በግልግል ዳኝነት የፍርድ ቤቶች ሚና
የግልግል ዳኝነት የፍትሐ ብሔር ሕግ ሥራ ላይ ከዋለበት ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ የሕግ ማዕቀፍ ያለዉ ቢሆንም ቀደም ሲል በነበሩ ጊዜያቶችም ባሕላዊ ደንቦችን መሰረት ባደረገ መልኩ ይፈፀም ነበር፡፡ የግልግል ዳኝነትን ጨምሮ አማራጭ የሙግት መፍቻዎች በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3307 እስከ ፍ/ብ/ሕ/ቁ 3346 በተቀመጡ ደንቦች እንዲሁም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 315- 319፣ 350- 357 በተቀመጡ ደንቦች የግልግል ዳኝነት ይመራ ነበር፡፡ እነዚህን የሕግ ማዕቀፎች መሰረት በማድረግ የግልግል ዳኝነት በአብዛኛዉ በሚባል ደረጃ ተቋማዊ ባልሆነ መልኩ ወይም ጊዜያዊ በሆነ የግልግል ዳኝነት /Ad hoc arbitration/ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን ያለዉ የግልግል ዳኝነት በሁለት መልኩ ሊገለጽ የሚችል ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ ደግሞ ጊዜያዊ የግልግል ዳኝነት (Adhoc arbitration) ሲሆን ሁለተኛ ተቋማዊ የግልግል ዳኝነት (institutional arbitration) ነዉ፡፡
ጊዜያዊ የግልግል ዳኝነት (Adhoc arbitration) አንድ የተወሰነ አለመግባባት ለመፍታት የሚመሰረት ሲሆን ተዋዋይ ወገኖች ዉልን መነሻ በማድረግ የሚያቋቁሙት ነዉ፡፡ ተዋዋይ ወገኖች በመካከላቸዉ የፈጠረዉን አለመግባት ተከትሎ በስምምነት አለመግባባታቸዉን የሚፈታ ገላጋይ ዳኛ በመምረጥ የግልግል ጉባዔ በማቋቋም የግልግል ዳኝነተ ሂደቱ ይጀመራል፡፡ ተዋዋይ ወገኖች አለመግባባታቸዉን የሚፈታ የግልግል ጉባዔ በስምምነት መምረጥ ባልቻሉ ጊዜ በአንደኛዉ ወገን ጠያቂነት በፍርድ ቤት ወይም በዉላቸዉ ገላጋይ ጉባዔዉን እንዲያቋቁም በመረጡት ተቋም አማካኝነት የግልግለ ጉባዔ እንዲቋቋም ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መልኩ የሚቋቋመዉ ጉባዔ የተቋቋመበትን አለመግባባት ብቻ ለመፍታት የተቋቋመ በመሆኑ ምክንያት ጊዜያዊ የግልግል ዳኝነት ያስብለዋል፡፡
ሁለተኛዉ የግልገል ዳኝነት ተቋማዊ የግልግል ዳኝነት (institutional arbitration) የሚባለዉ ሲሆን በተቋም ደረጃ የማስማማት እና የግልግል ዳኝነት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋሞችን የሚመለከት ነዉ፡፡ የግልግል ዳኝነት በተቋም ደረጃ ይሰራል ሲባልም የግልግል ተቋሞቹ የግልግል እና የማስማማት ደንብ በማዘጋጀት የግልግል ዳኝነትን አገልግሎት የሚሰጡበት ነዉ፡፡ ይህ ተቋማዊ የግልግል ዳኝነት በሀገራችን በሰፊዉ ተሰርቶበታል ለማለት የሚቻል ባይሆንም በጣት የሚቆጠሩ ተቋሞች ውስጥ የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የግልግል ዳኝነት የእርቅ አሰራር ሥርዓት አዋጅ 1237/2013 የግልግል ማዕከላት የግልግል ዳኝነትን የሚመራበትን ሥርዓት ለመወሰን ሲወጣ የግልግል ማዕከላት በግል ዘርፍም ሊቋቋም እንደሚችል ፈቃጅ ድንጋጌ ይዟል፡፡ ይህ ድንጋጌ በመንግስት ከተቋቋሙ የግልግል ማዕከላት ተጨማሪ የግል ዘርፉንም አሳታፊ የሚያደርግ እንደመሆኑ ብዙ መነቃቃትን ሊፈጥር የሚችል ነዉ፡፡ እስካሁን ባለዉ ሁኔታ የግልግል ማዕከላት ለማቋቋም የሚያስችል ፍቃድ አሰጣጥ ደንብ ባለመዉጣቱ ቀደም ሲል ከተቋቋሙ የግልግል ማዕከሎች ዉጪ አዲስ የተቋቋመ ማዕከል የለም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የግልግል ዳኝነት ማዕከል ፈቃድ አሠጣጥ፣ ምዝገባ እና ቁጥጥር ደንብን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለማፀደቅ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡
በግልግል ዳኝነት የሚታዩ የንግድ ጉዳዮች
የንግድ ክርክር በባሕሪዉ ፍትሐ ብሔራዊ ቢሆንም ከሌሎች የፍትሐ ብሔር ክርክሮች የተለዬ የሚያደርገዉ አለመግባባቶቹ የሚነሱት ከንግድ ግብይት ወይም እንቅስቃሴ በመሆኑ ነዉ፡፡ እነዚህ የንግድ እንቅስቃሴ እና ግብይቶች በንግድ ሕግ አዋጁ አንቀጽ 5 እና ሌሎች ሕጎች ተመላክተዉ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የግልግል ዳኝነት እና የዕርቅ አሠራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 2(7) ንግድ ነክ ጉዳዮች የንግድ ባህሪ ያላቸዉ ከዉል ወይም ከዉል ዉጪ ባሉ ግንኙነቶች ሁሉ የሚመነጩ ሆነዉ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በማቅረብ ወይም በማከፋፈል የሚደረግ የንግድ ግንኙነት፣የንግድ ወኪልነትን፣ ኪራይን፣ የግንባታ ሥራን፣ የማማከር ሥራን፣ የምህንድስና ሥራን፣ ለንግድ ጉዳይ የሚደረጉ የፈቃድ ጉዳዮች፣ የኢንቨስትመንት፣የፋይናንስ ሥራ፣የባንክ ሥራ፣ ኢንሹራንስ፣ የማዕድን ሥራዎች፣ የእሽሙርና ሌሎች ንግድ ማኅበራት ጉዳዮች፣ በአየር፣ በባህር ወይም በየብስ የሚደረገ የሰዉ እና የዕቃ የማጓጓዝ ስራዎች እና የመሳሰሉትን እንደሚያካትቱ አመላክቷል፡፡ እነዚህን ግንኙነቶች ተከትሎ ከዉል ወይም ከዉል ዉጪ በሚፈጠሩ ጉዳዮች የሚነሱ አለመግባባቶች ሁሉ እንደ ንግድ ክርክሮች ተደርገዉ የሚወሰዱ ናቸዉ፡፡
በግልግል ዳኝነት የፍርድ ቤቶች ሚና
ከላይ የተጠቀሱት የንግድ ዘርፎች በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ላይ ወሳኝነት ያላቸዉ እንደሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ በንግድ ዘርፉ ላይ የሚነሱ አለመግባባቶች የንግድ እንቅስቃሴዉ እና የገበያ መረጋጋቱን ሊጎዱ የሚችሉ በመሆኑ አለመግባባቶቹ የሚፈቱበት መንገድም የንግድ ዘርፉን ጤናማነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች እንደ ዋና ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ነዉ፡፡ የክርክር አፈታት ዘዴዎች በሚመሩበት ሂደት፣ በሚወስዱት ጊዜ እና ገንዘብ እንዲሁም ዉጤቱ ከሚፈጥረዉ ተፅዕኖ አንፃር ሲታይ በንግዱ ዘርፍ ያላቸዉ ሚና በቀላሉ ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡ የንግድ ዘርፉን ከባቢ ጤናማ በማድረግ ብቻ ሳይሆን ለኢንቨስትመንት ሳቢ የሆነ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ የሆነ ሚና አላቸዉ፡፡
