ስለቀዳሚ ምርመራ (Preliminary Inquiry) ፍርድ ቤት ተልዕኮ፣ ሥልጣን እና ተግባር

በዘመናዊ አሠራር የወንጀል ጉዳይን እንዲከታተል የተቋቋመ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ለፍርድ ሊቀርቡ የሚገባቸውን ጉዳዩች አይነትና ብዛት ለመለየት የሚያስችለው ሥነ ሥርዓት ይቀይስለታል፡፡ ይህ እንዲሆን የሚያሰፈለገውም በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ አንድ ሰው ወንጀል ሰርተሃል ተብሎ በሚከሰሰበትና ለፍርድ በሚቀርብበት ጊዜ ብዙ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ በወንጀል ተግባር ተከሶ ለፍርድ የሚቀርብ ሰው የሚደርስበት የማሕበራዊና የኢኮኖሚያዊ ቀውስ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ አይነቱ ከባድ ጉዳት ሊደርስ የሚገባው በእርግጥ ወንጀል በሰሩና ወንጀል ለመስራታቸውም የማያጠራጠር ማስረጃ በቀረበባቸው ሰዎች ላይ መሆን አለበት፡፡ አንድን ሰው ወንጀል ሰርተሃል ብሎ መክሰስና በማሕበራዊ ኑሮ ውስጥ ያለውን ክብር ዝቅ ማድረግ ቀላል ነው፡፡ ክሱን በማስረጃ ማረጋገጥና ተከሣሹን ጥፋተኛ ማስደረግ ግን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ በማስረጃ ሊረጋገጡ የማይችሉ ወንጀሎች በተቻለ መጠን በአጭሩ መቋጫ እንዲያገኙ ማድረግ የመንግሥት ሃላፊነት ነው፡፡

ሁለተኛ የወንጀልን ጉዳይ በፍጥነት ውሣኔ ማሰጠት ሲገባ በልማድ እንደሚታየው ግን ይህን ማድረግ እንዲህ ቀላል ሆኖ አልተገኘም፡፡ በማንኛውም አገር እንደሚታየው የወንጀል ሥራ በየአቅጣጫው እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ቢሆንም እንኳን ሁሉንም ወንጀል አድራጌዎች ወዲያውኑ ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብና ለማስቀጣት አይቻልም፡፡ ከወንጀሎቹ ብዛት አንፃር ሲታይ ደካማወቹ ጉዳዩች በአጭሩ የሚቋጩበት ዘዴ መኖር አለበት፡፡ ከማስረጃ አኳያ ጠንካራዎቹን እና ደካማዎቹን ጉዳዩች የምናጣራበት ዘዴ ቀዳሚ ምርመራ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ጠንካራዎቹን እና ደካማዎቹን ጉዳዩች የማበጠሩና የመለየቱ ተግባር እንደየ አገሩ የሕግ ሥርዓት ለዐቃቤ ሕግ ወይም ለመርማሪ ዳኛ (investigating Judge) ወይም የሕግ ሙያ ለሌላቸው እማኝ ዳኞች (Grand juries) ሊሰጥ ይችላል፡፡ ከፖሊስ የምርመራ መዝገብ የደረሰው ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩ በቀዳሚ ምርመራ አድረጌ ፍርድ ቤት መጣራት የሚገባው ሆኖ ካገኘው ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እንዲያጣራ ሊያዝ ይችላል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩ ለቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ትዕዛዝ የሚሰጠው ምን ምን ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ ነው? ጉዳዩ ለቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ሣያቀርብ በቀጥታ ክሱን በዳኝነት ለማየት ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ቢያቀርብ ሊመጣ የሚችለው ውጤት ምንድን ነው ?  የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ሥልጣን ተግባርና ዓላማ ምንድን ነው?

ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ለማገኘት ቀዳሚ ምርመራን (ቀዳሚ ምርመራ (Preliminary Inquiry) በሌሎች ሐገራት Preliminary Hearing, Preliminary Examination ወይም Examining Trial በመባል ይጠራል) አስመልክቶ በሌሎች ሐገራት ያለውን የሕግ ማዕቀፍ ይዘትና አሠራር በቅድሚያ መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡

ቀዳሚ ምርመራ በዩናይትድ ስቴትስ ሕግ (The Preliminary Inquiry in United States Law) 

