቱም የተዘጋ መሆኑን የሰበሰበዉ ብር 3,000.00(ሦስት ሺህ ብር) መሆኑን ይህም ገንዘብ ለባለጉዳዩ ለቢታኒያ ኃ/የተወ/የግል ማህበር ተመላሽ የተደረገ መሆኑን  በመገልጽ  የመከላከያ መልሳቸዉን በማጠናክር ክርክራቸዉን አቅርቧል፡፡

የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ቀጠሎ የተመለከቱትን ጭብጦች በመያዝ መዝገቡን እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡

1ኛ)  ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር ሊወጣ ይገባል ወይስ አይገባም?

2ኛ) ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህብር የጣምራ ስራ አስኪያጅነት ሊሻር ይገባል ወይስ አይገባም?

3ኛ) ተከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀሱትን ላፕቶፖች ለ1ኛ ከሳሽ ሊያስረክብ ይገባል ወይስ አይገባም?

4ኛ) ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ማህበርን ሰነዶች ሊያስረክቡ ይገባል ወይስ አይገባም?

5ኛ) ተከሳሽ ከ1ኛ ተከሳሽ ማህበር በበድር ወሰደዋል የተባለዉን ብር 369,000.00(ሶስት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺህ) ለ1ኛ ከሳሽ ሊክፍሉ ይገባል ወይስ አይገባም?

6ኛ) ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ማህበርን የባንክ ሂሰብ እንዳያንቀሳቀስ ሊከለከል ይገባል ወይስ አይገባም እንዲሁም ተከሳሽ ከባንክ ፈራሚነት ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም?

7ኛ) ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሲያገለግል ያወቃቸዉን የ1ኛ ከሳሽ ድህረ ገጽ ዉስጥ አንዳይገባ፤የይለፍ ቁጥሩን እና መረጃዎችን አንዳይጠቀም ሊከለከል ይገባል ወይስ አይገባም?

8ኛ) ተከሳሽ ያደረሰዉ ጉደት መጠን በተመለከተ ለከሳሾች ወደፊት ክስ የማቅርብ መብታቸዉ ሊጠበቅ ይገባል ወይስ አይገባም?

የመጀመሪያዉን ነጥብ በተመለከተ 1ኛ ተከሳሽ ማህበር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን ይህን ማህበር የሚገዛዉ የንግድ ህጉ ክፍል ከአንቀጽ 510-543 ስር የተገለጹት ድንጋጌዎች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ደንጋጌዎች ደግሞ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አባል የሆነ ሰዉ ከማህበሩ ሊሰናበት የሚችልበትን አግባብ አያስቀምጡም፡፡በርግጥ ሃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር የሽርክና ማህበር እና የአክሲዮን ማህበራት የተቀላቀለ ባህሪ ያለዉ ማህበር መሆኑን ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል፡፡

በሽርክና ማህበራት ዉስጥ የአባሉቱ ማንነት እና ባህሪ (personality of members) ለማህበሩ ቀጣይነት ዋሳኝ ነዉ ይህም የሆነዉ የሽርክና ማህበራት የሰዎች ስብስብ (association of persons) ስለሆነ ሲሆን የአክሲዮን ማህበር ዉስጥ ደግሞ የአባላቱ ማንንትም ሆነ ባህሪ ለማህበሩ ቀጣይነት ጠቃሚ አይደለም ይህም የሆነበት ምክንያት የአክሲዮን ማህበራት የካፒታል ስብስብ(association of capital) በመሆናቸዉ ነዉ፡፡ ከዚህ አንጻር ተከሳሽ ከማህበሩ ሊሰናበት ይገባል ወይስ አይገባም የሚለዉን ነጥብ ሃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማህበር ያለዉን የተቀላቀለ ባህሪ መሰረት በማድረግ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

