የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ የተሰጠው ሰው እና በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ የግብር ግዴታ

መግቢያ

ማንኛውም ገቢ የሚያገኝ ሰው በፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 እና በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 መሰረት ግብር የመክፈል ኃላፊነት አለበት፡፡[1] በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ሰው ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት፤ በኢትዮጵያ ነዋሪ ላልሆነ ሰው የትርፍ ድርሻ፣ የንዑስ ሥራ ተቋራጭ፣ የወለድ፣ የሮያሊቲ፣ የሥራ አመራር፣ የቴክኒካል፣ የመድን አረቦን፣ ወደ ውጭ አገር የሚላክ ትርፍ፣ እንዲሁም የሌሎች ገቢዎች ክፍያ ሲፈጽሙ ከጠቅላላ ክፍያው ላይ በግብር ሕጉ መጣኔ መሰረት ግብር ቀንሰው መያዝ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡[2] በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ሰው ወይም በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ከመቀጠር ከሚገኝ ገቢ፣ ከትርፍ ድርሻ ወይም ካልተከፋፈለ ትርፍ፣ ከወለድ፣ ከሮያሊቲ፣ እና ከሌላ በአገር ውስጥ ከሚፈጸም ክፍያ ላይ በግብር ሕጉ መጣኔ መሰረት ግብር ቀንሰው መያዝ አለባቸው፡፡[3]

ግብር ቀንሶ የማስቀረት ግዴታ ያለበት ሰው ቀንሶ የያዘውን ግብር በ30 ቀናት ውስጥ ለሚኒስቴሩ[4] መክፈል ያለበት ሲሆን፤ ይህንን ግዴታ ያልተወጣ ሰው መከፈል የሚኖርበትን ግብር በተመለከተ ኃላፊ ነው፡፡[5] የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ የተሰጠው ሰው እንደማንኛውም ታክስ ከፋይ ከሚያገኘው ገቢ ላይ ግብር የመክፈል እና ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ግብር ቀንሶ በመያዝ ለሚኒስቴሩ ገቢ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ፤ ፈቃድ የተሰጠው እና ሰው ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ማነው? የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ የተሰጠው ሰው የግብር ግዴታ ምንድነው?  ፈቃድ የተሰጠው ሰው ለንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ክፍያ ሲፈጽም ቀንሶ የሚይዘው የግብር መጣኔ ምን ያህል ነው? እንዲሁም በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ያለበት የግብር ኃላፊነት ምን ይመስላል? ለሚሉ ጥያቄዎች ዝርዝር ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል፡፡

ቃድ የተሰጠው ሰው ማነው?

ከ2008 ዓ/ም በፊት የማዕድን ሥራዎች ገቢ ግብር ከሌላው የገቢ ግብር ተለይቶ፤ እራሱን ችሎ በአዋጅ ቁጥር 53/1985፣ በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 23/1988 እና 802/2005 ተደንግጎ የነበረ ቢሆንም፤ የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 በምዕራፍ አራት ከአንቀጽ 36 እስከ 44 ስለማዕድን እና ነዳጅ ሥራዎች ግብር በመደንገግ፤ ሁሉም ገቢዎች በአንድ አዋጅ ስር በማጠቃለል ግብር ጥሏል፡፡

የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጁ የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ የተሰጠውን ሰው “ፈቃድ የተሰጠው ሰው” በሚል ትርጓሜ የሚሰጠው ሲሆን የማዕድን መብት ደግሞ ከማዕድን ሥራዎች በተገናኘ በመንግስት የሚሰጥ የቅኝት፣ የምርመራ፣ ፈቃድን ይዞ የመቆየት ወይም የማዕድን ማምረት ፈቃድ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡[6] በዚሁ የገቢ ግብር አዋጅ ድንጋጌ፤ ፈቃድ የተሰጠው ሰው ግለሰብ፣ ድርጅት፣ መንግስት፣ የመንግስት አስተዳደር አካል ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅት ሊሆን እንደሚችል የተደነገገ ሲሆን፤[7] የማዕድን ሥራዎች አዋጁም ሰው ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው[8] ሲል ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ስለሆነም ፈቃድ የተሰጠው ሰው የማዕድን ሥራዎችን ለማከናወን በመንግስት ፈቃድ የተሰጠው ግለሰብን ወይም ድርጅትን ወይም መንግስትን ወይም የመንግስት አካላትን ያጠቃልላል፡፡ 