በዓለማችን የኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት ተከታይ ከሆኑ ሐገራት መካከል ዩናይትድ እስቴት ብቸኛዋ የቀዳሚ ምርመራን ጉዳይ ግራንድ ጁሪ በተባለ አካል የምታጣራ ሐገር ነች፡፡ ግራንድ ጁሪዎች ስለሕግ ምንም እውቀት የሌላቸው ወንጀሉ ከተፈፀመበት አካባቢ ለተወሰነ ጊዜ ቀዳሚ ምርመራ እንዲያከናውኑ በሕዝብ የሚመረጡ ናቸው፡፡ የቀዳሚ ምርመራ ሥራ መደበኛ ሥራቸው ሳይሆን እንደየአንዳንዱ ስቴት ሕግ መሠረት በሳምንት ለተወሰነ ቀን ተሰብስበው ጉዳዩን ከሰሙ በኃላ ይወስናሉ፡፡ የፌዴራል የወንጀል ሥነ ሥርዓት ደንብ መርህ 6 ግራንድ ጁሪ የሚመሩበትን ሥርዓት ይደነግጋል፡፡ ደንቡ ገራንድ ጁሪዎች ከ16-23 አባላትን ሊያቅፉ እንደሚችሉና ክሱን ለመመርመር 12 አባላት የግድ መሰየም እንዳለባቸው ይጠይቃል፡፡ ግራንድ ጁሪው ለክሱ በቂ ማስረጃ መኖሩን እና ድርጊቱ በሕግ ወንጀል ተብሎ ተፈርጆ የነበረ መሆኑን ካረጋገጠ በኃላ የክስ አቤቱታውን ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት የልከዋል፡፡ ግራንድ ጁሪው ብቃት የሌለው ወይም የተንኮል ክስ እንዳይቀርብ የማበጠር ሥራ ይሰራሉ፡፡ እንደዩኒትድ እስቴት አምስተኛ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ድንጋጌ ከሆነ ማንኛውም በከባድ ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው ክሱ ለግራንድ ጁሪ ሳይቀርብ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ በአብዛኛው የሕግ ሥርዓቶች ቀላል የወንጀል ጉዳዩች (Misdemeanor) ለቀዳሚ ምርመራ ሳይቀርቡ በዐቃቤ ሕጉ አማካኝነት በቀጥታ ክሱ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ተከሣሹ ከዐቃቤ ሕግ ጋር የጥፋተኝነት ስምምነት(Plea Agreement) ከፈፀመ ጉዳዩን በግራንድ ጁሪ የማሰማት መብቱን እንደተወው ይቆጠራል፡፡ ተከሣሹ  ጉዳዩን በግራንድ ጁሪ የመሰማት መብቱን ትቶታል ማለት የሚቻለው በሕግ በሚፀና ሁኔታ በግልጽ ችሎት ሲፈፀም እና ለተከሣሹ ስለ ክሱ ይዘትና ስላለው መብት ከተነገረው በኃላ ነው፡፡ የግራንድ ጁሪ ውሣኔ አንድም የክሱን እውነትኝነት ወይም የክሱን ሃሰተኝነት ማረጋገጥ ነው፡፡ የግራንድ ጁሪ የክስ ሂደቶች ሚስጢራዊ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የክሱ እውነተኝነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ሂደቱ ግልጽ እንዲሆን መፍቀድ ተገቢነት የለወም፡፡ በዚሁ ምክንያት ያልተፈቀደላቸው ሰዎች የቀዳሚ ምረመራ የችሎት ሂደት እንዲታዘቡ አይፈቀድላቸውም፡፡ በቀዳሚ ምረመራ የሚከናወኑ ተግባራተን ለሕዝብ መግለጽ በጠቅላላ የተከለከለ ነው፡፡ ግራንድ ጁሪዎች በሚያከናውኑት የቀዳሚ ምርመራ ሂደት ውስጥ ተከሣሽ የመከላከያ ማስረጃ የማቅረብ መብት የሌለው ቢሆንም በራሳቸው ፈቃደ ሥልጣን (The discretion of the grand jury) ተከሣሹ የመከላከያ ማስረጃውን አቅርቦ እንዲያሰማ እድል ሊሰጡት ይችላሉ፡፡

ምንም እንኳን ግለሰቡ በወንጀል የተጠረጠረ ቢሆንም በግራንድ ጁሪዎች ፊት ሲቀርብ የሕግ አማካሪ የማያዝ መብት የለውም፡፡3 ግራንድ ጁሪ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች የሚያውቁትን እንዲመሰክሩ ማስገደድ ይችላል፡፡ የግራንድ ጁሪ ተግባር በዐቃቤ ሕጉ የተሰበሰቡ ማስረጃዎችን መርምሮ ወንጀል መፈፀሙን እና የተፈፀመውም በተከሣሹ ለመሆኑ የማያጠራጥር በቂ ማስረጃ ከተገኘ ተከሣሹ እንዲከሰስ ማድረግ ብቻ ሳይሆን አግባብነት የሌለው የወንጀል ክስ በዜጎች ላይ እንዳይቀርብባቸው ጥበቃ ማድረግንም ያካትታል፡፡ ግራንድ ጁሪዎቹ ጉዳዩ የክስ ምክንያት (Probable Cause) ካለው ሙግቱን ለሚሰማው ፍርድ ቤት ክሱ እንዲተላለፍ ከመወሰን ውጭ የተከሣሹን ጥፋተኝነት አይመረምሩም፡፡ ነገር ግን በዐቃቤ ሕግ የቀረበው የወንጀል ክስ የክስ ምክንያት ከሌለው ወይም የተሰበሰቡት ማስረጃዎች ደካማዎች ሁነው ተከሣሹን ሊያስከስሱት የማይችሉ መሆናቸውን ግራንድ ጁሪው ካመነ ወዲያውኑ ተከሣሹ በነፃ እንዲለቀቅ ይወስናሉ ከአጠቃላይ ሂደቱ መረዳት የሚቻለው በዩናይትድ እስቴት የቀዳሚ ምረመራ ዓላማ በተከሣሽ ላይ በማስረጃ ያልተደገፈ መሠረተ ቢስ ወይም ወንጃይ ክስ ክሱን በሚሰማው መደበኛ ፍርድ ቤት በተከሣሽ ላይ እንዳይቀርብበት ጥበቃ የሚያደረግ ነው፡፡  በዐቃቤ ሕግ የሚቀርቡትን የምስክሮች ቃል ወዲያውኑ መቀበሉ ጉዳዩ ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ጊዜ ምስክሮቹ የመጀመሪያ ቃላቸውን በልዩ ልዩ ምክንያት በመቀየር ወይም በመርሳት ሊፈጠሩ የሚችሉትን አንዳንድ ችግሮች ለማስወገድ ይጠቅማል፡፡ ተከሣሹም የዐቃቤ ሕጉን ማስረጃ በቀዳሚ ምርመራ ወቅት ስለሚያውቅ መከላከያ ማስረጃውን በአግባቡ እንዲያዘጋጅ ይረዳዋል፡፡

ቀዳሚ ምርመራ በእንግሊዝ ሕግ (The Preliminary Inquiry in English Law)

በወንጀል ጉዳይ ላይ ምርመራ የሚያጣራው ፖሊስ በተለመደው መልኩ ሥርዓቱን ጠብቆ ጉዳዩን ያጣራል፡፡ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ከባድ ወንጀል መደረጉን እና ወንጀል ፈፃሚውንም የሚያስረዳ ከሆነ የምርመራ መዝገቡ ወደ ዐቃቤ ሕግ ይተላለፋል፡፡ ዐቃቤ ሕጉም ጉዳዩን በሚገባ ካጠናና ከመረመረ በኃላ ክስ ሊቀርብበት የሚገባ ከሆነ ወደ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ያቀርባል፡፡

