Font size: +
29 minutes reading time (5720 words)

በይርጋ የማይታገዱ የውርስ ጉዳዮች እና ከኑዛዜ ጋር የተያያዙ ይርጋዎች

ይህ ፅሑፍ “የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ መሰረተ-ሐሳቦች” ከሚለው 3ኛ ዕትም መፅሐፍ በ9ኛ ምዕራፍ ላይ የተከተበ ሲሆን በዚህ መፅሐፍ በመጀመሪያ እና በ2ኛ ዕትም ምዕራፍ 9 ተብሎ የነበረውን በአዲስ መልክ የውርስ ጉዳይ ይርጋዎችን በማዋቀር በመፅሐፉ ተሰንዷል፡፡ በምዕራፍ 9 ላይ ከተቃኙ ከ20 በላይ የሆኑ የውርስ ይርጋ ጉዳዮች መካከል ለቅምሻ ያክል በጣም ጥቂቶቹን ማለትም ሶስት ጉዳዮች ብቻ እነሆ ጀባ ብያለሁኝ፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህ ፅሑፍ መፅሐፉ በሕግ የሚጻፉ ጉዳዮችን የማጣቀሻ ሥነ-ሥርዓት (based on legal citation rule) ተከትሎ የተጻፈ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ፅሑፍ በበየነ-መርብ በሚለቀቅ በድህረ-ገፅ ላይ የሚነበብ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለአንባቢዎች ይህንን ፅሑፍ ሲያነቡ በሚመች አግባብ የማጣቀሻ ሁኔታዎች ከመፅሐፉ ከነበረው በሕግ የሚጻፉ ጉዳዮችን የማጣቀሻ ሥነ-ሥርዓት (based on legal citation rule) በተለየ መልኩ የተቀመጡ ለመሆኑ ለማሳሰብ እወዳለሁኝ፡፡

1ኛ. የውርስ ይርጋ ማቋረጫ ምክንያቶች

በፍትሐብሔር ክርክር በፍ///. 1851 እና 1853 መሰረት የይርጋ ማቋጫ የሚባሉት ባለዕዳው ዕዳውን ማመኑበፍ/ቤት ክስ ማቅረብ እና የአዘዝና ታዛዥ እንዲሁም የቤተዘመድ ግንኙነት መኖር ሲሆኑ ከዚህ ውጭ ሰዎች መብታቸውን ለማስከበር ከፍርድ ቤት የክስ ክርክር ሂደት በፊት በሽማግሌ፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በባህል፣ በአስፈጻሚው አካል፣ በህግ አውጭው አካል እንዲሁም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በተለያየ መልኩ የሚያቀርቧቸው አቤቱታዎች እና ድርድሮች የይርጋ ማቋረጫ የማይሆኑ ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡(ዝርዝሩ መፅሐፉ ላይ ይገኛል)

የይርጋ መቋረጥ ሁለት ዋና ዋና ውጤቶች አሉት፡፡ እነሱም የይርጋ ጊዜውን በአዲስ መልክ መቁጥር መጀመር እና በፍትሐብሔር ህጉ በውል ድንጋጌ ላይ 10 ዓመት የይርጋ ጊዜ  ከተቀመጠው በታች/ያነሰ የይርጋ ጊዜ ያላቸው ጉዳዮች የይርጋ ጊዜያቸው ከአጭሩ የይርጋ ጊዜ ወደ መደበኛ 10 ዓመት እንዲመጣ ማድረጉ ነው፡፡ የይርጋ መቋረጥ ውጤትን በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጣቸው ውሳኔዎች እና የተለያዩ የሕግ ምሁራን ምልከታዎች በመፅሐፉ በዝርዝር ተሰንዷል፡፡

በውርስ ይጣራልኝ ጉዳይ የይርጋ መቃዎሚያ የሚቀርብበት የሙግት ደረጃ ከሌላው የመደበኛው የፍትሐብሔር ክርክር በተለዬ ሁኔታ የሚታይበት አግባብየፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 16 በሰ//.85815 በሆኑ መዝገብ ላይ እና የውርስ ክርክር ካለው ተፈጥሯዊ ባሕሪ ማለትም ውርስ ማጣራት፣ የወራሽነት ማስረጃ መውሰድ እና የድሻ ክፍፍል ክስ የሚቀርብ በመሆኑ በውርስ ማጣራት የተነሳ ይርጋ በድጋሜ የወራሽነት ማስረጃ ለመውሰድ በቀረበ ክስ ከተነሳ ወይም በውርስ ማጣራት አለያመው የወራሽነት ማስረጃ ለመወስድ በነበረ ክርክር ይርጋው ተነስቶ ውሳኔ ከተሰጠበት በድጋሜ በድርሻ ክፍፍል የይርጋ ክርክር ከተነሳ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 10 በሰ//.40418 በሆኑ መዝገብ ላይ ከሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ላይ ለመረዳት የሚቻለው የይርጋ መቃዎሚያ በውርስ ማጣራት ተነስቶ ውድቅ ተደርጎ ብይን ከተሰጠ በኋላ በድርሻ ክፍፍል በድጋሜ የይርጋ መቃዎሚያ ከቀረበ ፍርድ ቤቱ በፍ/////.5 መሰረት በውሳኔ ያለቀ ጉዳይ በድጋሜ የቀረበ ነው በሚል ውድቅ ማድረግ ያለበት ለመሆኑ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሳሽ እና ተከሳሽ የውርስ ይጣራልኝ ክርክር ከማድረጋቸው በፊት በሃሰት በተሰጠ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ላይ የተደረገ ክርክር ተደረጎ የነበረ እና በዚህ በሃሰት የወራሽነት የምስክር ወረቀት ላይ በተደረገ ክርክር የይርጋ ጊዜ ያላነሳ ተከሳሽ በውርስ ይጣራልኝ ክርክር የይርጋ ጊዜ ቢያነሳ የይርጋ መቃዎሚያው ተቀባይነት የሌለው ለመሆኑ በቅፅ 20 በሰ//.117435 በሆነ መዝገብ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

በሀሰት በቀረበ አቤቱታ መነሻነት በተሰጠ የወራሸነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ውርስ ተጣርቶ የሟችን ንብረት በያዘ ሰዉ ላይ ተቃውሞ ቀርቦ የወራሽነት ማስረጃው ከተሰረዘ ከወራሸነት ማስረጃው በመነሣት የተሠጠ ውሳኔ ይሠረዝልኝና ትክክለኛው ወራሽ በመሆኔ ውርስ ይጣራልኝ በሚል የሚቀርብ አቤቱታ በይርጋ ሊታገድ አይገባም። በሀሰት አቤቱታ መሠረት የተሠጠው የወራሸነት ማስረጀ እንዲሠረዝ ሲደረግና የራሡን ወራሽነት ሲያረጋግጥ የይርጋ መቃወሚያ ሣይነሣ ታልፎ በሀሰት አቤቱታ የተሠጠውን የወራሽነት ማስረጃ አሰርዞና የእርሡን ወራሽነት አረጋግጦ እያለ የውርስ ማጣራት ሂደቱ ላይ በይርጋ ይታገዳል ሊባል አይገባም።

ከእነዚህ የሰበር ውሳኔዎች እና ከፍ/////.5 እና 244 አንጻር አንድ ተከሳሽ ወይም ጣልቃ-ገብ በውርስ ክርክር ጊዜ በውርስ ማጣራት ወይም በወራሽነት ማስረጃ ይሰጠን የይርጋ መቃዎሚያ በማንሳት ውድቅ ከተደረገ በኋላ በድርሻ ክፍፍል ወይም በሌላ ክርክር በድጋሜ ከቀረበ ከዚህ በፊት ውሳኔ ተሰጥቶበታል በድጋሜ የቀረበ ነው ተብሎ ውድቅ ሊደርግ ይገባል፡፡

