Font size: +
11 minutes reading time (2189 words)

በኢትዮጵያ የሲቪክ ምህዳር መብቶች ጥበቃ እና የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮች

“The importance of ensuring the broadest possible civic space in every country cannot be overstated…The protection of the civic space, and the empowerment of human rights defenders, needs to become a key priority for every principled global, regional and national actor."

Ms.Michelle Bachelet, United Nations High Commissioner for Human Rights October 29, 2018, Human Rights Defenders World Summit.

 እንደ መነሻ

የሲቪክ ምህዳር መብቶች በዘመናዊው ዓለም እውቅና ማግኘት የጀመሩት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እኤአ ከ1948 ጀምሮ ነው፡፡ በተለይም የሰብዓዊ መብቶች የማዕዘን ድንጋይ የሆነው ዓለምአቀፍ ሰነድ ማለትም ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights)  መምጣትን ተከትሎ የሲቪክ ምህዳር መብቶች በሰፊው ብቅ ብቅ ያሉበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡ በተለይም በዚህ ዓለምአቀፍ ህግ መሰረት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ መብት፣ የመደራጀት መብት እንዲሁም በፓለቲካ እንቅስቅሴ የመሳተፍ መብቶችን እንደ ዋና የሲቪክ ምህዳር መብቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡

 

በኢትዮጵያም ጥበቃው ይለያይ እንጂ የሲቪክ ምህዳር መብቶች እውቅና ያገኙት በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ነበር፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ምንም እንኳን በአተገባበር ብዙ ህጽጾች ቢኖሩትም እነዚህ መብቶች በሰፊው ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት (አንቅጽ 29) ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት (አንቀጽ 30) እና የመደራጅት መብት (አንቅጽ 31) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

 

የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማም በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት ያለውን የሲቪክ ምህዳር መብቶቸ ጥበቃ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና ሕገ መንግስቱ አስተምህሮ አንጻር አጭር ዳሰሳ ማድረግ፣ በኢትዮጵያ በተግባር የሚስተዋሉ ችግሮችን መዳሰስ ብሎም ከመንግሥትና መንግስታዊ ካልሆኑ አካልት (non-State actors) የሚጠበቁ ግዴታዎችን በመለየት ምክረሃሳብ ማቅረብ  ናቸው፡፡

 

1. የሲቪክ ምህዳር መብቶች ምንነት እና አስፈላጊነት

 

የሲቪክ ምህዳር መብቶችን (civic space rights) ትርጓሜና ይዘት ከማየታችን በፊት ስለ ሲቪክ ምህዳር ምንነት ጥቂት ነጥብ ላንሳ፡፡ የሲቪክ ምህዳር ማለት ግለሰቦች ወይም የሲቪክ ማህበራት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ህይወት ላይ በንቃት በመሳተፍ፣ መረጃ በማግኘት፣ በውይይት በመካፈል፣ ተቃርኖን በመግለጽና በመደራጀት ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበት ስፍራ ነው፡፡ በጣም ክፍት እና ብዝሃነትን አቃፊ የሆነ የሲቪክ ምህዳር መኖር የመናገር ነጻነትን ከማጎልበቱ ባሻገር የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብት እንዲሰፍኑ ያግዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለዘላቂ ሰላምና ልማት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

       

ሲቪከስ (CIVICUS) የተባል የሲቪክ ማህበር የሲቪክ ምህዳርን እንደሚከተለው ትርጉም ለመስጠት ይሞክራል፡-

 

Civic space is the bedrock of any open and democratic society. When civic space is open, citizens and civil society organisations are able to organize, participate and communicate without hindrance. In doing so, they are able to claim their rights and influence the political and social structures around them. This can only happen when a state holds by its duty to protect its citizens and respects and facilitates their fundamental rights to associate, assemble peacefully and freely express views and opinions.

 

ይህም ማለት የሲቪክ ምህዳር ማለት ለማነኛውም ግልጽና ዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ የመሰረት ድንጋይ ነው፡፡ የሲቪክ ምህዳሩ ክፍት ሲሆን ፤ ዜጎች እና የሲቪክ ማህበራት ያለምንም እንቅፍት እራሳቸውን ያሳትፋሉ፣ ይግባባሉ እንዲሁም ይደራጃሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በሚንቀሳቅሱበት ቦታ ሁሉ መብታቸውን ይጠይቃሉ እንዲሁም በማህበረ ፖለቲካዊ መዋቅሮች ውስጥ ተጽኖ እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል፡፡ ታዲያ ይህ ምህዳር እውን የሚሆነው መንግሥት የዜጎችን ወይም ማህበራትን መብቶች ከጥሰት ሲጠብቅ ብሎም እንዲደራጁ፣ በሰላማዊ መንገድ እንዲሰበሰቡ እና ሃሳባችውን በነጻ እንዲገልጹ የሚያስችሉ ነገሮችን ሲያሟላ ነው፡፡

የሲቪክ ምህዳር መብቶች ማለት በዲሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ እንድንሳተፍ የሚያደርጉ እና የሚያግዙ ሰብዓዊ መብቶች ሲሆኑ በተለይም ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት፣ የመሰብሰብ መብት፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እና የመደራጀት መብት ናቸው፡፡

ሰፊ የሆነ የሲቪክ ምህዳር መኖር የሚከተሉት ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ምቹ የሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይፈጥራል፡፡ በዚህም የተነሳ ዜጎች እና የሲቪክ ማህበራት በፖለቲካ ዙሪያ የጎላ እና የነቃ አስታዋጻኦ እንዲያደርጉ ያስችላል፡፡ ይህም ሲሆን የመንግሥት አካላት እና ባለስልጣናት ለሲቪክ ማህበራት ቀናዒ አመለካከት ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የተ.መ.ድ የጸረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዊኒ፡ባኒያማ ባንድ ወቅት ያሉትን ንግግር ማንሳት ጠቃሚ ነው፡፡ “Civil society space provides the oxygen for citizens to participate and meaningfully hold their governments and the private sector to account - and ensure that decisions are made in the interest of the majority and not the few. Without it, citizens have limited space to dissent and challenge the elites.” ከዚህ ንግግር የምንረዳው የሲቪክ ምህዳር መኖር የሲቪክ ማህበራት እንደልባቸው እንዲንቀሳቅሱ ያግዛል ብሎም ለዜጎች ዲሞክራሲያዊ ሂደት የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ትልቅ ኦክስጅን ጭምር እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡

ሁለተኛ አጋዥ የሆነ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ያስችላል፡፡ በተለይም ለሲቪክ ማህበራት ሥራ ደጋፊ የሆኑ ከዓለምአቀፍ አሰራሮች ጋር የተቃኙ ህጎችና ድንቦች እንዲኖሩ ያስችላል፡፡ ሆኖም ግን የሲቪክ ምህዳሩ ሲጠብ አፋኝ ህግጋት በሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ ለምሳሌ፦ኢትዮጵያ ከ1997ዓ.ም ወዲህ አፍኛ የሚባል የበጎ አድራጎት እና ማህበራት አዋጅ ቁ.621/2001 በሥራ ላይ አውላ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ በርካታ የሲቪክ ማህበራት የመዘጋት ዕድል አጋጥሟቸዋል፡፡

ሦስተኛ ሰፊ የሆነ የሲቪክ ምህዳር ሲኖር በአንድ አገር ውስጥ ያለው የመረጃ ፍሰት ጥሩ ይሆናል፡፡ በተለይም ዜጎች በአገራቸው ስለሚካሄዱ ጉዳዮች በጣም የጠራ መረጃ፣ ሪፖርት እንዲሁም ስለ ተለያዪ ጉዳዮች ንቁ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰፊ የሲቪክ ምህዳር መኖር ድምጽ አላባ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አቅም ይፈጥራል ብሎም ያለንን ሃብት በጋራ ለመጠቀም እንዲሁም በትብብር ለመስራት ያግዛል፡፡

የሲቪክ ምህዳር መብቶች በመንግሥት ላይ ሦስት ግዴታዎችን ይጥላሉ፡፡ በዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብት ሕግ አስተምህሮ አገራት ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ ሦስት ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡ (Asbjorn Eide:1987:67) እነዚህም፦ የማክበር (respect) ፣ የማስጠበቅ (protect) እና የማሟላት (fulfill) ግዴታ ናቸው፡፡ የማክበር ግዴታ ሲባል የመንግሥት አካላት (ሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው)  የሲቪክ ምህዳር መብቶችን ከመጣስ መቆጠብ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ፦መንግሥት ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ለማፈን ፈቃድ አልተሰጠም ወይም እውቅና አንሰጥም ማለት የለበትም፡፡

