Font size: +
4 minutes reading time (762 words)

መመሪያ የማውጣት ሥልጣን እና ሌሎች ጉዳዮች ከአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ከወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2021 አንጻር ሲታይ

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 1/1995 አንቀፅ 74 እና አንቀፅ 75 የጠቅላይ ሚኒስትሩን እና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን እና ተግባር በቅደም ተከተል አስቀምጧል። የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ከህግ የመነጨ ሥልጣን ሊኖራቸው ስለሚገባ የተቋማቱን ሥልጣንና ተግባራት ለመወሰን በተለያዩ ጊዜያት አዋጆች መውጣታቸው ይታወሳል። የፌደራል መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣንና ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እንዲያስችለው የአስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ (55) መሰረት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን አዋጅ ቁጥር 1097/2018 ወጥቶ ነበር።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2018 ወጥ የሆነ የተቋማት አደረጃጀትና ስያሜ ለመፍጠር ያልቻለ በመሆኑ የተቋማት ቀጣይነትን ለማረጋገጥና የስያሜ ወጥነትን ለማስቀጠል፤ ተቋማት ከሌሎች ተቋማት ሥልጣንና ተግባር ጋር የማይጋጭና ተናባቢ የሆነ ተግባርና ኃላፊነት እንዲኖራቸው ለማድረግ አዋጁ ከወጣ ከሶስት አመት በኃላ በአዲሱ አዋጁ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2021 ተሸሯል።  

የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2021 በስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባው የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በ386 ድጋፍና በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

አዋጁ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ስለሚኒስትሮች ም/ቤት፤ የፌደራል አስፈፃሚ አካላት ስያሜ፤ ስለሚኒስትሮች መቋቋም፣ ሥልጣንና ተግባራት እና የሚኒስትሮች ተጠሪነት፤ ስለ ሌሎች አስፈፃሚ አካላት፤ በሚኒስቴር መ/ቤቶች ወይም በሌላ አስፈፃሚ አካል እና በተጠሪ ተቋማት መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት እንዲሁም አስፈፃሚ አካላትን እንደገና ማደራጀትን በተመለከተ የተለያዩ ክፍሎች ይዟል።

በአዋጁ በክፍል ሶስት የፌደራል አስፈፃሚ አካላት ስያሜ በተመለከተ አንድ ተቋም ሚኒስቴር፤ ኮሚሽን፤ ባለሥልጣን፤ አስተዳደር ወይም ልማት፤ አገልግሎት፤ ፅ/ቤት ወይም ኢንስቲትዩት ተብሎ ሲሰየም ተቋሙ የሚያከናውነው ተግባራትና ሥልጣን፤ ተጠሪነቱ ለማን አንደሚሆን በዝርዝር አስቀምጧል። በአዋጁ አንቀፅ 106 መሰረት ለሚቋቋሙ አስፈፃሚ አካላት ስያሜ ተቋሙ ሊያከናውነው በሚቋቋመው ተግባራት እንዲገደብ ያደርገዋል። ለምሳሌ አንድ ተቋም ኢንስቲትዩት የሚለውን ስያሜ በሚል ለመቋቋም ተቋሙ በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር እና በማማከር አገልግሎት ላይ የሚያተኩር በተቋቋመበት ዘርፍ ልምድ እና ሙያዊ ብቃት ያለው አመራር ያለው መሆን ይጠበቅበታል። ስለሆነም የጥናትና ምርምር ሊሰራ የሚቋቋም ተቋም በ"ባለሥልጣን" ስያሜነት እንዲቋቋም ህጉ አይፈቅድለትም።

ሌላው በአዋጁ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ቁጥር ከ19 ወደ 22 ከፍ የተደረጉ ሲሆን ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትነት የመጡ ሁለት ተቋማት፣ ተጨማሪ ሥልጣን የተሰጣቸው ሚኒስቴር መ/ቤቶችም ይገኛሉ።  ከሚኒስቴር መ/ቤት ውጪ ያሉ ሌሎች አስፈፃሚ አካላት በዚህ አዋጅ የተቋቋሙ ያሉ ሲኖሩ የተቋሞች አደረጃጀት እና ሥልጣንና ተግባራት በሚኒስትሮች ም/ቤት በሚወጣ ደንብ እንደሚወሰን ተቀምጧል። በተጨማሪም የተጠሪነት እና የስያሜ ለውጥ የተደረገባቸው አስፈጻሚ አካላት ይገኛሉ።  

አዲሱ አዋጅ ከዚህ በፊት ከነበረው የፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2018 በተለየ ምን አዲስ ነገር ይዟል የሚለውን ዋና ዋና ጉዳዮችን በዚህ ፁሁፍ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