በእንግሊዝ አገር ሕግ መሠረት የማናቸውም የከባድ ወንጀል ጉዳይ በቀዳሚ ምርመራ ተጣርቶ ካላለፈ በቀር በቀጥታ ነገሩን ለመስማት እና ውሣኔ ለመስጠት ወደሚችለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት መቅረብ አይችልም፡፡ የዚህ የቀዳሚ ምርመራ ዋና ዓላማ ተፈፀሙ የተባሉት ከባድ ወንጀል ድርጊቶች የተፈፀሙት ክስ በቀረበበት ሰው መሆኑ ካልታመነ ወይም ካልተረጋገጠ በቀር ክስ እንዳይቀርብ ለማድረግ ነው። 5 ይህም የሚያረጋግጠው በቀደምትነት ጉዳዩ የቀረበለት የፖሊስ ክፍል በተከሣሹ ላይ የሰበሰበውን እና ያጣራውን ነገር በግልጽ ችሎት ለመርመራ አድራጊው ዳኛ በማቅረብ ነው፡፡ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ዳኛ በፖሊስ ያልተጠናቀሩ አዳዲስ ማስረጃዎች እንዲሰበሰቡ የሚያደርግ ሳይሆን በክስ አቅራቢዎቹ ክፍሎች የተሰበሰቡትን ማስረጃዎች የሚመዝን እና ብቃታቸውን የሚወስን ነው፡፡ በዚህ በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት በከሣሽ ክፍል በኩል መቅረብ የሚገባቸው የማስረጃ አይነቶች ለምሳሌ የሰው ምስክር ቴክኒካዊ መረጃዎች እና ሌሎችም ቀርበው መሰማትና መታየት አለባቸው፡፡ ዐቃቤ ሕጉ ተከሣሹ የተከሰሰበትን ወንጀል  መሥራቱን  የሚያስረዱ  ማስረጃዎችን ብቻ ሳይሆን  ጉዳዩን  ለቀዳሚ ምርመራ  ባቀረበበት ጊዜ ያወቃቸውን እና በእጁ የሚገኙትን ማስረጃዎች ሁሉ ማሳየት አለበት፡፡ ተከሣሹ ግን የቀረበበትን ክስ ለማስተባበልና መከላከያዎቹን ለማቅረብ ወይም በዝምታ የማለፍ መብት አለው፡፡ ስለዚህ ተከሣሹ በቀዳሚ ምርመራ ወቅት ክሱን ለማስተባበል መከላከያ ማስረጃውን ያቀርብ ወይም አያቀረብ እንደሆነ ምርጫው ሊታወቅ የሚችለው ዐቃቤ ሕጉ ክሱን እና ማስረጃዎቹን አቅርቦ ከጨረሰ በኃላ ነው፡፡ የቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት በዐቃቤ ሕጉ ብቻ ወይም በዐቃቤ ሕጉ እና በተከሣሹ የቀረበለትን ማስረጃ ሰምቶ ተገቢውን ውሣኔ ይሰጣል፡፡

በዐቃቤ ሕግ የቀረቡት ማስረጃዎች ወንጀል መደረጉን እና የተደረገውም በተከሣሹ መሆኑን የሚያሳምኑ ከሆነ ጉዳዩ ታይቶ የመጨረሻ ውሣኔ እንዲሰጥበት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ያደርጋል፡፡ በዐቃቤ ሕጉ የቀረበው ማስረጃ ደካማ ከሆነ ወይም ተከሣሹ መከላከያውን አቅርቦ ወንጀል አለማድረጉን ተደርጎም ከሆነ በእርሱ አለመደረጉን ካስረዳ ነፃ እንዲለቀቅ ያዛል፡፡ ስለዚህ በእንግሊዝ አገር የቀዳሚ ምርመራ ዓላማ ያለአግባብና ያለበቂ ማስረጃ የሚከሰሱትን እና የሚንገላቱትን ተከሣሾች ለመጠበቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ተከሣሾች ስለተከሰሱበት ጉዳይ እና ስለተሰበሰበባቸው ማስረጃዎች በሚገባ በዝርዝር ሊያውቁ የሚችሉበት ዘዴ ሲሆን ስለተከሣሾቹ የመከላከያ ማስረጃ ግን ነገሩ ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ሲቀርብ ከፈለጉ እዛው እንዲያቀርቡ የተለየ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቀዳሚ ምርመራን እንደማስረጃ ማወቂያ መሣሪያ (As a discovery device) በምንቆጥርበት ጊዜ በተለየ ለተከሣሹ ከሌላ አገር ይልቅ በእንግሊዝ አገር ከፍ ያለ ጥቅም ይሰጠዋል፡፡ የቀዳሚ ምርመራ ጉዳይ በሚገባ ከተሰራበትና በዐቃቤ ሕጉ በኩል የተሰበሰቡት ማስረጃዎች ለተከሣሹ ከተገለጹለት ጉዳዩ ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ለመጨረሻ ውሣኔ በሚቀርብበት ጊዜ ከፍ ያለ ጥቅም አለው፡፡ ጥቅሙም በዐቃቤ ሕግ በኩል የማያጠራጥርና በቂ ማስረጃ መቅረቡን ተከሣሽ ሲረዳ ጉዳዩ ለመጨረሻ ውሣኔ ክሱን ለሚሰማው ፍርድ ቤት ሲቀርብ ጊዜ ሳያራዝምና አንዳንድ የሕግ ክርክር ሳይፈጥር በክስ ማመልከቻው ላይ የተመለከተውን የወንጀል ዝርዝር በሙሉ የፈፀመ ለመሆኑ ያምናል፡፡

ደቡብ አፍሪካ የእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ስለነበረች የቀዳሚ ምርመራ ሕጓም በብዙ ሁኔታዎች ከዚሁ ከእንግሊዝ አገር ሕግ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሚሰሙ ጉዳዩች ሁሉ ቀዳሚ ምርመራ የግድ አስፈላጊ ነው። ምርመራውም የሚከናወነው በግልጽ ችሎት ሲሆን የቀዳሚ ምርመራ የመጨረሻ ውሣኔ የሚሆነው በመንግሥት በኩል በቂ  ማስረጃዎች መቅረብ ወይም  አለመቅረባቸውን  ለማረጋገጥና ካልቀረቡ ነፃ ለመልቀቅ ከቀረበ ግን ጉዳዩን ለመስማት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ለመላክ ነው፡፡ 

ቀዳሚ ምርመራ በፈረንሳይ ሕግ (The Preliminary Inquiry in French Law)

ቀዳሚ ምርመራን አስመልክቶ በፈረንሳይ ሕግ ያለው ሁኔታ ከዩናይትድ እስቲት እና ከእንግሊዝ የሕግ ማዕቀፍ በይዘቱ የተለየ ነው፡፡ በፈረንሳይ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እንደተሻሻለው አንድ የወንጀል ክስ ሂደት በሦስት ተለይተው በታወቁ ደረጃዎች የተከፈለ ነው፡፡ እነዚህም 1ኛ/ የምርመራ ደረጃ 2ኛ/ የቅድመ-ትሪያል የዳኝነት ደረጃ(Pre-trial judicial stage) እና 3ኛ/ ዋናው የትሪያል ደረጃ(main trial) ናቸው፡፡ አንድ የተፈፀመን የወንጀል ድርጊት የመመርመርና የማጣራት ተቀዳሚ ኃላፊነት የሚወድቀው በፖሊሱ ክፍል ላይ ነው፡፡ እነዚህም ‟ የዳኝነት ፖሊስ ”(judicial police, officiers de police judiciaire) በመባል የሚታወቁ ሲሆን ተጠሪነታቸው ለዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ነው፡፡ መርማሪዎቹ የምርመራ ተግባሮቻቸውን የሚያከናውኑት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ነው፡፡

በፈረንሳይ የወንጀል ፍርድ ቤቶች በሁለት የተከፈሉ ናቸው፡፡ እነዚህም የወንጀል ምርመራ የሚያካሂዱ ፍርድ ቤቶች (jurisdictions instruction) እና በወንጀል ጉዳዩች ውሣኔ የሚሰጡ ፍርድ ቤቶች (jurisdiction de jugement) በመባል ይታወቃሉ፡፡ መርማሪ ዳኞች (Investigative judges) የሚባሉትም ከመደበኛ የዳኝነት ሥራቸው ተለይተው ለ3 ዓመታት ያህል ከባድ የሆኑ የወንጀል ጉዳዩችን በመመርመር ተግባር ላይ እንዲያተኩሩ የሚመረጡ ዳኞች ናቸው፡፡ እንግዲህ የቅደመ-ትሪያል የዳኝነት ምርመራ ተግባሮችን የሚያከናውኑት እነዚህ መርማሪ ዳኞች ናቸው፡፡ በፈረንሳይ ሕግ መሠረት እያንዳንዱ ከባድ ወንጀል ጉዳዩን ለመስማት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት ለመርማሪ ዳኞች መቅረቡ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን የተፈፀመው ወንጀል ቀላል ወንጀል ከሆነ ጉዳዩ ለቀዳሚ ምርመራ ይቅረብ ወይም አይቅረብ የማለቱ ውሣኔ ለዐቃቤ ሕጉ ተትቷል፡፡

አንድ ሰው የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን የሚያመለክቱ ጠንካራ ምክንያቶች  ሲኖሩ ወዲያውኑ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ዳኛ ፊት ለምርመራ እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ መርማሪው ዳኛ ለተጠርጣሪው ክስ ሊመሰረትበት እንደሚችል ተከላካይ ጠበቃ የማቆም መብትና ጉዳዩን የያዘውን መዝገብ የመመልከት መብት እንዳለው ይነግረዋል፡፡ የቀረበበትን የክስ አይነት እንዲረዳው ገለጻ ይደረግለታል፡፡ መርማሪው ዳኛ አንደኛውን ወገን ብቻ ማለት ወደ ክስ አቅራቢው በማድላት ተከሣሹን ጥፋተኛ ሊያደርጉ የሚችሉትን ማስረጃዎች ብቻ ማጣራትና ማመዛዘን ሳይሆን አድላዊነት በሌለበት ትክክለኛውን ነገር አውቆ ለፍርድ ሰጭው ክፍል ለማቅረብ እንዲቻል ተከሣሹንም መደገፍ የሚችሉትን ሁኔታዎች ለማወቅና ለማቅረብ መሞከር አለበት፡፡ 

መርማሪው ዳኛ ሥራውን በሚሰራበት ጊዜ ከምስክሮች ቃል ከመቀበሉም በተጨማሪ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዙትንና የሚያስፈልጉትንም ዘዴዎች ይጠቀማል፡፡ ለምሳሌ ወንጀል የተደረገበትን ቦታ መመልከትን የመኖሪያ ቤት መበርበርን/ በፈረንሳይ ሕግ የመኖሪያ ቤት ጉብኝት በመባል ይታወቃል / የተገኙትን እቃዎች መያዝን ይጨምራል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደረግ የአመራመሩ፣ የአበራበሩና የአያያዙ ሁኔታዎች ሁሉ በሕግ መሠረት መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ምርመራ አድራጊው ዳኛ በዚህ መልክ የተገኙትን ማስረጃዎች አይቀበልም፡፡ ተቀብሎ ቢገኝ እንኳን በኋላ ጉዳዩ ክሱን በሚሰማው ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ጊዜ ምርመራው ሁሉ ዋጋ ያጣ ይሆናል፡፡

ማናቸውም የተገኙ ምስክሮች ለብቻ በምርመራ አድራጊው ዳኛ ይጠየቁና የሚሰጡት ቃል በጽሑፍ ሰፍሮ ቃሉን የሰጠው ሰው ይፈርምበታል፡፡ ይህ ምስክር የሰጠው ቃል ከምርመራ መዝገቡ ጋር በሚገባ ተያይዞ ተከሣሹ ወይም ጠበቃው ማየት ወይም ማግኘት በሚፈልግበት ጊዜ እንዲያየው ይፈቀድለታል፡፡ ማናቸውም በተከሣሹ ፋይል ውስጥ የሚገኙት ሠነዳዊ መረጃዎች ተከሣሹ ለምርመራ ጉዳይ ከመርማሪው ዳኛ ዘንድ ከመቅረቡ በፊት ቢያንስ ከ24 ስዓት ቀደም ብሎ ለጠበቃው ሊሰጠው ይገባል፡፡ በፈረንሳይ የማስረጃዎችን ብዛት የሚወስን ደንብ ስለሌለ ከወንጀሉ እና ከወንጀል አድራጊው ጋር ግንኙነት ኖሮቸው ይጠቅማሉ የሚባሉ ማስረጃዎች ሁሉ ለምርመራ አድራጊው ዳኛ ይቀርባሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ከቀረቡለት በኃላ እንደታማኝነታቸው ሁኔታ ዋጋ ሰጥቶ ወይም ነስቶ ተከሣሹን በነፃ ሊለቅ ወይም ጉዳዩ ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ተላልፎ የመጨረሻ ውሣኔ እንዲሰጥ ሊያስተላልፍ ይችላል። ከሂደቱ መረዳት የሚቻለው ነገሩ ክሱን ለመስማት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት የሚቀርበው ጉዳዩ የቱን ያህል እንደተጣራና ብዙ ጥንቃቄም እንደተደረገበት ስለሚያረጋግጥ ተከሣሹን በሀሰት ማስረጃ ለማስቀጣት ያለው እድል በጣም ያነሰ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ቀዳሚ ምርመራ በኢትዮጵያ ሕግ 

ከጋራ ብልፅግና አገሮች የተወረሰው የኢትዮጵያ የቀዳሚ ምርመራ ጉዳይ ጥቂት ማውሳቱ የሚጠቅም ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ሥራ ላይ ከማዋሉ በፊት አንድ የነፍስ ግድያ ወንጀል መደረጉ በወረዳው ውስጥ ለሚገኘው የወረዳ ወይም የአውራጃ ፍርድ ቤት ሲነገር ፍርድ ቤቱ ወንጀሉ ሲደረግ አዩ  የሚባሉትን ምስክሮች  ስለጉዳዩ  አንዳንድ  ጥያቄዎች ካቀረበላቸው በኋላ ጉዳዩን ለመስማት ሥልጣን የሌለው መሆኑን ለተጎዳው ወገን በመግለጽ ወደሚቀጥለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይለከዋል፡፡ የሚቀጥለው ፍርድ ቤት እንዲሁ የመጀመሪያው ፍርድ ቤት እንዳደረገው ነገሩን ለመስማት ሥልጣን አለመኖርን ምክንያት በማድረግ ነገሩን ለመስማትና ውሣኔ ለመስጠት ሥልጣን ወደተሰጠው የንጉሰ-ነገሥቱ መንግሥት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይመረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ ብዙ ወራቶችና እንዲሁም ዓመታት ያልፋሉ፡፡ ተከሣሹም በዚህን ጊዜ ሁሉ የሚቆየው እሥር ቤት ውስጥ ሲሆን በትክክል ስለቀረበበት ክስ ጉዳይ በወሬ ከመስማት በስተቀር ከደንበኛው ፍርድ ቤት ምንም የሚገለጽለት ነገር የለም፡፡ የተጎዳውም ሰው ቤተሰብም በከሣሽ መልክ በሚቀርብበት ጊዜ የማስረጃ ማቅረቡን ኃላፊነት ተሸክሞ ብዙውን ጊዜ ያልተጠናቀቀውን የፖሊስ የምርመራ መዝገብ በመያዝ በተጨማሪ አሉ የሚላቸውን ምስክሮች ጉዳዩ ወደሚሰማበት ቦታ ሂደው የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲያስደርግ ረዘም ያሉ ጊዜያቶች ያልፋሉ፤ ስለዚህ በወንጀል ሥራ የተከሰሱትን ሰዎች መብት መጠበቅና ማክበር እንዲሁም ያለአግባብ የተከሰሱበት ጉዳይ ውሣኔ ከማግኘቱ በፊት እንዳይራዘምና እንዳይቆይ በማድረግ ሕገ-ወጥ ሥራዎችን ማጥፋት አስፈለገ፡፡

የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እነዚህን ጉድለቶች እንዲያስቀር በሚገባ ተጠንቶ እንዲዘጋጅ ሲደረግ የቀዳሚ ምርመራ ጉዳይ ለማናቸውም በሞት ፍርድ ወይም በዕድሜ ልክ እስራት ለሚያስቀጡ ወንጀሎች አስፈላጊ እንዲሆን ታዘዘ፡፡ ይህም የሚሆነው ተደረገ የተባለውን ከባድ ወንጀል ለመስማትና ውሣኔ ለመስጠት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት በምን እንደሚከሰስ መርምሮ ለማረጋገጥ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ምርመራውን ሲጨርስ ማስረጃው ደካማ ሆኖ ካገኘው ተከሣሹን በነፃ ለመልቀቅ፤ ማስረጃው ጠንካራ ሆኖ ከተገኘና ተከሣሹ የተከሰሰበትን ወንጀል  ለማድረጉ ማስረጃዎቹ የሚያረጋግጡ ከሆነ ግን ጉዳዩን ሰምቶ ውሣኔውን  ለመስጠት ወደሚችለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለማስተላለፍ ታልሞ ነበር፡፡  ይሁን እንጂ አሁን ተደንግጎ በሚገኘው ሁኔታ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት በምርመራው ጊዜ ማስረጃው ደካማ ቢሆንም እንኳን በነፃ መልቀቅ አይችልም፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጋችን በሦስተኛው መጽሐፍ (Book III) ውስጥ የሰፈረው የቀዳሚ ምርመራ ዓላማ እስከዚህም ግልጽ አይደለም፡፡ ይህው የቀዳሚ ምርመራ ሥርዓት በመሠረቱ ተፈፃሚ የሚሆነው ለሁለት ዓይነት ወንጀሎች ብቻ ነው፡፡ እነዚህም ከባድ የግፍ አገዳደል (Homicide in the first degree, አንቀጽ 522) እና ከባድ የወንበዴነት ሥራ (Aggravated robbery, አንቀጽ 637) ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁለት ዓይነት ጉዳዩችም ላይ ሆነ በሌሎች በከፍተኛው ፍርድ ቤት መታየት ባለባቸው ጉዳዩች ላይ ይህው ምርመራ እንዲደረግ ለመወሰንና ላለመወሰን ሥልጣኑ የተሰጠው ለዐቃቤ ሕግ ነው (አንቀጽ 80/2/)፡፡ ሆኖም ቀዳሚ ምርመራ ማድረግ ሳያስፈለግ ጉዳዩ መታየት አለበት በማለት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ሃሳብ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የተቀበለው ከሆነ ፍርድ ቤቱ ቀዳሚ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ አይደለም ብሎ መወሰን ይችላል(አንቀጽ 80/1/)፡፡ በሌሎች በከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚታዩ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕጉ ካላዘዘ በቀር ቀዳሚ ምርመራ መደረግ የለበትም(አንቀጽ 80/2/)፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ወይም በወረዳ ፍርድ ቤቶች በሚታዩ ወንጀሎች ቀዳሚ ምርመራ ማድረግ አያስፈልግም፡፡

የቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ሆኖ የሚያገለግለውም ወንጀሉ በተፈፀመበት ሥፍራ ሥልጣን ያለው የወረዳ ወይም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው(አንቀጽ 81)፡፡ ጉዳዩ በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት መጣራቱ በክሱ ውጤት ላይ የሚያስከትለው ለውጥ የለም፡፡ ቀዳሚ ምርመራ ያደረገው ፍርድ ቤት ማስረጃውን ከሰማ በኃላ ማስረጃው በቂ አይደለም ብሎ ተከሣሹን ነፃ መልቀቅ አይችልም፡፡ ነገሩን አጣርቶ ክሱ በከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርብና ነገሩ እንዲሰማ ያደርጋል(አንቀጽ 89/1/)፡፡ ቀዳሚ ምርመራ የሚያደርገው ፍርድ ቤት ክሱ የሚያሟግት ያለመሆኑንና የተከሣሹን ጥፋተኝነት ወይም ነፃ መሆን በዚሁ በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ሳይሆን በከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚወሰን መሆኑን ለተከሣሹ ይነግረዋል በማለት በማያሻማ ቋንቋ ተገልጻል (አንቀጽ 85/2/)፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጋችን ላይ ቀዳሚ ምርመራ ይህን የመሰለ መልክ ያለው ቢሆንም ይህም ሆኖ በጸሃፊው እምነት ቀዳሚ ምርመራ ሦስት ዋና ዋና ጠቀሚታዎች ያሉት ይመስለኛል፡፡

አንደኛው ጠቀሜታው ማስረጃን የመለዋወጫ ዘዴ (Discovery device) ሆኖ የሚያገለግል መሆኑ ነው፡፡ በሕጉ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው፤ የተከሰሰው ሰው እራሱ ሲቀርብ ወይም እንዲቀርብ ከተደረገ በኃላ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ነገሩን እንዲጀምርና ምስክሮቹን እንዲጠራ ይደረጋል( አንቀጽ 84)፡፡ ምስክርነታቸው ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት አስፈላጊ መስሎ ከታየው ዐቃቤ ሕግ ያልቆጠራቸውን ምስክሮች ፍርድ ቤቱ በማናቸውም ጊዜ መጥራትና ማስመስከር ይችላል (አንቀጽ 87)፡፡ በአንቀጽ 147 በተነገረው መሠረት ማስረጃው መመዝገብ አለበት፡፡ እንዲሁም የእያንዳንዱ ምስክር ቃል ለየብቻው በወረቀት ላይ መጻፍ አለበት(አንቀጽ 88)፡፡ ተከሣሹ መጥራት የሚፈልጋቸውን ምስክሮች ዝርዝር እስከነ አድራሻቸው እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትህዛዝ ይሰጣል (አንቀጽ 89/3/)፡፡ ተከሣሹ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነገሩ እንዲታይ ሲላክ ዋናው መዝገብና ለፍርድ ቤት የሚቀርብ ማናቸውም መረጃ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሹም ይላካሉ፤ በብዛቱ ወይም በሌላ ምክንያት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሹም ለመላክ አስቸጋሪ የሆነ ማንኛውም መረጃ በፖሊስ እጅ ሊቆይ ይችላል፡፡ በፖሊስ እጅ የቆዩትንና ለከፍተኛው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሹም የተላኩትን መረጃዎች የሚገልጽ ዝርዝር ከመዝገቡ ጋር ይላካል፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የመዝገብ ቤት ሹምም ከቀዳሚ ምርመራው ፍርድ ቤት የመጣውን መዝገብ ግልባጭ ማድረግና ለዐቃቤ ሕግና ለተከሣሹ የመስጠት ኃላፊነት አለበት (አንቀጽ 91) ከዚህ በላይ በመዝገቡ ውስጥ ሊገለጹ የሚገባቸው ዝርዝር መረጃዎች በአንቀጽ 92 ላይ ከ(ሀ) እስከ (ኘ) ተራ ቁጥር ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ መረጃዎች ተከሣሹም ሆነ ዐቃቤ ሕግ ክሳቸውንና መከላከያቸውን በሚገባ እንዲያዘጋጁ የተሻለ ዕድል የሚያስገኙ መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡

ሁለተኛው ጥቀሚታው  ቀዳሚ ምርመራን ብዙ አገሮች ማስረጃን በጊዜው ለመያዝና እንዳይባክን ለመቆጣጠር ይጠቀሙበታል፡፡ የእኛው ሕግ ቀዳሚ ምርመራ ሥርዓትን የዘረጋው ከዚህ ዓላማ አንጻር መሆኑ ግልጽ ቢሆንም በአግባቡ ሥራ ላይ ባለማዋሉ የታለመለትን ዓላማ ሊያሳካ አልቻለም፡፡ የክሱ መሰማት እየዘገየ በሄደ መጠን በዚያው ልክ የምስክሮችም የማስታወስ ችሎታ እየተዳከመ መሄዱ ስለማይቀር እነዚህ ማስረጃዎች ሳይረሱና ሳይዘነጉ ገና በትኩሱ ተመዝግበው እንዲቆይ ለማድረግ ይረዳል፡፡ እየቆዩ ምስክርነታቸውን የሚለዋውጡ ምስክሮችን ለመቆጣጠርም ይረዳል፡፡ ማስረጃው ወንጀሉ እንደተፈፀመ ወዲያውኑ ለቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ማቅረብ ቢቻል ደግሞ ምስክሮች ያዩትን ነገር የመመስከሩ ዕድል ስለሚያይል ትክክለኛ ፍርድ ላይ ለመድረስ ከፍተኛ አስተዋፆኦ ያደርጋል፡፡ ምስክሮች ሳይገኙ ሲቀሩ በቀዳሚ ምርመራ የተሰጠ የምስክርነት ቃል ለፍርድ ቤት በማስረጃነት እንዲቀርብ ስለሚፈቀድ (አንቀጽ 144) የዚህ ሥራ መጀመር ፍርድ ቤቶች ለፖሊስ በተሰጠ ምስክርነት ላይ ተንጠልጥሎ ውሣኔ ከመስጠትም ያድናቸዋል፡፡

ሦስተኛው ጠቀሚታው ደግሞ ተከሣሹ ገና በትኩሱ የሚሰጠው የእምነት ቃል (Confession) ካለ በአማካሪ ብዛት ሃሳቡን ሳይቀይር ተመዝግቦ እንዲቆይ ለማድረግ ይረዳል፡፡ ሕጉ ስለዚሁ ሲገልጽ፦ 

‟የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከተሰሙና ቃላቸውም ከተመዘገበ በኃላ ለክሱ መልስ ተከሣሹ ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ይጠይቀዋል (አንቀጽ 85/1/)፡፡ ቃሉን እንዲሰጥ የማይገደድ መሆኑን እና በፍቃዱ የሰጠው ቃል ግን በጽሁፍ ሆኖ በማስረጃነት ነገሩ ሲሰማ የሚቀርብ መሆኑን ለተከሣሹ ይነገረዋል (አንቀጽ 85/3/)፡፡  ተከሣሹ ቃሉን መስጠት ያለመረጠ እንደሆነ ነገሩ እንዲሰማ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀርባል (አንቀጽ 87/1/)፡፡ ተከሣሹ ቃሉን መስጠት የመረጠ እንደሆነ ቃሉ ተጽፎ ለተከሣሹ ተነቦለት ፍርድ ቤቱ ከፈረመበት በኃላ በመዝገቡ ውስጥ ይቀመጣል ይላል (አንቀጽ 87/2/)፡፡ ”

በረቂቁ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 169 ንዑስ-አንቀጽ (1) ላይ የተመለከተው ድንጋጌ በሥራ ላይ ካለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ውስጥ የሌለ አዲስ ድንጋጌ ሲሆን እንዲህ ይላል ‟ ቀዳሚ ምርመራ ያደረገው ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ እና የተከሳሹን ቃል ከመረመረ በኋላ ክስ ለመመስረት የሚያስችል ምክንያት አለመኖሩን ከተረዳ መዝገቡን በመዝጋት ተከሳሹ እና በወንጀሉ ምክንያት የተያዘ ንብረት ካለ እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ይሰጣል” በማለት ለቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት ያልነበረውን አዲስ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ ከረቂቁ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው ቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ መሠረት ያለው መሆኑን በቅድሚያ ማጣራት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም መሠረት የቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕጉ ተከሣሹን የጠረጠረው በቂ ባለሆነ ምክንያትና ማስረጃ በሌለበት ነው ብሎ ካመነ በተከሣሹ ላይ የበለጠ ጉዳት ሳይደርስ ከክሱ እንዲሰናበት በማድረግ መብት እንዳይጣስም ሆነ የሥልጣን አላግባብ መጠቀም እንዳይኖር በመከላከል ሰፊ ሚና እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ይህ አሠራር የፍትሐብሔር ጉዳዩችን የሚያይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ Cause Of Action መኖር አለመኖሩን ለማጣራት የተሰጠው ሥልጣን ዓይነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ለፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳዩች ላይ የዚህ ዓይነት ሥልጣን አልሰጠም ነበር ነገር ግን አሁን በረቂቅ ሕጉ ውስጥ እንዲካተት መደረጉ ተገቢ ነው፡፡ በዋስትና ወረቀት መለቀቅን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት ክሱ በከፍተኛው ፍርድ ቤት እስኪታይ ድረስ ተከሣሹ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ለማዘዝ ይችላል (አንቀጽ 93)፡፡

ማጠቃለያ እና የመፍተሄ ሃሳቦች

የኢትዮጵያ የቀዳሚ ምርመራ የሕግ ሥርዓት ከሌሎች ሐገራት የቀዳሚ ምርመራ የሕግ ሥርዓት ጋር በነጽጽር ሲታይ ሰፊ ልዩነት አለው። የኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት ተከታይ የሆኑት ሐገራት ለምሳሌ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ካናዳና ማሊዢያ የቀዳሚ ምርመራ ሕጎቻቸው ዋና ዓላማዎች የሲቪል ሎው የሕግ ሥርዓት አራማጅ ከሆኑት ለምሳሌ ከፈረንሳይ ጋር አንድና ተመሳሳይ ሲሆን በሁለቱ የሕግ ሥርዓቶች መካከል መሠረታዊ ልዩነታቸው የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤቶቻቸው ተቋማዊ አደረጃጀት እና አሰራራቸው እንደ ሐገሮቹ ልዩ ሁኔታ አንድና ተመሳሳይ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል።

ቀዳሚ ምርመራ እንዲያደርጉ በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው በአሜሪካ ግራንድ ጁሪዎች (Grand juries)፣ በእንግሌዝ የማጂስትሬት ፍርድ ቤቶች (Magistrate courts)፣ በፈረንሳይ መርማሪ ዳኞች (investigative judges) ዋና ዓላማ በማስረጃዎች ላይ ምዘናዎችን በማድረግ በጉዳዩቹ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ውሣኔ የመስጠት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ፍርድ ቤቱ ተከሣሹ የተጠረጠረበትን ወንጀል ፈጽሟል የሚል መደምደሚያ ላይ ከደረሰ (Prima facie case) ክሱ እንዲቀርብ ጉዳዩን ለመስማት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ይመረዋል፡፡ የቀረቡት ማስረጃዎች ተከሣሹ ላይ ክስ ለማቅረብ የሚያበቁ አይደሉም የሚል መደምደሚያ ላይ ከደረሰ ክሱን ውድቅ (Screening power) የማድረግ ሥልጣን አለው።

በአገራችን የተዘረጋው የቀዳሚ ምርመራ የሕግ ሥርዓት ማስረጃን ከመመዝገብ ባለፈ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤቶች በዐቃቤ ሕግ የቀረቡትን ማስረጃዎች የመመዘን ወይም የቀረቡት ማስረጃዎች ተከሣሹ ላይ ክስ ለማቅረብ የሚያበቁ አይደሉም በማለት ክሱን ውድቅ (Screening power) እንዲያደርጉት ሥልጣን አይሰጣቸውም። በእርግጥ በአለማችን ያሉ አገሮች ፍትህን ለማስፈን የሚጠቀሙባቸው የሕግ ማዕቀፎች አይነትና ይዘት፣ የሕግ ምዕቀፎቹ የሚወጡበትና ሥር ላይ የሚውሉበት ሁኔታ፣ በፍትህ አሰጣጥ ሂደት ተሣታፊ እንዲሆኑ ያቋቋሟቸው የመንግሥት አካላትና በሂደቱ እንዲሳተፉ የሚፈቀድላቸው የግል ተቋማት፣ ለተቋማቱ የሚሰጡት ሥልጣንና ሃላፊነት የተቋሞቹ አሠራርና እሴቶች የሚለያቸው በርካታ ሁኔታዎች እንዳሉ አያከራክርም። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የእያንዳንዱ አገር የፍትህ ሥርዓት የአገሪቱን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች መሠረት በማድረግ የተገነባና በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የተለያዪ ችግሮች ለመፍታት በሚችለበት መንገድ የተደራጀ አሠራር የቀረፀና አገራዊ አላፊነቱን የሚወጣ በመሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት የአንዱ አገር የፍትህ ሥርዓት ከሌላው የሚለየበት የራሱ የሆነ ልዩ ባህሪያት ያሉት ቢሆንም በአንዱ ወይም በሌላው መልኩ የአንዳንድ አገሮች የፍትህ ስርዓት የሚጋሯቸው እሴቶችና የሚመሳሰላቸው መሠረታዊ ሁኔታዎች አሉ።

ቀዳሚ ምርመራን አስመልክቶ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ የተደነገጉት ድንጋጌዎች ይዘት ሲታይ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት ማስረጃዎችን ከመመዝገብ ባለፈ በተከሣሹ ተፈጽሟል የተባለውን ወንጀል ለማስረዳት ብቃት ያላቸው ስለመሆን አለመሆናቸው፣ እንዲሁም ክስ እንዲቀርብ ወይም እንዳይቀርብ የማዘዝ ሥልጣን የተሰጠው አለመሆኑን መረዳት ይቻላል። በመሆኑም ተከሣሽ ላይ ክስ እንዲቀርብ፣ የሚቀርብ ከሆነም ምን አይነት ክስ መቅረብ እንዳለበት መወሰን ካልቻለ፣ እንዲሁም ዋና ተግባሩ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃዎች መመዝገብ ብቻ ከሆነ እና እነዚህን ተግባራት ክሱን የሚሰማው ፍርድ ቤት ማከናውን የሚችል ከሆነ ወይም በሌላ አገላለጽ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊው ፍርድ ቤት የሚያከናውናቸውን ተግባራት ክሱን በዳኝነት የሚያየው ፍርድ ቤት የሚሰራቸው ከሆነ በእርግጥም የድንጋጌዎቹ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ውስጥ መቀመጥ ጠቀሚታው ግልጽ አይደለም። ምናልባት ለዚህ ይሆናል በተግባር ያለው አፈፃፀም በጣም ዝቅተኛ የሆነው ወይም ጨርሶውኑ ቀርቷል ሊባል በሚችል ደረጃ ላይ የሚገኘው።

ረቂቁ የወንጀል የሥነ ሥርዓት ሕግ ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤቶች በዐቃቤ ሕግ የቀረበው የወንጀል ክስ የክስ ምክንያት (Probable Cause) ካለው ክሱን ለሚሰማው ፍርድ ቤት (Trial Court) ጉዳዩ እንዲተላለፍ ይወስናሉ። ነገር ግን በዐቃቤ ሕግ የቀረበው የወንጀል ክስ የክስ ምክንያት ከሌለው ወይም የተሰበሰቡት ማስረጃዎች ደካማዎች ሁነው ተከሣሹን ሊያስከስሱት የማይችሉ መሆናቸውን ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ካመነ ወዲያውኑ ተከሣሹ በነፃ እንዲለቀቅ የመወሰን ሥልጣን እንዳለው ተመልክቷል፡፡ የረቂቁ የወንጀል የሥነ ሥርዓት ሕግ የቀዳሚ ምረመራ ዋና ዓላማ ማስረጃን መዝገቦ ከመያዝ ባለፈ በተከሣሽ ላይ በማስረጃ ያልተደገፈ መሠረተ ቢስ ወይም ወንጃይ ክስ ክሱን በሚሰማው መደበኛ ፍርድ እንዳይቀርብ የሕግ ጥበቃና ከለላ ያደርጋል። ይህም ረቂቁ የወንጀል የሥነ ሥርዓት ሕግ ቀዳሚ ምርመራን አስመልክቶ በሥራ ላይ ካለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ጋር ሲነጻጸር መሠረታዊ ልዩነት ያለው ለመሆኑ መረዳት ይቻላል።

ረቂቁ የወንጀል የሥነ ሥርዓት ሕግ ቀዳሚ ምርመራን አስመልክቶ በነባሩ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ የሚታዩትን የሕግ ክፍተቶች እና ጉድለቶች በሙሉ በዝርዝርና በግልጽ የሚሞላ አይደለም። በመሆኑም ረቂቁ የወንጀል የሥነ ሥርዓት ሕግ የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤቶች የሥልጣን ወሰንን በማስፋት የተከሣሽን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች እንደ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች መዝገብው መያዝ እንዳለባቸው የሚደነግግ ድንጋጌን እና ተከሣሽ የቀረበበትን ክስ ለማስተባበልና መከላከያዎቹን አቅርቦ ለማሰማት መብት ያለው ለመሆኑ የሚያመላከት አዲስ የሕግ ማዕቀፍን ቢያካትት መልካም ነው። በዐቃቤ ሕጉ የቀረበው ማስረጃ ደካማ ከሆነ ወይም ተከሣሹ መከላከያውን አቅርቦ ወንጀል አለማድረጉን ተደርጎም ከሆነ በእርሱ አለመደረጉን ካስረዳ ነፃ እንዲለቀቅ የሚፈቅዱ የሕግ ማሻሻያዎችን በማድረግ ግልጽ መሆን የሚገባቸውን መሠረተ ሀሳቦች በግልጽና በዝርዝር መደንገግ ያስፈልጋል፡፡

Download with full citation

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 አፈፃፀም ላይ የሚስተዋል መሠረታ...
በኢትዮጵያ ሕግ የግል የኮንስትራክሽን ውሎች ምንነት፣ የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 19 May 2024