የመጠበቅ ግዴታ ሲባል መንግሥት የመብቱን ባለቤቶች ከሦስተኛ ወገኖች ወይም መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጥቃት/ጉዳት መጠበቅ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝባዊ ስብሰባዎች ወይም ጋዜጣዊ መግልጫዎች ሊሰጡ ሲሉ በርካታ ወጣቶች በተለያየ ስያሜ በመቧደን ሲያውኩ ይስተዋላል፡፡ ታዲያ መንግሥት የተሰብሳቢዎችን መብት ለመጠበቅ ከእንዲህ ዓይነት ሁከት መጠበቅ አለበት፡፡

የማሟላት ግዴታ ደግሞ መንግሥት አወንታዊ እርምጃዎች (positive measures) እንዲወስድ የሚያድርግ ሲሆን በተለይም የሲቪክ ምህዳር መብቶች እንዲሟሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ፡ በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ጋር በተያያዘም መንግሥት ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት በሎም ጥራት ያለው አቅርቦት እንዲኖር መንገዶችን ማመቻችት እንዲሁም የቴሌኮሚኒኬሽን ግብዓቶች እንዲሟሉ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል ፡፡

 

2. ስጋት ውስጥ የወደቀው የኢትዮጵያ የሲቪክ ምህዳር መብቶች ይዞታ

 

በበርካታ አገራት ውስጥ የሲቪክ ምሃዳር በተለያዩ ጫና ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፕ/ር አንቱዋን ቡያስ የሚከተለውን ብለዋል፡_“Civic space – the layer between state, business, and family in which citizens organise, debate and act – seems to be structurally and purposefully squeezed in a very large number of countries. “ በተለየም የጽረ ሲቪክ ማህበራት ህጎች፣ ዘፈቀዳዊ ምርመራዎች፣ ማዋከቦች እንዲሁም በሃሰት ውንጀላ ማሰር እና መቅጣት ናቸው፡፡ (አንቶዋን ቡያስ፡2018:966)

አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥም የሲቪክ ምህዳር መብቶች በርካታ ስጋቶች እና ተጽኖዎች ተጋርጠውበታል፡፡ ተጽኖው ከመንግሥት አሊያም መንግስታዊ ካሉሆኑ አካላት (Non-State actors) ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ እየመጣ ብሎም የህግ ማሻሻያ መርሃግብር (law reform programmes) ቢኖርም፤ የሲቪክ ምህዳርን የሚፈታተኑ ማነቆ የሆኑ አፍኝ ህጎች፣  መመሪያዎች እና አሰራሮች አሉ፡፡ እንዲሁም መንግሥት ከፍተኛ የስለላ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችን እንዲሁም የማህብረሰብ አንቂዎችን የማህበራዊ ትስስር ገጾች የመሰለል ተግባራት (illegal surveillance)  ይስተዋላል፡፡

ከዚህ በታች ሦስቱን አንኳር የሲቪክ ምህዳር መብቶች ማለትም ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እና የመደራጅት መብትን በአጭር በአጭሩ አሁናዊ ይዞታ (current state of play) አቀርባለሁ፡፡

 

2.1. ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት

 

ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት (freedom of expression) ሲባል ግለሰቦች ሃሳባችውን መግለጽ፣ መረጃ ማግኘት፣ መጠየቅ እንዲሁም ለሌሎች የማካፈል መብትን ጨምሮ በፈለጉት መንገድ ማለትም በጽሑፍ፣ በንግግር፣ በምልክት፤ በኢንተርኔት ወይም በሌላ መንገድ በመጠቀም መልዕክት የማስተላልፍ መብት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 29 (2) የህግ መሰረት ያለው ሲሆን የመብቱ ባለቤትም ማነኛውንም መንገድ በመጠቀም ሃሳብን መግለጽ፣ መረጃ የመጠየቅ፣ የመቀበል እና የማጋራት መብቶች አሉት፡፡ ይህ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ ከዓለምአቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR)  አንቀጽ 19 ጋር ተመሳሳይ በሚባል መልኩ መብቱን ደንግጓል፡፡

