Font size: +
9 minutes reading time (1854 words)

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ትኩረት ያልሰጠበት የገበያዉ ሁኔታ እና አተገባበሩ

የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ በሽታዉን ከመቋቋም ጎን ለጎን ኢተዮጵያ ካጋጠማት ችግሮች መካካል አንዱ የገበያ በተለመደዉ የፍላጎትና አቅርቦት መርህ (Demand and supply) አለመሄድ ነዉ፡፡ ይህ ችግር በአብዘኃኛዉ ያደጉ ሃገራት ላይ በተለይ በእንደዚህ አስጊ ሰዓት የመፈጠር እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነዉ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በንጽጽር በአደጉት ሃገራት ያሉ ነጋዴዎች ያዳበሩት የንግድ ስነ ምግባር (Business ethics) ከእኛ የላቀ መሆኑ ነዉ፡፡ በሽታዉን አስመልክቶ በገበያዉ ብዙ አይነት ሸማቹን አደጋ ላይ የጣሉ ነገሮች ከአዋጁም በፊት ይሁን እሱን ተከትሎ እየተከሰቱ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያክል ወደ ጎን /ወደ ታች/ ባሉ ነጋዴዎች የሚደረግ የንግድ ዉድድሩን የሚገቱ ስምምነቶች፤ እነዚህም ስምምነቶች ዋጋን ከፍ ማድረግ፣ መጠንን መቀነስ፣ የንግድ እቃዎችን መደበቅ፣ ሸማቾችን መምረጥ (ማግለል ) እና መሰል ድርጊቶችን ያካተቱ ናቸዉ፡፡ እንዲሁም ነጋዴ ወይንም ነጋዴ ባልሆኑ ሰዎች ደግሞ የማከማቸት ስራዎች በተለይ በከተሞች ላይ ጎልተዉ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸዉ፡፡ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን እነዚህን ጉዳዮች የሚገዛ የህግ ማዕቀፍ ማለትም (የገበያ ዉድድር ና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ 813/2006) ቢኖራትም ነገር ግን ችግሩን ለማቃለል ብዙ የአፈጻፀም ጉድለቶች ይስተዋሉበታል፡፡ ይሀንንም አስመልክቶ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁና አሱን የሚያብራራዉ ደንብ ነበር፡፡ ነገር ግን በተጠበቀዉ ደረጃ ሳይሆን ገበያን ከመቆጣጠር አንጻር ትልቅ ክፍተትን ያሳያል፡፡

በዚህ አጠር ያለ ፅሁፍ ላይ አዋጁ ገበያን ከማረጋጋት አንጻጻር ትኩረት ማድረግ የነበረበትን ነገሮች እና ክፍተቶቹን፣ እንዲሁም ደግሞ በአፈጻጸም ደረጃ መሻሻል ያለባቸዉን ነገሮች ለመዳሰስ እንሞክራልን፡፡

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁና ዝርዝር ደንቡ ያሉበት ክፍተቶች፡- ከገበያ ቁጥጥር አንጻር

የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣዉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ቁጥር 3/12 እንዲሁም እርሱን ለመስፈፀም የወጣዉ ደንብ ቁጥር 466/2012 ገበያዉን በመቆጣጠር ደረጃ የሰጡት የህግ ማዕቀፍ በጣም ዝቅተኛ ነዉ፡፡ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ቁጥር 3/12 መግቢያ አንቀጽ (Paragraph) ሶስት ላይ እንዲሁም በደንቡ መግቢያ ላይ ዋነኛ ተድርጎ ከተነሱት አለማዎች መካከል በወረርሽኙ የሚመጣዉን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመቀነስና ለመቆጣጠር እንደሆነ ተሰምሮበታል፡፡ ኢኮኖሚዉን ደግሞ ፈር ከምናሲዝበት መንገዶች አንዱ የገበያዉ መረጋጋት ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ምንም እንኳን ህዝቡ ከወረርሽኙ ባሻገር በስግብግብ ነጋዴዎች በኩል የሚመጣዉን ረሃብን ቢፈራና ችግርም እየደረሰበት ቢገኝም አብዝኃኛዉ የደንቡ ዝርዝር ድንጋጌዎች ወረርሽኝ ስርጭቱ ላይ ያተኮሩ ናቸዉ፡፡ ለምሳሌ ስብሰባዎችን የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን መከልከል፣ የትራንስፖርት ተሳፋሪዎችን ቁጥር መገደብ፣ እንዲሁም መሰል የሰራተኞችና ተከራዮችን ጥቃም የያዙ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ ይህን ማድረጉ የሚነቀፍ አይደለም ነገር ግን ከበሽታዉ እኩል ህብረተሰቡን እረፍት የነሳዉን የገበያ አለመረጋጋት እና ስርዓት አልበኝነቱ ለምን እንደታለፈ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነዉ፡፡

ይህንን አስመልክቶ በደንብ ቁጥር 466/2012 አንቀጽ 4 (16) ላይ ብቻ አንድ ነገርን አስቀምጧል፡፡ ይህም ምን ይላል፤ በቂ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉን እንደሚከተለዉ እናያለን፡፡

 ማንኛዉም አምራች ወይንም አገልግሎት ሰጭ ድርጅት የኮቪድ 19 ን ስርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለዉን ጉዳት ለመቀነስ ለሚደረገዉ ጥረት አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎት እንዲሰጥ፤ አገልግሎቱን እንዲያሰፋ፣ ምርት እንዲያመርት የሚያመርተዉን ምርት መጠን እንዲጨምር፣ አዲስ ምርት አይነት እንዲያመርት ወይንም ምርቱን መንግስት በሚወስነዉ ተመጣጣኝ ዋጋ ለመንግስት፣ ለሸማቾች እንዲሁም ለህብረት ስራ ማኃበራት እንዲሸጥ መሚኒስትሮች ኮሚቴ ወይንም ኮሚቴዉ ዉክልና በሰጠዉ የመንግስት አካል የሚሰጠዉን ትዕዛዝ ተግባራዊ ማድረግ አለበት፡፡

እዚህ ላይ የተዳሰሱት ነገሮች በደንብ በጥልቀት ስናያቸዉ ከአምራች ምርትን በመረከብ የሚሸጠዉን ነጋዴ ለመቆጣጠር የወጣ አይነት ህግ አይደለም፡፡ ምርት የሚያመርት ወይንም ግልጋሎት የሚሰጡ ድርጅቶች መንግስት ምርቱን አስመልክቶ የብዛት፣ የጥራት ና ዋጋ ገደብን መስቀመጥ እንደሚችል ለማሳወቅ ታስቦ የወጣ አይነት ድንጋጌ ነዉ (Quantity, quality and price of goods may be regulated) ምና አልባት እንኳን አገልግሎት ሰጭ የሚለዉ ነጋዴዎችን እንኳን ይመለከታል ቢባል በእነርሱ በኩል ተንሰራፍቶ የሚገኘዉን፤ከኮሮና እኩል ህብረተሰቡን አደጋ ላይ የጣለዉን ምርት ማከማቸት ና መደበቅ ግን ታሳቢ ያላደረገ ድንጋጌ ነዉ፡፡ ይህም ማለት በ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ዉስጥ በክልክል ሁኔታ ተቀምጠዉ ነገር ግን ለትርጉም አሻሚ እና ለአፈጻጸም አስቸጋሪ የሆኑትን የንግድ ዕቃን ማከማቸት ና መደበቅን አስመልክቶ ደንቡ ምንም የሚያወራዉ ነገር የለም ማለት ነዉ፡፡ ቢቻል ደንቡ እነዚህን እና መሰል በገብያ እያጋጠሙ ያሉ ከ ወረርሽኙ እኩል የሚስተካከሉ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ ነበረበት፡፡ ምክንያቱም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ዋናዉ አላማ በ ተለመደዉ የህግ ሥርዓት ለመፍታትና ዉሳኔ ለመስጠት አስቸጋሪ የሆኑ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ መሰናክሎችን ማሳለፍ ነዉ፡፡ ስለዚህ ይህ ከሆነ በሰፊ ደረጃ የሚታየዉን የገበያ ችግር በተለይ የንግድ ምርቶችን መደበቅ፣ ማከማቸት ና በተጋነነ ዋጋ መሸጥ ላይ በግልጽ ትኩረት መስጠት ነበረበት፡፡ ይህም ማከማቸት ማለት ምን እንደሆነ፣ የትኞቹን የንግድ እቃዎችን እንደሚመለከት፣ ፍጹም ክልከላ ነዉ ወይንስ ልዩ ሁኔታ ይኖረዋል፣ ለሸማቾችች ይህ መብት የሚሰጥ ከሆን ምን ያክል ነዉ የሚፈቀደዉ የሚለዉ ግልጽ መሆን አለበት ትረጉሙም እንደሚያሳየን (hoarding means the practice of obtaining and holding resources in quantities greater than needed for one's immediate use.) በተጨማሪም ኃላፊነቱንም በተመለከተ እርምጃ መዉሰድ ያለበት ማን እንደሆነ በግልጽ መመላከት ይኖርበታል፡፡ የንግድ ቢሮ/የሸማቾች ባለስልጣን/ ነዉ ወይንስ የኮማንድ ፖስቱ የሚለዉ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ተከማችቶ የሚገኘዉም ምርት በምን መንገድ መስተናገድ እንዳለበት መቀመጥ ይኖርበታል፡፡