  1. መመሪያ የማውጣት ሥልጣን በተመለከተ

እንደሚታወቀው ሚኒስቴር መ/ቤቶች በህግ የተጣለባቸውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት መመሪያ ማውጣት ቢያስፈልጋቸው በአዋጅ ወይም በደንብ ሚኒስቴር መ/ቤቱ መመሪያ ማውጣት እንዲችል ሥልጣን መስጠት እንዳለበት ይታወቃል። አስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ 1097/2018 መሰረት በማድረግ ሚኒስቴር መ/ቤቶች መመሪያ ማውጣት አይችሉም ነበር። ይህም አንድ ሚኒስቴር መ/ቤት በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት መመሪያ መውጣት የሚያስፈልገው ጉዳይ በሚኖርበት ጊዜ ተቋሙ መመሪያ ለማውጣት የሥልጣን ምንጭ አዋጅ 1097/2018 ማድረግ አይችልም ነበር። ስለሆነም ሚኒስቴር መ/ቤቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በህግ አግባብ ለመወጣት አዳጋች ሊሆንበት ይችላል። በዚህም ምክንያት በመመሪያ መሸፈን ያለባቸው አንዳንድ ጉዳዮች የህግ ሽፋን ሳይኖራቸው ይቀራሉ።

ይሁን እንጂ በአዲሱ አዋጅ አንቀፅ (19) የሚኒስትሮችን የወል ሥልጣንና ተግባር ባስቀመጠው ንኡስ አንቀፅ (4) ላይ እያንዳንዱ ሚኒስቴር በህግ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችለውን መመሪያ ማውጣት እንደሚችል ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።  

ስለሆነም አንድ ሚኒስቴር መ/ቤት በአዋጁ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት መመሪያ ማውጣት ካስፈለገው መመሪያ የማውጣት የሥልጣን ምንጭ በሌላ አዋጅ ወይም ደንብ መሰጠት ሳያስፈልገው የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2021 መሰረት በማድረግ መመሪያ ማውጣት እንዲችል ሥልጣን ተሰጥቶታል።

ይህም ሚኒስቴር መ/ቤቶች በአዋጁ የተሰጣቸውን ተግባር እና ኃላፊነት ለመወጣት የህግ ማእቀፍ ለሚያስፈልጓቸው ጉዳዮች መመሪያ በማውጣት የተቋቋሙበትን አላማ በአግባቡ እንዲወጡ ያስችላቸዋል።  

  1. በሚኒስቴር መ/ቤቶች ወይም በሌላ አስፈፃሚ አካል እና በተጠሪ ተቋማት መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት በተመለከተ

በተለምዶ አንዳንድ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ወይም አስፈፃሚ አካል በስራቸው የሚገኙትን ተጠሪ ተቋማትን የሚያዩት የተቋማቸው አንዱ የስራ ክፍል ወይም የዋናው መ/ቤት ቅርንጫፍ አድርገው ነው እንጂ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት እንደሆኑ አድርገው አይመለከቱም። በዚህም ምክንያት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ወይም አስፈፃሚ አካል በተጠሪ ተቋማት የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ጣልቃ እንዲገቡ ክፍተት ሲፈጥር ነበር። በሚኒስቴር መ/ቤቶች እና በተጠሪ ተቋማት መካከል የሚኖረው ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት በህግ የተቀመጠ ነገር አልነበረም።

ይሁን እንጂ በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ወይም ሌላ አስፈፃሚ አካል እና በተጠሪ ተቋማት መካከል ስለሚኖር ግንኙነት በአዲሱ አዋጅ በክፍል 6 ተደንግጓል። በአዋጁ አንቀፅ(77) ላይ እንደተቀመጠው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ወይም ሌላ አስፈፃሚ አካል የተጠሪ ተቋሙን የሰው ኃይል አስተዳደር፣ የፋይናንስ አስተዳደርና መሰል ስራዎችን እንደሚያከናውን፣ ስራዎች ከመምራት፤ ከማስተባበር እና ከመደገፍ ውጪ በእለት ከእለት እንቅስቃሴው ላይ ጣልቃ እንደማይገባ በግልፅ አስቀምጧል።

ማጠቃለያ

የግልፅነትና ተጠያቂነት መርሕ እውን እንዲሆን የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር በህግ መወሰን እና በግልፅ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም በአዋጁ የአስፈፃሚ አካላት ስያሜ በተመለከተ በዝርዝር መቀመጡ ተቋሙ ሊያከናውነው በሚቋቋመው ተግባራት እንዲገደብ ያደርገዋል። ይህም የተቋሙ ተግባርና ኃላፊነት ከሌሎች ተቋማት ሥልጣንና ተግባር ጋር የማይጋጭ እንዲሆን ያደርገዋል።

ሌላው አዋጁ በሚኒስቴር መ/ቤት ወይም በአስፈፃሚ አካል እና በተጠሪ መካከል የሚኖረውን ግንኙነት በግልፅ ማስቀመጡ በመካከላቸው ጤናማ የሆነ የስራ ግንኙነት እንዲኖር ይረዳቸዋል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የውል ሕግ ይርጋዎች ከተመረጡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳ...
ስለ ይዞታ እና የቀዳሚነት ግዥ ይገባኛል የማለት መብት

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 16 July 2024