አዋጅ ቁጥር-1160/2011 የጉምሩክ አዋጅ 859/2006 ማሻሻያ አዋጅ ሲሆን በዚህ አዋጅ የጉምሩክ አዋጅ 859/2006 ውስጥ ባሉት አንዳንድ ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ ከተደረጉ ማሻሻያዎች በዋናነት የሚጠቀሰው በአከራካሪ የወንጀል ድንጋጌዎች ላይ የተደረገው ማሻሻያ ሲሆን በዚህ ፅሁፍ በማሻሻያ አዋጁ የተሸሩ፣የተሸሻሉና እንደ አዲስ የተካተቱ የወንጀል ድንጋጌዎች አጠር ባለመልኩ ተዳሰዋል፡፡

1. የኮንትሮባንድ ወንጀል፡-

2. በድብቅ ወይም ከህጋዊ መተላለፊያ መስመር ውጪ[1]/smuggling or out of legal route/

በጉምሩክ ማሻሻያ አዋጅ 1160/2011 መሰረት መሻሻያ ከተደረገባቸው አንዱ የጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንቀፅ 168/1 ነው፡፡

የአዋጅ 859/2006 አንቀፅ 168/1- ድንጋጌ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

“ማንኛውም ሰው እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የጉምሩክ ህጎችን በመተላለፍ የተከለከሉ፣ገደብ የተደረገባቸው ወይም የንግድ መጠን ያላቸውና የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመባቸው ዕቃዎችን በድብቅ ወይም ከህጋዊ መተላለፊያ መስመሩ ውጪ ወደ ሀገር ካስገባ፣ከሀገር ካስወጣ፣ከሀገር ለማስገባት፣ወይም ለማስወጣት ከሞከረ፣ወይም በህጋዊ መንገድ የወጡ እቃዎችን በህገ-ወጥ መንገድ መልሶ ካስገባ ከአምስት አመት በማያንስ ከአስር አመት በማይበልጥና ከ50 ሺ-200 ሺ በሆነ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል”

ከላይ በተመለከተው የህግ ድንጋጌ ውስጥ ያለው “በድብቅ ወይም ከህጋዊ መተላለፊያ መስመሩ ውጪ” የሚለው ሀረግ በፍርድ ቤት፣በጠበቆችና በአቃቢያነ ህግ መኃከል የክርክር ነጥብ ነበር፡፡ አንድ ሰው በኢትዮጵያ አየርመንገድና በመሳሰሉት ህጋዊ የመተላለፊያ መስመሮች ወደ ጉምሩክ ክልል ዕቃ ይዞ ቢገባ፣የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመበት ህጋዊ ዕቃ በኪሱ ይዞ በነዚህ ህጋዊ የጉምሩክ መተላለፊያ መስመር ላይ ቢያዝ ይዞ የተገኘው ዕቃ ደበቀ ሊባል ይችላል?---የሚለው ጉዳይ የክርክር ነጥብ የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመባቸውን ዕቃዎች ሳይደብቅ ወደ ጉምሩክ ክልል ገብተው የሚያዙ መንገደኞችን በሚመለከት ድንጋጌው የክርክር መነሻ ነበር፡፡

በጠቅላይ ዕቃቤ ህግ በኩል ሲቀርብ የነበረው ክርከር መደበቅ ማለት ከታክስ ስርዓት መደበቅ(smuggling) እንጂ አካላዊ መደበቅ(concealing) ባለመሆኑ መታየት ያለበት እቃው በተለምዶ መደበቅ በሚባል ሁኔታ(act of concealing) ወደ ጉምሩክ ክልል መግባት አለመግባቱ ሳይሆን ቀረጥና ታክስ የተከፈለበት መሆን አለመሆኑ ነው በሚል ነበር፡፡ በዚህ ክርክር መሰረት ወደ ጉምሩክ ክልል የገባ ማንኛውም ዕቃ ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለበት ከሆነ እንደተደበቀ እቃ ይቆጠራል፡፡

“ማንኛውም ሰው ይህን አዋጅ ወይም ባለስልጣኑ የሚያስፈፅማቸውን ሌሎች ህጎች ወይም  በእነዚሁ  ህጐች  መሰረት  የወጡ  ደንቦችን  ወይም  መመሪያዎችን በመተላለፍ የተከለከለ፣ ገደብ የተደረገበት ወይም የጉምሩክ ሥነ  ስርዓት ያልተፈፀመበት ዕቃ ወደ ጉምሩክ ክልል ያስገባ ወይም  ከጉምሩክ  ክልል  ያስወጣ ወይም ለማስወጣት ወይም ለማስገባት የሞከረ ወይም በህጋዊ መንገድ የወጣውን ዕቃ በህገ ወጥ መንገድ መልሶ ያስገባ እንደሆነ የዕቃው መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከብር 50 ሺ- 200ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮና  ከአምስት  እስከ  አሥር  ዓመት  በሚደርስ  ጽኑ እስራት ይቀጣል”

2. የጉምሩክ ማጭበርበር ወንጀል

ሌላኛው ማሻሻያ የተደረገበት የወንጀል ድንጋጌ የጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንቀፅ 169 ላይ የተመለከተው የጉምሩክ ማጭበርበር ወንጀል ተግባር ሲሆን በአዋጅ 1160/2011 አንቀጽ 45  እና 46 መሠረት የተደረጉ ማሻሻያዎችና እንደ አዲስ የተካተቱ ንዑስ አንቀፆች እንደሚከለው ቀርቧል፡፡

 

 

ማንኛውም ሰው ክልከላ የተደረገበት ዕቃ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የተከለከለን ዕቃ በህጋዊ ዕቃ ከላላነት ወደ ጉምሩክ ክልል ይዞ መግባት/ማስገባትና ማስወጣት፣ለማስገባትና ማስወጣት የሞከር እንደሆነ የወንጀል ተግባር የፈፀመ ስለ መሆኑ በአዋጅ 859/2006 አንቀፅ 169/1 ላይ ተደንግጎ የነበረ ሲሆን ድርጊቱ መፈፀሙ በፍርድ ቤት ከተረጋገጠ ከ5-10 በሆነ ፅኑ እስራትና ከ50 ሺ-200 ሺ ብር በሆነ የገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል፡፡ ሆኖም በረቂቅ አዋጅ ላይ ቅጣትን በሚመለከት ማሻሻያ እንዲደረግበት ሀሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ማሻሻያ አዋጁ ሲፀድቅ በአንቀፅ 169/1 ላይ ምንም አይነት ማሻሻያ አልተደረገም፡፡

 

 

ሌላኛው የጉምሩክ ማጭበርበር ተግባር ክልከላ ከተደረገባቸው ዕቃዎች ውጭ ያሉትን ተደብቀው የሚገኙ ሌሎች ዕቃዎችን የሚመለከት ሲሆን ይህም በአዋጅ 859/2006 አንቀፅ 169/2 በግልፅ ተደንግጎ ነበር፡፡

 

በአዋጅ 859/2006 አንቀፅ 169/2 ላይ እንደተመለከተው፡-

 

 “ተደብቆ የተገኘው ዕቃ ዋጋ በዴክለራሲዮን ላይ ከተገለፀው ጠቅላላ ዋጋ 50 በመቶ በላይ ሆኖ ከተገኘ ዕቃዎችን በመደበቅ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ከሀገር ለማስወጣት የሞከረ ማንኛውም ሰው ከ5-10 አመት ፅኑ እስራትና ከ50ሺ-100 ሺ በሆነ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል”

ከአዋጅ 859/2006 አንቀፅ 169/1 እና 169/2 መረዳት የሚቻለው ማንኛውም ሰው በህጋዊ ዕቃ ከላላነት ክልከላ የተደረገበትን፣ገደብ የተደረገበትን[3]ና የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመበትን ዕቃ ይዞ ወደ ጉምሩክ ክልል የገባ/ያስወጣ፣ለማስገባትና ለማስወጣት የሞከረ እንደሆነና እቃው ገደብ የተደረገበትና መግለጫ ያልተሰጠበት/የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመበት በሚሆንበት ግዜ የዕቃው ዋጋ በዴክለራሲዮን ከተገለጣ ጠቅላላ ዋጋ ከ50% በላይ ሲሆን በጉምሩክ ማጭበርበር ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ ነው፡፡

አንቀፅ 169/2 ላይ ያከራክር የነበረው የንፅፅር መሰረት(base) ቀረጥና ታክስ መሆኑ ቀርቶ ዋጋ መሆኑ ሲሆን ተደብቆ የተገኘው ዕቃ በፐርሰንት ለማስቀመጥ በሚደረግ ስሌትም ተደብቆ የተገኘው ዕቃ ከ50 ፐርሰንት በላይ መሆኑ የሚታወቀው ከተያዘው ጠቅላላ ዕቃ ዋጋ ጋር ነው ወይስ የተደበቀው ከስሌት ወጥቶ በዴክለረሲዮን ላይ ከነበረው ዋጋ ጋር ነው የሚለው ነጥብ የክርክር መነሻ ነበር፡፡

ሆኖም አዋጅ 859/2006ን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ 1160/2011 አንቀፅ 45 ላይ እነዚህ የክርክር ነጥቦች መፍትሔ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በአንቀፅ 45 ላይ በተተካው አዲስ አንቀፅ 169/2 እንደተመለከተው፡-

 “ማንኛውም ሰው በዲክላራሲዮን ያልተመዘገበ ወይም ትክክለኛ መግለጫ ያልተሰጠበት ዕቃ በህጋዊ ዕቃ ከለላነት ወደ አገር ውስጥ ያስገባ ወይም ወደ ውጪ የላከ ወይም ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ወይም ከአገር ለማስወጣት የሞከረ እንደሆነ የተገኘው የቀረጥና ታክስ ልዩነት ህጋዊ በሆነው ዕቃ ላይ ከተከፈለው ወይም ሊከፈል ከሚገባው ጋር ሲነፃፀር ከሃምሣ በመቶ በላይ ከሆነ እና በልዩነት የተገኘው ቀረጥና ታክስ መጠን ከብር አንድ ሚሊዬን በላይ ከሆነ ከሦስት እስከ አምስት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል”

 

የአዋጅ 859/2006 አንቀፅ 169 ሁለት ንዑስ አንቀፆችን ብቻ ይዞ የነበረ ሲሆን በአዋጅ 1160/2011 አንቀፅ 45 እና 46 መሰረት የተሸሻለው አንቀፅ 169 ግን 5 ንዑስ አንቀፆችን ይዟል፡፡

አዲስ በአዋጅ 1160/2011 መሰረት ከተካተቱ የጉምሩክ ማጭበርበር ወንጀሎች ውስጥ ሁለቱ የቀረጥ ነፃ መብትን የሚመለከቱ ሲሆን ሌላኛው ሀሰተኛ ሰንደን የሚመለከት ነው፡፡

169/3፡-

‘‘ማንኛውም ሰው የቀረጥና ታክስ ነፃ መብት ሳይኖረው የቀረጥና ታክስ ነፃ መብት ያለው በማስመሰል በማንኛውም የተጭበረበረ ሁኔታ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት ዕቃን ወደ ጉምሩክ ክልል ያስገባ/ያስወጣ፣ለማስገባትና ለማስወጣት የሞከረ እንደሆነ 7-10 አመት እና ከ 100 ሺ-200 ሺ በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ይቀጣል’’

  

 

የጉምሩክ ማጭበርበር ወንጀሎች ለጉምሩክ ስነ-ስርዓት በሚቀርቡ ሀሰተኛ ሰነዶች፣መግለጫዎች፣መረጃዎችና ሌሎች የማጭበርበር ዘዴዎች ሊፈፀም ይችላል፡፡

ከሀሰተኛ ሰነድ ጋር ተያይዞ የሚፈፀም የጉምሩክ ማጭበርበር ወንጀሎች በማሻሻያ አዋጅ 1160/2011 አንቀፅ 169/4 ላይ የተካተተ ሲሆን የድንጋጌው ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

አንቀፅ 169/4፡- ማንኛውም ሰው፡-

ማንኛውም ሰው ሊከፈል የሚገባውን ቀረጥና ታከስ ላለመክፈል ወይም ለማሳነስ በማሰብ፣

በአጠቃላይ ከተደረገው ማሻሻያ መረዳት እንደሚቻለው የጉምሩክ መሻሻያ አዋጅ 1160/2011 ከዚህ በፊት በዐቃቤ ህግና በጉምሩክ ኮሚሽን/ገቢዎች ሚኒስተር፣በፍርድ ቤት፣ዐቃቤ ህግና ጠበቆች መኃከል የክርክር መነሻ የነበሩትን ነጥቦችን ግልጽነት በተሞላበት ሁኔታ ያካተተና ወንጀልነቱ ቀሪ ተደርጎ ከነበረው ከቀረጥ ነፃ መብት ጋር በተያያዘ ይነሱ ለነበሩት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ በመሆኑ ስራ ላይ ያለውን አዋጅ 859/2006ን ሙሉ በማድረግ የጉምሩክ ህግ ፍትሓዊነትና ተገዢነትን ከማረጋገጥ አንፃር በጎ ተፅኖ ይኖረዋል፡፡

............................................               

[1]የጉምሩክ መተላለፊያ መስመር በጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንቀፅ 2/17 ላይ ትርጉም የተሰጠው ሲሆን በጉምሩክ ቁጥጥር ስር ያሉ ገቢና ወጪ ዕቃዎች እንዲጓጓዙበት በባለስልጣኑ የተወሰነ ማናቸውም መንገድ ነው፡፡

[2] የተከለከለ ዕቃ ለሚለው ሀገረግ በአዋጅ 859/2006 አንቀፅ 2/30 ትርጉም የተሰጠው ሲሆን በኢትዮጵያ ህግ ወይም ኢትጵያ ባፀደቀቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች ወደ ሀገር እንዳይገቡ፣ከሀገር እንዳይወጡ ወይም እንዳይተላለፍ የተከለከለ ማንኛውም ዕቃ ማለት ነው፡፡

[3] ገደብ የተደረገበት ዕቃ በጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንቀፅ 2/31 ላይ ትርጉም የተሰጠው ሲሆን በህግ በተደነገገ ስነ-ስርዓት መሰረት ስልጣን ባለው አካል በተሰጠ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር ወደ ሀገር እንዳይገባ. ወይም እንዳይወጣ ወይም እንዳይተላለፍ ገደብ የተደረገበት ዕቃ ነው፡፡