 

ይህ ደግሞ ወጥ የሆነ አሰራር ሃገሪቱ ላይ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ወደ ግብረ ኃይሉ ገብቶ ለ አደጋ ግዜ ቁጥጥር ወደ ሚሰበሰበዉ ነዉ ገቢ የሚደረገዉ ወይንስ ተመልሶ ወደ ሸማቾች ኅብረት ተሸጦ ከእዚያም ለህብረተሰቡ በተተመነ ዋጋ ይከፋፈላል የሚለዉ ነገር ጥርት ብሎ መታወቅ ያለበት ነገር ነዉ፡፡

ይህንንስ መወሰን ያለበት ፍርድ ቤት ነዉ፣ ከተማ አስተዳደሩ ነዉ ወይንስ ግብር ኃይሉ የሚለዉም መታዎቅ ያለበት ነገር ነዉ፡፡ ይህ ችግር አጉልቶ ለማሳየት ለምሳሌ በደሴ ከተማ አስተዳደር በቧንቧ ወሃ ክፍለ ከተማ በቀን 29/07/12 ተከማችቶ የተገኘዉን የፓልም ዘይት ባለ 20 ሊትር 1990 ጀሪካን፣ ባለ 3 ሊትር 5850 ጀሪካን፣ ፈሰሽ ዘይት ባለ 5 ሊትር 933 ጀሪካን፣ 602 ኩንታል ስኳር ና 112 ኩንታል ሩዝን አስመልክቶ ከተማ አስተዳደሩ በተተመነ ዋጋ ለ አምስቱም ክፍለ ከተማ ሸማቾች ማኅበር በኩል ለህዝብ እንዲሸጥ እና ከዚያም ገንዘቡ በሞዴል 85 ደረሰኝ ተቆርጦለት በአደራ በገቢዎች እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡ የሌሎች ከተማ ተሞክሮ ምን ይመስላል የትኛዉ የተሻለ እንደሚሆን በጥናት አረጋግጦ መስቀመጥ ይኖርበታል፡፡

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ በዝርዝር ማከማቸትና መደበቅ ምን እንደሆነ፣ በምን ደረጃ ሲሆን እንደሚያስቀጣና ተያያዥ ጉዳዮችን፤ እንዲሁም ደግሞ የሌሎችን ህግ ተግባራዊነት ጉዳይ ሳያነሳ ነገር ግን በአንቀጽ 6 (2) ላይ የክልል እና የፊደራል ፍርድ ቤቶች በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ ለሚመጡ የንግድ ዕቀዎችን ማከማቸት ና መደበቅን በአፋጣኝ ለማስተናገድ የሚዉል ችሎት እንዲያዘጋጁ ያዛል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ ደንቡ ስለ ማከማቸት ቃላትን የተጠቀመዉ አዚህ ላይ ነዉ፡፡ ወደ ፍርድ ጉዳይ ከመሄድ በፊት ዝርዝር ሁኔታዎችን በደንቡ ማስቀመጥ ነበረበት፡፡

 

ለምን አስቸኳይ ግዜ አዋጁ በገበያ ያለዉን አለመረጋጋት እንዲፈታ ይጠበቃል? 

 