አብዛኛው የንግድ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የሚነሱ አለመግባባቶች ከፍርድ ቤት ውጪ ባሉ የሙግት መፍቻ መንገዶች የሚፈቱበት እድል ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶች በሚታዩ ጉዳዮች ላይ በአንድም ሆነ በተለያዬ ምክንያት የፍርድ ቤቶች ተሳትፎ የግድ የሚጠይቁበት ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ከፍርድ ቤት ውጪ የሚታዩ ይሁኑ እንጅ የፍርድ ቤትን ጣልቃ ገብነት ወይም ተሳትፎ የሚፈልጉበት ሁኔታ አለ፡፡ ከፍርድ ቤት ውጪ በሚታዩ የንግድ ጉዳዮች ውስጥ የፍርድ ቤቶች ሚና በሚከተለዉ መልኩ ይገለፃል፡፡
1. የግልግል ጉባዔ ማቋቋም
ከሕግ በመነጨ ግዴታ ወይም ተዋዋይ ወገኖች በውል በሚያደርጉት ስምምነት ከንግድ ጋር በተገናኘ የሚነሱ አለመግባባቶች ከፍርድ ቤት ውጪ ባሉ የሙግት መፍቻ መንገዶች ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ተከራካሪ ወገኖች በራሳቸዉ ነገሩን የሚፈታ አስታራቂ ወይም ገላጋይ ዳኛ በስምምነት መምረጥ ባልቻሉ ጊዜ ወይም የየራሳቸዉን ገላጋይ ዳና መርጠዉ ሰብሳቢዉን ለመምረጥ ስምምነት መድረስ ሳይችሉ ሲቀሩ በአንደኛዉ ወገን አመልካችነት ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቅርበዉ ገላጋይ ዳኛ እንደሚያሾሙ በአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 12(3)(ለ) ተመላክቷል፡፡ ገላጋይ ዳኛ በፍርድ ቤት የሚሾመው የግልግል ጉባዔዉን ለማቋቋም ብቻ ሳይሆን የተከራካሪ ወገኖች በተጓደሉ ወይም እንዲነሱ በተደረጉ ዳኞች ምትክ በስምምነት መምረጥ በማይችሉበት ጊዜም ጭምር ነው፡፡ ከፍርድ ቤት ውጪ በሚታዩ ጉዳዮች ቀዳሚ እና ዋናው ተግባር ግልግል ጉባዔዉን ማቋቋም እንደመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉባዔውን በማቋቋም ረገድ ወሳኝ የሆነ ሚና አላቸው፡፡
2. ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ (Provisional Interim measure) መስጠት
ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ የሙግቱን ዉጤት ሊጎዳ የሚችልን ያልተገባ ተግባር ለመከላከል ከፍርድ በፊት የሚሰጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ከሚሰጠዉ ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ (temporary injunction) ጋር አቻ የሆነ የትዕዛዝ ዓይነት ነዉ፡፡ የትዕዛዙ ዋና ዓላማም የአንድን ነገር ነባራዊ ሁኔታን ለመጠበቅ ሲሆን አፋጣኝ እርምጃ በመዉሰድ በተዋዋይ ወገን ላይ ሊደርስ የማይችል ጉዳት ወይም ኪሳራ መከላከል ነዉ፡፡ በአብዛኛዉ ሀገሮችም ይህ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ የግልግል ዳኝነት እና ዕርቅ ከመጀመሩ በፊት ወይም በሂደት ላይ እያለ በፍርድ ቤት ወይም በግልግል ጉባኤ የሚታዘዝ ነዉ፡፡