የፌ///ቤት///ችሎ በቅፅ 21 በሰ//.132208፣ በቅፅ 11 በሰ//.47201 እና በቅፅ 11 በሰ//.47201 በሆኑ መዛግብት ከሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም መረዳት የሚቻለው የይርጋ ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው በመርህ ደረጃ የይርጋ መቃወሚያ ያነሳው ተከራካሪ ንብረቱን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን የሚከተሉት ልዩ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

1.የውርስ መነሻው የመጥፋት ውሳኔ ሲሆን

2. ክስ ያቀረበው ህጻን ሞግዚት የነበረው/ያልነበረው እና 18 ዓመት በታች የነበረ ሲሆን

3. ከሳሹ መብቱን ለመጠቀም የሚችል ለመሆኑ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን

4. ገንዘቡ በየጊዜው የሚከፈል ሲሆን

5 የውርሱ መነሻ የቀበሌ ቤት ሲሆን

6 ንብረቱን በጋራ እየተጠቀመ የነበረ ከሳሽን የሚመለከት ይርጋ ሲሆን

ተደራሲያን ሆይ ለዚህ ፅሑፍ ሲባል በአጭሩ ልዩ ሆኔታዎችን ለመጠቆም ያክል ተዘረዘሩ እንጅ ከሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እና ከምሁራን እይታ በመፅሐፉ በጥልቀት የተዳሰሱ በመሆኑ ዝርዝሩን ከመፅሐፉ ማንበብ የምትችሉ ለመሆኑ ለመጠቆም እወዳለሁኝ፡፡

የውርስን የይርጋ ጊዜ የሚያቋርጡ ምክንያቶች  

በመጨረሻም መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ለሌሎች ክርክሮች የይርጋ መቋረጫ በቂ ምክንያት የሚሆኑ እና ይርጋን ለማቋረጥ በቂ ምክንያት የማይሆኑ ጉዳዮች እንደየ ሁኔታው እና አግባብነቱ ለውርስ ክርክርም በፍ/ብ/ህ/ቁ.1677 (1) መሰረት ተፈጻሚነት ያላቸው ለመሆኑ ነው፡፡በመደበኛው የውርስ ክርክር የይርጋ መቋረጫ ምክንያቶች ለውርስ ጉዳይም የሚያገለግሉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በመፅሐፉ ውስጥ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ከሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እና ከውርስ ክርክር ተፈጥሯዊ ባሕሪ እንዲሁም በፍርድ ቤት በተግባር ከሚገጥሙ ክርክሮች በመነሳት የውርስ ይርጋን የሚያቋርጡ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

. የኑዛዜ ይፅደቅልኝ ክርክር (በቅፅ 11 በሰ//.49359 “ን” ይመልከቱ)

. የውርስ ሃብቱን ለከሳሽ ለመስጠት ማመን (በሰ//.221940 ይመልከቱ)

. የመከባበርና የመፍራት ስሜትና የቤተ-ዘመድ ግንኙነት (በሰ//.194929 ይመልከቱ)

. የውርስ ሃብቱን በግል ሆነ በጋራ ይዞ መጠቀም (በቅፅ 10 በሰ//.44025 ይመልከቱ)

. የሟች የትዳር አጋር ነኝ በሚል ከፍ/ቤት የተወሰድን የጋብቻ የምስክር ወረቅትን ለማሻር በፍ/ቤት ክርክር የወሰደው ጊዜ (በሰ//.193246 ይመልከቱ)

ውድ አንባቢያን ሆይ ለዚህ ፅሑፍ ሲባል በአጭሩ የውርስ ይርጋን የሚያቋርጡ ምክንያቶችን ለመጠቆም ያክል ተዘረዘሩ እንጅ ከሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እና ከምሁራን እይታ በመፅሐፉ በጥልቀት የተዳሰሱ በመሆኑ ዝርዝሩን ከመፅሐፉ ማንበብ የምትችሉ ለመሆኑ ለመጠቆም እወዳለሁኝ፡፡

2ኛ. በይርጋ የማይታገዱ የውርስ ጉዳዮች

1.     የድርሻ ክፍፍል ጥያቄ

ከላይ እንዳየነው በፍ///.1062 መሰረት በይርጋ የማይታገድ ወራሽነቱን በህጉ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ያረጋገጠው ወራሽ የውርስ ሀብት ክፍፍል (Partition of estate) ዳኝነት መጠየቅ ሲሆን ይህ ጉዳይ በይርጋ የማይታገድ ለመሆኑ የፌ///ቤት///ችሎ በቅፅ 10 //ቁጥር 38533 በሆነ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወራሽነቱን በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገድብ ውስጥ ያረጋገጠ ወራሽ የውርስ ሃብቱን ባያጣራም በማንኛውም ጊዜ የውርስ ሃብት የድርሻ ክፍፍል የመጠየቅ መብት ያለው ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.224889 በሆነ መዝገብ በቀን 03/02/2015 . የሚከተለው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

የፌደራል ጠቅላይ /ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 44237 ላይ በሰጠው ውሳኔ የወራሽነት መብትን በህግ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ያረጋገጡ ወራሾች የውርስ ንብረት ክፍፍል ጥያቄን በማናቸውም ጊዜ ማቅረብ የሚችሉ ስለመሆኑ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሰጠበት ነው። እንዲሁም የፌደራል ጠቅላይ /ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 34703 ላይ በሰጠው ውሳኔ የውርስ ሀብት ክፍፍልን መነሻ ያደረገ ክስ የግዴታ ውርስ ከተጣራ በኋላ መቅረብ የሌለበት ስለመሆኑ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቶበት ይገኛል። ከሳሽ ወራሽነቱን በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ከሌሎቹ ወራሾች ጋር አረጋግጦ እያለ የቀረበው ክስም የውርስ ንብረት ክፍፍል መሆኑ ከታወቀ አውራሹ ሞቶ 3 ዓመት ጊዜ ውስጥ የውርስ ንብረት አልተጣራም በሚል በቂ ባለሆነ ምክንያት ክሱን በይርጋ ውድቅ መደረጉ ተገቢነት የለዉም።

ከዚህ ላይ አንድ ነገር መረሳት የሌለበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.98517 በሆነ መዝገብ በቀን 26/01/2008 . በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የፍ///.1062 ተፈጻሚነቱ በወራሾች መካከል በሚነሳ ክርክር ብቻ ነው በማለት ወስኗል፡፡ በመሆኑም የፍ///.1062 ወራሽ እና ወራሽ ባልሆኑ ሰዎች መካከል ለሚደረግ ክርክር ተፈጻሚነት ይህ ድንጋጌ የለውም፡፡ ምክንያቱም የውርስ ሃብት የድርሻ ክፍፍል ዳኝነት የሚጠየቀው በወራሾች መካከል ለመሆኑ ከውርስ ሕጉ አጠቃላይ ይዘት እና መንፈስ መረዳት የሚቻል በመሆኑ ነው፡፡

2.      ከሕገ-ወጥ ተግባር ጋር የተገናኘ የኑዛዜ ሁኔታ

ከላይ እንዳየነው በይርጋ የማይታገድ ጉዳይን አስመልክቶ መዘጋት የሌለበት ነገር ህገ-ወጥ ውልን (unlawfull contract) አስመልክቶ የሚነሳን ክርክር ነው፡፡ ምክንያቱም የህገ-ወጥ ውል ውጤት መታወቁ ከይርጋ ጋር ያለው ግንኙነት ለውርስ ህግ፣ ለንብረት እና ሌሎችም ግዴታዎችን በፍ///.1676 (2) መሠረት ተፈጻሚነት ስለሚኖረው ነው፡፡ የፌ///ቤት///ቸሎት በቅፅ 12 በሰ//.43226 ላይ በሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም ህገ-ወጥ ውልን ለማስፈረስ የሚቀርብ ዳኝነት የይርጋ ጊዜ የለውም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል በውርስ ላይ አልፎ አልፎም ቢሆን ሊከሰት የሚችል ጉዳይ ይህ የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አግባብነቱን በምሳሌ እንመልከት፤

