በሀገራችን የንግድ ሕግ ሥርዓት መሠረት ነጋዴነት ምን መብቶችና ግዴታዎች አሉበት? ለመሆኑ አንድ ነጋዴ በሥሙ ያወጣውን የንግድ ፈቃድ ለሌላ ሰው ማከራየትና በኪራይ ውል ማስተላለፍ ይችላል? አከራይቶ ቢገኝስ በወንጀል ሊያስከስሰውና ሊያስቀጣው ይችላልን? የነጋዴነት መብቶችና ግዴታዎች በየትኞቹ ህግጋት ይገዛል? የነጋዴዎችን መብትና ግዴታዎች በዋናነት የሚመለከቱት ሕግጋት በአዋጅ ቁጥር 166/1952 የወጣውና ከመስከረም 1 ቀን 1953 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለው የንግድ ሕግ፣ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅና ደንብ እና ግብርን የሚመለከቱ ሕጎች ሲሆኑ ሌሎች ህግጋትም እንደ የውል ሕግ፣ የኪራይ ሕግ፣ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ፣ የወንጀል ሕግ.... በነጋዴዎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያስከትሉት መብትና ግዴታዎች ይኖራሉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ ስለ ነጋዴዎች መብትና ግዴታዎች በዝርዝር ለመጻፍ የማይቻል በመሆኑ ጽሁፉ ለመዳሰስ የሚሞክረው በነጋዴነት የተመዘገበ የንግድ ፈቃድ የተሰጠው ሰው የንግድ ፈቃዱን ለሦስተኛ ወገን በኪራይ ውል ማስተላለፍ ህጋዊ መብት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ ነው፡፡
ጽሁፉን በተጨባጭ የፍርድ ቤት ጉዳይ ለመደገፍ ይቻል ዘንድ የሚከተለውን አንድ ጉዳይ እንመልከት፡-
አቶ ተፈራ… (ስሙ ለጽሑፉ ሲባል የተቀየረ) ባለትዳርና የልጆች አባት ሲሆን በባለቤቱ ሥም በቅድመ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አገልግሎት በሚል ዘርፍ በአፀደ ሕጻናት አገልግሎት የንግድ ፈቃድ የወጣበትን ድርጅት ለማስተዳደር የውክልና ስልጣን የተሰጠው በመሆኑ በራሱ እየሠራበት እያለ በጤና እና በሌሎች ምክንያቶች ድርጅቱን የማስተማር ልምድ ካለው ሰው ጋር በኪራይ ለማሠራት ተስማምተው በጽሑፍ የኪራይ ውል አስተላለፈው፡፡ ይሁንና ተከራይው ግለሰብ ድርጅቱን እንደ ባለቤቱ/ወኪሉ ሆኖ ለመምራት ባለመቻሉ የተማሪዎች ቁጥር እየቀሰነበትና ኪሣራ እየደረሰበት በመምጣቱ በመሐከላቸው አለመግባባት በመፈጠሩ በፍትሐብሔሩ አለመግባባት ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ደረሰ፡፡ ተከራይው ግለሰብ የንግድ ፈቃዱን ተከራይቶ መሥራቱን ለተቆጣጣሪ አካላት መረጃ በመስጠቱ አቶ ተፈራ በፖሊስ ለምርመራ እንደሚፈለግ ጥሪ ደርሶት የወንጀል ምርመራ ተደረገበት፡፡ ጉዳዩ በምርመራ ብቻ ሳያበቃ በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 ድንጋጌዎችን በመተላለፍ የንግድ ፈቃድን ማከራየት ወንጀል ፈጽመሃል በማለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት በወንጀል ተከሳሽ ሳጥን ለመቆም በቃ፡፡ ተከሳሽ ክሱ ደርሶት ስለ ድርጊቱ በፍርድ ቤቱ ሲጠየቅ ድርጅቱን ማከራየቱን ሳይክድ፣ ያከራየሁት መብቴን ተጠቅሜ የድርጅቱን መልካም ዝና እንጅ የንግድ ፈቃዱን ብቻ ነጥዬ ለሌላ ሰው ያላከራየሁ በመሆኑ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ክርክሩን አቅርቧል፡፡ ከንግድ ሕጉና ከንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንጻር ተከሳሽ በወንጀል ጥፋተኛ ሊሆን ይችል ይሆን? በህጉ መሠረት የንግድ ፈቃድን ማከራየት የንግድ መደብርን ከማከራየት ተለይቶ የሚታይ ነውን? በተከሳሽ ላይ የቀረበውን ክስና የክርክሩን ውጤት ወደኋላ እናቆየውና በቅድሚያ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የህጉን ድንጋጌዎች እንመልከት፡፡