አንድ አንድ ሰዉ የንግድ ዉደድር ና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 በቂ ድንጋጌ እያለዉ በዚህ ላይ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ መዘርዘር አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡፡ የእዚህም መሰረቱ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጁ የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ተግባራዊ ከመሆን የሚያግደዉ ባለመሆኑ ነዉ፡፡ ነገር ግን በሦስት ምክንያቶች ይህን የገበያ ችግር በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ቢታቀፍ የተሻለ አተገባበር ይኖረዉ ነበር፡፡ አንደኛ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሚከለከሉ ክልከላዎች በተሸለ መንገድ እንዲሁም በፍጥነት የመተግበር ዕድላቸዉ ከፍተኛ ነዉ፡፡ የተጠናከረ ግብረ ኃይል ለእዚሁ አላማ ስለሚዋቀር ይህንን ችግር ተከታትሎ የመስፈፀም ና እርምጃ የማስወሰድ አቅሙ ትልቅ ነዉ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ የንግድ ሁኔታዎችን ተፈጻሚ የሚያደርጉት የገበያ ዉድድር ና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን እና ንግድ ቢሮ ድክመት ማሳየታቸዉ ነዉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማህበረሰቡ ደረጃ የመሰማት ና ዕዉቅና የማግኘት ሁኔታዉ ከተራዉ አዋጅ የተሸለ ነዉ፡፡ በተለይ ይህ ምክንያት በነጋዴዉና በ ሸማቾች ማህበረሰብ ዘንድ ብዙም ዕዉቅና እና የግንዛቤ ስራ ያልተሰራበትን የንግድ ዉደድር ና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ችግርን የማቃለል ዕድል ይኖረዉ ነበር፡፡ ይህ ህግ ማለትም አዋጅ ቁጥር 813/2006 በአብዝኃኛዉ የሚተቸዉ በንግድ ማህበረሰቡ ዘንድ እንኳን ምን እና የትኛዉ የንግድ ሁኔታዎች ክልክል ና የተፈቀደ መሆኑ የግንዛቤ እጥረት መኖሩ ነዉ፡፡ ለእዚህም ችግር ተጠያቂ የሚሆነዉ የንግድ ዉድድር ና ሸማቾች ባለስልጣን (Trade competition and consumer protection authority) ነዉ፡፡ ምክንያቱም በ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ (2) ና (6) ላይ ከተደነገጉት የባለስልጣኑ ተግባር ና ኃለፊነት ዋነኛዉ የአዋጁን ተፈጻሚነት በህዝብ ዘንድ እዉቅና እንዲኖረዉ ማድረግ፣ በህጉ ላይ ግንዛቤ እንዲኖር የትምህርት ና ስልጠና መድረኮችን ማመቻቸት ነዉ፡፡ ነገር ግን በእዚህ ላይ ባለስልጣኑ የሚሰራዉ ስራ አነስተኛ እንደሆነ ጥናታዊ ጽሁፎች ያሳያሉ፡፡ ህጉን አስመልክቶ በዳኞችና በአስፈጻሚ አካላትም ሳይቃር ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ለየት ባለ መልኩ ይህ የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ማከማቸትና መደበቅን አስመልክቶ አሻሚ እና ሙሉ ባለሆነ መንገድ ያስቀመጠዉ ድንጋጌ ነዉ፡፡ በተለይ የኮሮናን በሽታ እና የወቅቱን የገብያ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ይህ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ በተሸለ ና ግልጽ በሆነ መንገድ ቢያስቀምጠዉ ጥሩ የሆነ አፈፃፀም ይኖረዉ ነበር፡፡ በዋነኝነት የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 በወቅቱ ያለዉን የማከማቸት ና የመደበቅ ሁኔታ አሁን ባለዉ የህግ ማዕቀፍ ይፈታል የሚል እምነት የለኝም፡፡

