በኮንስትራክሽን ውሎች አፈጻጸም ወቅት ለሚስተዋሉ ጉዳቶች (Risks) ተጠያቂ ማን ነው?

“All courses of action are risky, so prudence is not in avoiding danger (it’s impossible), but calculating risk and acting decisively. Make mistakes of ambition and not mistakes of sloth. Develop the strength to do bold things, not the strength to suffer.” 

Niccolo Machiavelli, The Prince

መግቢያ

እንደሚታወቀው ግጭትና አደጋ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዋና መገለጫወች እስኪመስሉ ድረስ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ነገሮች ናቸው፡፡  (ብሪያን ሻፒሮ፡1) የኮንስትራክሽን ውል በጣም ውስብስብና ብዙ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ውል ነው፡፡ በይዘትም ሆነ በጥልቀት በጣም ሠፊ ከመሆኑ የተነሳ ውቂያኖስ መሰል ውል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለምን ቢባል በተለያየ ዕውቀትና ሙያ ዘርፍ የሚሳተፋ ሰወች ከመኖራቸው አልፎ በየደረጃው ዘርፈ-ብዙ ግንኙነቶች መኖራቸው፤  የተለያዩ ጊዜ ወሰድ የዲዛይን ለውጦችና ማሻሻያወች ስለሚስተዋሉበት ነው፡፡  (ዮሐንስ እንየው፡2008፡1)

ታዲያ! ይህ ውል በሚፈጸምበት ወቅት የተለያዩ ግጭቶችና አለመግባባቶች መነሳታቸው የማይቀር ነው፡፡ ለነዚህ ግጭቶች ደግሞ መነሳት የአንበሳውን ድርሻ (lion’s share) የሚወስደው ጉዳቶችን እና አደጋን ማን ይሸከም (shouldering risks) እንዲሁም ማን ይውሰድ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ጸሀፊው በዚህ አጭር ጽሁፍ ከዓለም አቀፋ የአማካሪ ማህንዲሶች ፌዴሬሽን/FIDIC/ ህግ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ህግጋት አንጻር የኮንስትራክሽን ኃላፊነቶችን እና አደጋወችን በአጭሩ ለመቃኘት ይሞክራል፡፡

የአደጋ ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች /The jurisprudence of risk/

ጉዳት የሚለው ቃል በራሱ ከሕግ አስተምህሮ ብቻ የሚታይ እና የሚተነተን ቃል አይደለም፡፡ ለምን ቢባል ቃሉ በተለየም በምጣኔ ሃብት፤ በንግድ፤ በምህንድስና፤ በህክምና እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስም ጭምር የራሱ የሆነ ትንተና እና ትርጓሜ ስለሚሰጠው ነው፡፡

በፍልስፍናው ካየነውም አደጋ ማለት የነገሮች መከሰት እርግጠኛ ካለመሆን /uncertainty/ ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ እንዳውም አደጋ ሲኖር የአንድ ነገር አለመታወቅ ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም የተጓዳኝ ውጤቱ ከጥርጣሬ የሚመነጭ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡  (ሰቭን ሐንሰን፡2002፡1)

በአጠቃላይ የውል ህግ መርሆ እንደሚያስገነዝበው ጉዳት ምንጊዜም ቢሆን ንብረቱ ባለበት አብሮ የሚሄድ እንዲሁም ኃላፊነቱን የሚወስደውም ንብረቱን እጅ ያደረገው አካል እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሳይጠቀስ የማይታለፍ አንድ አባባል አለ፡፡ ይህም በተለይ የሲቪል ሕግ ሥራዓት በሚከተሉ ሃገራት(Civil law legal system) የሚነገር ብሂል ነው::ይህም አባባል latin “res peri domino”/ English translation “risk follows ownership”.

ዛሬ ዛሬ ታዲያ ከዚህ ብሂል በመነሳት አብዛኛው ሰው አንድ ንብረት በቁጥጥራችን ሥር ሲሆን ሃላፊነቱን/ risk/ ትወስዳለህ በማለት አስቀድመው ንብረቱን ልንይዝ ስንል የሚናገሩን ተግሳጽ እና ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ይህንን መርሆ ለማስገንዘብ ይመስላል፡፡

አደጋ (risk) ምንድን ነው?

አደጋ ማለት የተቃጣ፤ የተዘበበ፤ የሚደርስ ወይም የደረሰ ጉዳት ማለት ነው፡በታላቋ ብሪታኒያመሰረቱን ያደረገው የፕሮጀክት ሥራ አመራር ማህበር አደጋን አስመልክቶ እኤአ በ2004 በሰጠው ትርጉም risk as “Any uncertain event or set of circumstances that, should it occur, would have an effect on one or more objectives”በዚህም መሰረት አደጋ ማለት ማነኛውም ያልተረጋገጠ ክስተት ሲሆን በአንድ ወይም በርካታ ዓላማወች ላይ ተጽኖ የሚያሳድር ነገር ነው፡፡ በተለይም ብላክስ ሎው መዝገበ ቃላት የሚከተለውን ነጥብ አስቀምጧል፡- “Risk means the uncertainty of a result, happening, or loss; the chance of injury, damage, or loss; esp., the existence and extent of the possibility of harm.” አደጋ ማለት ያለተገመተ ጉዳት ወይም ክስተት ብሎም ህጸጽ እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡

በሌላ በኩል የቢዝነስ መዝገበ ቃላትም ደግሞ የሚከተለውን ዘርዘር ያለ ትርጉም ሲሠጠው እናያለን “Risk is a probability or threat of damage, injury, liability, loss or any other negative occurrence that is caused by external or internal vulnerabilities and that may be avoided through preemptive action.” በማለት አደጋ ሊደርስ ከሚችል ጉዳት፤ ጥፋት እና ኃላፊነት ጋር ይገልጸዋል እንዲሁም መንስኤውም የውስጥ ወይም የውጪ ተጋላጭነት እንደሆነ ብሎም አደጋን አስቀድመው ሊከላከሉተ እንደሚቻል ጭምር በአጽኖት ትርጉም ለመስጠት ይሞክራል፡፡

በግንባታ ወቅት ባለቤቱ፤ ኮንትራክተሩ፤ ቀራጺው እንዲሁም መሃንዲሱ በፕሮጀክተቱ ወቅት ሊደርሱ የሚችሉ አደጋወችን አስቀድመው ሊያስቡ ይገባል፡፡ በተለይም አንዳንድ አደጋወች በሁሉም ፕሮጀክቶች የሚከሰቱ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ በተወሰኑት ብቻ ሲስተዋሉ ይታያሉ፡፡ በአብዛኛው የኮንስትራክሽን ግንባታ ውሎች የሚታዩትም የዲዛይን አተረጓጎም፤ የአካባቢያዊ ተጽኖ፤ የገንዘብ ነክ ጉዳዮች፤ የፕሮጀክት ገንዘብ ወጪ ዝርዝር፤ የግንባታ ሥህተቶች፤ የቦታ መረጣ ሥህተት፤ የሥነ-ምድር ቴክኒካዊ ጉዳዮች፤ የአፈጻጸም መዘግየት፤ ተጨማሪ ሥራወች፤ ምርታማነት መቀነስ፤ በቦታው ያሉ መንግስታዊ አካላት ተጽኖ እና ከሃቅም በላይ የሆኑ ችግሮች/force majeure/ ይጠቀሳሉ፡፡

 የፕሮጀክት አደጋወች

የተፈጥሮ

ፓለቲካዊና ማህበራዊ

ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ

ባህሪ

የአየር ንብረት ለውጥ

ጦርነት፤ ብጥብጥ

የዋጋ ንረት

የአሠሪ ባህሪ

መልካምድራዊ እና ስነ መሬታዊ ሁኔታ

የሥራ ውዝገቦች፤ ሥራ ማቆም አድማ

የግብዓት እጥረት

የኮንትራክተሩ ጠባይ

ሌሎች የተፈጥሮ ሁኔታወች

ዘረፍ፤ ውንብድና

የሠራተኛ እጥረት

 

የንዑስ ተቋራጮች አመል

 

የሕግ መቀየር

የሦስተኛ ወገኖች ባህሪ

 የአደጋ ዓይነቶች መግለጫ

ዓለም አቀፉ የአማካሪ ማህንዲሶች ፌዴሬሽን /International Federation of Consulting Engineers /FIDIC/1999/ ይዞታ

እንደሚታወቀው ዓለማቀፉ የአማካሪ ማህንዲሶች ማህበር/FIDIC/ ኃላፊነትን አስመልክቶ የተለያዩ ድንጋጌወችን አስቀምጧል፡፡ አንቀጽ 17 ንዑስ ቁ.2 ላይ የሚከተለውን ይደነግጋል፡፡

ኮንትራክተሩ ሥራው ተጀምሮ እስከሚያስረክብበት ድረስ ሙሉ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሆኖም በአንቀጽ 10(1) መሠረት የርክክብ ሠረተፍኬት ከተሠጠው ኃላፊነቱ የደንበኛው ወይም አሠሪው ይሆናል፡፡ ሆኖም ከአንቀጽ 17(3) ላይ ከተዘረዘሩት የደንበኛው(አሠሪው) የአደጋ/risks/ ኃላፊነት ውጪ ጉዳት ቢደርስ፤  ኮንትራክተሩ በራሱ ወጪ እና ሃላፊነት የተበላሹ እንዲሁም የተጎዱ ሥራወችን ማስተካከል ግዴታ አለበት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ የርክክብ ሠርተፊኬት ከተሰራ በኃላም ቢሆን ኮንትራክተሩ ኃላፊ የሚሆንበት አጋጣሚም አለ፡፡ ይህም ኮንትራክተሩ የሠራው ሥራ ጉዳት ወይም ጥፋት ካስከተለ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

በዚህ አጋጣሚ በFIDIC ህግ መሠረት የኮንስትራክሽን ውሎች በሚፈጸሙበት ወቅት የሚከተሉት ነገሮች ከተከሰቱ ጉዳቱን/risks/ የሚሸከመው ደንበኛው(አሠሪው) ነው፡፡ እነዚህም እንደ ጦርነት፤ ብጥብጥ፤ ወረራ፤ አመጽ፤ ሽብርተኝነት፤ አብዮት፡እርስበእርስ ጦርነት፤ የሽምቅ ጥቃት ወይም በፕሮጀክት ሳይቱ ላይ ከኮንትራክተሩ እንዲሁም አብረውት ከሚሰሩ ሠራተኞች ውጪ አመጽ እና ግርግር ቢፈጠር ወይም ከኮንትራክተሩ ጥፋት ውጪ ፈንጅና ተቀጣጣይ የጦር መሠሪያ የፕሮጀክቱን ሥራ ላይ ጥቃት ቢፈጸም ወይም በጣም ከፍተኛ ድምጽ ያለው ከአየር ግፊት ሞገዶች በተለየ በአውሮፕላን እና መሰል በራሪ ነገሮች የሚመጣ ጉዳት ወይም የፕሮጀክት ሳይቱን አሠሪው ከመጠናቀቁ በፊት መገልገል ቢጀመር አሊያም በአሠሪው የዲዛይን ለውጥ ከተደረገ እና አሠሪው ኃላፊ ከሆነ በመጨረሻም ማነኛውም ያለተገመተና ያለተጠበቀ የተፈጥሮ ኃይል በመድረሱና አንድ ምክንያታዊ ኮንትራክተር ያደርገዋል ተብሎ የማይጠበቅ ተግባር ተፈጽሞ ሲገኝ እንደሆነ ህጉ የአሠሪው ኃላፊነት ነው ሲል በማያሻማ መልኩ ያስቀምጣል፡፡

በአንጻሩ ደግሞ በፕሮጀክቱ ሥራ ላይ ዘረፋ እና ስርቆት ቢፈጸምበት ሙሉ ኃላፊነት የሚወስደው ኮንትራክተሩ ነው፡፡ ለምን ቢባል በአንቀጽ 9(1) መሠረት በሳይቱ ላይ ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ የኮንትራክተሩ ሥለሆነ ነው፡፡

ታዲያ ከላይ ከተዘረዘሩት አደጋ ውስጥ አንዱ በሚፈጸምበት ወቅት ውጤቱ እንደምን ነው ቢሉ ሕጉ በአንቀጽ 17(4) ላይ መልስ ይሠጥበታል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ኮንትራክተሩ ወዲያውኑ ከላይ የተዘረዘሩት ነገሮች ሲከሠቱ እና በሥራው፤ እቃወች ወይም ሠነዶች ላይ ችግር ካስከተሉ ለማሃንዲሱ ማስታወቅ አለበት፡፡ ሆኖም ግን ይህን እረምጃ በሚወስድበት ጊዜ ኮንትራክተሩ አፋጣኝ ምላሽ ካላገኘ ለዘገየበት እና ላወጣው ወጪ በአንቀጽ 20(1) መሠረት ክፍያ መጠየቅ ይችላል፡፡

ሌላው ጉዳይ በፕሮጀክት አፈጻጸም ወቅት አድስ ሕግ ቢወጣ የማን ኃላፊነት/risk/ነው? የሚለው ጥያቄ ተገቢ ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ FIDIC በአንቀጽ 13(7) ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የተቀየረ ህግ ወይም የተሻሻለ ህግ መኖሩ ብሎም ኮንትራክተሩ ተጨማሪ ወጪ ካስወጣው ኮንትራክተሩ የማራዘሚያ ክፍያ በአንቀጽ 20(1) መሠረት እንዲሁም ወጪወችን አሠሪው(ደንበኛው) እንዲሸፍን ይደረጋል፡፡ ሥለዚህ ከሕግ ጋር የተያያዙ ጉዳቶች/risks/ የአሠሪው እንደሆኑ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም ከባህሪ እና ሥነ ምግባር አንጻር የሚመጡ አደጋወች/Behavioral risks/ ማን ይሸከም የሚለው ጉዳይ ማየቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ለምን ቢባል አብዛኛውን ጊዜ ከባህሪ ጉድለት የመነጩ ችግሮች ፕሮጀክቶችን ሲያጓትቱ ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ ባለሃብቶች እንዳሻቸው በሳይት ማሃንዲሱ አማካኝነት ሥራው ከተጀመረ በኃላ የተለያዩ ትዕዛዞች እና መልዕክቶች ለኮንትራክተሩ ሲያስተላልፉ በአንጻሩ ደግሞ ወደ መጠናቀቂያው አካባቢ ከርክክብ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ንትርኮችኛ እና ዱላ ቀረሽ ስድቦች በአንዳንድ ባለሃብቶች ሲስተዋሉ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ኮንትራክተሩም አንዳንድ የባህሪ ችግሮች ይስተዋሉበታል ለምሳሌ ከጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች ብሎም ሥራውን በወከባ አጣድፎ ለመጨረስ መሞከረ ወ.ዘ.ተ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

የሆነው ሆኖ ከባህሪ ጋር የተያያዙ ጉዳቶች በአሰሪው እና በኮንትራክተሩ ሊሸፈኑ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡  በዚህም መሠረት የዘገየ ወይም የተሳሳተ ትዕዛዝ ከአሠሪው በማህንዲሱ በኩል ለኮንትራክተሩ ሲመጣ(አንቀጽ 16(4)፤ ሥራው የሚሠራበትን መሬት ርክክብ ዘግይቶ መስጠት(አንቀጽ 8(1)፤ በወቅቱ ክፍያ አለመፈጸም(አንቀፅ 13(1)፤ 24፤ 26(4))፤ የአለአግባብ ጣልቃ ገብነት እና የኮንትራክተሩን ሥራ በሳይት ማስተጓጎል(አንቀጽ 16(3)) መሠል ከባህሪ ጋር የተያያዙ ጉዳቶች በአሠሪው የሚሸፈኑ ሲሆን ዳሩግን ኮንትራክተሩ አደጋ እና ከባድ ጥፍት ቢያስከትል(አንቀጽ 22(1))፤ የንዑስ-ተቋራጮች/sub-contractors/ ያልተገባ ሥራ እንዲሁም ከጥራት ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚታዩ የኮንትራክተሩ ድርጊቶች ባጠቃላይ ኮንትራክተሩ የሚሸከማቸው አደጋወች /risks/ እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሆኖም ግን አንዳንዴ ከአሰሪውም ሆነ ከኮንትራክተሩ ውጪ በሦስተኛ ወገኖች ችግር ምክንያት የፕሮጀክት ሥራ ሲስተጓጎል ይታያል፡፡ (አንቀጽ 8(5)) ለምሳሌ የውሃ አቅርቦት መቋረጥ፤ የመብራት መጥፋት እንዲሁም መሠል ማህበራዊ ግልጋሎቶች መቆራረጥ በተደጋጋሚ ሲስተዋሉ ይታያል፡፡ ስለዚህ የሦስተኛ ወገኞች አደጋ /risks/ የሚመለከታቸው አካላት ይጠየቁበታል እንጀ የአሠሪው ወይም የኮንትራክተሩ ግዴታ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ ሕግ ያለው እይታ

