የኮ/መ/ቁ 178843 - ብሩክ ሳህሉ እና ኤርዝ ዋርክ ጂኦቴክ ኃ/የተ/የግል/ማህበር

 

የኮ/መ/ቁ 178843

ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ/ም

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ

ከሳሽ፡- ብሩክ ሳህሉ ከጠበቃ ስራብዙ ሲራክ ጋር ቀረቡ

ተከሳሽ ፡- ኤርዝ ዋርክ ጂኦቴክ ኃ/የተ/የግል/ማህበር ጠበቃ አሸናፊ ሀይሌ ቀረቡ  

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ  ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ ጥቅምት 28 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ተከሳሽ ኩባንያ በ16/01/2010 ዓ/ም በደብዳቤ ቁጥር EWG/01/270/17 ብር 135,000 የያዘ የቃል ኪዳን ሰነድ የሰጧቸዉ መሆኑን በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ የተመለከተዉን የገንዘብ መጠን በሶስት ወር ጊዜ ዉስጥ ለመክፈል ግዴታ የገቡ መሆኑን ይሁን እንጂ ተከሳሽ ላለፉት ሁለት አመታት ገንዘቡን ሳይከፍላቸዉ የቀረ መሆኑን ገልጸዉ ተከሳሽ ገንዘቡ መከፈል ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ከሚታስብ ህጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡ በማስረጃነትም ሰነዱን አያይዘዉ አቅቧል፡፡፡

ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ከነ አባሪዎቹ ለተከሳሽ ድርሶ ተከሳሽ ህዳር 20 ቀን 2011 ዓ/ም በተጻፈ የመከላከያ ማስፈቀጃ ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ ያቀረበዉን የመከላከያ ማስፈቀጃ ከመረመረ በኃላ ህዳር 21 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ተከሳሽ ክሱን እንዲከላከል ፈቅዷል፡፡ በዚህም መሰረት ተከሳሽ በቀን 09/4/11ዓ/ም በተጻፈ የመካለከያ መልስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መልስ የሰጠ ሲሆን ተከሳሽ ያቀረበዉን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ጥር 23 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ወድቅ ያደረገዉ ስለሆነ ከዚህ ማስፈር ሳያስፈልግ ታልፏል፡፡

ተከሳሽ በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት የመከላከያ መልስ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን የመተማመኛ ሰነድ ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠዉ የማህበሩ ተወካይ የተሰጠዉ ውክልና ጠቅላላ ውክልና መሆኑን የመተማመኛ ሰነዱ እንደ የሚተላለፉ ሰነዶች የሚቆጠር በመሆኑ ሰነዱን ለመፈርም ልዩ ውክልና የሚያስፈልግ መሆኑን የዕዳ አለብኝ ሰነዱን ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠዉ ግለሰብ ተራ የድርጅቱ ተወካይ ወይም ጉዳይ አስፈጻሚ መሆኑን ግለሰቡም በደርጅቱ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ስልጣን የተሰጠዉ ዳሬከክተር አለመሆኑን ተከሳሽ ስልጣን ባልተሰጠ ሰዉ የሚገደድበት ህጋዊ ምክንያት የሌለ መሆኑን፤ተከሳሽ ከሳሽ ስራ የሰራ መሆኑን የማያውቅ መሆኑን እንዲሁም ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር የገባዉ ውል የሌለ መሆኑን በመግለጽ የመከላከያ መልሱን አቀርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱም የካቲት 11 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ሰነድ የፈረሙት ህጋዊ የተከሳሽ ስራ አስኪያጅ መሆናቸዉን የመተማመኛ ሰነዱን የፈረመዉም ግለሰብ በዬትኛዉም መስሪያ ቤት ቀርቦ ውል ለመዋዋል የሚያስችለዉ ውክልና የተሰጠዉ መሆኑን እንዲሁም ክፍያዎችን እንዲፈጽም በተከሳሽ ውክልና የተሰጠዉ መሆኑን ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን የመተማመኛ ሰነድ ግለሰቡ መፈረም የሚችሉ መሆኑን ገልጸዉ ሲከራከሩ ተከሳሽ በበኩላቸዉ ግለሰቡ ውክልና ያላቸዉ መሆኑን ነገር ግን ሁሉንም ነገሮች የመፈረም ስልጣን የተሰጣቸዉ አለመሆኑን ውል መዋዋል የሚችሉ መሆኑን ክፍያ መፈጸም የሚችሉ መሆኑን ነገር ግን የዕዳ መተማመኛ ሰነድ መስጠት የማይችሉ መሆኑን ግለሰቡ የመተማመኛ ሰነዱን የፈረሙት በፍ/ሕ/ቁ 2205(2) መሰረት የተሰጠ ልዩ ውክልና ሳይኖራቸዉ መሆኑን በተፈረመዉም የመተማመኛ ሰነድ ተከሳሽ ሊገደድ የማይችል መሆኑን ከሳሽ ስራ ሰርተናል ከሚል በቀር ሰራ የሰሩ ስለመሆኑ ያቀረቡት ማስረጃም ሆነ ውል የሌለ መሆኑን በመግለጽ የከሳሽ ክርክር ወድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡   

የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ለክርክሩ መነሻ በሆነዉ  ሰንድ ላይ የተመለከተዉን የገንዘብ መጠን ተከሳሽ የመክፈል ሃላፊነት አለበት ወይስ የለበትም የሚለዉን ነጥብ እንደሚከተለዉ መርምረናል፡፡

እንደመረመረዉም ከሳሽ የሚከራከረዉ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ የተስፋ ሰነድ ነዉ በመሆኑም ለክርክሩ መነሻ በሆነዉ ሰነድ ላይ የተመለከተዉን ገንዘብ ተከሳሽ ሊከፍለኝ ይገባል በማለት ሲሆን ተከሳሽ የሚከራከረዉ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ሰነድ ፈርሞ ለከሳሽ የሰጠዉ ግለሰብ ከተከሳሽ የተሰጠዉ ልዩ ውክልና የለም ሰነዱም እንደሚተላላፉ ሰነዶች የሚቆጠር በመሆኑ ሰነዱን ለመፈረም በፍ/ሕ/ቁ 2205(2) መሰረት ልዩ ውክልና ያስፈልጋል በመሆኑም ይህ አይነት ውክልና ባልተሰጠበት የተፈረመ ሰነድ ሊያስገድድን አይገባም በማለት ነዉ፡፡

ወደ ዋናዉ ጭብ ከመግባታችን በፊት ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ እንደሚተላላፉ ሰነዶች(የተስፋ ሰነድ /የሐዋላ ወረቀት)  የሚቆጠር ሰነድ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉን ነጥብ መየቱ ጠቃሚ ነዉ፡፡

በንግድ ህጉ አንቀጽ 715(1) እንደተመለከተዉ የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ ማለት መብቱ ከሰነዱ ተለይቶ ሊሰራበት ወይም ሊተላለፍ የማይችል ያገልግሎት መብት ያለበት ሰነድ ሁሉ ስለመሆኑ የተመለከተ ሲሆን የድንጋጌዉ ንዑስ ቁጥር 2 ደግሞ የንግድ ወረቀቶችም እንደሚተላለፉ ሰነዶች የሚቆጠሩ ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡

በንግድ ህጉ አንቀጽ 732(1) ደግሞ የንግድ ወረቀቶች ማለት በገንዘብ መክፈል የሚሆነዉን ግዴታ የሚናገሩ ሰነዶች ስለመሆናቸዉ የተመለከተ ሲሆን የድንጋጌዉ ንዑስ ቁጥር 2 ደግሞ የተሰፋ ሰነድ ከንግድ ወረቀቶች መካከል አንዱ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

በንግድ ህጉ አንቀጽ 823 እንደተደነገገዉ አንድ ሰነድ የተሰፋ ሰነድ ለመባል በሰነዱ ዉስጥ የተስፋ ወረቀት የሚል ቃል መገኝትና ሰነዱ በተጻፈበት ቋንቋ መገለጽ ያለበት መሆኑን  የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ሀተት የሌለበት መሆን አንዳለበት፤የሚከፈልበት ጊዜ መገለጽ ያለበት መሆኑን ገንዘቡ ሊከፈልበት የሚገባዉ ቦታ መገለጽ ያለበት መሆኑን ገንዘቡ የሚከፈለዉ  ሰዉ ስም ወይም የታዘዘለት ሰዉ ስም ወይም ወረቀቱ ለአምጪዉ መክፈል የሚገባዉ መሆኑ መገለጽ ያለበት መሆኑን ሰነዱ የተጻበት ቀንና ቦታ እንዲሁም ሰንዱን ያወጣዉ ሰዉ ፊርማ በሰነዱ ላይ መኖር ያለበት መሆኑን ይደንግጋል፡፡ ከነዚህ ከላይ ከተገለጹት ነገሮች አንዱ እንኳን ቢጎል ሰነዱ እንደ ተስፋ ሰነድ የማይቆጠር መሆኑን የንግድ ህጉን አንቀጽ 824 ይደነግጋል፡፡ ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉን ሰነድ ስንመለከተ የተስፋ ሰነድ መገለጫዎች ከሆኑት መካከል ሰነዱ ላይ የተስፋ ወረቅት በሚል የተመለከተ ነገር የለም፤ገንዘቡ ሊከፈልበት የሚገባዉ ቦታ በሰነዱ ላይ አልተገለጸም እንዲሁም ሰነዱ የተጻፈበት ቦታ አልተገለጸም፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ በንግድ ህጉ አንቀጽ 823 እና 824 ጣምራ ንባብ (cumulative reading) ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ የተስፋ / የቃልኪዳን ሰነድ ሊባል አይችልም ፡፡

በተመሳሳይ ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ በንግድ ህጉ 735 የተቀመጡትን ቀድመ ሁኔታዎች የማያሟላ በመሆኑ እንድ ሐዋለ ወረቀት (bill of exchange) ሊቆጠር እንደማይችል ከንግድ ህጉ አንቀጽ 735 እና 736 መረዳት ይቻላል፡፡

ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ የተስፋ ሰነድ/የሐዋለ ወረቀት አይደለም የሚተላላፉ ሰነዶች ባህሪም የለዉም ከተባለ ደግሞ ሰነዱን ለመፈረም ልዩ ውክልና አያስፈልግም ከሰነዱ ላይ ለመመለከት የሚቻላዉ ሰነዱን ፈርሞ የሰጠዉ ግለስብ ያረጋገጠዉ ነገር ቢኖር ከሳሽ ያለዉን ቀሪ ተከፋይ ገንዘብ ነዉ ግለሰቡም በማህበሩ ስም ክፍያ እንዲፈጽም፤ሰነዶችን እንዲፈርም እንዲሁም ውል እንዲዋዋል ስልጣን የተሰጠዉ ስለመሆኑ የቀረበዉ የውክልና ሰነድ ያረጋግጣል፡፡ይህ ከሆነ ደግሞ የተከሳሽ ማህበር ተወካይ አቶ አያልነህ አበበ ቀሪ ተከፋይ ገንዘብ መኖሩን ማረጋገጡ በተሰጠዉ ውክልና ውል የማዋዋል እና ሰነዶችን የመፈረም ሰልጣኑ  በማህበሩ ላይ ግዴታን የሚያስከትሉ ተግባራት መፈጸም የሚችል መሆኑን መረዳት አያዳግትም፤ለክርክሩ መነሻ የሆነዉም ሰነድ በተከሳሽ ላይ ግዴታን የሚፈጥር ነዉ ይህ ደግሞ አንደ ውል የሚቆጠር መሆኑ ገልጽ ነዉ፡፡

ሲጠቃለልም የሚተላላፉ ሰነዶችን ለመፈረም ልዩ ውክልና የሚያስፈልግ መሆኑ በተለይም ከአንግሊዘኛዉ የፍ/ሕግ 2205 (2) በተለይም to signs bill of exchange ከሚለዉ ሀረግ  መረዳት የሚቻል ቢሆንም ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ ሰነድ የሚተላላፉ ሰነዶች ባህሪ የሌለዉ እና ከሚተላላፉ ሰነዶች መካከል አንዱ ባለመሆኑ ተከሳሽ ሰነዱን የፈረመዉ ሰዉ ልዩ ውክልና የሌለዉ ስለሆነ በሰነዱ ልንገድድ አይገባም በማለት ያቀረበዉን ክርክር ፍርድ ቤቱ  አልተቀበለዉም ሰነዱን ለፈረመዉ ግለሰብ የተሰጠዉን ውክልና ይዘትም ስንመለከተ ግለሰቡ ውል ለመዋዋል፤ ሰነዶችን ለመፈረም እና ክፍያ ለመፈጸም ስልጣን የተሰጠዉ ከመሆኑ አንጻር ቀሪ ተከፋይ ገንብብ መኖሩን በማረጋገጥ ለከሳሽ የሰጠዉ ሰነድ ከስልጣኑ ውጭ የተሰጠ ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ ስለሆነም ተከሳሽ በክሱ ላይ የተመለከተዉን የገንዘብ መጠን ሊከፍል ይገባል ተብሎ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡   

   ውሣኔ

  1. ተከሣሽ ብር 135,000.00(አንድ መቶ ሰላሳ አምስት ሺህ) ገንዘቡ መከፈል ከነበረበት ከ16/4/2010 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሠብ 9% ወለድ ጋር ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
  2. ወጪና ኪሣራ ከሳሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 3,875፣ለቴምብር ቀረጥ ብር 15፣ እንዲሁም የጠበቃ አበል 13,500 ተከሣሽ ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡

ትዕዛዝ

  • ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡
  • መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

Read 3991 times