ከሳሾች ተከሳሽ ከማህበሩ እንዲሰናበት መሰረት አድርገዉ የሚከራክሩት የንግድ ህጉን አንቀጽ 261 እና 279 ሲሆን እነዚህም ድንጋጌዎች እንደየቅደመተከተላቸዉ የሚገኙት በንግድ ህጉ ስለ ተራ ሽርክና እና ስለ እሽሙር ማህበር  በሚደነግገዉ የህግ  ክፍል ነዉ፡፡ የነዚህንም ድንጋጌዎች ይዘት ስንመለከተ ፍርድ ቤት በቂ ምክንያት ሲኖር እንዱን ማህበርተኛ ከማህበሩ እንዲወጣ ሊፈርድ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡እነዚህ ድንጋጌዎችም የሚገኙት ስለ ተራ የሽርክና ማህበር እና ስለ እሽሙር ማህበር በሚደነግገዉ የህግ ክፍል እንደመሆኑ መጠን እና ስለ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚደነግገዉ የንግድ ህጉ ክፍል ተጠቃሾቹ ድንጌዎች አገልግሎት ላይ ሊውል እንደሚችል የተመለከተ ገልጽ ነገር ባለመኖሩ ደንጋጌዉ በሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ ተፈጻሚነት የሌለዉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡በመሆኑም በንግድ ህጉ አንቀጽ 261 የተራ ሽርክና ማህብርተኞችን እና በአንቀጽ 279(1) ላይ የእሽሙር የሽርክና ማህበር አባልን በፍርድ ቤት ከሽርክና ማህበር እንዲወጣ ለመወሰን የሚያስችል በግልጽ ተደንግጎ እያለ ስለ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አባልን ፍርድ ቤት ከአባልነት እንዲሰርዝ ለመወሰን እንደሚቻል ያለመደነገጉ ተጠቃሾቹ ደንጋጌዎች በሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ ተፈጻሚነት የሌላቸዉ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በ1ኛ ከሳሽ ማህበር የመመሰረቻ ጽሁፍም ሆነ የመተዳደሪያ ደንብ የማህበሩ አባል ከማህበሩ አባል ሊሰናበት የሚችልበትን አግባብ አልተቀመጠም፡፡ እንዲሁም ተራ የሽርክና ማህበር በንግድ ህጉ አንቀጽ 5 ስር በተዘረዘሩት የንግድ ስራዎች ላይ መሳተፍ እንደማይችል እንዲሁም ተራ የሽርክና ማህበር የንግድ ማህበራት ባህሪ የሌለዉ መሆኑን ከንግድ ህጉ አንቀጽ 213 እና 227 መረዳት የሚቻል ሲሆን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዓላማዉ ምንም ቢሆን የንግድ ማህበር መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 10(2) ስር የተቀመጠ በመሆኑ እና ሁሌም የንግድ ስራ የሚስራ  ከመሆኑ አንጻር እና ተራ የሽርክና ማህበር እንደ ንግድ ድርጅት የማይቆጠረ ከመሆኑ አንጻር በተራ የሽርክና ማህበር ስር የተደነገገን ደንጋጌ አመሳሰሎ(analogy) በግልጽ የንግድ ማህበር መሆኑ የተቀመጠ የንግድ ማህበር ላይ ተፈጻሚ ማድረግ አግባብነት የለዉም፡፡ ስለሆነም ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር ሊሰናበት የሚችልበት የህግ አግባብ የሌለ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የከሳሾች በዚህ ረገድ የጠየቁትን ዳኝነት ውድቅ አድርጓል፡፡

2ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ኃ/የተ/ግ/ማህበር በአንድ ወይም ብዙ ሥራ አስኪያጆች ሊተዳደር አንደሚችል እንዲሁም ሥራ አስኪያጅ ከማህበሩ አባላት ወይም ከማኅበረተኞች ውጭ ሊምረጥ እንደሚችሉ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 525 እና 526 ይደነግጋል፡፡ አሁን በተያዘው ጉዳይ ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ማህበር ጣምራ ስራ አስኪያጅ ሆነዉ የተሰየሙ መሆኑን ማህበሩ ህዳር 13 ቀን 2001 ዓ/ም የያዘዉ ቃለ ጉባኤ ያስረዳል፡፡ይህ ቃለ ጉባኤም የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ አካል እንደሆነ በቃለ ጉባኤዉ ላይ ተመልክቷል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ተከሳሽ በማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ የጣምራ ስራ አስኪያጅ ሆነዉ የተሾሙ መሆኑን መገንዘብ የሚቻል ሲሆን በማህበሩ የመመስረቻ ጽሁፍ የተሾመ ሥራ አስኪያጅ  ከሥራ አስኪያጅ ስልጣኑ ሊሻር የሚችለዉ በንግድ ህጉ 527(1) እና 536(2) መሰረት ከማህበሩ ባለአክሲዮኖች መካከል በሶስተኛ አራተኛ ድምጽ ባላቸዉ ባለአክሲዮኖች ሲደገፍ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህ ድንጋጌም ተፈጻሚነት ያለዉ የማህበሩን ሥራ አስኪያጅ በጠቅላላ ጉባኤ ለመሻር በቀረበ ጊዜ ሲሆን በሌላ በኩል እንድ ስራ አስኪያጅ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ የተሾመ ቢሆንም ስራ አስኪያጁ ከስልጣኑ እንዲነሳ ሊያደረጉ የሚችሉ ጥፋቶች እስካሉ የማህበሩ አባላት ስራ አስኪያጁ በፍርድ ቤት ዉሳኔ እንዲሻር መጠየቅ እንደሚቻሉ በንግድ ህጉ አንቀጽ 527(5) ተመልክቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ የማህበሩን ሥራ አስኪያጅ ከሥራ አስኪያጅነት ለማንሳት የሚስችሉ ጥፋቶችን በዝርዝር አለስቀመጠም፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ ደግሞ አንድ የማህበር ስራ አስኪያጅ በህግ ፤በማህበሩ የመመስረቻ ጽሁፍ እንዲሁም መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ግዴታዉን ካልተወጣ ጥፋት እንደፈጸመ የሚቆጠር መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ከሳሾች ተከሳሽ ከጣምራ ስራ አስኪያጅነቱ ሊሻር ይገባል በማለት በዋንኝነት የሚከራክሩት ተከሳሽ ያለከሳሾች ፈቃድ የ1ኛን ከሳሽ ድህረ ገጾች እንዲስተጓጎል አድርጓል፤1ኛ ከሳሽ ማህበር ውል ተዋውሎ የጀመረውን የድህረገጽና የሶፍትዌር ሲስተም ዝግጅት ስራ ሳይጨርስ እንዲቋረጥና የይለፍ ኮዶችን(Password) ይዞ በመሰወር ማህበሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል በማለት ሲሆን ተከሳሽ ይህን ድርጊት ስለመፈጸሙ በበቂ ማስረጃ አላስረዱም፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ከሳሾች ይህን ምክንያት በመጠቀስ ተከሳሽ ከጣምራ ስራ አስኪያጅነቱ ሊነሳ ይገባል በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም፡፡ሌላዉ ከሳሾች ተከሳሽ ከጣምራ ሥራ አስኪያጅነቱ ሊሻር ይገባል በማለት ያቀረቡት ምክንያት ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ደንበኞች ያለደንበኞቹ ፈቃድ ራሱ አዲስ ወደከፈተው ተመሳሳይ ድርጅት ሰርቨር በማዞር ህግን የሚቃረን ድርጊት ፈጽሟል በማለት ነዉ፡፡