በኢትዮጵያ ህግጋት ጉዳትን በተመለከተ አያሌ ድንጋጌወች አሉ፡፡ ለአብነት ያህልም በውል፤ በሽያጭ፤ በመድህን፤ በግንባታ ወዘተ የተለያዩ አናቅጽ እናገኛለን::

ሀ.የፍትሐ-ብሄር ሕግ

የኢትዮጵያ የፍትሃ-ብሄር ሕግ በ1952ዓ.ም ከወጣ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ፍትሃብሄራዊ ጉዳዮችን በስፋት እየገዛ ይገኛል፡፡  ለምሳሌ ሥለ ውል በጠቅላላው በሚናገረው ክፍል በተለይ የፍ/ሕ/ቁ 1758 ላይ እንዲህ የሚል ድንጋጌ እናገኛለን፡-

“አንድ እቃ የማስረከብ ግዴታ ያለበት ባለዕዳ በውላቸው መሠረት ለተዋዋለው ሰው ከአስረከበበት ቀን ድረስ በዚህ እቃ ላይ የሚደርሰውን የመበላሸትን ወይም የመጥፍት ጉዳት የሚችለው እሱ ነው፡፡ ”

ይህ የፍትሃ-ብሄር ድንጋጌም አደጋ ምንጊዜም ቢሆን ባለሃብትነትን ወይም ባለይዞታነትን ይከተላል ካልነው ቢሂል ጋር አብሮ የሚሄድ ይመስላል፡፡ በአንጻሩም ባለመብቱም ቢሆን እቃውን እንዲረከብ ማስጠንቀቂያ ከተነገረው ጀምሮ የሚደርሰውን አደጋ የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ /የፍ/ሕ/ቁ 1758(2)/ በነገራችን ላይ ከላይ የተቀመጠው ድንጋጌ አጠቃላይ ህግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሌሎች ልዩ ውሎችም ለምሳሌ እንደ ኮንስትራክሽን ውሎች ጭምር ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል ከፍ/ሕ/ቁ/1677(1)/ መገንዘብ ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ይሄው የፍትሐብሔር ሕጉ ስለ ሽያጭ በሚናገረው ክፍልም አደጋን አስመልክቶ ከአንቀጽ 2323-2328 ዘርዘር ያሉ ድንጋጌወችን ይዟል፡፡ ለማስረጃ ያህል የፍ/ህ/ቁ 2324(1) ላይ ሻጭ እቃውን በውል ወይም በህጉ መሠረት ለገዢው ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ የአደጋ አላፊነት የገዢው ይሆናል፡፡

ለዚህም ነው የአደጋው አላፊነት ለገዢው በአግባቡ የተላለፈለት እንደሆነ ዕቃው ላይ ጥፋት ቢደርስ ወይም ዋጋው ቢለዋወጥም እንኳ ገዢው ዋጋውን መክፈል ይገባዋል የሚባለው፡፡ /የፍ/ሕ/ቁ/2323/

ይህም ጉዳይ በጉዞ ላይ ባሉ ዕቃወች /goods under voyage/ ቢሆንም ልየነት እንደማያመጣ ህጉ በአንቀጽ 2326(1) ላይ በማያሻማ አኳሃን ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን ሻጩ እያወቀ ወይም ማወቅ እየተገባው የተበላሸ ወይም የተጎዳ እቃ የጫነለት እንደሆነ የተባለው አደጋ በገዢ ላይ እንደማይፈጽም ከፍ/ህ/ቁ 2326(2) ቀጥታ ንባብ መረዳት እንችላለን፡፡

ሌላው ደግሞ ለያዝነው ርዕስም በጣም ጠቃሚ የሆነ የፍትሃ-ብሄር ድንጋጌ አለ፡፡ እሱም ስለ ሥራ ውል በሚናገርበት ክፍል አንቀጽ 2629 ላይ የሚከተለውን ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡  

አንቀጽ 2629 ሊደርስ ስለሚችል አደጋ

1)     ሥራው በሚፈጸምበት ወቅት ጊዜ አስፈላጊዎች መሳሪዎች ከዐቅም በላይ በሆነ ኃይል የጠፋ እንደሆነ ኪሳራው መሳሪያወችን ባቀረበው ወገን ላይ ነው፡፡

