ጠበቃ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሙያን የመምረጥ መብትና ታክስ - Blog
Font size: +
4 minutes reading time (775 words)

ጠበቃ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሙያን የመምረጥ መብትና ታክስ

ይህ አጭር ጽሑፍ ጠበቆች በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የተረጋገጠላቸውን ሙያቸውን የመምረጥ መብት ከስራቸው ባህሪ አንፃር ከጥብቅና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ፣ ከንግድ ሕጉ እና ከሐምሌ 01/2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም ከፀደቀው የፌደራል ገቢ ግብር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 1395/2017 አንፃር ዳሰሳ ለማድረግና የግል ምልከታን ለማስፈር ነው፡፡ መልካም ንባብ!

በሀገራችን ኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ለሕግ የበላይነትና ፍትሕ መስፈን የፍትሕ ተቋማት ማለትም ፍ/ቤቶች፣ የዓ/ሕግ ፅ/ቤት (ፍትሕ ሚኒስቴር)፣ የፖሊስ ተቋም ዋነኛ ተዋናይና ጠበቆች ደግሞ በዚህ ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና እንዳላቸው የሚታወቅ ነው፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 41 (2) ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያውን፣ ሥራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት አለው በማለት በግልፅ ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ በማድረግ ደንግጓል፡፡ በዚህም መሰረት በርካታ የሕግ ባለሙያዎች ከዳኝነት፣ ከዓቃቤ ሕግነት፣ ከነገረፈጅነት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ መምህርነት ወደ ጥብቅና አገልግሎት ሙያ ተቀላቅለው ወይም ጎን ለጎን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

የፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 አንቀፅ 37 እና ተከታዮቹ አንቀፆች የፀና የጥብቅና ፈቃድ ያላቸው ቢያንስ ሁለት እና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች አንድ ላይ በመሆን የጥብቅና ድርጅት (LAW FIRM) ማቋቋም እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 47 (1) (ሠ) መሰረት በጥብቅና ድርጅት ውስጥ የሚሰራ ጠበቃ በግል የጥብቅና አገልግሎት መስጠት እንደማይችል ተከልክሏል፡፡

በሌላ በኩል የኢፌዲሪ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 አንቀፅ 534 (1) መሰረት ባለአንድ አባል ኃ.የተ.የግ ማህበር መመስረት እንደሚቻል እና ይህም ወደ ስራ እንደተገባ ይታወቃል፡፡ የፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጁ አንቀፅ 39 (5) የጥብቅና ድርጅት የጥብቅና ስራ መስራቱ የንግድ ወይም የኢንቨስትመንት ሥራ እንደማያሰኘው ይደነግጋል፡፡

የፌደራል ገቢ ግብር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 1395/2017 መግለጫ ተ.ቁ 4.4 አራተኛ ፓራግራፍ ላይ እንደተገለፀው በሙያ ስራ ላይ የተሰማሩ ግብር ከፋዮች አዕምሮአቸውን ተጠቅምው በአነስተኛ ወጪ ስራቸውን የሚያከናውኑ በመሆኑ እቃ ገዝተው ለሚሸጡ የተዘጋጀው በጠቅላላ ሽያጭ ላይ የተመሰረተው የማስከፈያ መጣኔ ለሙያ ስራ ተፈፃሚ እንዲሆን ማድረግ ፍትሀዊ አይሆንም፡፡ በዚህም መሰረት የሙያ ስራ የሚሰሩ የሂሳብ መዝገብ አቅርበው ግብር መክፈል እንደሚገባቸው በአዋጁ ረቂቅ (በኋላ በገንዘብ ሚ/ር በኦቪሻል ደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት የተሰራጨው) ላይ እንደተመለከተ ከደነገገ በኋላ በአንቀፅ 3 ላይ የግብር ከፋይ ደረጃዎች “ሀ” እና “ለ” እንደሆኑ በመደንገግ ዝርዝሩ አዋጁ ላይ የተመለከተ ሲሆን በተጨማሪነትም የሕግ አገልግሎት “የቴክኒክ አገልግሎት” በሚል የተካተተ ሲሆን በአዋጁ አንቀፅ 16 (አዲስ አንቀፅ 50) (2) መሰረት የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የግብር አከፋፈል በተመለከተ ግብሩ የሚጣለው እና የሚከፈለው በግብር ዓመቱ ውስጥ ከአገልግሎት ሽያጭ (የጥብቅና አገልግሎትን በተመለከተ) በሰበሰቡት ጠቅላላ የሽያጭ ገቢ ላይ ነው ይላል፡፡ አንቀፅ 16 (5) መሰረት በሕግ ሙያ የተሰማሩ ግብር ከፋዮች በዚህ አዋጅ ለደረጃ “ሀ” የሚጠየቀውን ሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 32 (10) መሰረት ኃ.የተ.የሽ.ማህበር ወይም በሙያ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሚያወጡት ወጪ ተቀናሽ የሚሆንበት ሁኔታ ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ እንደሚወሰን ያስቀምጣል፡፡

1.  የፌደራል ገቢ ግብር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 1395/2017 ጠበቆችን በተመለከተ በፊት ከነበረው አሰራር የተደረጉ ለውጦች

ጠበቃ በአዋጁ መሰረት ደረጃ “ሀ” ወይም ደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ ሆኗል፡፡ ደረጃ “ሐ” በቁርጥ ግብር የሚከፈልበት አሰራር እንዲቀር ሆኗል፡፡ ደረጃ “ሀ” ግብር ከፋይ የጠበቃ ድርጅት ወይም ግለሰብ ጠበቃ ዓመታዊ የአገልግሎት ሽያጭ ገቢው ከብር ሁለት ሚሊየን በላይ የሆነ ሰው እንደሆነ የተመለከተ በመሆኑ ግለሰብ ጠበቃ ዓመታዊ የአገልግሎት ሽያጭ ገቢው ከብር ሁለት ሚሊየን በታች ከሆነ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ ነው፡፡ አብዛኛው ጠበቃ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በአዋጁ መሰረት ማናቸውም ጠበቃ ወይም የጥብቅና ድርጅት የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ አለበት፡፡

2.  ጠበቃ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሙያን የመምረጥ መብት፣ የንግድ ሕጉና የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ፣

ጠበቆች በግለሰብ ደረጃ በፈለጉት አግባብ በግልም በጋራ ሙያቸውን በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትአንቀጥ 41 (2) መሰረት የመምረጥ ሕገ-መንግሥታዊ መብት ያላቸው በመሆኑ በፌደራል ጥብቅና ፈቃድ አስተዳደር አዋጅ አንቀፅ 37 መሰረት የተጣለው የሁለት ሰዎች ቅድመ ሁኔታ/ገደብ/ የጥብቅና ድርጅት የመክፈት ጉዳይ በንግድ ሕጉ በተፈቀደው መሰረት ባለአንድ አባል የሕግ አገልግሎት (የጥብቅና ድርጅት) በአስቸኳይ ሊፈቀድ ይገባል፡፡ ይህም በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሙያ የመምረጥ መብት ካለው አንድ ጠበቃ ብቻውን/ብቻዋን የጥብቅና ድርጅት ለማቋቋም ሲፈቀድ በንግድ ሕጉ በባለአንድ ሰው ኃ.የተ.የግ.ማህበር በተመለከተው አግባብ ይሆናል፡፡ ይህ ከተፈቀደ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ጉዳይ ከግለሰብ እና ከስራ የባንክ ሂሳብ አጠቃቀም ሂደትና ታክስ አከፋፈል ሥርዓት ላይ ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ አላስፈላጊ አለመግባባቶችን ያስቀራል፣ የግለሰቦችን ሕገ-መንግሥታዊ በፈለጉት መንገድ ሙያቸውን የመምረጥና የመስራት መብት ያረጋግጣል፡፡

3.  የመፍትሄ ሀሳብ

የፌደራል ጠበቆች ማህበር ጠበቆች ወይም የጥብቅና ድርጅቶች መብታቸው እንዲከበር እንዲሁም ግዴታቸውን እንዲወጡ የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም የፌደራል ገቢ ግብር (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 1395/2017 አተገባበር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን አስቀድሞ መፍትሄ ለመስጠት ይረዳ ዘንድ በአንድ በኩል በተ.ቁ 2 ላይ የተገለፀውን ሀሳብ ቢመለከተው፣ ቢያጤነውና የመፍትሔ እርምጃ ቢወስድ መልካም ነው ባይ ነኝ፡፡ በሌላ በኩል ማህበሩ  ከግብር ሰብሳቢው እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለ2018 የግብር በጀት ዓመት ግለሰቦች ጠበቆች የስራ የባንክ ሂሳባቸውን ወጥ በሆነ መንገድ እንዲከፍቱና እንዲያዝመዘግቡ እና ከግል የባንክ ሂሳባቸው የሚለዩበትን አሰራር እንዲበጅ ስራዎችን ቢሰራና በተረጋጋ መንፈስ የተጣለባቸው ሀላፊነት እንዲወጡ ቢደረግ፣  በፌደራል ገቢ ግብር (ማሻሻያ) አዋጁ አንቀፅ 32 (10) መሰረት ኃ.የተ.የሽ.ማህበር ወይም በሙያ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሚያወጡት ወጪ ተቀናሽ የሚሆንበት ሁኔታ ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ እንደሚወሰን በተገለፀው አግባብ ግልፅ የሆነ መመሪያ እንዲወጣ የራሱን አስተዋፅኦ ቢያደርግ፣ የሂሳብ መዝገብ በሚያዝበት ወቅት ደረሰኝ ሳይኖር (ባርኮድ ያለው የእጅ በእጅ ደረሰኝ ህትመት ተጠይቆ ያልደረሰላቸው ወይም ደረሰኝ የሌላቸውን በተመለከተ) የሂሳብ መዝገብ የሚያዝበትና የማይያዝበት አግባብና ተያያዥ ጉዳዮችን ከነሀሴ 01/2017ዓ.ም ጀምሮ የፌደራል ፍ/ቤቶች የከፊል የእረፍት ጊዜ ወቅት የፌደራል ጠበቆች ማህበር በበላይነት ሊመራው፣ ሊከታተለውና ሊያስፈፅመው የሚገባው ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በግልግል ዳኝነት የፍርድ ቤቶች ሚና
የመድህን እና የማጓጓዣ ሕግ ይርጋ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 18 November 2025