ምሳሌ፡ አቶ ከበደ ያየህ-ይራድ በኑዛዜው ላይ ወንድ ልጄ ዳዊት ከውርስ መካፈል የሚችለው የወንድሜን ገዳይ አቶ ቀለመ-ወርቅን በመግደል ደም ከመለሰ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ደም ካልመለሰ ከውርስ ሃብቴ እንዳይካፈል፤ ንብረቴን ሴቶቹ ልጆቼ ብቻ ይውረሱኝ በማለት ተናዘዘ እንበል፡፡

አቶ ዳዊት ከበደም አባቱ በሞቱ 2ኛው ዓመት የወራሽነቱን አስውጆ ቁጭ አለ፡፡ አባቱ በሞተ 12ኛው ዓመት እህቶቹን የወርስ ሃብት የሆነውን የአባቱን ህንፃ፣ እንዱስትሪና አክሲዮኖች እንዲያካፍሉት ሲጠይቅ እህቶቹ አቶ ዳዊት በአባታችን ኑዛዜ መሰረት የአባታችን ገዳይ የሆኑት አቶ ቀለመ-ወርቅ አሁንም በህይዎት ያሉና ወንድማችን በኑዛዜው መሰረት ደም ስላልመለሰ ወንድማችን የአባታችንን የውርስ ሃብት ሊጠይቀን አይገባም በማለት ተከራከሩ፡፡ አቶ ዳዊትም ኑዛዜው ሕገ-ወጥ በመሆኑ የኑዛዜ ይፍረስልኝ ዳኝነት ቢጠይቅ እና እህቶቹ ኑዛዜው ከተደረገ 5(አምስት) ዓመት አልፎ 12 ዓመት የሞላው በመሆኑ 5 ዓመት የይርጋ ጊዜ በይርጋ ይታገዳል በማለት መቃወሚያ በፍ//.973 በመሰረት ቢያቀርቡ ይህ የኑዛዜ ይፍረሰልኝ ኑዛዜው ከጅምሩሰው ግደልየሚል በመሆኑ ህገ-ወጥ ስለሆነ በይርጋ አይታገደም ሊባል ይገባል፡፡ ምክንያቱም የኑዛዜው ይዘት ከጀምሩ ህገ-ወጥ ነው፡፡

3.     የውርስ ሐብቱን ስመ-ሐብት በጋራ ያስመዘገበ ወራሽ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.151868 በሆነ መዝገብ በቀን 17/11/2010 . በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የውርስ ሃብት የሆነውን ንብረት ስመ-ሃብት በጋራ ያስመዘገበ ወራሽ የሚያቀርበው ክስ በይርጋ የማይታገድ ለመሆኑ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

ይርጋ ጽንሰ ሀሳብ አፈጻጸሙ የተለያየ ቢሆንም አብዛኞቹ የህግ ድንጋጌዎች የይርጋን ደንብ ተግባራዊ ያደርጋሉ። የይርጋ ደንብ የአንድ ወገን የመብት ጥያቄ በጊዜ ማለፍ ምክንያት ብቻ ቀሪ የሚያደርግበትና በአንጻሩ ደግሞ ምንም መብት የሌለውን ወገን በጊዜ ቆይታ ምክንያት መብት ሊያሰጥ የሚችል እንደሆነ የህግ አስተምርሆዎች ያስገነዝባሉ። ይህም አንደኛው የይርጋ ደንብ መብት የሚያስቀር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መብት የሚሰጥ የይርጋ ዓይነት መሆኑን ነው፡፡ በተጨማሪም የይርጋ ዋና አላማውም ዳተኛ የሆነውን ወገን መቅጫም ነው፡ ሆኖም ግን የይርጋ የሚቋረጡባቸው ምክንያቶች እንዳሉ መገንዘብ ተገቢ ነው። በተለይም የወራሽነት መብትን በህግ በተመለከተ ጊዜ ውስጥ ያረጋገጡ ወራሾች የውርስ ንብረት ክፍፍል ጥያቄን በማናቸውም ጊዜ ማቅረብ ይችላሉ። እንዲሁም የውርስ ሀብት የሆነውን በጋራ በመያዝ ወራሾች መጠቀማቸው ከተረጋገጠ የውርስ ሀብት ጥያቄ በይርጋ ሊታገድ አይችልም። የውርስ ሀብትን አስመልክቶ የሚቀርብ ክስ ላይ ተፈጻሚ የሚሆነው የይርጋ ገደብ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1851// መሰረት ሊቋረጥ የሚችልባቸው ሁኔታዎችም እንዳሉም መመልከት ይቻላል። እነዚህን ሁኔታዎች በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ//38533 44025 እና 49359 አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቶባቸዋል። ስለሆነም ወራሾች በቤቱ ላይ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በጋራ አዉጥተዉበት እያለ የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 10001677 እና 1845 ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ የሚነሳ የይርጋ ክርክር ተፈጻሚ የሚሆንበት የህግ አግባብ አይኖርም። ከዚህ በተጨማሪ የውርስ ሀብቱ በወራሾች በጋራ ባለንብረትነት ከተመዘገበ የውርስ ንብረት ክፍፍል ከሚሆን ውጪ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1000 ‹መሰረት ያደረገ የይርጋ ጥያቄ ሊነሳ አይችልም። ይህንን ከፍትሔብሔር ህግ ቁጥር 1060 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች የምንመለከተው ነው።

ይህ የሰበር ውሳኔ ከይርጋ ፅንሰ-ሐሳብ ጋር ስንመለከተው የውርስ ሃብቱ ከሟች ወደ ወራሾች ስሙ እንዲዞር ማድረጉ የውርስ ሃብቱ የወራሾች የጋራ ሃብት እንዲሆን የተደረገ በመሆኑ ከውርስ ሃብትነት ወደ ጋራ ሃብትነት የተዛወረ በመሆኑ አመክኒዮዊ ትርጉም ነው ማለት ይቻላል፡፡

4.     የወራሽነት ማስረጃ ይሰጠኝ ክስ የይርጋ ጊዜ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.236246 በሆነ መዝገብ በቀን 26/10/2015 . በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም አንድ ወራሽ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ከፍርድ ቤት ለመውሰድ ከፈለገ የይርጋ ጊዜ የሌለው ለመሆኑ “…አንድ ሰዉ የወራሽነት ማስረጃን በተወሰነ ጊዜ ዉስጥ ከፍርድ ቤት ካልወሰደ ወይም ወራሽነቱን ካላሳወጀ የመዉረስ መብት እንደሚያጣ (extinctive prescriptive) በህግ የተመለከተ ድንጋጌ የለም፡፡በማለት ወስኗል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በህንድ የውርስ ሕግ “…There is no period of limitation for an application for succession certificate” በሚል የተቀመጠ በመሆኑ በሕንድ የውርስ ሕግ የወራሽነት የምስክር ወረቀት በፍ/ቤት አሳውጆ ለመውሰድ የክስ ማቅረቢያ የጊዜ ገደብ ወይም ይርጋ የለውም፡፡

5.     በጋራ የውርስ ሃብቱን ይዞ መጠቀም

አንድ ሰው የውርስ ሃብቱን ይዞ የሚጠቀም ከሆነ ከይርጋ ፅንሰ-ሐሳብ አንጻር ክስ በሚያቀርብበት ጊዜ በይርጋ አይተገድም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.216383 በሆነ መዝገብ በቀን 28/06/2014 . በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ወራሾች በውርስ የሚገባቸን ንብረት በጋራ ይዘው ሲጠቀሙ የነበሩ ከሆነ ይህንኑ ንብረት በያዘው ሌላው ወገን ላይ የሚያቀርበው ክስ በይርጋ አይታገድም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።