አጠር ባለ መልኩ የአንቀጹን ክፍተት እንደሚከተለዉ እናያለን፡፡ የአዋጅ ቁጥር 813/2006 ማከማችትና መደበቅን በ አንቀጽ 24 ላይ አስቀምጧል፡፡ ከአንቀጽ 24 (1) ብንጀምር ተደበቀ ወይንም ተከማቸ የሚለዉ ነገር በንግድ ሚኒስተር በኩል እጥረት ያለባቸዉ የንግድ ዕቃዎች ተብለዉ መለየት እንዳለባቸዉ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ማለት በሚኒስተሩ በኩል በመመሪያ ካልወጣ ምንም እንኳን በገበያ ላይ እጥረት ያለበት ጉዳይም ቢሆን ማከማችታና መደበቅ ክልከላ እንዳልተደረገበት ነዉ፡፡ በዚህ ሰዓት የንግድ ሚኒስተር ወረርሽኙን አስመልክቶ በገበያዉ እጥረት ያጋጠሙትን ነገሮች ዘርዝሮ አላቀረበም፡፡ ስለዚህ አስቸኳይ ግዜ አዋጁ በደንቡ ላይ እጥረት ያለባቸዉን አቅርቦቶች ከንግድ ሚኒስተር ጋር በመሆን ግልጽ ቢያደርጋቸዉ እና በደንቡ ታቀፊ ቢያደርግ የተሻለ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ነጋዴ ባልሆኑ ሰዎች ደግሞ ተከማቸ/ተደበቀ/ ማለት በንግድ ሚኒስተር እጥረት አጋጥመዋል የሚባሉ እቃዎችን ከግል እና ከቤተሰብ ፍጆታ በላይ ማከማቸት አንደሆነ በአንቀጽ 24 (1)ሀ ላይ ተደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ አዋጅ በአንቀጽ 24 (5) ደግሞ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በግል እና በቤተሰብ ፍጆታ የሚከማቸዉ ምን ያክል መጠን እና ለምን ያክል ግዜ የሚለዉ በተመሳሳይ ንግድ ሚነስተር በኩል በሚዋጣ የህዝብ ማስታወቂያ ይፋ እንደሚሆን አስቀምጧል፡፡ ይህም በተመሳሳይ ሁኔታ አሁን ተፈጥሮ ያለዉን ኮሮና ወረርሽኝን አስመልክቶ የንግድ ሚኒስተሩ ምንም ያወጣዉ የመጠን አና የግዜ ሁኔታ የለም፡፡ ይህንንም አስመልክቶ አስቸኳይ ግዜ አዋጁ በደንቡ ላይ ቢያስቀምጠዉ ለተግባረዊነቱ የተሻለ እና ቀላል ይሆን ነበር፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በዚህ ጉዳይ ተከሰዉ ፍርድ ቤት በሚቆሙ ግለሰቦች ላይ ዳኞች ህጉን አስመልክተዉ የመተርጉም ችግርን በማስወገድ ወጥ የሆነ የዳኞች አሰራር/ትርጉም/ እንዲኖር ይረዳል፡፡

 

ሌላዉ ከእዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳዉ ለነጋዴዎች የሚፈቀደዉ የማከማቸት መጠን ካላቸዉ ካፒታል ከ 25% ባልበለጠ ደረጃ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ እዚህ ጋር ደግሞ ሊነሳ የሚችለዉ ጥያቄ ይህን ፐርስንት ድረስ መፍቀድ በእዚህ ሰዓት አግባብነቱ ምን ያህል ነዉ የሚለዉ አጠያያቂ ነዉ፡፡ ሌላዉ ችግሩ ደግሞ ጉዳዩን የመመርመር ስርዓቱን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ እስከ 25% ነዉ ወይንስ ከእዚያ በላይ የተከማቸዉ የሚለዉን መመርመር ብቻዉን ለተግባራዊነቱ ህፀፅ ይፈጥራል፡፡ እነዚህን ነገሮች አስመልክቶ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ዝርዝር ደንብ ምንም የታሰበበት ነገር አለመኖሩን ነዉ፡፡ ይፈቀዳል /ይከለከላል/ የሚለዉም በእንጥልጥል ያለ ጉዳይ ነዉ፡፡

 

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በገበያዉ ላይ ያለዉ አተገባበር ህጋዊነት እና የመፍትሔ ሃሳቦች

 

