Font size: +
4 minutes reading time (797 words)

የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መቁረጥ እና ሕጋዊነቱ

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ገበታ ለሃገር መርሃግብር የመንግሥት ሠራተኞች የወር ደሞዛቸውን ለገሱ የምትል ዜና በተደጋጋሚ በመስማቴ እና እውነት በዚህ የኑሮ ውድነት እነዚህ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዛቸውን የሚለግሱት ጎርጎራ፣ ወንጪ አሊያም ኮይሻ  ላይ ሆቴል መሰራቱ ከጊዚያዊ ችግሮቻችን ይበልጣል ብለው አምነው ወይስ በአለቆቻቸው ተፅዕኖ ሥር በመሆናቸው ተገድደው የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ውስጤ ሲመላለስ በመቆየቱ ነው፡፡ መልካም ንባብ!

ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ምስጋና ይግባቸውና አይነ-ግቡ የሆኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከቤተ-መንግሥታቸው ጀምረው እየገነቡልን ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ስራዎች የሃገርን ገፅታ ከመገንባት ጀምሮ ታሪክን ጠብቆ በማቆየት በቱሪዝም እንደሃገር የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው መሆናቸው በስፋት ይጠቀሳል ይሁን እንጂ በተቃራኒው ቅንጦት ነው፣ በዚህ ሰዓት ሰላም እና በልቶ ማደር እንጂ ቅንጡ ሆቴል የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ከቁጥር አይገባም ስለሆነም ያለጊዜው የመጣ ፕሮጀክት ነው በማለት የሚተቹትም አልጠፉም፡፡

ቤተመንግሥትን ከማስዋብ የተጀመረው ፕሮጀክት አሁን አድማሱን አስፍቶ ሃገራዊ ቅርፅን በመላበስ በሶስት ክልሎች ማለትም አማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ያሉ የመስህብ ስፍራዎችን ወደማልማት ተሸጋግሯል፡፡ ለዚህም እውን መሆን ገበታ ለሃገር በሚል በገቢ ማሰባሰቢያ መልክ የ10,000,000 ብር እና 5,000,000 ብር የሚከፈልበት እራት ግብዣ በጠቅላያችን ተሰናድቷል፡፡ በዚህ አላበቃም በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት ዜጋው ልቡ በፈቀደ መጠን ገንዘብ እንዲለግስ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ተዘጋጅቷል፤ የባንክ አካውንትም በተለያዩ ሚዲያዎች ይፋ በማድረግ ገቢ ማሰባሰብ ስራው ቀጥሏል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ይፋ ሲደረግ ያልተገለፀ ነገር ግን በተግባር እየሆነ ያለ አንድ እውነት አለ፡፡ ይህም የመንግሥት ሠራተኛው ለፕሮጀክቱ የወር ደሞዙን እንዲሰጥ ማድረግ፡፡ የእንትን ሚኒስቴር ሠራተኞች እና አመራሮች ለገበታ ለሃገር የወር ደሞዛቸውን ለገሱ የሚል ዜና በየዕለቱ እየሰማን ነው፡፡ ለመሆኑ የሠራተኛ ደመወዝ የሚቆረጠው እንዴት ነው?፣ አንድ የስራ ሃላፊ ስለፈለገ ወይም መስሪያቤቱ አመራሮች ተወያይተው ስላፀደቆ የሠራተኛን ደመወዝ መቁረጥ ይቻላል እንዲቆረጥብን አንፈልግም የሚሉ ሠራተኞች ሲኖሩ እንዴት ይደረጋል?፣ የሚሉ ጥያቄዎች በዚህ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት ይሞከራል፡፡

 

የመንግሥት ሠራተኛ ማነው፡-

እንደኢትዮጵያ ባሉ ፌደራሊዝም ሥርዓትን በሚከተሉ ሃገራት ሁለት መንግሥታት አሉ፡፡ እነዚህም የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ይሰኛሉ፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ የመንግሥት ሠራተኛ ስንል በእነዚህ መንግሥታት ሥር ተቀጥረው የሚሰሩትን የሚያካትት ነው፡፡ ፌደራል መንግሥቱም ሆነ ክልሎች ቀጥረው የሚያሰሯቸውን ሠራተኞች የሚያስተዳድሩባቸው አዋጆች አውጥተው ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ አላማ ስንል የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 እናያለን፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶች ሥር የሚሰሩ ሠራተኞች የሚተዳደሩበት ህግ በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 ይሰኛል፡፡ እነዚህ ሠራተኞች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከመንግሥት አስተዳደራዊ ቁጥጥር ውጪ ባለመሆናቸው እና ቀጣሪያቸው መንግሥት በመሆኑ ለዚህ ጽሑፍ አላማ ሲባል የመንግሥት ሠራተኛ ልንላቸው እንችላለን፡፡

የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ የሚቆረጠው በምን አግባብ ነው?

የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 በፌደራል መንግሥቱ ሥር ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች የሚተዳደሩበት ህግ ነው፡፡ በዚህ ህግ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በምን አኳኋን ሊቆረጥ እንደሚችል በግልፅ አስቀምጧል፡፡ የአዋጁ አንቀፅ 9 (2) የደመወዝ ክፍያ በሚለው ርዕስ እንዲህ ይነበባል፡፡

የማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ፣

ሀ)   ሠራተኛው ስምምነቱን በጽሑፍ ሲገልጽ፣

ለ)   በፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣

ሐ)   በሕግ በተደነገገው መሠረት፣

ካልሆነ በስተቀር ሊያዝ ወይም ሊቆረጥ አይችልም፡፡

አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ደግሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚተዳደሩበት ህግ ነው ይህም የህግ ማዕቀፍ ከቀደመው ጋር በተመሳሳይ የሠራተኛን ደመወዝ አሰሪው ሊቆርጥ የሚችለው ሠራተኛው በጽሑፍ ሲስማማ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡

ከላይ ካሉት ድንጋጌዎች መረዳት የምንችለው አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የደሞዜ ይሄን ያህን ፐርሰንት ይቆረጥብኝ ብሎ በጽሑፍ ወይም በፊርማው ስምምነቱን ካላረጋገጠ ሊቆረጥበት እንደማይችል ነው፡፡ የመንግሥት መ/ቤቶች ለተለያዩ መዋጮዎች የሠራተኛውን ደመወዝ ሲፈልጉ ምን ያህሉን ሠራተኛ "ደመወዝህን ልቆርጥብህ ስለሆነ ትስማማለህ ወይ?" ብለው ይጠይቃሉ? ይህም ቢሆን መስማማቱ ብቻ አይደለምና ምን ያህሉ ነው ስምምነቱን በፊርማው አረጋግጦ ደሞዙ የሚቆረጠው? ጭራሽ ሳይሰሙ እና ሳያውቁ ደሞዛቸው የተቆረጠባቸውስ የሉም? ወይ የሚሉትን እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ለአንባቢ እተዋለው፡፡ 

አቶ አንበሴ የሚሰሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚሰኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት ውስጥ ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል  ከሳቸው ጋር ባደረኩት ቆይታ ከፍቃዳቸው ውጪ እንዴት ደሞዛቸው እንደተቆረጠ የሚከተለውን ብለዋል፡- "እንኳን ደሞዛችሁ ሊቆረጥ ነው ፈቃደኛነታችሁን በጽሑፍ ግለፁ ተብለን ልንጠየቅ ቀርቶ ምንም አይነት ውይይት አላደረግንም፡፡ እንዳውም እንደሌላ ሰው በዜና ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኞች እና አመራሮች ለገበታ ለሃገር መርሃግብር የአንድ ወር ደሞዛቸውን በማዋጣት 102,000,000 (አንድ መቶ ሁለት ሚሊዮን) ብር ገቢ አደረጉ የሚል ዜና ሰማን፡፡" ከላይ ከጠቀስናቸው የህግ ድንጋጌዎች አንፃር ስንመዝነው ይህ አካሄድ ሙሉ ለሙሉ ከህግ ውጪ የሆነ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አላማም ከፍቃዳቸው ውጪ ከሰዎች ጉሮሮ ገንዘብ መንጠቅ ነው ብዬ አላምንም፡፡

