መፈንቅለ መንግሥት ከጥንታዊ የሥልጣኔ ባለቤት ሃገራት ጀምሮ በታሪክ የሚታወቅ ሕዝብን እየመራ ባለ የመንግሥት ወይም የገዢ አካል ላይ የሚደረግ ከሥልጣን የማዉረድ ሁኔታ ሲሆን የበርካታ ሃገራት የታሪክ አካልም ነዉ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ዋነኛ መነሻ የሆነዉ የመፈንቅለ መንግሥት ጽንሰ ሃሳብ እና ትርጓሜዉ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሚሰጠዉ ትንታኔ ከምን አንጻር የታየ እንደሆነ በዉል ባይታወቅም አብዛኞቹ ይህን መሰል ድረጊቶች መፈንቅለ መንግሥት ነዉ የሚል ስያሜ ሲሰጣቸዉ እንመለከታልን፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ጽንሰ ሃሳብ ምንድነዉ? መገለጫዎቹ ምን ምንድናቸዉ? የአፍሪካ ኅብረት የሕግ ማዕቀፍ ምን ይላል? በፌደራላዊ የመንግሥት ሥርዓት ተከታይ ሃገራት በፌዴሬሽኑ አባላት ዉስጥ የሚከናወኑ የሥልጣን ቅምያ ሙከራዎችንስ መፈንቅለ መንግሥት ልንላቸዉ ይቻላል? እንመልከት፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ጽንሰ ሃሳብ

መፈንቅለ መንግሥት ወይም በእንግሊዘኛ መጠሪያዉ coup d’etat ከፈረንሳይ የተወሰደ ቃል ሲሆን ፍቺዉም blowing state ወይም መንግሥትን መበታተን የሚለዉን ትርጓሜ የያዘ እንደሆነ መጽሃፈት ያስቀምጣሉ፡፡ ይኸዉም በሥልጣን ላይ ያለን መንግሥት ወይም ገዢ በጉልበት ሳይታሰብ ከሥልጣን መጣል መሆኑን እንደሚያመላክት ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሰዉን የፈረንሳይኛ ፍቺ የያዘ ቢሆንም በበርካታ ጽሁፎች እና መሰል ሰነዶች ላይ ወጥ እና ተመሳሳይ አይነት ትርጉም ማግኘት ያስቸግራል፡፡ የኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ መዝገበ ቃል 2ኛዉ ዕትም  በተመሳሳይ ሁኔታ  ቃሉን ሲተረጉም በሥልጣን ላይ ያለን መንግሥት አነስተኛ በሆነ ቡድን ወይም አካል በድንገት ከሥልጣን ማዉረድ ነዉ በሚል ይፈታዋል፡፡

“Coup d’état, also called coup, the sudden, violent overthrow of an existing government by a small group..

በዘመናዊ የመፈንቅለ መንግሥት ታሪክ የ1799ኙ የፈረንሳዩ ናፖሊዎን መፈንቅለ መንግሥት እንዲሁም የ1851ዱ የሉዊስ ናፖሊዎን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ከ20ኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮም በደቡብ አሜሪካ ፣ በእስያ እና በአፍሪካ መፈንቅለ መንግሥት ባሕሪዉን እና መገለጫዉን እቀየረ እየተበራከተ መምጣቱን መመልከት ይቻላል፡፡ በተለይ በደቡብ አሜሪካ እና እስያ ከቀዝቃዛዉ የዓለም ጦርነት ጋር ተያይዞ  በአፍሪካ ደግሞ ከቀኝ ግዛት ነጻነት ማግስት በአህጉሪትዋ በስፋት ታይቷል፡፡ በአለም ባንክ የ1991 የዓለም እድገት ሪፖርት መሰረትም እያደጉ ባሉ ሃገራት በአማካይ በአምስት አመት ዉስጥ አንድ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንደሚካሄድ በተቋሙ ሪፖርት ሰፍሯል፡፡

መፈንቅለ መንግሥት በምን ይገለጻል?