6.     ሟች ሳይሞት ንብረቱን በያዘ ሰው ላይ የሚቀረብ ክስ የይርጋ ጊዜ

አንዳንድ ጊዜ ሟች በሕይዎት እያለ ቤቱን ለሰዎች በነጻ ወይም በኪራይ እንዲኖሩበት ፈቅደውላቸው እየኖሩ እያለ የቤቱ ባለቤት ሲሞቱ ወራሾቹ ቤቱን እንዲለቁ ቤቱን የያዙትን ሰዎች ሲጠየቁ ለመልቀቅ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ፡፡ ቤቱን እንደያዙ መጠቀም ይቀጥላለ፡፡ በዚህ ጊዜ ወራሾች መብታቸውን ለማስከበር በፍ/ቤት ክስ አቅርበው ቤቱን የያዙት ሰዎች ቤቱን ለቀው እንዲያስረክቧቸው ሲጠየቁ በቡቱ ላይ መብት የሌላቸው ቤቱን የያዙት ሰዎች በተከሳሽነት መልስ ይዘው ሲቀርቡ የወራሾች መብት በይርጋ የታገደ በመሆኑ ቤቱን ልንለቅ አይገባም የሚል የመጀመሪያ ደረጃ መቃዎሚያ የሆነውን የይርጋ መከራከሪያ ይዘው ሲቀርቡ በፍ/ቤቶች በተግባር ሲቀርብ ይታያል፡፡ ይህንን ዓይነት መከራከሪያ በተመለከተ አንድ ሰው የሟችን ንብረት የያዘው ከሟች ጋር በነበረው መልካም ግንኙነት ከነበር ይህ ንብረቱን የያዘ ሰው እንዲለቅ ክስ ለማቅረብ የይርጋ ጊዜ የሌለው ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.213601 በሆነ መዝገብ በቀን 28/07/2014 . የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

ክሱ የቀረበው በከሳሽ አውራሽ እና በተጠሪዎች መካከል በነበረ መልካም ግንኙነት መነሻነት በተጠሪዎቹ እጅ ገብቶ አልለቀቅ በተባለ የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለን የባለሃብት መብት ለማረጋገጥ እና ለማስመለስ የሚቀርብ የቀረበ የመፋለም ክርክር በሰ///43600 እና በሌሎች በርካታ መዛግብት ላይ በተሰጠዉ አስገዳጅ የህግ ትርጉም መሰረት በይርጋ አይታገድም።

ከዚህ ነጥብ ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ በፍርድ ቤት በተግባር የሚገጥመው ችግር የውርሱን፤ የሽያጭ፣ የስጦታ እና ሌሎችን ጉዳዮች በይርጋ እንዳይታገድ በሚል በሚመስል ሁኔታ የመፋለም ክስ በሚል ርዕስ በመስጠት ክሶች ሲቀርቡ ይስተዋላል፡፡ ይህ የሙግት አካሄድ ትክክል ላለመሆኑ እና በይርጋ መታገድ ያለባቸው ጉዳዮች መታገድ እንዳለባቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.141347 በሆነ መዝገብ በቀን 30/05/2010 . የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

ከባለቤትነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገር ግን ከመፋለም መብት ውጪ ያሉ ሌሎች ክሶች እንደሚጠየቁ መፍትሔ እና ለክሱ ምክንያት እንደሆነው ጉዳይ አይነት /ጋብቻ፣ ውርስ፣ ሽያጭ ... በሌሎች ልዩ ሕጎች የይርጋ ደንቦች የሚተዳደሩ ናቸው።

በውርስ ያገኘሁት ሀብት ያለአግባብ የተያዘብኝ ስለሆነ ይልቀቅልኝ የሚል ይዘት ያለው ክስ የመፋለም ክስ ነው በሚል ስለተገፀ ብቻ ክሱም ሆነ ክርክሩ የመፋለም ክስ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። የሟች ወራሽ ነኝ ወይም ወራሽነቴ ይረጋገጠልኝ ከሚል ጥያቄ ጀምሮ የውርስ ንብረት ያለአግባብ ተይዞብኛል በሚል የሚቀርብ ክስ ተፈፃሚነት ያለው የፍ///. 9991000 እንዲሁም 1845 ላይ የተቀመጠው የይርጋ ድንጋጌ ነው። ክርክሩ የሚካሄደው ወራሽ በሆንና ባልሆነ ሰው መካከል በመሆኑ በፍ///.1845 መሰረት ጉዳዩ 10 ዓመት የይርጋ ጊዜ የሚታገድ በመሆኑ የፍ///.1206 በመጥቀስ እንደዚህ አይነት ክስ የመፋለም ክስ በመሆኑ በይርጋ አይቋረጥም ሊባል አይገባም።

ከእነዚህ ሁለት የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለመረዳት የሚቻለው ወራሽ በሆነ እና ወራሽ ባልሆነ ሰዎች መካከል የሚደረግ ክርክር 10 ዓመት የይርጋ ጊዜ የሚታገደው የውርስ ሃብት የሆነውን ቤት ወራሽ ያልሆነው ሰው የያዘው አውርሹ ከሞተ በኋላ ወራሹ እያወቀ ሲይዘው/በእጁ ሲያስገባው ሲሆን እንጅ አውራሽ በሕይወት እያለ ወራሽ ያልሆነ ሰው የውርስ ሃብት የሆነውን ቤት ከያዘው ይህንን ቤት እንዲለቅ የሟች ወራሽ ክስ ሲያቀርብ ክሱ በይርጋ ሊታገድ የማይችል መሆኑን ነው፡፡

7.      የወራሽነት የምስክር ወረቀትን በሕጉ የጊዜ ገደብ ያረጋገጠ ከሳሽ

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አንድ ወራሽ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ሕጉ ባስቀመጠው ጊዜ ውስጥ ካረጋገጠ የሚያቀርበው የድረሻ ክፍፍል ጥያቄ በይርጋ የማይታገድ ለመሆኑ በሰ//.224889 በሆነ መዝገብ በቀን 03/02/2015 . የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

የፌዴራል ጠቅላይ /ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 44237 ላይ በሰጠው ውሳኔ የወራሽነት መብትን በህግ በተመለከተው ጊዜ ውስጥ ያረጋገጡ ወራሾች የውርስ ንብረት ክፍፍል ጥያቄን በማናቸውም ጊዜ ማቅረብ የሚችሉ ስለመሆኑ አስገዳጅ የህግ ትርጉም የሰጠበት ነው። እንዲሁም የፌደራል ጠቅላይ /ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 34703 ላይ በሰጠው ውሳኔ የውርስ ሀብት ክፍፍልን መነሻ ያደረገ ክስ የግዴታ ውርስ ከተጣራ በኋላ መቅረብ የሌለበት ስለመሆኑ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቶበት ይገኛል። ከሳሽ ወራሽነቱን በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ከሌሎቹ ወራሾች ጋር አረጋግጦ እያለ የቀረበው ክስም የውርስ ንብረት ክፍፍል መሆኑ ከታወቀ አውራሹ ሞቶ 3 ዓመት ጊዜ ውስጥ የውርስ ንብረት አልተጣራም በሚል በቂ ባለሆነ ምክንያት ክሱን በይርጋ ውድቅ ተገቢነት የለዉም።

አንድ ወራሽ ሕጉ ባስቀመጠው መሰረት የወራሽነቱን የምስክር ወረቀት ማውጣት ያለበት በስንት ጊዜ ውስጥ ነው የሚለውን በተመለከት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.205248 በሆነ መዝገብ በቀን 25/05/2014 . የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