ደሞዙ ከፍቃዱ ውጪ የተቆረጠበት የመንግሥት ሠራተኛ ምን ማድረግ ይችላል

የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 79 የመንግሥት ሠራተኞች መብቴ ተጣሰ ብለው የሚያቀርቧቸውን የስራ ክርክር ክሶችን የሚዳኝ የአስተዳደር ፍርድ ቤት ተቋቁሟል፡፡ ይህ ፍርድ ቤት ከሚያያቸው ጉዳዮች መካከል ከህግ ውጪ የደመወዝ መያዝ ወይም መቆረጥ አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም ከላይ በተገለፀው አኳሃን በጽሑፍ ስምምነቱን ሳይገልፅ ደሞዙ የተቆረጠበት የመንግሥት ሠራተኛ ቀጣሪውን መ/ቤት በአስተዳደር ፍ/ቤት ቀርቦ መክሰስ እና የተቆረጠበትን ደሞዙን ማስመለስ እንደሚችል ህጉ ያስቀምጣል፡፡ በተመሳሳይ ለመንግሥት የልማት ድርጅት ሠራተኞችም በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት የስራ ክርክር ጉዳዮችን የማየት ስልጣን በተሰጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመቅረብ ከፈቃዴ ውጪ ደሞዜ ተቆርጧል የሚል ክስ አቅርቦ ገንዘቡን ማስመለስ ይችላል፡፡

 

ማጠቃለያ

የመንግሥት ሃላፊዎች የሚወስኗቸው እያንዳንዱ ውሳኔዎች ህግን መሰረት ያደረገ መሆኑን ማረጋገጥ ለሚመሩት ተቋምም ሆነ ለሚያስተዳድሩት ሠራተኛ ደህንነት መጠበቅ እጅግ ወሳኝ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በአንዳንድ ሃገራት በዓላትን አስታኮ በቦነስ መልክ ሠራተኞች የሚያወጧቸውን ወጪዎች እንዲሸፍኑ የ2 እና 3 ወር ደመወዝ መስጠት የተለመደ አሰራር ነው ይሁን እንጂ በእኛ ሃገር ነባራዊ ሁኔታ የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደሩ የሠራተኛውን ደመወዝ ፈቃዱን ሳይጠይቁ መቁረጥ ከህግ ውጪ ከመሆኑም ባሻገር በስራው እርካታ የራቀውን ሠራተኛ ከመፍጠር አልፎ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ሠራተኛውም በመሪዎች ተፅዕኖ ሥር ወድቆ በጀርባ ሆኖ ከማጉረምረም ይልቅ መብቱን እና ግዴታውን ጠንቅቆ በማወቅ በህግ ለተሰጠው መብት መታገል እና ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Major Departures of the New Micro-Finance Business...
Fly-by-Night: A Brief Overview of the Federal Cour...

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - Bonsa File on Thursday, 27 June 2024 11:56

የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 79 የመንግሥት ሠራተኞች መብቴ ተጣሰ ብለው የሚያቀርቧቸውን የስራ ክርክር ክሶችን የሚዳኝ የአስተዳደር ፍርድ ቤት ተቋቁሟል፡፡ ይህ ፍርድ ቤት ከሚያያቸው ጉዳዮች መካከል ከህግ ውጪ የደመወዝ መያዝ ወይም መቆረጥ አንዱ ነው፡፡
ከላይ ያስቀመጥኩት ለመንግስት ሰራተኞች ብቻ ነው የግል ሰራተኞችንም ይጨምራል እባኪህን በ ኢመይል በኩልም ሆነ በኮመንት በኩል ብተመልስልኝ ደስ ይለኛል። አመሰግ

የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 79 የመንግሥት ሠራተኞች መብቴ ተጣሰ ብለው የሚያቀርቧቸውን የስራ ክርክር ክሶችን የሚዳኝ የአስተዳደር ፍርድ ቤት ተቋቁሟል፡፡ ይህ ፍርድ ቤት ከሚያያቸው ጉዳዮች መካከል ከህግ ውጪ የደመወዝ መያዝ ወይም መቆረጥ አንዱ ነው፡፡ ከላይ ያስቀመጥኩት ለመንግስት ሰራተኞች ብቻ ነው የግል ሰራተኞችንም ይጨምራል እባኪህን በ ኢመይል በኩልም ሆነ በኮመንት በኩል ብተመልስልኝ ደስ ይለኛል። አመሰግ
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 25 July 2024