በንግድ ሕጉ ስለ ነጋዴዎችና ስለ ንግድ መደብሮች በሚለው ክፍል በአንቀጽ 5 ሥር ስለ ነጋዴነት ትርጉም ሲገልጽ “ነጋዴዎች” የሚባሉት ሰዎች የሞያ ሥራቸው አድርገው ጥቅም ለማግኘት ሲሉ በህጉ የንግድ ሥራዎች ተብለው የተቆጠሩትን ሥራዎች የሚሠሩ ሰዎች መሆናቸውን ተደንግጓል፡፡ በንግድ ሕጉና በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ መሠረት የንግድ ሥራዎች ተብለው ከተዘረዘሩት ሥራዎች መካከል ለምሳሌ፡- ጥሬ ዕቃዎችን ወይም ምርቶችን ገዝተው/አምርተው የሚሸጡ፣ ህንጻዎችን/ዕቃዎችን የሚያከራዩ፣ የሆቴል፣ የምግብ ቤት፣የቡና ቤት፣ የመጠጥ ቤት፣የመኝታ ቤት… አገልግሎት የሚሰጡ፣ የትምህርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ የላኪነትና አስመጭነት፣ የጉምሩክ አስተላላፊነት…ወ.ዘ.ተ ሥራ በንግድ መዝገብ ተመዝገበውና የንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰዎች የሚለው እንደአግባብነቱ የተፈጥሮ ወይም የሕግ ሰውነት የተሰጣቸውን ሁሉ የሚወክል ነው፡፡
በንግድ ህጉ አንቀጽ 100 በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የንግድ ሥራ የሚሠራ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም የውጭ አገር ሰው ወይም የንግድ ማህበር በመዝገብ መግባት እንዳለበት በአስገዳጅነት ተደንግጓል፡፡ በአንቀጽ 105 እንደተደነገገው አንድ ነጋዴ ለመመዝገብ ማመልከቻ ሲያቀርብ ከሚገልጻቸው መረጃዎች መካከልም የቤተዘመድ ስሙ፣ የተወለደበት ቀንና ቦታ፣ ዜግነቱ፣ የግል አድራሻው፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ የንግዱ ዓላማ፣ የንግዱ ሥም፣ ሥራ አስኪያጅ ካለው ስሙንና ሥልጣኑን ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በንግድ መዝገብ የመግባታቸው አስፈላጊነት የንግድ ሥራ ፈቃድ በግለሰቡ ማንነት የተወሰነ እንዲሆን ታስቦ ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በንግድ ህጉ አንቀጽ 112 መነገድን ስለመተው በተደነገገው መሠረት ደግሞ ማንኛውም የተመዘገበ ነጋዴ የተመዘገበውን የንግድ ሥራውን በማናቸውም ምክንያት በተወ ጊዜ ወይም የንግዱን መደብር በአከራየ ጊዜ በሁለት ወር ውስጥ ከመዝገቡ እንዲሰረዝ ማመልከቻ ማቅረብ እንደሚገባው ተደንግጓል፡፡
የነጋዴነት ሥራ የቫት(የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ) ከግብር ክፍያና በሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ደረሰኝ ግብይት የማከናወን ግዴታ ፣ ከሦስተኛ ወገኖች ወይም የብድርና ሌላ ውል ተዋዋዮች መብት፣ ከወንጀል ኃላፊነት፣ ከሠራተኞች መብት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ዘርፈ ብዙ የመብትና ግዴታ ግንኙነት ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻርም የንግድ ፈቃድን በማከራየት የንግዱ ሥራ ቢሠራ በአገልግሎቱ ጥራት፣ በተገልጋይው መብት፣ በንግዱ ቁጥጥር፣ በግብር ክፍያ፣ በተጠያቂነትና በሌሎች ሁኔታዎች ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ውጤት ይኖረዋልን? የሚለውን ሥጋቶች ለመከላከል የንግድ ፈቃዱን ላልተፈቀደለት ሰው በኪራይ እንዳይተላለፍ በሕግ መከልከሉ መፍትሔ ይሆናል የሚል ሃሳብ ያጭራል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 ከመውጣቱ በፊት ከ13 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ በነበረው አዋጅ ቁጥር 67/1989 ማንኛውም ሰው በንግድ መዝገብ ሳይመዘገብ የንግድ ሥራ መሥራት እንደማይችል፣ የንግድ ድርጅት ለሌላ ሰው በሚተላለፍበት ጊዜ የቀድሞው ፈቃድ ተመላሽ ተደርጎ ድርጅቱ የተላለፈለት ሰው በስሙ ፈቃድ ማውጣት እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን በአዋጁ መሠረት በወጣው ደንብ ቁጥር 13/1989 መሰረትም ከአዋጁ በተመሳሳይ ሁኔታ ነጋዴው የቅርብ ጊዜ ፎቶ ግራፉንና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎችን አሟልቶ መመዝገብ እንዳለበት በአስገዳጅነት ተደንግጓል፡፡