በንግድ ክርክሮችም ፍርድ ቤቶች ካላቸዉ ሚና አንዱ የግልግል ሂደቱን ሊጎዳ የሚችልን ለመጠበቅ የመጠባበቂያ እርምጃ ወይም ትዕዛዝ መስጠት ነዉ፡፡ ተዋዋይ ወገኖች የግልግል ዳኝነት ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ወይም ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ ፍርድ ቤት ትዕዛዙን እንዲሰጥላቸዉ መጠየቅ የሚችሉ መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 9 እና 27 ተደንግጓል፡፡ ይህ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ የሚሰጠዉም በአዋጁ አንቀጽ 20(3) እንደተመላከተዉ አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎችን ለመጠበቅ፣ የክርክሩ አካል የሆኑ ዕቃዎች እንዲጠበቁ ለማድረግ፣ የግልግል ዉሳኔ ሊያርፍባቸዉ የሚችሉ ሐብቶችና ፈንዶች እንዲጠበቁ ማድረግ፣ ለግልግል ምክንያት የሆነዉ ጉዳይ እስኪወሰን የነበረው ሁኔታ እንዲቀጥል ወይም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ ነው፡፡
3. ትዕዛዝ እና ውሳኔ ማስፈጸም
ከፍርድ ቤት ውጪ የሚታዩ ንግድ ነክ ጉዳዮችን ትዕዛዝ እና ውሳኔ ማስፈጸም የፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት ወይም ሚና ከሚገለጽበት መንገድ አንዱ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 25(1) እና 51(1) መሰረት ጊዜያዊ የግልግል ጉባዔ ሆኑ የግልግል ዳኝነት ማዕከል የሚሰጡት ትዕዛዝ እና ዉሳኔ በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደሚሰጡት ተመሳሳይ የሆነ አስገዳጅነት አላቸዉ፡፡ ይሁን እንጅ የግልግል ጉባዔ እና የግልግል ዳኝነት ተቋም እንደ ውስንነት ከሚነሳባቸዉ አንዱ ጉዳይ የሰጡትን ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ በራሳቸዉ ማስፈፀም አለመቻላቸው ነው፡፡ በንግድ ክርክሮች ከፍርድ ቤት ውጪ የተሰጠ መጠባበቂያ ትዕዛዝ እና ውሳኔ በፍርድ ቤት ቀርበው ይፈፀማሉ፡፡ ትዕዛዙ ለማስፈፀም ብቻ ሳይሆን ትዕዛዙ እዉቅና እንዲያገኝም ሊቀርብ ይችላል፡፡ ትዕዛዙ እዉቅና እንዲያገኝ ሲባል በተለያዩ መንገዶች ሊገለጽ የሚችል ቢሆንም በአብዛኛዉ ጊዜ በጊዜያዊ ግልግል ጉባዔ የሚሰጡት ትዕዛዞች የፍርድ ቤት ማኅተም እንዲደርግባቸዉ የሚጠየቁበት ሁኔታ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ የንግድ ጉዳዮችንም ለማየት የቋቋሙ ችሎቶችም ከፍርድ ቤት ውጪ ባለ አማራጭ የሙግት መፍቻ የተሰጠን ትዕዛዝ እና ውሳኔ እዉቅና ከመስጠት ጀምሮ በማስፈጸም ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡
4. ማስረጃ አሰባሰብ ላይ ድጋፍ ማድረግ
ከፍርድ ቤት ዉጪ በሚታዩ ጉዳዮች እንደ አንድ ችግር ይነሳ ነበረዉ የግልግል ጉባዔዎች ማስረጃ በማስባሰብ ረገድ ይታባቸዉ የነበረዉ ዉስንነት ነው፡፡ ይህ ዉስንነትም በተለይም ጊዜያዊ የግልግል ጉባዔዎች ላይ በይበልጥ ይስተዋል የነበረ ሲሆን ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸዉ፡፡ አዋጅ ቁጥር 1237/2013 በማስረጃ አሰባሰብ ረገድ ይታይ ነበረዉን ውስንነት ለመቅረፍም ፍርድ ቤቶች የሚኖራቸዉን ሚና ወስኖ አስቀምጧል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 37 የግልግል ጉባዔ በክርክሩ ሂደት በራሱ አንድን ማስረጃ ለማስቀረብ ወይም ለመስማት የማይችልበት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ ፍርድ ቤቶች እንደ ግልግል ጉባዔ በመሆን ራሱ ማስረጃዉን ሊሰማ ወይም እንዲሰማ ትዕዛዝ ሊሰጡ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡
ይህ ፍርድ ቤቶች በማስረጃ አሰባሰብ ዙሪያ የሚያደርጉት ድጋፍ በዓለም ዓቀፍ የግልግል ሂደትም የሚተገበር ሲሆን ፍርድ ቤቶች በተለያዩ ምክንያቶች ማስረጃ በማሰባሰብ ድጋፍ የማድረግ ስራ የሚሰሩበት ሁኔታ አለ፡፡ በግልግል ዳኝነት ሂደት ዉስጥ ጉባዔዉ አንድን ማስረጃ ከሶስተኛ ወገን ወይም ከመንግስት ተቋም እንዲቀርብ ትዕዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ የማይፈጸምበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በተለይም የግልግል ጉባዔ በጊዜያዊነት ሲቋቋሙ ወይም የግልግል ተቋማትን ከፍርድ ቤት ጋር እኩል አድርጎ ያለማየቱም ሁኔታ ስለሚኖር የሚሰጡ ትዕዛዞች መደበኛ ፍርድ ቤት እንደሚሰጡ ትዕዛዝ እኩል ላይፈፀሙ ይችላሉ፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤት አንድን ማስረጃ ማኅተም በሌለው ከተቋም ውጪ በሆነ ግለሰብ ወይም የግልግል ጉባዔ ሰብሳቢ ዳኛ ፊርማ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ቢሰጥ ተቀባይነት የማግኘት እድሉ አናሳ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ማስረጃ በበባህሪያቸዉ ወይም በሕግ በሚደረግ ክልከላ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ ለሶስተኛ ወገን ሊገለፁ የማይችሉ መረጃዎች የግልግል ጉባዔ በቀላሉ ሊያስቀረቡት የማይችሉበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በዚህ ጊዜ በፍርድ ቤት ድጋፍ ማስረጃው እንዲቀርብ በማድረግ የግልግል ሂደቱ የተሟላ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡
5. ትዕዛዝና ውሳኔዎችን በቅሬታ ወይም በይግባኝ ማየት
ከፍርድ ቤት ውጪ በሚደረጉ የንግድ ክርክሮች ፍርድ ቤቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡላቸዉን ቅሬታዎች በመመልከት የተሰጠዉን ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ ተገቢነት እንዲመረምሩ በሕግ የተሰጣቸዉ ስልጣን አለ፡፡ ፍርድ ቤቶች በቅሬታ መልክ የሚመለከቷቸዉ ጉዳዮችም እንደ መደበኛ ይግባኝ ወይም በክለሳ መልክ ሊቀርቡ የሚችሉ ሲሆኑ የግልግል ሂደቱ ቀጥሎ ባለበት ወይም ከተጠናቀቀ በኋላ ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው፡፡ እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ ከሚችሉት ዉስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
5.1. የግልግል ዳኛ እንዲነሳ የቀረበ የተቃውሞ አቤቱታ ላይ የተሰጠ ውሳኔ
