የኮ/መ/ቁ - 171853 - ወ/ሮ ሙሉ አጥናፍ ታዬ እና እነ ማራኪ ኃ/የተ/የግ/ማ (2 ተከሳሾች)

የኮ/መ/ቁ ፡- 171853

ቀን ፡- 21/10/11 ዓ.ም

ፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 7ኛ ንግድ ችሎት

ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ    

ከሳሽ ፡-    ወ/ሮ ሙሉ አጥናፍ ታዬ - ጠበቃ ዘውዱ ተሾመ - ቀረቡ

ተከሳሾች ፡-  1) ማራኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር -

ሥ/አስኪያጅ አቶ አስራት ጥላሁን ቀረቡ

2ኛ አስራት ጥላሁን አሸንጎ - ቀረቡ

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርመሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል::

ፍርድ

ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነው ከሳሽ መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም አሻሽለው ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ጋብቻ ፈፀመው ለ20 ዓመት አብረው ሲኖሩ የነበረ መሆኑን፤ በዚህ ወቅትም 1ኛ ተከሳሽ ማህበርን በ25/10/2007 ዓ.ም በጋራ አቋቁመው የፔንሲዮን አገልግሎት ሲሰጡ የነበረ መሆኑን፤ ከጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ በመካከላቸው ከፍተኛ ያለመግባባት የተፈጠረ በመሆኑ ከቤታቸው ወጥተው ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ያላቸው ጋብቻ እንዲፈርስ አመልክተው ጋብቻው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ በመ/ቁ 40455 በተሰጠ ውሳኔ የፈረሰ መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም የከሳሽ ወኪል ነኝ በማለት ማህበሩ ስለከሰረ እንዲፈርስ ተስማምተናል የሚል የሐሰት ቃለ ጉባኤ በፌደራል የሰነዶች ማረጋጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አቅርበው በማስመዝገባቸው በጋራ የሰሩትን ባለ 16 ክፍል ቤት በእናቱ ስም በማስመዝገቡ ስለ 1ኛ ተከሳሽ ማህበር ገቢ ወጪና ትርፍ ምንም የማያሳውቃቸው በመሆኑ የ1ኛ ተከሳሽ ማህበርን ንግድ ፈቃድ አሰርዞ የማህበሩ ዓላማ እንዳይሳካ በማድረጉ የ1ኛ ተከሳሸ ማህበርን ገንዘብ በማህበሩ ሂሳብ ውስጥ ገቢ ማድረግ ሲገባው ለግል ጥቅሙ በማዋሉ የጋራ የሆነው ቤታቸው ተሸጦ ለማህበሩ ካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል የተቀበለውን ብር 930,000 ለማህበሩ ገቢ ሳያደርግ ለግል ጥቅም በማዋሉ ለ1ኛ ተከሳሽ ማህበር የተገዛውን በሰሌዳ ቁጥር አአ-02-95088 የሚታወቀውን ተሽከርካሪ በመሸጥ ገንዘቡን ለግል ጥቅሙ ያዋለ በመሆኑ ከሳሽ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የነበራቸውን አክሲዮን በመሸጥ የተገኝውን ገንዘብ ለግል ጥቅሙ በማዋሉ ከዕቁብ የተቀበለውን ብር 480,000 ለ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ገቢ ማድረግ ሲገባው ለግል ጥቅሙ ያዋለ በመሆኑ ከ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ብር 2 ሚሊዮን ወጪ አድርጎ ለእናቱ ቤት የገነባበትን ገንዘብ ለማህበሩ ሳይመለስ 2ኛ ተከሳሽ ለግል ጥቅሙ ያዋለ በመሆኑ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥፋቶች የፈፀመ በመሆኑ በከሳሸ እና በ2ኛ ተከሳሽ መካከል ብርቱ ጭቅጭቅ የተፈጠረ መሆኑን ገልፀው ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም በፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የፀደቀው ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው እንዲወሰንላቸው፣ 2ኛ ተከሳሽ በፈፀመው ጥፋት የደረሰባቸውን ጉዳት በሌላ መዝገብ ከሰው ለመጠየቅ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው፣ 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ እንዲወሰንላቸው፣ የሂሳብ አጣሪ ተሹሞ የማህበሩ ሂሳብ እንዲጣራላቸው እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸው ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