የማዕድን ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ግለሰብ ከሆነ የኢትዮጵያ ነዋሪ ነው፡፡[9] መንግስት እና የመንግስት አካላትም ከሆኑ የኢትዮጵያ ነዋሪ ናቸው፡፡[10] ስለዚህ ማዕድን ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ሰው የማዕድን ሥራዎች በማከናወን በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያገኘው ገቢ ላይ የሰንጠረዥ “ሐ” ግብር ይከፍላል፡፡[11] በሌላ በኩል ድርጀቱ በኢትዮጵያ ነዋሪ ካልሆነ የማዕድን ማምረቻ እና ፍለጋ ሥፍራው በኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ስለሚሆን፤[12] በኢትዮጵያ ውስጥ ከማዕድን ሥራዎች የሚያገኘው ገቢ በኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘ ገቢ በመሆኑ የሰንጠረዥ “ሐ” ግብር ይከፍላል፡፡[13] ስለሆነም ፈቃድ የተሰጠው ሰው እንደማንኛውም ታክስ ከፋይ በአዋጁ[14] የተደነገገውን የግብር ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡

ፈቃድ የተሰጠው ሰው የግብር ግዴታ

ፈቃድ የተሰጠው ሰው የግብር ኃላፊነት ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የአዋጁን አንቀጽ 37(1) መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ የአንቀጽ 37(1) አማርኛ ቅጂ “በዚህ ምዕራፍ የተቀመጡት ማሻሻያዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ይህ አንቀጽ ፈቃድ በተሰጠው ሰው ወይም በሥራ ተቋራጭ ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡” በማለት ይደነግጋል፡፡ ይህ አንቀጽ የሚለው ሐረግ በእንግሊዘኛው ቅጂ “This Proclamation” በሚል ተደንግጓል፡፡ በሁለቱ ቅጂዎች መካከል የሚታይ ግልጽ የሆነ የአገላለጽ ወይም የቃላት አጠቃቀም ልዩነት ያለ ሲሆን፤ ከሁለቱ ቅጂዎች የትኛው ትክክል ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት፤ ፈቃድ የተሰጠውን ሰው የግብር ኃላፊነት ለመለየት ጠቃሜታ ይኖረዋል፡፡

ለአንቀጽ 37(1) ጥቅም የሚሰጠው ትርጉም በዚህ ምዕራፍ የተደነገጉ ማሻሻያዎች እንደተጠበቁ ሆነው አዋጁ በማዕድን እና ነዳጅ ሥራ ላይ ተፈፃሚነት አለው የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም 1ኛ) የገቢ ግብር አዋጁ ሲወጣ የተዘጋጀው ሀተታ ዘምክንያት (Technical note) አዋጁ ተፈፃሚነት እንዳለው ስለሚገልጽ፤ 2ኛ) ይህ አንቀጽ የሚለውን ሐረግ ትክክለኛ ነው ብንል እንኳን አንቀጽ 37(1) በምዕራፍ አራት ሥር የሚገኝ በመሆኑ የማዕድን እና የነዳጅ ጉዳይ ላይ ተፈፃሚነት ስላለው ድንጋጌው  ጥቅም የለሽ ስለሚሆን፤ 3ኛ) በሕግ አተረጓጎም መርህም ቢሆን ሕጎች ጥቅም በሚሰጥ እና ተግባር ላይ በሚውሉበት አኳኋን መተርጎም ያለባቸው በመሆኑ ይህ አዋጁ የሚለው ሐረግ ትክክለኛ ይመስላል፡፡

በተጨማሪም በአዋጁ በአንቀጽ 37(2) ላይ በአዋጁ ሌሎች ክፍሎች ውስጥ የተካተቱ ሌሎች ድንጋጌዎች ከአዋጁ ምዕራፍ አራት ድንጋጌ ጋር  እስካልተቃረኑ ድረስ በማዕድን እና ነዳጅ ሥራ ገቢ ላይ ተፈጻሚነት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን በአዋጁ ሌሎች ክፍሎች እና በምዕራፍ አራት ድንጋጌ መካከል አለመጣጣም የተፈጠረ እንደሆነ የአዋጁ ምዕራፍ አራት ድንጋጌ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡[15] ስለሆነም አማርኛው ቅጂ የቃላት ግደፈት ያለበት ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 3/1987 አንቀጽ 2(4) ላይ በአንድ ህግ የአማርኛ እና የእንግሊዘኛ ቅጅ መካከል የይዘት ልዩነት በሚፈጠርበት ጊዜ የአማርኛው የበላይነት እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ፤ የአዋጁን ሌሎች ክፍሎች ድንጋጌ ፈቃድ በተሰጠው ሰው ላይ ተፈፃሚ ማድረግ አዳጋች ስለሚሆን የአዋጁ አንቀጽ 37(1) አማርኛው ቅጂ ማሻሻያ ያስፈልገዋል፡፡

በማዕድን ሥራዎች ፈቃድ የተሰጠው ታክስ ከፋይ በአዋጁ ምዕራፍ አራት ከተመለከተው የግብር ግዴታ በተጨማሪ፤ የአዋጁ ሌሎች ክፍሎች ድንጋጌ የሚመለከታቸው በመሆኑ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ በዝርዝር ለማስቀመጥ፤ ማንኛውም ፈቃድ የተሰጠው ሰው የሚከተሉትን የግብር ግዴታዎች መፈጸም አለበት፡-