የሥራ አስኪያጅ መብቶችና ግዴታዎች ሰለ ውክልና በተወሰኑት ደንጋጌዎች መሰረት የሚመራ መሆኑን አግባብነት ካላቸዉ የንግድ ህጉ ድንጋጌዎች ማለትም ከአንቀጽ 33፤289፤292፤355 እና 364 መረዳት የሚቻል ሲሆን እነዚህ ድንጋጌዎች በማመሳሰል(by analogy) ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ ተፈጻሚነት ያላቸዉ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ከዚህ አንጻር አንድ የማህበር ስራ አስኪያጅ የሆነ ግለሰብ ለማህበሩ በቅን ልቦና ስራዉን መሰራት ያለበት መሆኑን እንዲሁም የጥቅም ግጭት ማሰወገድ ያለበት መሆኑን ከላይ ከተጠቀሱት የንግድ ህግ ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻል ከመሆኑም በላይ ከፍ/ሕ/ቁ 2208 እና 2209 መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተያዘዉ ጉዳይ ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ማህበር ጣምራ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሳለ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር ጋር ተመሳሳይ ሥራ የሚሰራ ቢቲኤ ቴክኖሎጂ የተባለ ማህበር መሰርቶ ሲሰራ የነበረ መሆኑን ተከሳሽ እራሱም ካለመካዱም በላይ በከሳሾች በኩል የቀረቡት ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ይህም የተከሳሽ ተግባር በንግድ ህጉ አንቀጽ 292፤355 እና 364 እንዲሁም በፍ/ሕ/ቁ 2208 እና 2209 የተጣለበትን ህጋዊ ግዴታ የጣሰ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ደንበኛ የሆነዉን ቢቲኒያ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ኃ/የተ.የግል ማህበርን ድረ ገጽ እራሱ  ወደ መሰረተዉ ቢቲኤ ቴክኖሎጂ ያዛወረ በመሆኑ ቢታኒያ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ከ1ኛ ከሳሽ ሲያገኝ የነበረዉ አገልግሎት የተቋረጠ መሆኑን፤ኢሜሎችን በአገባቡ መከታተል እና መመለስ ያልቻለ መሆኑን ድረገጹም ተከሳሽ ወደ መሰረተዉ ማህበር የተዛወረዉ ያለ ፈቃዳኛዉ መሆኑን ገለጸዉ ይህም እንዲሰተካከልላቸዉ 1ኛ ከሳሽን የጠየቁ መሆኑን የቀረበዉ ማስረጃ ያስረዳል እንዲሁም ተከሳሽ 1ኛ ከሳሽ የሚሰጠዉን አገልግሎት ማለትም የዌብሳይት ሆስቲንግ አገልግሎት በመስጠት ከላይ ከተገለጸዉ የ1ኛ ከሳሽ ደንበኛ ብር 3,000.00(ሦስት ሺህ ብር) የተቀበለ መሆኑን በማስረጃነት የቀረበዉ ደረሰኝ ያስረዳል ተከሳሽ ይህን የገንዘብ መጠን ተመላሽ ያደረገ መሆኑን በመግለጽ ክርክር ያቀረበ ቢሆንም እራሱ በሰጠዉ የምስክርነት ቃል ገንዘቡን ተመላሽ ያለደረገ መሆኑን መስክሯል እንዲሁም ተከሳሽ ማህበሩ አገልግሎት በመስጠት የሰበሰበዉን ገንዘብ ወደ ማህበሩ ሂሳብ ገቢ ሳያደርጉ ስራቸዉን ጥለዉ የሄዱ መሆኑን ተከሳሽ ካለመካዳቸዉም በላይ የከሳሾች ምስክሮች አስረድቷል፡፡ከላይ ከቀረቡት ማስረጃዎችም ተከሳሽ ጣምራ ስራ አስኪያጅ ሆነዉ ሳለ ከ1ኛ ከሰሽ ማህበር ጋር የጥቅም ግጭት የፈጠሩ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ደምድሟል፡፡ በሌላ በኩል ተከሳሽ የመሰረተዉን ቢቲኤ ቴክኖሎጂ የተባለዉን ማህበር ክሱ ከቀረበ በኃላ  ሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ/ም ከንግድ መዝገባ የተሰረዘ ቢሆንም ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር ጣምራ ስራ አስኪያጅ ሆነዉ የጥቅም ግጭት የፈጠሩ መሆኑን የሚያስቀር አይደለም እንዲሁም ተከሳሽ የመሰረትኩት ማህበር 1ኛ ከሳሽ ማህበር ከሚሰራዉ ሥራ ጋር የሚገናኛ አይደለም በማለት ያቀረቡት ክርክር ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር መመሰረቻ ጽሁፍ ለመመልከት እንደሚቻለዉም ሆነ 1ኛ ከሳሽ በተግባር የሚሰረዉ ሥራ በምስክሮች ከተረጋገጠዉ አንጻር እንዲሁም ተከሳሽ ለመሥራት በኢንተርኔተ ሲያሰተዋውቃቸዉ የነበሩት ስራዎች በ1ኛ ከሳሽ የሚሰሩ ሥራዎች ናቸዉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሽ ጣመራ ሥራ አስኪያጅ ሆነዉ የተሾሙት ለቁጥጥር መሆኑን በመገልጽ ክርክር አቅርቧል፡፡ለአንድ ማህበር ጣምራ ሥራ አስኪያጅ የሚሾመዉ በአብዛኛዉ ለቁጥጥር ዓለማ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ይገነዘባል ይሁን እንጂ ከጣምራ ሥራ አስኪጆቹ መካከል 1ኛዉ ጣምራ ሥራ አስኪያጅ በህግ የተጣለበትን ግዴታ ያልተወጣ እንደሆነ ከሥራ አስኪጅነት እንዳይሻር የሚያስቀር አይደለም እንዲሁም ሌላኛዉ ጣምራ ሥራ አስኪያጅ የማህበሩ አባል እስከሆነ ድረስ ጥፋት ፈጸሚዉ ሥራ አስኪያጅ ከስራ አስኪያጅነቱ እንዲሻር የመጠየቅ መብቱን የሚያስቀር አይደለም፡፡በመሆኑም ተከሳሽ 2ኛ ከሳሽ ጣምራ ሥራ አስኪያጅ ስለሆነ ከጣምራ ሥራ አስኪያጅነት እንዲሻር ዳኝነት ሊጠይቅ አይገባም በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም፡፡ ተከሳሽ 1ኛ ከሳሽ ወኪል እንደ መሆናቸው ለማህበሩ  ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ተግባር መፈጸም ብቻ ሲገባቸው ነገር ግን ተከሳሽ ከዚህ በተቃራኒ ማህበሩን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ሲፈጽሙ እንደ ነበር ከቀረበው ማስረጃ መመልከት ይቻላል፡፡ስለሆነም ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር የጣምራ ሥራ አስኪያጅነት ሊሻር ይገባል በማለት ፍርድ ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ይሁን እንጂ የማህበር ሥራ አስኪያጆች እንደ ማህበሩ ወኪል የሚቆጠሩ መሆኑን የንግድ ህጉ አንቀጽ 33 የሚደነግግ በመሆኑ፤የንግድ ህጉ ከአንድ በላይ የሆኑ ሥራ አስኪያጆች ማህበሩን የሚመሩ እና የተሰጣቸዉም ስልጣን በጋራ አንድ አይነት ጉዳይ ለመከናወን እንዲችሉ ከሆነ የአንዱ ሥራ አስኪያጅ ከሥራ አሰኪያጅነት መሻር ያላዉን ዉጤት የማያሰቀምጥ ስለሆነ  በንግድ ህጉ አንቀጽ 1 በተደነገገዉ መሰረት የፍ/ህ/ቁ 2231ን መጠቀም አሰፈላጊ ነዉ፡፡ከዚህ አንጻር ተከሳሽ እና 2ኛ ከሳሽ የማህበሩን የባንክ ሂሳብ በጋራ ለመከፈት፤ለማንቀሳቀስ፤ለመዘጋት የማህበሩን ንብረት በዋስትና ለማሲያዝ ከባንክም ሆነ ከድርጅት ገንዘብ በብድር ለመውሰድ  በጣምራ እንዲሰሩ የተሰየሙ መሆኑን ማህበሩ ታህሳስ 10 ቀን 2001 ዓ/ም እና ህዳር 13 ቀን 2001 ዓ/ም ከያዘዉ ቃለ ጉባኤ መረዳት የሚቻል ሲሆን በፍ/ሕ/ቁ 2231(1) ድግሞ ከአንድ በላይ የሆኑ ተወካዮች ተመሳሳይ ጉዳይ በጋራ እንዲያከናውኑ ስልጣን ተሰጥቷቸዉ እያለ አንደኛዉ የተሰጠዉን ስልጣን መከናወን እንዳይችል ከተደረገ ለሌላኛዉም ወኪል የተሰጠዉ ስልጣን ቀሪ እንዲሆን የተመለከተ ስለሆነ ተከሳሽ ከጣምራ ሥራ አስኪያጅነቱ በመሻሩ 2ኛ ከሳሽ ከተከሳሽ ጋር በጣምራ የተሰጠዉን ስልጣን ለብቻዉ ለማከናወን አያስችለዉም፡፡

3ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀሱትን አዲስ ላፕቶፕ ግምቱ ብር 18,645 (አስራ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ አርባ አምስት) የሆነ እና ግምቱ ብር 7,130 የሆነ ያገለገለ ላፕቶፕ) ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር የወሰደ መሆኑን አልካደም ተከሳሽ ያቀረቡት ክርክር ቢኖር ላፕቶፖቹ ከማህበሩ የተሰጡኝ ለግል አገልግሎት ነዉ በማለት የተከራከሩ ቢሆንም ይህን በማስረጃ አላረጋገጡም ከማህበሩ የጣምራ ሥራ አሰኪያጅነትም ስልጣን እንዲሻር የተወሰነ ስለሆነ እነዚህን ንብረቶች የማያስረክበበበት ህጋዊ ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ በክሱ ላይ የተጠቀሱትን ላፕቶፖች በአይነት እንዲያስረክብ ወይንም ግምታቸዉን እንዲከፍል ተወስኗል፡፡

4ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ከሳሾች ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ማህበር ሰነዶችን እንዲያስረክበን ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት የጠየቁ ቢሆንም በተከሳሽ እጅ የሚገኙት ሰነዶች ምን ምን እንደሆኑ ያቀረቡት ዝርዝር የለም እንዲሁም የ1ኛ ከሳሽ ማህበር ሰነዶች በተከሳሽ እጅ የሚገኙ ስለመሆኑም በማስረጃ አላረጋገጡም፡፡ ስለሆነም ከሳሾች በዚህ ረገድም ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም፡፡

5ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር በብድር ብር 369,000.00(ሶስትመቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺህ ብር) ወስዷል በመሆኑም ይህን የበድር ገንዘብ ተመላሽ ያላደረገ ስለሆነ ተመላሽ እንዲያደርግልን ይወሰንልን በማለት ጠይቋል፡፡ ተከሳሽ በበኩሉ ከ1ኛ ከሳሽ የተበደሩት የብድር ገንዘብ የሌለ መሆኑን ከ1ኛ ከሳሽ የወሰዱት ገንዘብም በብድር ተብሎ የተመዘገበዉ ለሂሳብ አያየዝ እንዲያመች ተብሎ ከሚደረሳቸዉ የትርፍ ክፍያ ላይ የተከፈላቸዉ ክፍያ መሆኑን ገልጸዉ ክርክራቸዉን አቅርቧል፡፡        

