Font size: +
8 minutes reading time (1663 words)

ያለደረሰኝ ግብይት የማከናወን ወንጀል

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ያለደረሰኝ ግብይት የማከናወን ወንጀል ላይ መሠረታዊ የሆነ መረዳት እንዲኖር ማድረግ እና ያለደረሰኝ ግብይት ከማከናወን ወንጀል ጋር በተያያዘ እየቀረቡ ያሉ አንዳንድ ማብራሪያዎች (commentaries) ላይ የሚስተዋሉትን ግድፈቶች ማቃናት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡

ያለደሰኝ ግብይት ወንጀል የኢትዮጵያ የታክስ ሕግ ወንጀል አካል ሆኖ የተደነገገው በ2001 ዓ.ም ሲሆን ይህም በአዋጅ 609/2001 አንቀጽ 50 (ሐ) እና 50 (መ) 2 መሠረት ነው፡፡ ምንም እንኳ ጥቂት ለውጥ ቢደረግባቸውም እነዚህ አንቀፆች በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀጽ 120/1 እና 131(1)(ለ) ላይ ከተደነገገውና ያለደረሰኝ ግብይትን የወንጀል ተግባር አድርጎ ከሚደነግጉት አንቀፆች ጋር የጎላ የይዘት ልዩነት የላቸውም፡፡

በዚህ ጽሑፍ የግብይት ምንነት፣ በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀጽ 120(1) እና 131(1)(ለ) ጋር በተያያዘ የሚነሱ የአተረጓጎም ልዩነቶችና የክስ አቀራረብ፣ ያለደረሰኝ ግብይት ወንጀል ክርክር ላይ በተከሳሾች የሚቀርቡ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና መከላከያዎች እንዲሁም ከአንቀጽ 131(1) (ለ) ጋር ተያይዞ እየተስተዋሉ ያሉት የአተረጓጎም እና የአተገባበር ልዩነቶችን በሚመለከት መሰረታዊ የሆነ ግንዛቤ በሚሰጥ መልኩ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡

1. ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ

በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀጽ 19/3 ላይ እንደተመለከተው ማንኛውም የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ታክስ ከፋይ ለሚያከናውነው ግብይት ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ የአዋጅ 983/2008 አንቀጽ 19/3ን ሀሳብ በአግባቡ ለመረዳት የግብይት ምንነት እና የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ታክስ ከፋይ ማነው የሚሉ ነጥቦች መለየት ያለባቸው ሲሆን በፌደራል ገቢ ግብር አዋጅ 979/2008 አንቀጽ 3 እና 82(1) እና (2) መሠረት ማንኛውም የደረጃ ሀ እና ለ ታክስ ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ደረጃ ሀ እና ለ ታክስ ከፋዮች ግብይት በሚያከናውኑበት ወቅት የታክስ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡

2. የግብይት ምንነት፡-

ግብይት ለሚለው ቃል በታክስ ሕግ ወጥና ቀጥተኛ የሆነ ትርጉም ተሰጥቶት አናገኝም፡፡ ሆኖም በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 285/94 አንቀጽ 9/1፣11/1 እና አዋጅ 285/94 ለማሻሻል የወጣውን አዋጅ 609/2001 አንቀጽ 2/10 ላይ የተመለከተውን በጣምራ ስናነብ የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብይት ማለት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በአዋጅ 285/94 አንቀጽ 9/1/ ላይ እንደተመለከተው በመርህ ደረጃ የተጨማሪ እሴት ታክስ ግብይት ተከናወነ የሚባለው የዕቃ ርክክብ በተደረገበት ቦታ ሲሆን ግዜውን በሚመለከት በተመሳሳይ አዋጅ አንቀጽ 11/1 ላይ ታክስ የሚከፈልበት ግብይት ተከናወነ የሚባለው ለግብይቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ በሚሰጥበት ወቅት መሆኑን በግልፅ ተመልከቷል፡፡ ትርጉሙን ሙሉ ለማድረግ ሻጭ ደረሰኝ መቼ መስጠት ይኖርበታል የሚለው ቃል መመለስ ያለበት ሲሆን በአዋጅ 609/2001 አንቀጽ 2/10 ላይ እንደተመለከተው ታክስ የሚከፈልበት ገብይት የሚያካሄድ ሰው ደረሰኝ ወድያውኑ(simultaneously) መስጠት እንዳለበት ተመልከቷል፡፡ ከላይ ከተመለከተው ትርጉም በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አሁን ባለው የሕግ ማቀፍ የተጫሪ እሴት ታክስን በሚመለከት የእቃ አቅርቦትና ደረሰኝ የመስጠት ትግባር አንድ ላይ(simultaneously) መከናወን እንደለባቸው ሕግ የሚያስገድድ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

በመሆኑም ማንኛውም ታክስ የሚከፈልበት ግብይት የሚያከናውን ታክስ ከፋይ ለሚያደርጋቸው ግብይቶች ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ይኖርበታል፡፡

ሊሰጡ የሚገባቸው ደረሰኞች አይነት፡- በመመሪያ 149/2011 ላይ እንደተመለከተው ገቢዎች ሚኒስቴር ታክስ ከፋዮች እንዲጠቀሙት ብዙ አይነት ደረሰኞችን ሊፈቅድ ይችላል፡፡

እነዚህም፡

  • የእጅ በእጅ የሽያጭ ደረሰኝ፣
  • የዱቤ ሽያጭ ደረሰኝ
  • የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ
  • የኤልክትሮንክስ ደረሰኝ፣
  • ማኑዋል ደረሰኝ እና የመሳሉት ናቸው፡፡

 

3. ያለደረሰኝ ግብይት የማከናወን ወንጀል

  • ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ጋር ተያያዞ የሚፈፀም ያለደረሰኝ ግብይት ወንጀል

ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ አጠቃቀም ጋር ተይይዞ የሚፈፀመው ያለደረሰኝ ግብይት ወንጀል በአዋጅ 983/2008 አንቀጽ 131/1/ለ ላይ የወንጀል ተግባር ሆኖ የተደነገገ ሲሆን የድንጋጌው ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

አንቀጽ 131-(/ለ) ፡-

ማንኛውም በሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ የመጠቀም ግዴታ ያለበት ሰው፡-

“መሳርያው በጥገና ላይ ባለበት ጊዜ ወይም በሌላ በቂ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ከታተመ ደረሰኝ ውጪ ወይም ያለ ደረሰኝ ግብት ካከናወነ፤ ከ 2 አመት በማያንስ እና ከ5 አመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል”

የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ዋነኛው ዓላማ ታክስ ከፋይ የሚያደርጋቸውን እያንዳንዱን ሽያጭ በአግባቡ መዝግቦ እንዲያቆይና ለገቢዎች ሚኒስተር ሽያጩን በትክክል ሪፖርት እንዲደረግ ታስቦ ነው፡፡

ከላይ ከተመለከተው የአዋጅ 983/2008 አንቀጽ 131/1(ለ) ላይ መረዳት እንደሚቻለው ማንኛውም ሰው የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በጥገና ላይ ከሆነ ወይም ሌሎች በቂ ምክንያቶች በመኖራቸው ምክንያት የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ መጠቀም ካልተቻለ በቀር ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከታተመ ደረሰኝ ውጭ በሆነ በሌላ ማንኛውም ደረሰኝ ወይም ያለደረሰኝ ግብይት ማከናወን አይችልም፡፡ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በስራ ላይ እስካለ ድረስ ታክስ ከፋይ ግብይት ማከናወን ያለበት ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በሚወጣ ደረሰኝ ብቻ ነው፡፡ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የመያዝ ግዴታ ያለበት ማንኛውም ታክስ ከፋይ መሣሪያው በስራ ላይ ባለበት ወቅት ያለደረሰኝ ግብይት የማከናወን ተግባር ወይም በሌሎች ደረሰኞች(ማኑዋል ደረሰኝን ጨምሮ) ግብይት ካከናወነ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ክስ ይቀርብበታል፡፡

በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያስችል ዘንድ ከታች የተመለከቱትን ፍሬ ነገሮች ማየቱ አስፈላጊ ነው፡፡

  • አንቀጽ 131 የሚመለከተው የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን የመያዝ ግዴታ ያለበትን ታክስ ከፋይ ብቻ ነው፡፡
  • የአንቀጽ 131/1/(ለ) የሽ/መ/መ የያዙ ሰዎች ማሽኑ ስራ ላይ እያለ ሌሎች ደረሰኞች እንዳይጠቀሙ ያለመ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሽ/መ/መ የሚደረጉ ግብይቶችን በቀላሉ ማጭበርበር ስለማይቻል ነው፡፡ በመሆኑም
  • የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በጥገና እና በሌሎች በቂ ምክንያቶች ስራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚደረግ ያለደረሰኝ ግብይት፣በማኑዋል ደረሰኝ የሚደረግ ግብይትም ሆነ በሌሎች ደረሰኞች የሚደረጉ ግብይቶች በዚህ ድንጋጌ ስር የሚሸፈኑ አይደሉም፡፡ የአዋጅ 983/2008 በአንቀጽ 131/1(ለ) ክልከላ የሚጥለው የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ስራ ላይ እያለ የሚፈፀሙ ተግባራትን በሚመለከት ብቻ ነው፡፡ ለአብነት ያክል አንድ ሰው የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ጥገና ላይ ባለበት ወቅት ያለደረሰኝ ግብይት ቢያከናዉን ድርጊቱ በአንቀጽ 131/1(ለ) ስር የማይሸፈን በመሆኑ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የወንጀል ክስ ማቅረብ አይቻልም፡፡ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በጥገና ላይ ነው ማለት ታክስ ከፋይ ያለደረሰኝ ግብይት ማከናወን ይችላል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ መሣሪያው በጥገና ላይ ባለበት ወቅት ታክስ ከፋይ ግብይቱን የእጅ በእጅ ሽያጭ ደሰረኝ(ማኑዋል) በመጠቀም የማከናወን ግዴታ አለበት፡፡ ሆኖም ማሽኑ በጥገና ላይ ሳለ ያለደረሰኝ ግብይት ተግባር የተከናወነ እንደሆነ ድርጊቱ መሣሪያው በጥገና ላይ ባለበት የተፈፀመ በመሆኑ በታክስ አስተዳደር አዋጅ 131/1/(ለ) መሠረት የሚሸፈን ስላልሆነ የወንጅለ ክስ ሊቀርብበት የሚገባው በአንቀጽ 120/1 መሠረት ነው፡፡
  • በአንቀጽ 131/1/ለ/ ስር ወይም ከሚል ቃል በኃላ የተገለፀው ያለደረሰኝ ግብይት የሚል ሀረግ በአንቀጽ 131(1)(ለ) ላይ የተመለከቱት ሁኔታዎች በሌሉበት እና የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ስራ ላይ ባለበት የሚፈጸመውን ያለ ደረሰኝ ግብይት የማከናወን የወንጀል ተግባር ለማሳየት እንጂ የሽ/መ/መሣሪያ ጥገና ላይ ባለበት ሁኔታ ያለደረሰኝ ግብይት የማከናወን የወንጀል ተግባር የተከናወነ እንደሆነ የወንጀል ክስ የሚቀርበበትን ስርዓት የሚደነግግ አይደለም፡፡ ለዚህ ሀሳብ ግልፅነት የድንጋዉን የእንግሊዘኛ ትርጉም ማየቱ አስፈላጊ ስለሆነ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

“ If he, except at the time sale register machine is under repair , or other justifiable reason, carried out transactions without receipt or invoice  or used any other receipt not generated by a sale register machine shall be punished with rigorous imprisonment 2-5”

ከላይ ከተመለከተው የእንግሊዘኛ ትርጉም ጭምር በግልፅ መረዳት እንደሚቻለው የሺያጭ መመዝገቢያ ማሸን የመያዝ ግዴታ ያለበት ሰው( If he) ማሽኑ ጥገና ላይ ባለበት እና ሌሎች በሌሎች በቂ ምክንያቶች ስራ ላይ ካልሆነ በቀር ማሽኑ ስራ ላይ ባለበት ሁኔታ -------

  1. ያለደረኝ ግብይት የተከናወነ እንደሆነ፣
  2. ከሽ/መ/መ ውጭ በሚወጡ ወይም በሌሎች ደረሰኞች የሚደረግ ግብይት ሲኖር፣

ማለትም በማኑዋል ደረሰኞች፣በኮምፕዩተር ደረሰኞች፣ሀሰተኛ ደረሰኞች፣የተፈቀዱ/ያልተፈቀዱ ደረሰኞ የሰጠ እንደሆነ በዚህ ድንጋጌ(131/1/ለ) መሠረት ክስ ሊቀርብ እንደሚገባ በግልጽ ተመልክቷል፡፡

በማጠቃለያነት፡- የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ አገልግሎት ላይ እያለ(ማለትም በጥገና እና ሌሎች በቂ ምክንያቶች ከአገሎግሎት ውጭ ባልሆነበት ሁኔታ)፡-

  1. ያለደረኝ ግብይት በሚከናወንበት ግዜ፣
  2. ማሽን እየሰራ በህጋዊ ማኑዋል ደረሰኝ ግብይት ሲከናወን፣
  3. በሌሎች ደረሰኞች የሚደረጉ ግብይቶች፣

 

የሽ/መ/መ ስራ ላይ በሌለበት ወቅት የሚፈፀም ያለደረሰኝ ግብይት የማከናወን ወንጀል፡

የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ያልያዙ፣ለመያዝ የማይገደዱ ነገር ግን ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ታክስ ከፋዮች እና ማሽኑ ጥገና ላይ በመሆኑና በሌሎች በቂ ምክንያቶች አገልግሎት መስጠት በማይችልባቸው ግዜያት ያለደረሰኝ ግብይት የተፈፀመ እንደሆነ የወንጀል ክስ ሊቀርብ የሚገባው በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀጽ 120/1 መሠረት ነው፡፡ የአንቀጽ 120/1 ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

አንቀጽ 120/1-

"ማንኛውም ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለበት ታክስ ከፋይ ያለ ደረሰኝ ግብይት ያከናወነ እንደሆነ ከ ብር 25ሺ እስከ 50ሺ የገንዘብ መቀጮ እና ከ3 አመት እስከ 5 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል"

ከላይ እንደተገለፀው ከደረሰኝ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለበት ሰው ደረሰኝ ሳይሰጥ ግብይት ያከናወነ እንደሆነ የሚከሰስበትና የሚቀጣበት ድንጋጌ ነው፡፡

ማንኛውም የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋይ ያለደረሰኝ ግብይት ካከናወነ በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀጽ 120/1 መሠረት የወንጀል ክስ ይቀርባል፡፡

ይህ ድንጋጌ ከሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን የሚወጣውን ጨምሮ ሁሉንም አይነት ደረሰኝ የሚመለከት ነው፡፡ ሆኖም የአንቀጽ 120/1 እና 131/1(ለ) ተፋፃሚነት ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 61 አንፃር በአግባቡ መመርመር አለበት፡፡ ምንም እንኳ አንቀጽ 131 በዋናነት ከሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን የሚመለከት ቢሆንም የአንቀፁ ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) ከደረሰኝ ጋር ተያይዞ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያን የምንጠቀምበት አግባብ የሚደነግግ በመሆኑ ሁለቱ ድንጋጌዎች መቼና በምን ሁኔታ ተፈፃሚ እንደሚደረጉ መለየትና ከተደራራቢነት እና በአንቀጽ 61 ላይ ከተመለከተው ለአንድ ጥፋት አንድ ቅጣት ከሚለው የወንጀል ሕግ መሰረታዊ መርሆ አንፃር በአግባቡ መመርመር ይኖርበታል፡፡  ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 61 አንፃር ሲታይ ያለደረሰኝ ግብይት የማከናወን ተግባር ተብሎ የቀረበው ድርጊት በአንድ ድንጋጌ ስር ሊሸፈን የሚችል፣በአንድ ወንጀል የማድረግ ሀሳብ የተፈፀመ እና ድርጊቱ ተመሳሳይ ሲሆን(same action) እንደሆነ በአንቀጽ 120/1 እና በ131/1/(ለ) መሠረት በአንድ ተግባር ላይ ሁለት የወንጀል ክስ የሚቀርብበት አግባብ አይኖርም፡፡

ሌላኛው ነጥብ አንቀጽ 120/1 መቼ ነው ስራ ላይ የሚውለው የሚል ሲሆን አንቀጽ 120/1 ን ከዚህ በታች የተመለከቱት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ስራ ላይ ይውላል፡፡

አንቀጽ 120/1 ተፈፃሚ የሚሆንበት አጋባብ፡-

  1. ታክስ ከፋይ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ከመያዙ/ከመግዛቱ በፊት ያለደረሰኝ ግብይት ያከናወነ እንደሆነ፣
  2. ሌሎች በ131/1(ለ) ላይ በተመለከተው ድንጋጌ መሠረት ያለደረሰኝ ግብይት የማከናወን ወንጀል ስር የማይሸፈኑ ተግባራት ተፈፅመው ሲገኙ፣

ለምሳሌ ያክል፡- የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ጥገና ላይ እያለ ያለ ደረሰኝ (ያለ ማኑዋል ደረሰኝ)፣ባልተፈቀዱ ደሰረሰኞች ግብይት የተከናወነ እንደሆነ የወንጀል ክስ ሊቀርብ የሚገባው በዚህ ድንጋጌ መሠረት ነው፡፡

4. ያለደረሰኝ ግብይት ወንጀል ጉዳይ ላይ በተከሳሽ የሚቀርቡ መከላከያዎች

ያለደረሰኝ ግብይት ከመከናወን ወንጀል ክስ ጋር ተያይዞ በሙግት ሂደት በጠበቆችና ተከሳሾች በርካታ መከራከሪያዎች ይነሳሉ፡፡ ለአብነት ያክል፡-

  1. ግብይቱ አልተጠናቀቀም፣
  2. ስራስኪያጅ በወቅቱ በስፍራው አልነበረም፣
  3. ተገቢው የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል፣እኔ

ውክልና ተሰጧል፣

እኔ ሳልፈቅድ የተከናወነ ግብይት ነው፣

ያለደረሰኝ ግብይት እንዳያከናውኑ ሰራተኞቼን አስፈርሚያለው፣

ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሂሳብ አይክፈሉ የሚል ጽሑፍ በሚታይ ስፍራ ተለጥፏል፣

  1. ምስክሮች ወከባ ፈጥረውብኝ ነው አንጂ ደረሰኝ እቆርጥ ነበር፣
  2. የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ተበላሽቶ ነበር፣
  3. የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ጥገና ላይ ነር፣
  4. በወቅቱ መብራት ጠፍቶ ነበር፣
  5. የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ዐቃውን ከእኔ አልገዙም፣

እና ሌሎች ምክንያቶች እንደ በመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ እና በመከላከያ ይቀርባሉ፡፡

ከላይ የተመለከቱትን የክርክር ነጥቦች የሚያነሱት ግለሰብ ነጋዴዎችና የድርጅት ስራስኪያጆች ሲሆኑ እያንዳንዱ መከራከሪያዎች በአግባቡ ሳይመረመሩ ይህ መከላከያ ተገቢ ነው ሌላኛው አይደለም ለማለት አይቻልም፡፡ ግብይት አልተጠናቀቀም በሚል የሚነሳውን ክርክር ብንወስድ ያለግብይት ስለ ደረሰኝ ማውራት አይቻልም፡፡ ግብይት ያልተጠናቀቀ እንደሆነ ወይም የግብይቱ በህሪ የተቀየረ እንደሆነ ታክስ ከፋይ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ አይኖርበትም፡፡

በተከሳሽ በኩል በብዛት የሚቀርበው መከላከያ ተገቢውን የአሰራር ስርዓት ዘርግቻለው የሚለው ሲሆን የዚህ መከራከሪያ መነሻ የታክስ አስተዳደር አዋጅ አንቀጽ 132 ነው፡፡ በእርግጥ ምን አይነት ተግባራት ሲከናወኑ ነው ተገቢ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል የሚባለው የሚለው ነጥብ አስማሚ አይደልም፡፡በአንድ የሕግ ባለሙያ ተገቢ የአሰራር ስርዓት የሆነ ተግባር ለሌላኛው ባለሙያ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያክል ታክስ ከፋይ ውክልና የሰጠ በመሆኑ ብቻ ተገቢውን የአሰራር ስርዓት ዘርግቷል በሚል የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡

 ታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀጽ 132/2 ላይ እንደተመለከተው አንድ ድርጅት የወንጀል ተግባር መፈፀሙ በዐቃቤ ሕግ ተረጋግጦ እንደሆነ ስራስኪያጅ ከወንጀል ነፃ የሚሆነው፣

  • ወንጀሉ የተፈጸመው ሥራ አስኪያጁ ሳይፈቅድ ወይም ሳያውቅ ከሆነ እና
  • በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያለና ነገሮችን በጥንቃቄ የሚያይ ሰው የጥፋቱን መፈፀም ለመከላከል ይወስዳቸዋል ተብለው የሚገመቱ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ ተገቢውን ትጋት እና የአሠራር ጥበብ የተሞላበት እርምጃ ወስዶ የተገኘ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

በተመሳሳይ ስራስኪያጅ ወይም ግለሰብ ነጋዴ ከወንጀል ተጠያቂነት ነፃ የሚሆኑበትን አግባብ በተመለከተ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በወ/መ/ቁ-54061 እና በወ/መ/ቁ 48850 ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በውሳኔው ታክስ ከፋይ ከታክስ ወንጀል ነፃ ሊሆን የሚችለው ውክልና በመስጠት ብቻ ሳይሆን ውክልና ከመስጠት በተጨማሪ በአዋጅ 983/2008 አንቀጽ 132 ላይ በተመለከተው አግባብ ተገቢ የሆነ የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ እንደሆነ ብቻ ስለመሆኑና ለአስተዳደራዊ ስራ የሚሰጥ ውክልና ተገቢ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን የማያሳይ መሆኑን በመግለፅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Updates on the recent administrative procedure pro...
ፍላጎት ላጣው መራጭ ምን ይደረግ?

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - Yitagesu on Tuesday, 15 August 2023 06:40

ይህ እየሰጣቹት ያለ አገልግሎት ዋጋው ቀላል እንዳይመስላቹ በርቱልን በጣም ነው የማመሰግነው።

ይህ እየሰጣቹት ያለ አገልግሎት ዋጋው ቀላል እንዳይመስላቹ በርቱልን በጣም ነው የማመሰግነው።
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 11 September 2024