2)    ከዚህ በቀር የአደጋን አላፊነት ስለማስተላለፍ በዚህ ሕግ ስለሽያጭ ተመለከቱትን ደንቦች (ከአንቀጽ 2323-2328) መሠረት አድርጎ መያዝ ይቻላል፡፡

ታዲያ በዚህ አጋጣሚ ከዐቅም በላይ የሆነ ኃይል ምንድን ነው? እንደሚታወቀው የፍትሐብሔር ህጋችን ሥለ ውል በጠቅላላው በሚናገርበት ክፍል “ከዐቅም በላይ የሆነ ኃይል” /በፈረንሳየኛ አቻ ቃሉ “force majeure” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን ከአንቀጽ 1792-1794 በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት ከዐቅም በላይ የሆነ ሊመለሱት የማይቻል ሃይል ደርሷል የሚባለው አንድ ባለዕዳ ባላሰበው ነገር ድንገት ደራሽ ሆኖበት ግዴታውን እንዳይፈጽም ፍጽም መሰናክል በሆነ ዐይነት የሚያግድው ነገር ባጋጠመው ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን በአእምሮ ግምት ባለዳው አስቀድሞ ሊያስብበት የሚቻል መሆኑ የታወቀ አንድ ድንገተኛ ደራሽ ነገር ወይም ለውሉ አፈጻጸም ከባድ የሆነ ወጪ ባለዕዳው ላይ የሚደርስበት ቢሆን ከአቅም በላይ የሆነ ሃይል ነው ተብሎ አይገመትም፡፡ /የፍ/ሕ/ቁ/1792 ተመለከቷል፡፡ /

የሚከተሉት ጉዳዮች ሲከሰቱ ከዐቅም በላይ የሆነ ኃይል እንደሆነ ሕጉ አስቀድሞ በአንቀጽ 1793 ላይ ወስኗል፡፡ እነዚህም ምክንያቶች እንደ ፡-

1)     ባለዕዳው አላፊ የማይሆንብት ያልታሰቡ እና በሌላ ሦስተኛ ወገን(ከተዋዋይ ውጪ ያለ ሌላ ሰው) የሚመጡ ድንገተኛ ነገሮች፤

2)    ውሉ እንዳይፈጸም የሚደረግ የመንግሰት ክልከላ፤

3)   እንደ መሬት መናወጽ(ርዕደ መሬት)፤ መብረቅ፤ ማዕበል ይህን የመሠል የተፈጥሮ መቅስፈት፤

4)   የጠላት የውጭ አገር ጦርነት ወይም የአገር ውስጥ ጦርነት፤

5)   የባለዳው መሞት ወይም ባልታሰበ ሁኔታ የሚደርሰበት አደጋ ወይም ጽኑ ህመም ናቸው፡፡

ዳሩ ግን በተዋዋዮች ዘንድ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር የሚከተሉት ድርጊቶች መከሰታቸው ከአቅም በላይ የሆነ ሃይል ነው አይሰብለውም፡፡ ለምሳሌ ሥራው በሚሰራበት የፕሮጀክት ሳይት፤ ፋብሪካ ወይም መስሪያ ቤት በሰራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ቢደረግ ወይም የሥራ መዘጋት አደጋ ወይም ለውሉ አፈጻጸም ዋነኛ የሆነው እቃ መወደድ ወይም መርከስ ወይም ደግም ባለዕድው ያለበት ግዴታ አፈጻጸም የሚያከብድበት አዲስ ሕግ መውጣት ናቸው፡፡ /የፍ/ሕ/ቁ.1794/

የሆነው ሆኖ ግን የስራ ማከናወኛ ውሎች ተፈፃሚነትና የህጉም ወሰን በጣም የተገደበ ነው ለምን ቢባል የፍ/ሕ/ቁ፣2610-2631 የሚፈፀሙት የግንባታ ወጪያቸው ከ አምስት መቶ (500) የኢትዮጵያ ብር በማይበልጡ ስራወች ላይ ነው/የፍ/ሕ/ቁ/2611(2)፡፡ (ዮሐንስ፡2008፡5)

ለ.የሥራ እና ከተማ ልማት ሚነስቴር (ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር) ወጥ ውል