ወራሾች ሟች በሞቱ በሶስት ዓመት ዉስጥ ወራሽነታቸውን በፍ/ቤት ካስወሰኑ በፍ///.1000(1) በተቀመጠው የግዜ ገደብ ውስጥ ወራሽነታቸውን ማረጋገጣቸውን የሚያስገነዝብ ነው። የፌ///ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ.. 44237 (ቅጽ 10) 20/7/02. አመልካቹ የሟች ወራሽነቱን በህጉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ አረጋግጦ ከቆየ በኋላ የውርስ ንብረቱን የክፍፍል ጥያቄ ማቅረቡ በፍ/// 1000(1) እና (2) ስር በተመለከተው የይርጋ ድንጋጌ የሚታገድ ሳይሆን በፍ/// 1062 ድንጋጌ መሰረት በማናቸውም ግዜ የሚቀርብ መሆኑን በሰጠው ውሳኔ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ሰጥቷል። ስለሆነም ሟች ከሞተ ከሶስት አመት በፊት ወራሽነቱን ያስወሰነ ሰዉ ዉርስ ይጣራልኝ በሚል የሚያቀርበዉ አቤቱታ ክስ በይርጋ አይታገድም።

አንድ ወራሽ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ሟች ከሞተ ጀምሮ 3 ዓመት ጊዜ ውስጥ የወራሽነት ከወሰደ ይህ ወራሽ በማንኛውም ጊዜ የውርስ ይጣራልኝ ሆነ በቀጥታ የድርሻ ክፍፍል ክስ የማቅርብ መብት ያለው ሲሆን ይህ መብቱ በይርጋ የማይታገድ ለመሆኑ ከዚህ የሰበር ውሳኔ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ ነጥብ ጋር በተያያዘ ከላይ በዚህ መፅሐፍ በዚህ ምዕራፍ ላይ እንደተቀመጠው የፌዴራል ጠቅላይ /ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.236246 በቀን 26/10/2015 . በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ልክ እንደ ህንድ ሀገር የውርስ ሕግ በኢትዮጵያ የውርስ ሕግም የወራሽነት የምስክር ወረቀት ክፍ/ቤት አሳውጆ ለመውሰድ የይርጋ ጊዜ የለውም ማለት የውርስ ሃብቱን ሳይዝ አውራሹ መሞቱን እያወቀ 3 ዓመት በኋላ የወራሽነት ከፍ/ቤት ወስዶ የውርስ ሃብቱን ሲጠይቅ የውርስ ሃብቱን የያዘው ወራሽ በፍ///.1000(1) መሰረት 3 ዓመት የይርጋ መቃዎሚያ ካቀረበ የዚህ ወራሽ መብት በይርጋ የሚታገድ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ነጥባ ጋር ሊነሳ እና ሊረሳ የማይገባው ጉዳይ ልክ እንደ ህንድ ሀገር የውርስ ሕግ በኢትዮጵያ የውርስ ሕግም የወራሽነት የምስክር ወረቀት ክፍ/ቤት አሳውጆ ለመውሰድ የይርጋ ጊዜ የለውም የተባለው መብት ገላጭ የሆነውን የወራሽነት የምስክር ወረቀት ለመውስድ እንጅ 3 ዓመት በኋላ የወራሽነት ያሳወጅ ወራሽ በዚህ የወራሽነት የምስክር ወረቀት መብቱን ለመጠቀም እንደ ክርክሩ እና እንደተከራካሪው ዓይነት፣ እንዲሁም ሌሎችን ሁኔታዎች መሰረት በማድረግ የውርስ ሃብቱን የሚያገኝበት መብቱ በይርጋ ታግዶ ከሆነ በማንኛውም ጊዜ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ወራሹ የመውሰድ መብት አለው ማለት መብቱ በይርጋ አያግደውም ማለት አለመሆኑን ነው፡፡

8.     በሀሰት የተሰጠን የወራሽነት የምስክር ወረቅ ማሰረዝ

የፌ///ቤት///ችት በሰጠው አስገዳጅ ውሳነ በሀሰት የተገኘ የወራሽነት ማስረጃ ይሰረዝልኝ ጥያቄ ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ጊዜ በፍ///. 16771845 እና 1846 መሰረት 10 ዓመት ለመሆኑ የወሰን ሲሆን ከእነ ምክንያን እንደሚከተለው ያብራራል -

የፍ///ቁጥር 1000 ድንጋጌ ተፈፃሚነት የሚኖረው አንድ እውነተኛ የሆነ ወራሽ ትክክለኛው ወራሽ መሆኑ ታውቆለት ዋጋ ያለው የወራሽነት ማስረጃ ሳይኖረው የውርሱን ንብረት በእጁ ያደረገው ሰው የውርሱን ንብረት እንዲሆንለት ክስ በሚያቀርብበት ጊዚ ስለመሆኑ የድንጋጌው ይዘት በግልጽ ያሳያል፡፡ ነገር ግን በተያዘው ጉዳይ የተጠሪ ክስ የሟች አቶ አየለ ግዛው የውርስ ንብረት በአሁኑ አመልካች ስለተያዘ ይለቀቅልኝ የሚል ይዘት የሌለው ሲሆን በአመልካች ላይ የፍርድ መቃወሚያ አቤቱታ የቀረበው አመልካች ከሟች አቶ አየለ ግዛው ጋር ምንም ዓይነት የተወላጅነት ግንኙነት ሳይኖራቸው አመልካች የሟቹ ልጅ ነኝ በማለት የወሰደት የወራሽነት ማስረጃ ይሰረዝልኝ የሚል መሆኑን የክርክሩ ሂደት በግልጽ  ያሳያል፡፡ በመሆኑም የፍ///ቁጥር 1000 ድንጋጌ ለዚህ ጉዲይ ተፈፃሚ ሊደረግ የሚችልበት የህግ አግባብ የለውም፡፡

ሰበሩ በዚህ መዝገብ ላይ የፍ///.1000 ተፋፃሚነት ከሌለው እና ለተያዘው ጉዳይ የውርስ ህጉ የይርጋ ጊዜ ያላስቀመጠ ስለሆነ በምን አግባብ እልባት ሊሰጠው ይገባል የሚለውን በሚከተለው የህግ ትርጉም መሰረት እልባ ሰጥቶታል -

የውርስ ህጉ በዚህ ረገድ ክፍተት ካለበት ወደ ጠቅላላው ህግ በመሄድ ለጉዳዩ እልባት መስጠት በህግ አተረጓጎም መርህ /principles of legal interpretation/ የተፈቀደ ነው፡፡ በዘሁ መሠረትም ጉዳዩን በፍትሐብሔር ህጉ ጠቅላላ  ስለውሎች ከተደነገገው አንፃር መመልከት የግዴ ይላል፡፡ በዚህ ክፍልም ግዴታዎች ከውሉ የተገኙ ባይሆንም በውል ህግ ላይ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት እንዳሏቸው በቁጥር 1677/1/ ላይ ተመልክተዋል፡፡ በውል ህግ ደግሞ ዋናው የይርጋ ድንጋጌ በቁጥር 1845 ሊይ የተመለከተው 10 ዓመት የይርጋ ጊዜ ነው፡፡ የይርጋ አቆጣጣር ጊዜ መነሻ ሊሆን የሚችለው ጊዜም በፍ///ቁጥር 1846 ድንጋጌ አግባብ ሊታይ የሚችል ነው፡፡

በሌላ በኩል የሃሰት የወራሽነት ማስረጃን እውነተኛ ወራሽ ካሰረዘ በኋላ የውርስ ማጣራት ሙግት ሲጀምር የሚቀርብ የይርጋ መቃዎሚያ ተቀባይነት የሌለው ለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 20 በሰ//.117435 በሆነ መዝገብ ላይ ተከታዩን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

በሀሰት በቀረበ አቤቱታ መነሻነት በተሰጠ የወራሸነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ውርስ ተጣርቶ የሟችን ንብረት በያዘ ሰዉ ላይ ተቃውሞ ቀርቦ የወራሽነት ማስረጃው ከተሰረዘ ከወራሸነት ማስረጃው በመነሣት የተሠጠ ውሳኔ ይሠረዝልኝና ትክክለኛው ወራሽ በመሆኔ ውርስ ይጣራልኝ በሚል የሚቀርብ አቤቱታ በይርጋ ሊታገድ አይገባም። በሀሰት አቤቱታ መሠረት የተሠጠው የወራሸነት ማስረጀ እንዲሠረዝ ሲደረግና የራሡን ወራሽነት ሲያረጋግጥ የይርጋ መቃወሚያ ሣይነሣ ታልፎ በሀሰት አቤቱታ የተሠጠውን የወራሽነት ማስረጃ አሰርዞና የእርሡን ወራሽነት አረጋግጦ እያለ የውርስ ማጣራት ሂደቱ ላይ በይርጋ ይታገዳል ሊባል አይገባም።