ከላይ ከተቀመጡት ትርጓሜ በመነሳት ምንም እንኳን ወጥ የሆነ የጉዳዩ ጽንሰ ሃሳብ ሰፈሮ እና ተተንትኖ ባይገኝም ካሉት ሰነዶች በመነሳት መፈንቅለ መንግሥት በምን ይገለጻል ወይም መፈንቅለ መንግሥት ልንል የምንችለዉ ምን ምን ነጥቦች ሲሟሉ ነዉ የሚለዉን ከተለያዩ ዕይታዎች የጋራ የሆኑ ሶስት ነጥቦችን እንመልከት፡-

1ኛ. የፖለቲካ ቡድን ወይም የሽምቅ ተዋጊ (existence of a small group or political faction or military power)

መፈንቅለ መንግሥት ተደርጓል  ወይም ደግሞ ድርጊቱ መፈንቅለ መንግሥት ነዉ የሚለዉን ስያሜ ለማግኘት በቀዳሚነት መኖር እንዳለበት የሚጠበቅ ነጥብ የድርጊቱን ዉጤት የሚፈልግ ወይም ድርጊቱ ከተሳካ በኋላ ያሰበዉን ለማስፈጸም የተዘጋጀ ወይም ለመፈጽም ያቀደ አካል መኖር ነዉ፡፡ ይህ አካል ወይም ቡድን ብለን ልንጠራዉ የምንችለዉ በመንግሥት መዋቅር ዉስጥ አልያም ከመዋቅር ዉጭ ያለ የፖለቲካ ቡድን፣ የሽምቅ ተዋቂ ወይም ወታደራዊ ሃይል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሃይል በተለምዶ በረጅም ወይም በአጭር ግዜ እቅድ መንግሥትን ለመጣል ያሰበ በህቡዕ የተደራጀ ሃይል ነዉ፡፡ ይህ አካል ሳይኖር ወይም ተደራጅቶ ያቀደዉ እቅድ ሳይኖር መንግሥት ግልበጣን ማሰብ ከባድ እና አዳጋች ነዉ፡፡

2ኛ.  ሃይልን መጠቀም

ድርጊቱ በሚፈጸምበት ወቅት ዋነኛ ማሳኪያ ተደርጎ በበርካታ የመፈንቅል መንግሥት ክንዉኖች ዉስጥ የሚወሰደዉ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ መሰረታዊ ነጥብ ሃይልን መጠቀም ሲሆን ይህም በከፊል ወይም በሙሉ ሉዓላዊ በሆነች ሃገር ያለን የመከላከያ ወይም የፖሊስ ወይም የደህንነት መዋቅር  መቆጣጠር  እንደሆነ በርካታ ጽሁፎች ይስማሙበታል፡፡ እንደ ኢንሳይክሎፒድያ ትንተናም ጉልበትን መጠቀም ከቀዳሚ ሁኔታዎች አንዱ እንደሆን ያሰቀምጣል፡፡

“. . . the chief prerequisite for a coup is control of all or part of the armed forces, the police, and other military elements.”

ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ36ኛዉ የሎሜ መደበኛ ጉባኤ “ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥት ለዉጥን” (OAU response on un constitutional change of government)    እና የአህጉሪቱን የፖለቲካ ለዉጦች በተለይም የዲሞክራሲ ግንባታ አስመልክቶ  ተወያይቶ ባስቀመጠዉ ማዕቀፍ መፈንቅለ መንግሥት የሚለዉን ስያሜ “ሕገ-መንግሥታዊ አካሄድን ያልተከተለ የመንግሥት ለዉጥ” ብሎ አቻ መጠሪያ የሰጠዉ ሲሆን ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ ወታደራዊ ሃይልን በመጠቀም በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን ዕውቅና ያለዉ መንግሥት መጣል የመጀመሪያዉ የመፈንቅለ መንግሥት መገለጫ ወይም ድርጊቱ መፈንቅለ መንግሥት ነዉ ተብሎ አንዲጠራ እንደሚያደርገዉ አስቀምጧል፡፡ ከድርጅቱ ማዕቀፍ አንጻር በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት ብቻ ብሎ ማሰቀመጡ ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ባልተከተለ ሁኔታ ወደ ሥልጣን መጥተዉ በመንግሥት ግልበጣ በሃይል የተገረሰሱ መንግሥታት የወረዱበትን መንገድ መፈንቅለ መንግሥት አይደልም የሚል ፍቺ የሚሰጥ በመሆኑ ትርጓሜዉን ያጠበበና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ የሚመረጡ መንግሥታት ላይ የሚቃጣን ድርጊት ከላል የሚሰጥ እንደ ሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

በመሆኑም ከላይ በተቀመጠዉ መሰረት ሃይልን መጠቀም ሌላዉ ዋነኛ ሁኔታ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

3ኛ. ድንገታዊነት (it is a sudden act)

