በአገር ውስጥ እና በተለይም ወደ ሌሎች አገራት የሚካሄድ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በኢትዮጵያ ውስጥ የላቀ ትኩረት እያገኘ መጥቷል፡፡ ይህም ትኩረት በቅርቡ ጉዳዩ እያገኘ ካለው ሰፊ የሚድያ ሽፋን ባሻገር ችግሩን ለመፍታት በተከታታይ በመንግስት እየተወሰዱ ያሉ የሕግ፣ የፖሊሲና የፕሮግራም እርምጃዎች ላይ ይንፀባረቃል፡፡ ለዚህ ጉዳይ የተሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም አልፎ አልፎ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ምንነት ጋር በተያያዘ የተወሰነ ግራ መጋባት ይታያል፡፡ ይሕ አጭር ጽሁፍ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ለሚደረው ጥረት አስተዋጽኦ ያደርጋል በሚል እምነት የተዘጋጀ ነው፡፡
ትርጉም
የተ.መ.ድ. እ.ኤ.ኤ. በ2000 ዓ.ም. ያወጣውና የፓሌርሞ ስምምነት በመባል የሚታወቀው ስምምነት በሰዎች መነገድ ወይም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለብዝበዛ ዓላማ ሰዎችን (በተለይም ሴቶችና ሕፃናትን) በኃይል፣ በዛቻ፣ በተንኮል፣ በማታለል፣ በመጥለፍ ወይም በተበዳይ ላይ ኃላፊነት ላለው ሰው ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም በመስጠት መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማስተላለፍ፣ መደበቅ ወይም መቀበል ማለት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ሕፃናትን በተመለከተ ለብዝበዛ ዓላማ እስከሆነ ድረስ ሕፃናቱን መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማስተላለፍ፣ መደበቅ ወይም መቀበል በራሱ በሰዎች መነገድ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በሴቶችና በልጆች መነገድን የሚከለክለው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 597 እና 635 ላይም ይኸው ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ትርጓሜ መረዳት እንደምንችለው በሰዎች መነገድ በዋነኛነት ሦስት ነገሮችን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህም፡ - (1ኛ) በኃይል ወይም በማታለል መመልመል (ምልመላ)፣ (2ኛ) በአገር ውስጥ ወይም ወደ ሌላ አገር በህጋዊ ወይም ህገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር (ዝውውር)፣ እና (3ኛ) አዘዋዋሪዎች ተበዳዮችን የገንዘብ ጥቅም ማግኛ ማድረጋቸው (ብዝበዛ) ናቸው፡፡
በሰዎች መነገድ ከሌሎች የሰዎች ዝውውር ክስተቶች ጋር በተለይም ከኢ-መደበኛ የሰዎች ዝውውር እና ከሕገወጥ የድንበር ዝውውር ጋር የሚምታታበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ይህም የሰዎች ንግድ ተጎጂዎች እንደ ወንጀለኛ የሚታዩበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በአጠቃላይ ሰዎች በአገር ውስጥ ወይም ወደ ውጭ አገር ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወይም ስደት ስራ ፍለጋ፣ ለተሻለ ህይወት፣ መሳደድን በመፍራት፣ ከጭቆና ወይም የተፈጥሮ አደጋ ለመሸሽ ብሎም የመኖሪያ ቦታን ለመቀየር ሲባል ሊካሄድ ይችላል፡፡ በአንፃሩ በሰዎች መነገድ ዓላማው ብዝበዛ ሲሆን ስደተኞች ለዚህ ሁኔታ ተጋላጭ ናቸው፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት በአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል 76.7 በመቶ የሚሆኑት የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ናቸው፡፡ በተለይም እድሜያቸው ከ18 አመት በታች ከሆኑት እና ወደተለያዩ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ስራ ፍለጋና ሌሎች ምክንያቶች ከተጓዙት ኢትዮጵያውያን መካከል 7.5 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ13 እስከ 17 አመት መሆኑን እና ከነዚህም ውስጥ 87.1 በመቶ የሚሆኑት የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች እንደነበሩ ሌሎች ጥናቶች አመልክተዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአገሪቱ እስከ 50 ሺህ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን እስከ 95 በመቶ የሚሆኑት እዚያ የሚደርሱት በሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች በኩል ነው፡፡