  3ኛ. የኑዛዜ ይፍረስልኝ ጥያቄ የይርጋ ጊዜ

አንድ ኑዛዜ በሟች ተደርጎ በዚህ ኑዛዜ ላይ ተጎጂ የሆነ አካል የኑዛዜው ይፍረስልኝ ዳኝነት የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ኑዛዜ ይፍረስልኝ የሚለው አካል ደግሞ ኑዛዜው ሲፈስና ሲነበብ የነበረ ወይም ያልነበረ አካል ሊሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ የውርስ ህግም ይህንን ታሳቢ በማድረግ ኑዛዜው ሲነበብ ለነበሩ አካላትና ኑዛዜው ሲነበቡ ላልነበሩት አካላት ሁለት የተለያዬ የይርጋ ጊዜያትን አስቀምጧል፡፡

1.      ኑዛዜ ሲነበብ የነበሩ ሰዎች

ኑዛዜው ሲነበብ ራሳቸው ወይም ወኪሎቻቸው የነበሩ ሰዎች የተደረገው ኑዛዜ ሊፀና አይገባም የሚሉ ከሆነ ይህንን አቋማቸውን በጽሁፍ በማድረግ ኑዛዜው ከተነበበት ጊዜ አንስቶ 15 (አስራ አምስት) ቀን ውስጥ መግለጫ ለውርስ አጣሪው ወይም የውርሱን ጉዳይ ለሚሸመግሉ የሽማግሌ ዳኞች ወይም ለፍ/ቤቱ ማቅረብ ያለባቸው ሲሆን ከዚህ መግለጫውን ከሰጡበት ቀን አንስቶ 3 (በሶስት) ወር ውስጥ ኑዛዜው ይፍረስልኝ የሚል ክስ ለፍ/ቤቱ ወይም ለሽማግሌዎች ካላቀረቡ ኑዛዜ እንዲፈርስ የመጠየቅ መብታቸው በይርጋ ይታገዳል በማለት በፍ///.973 ላይ ተደንግጓል፡፡

ከዚህ ድንጋጌ ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው ኑዛዜው ይፍረስልኝ የሚለው አካል ኑዛዜው ሲነበብ መብቱን የሚጎዳው ወይም የሚጠቀም መሆኑን ይረዳል ተብሎ ስለሚገመት መጀመሪያ ኑዛዜውን የሚቃዎም ለመሆኑ አቤቱታ 15 ቀን ውስጥ ከቀረበ በኋላ 3 ወር ውስጥ የዳኝነት ከፍሎ ኑዛዜው ይፍረስልኝ በማለት ክስ ያቀርባል፡፡

ከፍ///. 973 ላይ የሚከተሉትን 3 ነገሮች የድንጋጌውን ሶስቱን ንዑስ አንቀፆች አጣምሮ በማንበብ ለመረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህም፡-

1. ኑዛዜን ለመቃዎም የሚቀርብ መግለጫ (Declaratoin) እና ኑዛዜ እንዲፈርስ የሚቀርብ ክስ (Application for nullification) የተለያዩ ናቸው፡፡ ልዩነታቸውም የመቃዎሚያ መግለጫ (declaration) ማለት ኑዛዜው ሲነበብ ኑዛዜው ህጋዊ ባለመሆኑ የሚፀና አይደለም በማለት ኑዛዜውን የማይቀበለው ለመሆኑ ሀሳቡን የሚያሳውቅበት ሲሆን ኑዛዜ እንዲፈርስ የሚቀርብ ክስ ግን ያው መደበኛ ክስ (suit) ይሆናል፡፡

2. ኑዛዜውን የማይቀበለው/የሚቃዎመው ለመሆኑ ሀሳቡን ለመግለጽ (መግለጫ መስጠት) በጽሁፍ አድርጎ ለውርስ አጣሪ ወይም ለሽማግሌዎች ወይም ለፍ/ቤት ማቅረብ የሚችል ሲሆን በሌላ በኩል ኑዛዜው ይፍረስልኝ የሚል ክስ የሚያቀርበው ለፍ/ቤት ወይም ለሽማግሌዎች ብቻ እንጂ ለውርስ አጣሪ ማቅረብ አይችልም፡፡ ከዚህ ላይ 15 ቀን ይርጋው ኑዛዜው የሚቃዎመው ሰው ለውርስ አጣሪ ወይም ለሽማግሌ ወይም ለፍ/ቤት በጽሁፍ ያቀርባል፡፡ 3 ወሩ የይርጋ ጊዜ የሚያገለግለው ክሱ ለፍ/ቤት ወይም ለሽማግሌ  ሲያቀርብ ብቻ ነው፡፡

3. ኑዛዜን ይፍረስልኝ በማለት ዳኝነት ለመጠየቅ በመጀመሪያ ኑዛዜውን የሚቃዎመው ለመሆኑ ሀሳቡን (Declaration) ለውርስ አጣሪ ወይም ለፍ/ቤት ወይም ለሽማግሌ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ምክንያቱም የፍ///.973 (3) “…መግለጫው ከተሰጠበት ቀን አንስቶ እስከ 3 ወር ክሱንካላቀረበ በቀር የመጠየቅ መብቱን ያጣልበማለት የደነገገ በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ላይ መነሳት ያለበት ነጥብ ኑዛዜውን የሚቃዎም ሰው ጧት ኑዛዜው እንደተነበበለት ከሰዓት ወይም በአዳሪ ለፍ/ቤቱ የኑዛዜ ይፍረስልኝ ክስ  ቢያቀረብ መጀመሪያ ኑዛዜውን የሚቃዎም ለመሆኑ የሀሳብ መግለጫ አላቀረበም በማለት ተከሳሹ ቢቃዋዎም /ቤቱ ይህንን ተቃዎሞ ሊቀበለው ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ነጥብ ነው፡፡ እንደዚህ ጸሃፊ የሀሳብ መስጫ ማቅረብ የኑዛዜ ይፍረስልኝ ዳኝነት ለመጠየቅ ቅድመ ሁኔታ/መስፈር ነው ብሎ አያምንም፡፡ ስለሆነም አንድ ኑዛዜን የሚቃዎም ተከራካሪ ኑዛዜው ከተነበበት 15 ቀን በፊት የኑዛዜ ይፍረስልኝ ክስ ካቀረበ መብቱ በይርጋ አይታገድም መግለጫ መስጠትም አይጠበቅበትም፡፡ በሌላ በኩል ኑዛዜውን የሚቃዎም ለመሆኑ 15 ቀን ውስጥ ሀሳቡን ሳይገልፅ 15 ቀኑ ካለፈ በኋላ ነገር ግን 3 ወር ሳይሞላው በመቀጥታ የኑዛዜ ይፍረስለኝ ዳኝነት ቢያቀርብና ተከሳሹ 15 ቀን ውስጥ ኑዛዜውን የሚቃዎም ለመሆኑ የሀሳብ መግለጫ ስላልተሰጠ ኑዛዜው ይፍረስልኝ ብሎ የመጠየቅ መብቱ በይርጋ ታግዷል በማለት ከጠየቀ የተከሳሽ ክርክር ተገቢነት ያለው በመሆኑ የከሳሽ መብት በይርጋ የሚታገድ ይሆናል፡፡

የፌ///ቤት///ችሎት ኑዛዜው ሲነበብ የነበረና የኑዛዜውን ይዘት የተረዳ ሰው መግለጫ የማቅርብ ግዴታ ያለበት ለመሆኑና የኑዛዜውን ይዘት ያልተረዳ ሰው ግን መግለጫ የማቅረብ ግዴታ የሌለበት ለመሆኑ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