  • በሰንጠረዥ “ሐ” መሰረት የንግድ ሥራ ትርፍ ግብር በ25% መጣኔ መክፈል፤[16]
  • ፈቃድ የተሰጠው ሰው በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ወይም በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው ሆኖ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት የሆነ እንደሆነ ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ተከፋይ ሂሳቦች ላይ ግብር ቀንሶ በመያዝ ለሚኒስቴሩ በ30 ቀናት ውስጥ ገቢ ማድረግ፡፡[17]
  • አዋጁ በአንቀጽ 11 በተደነገገው መጣኔ ሰራተኛ ቀጥሮ የሚያሰራ ከሆነ ከመቀጠር ከሚገኝ ገቢ ላይ ግብር ቀንሶ በመያዝ ግብር መክፈል፡፡[18]
  • በኢትዮጵያ ነዋሪ ላልሆነ ሰው ከሚፈጽመው የትርፍ ድርሻ ወይም ያልተከፋፈለ ትርፍ ላይ 10%፣ የንዑስ ሥራ ተቋራጭ ክፍያ ላይ 10%፣ የወለድ ክፍያ ላይ 10%፣ የሮያሊቲ ክፍያ ላይ 05%፣ የሥራ አመራር ክፍያ ላይ 15%፣ የቴክኒካል አገልግሎት ክፍያ ላይ 15%፣ የመድን አረቦን ክፍያ ላይ 05%፣ ወደ ውጭ የሚላክ ትርፍ ላይ 10%፣ ለአዝናኝ(Entertainer) ከሚፈጸም ክፍያ ላይ 10%፣ እንዲሁም ከሌሎች ገቢዎች ክፍያ ላይ 15% ግብር ቀንሶ ለሚኒስቴሩ ገቢ ማድረግ ፡፡[19]
  • ግብር ከሚከፈልበት የሮያሊቲ ክፍያ ላይ 05%፣ የትርፍ ድርሻ ክፍያ ወይም ያልተከፋፈለ ትርፍ ላይ 10%፣ የወለድ ክፍያ ላይ 10%፣ ወደ ውጭ የሚላክ ትርፍ ወይም ያልተከፋፈለ ትርፍ ክፍያ ላይ 10% ግብር ቀንሶ በማስቀረት ግብር መክፈል፡፡[20]
  • በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚፈጸም በአንድ የዕቃ ግዢ ወይም የዕቃ አቅርቦት ውል ክፍያ ከብር አስር ሺ በላይ ሲሆን፤ እንዲሁም በአንድ የአገልግሎት ውል ክፍያ ከብር ሶስት ሺ በላይ ከሆነ ከክፍያው ላይ 2% ግብር ቀንሶ ለግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ገቢ ማድረግ፡፡[21]

ስለሆነም የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ የተሰጠው ሰው ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ቀንሶ ለሚኒስቴሩ ገቢ የሚያደርገው የግብር መጠን እንደሚፈጽመው የክፍያ ዓይነት በግብር ሕግ በተደነገገው የግብር መጣኔ መሰረት ነው፡፡ 

ፈቃድ የተሰጠው ሰው ለንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ክፍያ ሲፈጽም ቀንሶ የሚይዘው ግብር ምን ያህል ነው?

ሚኒስቴሩ በማዕድን ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ታክስ ከፋዮችን ኦዲት በማድረግ ከማዕድን ጋር የተያያዘ አገልግሎት ከንዑስ­-ሥራ ተቋራጭ ሳይገኝ፤ በአዋጁ በአንቀጽ 37(4) ላይ በተደነገገው መሰረት በ10 በመቶ መጣኔ ግብር ቀንሶ ገቢ ማድረግ ትክክል አይደለም በማለት፤ በአዋጁ በአንቀጽ 51 መሰረት በ15 በመቶ የግብር መጣኔ ግብር በማስላት፤ በአዋጁ በአንቀጽ 97(3) መሰረት ሳይሰበሰብ የቀረውን ግብር ፈቃድ የተሰጠው ሰው እንዲከፍል ውሳኔ ሲሰጥ በተግባር ይታያል፡፡ በግብር ከፋዩ በኩል የማዕድን ሥራዎች ብቻ የምንሰራ በመሆኑ ወጪያችን በሙሉ ከማዕድን ስራ ጋር ተያያዥ ስለሆነ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀንሶ ሊያዝ የሚገባው ግብር በአዋጁ አንቀጽ 37(4) መሰረት ነው በሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡ ስለሆነም ፈቃድ የተሰጠው ሰው ለንዑስ ስራ ተቋራጭ ክፍያ ሲፈጽም ቀንሶ የሚይዘው ግብር ምን ያህል ነው? የሚለው ጉዳይ አፈፃፀሙ ክርክር የሚነሳበት ነው፡፡