በግልግል እየታዬ በሚገኝ ጉዳይ ላይ አንደኛዉ ተከራካሪ ወገን የግልግል ዳኛ ወይም ዳኞች እንዲነሱ ተቃዉሞ አቅርቦ ተቃዉሞ የቀረበበት ገላጋይ ዳኛ በራሱ ፈቃድ ካልተነሳ ወይም ሌላኛው ወገን በተቃውሞው ካልተስማማ ጉባዔዉ በቀረበው ተቃዉሞ ላይ ሊወስን እንደሚችልና በውሳኔዉ ላይ ቅሬታ ለፌደራል የጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚቀርበበት ሥርዓት እንዳለ በግልግል ዳኝነት እና የዕርቅ አሠራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 15(4) ተመላክቷል፡፡ በአዋጁ አንድ የግልግል ዳኛ ላይ ተቃዉሞ ሊቀርብ የሚችልበትን መነሻ ምክንያቶች ጠቅልል በማድረግ አስቀምጧል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 14 ዋና የተቃዉሞ ምክንያት ተደርገዉ የቀረቡት የገላጋይ ዳኛው ገለልተኛነቱና ነጻነቱ ወይም በግልግል መስፈርቱ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን የማያሟላ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የግልግል ዳኝነትን ስራ በተገቢዉ መንገድ መስራት አለመቻል ሌላ የተቃዉሞ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 16 ተመላክቷል፡፡ ከዳኞች መነሳት ጋር በተገናኘ የግልግል ጉባዔ ውሳኔ በቅሬታ መልክ ለፍርድ ቤት መቅረቡ የራሱ የሆነ አንድምታ ያለው ሲሆን የመጀመሪያዉ ፍርድ ቤቶች የግልግል ጉባዔው ሥራውን በገልተኛነት እየሰራ መሆኑ የሚያረጋግጡበት መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ይህም ፍርድ ቤቶች በጉዳይ ላይ ገለልተኛ አካል እንደመሆናቸው የግልግል ጉባዔው ዳኞች ላይ የቀረበውን ተቃውሞ የወሰነዉ ከገለልተኛነት መርህ እና ከጥቅም ግጭት በፀዳ መልኩ መሆኑን ቅሬታዉ ከቀረበበት ሂደት ጀምሮ እስከተወሰነበት ደረጃ ያለዉን ሂደት መመርመር እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛዉ ቅሬታዉ ለፍርድ ቤት መቅረቡ የግልግል ስምምነቱ ያለምንም እንከን ተፈፃሚ እንዲሆን ያስችላል፡፡ አንደኛዉ ወገን በግልግል ጉባዔ የተሰየሙትን ዳኛ እንዲነሱ እየጠየቀ ጉባዔዉን ዉድቅ በማድረግ ዉሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ፍርድ ቤት የጉባዔዉን ውሳኔ እንደ ይግባኝ የሚቀርበዉን ቅሬታ ተከትሎ መርምሮ ዉሳኔ መሰጠቱ የግልግል ጉባዔዉን ቀጣይነት በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ የግልግል ጉባዔዉ የተቃዉሞን አቤቱታ ዉድቅ ያደረገበት መንገድ ተገቢነት በፍርድ ቤት መረጋገጡ ቅሬታዉ አቅራቢዉ በቀጣይ የግልግል ሂደት ላይ የሚኖረዉን እምነት እንዲያስተካከል የማድረግ ዉጤት ይኖረዋል፡፡ ሶስተኛ የግልግል ጉባዔ ውሳኔ በቅሬታ መልክ መቅረቡና መመርምሩ ተቃዉሞን ተከትሎ በግልግል ሂደቱ ላይ ሊፈጠር የሚችለዉን መዝገየት እና መጓተት ያስቀረዋል፡፡
5.2. የግልግል ዳኝነት ወጪ
ለግልግል ዳኝነት በሚያስፈልገዉ ወጪ እና የግልግል አገልግሎት ክፍያን ጉባዔዉ በወጪ አከፋፈል ላይ ጉባዔዉ ሊወሰን እንደሚችልና በዉሳኔዉ ላይ ይግባኝ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚቀርብ በአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 46 ተመላክቷል፡፡ ይህ ከወጪ አከፋፈል ጋር ተገናኘ የሚቀርበዉ ቅሬታ ከወጪ ብዛት እና አለመጣጠን ጋር ተነስቶ የሚቀርብ ነው፡፡ በተለይም በጊዜያዊ ግልግል