በኢትዮጵያ ከ2010ዓ.ም ወዲህ መንግሥት በጀመረው የዲሞክራሲያዊ ለውጥ የመናገር ነጻነትን ሊደግፋ የሚችሉ የህግ ማሻሻያዎችን እየወሰደ ነው፡፡ ሆኖም ግን ጠንካራ ተቋማት ባልመኖራቸው ምክንያት አሁንም መብቱን በተሻለ መጠበቅ አልተቻለም፡፡

        በተለይም መንግሥት በጸጥታ ምክንያት ወይም ፈተና ለመቆጣጠር በሚል የሚውስደው የበየነ መረብ መዝጋት እርምጃ (Internet Shutdowns) የግለሰቦችን የመናገር መብት እየተፈታተነ ይገኛል፡፡ (ዮሐንስ፡እንየው፡2019፡208) የመንግሥትም በፖሊሲ በሚመስል መልኩ “ኢንተርኔት ውሃ አይደለም፤ ኢንተርኔት አየር አይደለም፡፡ ሲያሻን እስከመጨረሻውም ልንዘጋው እንችላለን፡፡” የሚለው የተሳሳት ትርክት መቀየር መቻል አለበት፡፡ በ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ የዲጂታል መብቶች ቡድን (Network for Digital Rights in Ethiopia)  ባካሂደው ጥናት የኢንተርኔት መዘጋት 65% የስራ ምርታማነትን ይገታል፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያት የዜጎችን የመናገርና መረጃ የማግኘት መብትን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችንም (socio-economic rights) ይጎዳል፡፡

        የበየነ መረብ ሳንሱር (internet censorship) ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ጸሀፊው የድህረገጾችን በትክክል መስራት የሚለካው ፕሮጅክት (The Open Observatory Network Interference (OONI) ሳይንሳዊ የሙከራ ዘዴ በመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ የታፈኑ ድረ ገጾችን ፈትሿል፡፡ በዚህም መሰረት እስክ ጥቅምት 24፣ 2012ዓ.ም. ደረስ ወደ 22 የሚደርሱ ድረገጾች ተሞክረው 2 ድረገጾች የተዘጉ ሲሆን ቀሪዎች ይሰራሉ፡፡ ለምሳሌ፦በወርሃ ነሀሴ 2011ዓ.ም. አካባቢ ስለ ሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሀተታ አቅርቧል በሚል African Arguments የተባል ደረገጽ መዘጋቱ ይታወሳል፡፡

        ሌላው ከሰኔ 15ቱ ጥቃት ጋር በተያያዘ በሚል የታሰሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 29 የተረጋገጠውን ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብትን ይጥሳል፡፡ እንዲህ አይነቱ ተግባር ምንም እንኳን አሁን አንዳንዶቹ የተፈቱ ቢሆንም በጋዜጠኝነት ሥራ ላይ ላሉ ግለሰቦች እንደ ማሸማቀቂያ (chilling effect)  የሚቆጠር ተግባር ነው፡፡

 

2.2. የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት

 

የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 30 ላይ ተመልክቷል፡፡ በተለይም ግለሰቦች ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዙ በሰላም የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንዳላቸው ከመብቱ ይዘት መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ ከዓለምአቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR)  አንቀጽ 21 እና የአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች መብት ቻርተር (African Charter on Human and Peoples’ Right-ACHPR አንቀጽ 11 ጋር ተመሳሳይ በሚባል መልኩ መብቱን ደንግጓል፡፡

        በአሁኑ ጊዜ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን የሚገዛው ህግ በሽግግር መንግሥት ጊዜ የወጣው አዋጅ ቁ. 3/1983 ዓ.ም ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት ማነኛውም ሰላማዊ ሰልፍ የጠራ አካል ከ 48 ሰዓት በፊት በጽሑፍ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ሆኖም ግን በተግባር ይህ የማሳወቅ ግዴታ (notification) ወደ ማስፈቅድ (permission ) ተቀይሮ መብቱ በሰፊው ሲጣስ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ፦በቅርቡ የአዲስ አበባ አስተዳድር በባልደራስ ም/ቤት የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ባልታወቀ ምክንያት የሰረዘበትን ማንሳት ይቻላል፡፡

በዚህ ረገድ የሌሎችን አገራት ልምድ ብናይ፤ ለምሳሌ፡ እንግሊዝ ውስጥ አይደለም አንድ ቡድን ሰልፍ ጠርቶ ይቅርና ሁለት ተጻራሪ ቡድኖች በአንድ ጊዜ ጠርተው በርካታ ጊዜ ሰልፍ በሰላም ተካሂዷል፡፡ ከመንግሥት ሚጠበቀው በቂ ጥበቃ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን መንግሥት ይህንን መብት በተግባር ለመፈጽም ሲያቅማማ ይስተዋላል፡፡

 

2.3. የመደራጀት መብት

 

የመደራጀት መብት (freedom of association) በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 ላይ ተመልክቷል፡፡ በዚህም መሰረት ማነኛውም ሰው የፈለገውን ማህበር ማለትም እንደ የሙያ ማህበር፣ የፓለቲካ ድርጅት፣ የሲቪክ ማህበር ወዘተ የመግባትና የመደራጀት መብት አለው፡፡ ይህ መብትም በአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች መብት ቻርተር አንቀጽ 10 እና በዓለምአቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR)  አንቀጽ 22 በስፋት ተመልክቷል፡፡

ሆኖም ግን ገዳቢ እና አፋኝ የምዝገባ ቅድመ ሁኔታዎች ሲኖሩ የመደራጀት መብት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይወድቃል፡፡ በዚህ ረገድ በቅርቡ የጸደቀውን የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ማንሳት ጠቃሚ ነው፡፡ በአዲሱ ህግ መሰረት አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ቢያንስ 10ሺ አባላት እንዲሁም ክልላዊ ፓርቲ 4 ሺ አባላት ሊኖሩት እንደሚገባ ይናገራል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን በበዙበት ሁኔታ ቁጥራቸውን በህግ መቀነስ አስፈላጊ ቢሆንም፤ የአናሳ መብቶች ላይ የሚሰሩ ፓርቲዎችን የመደራጀት መብት ጋር ተያይዞ ጥያቄ ያስነሳል፡፡

 

3.  በኢትዮጵያ የሲቪክ ምህዳር መብቶች ጥበቃ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች

 

በኢትዮጵያ የሲቪክ ምህዳር መብቶች በርካታ የሆኑ ጫናዎች አሉብት፡፡ የጫናው ምንጭ ይለያይ እንጂ መንግሥትም ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ አካልት (Non-State actors) እነዚህን መብቶች በጥሩ ሁኔታ እንዲጠበቁ ግዴታ አለባቸው፡፡ በተግባር የሚስተዋሉ ችግሮች እንደሚክተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

አንደኛ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ተጽኖ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ2009ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የተለያየ መጠሪያ በመያዝ መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተመሰረቱ የወጣቶች እንቅስቃሴዎች (irregular youth movements) በጉልህ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ቡድኖች ምንም እንኳን በአገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋጾ ቢኖራቸውም፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የደቦ ፍርድ (mob justice) እንዲስፋፋ ብሎም ሕገ ወጥነት (anarchy) እንዲበራከት አድርገዋል፡፡ የእነዚህ እንቅስቃሴዎች ልዩ ሚያደርገው ተቋማዊ አደረጃጀታቸው ህቡዕ (clandestine organizations) መሆኑ አሊያም ከሚመለከተው አካል አለመምዝገባቸው ነው፡፡ የሲቪክ ምህዳር መብቶችንም በተመለክተ በተለይም የመሰብሰብ መብትን በስፋት ጫና ሲያድርጉ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ፦ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዪ ቦታዎች በሚጠሩ ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ በወጣት ስም የተደራጁ ቡድኖች ፤ ስብሰባ ሲያውኩ አሊያም ከእኛ ፈቃድ ውጭ መሰብሰብ አትችሉም የሚሉ እንቅስቅሴዎች በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ እየተስተዋለ ነው፡፡

ሁለተኛ የመንግሥት ለሲቪክ ምህዳሩ መስፋት ቁርጠኝነት ማጣት ነው፡፡ በእርግጥ መንግሥት በተለያዩ መግለጫዎች የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፍት ብሎም የሲቪክ ምህዳሩን ለመጠበቅ ሲባል ብዙ ጉዳዮችን በዝምታ ያለፈበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ሆንም ግን በተግባር እንደሚታየው የመንግሥት ቁርጠኝነት ባለመኖሩ ምክንያት ከህግ ውጪ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ማፈን ብሎም ያለአግባብ መከልከል የእውነትኛ ቁርጠኝነት ማጣት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ሦስተኛ በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ የመጣው የህግ የበላይነት አለመከበር ነው፡፡ የህግ የበላይነት ከለለ ፤ ስለ ሲቪክ ምህዳር መብቶች ማሰብ ከንቱ ነው፡፡ የህግ የበላይነት ባለመኖሩ ምክንያት ግለሰቦች የመብት ጥሰት ሲያጋጥማቸው እራሱ በደላቸውን አቤት ወደ ማይሉበት ደረጃ ላይ እየሄድን ነው፡፡ የህግ ልዕልና (supremacy of law) ከሌል ዜጎች ስለ መብቶቻቸው መከበር ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡

በተጨማሪም የሲቪክ ምህዳር መብቶች ሲጣሱ በቂ የሆነ የፍትህ አለመኖር በተለይም ዜጎች መብቶቻቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበው እርማት (judicial review) አለማግኘት ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ መብቶችን የመተርጎም ስልጣን ባለመኖራችው ምክንያት፤ መብት የተጣሰባቸው ግለሰቦች ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት ጉዳያቸውን የማቅረብ ዝንባሌ በተግባር እምብዛም አይታይም፡፡

 

4.  የማጠቃለያ ምክረ ሃሳቦች

 

ከላይ ለማብራራት እንደተሞከረው የሲቪክ ምህዳር መብቶች ማለት በዲሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ እንድንሳተፍ የሚያደርጉ እና የሚያግዙ የሰብዓዊ መብቶች ሲሆኑ እንደ ሃሳብን በነጻ የመግልጽ መብት፣ የመሰብሰብ መብትና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ እና የመደራጀት መብት እንደሆኑ አይተናል፡፡ እነዚህን መብቶች በሚመለከት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፋን የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን እንዲሁም የአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች መብት ቻርተርን ፈርማ በማጽደቅ ተቀብላለች፡፡ እንዲሁም በሕገ መንግሥት ጭምር ከ አንቀጽ 29_31 ድረስ በስፋት አስፍራለች፡፡

ጸሀፊው ከላይ የተለዩትን ችግሮች ለመፈታት የሚከትሉትን  ምክረ ሃሳቦች ያቀርባል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት በሕገ መንግስቱ እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ስለ ሲቪክ ምህዳር መብቶች ያሉበትን ግዴታዎች ማለትም የማክበር፣ የማሟላት እና የመጠበቅ አላፊነቶች ጊዜ ሳይሰጥ መወጣት አለበት፡፡ እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት (እንደ ሆቴሎች፣ የንግድ ተቋማት እና የተደራጁ መደበኛ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች) የሲቪክ ምህዳር መብቶችን በሚመለከት የጎንዮሽ የሰብዓዊ መብት ግዴታ (horizontal obligation of human rights)  ስላለባቸው ፤ ይህንንም በሚመለከት መንግሥት የመጠበቅ (duty to protect) እና የመከታተል አላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡

ሁለተኛም የሲቪክ ምህዳር መብቶች ሲጣሱ ዜጎች ፍ/ቤት ቀርበው አቤት ማለት አለባቸው፡፡ ፍ/ቤቶችም ህግ የመተርጎም ( judicial review) ስላጣናቸውን መጠቀም አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ ምንም እንኳን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚያስፈልገው ቢሆንም ፤ ዜጎች የሲቪክ ምህዳር መብቶቻቸውን በሚመለከት በሚቅርቡ አቤቱታዎች ትርጉም በፍ/ቤቶች ቢሰጥ መልካም ነው፡፡

ሦስተኛም የህግ ባለሙያዎች እና የመብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ስልታዊና የህዝብ ጥቅምን የሚመለከቱ ክሶችን (public interest and strategic litigation)  ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በመጨረሻም መንግሥት የሲቪክ ምህዳር መብቶችን ይዞታ በተግባር ለማሻሻል እንዲረዳ የተዛቡ ትርክቶችን ማስተካከል ብሎም እቀባ የተደረገበትን የሲቪክ ምህዳር አስተምህሮ ለውይይት እና ክርክር ክፍት ማድረግ እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲከበር ቁርጠኝነት ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሰበር ዓላማ ወጥነትን ማስፈን ወይስ ሕገ-ወጥነትን ማስፋፋት?
The Role of ICT in Judicial Reform in Ethiopia

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 20 September 2024