በአዋጁ በአንቀጽ 37(4) ፈቃድ የተሰጠው ሰው በኢትዮጵያ ነዋሪ ላልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ከሚፈጽመው ማንኛውም ክፍያ ላይ 10 በመቶ ግብር ቀንሶ ለሚኒስቴሩ ገቢ ማድረግ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ እንደምንረዳው ፈቃድ የተሰጠው ሰው 10 በመቶ ግብር ተቀናሽ የሚያደርገው በኢትዮጵያ ነዋሪ ላልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ከሚፈጽመው ማንኛውም ክፍያ ላይ እንጂ፤ በኢትዮጵያ ነዋሪ ላልሆነ ሰው ሁሉ ከሚፈጽመው ማንኛውም ክፍያ ላይ አይደለም፡፡

በአዋጁ በአንቀጽ 36(20) ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ንዑስ ተቋራጭ ማለት በተቀጣሪነት አገልግሎት የሚሰጥን ሰው ሳይጨምር ፈቃድ ለተሰጠው ሰው ከማዕድን ማውጣት ሥራ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሰው ሲሆን፤ ከማዕድን ማውጣት ሥራ ጋር ያልተያያዙ አገልግሎቶችን ፈቃድ ለተሰጠው ሰው የማይሰጥ ድርጅትን አያጠቃልልም፡፡

የማዕድን ማውጣት ሥራ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ማየት ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ማን እንደሆነ ለመለየት አስፈላጊ ነው፡፡ በአዋጁ በአንቀጽ 36(14) መሰረት የማዕድን ሥራዎች ማለት በማዕድን መብት መሰረት የተፈቀዱ ሥራዎች ናቸው፡፡ በአዋጁ በአንቀጽ 36(15) መሰረት የማዕድን መብት ማለት ደግሞ በማዕድን ሥራዎች አዋጅ መሰረት በመንግሰት የሚሰጥ የቅኝት፣ የምርመራ፣ ፈቃድን ይዞ የመቆየት ወይም የማዕድን ማምረት ፈቃድ እንደሆነ የተደነገገ ሲሆን የማዕድን ሥራዎች አዋጅ ቁጥር 678/2008 በአንቀጽ 2(21ና 22) በተመሳሳይ ሁኔታ ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ ስለሆነም ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ማለት ከማዕድን ማውጣት ሥራዎች ጋር የተያያዘ አገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማራ ሆኖ ፈቃድ ለተሰጠው ሰው ይህንኑ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ መታየት ያለበት መሰረታዊ ጉዳይ ፈቃድ የተሰጠው ሰው ያወጣው ወጪ ቀጥተኛ የሆነ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ከማዕድን ሥራ ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በአዋጁ አንቀጽ 22 መሰረት ፈቃድ የተሰጠው ሰው በንግድ ሥራው ገቢ ውስጥ የተካተቱትን ገቢዎች ለማግኘት፣ ዋስትና ለመስጠት እና ለማስቀጠል ያወጣው ማንኛውም አስፈላጊ የሆነ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ፈቃድ የተሰጠው ሰው ከማዕድን ሥራው ጋር በተያያዘ ለደህንነት፣ ለመድን፣ ለመዝናኛ፣ ለጤና፣ ለሕግ እና ለአስተዳደር አገልግሎት ወዘተ የሚያወጣው ወጪ ከንግድ ሥራ ጋር የተያያዘ ወጪ በመሆኑ ከንግድ ሥራ ገቢ ላይ ተቀናሽ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን፤ እነዚህን ከማዕድን ስራ ጋር ያልተያያዙ አገልግሎቶች የሚሰጥ ሰው  ለግብር ህግ አላማ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ተደርጎ አይወሰድም፡፡ በመሰረቱ ፈቃድ የተሰጠው ሰው የንግድ ስራ ወጪው በሙሉ ከማዕድን ማውጣት ሥራ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የሚደረገው ግብር መጣኔ ሁልጊዜም 10 በመቶ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡

አዋጁ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ሁኔታ በ15 በመቶ መጣኔ ግብር የሚከፈልባቸውን ገቢዎችን ወደ 10 በመቶ ዝቅ የማድረግ፤ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ የሰጠው ፈቃድ ለተሰጠው ሰው ማንኛውንም ዓይነት አገልግሎት ለሚያቀርብ ሰው ሳይሆን፤ ከማዕድን ማውጣት ሥራ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን ፈቃድ ለተሰጠው ሰው ለሚሰጥ ሰው ብቻ ነው፡፡ የማዕድን ሥራ ሰፊ እና የተወሳሰበ እውቀት እና ቴክኖሎጂ የሚፈልግ የስራ ዘርፍ ነው፡፡ የህጉ ዓላማም በሀገሪቱ በማዕድን ዘርፍ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ክፍተት በጥቅል ወይም በአንድ ማዕቀፍ ወደሀገር በማስገባት ችግሩን መፍታት አዳጋች በመሆኑ፤ በማዕድን ሥራዎች ላብራቶሪ ምርመራ፣ ፍለጋ፣ አስተዳደር እና በሌላ ዘርፍ በሥራው ላይ ያለውን እውቀት እና ቴክኖሎጂ በየፈርጁ ወደ ሀገር በማስገባት የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እንዲቻል በኢትጵያ ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ እንዲሰራ ማበረታታት ነው፡፡

ፈቃድ ለተሰጠው ሰው ከማዕድን ሥራ ጋር ያልተያያዘ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ባለመሆኑ ፈቃድ የተሰጠው ሰው ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የሚደረገው ግብር እንደክፍያ ዓይነቱ በአዋጁ በሰጠረዥ “መ” ከአንቀጽ 51 እስከ 64 በተደነገገው መጣኔ መሰረት እንጂ በአዋጁ በአንቀጽ 37(4) መሰረት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በአዋጁ አንቀጽ 37(4) እና 36(20) መሰረት ፈቃድ የተሰጠው ሰው ከማዕድን ሥራ ጋር የተያያዘ አገልግሎት በኢትዮጵያ ነዋሪ ካልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ አግኝቶ ከሚፈጽመው ማንኛውንም ክፍያ ላይ ተቀናሽ የሚያደረገው ግብር 10 በመቶ ብቻ ነው፡፡    

በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ የንዑስ-ሥራ ተቋራጭ የግብር ኃላፊነት

በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ላይ አዋጁ ተፈፃሚ የሚሆነው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያገኘው ገቢ ላይ ብቻ ነው፡፡[22] እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ዋና ነጥብ በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያገኘው ገቢ ላይ የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጁ በምን መንገድ ግብር በመጣል ይሰበስባል? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አዋጁ በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያገኘው ገቢ ላይ በሁለት መንገድ ግብር በመጣል ይሰበስባል፡፡

1ኛው ድርጀቱ በኢትዮጵያ ነዋሪ ባይሆንም በአዋጁ በአንቀፅ 4 እና በደንቡ[23] በአንቀጽ 4 መሰረት በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት እንደሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሰራው የንግድ ስራ በሚያገኘው ገቢ ላይ የሰንጠረዥ “ሐ” ግብር የተጣለ ሲሆን ግብሩ በየዓመቱ ይሰበሰባል፡፡[24] 2ኛው በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያገኘው ገቢ ላይ  በአንቀጽ 51 መሰረት ግብር የተጣለበት ሲሆን፤ ግብሩ በኢትዮጵያ ነዋሪ በሆነ ሰው ወይም በቋሚነት በሚሰራ ድርጅት አማካኝነት ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ቀንሶ በማስቀረት ይሰበሰባል፡፡

የአዋጁ አንቀጽ 37(4) ፈቃድ የተሰጠው ሰው በኢትዮጵያ ነዋሪ ላልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ከሚፈጽመው ማንኛውም ክፍያ ላይ የሚሰበሰበው ግብር የጠቅላላ ክፍያውን 10 በመቶ ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል አዋጁ በአንቀጽ 51 በኢትዮጵያ ነዋሪ ባልሆነ ሰው ላይ በተለያየ መጣኔ ግብር ጥሏል፡፡ በአንቀጽ 37(4) እና 51 መሰረት  የተጣለው ግብር መጣኔው የተለያየ በመሆኑ፤ በሁለቱ ድንጋጌዎች መካከል አለመጣጣም አለ፡፡ ስለሆነም ነዋሪ ባልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ላይ ተፈፃሚነት ያለው የትኛው ድንጋጌ ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡

በአንቀጽ 37(2) ላይ በአዋጁ ሌሎች ክፍሎች እና በምዕራፍ አራት መካከል አለመጣጣም የተፈጠረ እንደሆነ ተፈፃሚነት ያለው የምዕራፍ አራት ድንጋጌ እንደሆነ የተደነገገ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ነዋሪ ባልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ላይ ተፈፃሚነት ያለው ድንጋጌ አንቀጽ 37(4) ነው፡፡ ስለሆነም ፈቃድ የተሰጠው ሰው በኢትዮጵያ ነዋሪ ላልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ማንኛውንም ክፍያ ሲፈጽም ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ቀንሶ ለሚኒስቴሩ ገቢ የሚያደረገው ግብር 10 በመቶ ብቻ በመሆኑ ከ10 በመቶ በላይም ሆነ በታች የሆነ ግብር ተቀንሶ ሊያዝ አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ በኢትዮጵያ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ያልሆነ እንደሆነ በዚህ አኳኋን የተሰበሰበው ግብር በአዋጁ በአንቀጽ 64(2) መሰረት በገቢው ላይ የመጨረሻ ግብር ይሆናል፡፡   