ከሳሽ ክሱን ያስረዱልኛል ያሏቸውን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርበዋል የሰው ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡

ከሳሽ ያቀረቡት የተሻሻለ ክስ ለከሳሾች ደርሶ ተከሳሾች ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም በተፃፈ የመከላከያ መልስ ያቀረቡ ሲሆን ባቀረቡት የመከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ  እና የፍሬ ነገር መልስ ሰጥተዋል፡፡ ተከሳሾች ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከሳሽ ያቀረቡት ክርክር የጋራ ንብረትን ጉዳይ ከማህበሩ ክርክር ጋር ደበላልቀው ያቀረቡት በመሆኑ ያቀረቡት ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል፡፡ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው እንዲሻርላቸው የጠየቁት በህጉ የተቀመጠው የሦስት ወር ጊዜ ካለፈ በኋላ በመሆኑ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ነው፡፡ እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ ማህበር በስምምነት የፈረሰ በመሆኑ ክሱ የቀረበው በስምምነት ባለቀና በተፈፀመ ጉዳይ ስለሆነ የከሳሽ ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስ በውልና ማስረጃ ማስረጃ ምዝገባ ፅ/ቤት የፀደቀው ቃለ ጉባኤ በህጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያልተሻረ ስለሆነ ስምምቱ ህጋዊ መሆኑን፤ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው ይሻርልኝ ከሚሉ በቀር ቃለ ጉባኤው የሚሻርበትን ህጋዊ ምክንያትን ያላስረዱ መሆኑን፤ ከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ በቀን 14/10/1992 ዓ.ም የሰጠሁትን ውክልና ሽሪያለሁ ቢሉም ውክልናው የተሻረ ስለመሆኑ ያልደረሳቸው መሆኑን፤ ውክልናው የተሻረ መሆኑን ሌላ የሚያውቁበት መንገድ የሌለ መሆኑን፤ ይህ ሆኖ ሳለ ከሳሽ ማህበሩ የፈረሰው ውክልናው ከተሻረ በኋላ ነው በማለት ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ከሳሽ በቀን 14/10/1992 ዓ.ም የሰጡት ውክልና ተሽሯል እንኳን ቢባል ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ በቀን 15/9/1999 ዓ.ም የሰጡት ውክልና መኖሩን፣ ይህ ውክልናም ያልተሻረ መሆኑን፣ በ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ውስጥ የአብላጫ አክሲዮን ባለ ድርሻ ስለሆኑ ማህበሩ እንዲፈርስ መወሰን የሚችሉ መሆኑን፣ ቃል ጉባኤውም ስልጣን ባለው አካል የተመዘገበ ስለሆነ የሚሻርበት ህጋዊ ምክንያት የሌላ መሆኑን፣ ማህበሩ የፈረሰው የተቋቋመበትን ጉዳይ መፈፀም ባለመቻሉ እና በገንዘብ እጥረት መሆኑን፣ ማህበሩ በኪሳራ የፈረሰ ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ የሌለ መሆኑን እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ የማህበሩን መመስረቻ ፅሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ በመተላለፍ የፈፀሙት ጥፋት የሌለ መሆኑን ገልፀው የመከላከያ መልሳቸውን አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተሻሽሎ በቀረበው ክስ ላይ ሚያዝያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር በክሱ ላይ የተገለፁትን ፍሬ ነገሮች የገለፁት በከሳሽ እና በ2ኛ ተከሳሽ መካከል ብርቱ ጭቅጭቅ መኖሩን ለማሳየት መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ ለብርቱ ጭቅጭቅ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ያልካዱ መሆኑን፤ ተከሳሾች የቀረበው ክስ በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት ያቀረቡትን ክርክር በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 13 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት በብይን ውድቅ ያደረገው መሆኑን፤ የንግድ ህጉ አንቀፅ 416 ኃላፊነቱ ለተወሰነ የግል ማህበር ተፈፃሚነት የሌለው መሆኑን፤ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር የፈፀሙት እርቅ ስምምነት የሌለ መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ ቃለ ጉባኤውን ያፀደቁት በተቃራኒ ዘንግ ቆመው በፍርድ ቤት የጋራ ንብረትን አስመልክቶ በክርክር ላይ በነበሩበት ወቅት መሆኑን ይህም 2ኛ ተከሳሽ ቅን ልቦና የሌላቸው መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን፤ ያፀደቀው ቃለ ጉባኤውም ሊሻር የሚገባው መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ቢሆንም ማህበሩን ማፍረስ የማይችሉ መሆኑን፤ ማህበሩም ሊፈርስ የሚገባው በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መሆኑን፤ 2ኛ ተከሳሽ በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ግዴታቸውን ተወጥተው የማያውቁ መሆኑን ገልፀው ሲከራከሩ፤ ተከሳሾች በበኩላቸው ባቀረቡት ክርክር ከሳሽ ቀደም ሲል ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው ያልጠየቁ መሆኑን ከሳሽ ቃለ ጉባኤውን ያወቁት በ29/6/2010 ዓ.ም መሆኑን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተሻሽሎ የቀረበው ክስ እስከቀረበበት ጊዜ ከሶስት ወር በላይ መሆኑን፤ በዚህም ምክንያት የቀረበው ክስ በይርጋ ቀሪ መሆኑን፤ ማህበሩ በስምምነት የፈረሰ መሆኑን፤ የፈፀሙት ጥፋትም የሌለ መሆኑን፤ ገልፀው የመከላከያ መልሳቸውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡

የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተውን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ከሳሽ ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ነው ወይስ አይደለም? የቀረበው ክስ በእርቅ ስምምነት ያለቀና የተፈፀመ ነው ወይስ አይደለም? ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ውልና ማስረጃ መዝገባ ጽ/ቤት የፀደቀው ቃለ ጉባኤ ሊሻር ይጋባል ወይስ አይገባም? 1ኛ ተከሳሽ ማህበር ሊፈርስ ይገባል ወይስ አይገባም? የ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ ሊጣራ ይገባል ወይስ አይገባም? እንዲሁም ከሳሽ 2ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በማስዳደር ረገድ በፈፀሙት ጥፋት ያደረሱትን ጉዳት በተመለከተ ከሰው የመጠየቅ መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል ወይስ አይገባም? የሚሉትን ነጥቦች እንደሚከተለው መርምሯል::

የመጀመሪያውን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሽ የሚከራከሩት ከሳሽ የፀደቀው ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው የጠየቁት መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም አሻሽለው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከሳሽ የፀደቀውን ቃለ ጉባኤ ያወቁት በ29/6/2010 ዓ.ም ነው፡፡ በመሆኑም የቀረበው ክስ በንግድ ህጉ አንቀፅ 416(2) መሰረት በይርጋ ቀሪ ነው በማለት ክርክር አቅርቧል፡፡

በንግድ ህጉ አንቀፅ 416(2) እንደተደነገገው ህግን፣ የማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍና መተዳደሪያ ደንብን ባለመከተል የተደረጉትን ውሳኔዎች ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ አንስቶ በሦስት ወር ውስጥ ወይም በንግድ ምዝገባ ተመዝግቦ እንደሆነም ከተመዘገበበት ቀን አንስቶ በሦስት ወር ውስጥ ማንኛውም ባለጥቅም ሊቃወመው እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ ለመረዳት እንደሚቻለው ድንጋጌው ተፈፃሚነት የሚኖረው የማህበሩ አባላት በተገኙበት ወይንም በህጋዊ ወኪል አማካኝነት ተወክለው በተሰጠ ውሳኔ ላይ ከመሆኑም በላይ የማህበሩ አባላት ውሳኔው ከመስጠቱ በፊት አግባብነት ባለው ህግ፣ በማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የሰበሰበው አጀንዳ ተገልፆ ጥሪ የተደረገላቸው እንደሆነ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል (የንግድ ህጉ አንቀፅ 416(1)) ይመለከታል፡፡

1ኛ ተከሳሽ ማህበርን የማፍረስ ስልጣን በማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ እንቀፅ 8.6 መሰረት ለማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የተሰጠ ሲሆን የጠቅላላ ጉባኤ አጠራርም በ1ኛ ተከሳሽ ማህበር መመስረቻ ፅሁፍ አንቀፅ 6.2 እንደተመለከተው የማህበሩ ስብሰባ ከመደረጉ ከአስር/አስራ አምስት ቀናት በፊት በአባላቱ በአደራ ደብዳቤ የስብሰባውን ጥሪ ማሳወቅና ለውሳኔ ወይም ለውይይት ቀርበው ሀሳባቸው ምን እንደሆነ በግልፅ ማስረዳት ያለበት ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ አጀንዳ የተያዘ መሆኑን በመግለፅ ለከሳሽ በፅሁፍ ያሳወቁ እና ስበሰባ የጥሩ መሆኑን በመግለፅ ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ይህም የሚያሳየው ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ተይዞ በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የፀደቀው ቃል ጉባኤ ከሳሽ በህጉ አግባብ ማለትም በንግድ ህጉ አንቀፅ 391፣ 392 እና 532 እና በማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ አንቀፅ 6.2 መሰረት ጥሪ ሳይደረግላቸው የፀደቀ ቃለ ጉባኤ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቃለ ጉባኤ የፀደቀው ከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀፅ 543 የተጠበቀላቸው ድምፅ የመስጠት መብት ሳይከበርላቸወ መሆኑን እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ከሳሽን በመወከል ድምፅ ሰጥቻለሁ በማለት የሚከራከሩት በንግድ ህጉ አንቀፅ 409(1) ስር የተመለከተውን ገደብ በመተላለፍ ከከሳሽ ጋር በጉዳዩ ላይ የጥቅም ግጭት እያላቸው እና በፍቺ ተለያይተው በክርክር ላይ እያሉ እና ከሳሽንም ወክለው ድምፅ ለመስጠት የህግ ክልከላ በተቀመጠበት ሁኔታ ነው፡፡

ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቃለ ጉባኤ የፀደቀው ለከሳሽ ጥሪ በአግባቡ ሳይደረግላቸው እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር የጥቅም ግጭት እያላቸው ከሳሽን በመወከል ድምፅ የሰጡ በመሆኑ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው መኖሩን እያወቁ ግራ ቀኙ በፍቺ ከተለያዩ በኋላ በነበራቸው የጋራ ንብረት  ክርክር በመሆኑ የንግድ ህጉ አንቀፅ 416 (2) ተፈፃሚነነት የሚኖረው በቃለ ጉባኤው የተወሰነው ውሳኔ የተወሰነው አባሉ በአካል ወይም የጥቅም ግጭት ሳይኖር በአግባቡ ተወክሎ ወይንም በአግባቡ ጥሪ ተድርጎላቸው በስብሰባው ላይ ሳይገኝ የተሰጠ ውሳኔ ከሆነ ብቻ መሆኑን መረዳት የሚቻል በመሆኑ እና ድንጋጌው ከላይ በተገለፁት ምክንያቶች በተያዘው ጉዳይ ላይ ተፈፃሚነት የሌለው ከሆነ በፍ/ሕ/ቁ 1677(1)እና 1885 መሰረት ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ደንብ የአስር ዓመት ጊዜ በመሆኑ ተከሳሾች ከሳሽ ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

     የንግድ ህጉ አንቀፅ 416(2) ለተያያዘው ጉዳይ ተፈጻሚነት አለው እንኳን ቢባል ከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር የነበራቸው ጋብቻ እዲፈርስ ለፍርድ ቤት ያመለከቱት ታህሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም መሆኑን በማስረጃት ከቀረበው የፍቺ ውሳኔ መረዳት የሚቻል ሲሆን ከሳሽ ከጥቅምት 2008 ዓ.ም ጀምሮ ከ2ኛ ተከሳሽ መኖርያ ቤት ወጥተው መኖር የጀመሩ ስለመሆኑም በተከሳሾች የተካደ ፍሬ ነገር አይደለም፡፡ ከዚህም መረዳት የሚቻለው ከሳሽ በቀን 27/5/2008 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የጸደቀውን ቃለ ጉባኤ የሚያውቁት መንገድ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ በቀን 17 /8/ 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስ በሰማ ዕለት ከሳሽ ቃለ ጉባኤውን በቀን 29/6/2010 ዓ.ም ያውቁ መሆኑን ገልጸው ክርክራቸውን አቅርቧል፡፡ ይህ ደግሞ ይርጋ የሚቆጠረው በፍ/ሕ/ቁ 1846 እንደተደነገገው በመብቱ መስራት ከሚችልበተ ቀን አንስቶ በመሆኑ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው እንዲሻርላቸው ሊጠይቁ የሚችሉበት ቃለ ጉባኤው መኖሩን ካወቁበት ከቀን 29/6/2010 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ በሌላ በኩል በዚህ መዝገብ በቀን 30/6/2011 ዓ.ም ያቀረቡ መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀፅ 416(2) መሰረት የፀደቀውን ቃለ ጉባኤ በአወቁ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ክስ ማቅረባቸውን መረዳት የሚቻል በመሆኑ በዚህ ረገድም ተከሳሾች ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሾች ያቀረቡት ክርክር ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቃለ ጉባኤ ከሳሽ እንዲሻርላቸው የጠየቁት መጋቢት 24 ቀን 2011 ዓ.ም አሻሽለው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ነው፤ ቀደም ሲል ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ላይ ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው አልጠየቁም እንዲሁም ከሳሽ የጸደቀ ቃለ ጉባኤ መኖሩን በቀን 29/6/2010 ዓ.ም አውቀዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው ቃለ ጉባኤው መኖሩን በአወቁ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ መጠየቅ ሲገባቸው አልጠየቁም እንዲሻርላቸው የጠየቁት ቃለ ጉባኤው መኖሩን ካወቁ ከሶስት ወር በኃላ ነው በማለት ያቀረቡተትንም ክርክር በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ከመሻሻሉ በፊት ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ ያቀረቡት ክስ በይርጋ ቀሪ ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ ይዞ የተከሳሾችን የይርጋ መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሳሽ ቃለ ጉባኤው እንዲሻርላቸው የጠየቁ መሆኑ ቀደም ሲል ባቀረቡት ክስ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ ግልጽ የሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ከሳሽ ቀደም ሲል ባቀረቡት ክስ ቃለ ጉባኤው እንዲሻርላቸው አልጠየቁም በማለት ያቀረቡት ክርክር ፍርድ ቤቱ የሚቀበለው አይደለም፡፡

   2ኛውን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሾች ከሳሽ ያቀረቡት ክስ በእርቅ ያለቀና የተፈፀመ ጉዳይ ስለሆነ ውድቅ ሊደረግ ይገባል በማለት ክርክር አቅርቧል፡፡ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 244(2)(ረ) እንደተደነገገው ክሱ የተነሳበት ነገር በሽምግልና ታይቶ በስምምነት የተፈፀመ መሆኑን የሚገልፅ መቃወሚያ ቀርቦ በማስረጃ ከተጋገጠ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ዘግቶ ባለጉዳዮችን ማሰናት ያለበት ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ከሳሽ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ የጠየቁት ዳኝነት በቀን 27/5/2008 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የጸደቀው ቃለ ጉባኤ እንዲሻርላቸው 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ እንዲወሰንላቸው የ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ እንዲጣራ እንዲወሰንላቸው እንዲሁም ከሳሽ 2ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በማስተዳደር ረገድ በፈጸሙት ጥፋት ያደረሱትን ጉዳት በተመለከተ ከሰው የመጠየቅ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ሲሆን እነዚህን ጉዳቶች ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው ድንጋጌ መሰረት በሽምግልና ታይተው በስምምነት የተፈፀሙ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ማስረጃ አልቀረበም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ተከሳሾች ጉዳዩ በእርቅ ያለቀ ነው በማለት ያቀረቡት ክርክር የህግ መሰረት ያለው ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

   3ኛውን ነጥብ በተመለከተ 2ኛ ተከሳሽ የሚከራከሩበት በከሳሽ የተሰጠኝ ውክልና ስለነበረ በተሰጠኝ ውክልና 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ አድርጊያለሁ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ቃለ ጉባኤው የሚሻርበት ህጋዊ ምክንያት የለም በማለት ነው፡፡ በርግጥ ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ በቀን 15/9/1999 ዓ.ም እና 14 /10/ 1992 ዓ.ም የሰጡት ስለመኖሩ ወይም ውክልና ከሳሽን ወክለው ስለማህበሩ ጉዳይ ድምጽ መስጠት የሚያስችላቸው መሆኑን ግራ ቀኙ አልተካካዱም፡፡ ይሁን እንጂ ከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ላይ ታህሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም የፍቺ ክስ አቅርበው በክርክር ላይ የነበሩ መሆኑን የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ከማስረዳታቸውም በላይ ግራ ቀኙ የተካካዱት ፍሬ ነገር አይደለም፡፡ ተወካይ የሆነ ሰው ከወካዩ ጋር በሚያስተሳስረው ግንኙነት ውስጥ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና ሊኖረው የሚገባ መሆኑን፤ ተወካዩ ስራውን የሚፈፅመው ለወካዩ ጥቅም ሊሰጥ በሚችልበት መንገድ ብቻ መሆኑን እንዲሁም ተወካዩ በውክልና ስራው በሚገኝባቸው ጊዜዎች ሁሉ በውክልናው የተሰጠውን አደራ እንደ መልካም ቤተሰብ አባት ቤተሰቡን ለመጠበቅ እንዲሚያደርገው ሁሉ በትጋትና በጥንቃቄ መጠበቅ ያለበት ስለመሆኑ በፍ/ሕ/ቁ 2208፣2209 እና 2211 ስር ተመልክቷል፡፡ እንዲሁም ተወካዩ ከወካዩ ጋር የጥቅም ግጭት ያለው እንደሆነ ወካዩን በመወከል ድምጽ መስጠት የሌለበት ስለመሆኑ በንግድ ህግ አንቀፅ 409(1) ስር ተመለክቷል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ከላይ የሰፈሩትን ድጋጌዎች በመተላለፍ ከከሳሽ ጋር በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እያለ ከሳሽን በመወከል ማህበሩ እንዲፈርስ ድምጽ መስጠቱ ቅን ልቦና የሌለው መሆኑን እና ከላይ የተጠቀሱትን ግዴታዎቹን ያላከበረ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የጸደቀው የ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ቃለ ጉባኤ እንዲሻር በንግድ ህጉ አንቀፅ 416 መሰረት ተወስኗል፡፡

  ሌላው 2ኛ ተከሳሽ ያቀረቡት ክርክር በ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ውስጥ አብላጫ ድምጽ ያለኝ በመሆኑ ማህበሩ እንዲፈርስ መወሰን እችላለው፡፡ በመሆኑም ቃለ ጉባኤው ሊሻር አይገባም በማለት ያቀረቡት ክርክር በተመለከተ ማህበሩን ለማፍረስ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት ያለበት ስለመሆኑ የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ አንቀፅ 6.2 ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን ለማፍረስ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ 2ኛ ተከሳሽ ይህን ስለማድረጋቸው ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ በመሆኑም 2ኛ ተከሳሽ በዚህ ረገድ ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

    4ኛውን ነጥብ በተመለከተ 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በማፍረስ የጸደቀው ቃለ ጉባኤ እንዲሻር ከላይ የተወሰነ ስለሆነ እና ውጤቱም ማህበሩ እንዳልፈረሰ የሚቆጠር (የንግድ ሕግ አንቀፅ 416 (5) እና (6)) ይመለከታል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽ ማህበሩ እንዲፈረሰ የመጠየቅ መብት ያላቸው መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ከሳሽ ባቀረቡት ክርክር ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ብርቱ ጭቅጭቅ የተፈጠረ ስለሆነ ማህበሩ ሊፈርስ ይገባል በማለት ክርክር አቅርበዋል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር ብርቱ ጭቅጭቅ የሌለ መሆኑን ክደው አልተከራከሩም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማህበሩ አባላት ከሳሽ እና 2ኛ ተከሳሽ እንደመሆናቸው መጠን በመካከላቸው የነበረው ግንኙነት በፍቺ ፈርሷል፡፡ ይህም በአባላቱ መካከል የማህበሩን እንቅስቃሴ እና ዓላማ ከግብ ለማደረስ የሚያስችል መልካም ግንኙነት አለ ሊባል አይችልም፡፡ በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ ማህበር በአባላቱ መካከል ብርቱ ጭቅጭቅ ያለ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ያረጋገጠ ስለሆነ በንግድ ህጉ አንቀፅ 218 እ 542 መሰረት እንዲፈርስ ተወስኗል፡፡

  5ኛውን ነጥብ በተመለከተ 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ የተወሰነ በመሆኑ እና ማህበሩ እንዲፈርስ ከተወሰነ ደግሞ የማህበሩ ሂሳብ ሊጣራ የሚገባ መሆኑን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 189 የተደነገገ ስለሆነ የማህበሩ ሂሳብ ሊጣራ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡

  6ኛውን ነጥብ በተመለከተ 2ኛ ተከሳሽ በማህበሩ ጉዳት ያደረሱ መሆን አለመሆኑ የሚታወቀው የማህበሩ ሂሳብ ከተጣራ በኃላ በመሆኑ 2ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በማስተዳደር ረገድ በፈጸሙት ጥፋት ያደረሱት ጉዳት በተመለከተ ከሰው የመጠየቅ መብታቸው ተጠብቋል፡፡

ው  ሳ  ኔ

  1. በቀን 27 /5/ 2008 ዓ.ም በውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት የጸደቀው የ1ኛ ተከሳሽ ማህበር ቃለ ጉባኤ ተሽሯል፡፡
  2. 1ኛ ተከሳሽ ማህበር እንዲፈርስ ተወስኗል፡፡
  3. የ1ኛ ተከሳሽ ማህበርን ሂሳብ የሚያጣራ ባለሙያ የምድቡ ሬጅስትራር ይመድብ፡፡
  4. ከሳሽ 2ኛ ተከሳሽ በማህበሩ ላይ ወይም በእርሳቸው ያደረሱት ጉዳት ካለ ከሰው የመጠየቅ መብታቸው ተጠብቋል፡፡
  5. ከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ላይ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብታቸው ተጠብቋል፡፡

ት  ዕ  ዛ  ዝ

  • ይግባኝ ለጠየቀ ተገልብጦ ይሰጠው፡፡
  • መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡

 

 

Read 3660 times