አሁን በተግባር አስቸኳይ ግዜ አዋጁን እንዲፈጸም የሚያደርጉት ግብር ኃይላት ከሚሰሩት ተግባራት ዉስጥ አንዱ የንግድ እቃ ክምችት እና መደበቅን ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ክትትል ማድረግ ነዉ፡፡ ይህንን አስመልክቶ የሚያስነሳዉ ትልቅ ጥያቄ፤ ይህ ጉዳይ በአዋጁም ይሁን በደንቡ ምንም የዝርዝር ሁኔታ ያልተቀመጠበት ጉዳይ መሆኑ ነዉ፡፡ ይህም ማለት ምን አይነት የንግድ እቃዎች?፣ በማን?፣ በምን ያክል መጠን መከማቸትን እንደሚያስብል፤እንዲሁም ተከማችተዉ የሚገኙት እቃዎች እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን በግልጽ ያላካተተ ነዉ፡፡ ነገር ግን ከህጋዊነት በተፃራሪ መንገድ በየደረጃዉ ያሉ ግብር ኃይላት ዛሬ ላይ ክትትል እንደሚያደርጉ እና ለህግ እንደሚያቀርቡ በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ነገር በአስቸኳይ ግዜ አዋጁም ይሁን በደንቡ ስልጣን ያልተሰጠበት፤ሆን ብሎም ይሁን በቸልተኝነት ህግ አዉጭዉ የንግድ ሁኔታዎች በተለይ ከማከማቸት ና ከመደበቅ አንጻር ያለፈዉ ነገር ግን በተግባር እየተሰራበት ያለ ሁኔታ ነዉ፡፡ ከአተገባበር አንጻር ይህ ህጋዊነትን ተከትሎ እየተሰራ ያለ ስራ አይደለም፡ ስለዚህ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ደንብ እንደማንኛዉም ህግ መሻሻል የሚችል በመሆኑ የሚኒስትሮች ምክርቤት በኩል ደንቡ በገበያዉ ላይ ያለዉን አተገባበር በተለይ በኮሮና ምክንያት በገበያዉ አይሎ ያለዉን እና በአዋጅ ቁጥር 813/2006 በአሻሚ ሁኔታ የተቀመጠዉን የንግድ ዕቃ ማከማቸት ና መደበቅና መሰል ሁኔታዎችን ከንግድ ሚኒስተር ጋር በመሆን በግልጽ በደንቡ ታቃፊ ቢሆን ለአፈጻጸምም ይሁን ለህጋዊነቱ ትልቅ አስተዋፆ ይኖረዋል፡፡ የንግድ ሚኒስተርም ቢሆን እሰካሁን ያሉትን የገበያ ሁኔታ ለይቶ በማስቀመጥ ዝርዝር የገበያዉን ክፍተቶች በመደበኛዉ ህግ ለመፍታት አዳጋች ስለሚሁን፤በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ደንብ በግልጽ እንዲታቀፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

 

ማጠቃልያ

 

መንግስት ከኮሮና በተያያዘ ያጋጠመዉ ትልቅ ችግር የገበያዉ አለመረጋጋት ነዉ፡፡ በተለይ ደግሞ ነጋዴዎች እና አንድ አንድ ግለሰቦች የሚፈጽሙት የምርት ማከማቸት ና መደበቅ በዋነኝነት ይነሳል፡፡ ይህንንም ችግር አስመልክቶ ለመቅረፍ ኢትዮጵያ በአዋጅ ቁጥር 813/06 ላይ የንግድ ና ሸማቾች ጉዳይን የሚገዙ ድንጋጌዎችን አስቀምጣለች፡፡ ነገር ግን ይህ ህግ በእንደዚህ አይነት ከባድ ሁኔታ ላይ አይደለም፤ ከወረርሽም በፊት ብዙ የአፈጻጸም ችግር የሚስተዋልበት የህግ ክፍል ነዉ፡፡ ለእዚህ ትልቁ መፍትሄ ደግሞ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ነበር፡፡ ነገር ግን በተጠበቀዉ ደረጃ ሳይሁን ይህ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁና ዝርዝር ደንቡ የገበያዉን አለመረጋገት በተለይ ደግሞ የነጋዴዎች ምርትን ከማከማቸትና ከመደበቅ አንጻር ችግሩን ለመፍታት በዙ ክፍተት የሚታይበት ሁኗል፡፡ በተግባር ግን ይህንን የገበያ ችግር መንግስት ና ኮማንድ ፖስቱ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንደሚፈቱት ና ሙከራ እየተደረገ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ነገር ግን በየትኛዉ ድንጋጌ እንደሆነ ግር የሚያሰኝ ነገር ነዉ፡፡ ስለዚህ ከወረርሽኙ እኩል ህዝቡን እየፈተነ የሚገኘዉን የገበያ አለመረጋጋት ከመደበኛዉ ህግ ስርዓት ይልቅ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መፍታት ጉልህ ሚና ስለሚኖረዉ ና አሁን ያለዉ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ አስከ አምስት ወር እንደአስፈላጊነቱ የሚቆይ በመሆኑ፤የሚኒስትሮች ምክር ቤት የገበያዉን ሁኔታ ቸል ሳይል ደንቡን በማሻሻል ዝርዝር የንግድ እቃን ማከማቸትና መደበቅን ቅጣቱን እና አፈጻጸሙን ሳይቀር ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ በሚሆንበት ግዜ አንገብጋቢዉ የገበያ ጉዳይም ቢሆን አፋጣኝ የሆነ ህጋዊ መስመሩን የጠበቀ ዉጤታማ ስራ ይሰራበታል፡፡  

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ሐሰተኛ ደረሰኝ - ገቢዎች ሚኒስቴር እራሱ በድሎ እራሱ አለቀሰ !
Corona Virus and Force Majeure

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 20 September 2024