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት የምክር አገልግሎት እና ማናቸውንም አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ፤ እንዲሁም የማዕድን ማምረቻ ሥፍራው በኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ጋር በአዋጁ በአንቀጽ 6(3(ሀ)) መሰረት በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ የሰንጠረዥ “ሐ” ግብር መክፈል አለበት ወይስ የለበትም? ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭስ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት በመሆኑ የሰንጠረዥ “ሐ” ግብር የሚከፍል እንደሆነ ከአዋጁ ምዕራፍ አራት ድንጋጌ ጋር አለመጣጣም ይፈጠራል ወይስ አይፈጠርም? የሚሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ 

ጥያቄዎች ከማየታችን በፊት በአዋጁ በአንቀጽ 51 መሰረት ነዋሪ ባልሆነ ሰው ላይ የተጣለውን ግብር ምንነት ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ በአዋጁ በአንቀጽ 51 መሰረት ነዋሪ ያልሆነ ሰው ግብር ለአስተዳደር አመቺነት ሲባል ግብሩ የሚሰበሰበው ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ በማድረግ ሲሆን ከጠቅላላ ክፍያው ላይ በሕግ በተደነገገው መጣኔ መሰረት የሚሰላ በመሆኑ ገቢውን ለማመንጨት የወጣ ወጪ ተቀናሽ አይደረግም፡፡ ነዋሪ ያልሆነ ሰው የተለየ ግብር (separate taxation) የተጣለበት ምክንያት፤ በአዋጁ በአንቀጽ 6(3(ሀ)) መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ በተገኘ ገቢ ላይ ግብር የተጣለበት ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ የማይገኝ ስለሆነ ግብሩን መሰብሰብ የማይቻል በመሆኑ፤ እና በኢትዮጵያ የሚገኝ ቢሆን እንኳን የግብር ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት ከሀገር የሚወጣ በመሆኑ በመደበኛው የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ግብሩን መሰብሰብ ስለማይቻል ነው፡፡ በተጨማሪም በመደበኛው ግብር አሰባሰብ ሥርዓት ግብር መሰብሰብ ይቻላል እንኳን ቢባል ግብር የሚከፈልበት ገቢ ውስጥ የተካተቱ ገቢዎችን  ለማመንጨት ከአገር ውጪ የወጣውን ወጪ ተቀናሽ ለማድረግ ወጪውን መደልደል (Cost allocation) ውስብስብ ነው፡፡ ስለሆነም ነዋሪ ላልሆነ ሰው ክፍያ ሲፈጸም ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ግብሩን ቀንሶ ለሚኒስቴሩ ገቢ በማድረግ  ግብሩ ይሰበሰባል፡፡  

ነገር ግን በአዋጁ በአንቀጽ 51 የተጣለው ግብር የሚሰበሰበው በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከናወን የንግድ ሥራ በኢትዮጵያ ነዋሪ ባልሆነ በቋሚነት በሚሰራ ድርጅት እንደሆነ በአንቀጽ 51(3) መሰረት የአንቀጹ ንዑስ አንቀጽ 2 ድንጋጌ ተፈፃሚ የማይሆን ሲሆን ገቢዎቹ እንደሁኔታው የሰንጠረዥ “ሐ” ወይም “መ” ግብር ይጣልባቸዋል፡፡ ምክንያቱም በአዋጁ በአንቀጽ 64(1) መሰረት የሰንጠረዥ “መ” ግብር በሌሎች ሰንጠረዦች ግብር በሚከፈልበት ገቢ ላይ ተፈጻሚነት የለውም፡፡ ስለሆነም በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት በኢትዮጵያ በሚያገኘው ገቢ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የሚደረገው ግብር በአንቀጽ 64(2) መሰረት የመጨረሻ ግብር አይሆንም፡፡ በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ግብር ተቀናሽ የተደረገበት እንደሆነ በአንቀጽ 98 መሰረት ከሚከፍለው የንግድ ሥራ ግብር ላይ ይካካስለታል፡፡[25]

