የማስረጃ ሕግ የማስረጃን አግባብነት፣ የማስረጃን ተቀባይነት እንዲሁም የማስረጃን ክብደትና ብቃት የሚገዙ ደንቦችና መርሆዎች ጥርቅም ነው፡፡ ማስረጃ ተሟጋቾች በአቤቱታቸው አማካኝነት ፍርድ ቤት የያዘውን ጭብጥ የሚያረጋግጡበት ዘዴ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ማስረጃ ማለት ፍርድ ቤት የያዘውን አከራካሪ ጉዳይ ወይም ጭብጥ በሚሰማበት ጊዜ ተሟጋቾች የጥያቄውን አግባብነት፣ እውነትነት፣ በምስክሮች፣ በሠነድ፣ ተጨባጭነት ባላቸው ሌሎች ነገሮች፣ ወዘተ… ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ የሚያረጋግጡበት አሊያም ውድቅ የሚያደርጉበት ዘዴ ነው፡፡ ማስረጃ ሲባል የአንድን ፍሬ ነገር ህልው መሆን ወይም አለመሆን ለማረጋገጥ ያገለግል ዘንድ ክስ በሚሰማበት ጊዜ ወይም የክርክር ጭብጥ በሚጣራበት ወቅት በተከራካሪ ወገኖች ወይም ክርክሩን በሚያየው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አማካኝነት የሚቀርብ ማናቸውም ዓይነት የአስረጂነት ባህርይ ያለው ነገር ነው፡፡ ማስረጃ በምስክሮች (Witnesses)፣ በዘገባ (Record)፣ በሠነድ (Document)፣ ተጨባጭነት ባላቸው ሊታዩ ሊዳሰሱ በሚችሉ ነገሮች (Concrete Objects) እና በኤግዚቢት መልክ ሊቀርብ ይቸላል፡፡ አቀራረቡም በሕግ በተደነገገው ሥርዓት መሠረት ነው፡፡ የክርክሩን ጭብጥ ፍሬ ነገር እውነት ወይም ሀሰት መሆኑን የማሳመን ኃይል ያለው እንደመሆኑ እና በዚህም ወደ ውሳኔ የሚያደርሰው ስለሆነ ሊገኝም ሊቀርብም የሚገባው በሕግ አግባብ ነው፡፡ ማስረጃው ተቀባይነት ወይም ውድቅ የሚደረገው እንደዚሁም ሊሰጠው የሚገባው ክብደት የሚመዘነውም በሕግ አግባብ ነው፡፡
Copyright © 2023 Abyssinia Law | Making Law Accessible! . All Rights Reserved.
Maintained by Liku Worku Legal Service