በዓለም ላይ የተከናወኑ የተሳኩ ወይም ያልተሳኩ የመንግሥት ግልበጣዎች በታሪክ እንደሚያሳዩት ድርጊቱ ተወጥኖ እሰኪፈጸም ድረስ በህቡዕ በተደራጀ ሃይል በድንገት የሚፈጸም መሆኑን ነዉ፡፡ ይህም መፈንቅለ መንግሥቱ እንደሚከናወን ግንዛቤ ያላቸዉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያዉቁ የቡድኑ አባላት በታቀደዉ ግዜ ለመፈጸም የሚያሰችላቸዉን ዝግጅት ካጠናቀቁ በኋላ በሥልጣን ላይ ያለዉን መንግሥት ያወርዱታል፡፡ ይህንን በርካቶች እንደ አንደ መስፈርት የሚወስዱት ቢሆንም እንኳን ይህ ቅድመ ሁኔታ በሽምቅ ዉግያ በረጅም ግዜ ሂደት ወደ ከተማ በመግባት ሥልጣን የሚይዙ ሃይሎችን ከላይ በተጠቀሰዉ መልኩ አካቶ ያስረዳል ወይ ብለን የተመለከትን ከሆነ አጠያያቂ ነዉ፡፡

ይሁንና በርካቶች እንደሚስማሙበት እና እንደሚያሰቀምጡት ሽምቅ ተዋጊዎችም ቢሆን ወደ ከተማ ገብተዉ ሥልጣን የሚቆጣጠሩበት ሁኔታ ድብቅነትና ድንገተኝነቱ ከላይ ከተቀመጡት አንጻር ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በተወሰነ መልኩ መሆኑ አይቀሬ ስለሆነ ድንገተኛነቱን (the sudden act) እንደ አንድ መንግሥት ግልበጣ መገለጫ ወይም ቅድመ ሁኔታ መቆጠር የማይቀር ነዉ ብለዉ ይመለከቱታል፡፡

የተለየዉ የአፍሪካ ኅብረት ዕይታ

ከላይ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ እንደሰፈረዉ መፈንቅለ መንግሥት የዓለማችን አንዱ የሃገራት የፖለቲካ ታሪክ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን በዘመናዊ የሰዉ ልጅ የሕዝብ አስተዳደር በተለይም ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች እና ከቀዝቃዘዉ የዓለም ጦርነት በኋላ የተለመደ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ይህ የመንግሥት ሥርዓት ግልበጣ መልኩ እና ባህሪዉ ከሃገራት ሃገራት የተለያየ ቢሆንም በአፍሪካ የተከናወኑ በርካታ የመንግሥት ግልበጣዎች የሚያመሳስላቸዉ ጉዳዮች አሉ፡፡ አህጉሪቱን ከቀኝ ግዛት ለማላቀቅ ሲደረጉ የነበሩ ትግሎችን እንደ መነሻ ወስደን ያየን እንደሆነ ከቀኝ ገዢዎቻቸዉ ነጻ የወጡ ሃገራት የመሰረቷቸዉ መንግሥታት እና እነሱን የተኩ በርካቶች በዚሁ የመንግሥት ምሰረታ የተዋቀሩ ናቸዉ፡፡

በዚህ መሰርት ከላይ የተቀመጡ ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆኖ የቀደሞዉ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት በሃይል የሚደረግ የመንግሥት ግልበጣን “ Un constitutional change of government’’ በሚል ስያሜ ከመስጠት ባሻገር መፈንቅለ መንግሥት የሚለዉን ጽንሰ ሃሳብ ዕዉቅና የሰጠበት አግባብ ለየት ያሉ አህጉራዊ እይታዎች አሉት፡፡ ድርጊቱን ከዴሞክራሲያዊ ሃገር ግንባታ ጋር የሚያይዘዉ ህብረቱ የሚከተሉትን ነጥቦች ያስቀምጣል፡-

In order to give practical effect to the principles we have enunciated, we have agreed on the following definition of situations that could be considered as situations of unconstitutional change of government:

  1. military coup d'etat against a democratically elected Government;
  2. intervention by mercenaries to replace a democratically elected Government;
  3. replacement of democratically elected Governments by armed dissident groups and rebel movements;
  4. the refusal by an incumbent government to relinquish power to the winning party after free, fair and regular elections.