በፍ/ህ/ቁ 2472 እንደተደነገገዉ በብድር የተሰጠዉ ገንዘብ ከ500 የኢትዮጵያ ብር በላይ ሲሆን የብደሩን ውል በጽሁፍ ወይም በፍርድ ቤት በተደረገ የእምነት ቃል ወይም መሐላ ካልሆነ በቀር ለማስረዳት እንደማይቻል እንዲሁም ለብድር ውል ማናኛቸዉም ሌላ አይነት ማስረጃ ለማቅርብ እንደማይቻል ተመልክቷል፡፡ከዚህ አንጻር የተያዘዉን ጉዳይ ስንመለከተ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር የብድር ውል ያለዉ ስለመሆኑ ክዶ የተከራከረ ከመሆኑ አንጻር ከሳሽ ከተከሳሽ ጋር የብድር ውል ግኑኝነት ያለዉ ስለመሆኑ የማስረዳት ሸክም አለበት፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ የጠየቀዉ ከብር 500 ብር(አምስት መቶ ብር) በላይ የብድር ገንዘብ ስለሆነ ከተከሳሽ ጋር የፈጸመዉን የብድር ውል ከላይ በተጠቀወሰዉ ድንጋጌ መሰረት በማስረጃነት ሊቀርብ ይገባል፡፡ይሁን እንጂ ከሳሽ በማስረጃነት ያቀረበዉ በቀን 4/12/2007 ዓ/ም የገንዘብ መከፈያ በሚል ሰነድ ላይ የተከፈለበት ምክንያት የባለአከሲዮን ብድር በሚል ተከሳሽ ብር 24,000.00(ሃያ አራት ሺህ ብር) የተከፈለዉ መሆኑን የሚገለጽ፤በቀን 26/7/2008 ዓ/ም የጥሬ ገንዘብ ደረሰኝ በሚል ብር 40,000.00(አርባ ሺህ ብር) ለባለአክሲዮን ብድር ተብሎ ለተከሳሽ የተከፈለበትን ደረሰኝ፤በቀን 7/6/2008 ዓ/ም ብር 75,000(ሰባ አምስት ሺህ ብር) ብድር በሚል ለተከሳሽ የተከፈለበትን ደረሰኝ እንዲሁም በቀን 10/1/2009 ዓ/ም ለተያዥ ዲቪደንድ በሚል ለተከሳሽ ብር 230,755(ሁለት መቶ ሰላሳ ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ አምስት) የተከፈለበተን ደረሰኝ ነዉ፡፡እነዚህ ማስረጃዎች ድግሞ በከሳሽ እና በተከሳሽ መካከል የብድር ውል ግኑኝነት ስለመኖሩ እንዲሁም የብድር ውል ሰለመኖሩ አያስረዱም፡፡በመሆኑም 1ኛ ከሳሽ ተከሳሽ በብድር የወሰደዉን ብር 369,000.00(ሶስት መቶ ስልሳ ዘጠን ሺህ ብር) እንዲወሰንልኝ በማለት ያቀረቡት ክርክር አግባብነት ባለዉ(የብድር ውል) ማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡

6ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር የጋራ ሥራ አስኪያጅነት እንዲሻሩ በተራ ቁጥር 1 በተያዘዉ ጭብጥ የተወሰነ ስለሆነ ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽን የባንክ ሂሳብ እንዳያንቀሳቅሱ እንዲሁም ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር የባንከ ፈራሚነት እንዲነሱ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡

7ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር የጣምራ ሥራ አስኪያጅነት የተሻረ ሰለሆነ እና የ1ኛ ከሳሽ ማህበርን ዌብሳይት የሚገባበት ህጋዊ ምክንያት ስለሌለ ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ማህበር ዌብሳይት ዉስጥ እንዳይገባ፤የይለፍ ቁጥር እና መረጃዎችን እንዳይጠቀም ተብሎ ተወስኗል፡፡

ዉሳኔ

1ኛ) ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር ሊሰናበት የሚችልበት የህግ አግባብ የለም ተብሎ ተወሰኗል፡፡

2ኛ) ተከሳሽ ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር የጣምራ ሥራ አስኪያጅነት ሊሻር ይገባል ተብሏል፡፡

3ኛ) ተከሳሽ አዲስ ላፕቶፕ ግምቱ ብር 18,645 (አስራ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ አርባ አምስት) የሆነ እና ግምቱ ብር 7,130 የሆነ ያገለገለ ላፕቶፕ ለ1ኛ ከሳሽ ማህበር በአይነት ያስረከክብ ወይንም ግምቱን ይክፈል ተብሏል፡፡

4ኛ) ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽ ማህበር ዌብሳይት ዉስጥ እንዳይገባ፤የይለፍ ቁጥር እና መረጃዎችን እንዳይጠቀም ተብሎ ተወስኗል፡፡

5ኛ) ተከሳሽ የ1ኛ ከሳሽን የባንክ ሂሳብ እንዳያንቀሳቅሱ እንዲሁም ከ1ኛ ከሳሽ ማህበር የባንከ ፈራሚነት እንዲነሱ ተወስኗል፡፡

6ኛ) ከሳሾች በከሳሽ ጥፋት የደረሰባቸዉ ጉዳት ካለ ወደፊት ክስ አቅርበዉ የመጠየቅ መብታቸዉ ተጠብቋል፡፡

7ኛ) ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ፡፡

 

ትዕዛዝ

ይግባኝ ለጠየቀ ገልባጭ ይሰጥ፡፡

መዝገቡ ተዘግቷል ይመለስ፡፡

Read 2701 times