እርግጥ ነው አሁን ያለንበት የኮሮና ቫይርስ ወረርሽኝ ወቅት እጅግ ፈታኝ፣ ፈጣን አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመስጠት የሚከብድበት የቱ ትክክልየቱ ስህተት እንደሆነ ለማመዛዘን የሚቸግር ጊዜ ነው፡፡ በተለይም በወረርሽኙ ምክንያት የሰዎች ህይወት አደጋ ላይ መውደቁ ሲታይ አሳሳቢና አስጨናቂ ነው፡፡
በዛው መጠን ደግሞ በማዕበሉ ወቅትም ቢሆን ህዝብና የመንግሥት አስተዳደር ይቀጥላል፡፡ ፍርድ ቤቶች ደግሞ እጅግ በጣም አስፈላጊና ወሳኝየህዝብ አገልግሎት ሰጪ አካላት መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ሐቅነው፡፡ ፍ/ቤቶች ከሶስቱ የመንግሥት አካላት (the three organs of Government/state) አንደኛው ቅርንጫፍ/አካል ናቸው፡፡ ሌሎቹ የመንግሥት አካላት(አስፈፃሚውና ሕግ አውጪው) ሥራቸውን እያስኬዱ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም በወረርሽኙ ምክንያት የሰውን ህይወት ለአደጋ በማያጋልጥና በጥንቃቄ ሥራቸውን የሚያስኬዱበት መንገድ ሊፈተሸ ይገባል፡፡
በጣም የሚያስደነግጠው ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ‹‹የኮሮና ቫይረስ ለማጥፋት በርካታ ዓመታት ሊወስድ ይችላል፡፡ የሚጠፋበት ጊዜ ቅርብ አይደለም እንደውም እንደ ኤች.አይ.ቪ ላይጠፋ ይችላል›› የሚል መግለጫን አውጥቷል፡፡
ስለዚህ ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች ወሳኝ አገልግሎት ሰጪ አካላት በቀጣይ ከቫይረሱ ጋር በጥንቃቄ ህይወት የሚቀጥልበትን መንገድ ሊያስቡበት ግድ ይላቸዋል ማለት ነው፡፡ እጅን አጣጥፎ ‹‹ጥሩ ቀን ቶሎ ና›› እያሉ ብቻ መጠበቅ አያስኬድም አያዋጣም፡፡