የአዋጁ አንቀጽ 37(4) ድንጋጌ የሚያመለክተው ፈቃድ የተሰጠው ሰው ነዋሪ ላልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ክፍያ ሲፈጸም ተቀናሽ የሚደረገው ግብር (withholding tax) መጣኔ ሁል ጊዜ 10 በመቶ ስለመሆኑ እንጂ፤ በኢትዮጵያ ነዋሪ ካልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የሚደረገው ግብር የመጨረሻ እንደሆነ አልተደነገገም፡፡ እንዲሁም ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ከሆነ የሰንጠረዥ “ሐ” ግብር የማይጣልበት መሆኑ በአዋጁ ምዕራፍ አራት ላይ አልተደነገገም፡፡ በሌላ በኩል በአዋጁ በአንቀጽ 51(3) መሰረት በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያገኘው ገቢ ላይ የሰንጠረዥ “ሐ” ወይም “መ” ግብር እንደሁኔታው እንደሚጣልበት ተደንግጓል፡፡ በአዋጁ በአንቀጽ 37(1) እና (2) መሰረት የአዋጁ ሌሎች ክፍሎች ድንጋጌ ከምዕራፍ አራት ጋር ካልተቃረኑ በስተቀር በማዕድን እና ነዳጅ ሥራዎች ገቢ ላይ ተፈፃሚነት አላቸው፡፡ ስለሆነም በአዋጁ በአንቀጽ 37(4) እና በአንቀጽ 51(3) መካከል ምንም ዓይነት አለመጣጣም የሌለ በመሆኑ፤ የአዋጁ አንቀጽ 51(3) ድንጋጌ በኢትዮጵያ ነዋሪ ባልሆነ በቋሚነት በሚሰራ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ላይ ተፈፃሚነት አለው፡፡

በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ የንዑስ-ሥራ ተቋራጭ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያገኘው ገቢ ላይ በአዋጁ በአንቀጽ 4፣ 6(3(ሀ))፣ 21 እና 51(3) መሰረት የሰንጠረዥ “ሐ” ግብር ተጥሎበታል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ በአዋጁ በአንቀጽ 64(1(ሀ)) ላይ እንደተመለከተው የሰንጠረዥ “መ” ግብር ተፈፃሚ የማይሆንበት በመሆኑ በአዋጁ በአንቀጽ 37(4) መሰረት ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የተደረገበት ግብር በአዋጁ በአንቀጽ 98 መሰረት ከሚከፍለው ግብር ላይ እንዲካካስ ይደረጋል፡፡[26] 

በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ በማዕድን ሥራዎች ፈቃድ የተሰጠው ሰው እንደሆነ በአዋጁ በአንቀጽ 37(3) መሰረት የንግድ ሥራ ግብር መጣኔ ቅናሽ ማግኘቱ፤ ንግድ ሥራ ገቢው ላይ የተካተቱ ገቢዎችን ለማመንጨት የወጡ ወጪዎች ተቀናሽ የሚደረጉለት መሆኑ፤ እንዲሁም በአዋጁ በአንቀጽ 37(4) ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የተደረገውን ግብር በአንቀጽ 98 መሰረት በግብር ዓመቱ መጨረሻ ላይ ማካካሻ የማግኘት መብት ያለው መሆኑ፤ በዘርፉ ለመሰማራት ያበረታታል፡፡ ነገር ግን ማካካሻ የማግኘት መብቱ በግብር ዓመቱ መጨረሻ ላይ መሆኑ በማዕድን ሥራዎች ላይ እንዳይሰማሩ የሚያደርግ እና የአዋጁን ዓላማ የሚቃረን ነው፡፡

ምክንያቱም የማዕድን ሥራ በባህሪው ረዥም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ቆይታ ጊዜ ረዥም በመሆኑ፤ እና የማዕድን ማምረቻ ስፍራው ኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ፤ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ በአዋጁ በአንቀጽ 4 እና በደንቡ በአንቀጽ 4 መሰረት በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀንሶ የተከፈለው ግብር  በግብር ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከሚከፍለው ግብር እንዲካካስ መደረጉ ገንዘቡን በወቅቱ ጥቅም ላይ እንዳይውል የሚያደርግ በመሆኑ በዘርፉ ለመሰማራት አያበረታታም፡፡ በመሆኑም የማካካሻ ሥርዓቱ ወይም የአዋጁ አንቀጽ 37(4) ድንጋጌ ማሻሻያ ካልተደረገበት በዘርፉ የተሰጠው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

ማጠቃለያ

ፈቃድ የተሰጠው ሰው የሰንጠረዥ “ሐ” ግብር የተጣለበት ሲሆን ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ደግሞ በአዋጁ መሰረት ግብር ቀንሶ ለሚኒስቴሩ ገቢ ማድረግ አለበት፡፡ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ፈቃድ ለተሰጠው ሰው ከማዕድን ማውጣት ሥራ ጋር የተያያዘ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ነው፡፡

ፈቃድ የተሰጠው ሰው በአዋጁ በአንቀፅ 37(4) መሰረት በኢትዮጵያ ነዋሪ ላልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ከሚፈጽመው ክፍያ ላይ ቀንሶ የሚያዘውን ግብር ከሌሎች የሰንጠረዥ “መ” ግብር ጋር በመቀላለቀል፤ ለማንኛውም ሰው ከሚፈጽመው ማንኛውም ክፍያ ላይ 10 በመቶ ብቻ ግብር በመያዙ ምክንያት ለሚኒስቴሩ ሳይሰበሰብ ለቀረው ግብር ኃላፊ እንዳይሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡

በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ በኢትዮጵያ በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ያልሆነ እንደሆነ በአዋጁ በአንቀጽ 37(4) ፈቃድ የተሰጠው ሰው ከሚፈጽመው ክፍያ ላይ ቀንሶ የሚይዘው 10 በመቶ ግብር በአዋጁ በአንቀጽ 64(2) መሰረት በገቢው ላይ የመጨረሻ ግብር ነው፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ የሰንጠረዥ “ሐ” ግብር የሚከፍል በመሆኑ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የሚደረገው ግብር በአዋጁ በአንቀጽ 51(ሐ) እንደተመለከተው የመጨረሻ ግብር ባለመሆኑ፤ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የተደረገው ግብር በአንቀጽ 98 መሰረት በግብር ዘመኑ መጨረሻ ከሚከፍለው ግብር ላይ ማካካሻ የማግኘት መብት አለው፡፡

ይህ የማካካሻ ሥርዓት በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ በቋሚነት የሚሰራ ንዑስ-ሥራ ተቋራጭ ገንዘቡን በወቅቱ እንዳይጠቀም የሚያደርግ ሲሆን፤ ይህም በዘርፉ ላለመሰማራት ተግዳሮት የሚሆን በመሆኑ እና የአዋጁን ዓላማ የሚቀረን ስለሆነ የማካካሻ ሥርዓቱ አልያም የአዋጁ አንቀጽ 37(4) ድንጋጌ ማሻሻያ ያስፈልገዋል፡፡ 

 

 

[1] የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ 22ኛ ዓመት ቁጥር 104፣ ነሐሴ 02 ቀን 2008 ዓ/ም፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ አንቀጽ 9፡፡

[2] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 89፡፡

[3] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 88፣ 90 እና 92፡፡

[4] በዚህ ጹሑፍ ውስጥ የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር ሚኒስቴሩ ማለት የኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር ነው፡፡

[5] ዝኒ ከማሁ በአዋጁ አንቀጽ 97፡፡

[6] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 36(11 እና 15) ፤ የማዕድን ስራዎች አዋጅ ቁጥር 678/2002 ፣ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ 16ኛ ዓመት ቁጥር 45፣ ሐምሌ 28 ቀን 2002፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ አንቀጽ 2(22)፡፡

[7] የፌደራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ፣ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ 22ኛ ዓመት ቁጥር 103፣ ነሐሴ 14 2008 ዓ/ም፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፣ አንቀጽ 2(26)፡፡

[8] ዝኒ ከማሁ (ቁጥር 6) አንቀጽ 2(25)፡፡

[9] ዝኒ ከማሁ (ቁጥር 1) አንቀጽ 5(1፣ 2፣ 3 እና 4) ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌደራል የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 ፣ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ 23ኛ ዓመት ቁጥር 82፣ ነሀሴ 15 ቀን 2009 ዓ/ም፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ አንቀጽ 5፡፡

[10] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 5(1(ሐ))፡፡

[11] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 7(1) ፣ 18 እና 37(3)፡፡

[12] ዝኒ ከማሁ (ቁጥር 1) አንቀጽ 4(2(ለ))፡፡

[13] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 6(3(ሀ)) ፣ 7 እና 18፤ ዝኒ ከማሁ (ቁጥር 10) አንቀጽ 4(1)፡፡

[14] በዚህ ጹሑፍ ውስጥ በቃሉ አገባብ በሌላ አኳኋን ካልተገለጸ በስተቀር አዋጁ ማለት የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 ነው፡፡

[15] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 37(2)፡፡

[16] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 37(3)፡፡

[17] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 97፡፡

[18] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 88 እና 97፡፡

[19] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 51(2) ፣ 53፣ 55፣ 56፣ 63፣ 89እና 97፡፡

[20] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 90፣ 54፣ 55፣ 61፣ 56፣ 62 እና 97፡፡

[21] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 92 እና 97፡፡

[22] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 7(2)፡፡

[23] በዚህ ጹሑፍ ውስጥ በቃሉ አገባብ በሌላ አኳኋን ካልተገለጸ በስተቀር ደንቡ ማለት የፌደራል የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 ነው፡፡

[24] ዝኒ ከማሁ አንቀጽ 6(3(ሀ))፡፡

[25] Ministry of Finance Economic Cooperation, ‘FDRE Proclamation No. 979/2010 Technical Notes’,  February 2018, 133-137

[26] ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 137

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

The legality of Levying Income Tax on Illegal Amou...
አዲስ ለተወለደ ህፃን ልጅ ስም የማውጣት መብት፤ የእናት ወይስ የአባት? - የሕ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 28 March 2024