በ1994 የወጣው የሥራ እና ከተማ ልማት ወጥ ውል(standard conditions of contract) ስለ አደጋ በአንቀጽ 65 እና 66 ላይ በስፋት ይናገራል፡፡  በዚህም መሠረት ልዩ አደጋወች እንደ ጦርነት፤ ብጥብጥ፤ የውጭ አገር ወረራ፤ የራዴዮ ጨረራ፤ የአውሮፕላን ሞገድ ግፊት፤ የኑክሌር ዝቃጭ አደጋ፤ እንዲሁም ሌሎች አደገኛ ተቀጣጣይ፤ ከኮንትራክተሩ ሰራተኞች ውጪ የሚነሱ ግርግሮችና አምባ ጓሮች እና የሰርጎ ገብ ጥቃት ብሎም እርስ በእርስ ጦርነት ሲከሰት ኮንትራክተሩ የአደጋ ኃላፊነት እንደማይወስድ ሕጉ አጥብቆ ይናገራል፡፡ ይህ በመሆኑም በሳይቱ ላይ የኮንትራክተሩ የሥራ ማቴሪያሎች ጉዳት በማሰተናገዳቸው ከጥቅም ውጪ ቢሆኑ ከአሰሪው ካሳ ሊጠየቅ እንደሚቻል በአንቀጽ 65(3) ላይ ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል ከሁለቱም ወገን ማለትም ከአሰሪው እና ኮንትራክተሩ ቁጥጥር ውጭ በሆነ ጦርነት ወይም ሌላ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ቢመጣ እና ሁለቱንም የየራሳቸውን ግዴታ ከመወጣት ቢያግዳቸው ከጣይ ሥራቸውን ከመፈፀም ነጻ ያደርጋቸዋል፡፡ ሆኖም እስከ ደረሰው አደጋ ጊዜ የተከናወነ ሥራ ካለ አሰሪው ለኮንትራክተሩ ኪሳራ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ /አንቀጽ 66/

የሥራ እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውል ኮንትራክተሩ ሥራው ተጀምሮ እስከሚያስረክብበት ድረስ ሙሉ ኃላፊነት አለበት ብሎ በግልጽ አልደነገገም ወይም የርክክብ ሠረተፍኬት ከተሠጠው ኃላፊነቱ የደንበኛው ወይም አሠሪው ይሆናል አይልም፡፡ ነገር ግን ይህ ወጥ የሆነ አጠቃላይ ውል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሰሪው እና ኮንትራክተሩ ልዩ ልዩ ውሎች መዋዋል ይችላሉ፡፡

ሐ.የመንግስት ግዢ ኤጄንሲ አጠቃላይ ውል(standard conditions of contract 2006)

በ1998 ዓ.ም በወጣው በኢፌዴሪ የመንግስት ግዢ ኤጀንሲ አጠቃላይ ውል አንቀጽ 20 ላይ በግልጽ እንደተመለከተው አማካሪው በልዩ ውሉ ላይ የተቀመጡት አደጋወች ሲከሰቱ እና አስቀድሞ ለመጋፈጥ የመድህን ሽፍን ሊኖረው እንደሚገባ ይህ አጠቃላይ ሕግ ይናገራል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ በስተጅርባ በአመክንዮነት ሊጠቀስ የሚገባው የመንግስት እና የህዝብ ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ለምን ቢባል የመንግስት ግዢ ኤጄንሲ በአዋጁ በተሰጠው ስልጣን መሠረት መንግስት የኮንስትራክሽን ውል ሲገባ አሰሪ ሆኖ ስለሚዋዋል ነው፡፡

ማጠቃለያ

አደጋ ማለት ያለተገመተ ጉዳት ወይም ክስተት ብሎም ህጸጽ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከላይም ሥለ ውል በጠቅላላው ለማየት እንደሞከርነው አደጋን ማን ይሸከም የሚለውን ተዋዋይ ወገኞች የሕጉን ክልከላ ሳያልፉ መዋዋል እንደሚቸሉ ለማየት ሞክረናል፡፡ በተለይም የኮንስተራክሽን ውሉ የግል በሚሆንበት ጊዜ በተዋዋሉበት ወጥ ውል(standard conditions of contract)የሚወሰን ሲሆን የመንግስት ግዢ ሲሆን ግን አደጋ ማን ይሸከም የሚለው ጉዳይ በጥንቃቄ መታየት አለበት ለምን ቢባል የመንግስት እኛ የሕዝብ ጥቅም መጠበቅ ስለሚኖርበት ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ግብር ስወራ
Letters of Credit in General

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 17 April 2024