ጉባዔ ወጥነት ያለዉ የወጪ አከፋፈል ሥርዓት ስለሌለና የተዘጋጀለት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ለችግሩ ምንጭ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ተዋዋይ ወገኖች ከፍርድ ቤት ውጪ ባለ መንገድ አለመግባባታቸዉን ለመፍታት ሲስማሙ የሚያስገኘዉን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ የሚታመን ነው፡፡ ይሁን እንጅ ለግልግል ዳኝነት የሚከፈል ክፍያ ተመጣጣኝ መሆን ካልቻለ አማራጭ የሙግት መፍቻውን ከመጠቀም ይልቅ አለመጠቀም ተመራጭ እንዲሆን ከማድረግ አልፎ በውሳኔዉ ላይ ይግባኝ በማቅረብ የክርክር ሂደቱን እንዲጓተት ምክንያት ይሆናል፡፡ የንግድ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶችም የግልግል ጉባዔ ወጪ አከፋፈል ዉሳኔ ላይ በይግባኝ መመልከታቸዉ የወጪዉን ተመጣጣኝነት በመወሰን ረገድ ላይ ብቻ ሳይሆን የጉባዔውን ቀጣይነት እና ተመራጭነት ላይም የራሱን አስተዋጽዖ ይኖረዋል፡፡
5.3. የግልግል ጉባዔ ስልጣን ላይ የተሰጠ ውሳኔ
ከፍርድ ቤት ውጪ የንግድ ክርክሮችን የሚመለከቱ የግልግል ጉባዔ ስምምነት መኖር አለመኖርን ጨምሮ ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለቸዉ መሆን አለመሆኑን መርምሮ የመወሰን ስልጣን ያላቸው መሆኑን አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 19(1) ተደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ንዑስ (2) መሰረት ጉባዔዉ ክርክሩን ለመመልከት በስልጣኑ ላይ በሰጠዉ ዉሳኔ ላይ የሚቀርበዉን ይግባኝ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመመልከት ስልጣን አላቸዉ፡፡ ይህም ግልግል ጉባዔ አንድን ነገር ለመመልከት ስልጣን አለኝ ወይስ የለኝም በማለት የሚሰጡት ውሳኔ ትክክለኝነት በማረጋገጥ ረገድ ፍርድ ቤቶች ወሳኝ የሆነ ሚና አላቸው፡፡
5.4. የግልግል ዉሳኔን መቃወም
ፍርድ ቤቶች በግልግል በሚታዩ ንግድ ነክ ክርክሮች ላይ በሚሰጡ ዉሳኔ እና አፈጻጸሙ ላይ ላይ በክርክር ተሳታፊ ባልነበር ሰዉ ከይግባኝ በመለስ የሚቀርብን መቃወሚያ የመመልከት ስልጣን ያላቸው መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 123/2013 አንቀጽ 48 ተመላክቷል፡፡ ይህም በመደበኛ ክርክር በክርክሩ ያልተሳተፈ ሰዉ ዉሳኔዉን ለሰጠዉ ፍርድ ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 358 መሰረት የሚያቀርበዉን መቃወሚያ ዓይነት ሲሆን በግልግል ጉባዔ በተሰጠ ዉሳኔ ላይ የሚቀርበዉ መቃወሚያ በመደበኛ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡
በሌላ በኩል በክርክሩ የተሳተፈ ወገን ዉሳኔዉ እንዲሻር የሚያቀርበዉን አቤቱታ ፍርድ ቤቶች አይተዉ የመወሰን ስልጣን አላቸዉ፡፡ የግልግል ዳኝነት እና የዕርቅ አሠራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 በግልግል ጉባዔ የተሰጠን ዉሳኔ መቃወም የሚቻልበትን አግባብ በሁለት መንገድ አስቀምጧል፡፡ የመጀሪያዉ በአንቀፅ 50 በተደነገገዉ መሰረት የሚፈፀም ሲሆን በግልግል ጉባዔ የተሰጠዉን ዉሳኔ ጉዳዩ በግልግል ባይታይ ኑሮ ነገሩን ለመመልከት ስልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት ሊያቀርቡ እንደሚችሉ የሚገልፅ ነዉ፡፡ሁለተኛዉ ዉሳኔዉ እንዳይፈፀም መቃወሚያ ሊቀርብ የሚችለዉ ዉሳኔዉ እንዲፈፀም አፈፃፀም በሚቀርብበት ወቅት ሲሆን በአዋጁ አንቀፅ 52 በዝርዝር ተመላክቷል፡፡ ይህ ዉሳኔዉ እንዲሻር የሚቀርበዉ አቤቱታ ችሎታ በሌለዉ ሰው የተደረገ ስምምነት፣በሕግ ፈራሽ የሆነ ስምምነት ከሆነ፣በግልግል ጉባዔዉ ሹመትና ሂደት አለመሳተፍና አለማወቅ፣ ገለልተኛነትን ወይም ነፃነትን ሳይጠበቅ ዉሳኔ ሲሰጥ፣ በጉባዔዉ አመሰራረትና ሂደቱ ከተዋዋይ ወገኖች ስምምነት እና ከሕጉ ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ ሲደረግ የሚፈፀም ነዉ፡፡ ፍርድ ቤቶችም የሚቀርብላቸዉን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ዉሳኔዉን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሊሽሩት ይችላሉ፡፡ ይህ ዉሳኔ የሚሻርበት ሥርዓት ከመደበኛ ይግባኝ የሚለዬዉ አቤቱታዉን ለማቅረብ መነሻ ከሆኑት ምክንያት እና የሚቀርብት ፍርድ ቤት ጉዳዩ በቀጥታ ቢቀርብ ለመመልከት ስልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት መሆኑ ነዉ፡፡
እንደ መዉጫ!
በአብዛኛዉ የንግድ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የሚነሱ አለመግባባት ከፍርድ ቤት ዉጪ ባሉ የሙግት መፍቻ መንገዶች የሚፈቱበት እድል ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የግልግል ዳኝነት በሀገራችን የሕግ ማዕቀፍ እውቅና ከተሰጠው የረዥም ጊዜ ታሪክ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ዳብሯል ማለት የሚቻል አይደለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የግልግል ዳኝነት አገልግሎት ፍላጎቶች በተለያዩ ምክንያቶች እየጨመረ ሊሄድ የሚችል ነዉ፡፡ የንግድ አለመግባባቶች መጨመር እና ከውጪ ኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር በተገናኘ የኮንስትራክሽን እና መሰረተ ልማት፣ የቴሌኮሙንኬሽን አገልግሎት መስፋፋት፣ የፋይናንስ አገልግሎት፣ የማዕድን እና ኢነርጅ፣ የኤሌክትሮኒክ ንግድ ፣ የዲጂታል ግንኙነቶች መስፋፋት አማራጭ የሙግት መፍቻን ቀዳሚ አማራጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ የግልግል ዳኝነት መደበኛ በሚባል ደረጃ ለአለመግባባቶች መፍትሔ እሰኪሰጥ እና ራሱን ችሎ እስከሚቆም ድረሰ የፍርድ ቤቶች ድጋፍ የግድ ይላል፡፡ በተለይም ከፍርድ ቤት ዉጪ በሚታዩ ጉዳዮችም የግልግል ጉባዔ ከመቋቋሙ በፊት ከሚሰጡ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ ጀምሮ የግልግል ጉባዔ ማቋቋም፣በግልግሉ ሂደቱ የሚነሱ አለመግባባቶችና የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ማስተናገድና መወሰን፣ዉሳኔን ማስፈፀም እና በይግባኝ ትክክለኝነታቸዉን ማረጋገጥ የፍርድ ቤትን ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments