ለፌዴራል እና ለክልል ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች የሕዝብ እንደራሴዎችን ለመምረጥ የሚከናወነው መጪው አገር አቀፍ ምርጫ ከተደጋጋሚ መስተጓጎሎች በኋላ የድምጽ መስጫ ዕለቱ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲደረግ ቀን ተቆርጦለት ዝግጅቶቹ ቀጥለዋል፡፡ ይህ ምርጫ ከዓመት በፊት ማለትም በሕገ-መንግሥታዊ ትርጉም ከመራዘሙ በፊት ካለው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር፤ በትግራዩ ጦርነት፣ በሰላምና ደህንነት ስጋቶቹ፣ የተዳከመው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ፣ የተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች እስር፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እና የውጪ አገራት ጫና ያደበዘዘው ይመስላል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን፤ ድህረ-2010 የታዩት የሕግ እና የተቋማት ማሻሻያዎች፣ አንጻራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የሲቪክ ምሕዳሮች ስፋት የዘንድሮውን ምርጫ በጉጉት ተጠባቂ እንዲሆን ማድረጋቸው አልቀረም፡፡
ምርጫ 2013 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳውን ይፋ ካደረገበት ወርኃ ጥር ጀምሮ እስካሁን ድረስ በርከት ያሉ የቅድመ-ምርጫ ተግባራት ተከናውነውበታል። ከእነዚህ መካከል የምርጫ ቁሳቁሶች ዝግጅት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ፣ የእጩዎች ምዝገባ፣ የመራጮች ትምህርት እና የመራጮች ምዝገባ ተጠቃሽ ክንውኖች ናቸው።
በእነዚህ ወሳኝ የቅድመ-ምርጫ ክንውኖች ውስጥ የተነሱት እና በቀሩት ጊዜያትም ሊነሱ የሚችሉት በተለይም የሕግ ጉዳዮች የዘንድሮውን ምርጫ የተለየ መሆንነት አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለአብነት እንኳ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ያስከተለው ውዝግብ፣ ከፌዴራሉና ከሌሎቹ ክልሎች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ቀን ተለይቶ የነበረው የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ምክር ቤቶች ምርጫ ጉዳይ፣ የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች የምርጫ ጣቢያዎች ውዝግብ፣ የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ምርጫ እና አነጋጋሪው የእጩዎች ምዝገባ የፍርድ ቤቶች ክርክር የዘንድሮው ምርጫ በቀጣይ ለሚከናወኑ ምርጫዎች አስቀምጦ የሚያልፈው ልምምድ ቀላል የሚባል አለመሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡
ወሳኝ የምርጫ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ልዩ ልዩ ተቋማት መካከል ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በእስካሁኖቹ የምርጫ ሂደቶች ያሳዩት ጥረት የምንመኘውን ነጻ፣ ትክክለኛ እና ተዓማኒ ምርጫ ወደፊት ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ ናቸው። በዚያው ልክ ግን በሒደቶቹ ውስጥ የታዩ የጎሎ ክፍተቶች የዘንድሮውን ጨምሮ በቀጣይ ለሚደረጉትም ምርጫዎች የራሳቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም።