ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ገበታ ለሃገር መርሃግብር የመንግሥት ሠራተኞች የወር ደሞዛቸውን ለገሱ የምትል ዜና በተደጋጋሚ በመስማቴ እና እውነት በዚህ የኑሮ ውድነት እነዚህ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዛቸውን የሚለግሱት ጎርጎራ፣ ወንጪ አሊያም ኮይሻ ላይ ሆቴል መሰራቱ ከጊዚያዊ ችግሮቻችን ይበልጣል ብለው አምነው ወይስ በአለቆቻቸው ተፅዕኖ ሥር በመሆናቸው ተገድደው የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ውስጤ ሲመላለስ በመቆየቱ ነው፡፡ መልካም ንባብ!
ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ምስጋና ይግባቸውና አይነ-ግቡ የሆኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከቤተ-መንግሥታቸው ጀምረው እየገነቡልን ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ስራዎች የሃገርን ገፅታ ከመገንባት ጀምሮ ታሪክን ጠብቆ በማቆየት በቱሪዝም እንደሃገር የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው መሆናቸው በስፋት ይጠቀሳል ይሁን እንጂ በተቃራኒው ቅንጦት ነው፣ በዚህ ሰዓት ሰላም እና በልቶ ማደር እንጂ ቅንጡ ሆቴል የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ከቁጥር አይገባም ስለሆነም ያለጊዜው የመጣ ፕሮጀክት ነው በማለት የሚተቹትም አልጠፉም፡፡
ቤተመንግሥትን ከማስዋብ የተጀመረው ፕሮጀክት አሁን አድማሱን አስፍቶ ሃገራዊ ቅርፅን በመላበስ በሶስት ክልሎች ማለትም አማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ያሉ የመስህብ ስፍራዎችን ወደማልማት ተሸጋግሯል፡፡ ለዚህም እውን መሆን ገበታ ለሃገር በሚል በገቢ ማሰባሰቢያ መልክ የ10,000,000 ብር እና 5,000,000 ብር የሚከፈልበት እራት ግብዣ በጠቅላያችን ተሰናድቷል፡፡ በዚህ አላበቃም በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት ዜጋው ልቡ በፈቀደ መጠን ገንዘብ እንዲለግስ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ተዘጋጅቷል፤ የባንክ አካውንትም በተለያዩ ሚዲያዎች ይፋ በማድረግ ገቢ ማሰባሰብ ስራው ቀጥሏል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ይፋ ሲደረግ ያልተገለፀ ነገር ግን በተግባር እየሆነ ያለ አንድ እውነት አለ፡፡ ይህም የመንግሥት ሠራተኛው ለፕሮጀክቱ የወር ደሞዙን እንዲሰጥ ማድረግ፡፡ የእንትን ሚኒስቴር ሠራተኞች እና አመራሮች ለገበታ ለሃገር የወር ደሞዛቸውን ለገሱ የሚል ዜና በየዕለቱ እየሰማን ነው፡፡ ለመሆኑ የሠራተኛ ደመወዝ የሚቆረጠው እንዴት ነው?፣ አንድ የስራ ሃላፊ ስለፈለገ ወይም መስሪያቤቱ አመራሮች ተወያይተው ስላፀደቆ የሠራተኛን ደመወዝ መቁረጥ ይቻላል እንዲቆረጥብን አንፈልግም የሚሉ ሠራተኞች ሲኖሩ እንዴት ይደረጋል?፣ የሚሉ ጥያቄዎች በዚህ ጽሑፍ መልስ ለመስጠት ይሞከራል፡፡