ኅብረቱ ካሰቀመጠዉ ነጥቦች አንጻር ሁለት ለየት ያሉ ምልከታዎችን አካቷል፡-

1ኛ. ድርጊቱ የሚፈጸመዉ በወታደራዊ አካል ወይም ሃይል ብቻ መሆኑ እና

2ኛ. በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ መሰረት ነጻ፣ ገለልተኛ እና በግዜ ገደቡ መሰረት በተከናወነ ምርጫ ላሸነፈ አካል ሥልጣንን አለቀም ማለተንም እንደ መፈንቅለ መንግሥት የሚቆጥረዉ መሆኑን ነዉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በሁለተኝነት ያሰቀመጠዉ (intervention by mercenaries to replace a democratically elected overnment) እንደ ማሊ ያሉ ሃገራት በዉጭ ሃገራት ሙሉ ድጋፍ ከሥልጣን የወረዱ የቶማስ ሳንካራ ዓይነት የመንግሥት ግልበጣዎችም በመንግሥት ግልበጣነት ዕዉቅና የሚሰጥ ይመስላል፡፡

ከላይ በተቀመጠዉ ሃሳብ መሰረት ህብረቱ መፈንቅል መንግሥት ተከናዉኗል ብሎ ሊያመንባቸዉ የሚችልባቸዉ ጉዮች በዚህ መልኩ የተገደቡ መሆናቸዉ ምናልባትም ሕገ-መንግሥት ሳይኖራቸዉ ወደ ሥልጣን የወጡ በርካታ የአህጉሪቱን መንግሥታት፣ የቀድሞ ቡድኖች ወይም ሽምቅ ተዋጊዎች እንዲሁም በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተሸነፉ መንግሥታትን በሃይል ከሥልጣን ለማዉረድ የሚደረግዉ  ሁኔታስ እንዴት ያየዋል ለሚለዉ ህብረቱ በዝርዝር ያስቀመጠዉ እና እየተተገበረ ያለ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል ነገር የለም፡፡

ማጠቃለያ

መፈንቅል መንግሥት ወይም የአፍሪካ ኅብረት አንዲመያስቀምጠዉ ሕገ-መንግሥታዊ አካሄድን ባልተከተለ መልኩ ሥልጣን ለመያዝ መሞከር ወይም መያዝ የሚለዉ ጽንሰ ሃሳብ በበርካታ ጽሁፎች እና ዘገባዎች የድርጊቱን መስፈርት ወይም መገለጫዎቹ ምን እንደሆኑ በዝርዝር ሳይታወቅ መፈንቅለ መንግሥት ወይም የመንግሥት ግልበጣ ብሎ መሰየም የተለመደ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ወጥ፣ ያለቀለት ትርጓሜና መገለጫ የተቀመጠለት ባይሆንም ጽንሰ ሃሳቡ ምን ምን ነጥቦችን በአማዛኙ ሲያሟላ መንግሥት ግልበጣ የሚለዉ ስያሜ ሊሰጠዉ እንደሚገባ እንደመነሻ ለማብራራት ተሞክሯል፡፡ ስለሆነም ጽንሰ ሃሳቡን ከላይ ከተቀመጡት መገለጫዎች ዉጭ የሚከናወኑ ድርጊቶችን ሁሉ መፈንቅለ መንግሥት ነዉ ብሎ መቀበል አስቸጋሪ ከመሆኑ ባለፈ ስያሜዉን ተከትሎ የሚያመጡት አሉታዊ የሃገራት የዉስጥ ፖለቲካ ቀዉስ በርካታ ነዉ፡፡

በሃገራችን ነባራዊ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በአህዳዊ የመንግሥት ሥርዓት ግዚያቶች ከተከሰቱት የመንግሥት ግልበጣ ባህሪያቶች አንጻር ሲታይ እየተከተልን ካለዉ የመንግሥት ሥርዓት በፌዴሬሽኑ አባል ሃገራት የዉስጥ ችግሮችን እና የሚፈጠሩ ቀዉሶችን መፈንቅለ መንግሥት የሚል ስያሜ ሲሰጣቸዉ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ በጽሁፉ ከተዘረዘሩት መነሻዎች አንጻር በሶስቱ መገለጫዎች ድርጊቶቹን ስንመዘን የማያሟሉ ነጥቦች እንዳሉ መመልከት ይቻላል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት የመንግሥት አዋቃቀር መንፈስ በመነሳት የሃገርን ቁመና ይዞ ያለዉ የፌደራል መንግሥት ሥልጣን ህልዉና አደጋ ላይ ሳይወድቅ እና ለሃገርም ስጋት ሆኖ ሊታይ የሚችል ሁኔታዎች በሌሉበት በተጠቀሰዉ መልኩ መሰል ድርጊቶችን መሰይም የሚያመጣዉ የፖለቲካ እና የሕግ ትርጓሜ የተዘባ ያደርገዋል፡፡

ስለሆነም ከላይ በተቀመጠዉ መልኩ በአመዛኙ በመነሻነት ለመመልከት መሞከር የተሻለ ይሆናል፡፡