ኑዛዜ መኖሩን ማወቅና የኑዛዜውን ሙሉ ይዘት ማወቅ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡በፍ///. 973 (1) የተመለከተው 15 ቀን የጊዜ ገደብ የክስ ማቅረቢያ ጊዜ ሳይሆን የመግለጫ ማቅረቢያ ጊዜ ነው፡፡ በኑዛዜው የተሰየሙት አጣሪ ናቸው የተባሉት የአሁኗ 3 አመልካች ስለ ንብረት ድልድሉ ለአሁን ተጠሪዎች ያሳውቁት  ነገር አለመኖሩን ይግባኝ /ቤት አረጋግጧል፡፡ ተጠሪዎች የንብረት ድልድሉን እንዲያውቁ አልተደረጉም ከተባለ ደግሞ መግለጫ የማቅረብ ግዴታ አይኖርባቸውም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ግዴታ ከሌለባቸው ደግሞ ጊዜው መቆጠር የሚጀምረው ተጠሪዎች በኑዛዜው የተደረገውን የንብረት ድልድል ማወቃቸው ከተገለፀበት…. ጀምሮ የመቃወም አቤቱታ በፍ///. 973 (3) በተመለከተው አነስተኛው የሶስት ወር የይርጋ ዘመን እንኳ የይርጋ ጊዜ ያለፈበት ሆኖ አልተገኘም ፡፡

2.     ኑዛዜው ሲነበብ ያልነበሩ ወራሾች

የሟች ኑዛዜ ሲፈስ ያልነበሩ/ያልተወከሉ ተከራካሪዎች የይርጋ ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው ውርስ አጣሪው ኑዛዜው ተከፍቶ ሲነበብ ያልነበሩ ሰዎችን የንብረት ክፍፍሉን/አመዳደቡን አስመልክቶ ያዘጋጀውን ዕቅድ ለእነዚህ ኑዛዜው ሲነበብ ላልነበሩ (ላልተወከሉ) ሰዎች ሲነግራቸው ከዚህ ከተነገራቸው ቀን አንስቶ ሲሆን ኑዛዜውን የሚቃዎሙት ከሆነ መግለጫቸውን 15 ቀን ውስጥ ለውርስ አጣሪ ወይም ለፍ/ቤት ወይም ለሽማግሌዎች ማቅረብ ያለባቸው ሲሆን ኑዛዜው ይፍረስልኝ የሚለውን ክስ ደግሞ ለፍ/ቤት ከዚህ መግለጫ ከሰጡበት ቀን አንስተው 3 (ሶስት) ወር ጊዜ ማቅረብ ያለባቸው ሲሆን 3 ወር ጊዜ ኑዛዜው የማይፀና በመሆኑ ይፍረስልኝ በማለት ክስ ካላቀረቡ በይርጋ የሚታገዱ ይሆናል ፡፡

ኑዛዜው ሲነበብ የነበሩ (የተወከሉ) ሆነ ያልነበሩ (ያልተወከሉ) ሰዎች የሟች ኑዛዜ ከፈሰሰበት ቀን አንስቶ 5 (አምስት) ዓመት በኋላ ወይም ሟች ኑዛዜ ያልነበረው ከሆነ ሟች ከሞተበት ቀን አንስቶ 5 (አምስት) ዓመት በኋላ ስለ ኑዛዜ መጽናት ወይ አለመጽናት ሆነ ውርስ አጣሪው በአቀረበው የንብረት ድልድል (ክፍፍል) ሃሳብ ላይ በማንኛውም ሁኔታ በይርጋ የሚታገድ በመሆኑ ክስ ማቅረብ አይችሉም ፡፡

ከዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ነጥብ ኑዛዜ ሲነበብ የነበሩ (የተወከሉ) ሆነ (ያልነበሩ) ያልተወከሉ ሰዎች ኑዛዜውን በተመለከተ ክስ ለማቅረብ ኑዛዜውን የሚቃዎሙት ለመሆኑ መግለጫ የመስጠት ግዴታ 15 ቀን ውስጥ ያለባቸው እና 3 ወር ጊዜ ውስጥ ክሱን ካላቀረቡ በይርጋ የሚታገድ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ኑዛዜው ሲነበብ የነበሩ እና ያልነበሩ ሰዎች በይርጋ ላይ የሚኖረው ልዩነት የይርጋ መቆጠር የሚጀምርበት ጊዜ ላይ ነው፡፡ ሲነበብ የነበሩ ሰዎች የይርጋ መቁጠሪያው ጊዜ የሚጀምረው ኑዛዜው ከተነበበት ቀን አንስቶ ሲሆን ኑዛዜውን ሲነበብ ያልነበሩ ሰዎች የይርጋ መቆጠሪያው ጊዜ የሚጀምረው ግን ውርስ አጣሪው ለእነዚህ ኑዛዜ ሲነበብ ያልነበሩ ሰዎችን አግኝቷቸው የውርስ ሃብት ክፍፍል/ድልድል በተመለከተ ያዘጋጀውን እቅዱን  ከነገረበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡

ስለሆነም ውርስ አጣሪው ኑዛዜው ከተነበበ በኋላ 3ኛው ዓመት አግኝቶ ኑዛዜው ሲነበብ ላልነበሩ ሰዎች ቢነግራቸው ይርጋ መቆጠር የሚጀምረው ከዚህ 3 ዓመታት በኋላ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ውርስ አጣሪው እነዚህን ኑዛዜ ሲነበብ ያልነበሩ ሰዎችን ሳያገኛቸው ውርሱን አጣርቶ በፍ/ቤት በኑዛዜው መሰረት የድርሻ ክፍፍል አድርጎ /ቤቱም የውርስ አጣሪ ሪፖርቱን ቢያጽድቀውም እነዚህ ኑዛዜው ሲነበብ ያልነበሩ ሰዎች ኑዛዜው ከተነበበት ጀምሮ እስከ 5 (አምስት) ዓመት ድረስ ኑዛዜው ይፍረስልኝ በማለት ወይም በኑዛዜው ላይ ያላቸውን ሌላ ማንኛውም ተቃዎሞ የማቅረብ መብት ያላቸው ሲሆን 5 ዓመት በኋላ ግን በይርጋ ይታገዳል፡፡

ከዚህ ላይ አንድ ነገር መረሳት የሌለበት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 11 በሰ//.53223 በሆነ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የፍ/// 973 እና 974 የተፈጻሚነት ወሰን ወራሽ ነኝ ኑዛዜ ሲነበብ አልነበርሁም ወይም አልሰማሁም የሚሉ ወራሾች የሚያነሱትን መቃወሚያ አቀራረብና የጊዜ ገደብ የሚመለከት እንጂ ወራሽ ያልሆነ ሰው ስለ ኑዛዜው የሚቃወምበትን የጊዜ ገደብ የሚመለከት አለመሆኑን ነው።

3. በመንፈስ ጫና የተደረገ ኑዛዜ እንዲፈርስ/እንዲቀነስ የመጠየቂያ የይርጋ ጊዜ

ሟች ኑዛዜውን በመንፈስ ጫና ለሞግዚት (አስተዳዳሪ) ለሃኪም፣ ለመንፈሳዊ አባት፣ ለውል አዋዋይ፣ በኑዛዜው ላይ ለተጠቀሱት ምስክሮች፣ ለባሏ/ለሚስቱ፣ ለተወላጅ ወይም ለወላጅ ካደረገ /ቤቶች የኑዛዜውን ስጦታ አቤቱታ ሲቀርብለት የመቀነስ ስልጣን ያለው ለመሆኑ በምዕራፍ 5 ላይ በዝርዝር አይተናል፡፡ የኑዛዜው ስጦታ በመንፈስ ጫና የተደረገ በመሆኑ ይቀነስልኝና ይሻርልኝ በማለት ዳኝነት የሚጠይቅ ከሆነ ኑዛዜው እንዲፈጸምለት ጥያቄውን ካቀረበበት አንስቶ 3 (ሶስት) ወር ጊዜ ውስጥ ዳኝነቱን ካልጠየቀ በይርጋ መብቱ የሚታገድ ለመሆኑ በፍ///. 874 (3) ተደንግጓል፡፡

ከዚህ ላይ የኑዛዜው ይቀነስልኝ (ይሻርልኝ) የይርጋ ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው ኑዛዜው እንዲፈጸምለት ከጠየቀበት ጀምሮ /from the application for the execution of will) የሚለው አቤቱታ አቅራቢው ውርስ ለማጣራት ክስ ያቀረበበት ጊዜ ነው ወይስ የድርሻ ክፍፍል ያቀረበውን ክስ ወይስ ለአፈጻጸም የአቀረበውን ክስ ነው መነሻ አድርገን የምንወስደው የሚለውን የትኛው እንደሆነ መለየት አለበት፡፡ እንደዚህ ጸሐፊ አረዳድ አቤቱታ አቅርበው በፍ/ቤት ለውርስ ማጣራት ክስ ካቀረበ እና በእጁ ኑዛዜ ካለና በኑዛዜው መሰረት የውርስ ማጣራቱን ካቀረበ ይርጋው መቆጠር ያለበት ውርሱን ለማጣራት ያቀረበው ክስ ነው እንጂ ለድርሻ ክፍፍል ወይም የአፈጻጸም ክስ እስኪያቀርብ የሚጠበቅ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም በኑዛዜው ላይ እውቅና ያለው በመሆኑ ተቃዎሞውን ለማቅረብ እድሉን አግኝቷል፡፡

በሌላ በኩል በመንፈስ ጫና የተደረገ ኑዛዜ ከውርስ የሚነቅል በመሆኑ ኑዛዜው እንዲቀንስልኝ የሚል ክስ የይርጋውን ጊዜ በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.231510 በሆነ መዝገብ በቀን 30/09/2015 . የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ተሰጥቷል፡-

በኑዛዜ ከውርስ ተነቅያለሁ የሚል ወራሽ ኑዛዜ እንዲፈርስ በፍ//ቁጥር 1123/3 መሰረት በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 152134 (በቅጽ 23 የታተመ) በየትኛውም ደረጃ ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠበት ጉዳይ ነው። በዚህ መሰረት ሟች በኑዛዜ ተጠቃሚዎችች ከፍተኛ የመንፈስ ጫና ተደርጎባቸው ያደረጉት ኑዛዜ ከውርስ የነቀለ በመሆኑ ህጋዊ ውጤት ሊኖረው አይገባም ለሚል ክስ ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ጊዜ በፍ//ቁጥር 1123/3 የተመለከተው 10 ዓመት የይርጋ ጊዜ ነዉ።  (አንክሮ እና ማጥቆር የፀሐፊው ነው)

3.     በሃይል የተደረገ ኑዛዜን የማፍረሻ የይርጋ ጊዜ   

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.228208 በሆነ መዝገብ በቀን 26/03/2015 . በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ኑዛዜው በኃይል ተደርጓል በሚል ምክንያት ኑዛዜ እንዲፈርስ ክስ ሊቀርብ የይርጋው ጊዜን በተመለከተ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡-

//ቁጥር 973 እና 974 ከላይ እንደተመለከተው በወራሾች መካከል ኑዛዜ እንዲፈርስ የሚጠየቅበትን የጊዜ ገደብ የሚመለከት ከመሆኑም በተጨማሪ ከኃይል ተግባር ውጪ በሌላ በማንኛውም ህጋዊ ምክንያት ኑዛዜ እንዲፈርስ የሚቀርብ ክስ በእነዚህ ድንጋጌዎች በተመለከተው የጊዜ ገደብ ውስጥ መሆኑን አመላካች ነው። ኑዛዜው እንዲፈርስ የሚጠየቀው የኃይል ድርጊት ተፈጽሟል በሚል ምክንያት ከሆነ ግን የፍ//ቁጥር 867/2 ወደ //ቁጥር 1810 የሚመራ በመሆኑ በዚህ ድንጋጌ የተመለከተው 2 ዓመት የይርጋ ጊዜ ተፈጻሚ ይሆናል። በሌላ አባባል በፍ//ቁጥር 1810 ላይ የተመለከተው በኃይል ድርጊት ምክንያት ኑዛዜ እንዲፈርስ የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ጊዜ የፍ//ቁጥር 973 እና 974 ልዩ ድንጋጌ(exception) ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በኃይል የተደረገ ኑዛዜ እንዲፈርስ ክስ የማቅረቢያ ጊዜ በፍ//ቁጥር 974/2 ከተመለከተው 5 አመት የይርጋ ጊዜ እንዲያንስ የተፈለገበት ምክንያትም በተናዛዡ ላይ የኃይል ድርጊት መፈጸሙን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ጊዜ በቆየ ቁጥር እየጠፉ ሊሄዱ ስለሚችሉ ማስረጃዎች ሊገኙ በሚችሉበ ጊዜ ውስጥ ክሱ እንዲቀርብ ለማስቻል እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም በማስፈራራት ወይም በኃይል ድርጊት ተፈጽሟል የተባለ ኑዛዜ እንዲፈርስ ክስ ማቅረብ የሚቻለው በተናዛዡ ላይ የኃይል ድርጊቱ ከቀረበት በሁለት አመት ውስጥ ወይም ሟች ሲሞት የኃይል ድርጊቱ ቀሪ የሚሆን በመሆኑ ሟች ከሞተበት ጀምሮ በሚቆጠር 2 ዓመት ውስጥ ሲሆን በሁለት ዓመት ውስጥ ክሱ ካልቀረበ በይርጋ የሚታገድ ይሆናል።

ሰበሩ በዚህ መዝገብ ላይ በመጨረሻም ኑዛዜው በኃይል ተደርጓል በሚል ምክንያት ኑዛዜ እንዲፈርስ ክስ ሊቀርብ የይርጋው ጊዜን ሁለት ዓመት ለመሆኑ እንደሚከተለው ይደመድማል፡-

ስለሆነም የፍ//ቁጥር 973 እና 974 ድንጋጌዎች የሟች ወራሽ የሆነ ወገን ኑዛዜን የሚቃወምበት የይርጋ ድንጋጌ እንጂ ወራሽ ያልሆነ ከሳሽ መቃወሚያ የሚያቀርብበት አይደለም። ኑዛዜው በኃይል ተደርጓል በሚል ምክንያት ኑዛዜ እንዲፈርስ ክስ ሊቀርብ የሚችለው በፍ//ቁጥር 1810/1 መሰረት የሀይል ድርጊቱ ከቀረበት ጊዜ ጀምሮ 2 ዓመት ውስጥ ነው።

4.     ከውርስ የተነቀለ ሰው የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ጊዜ

ከላይ በሰፊው እንዳየነው አንድ ወራሽ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከውርስ ሊነቀል ይችላል፡፡ ከውርስ የተነቀለው ሰው ደግሞ በፍርድ ቤት ከውርስ እንዲነቀል በሟች የተደረገውን ኑዛዜ ለማስፈረስ ክስ ያቀርባል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከውርስ በመንቀል የተደረገው ኑዛዜ እንዲፈረስ የመቀርብ ክስ የይርጋውን ጊዜ በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በተለያዩ መዛግብት አስገዳጅ የሕግ ጥርጉም የሰጠ ሲሆን ሰበሩ በሰ//.147662 በሆነ መዝገብ በቀን 28/09/2010 . የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል፡-

በፍ///ቁጥር 973 እና 974 ድንጋጌዎች የተመለከተውን የተለያየ የይርጋ ጊዜ የተፈጻሚነት ወሰን በተመለከተ ሰበር ሰሚ ችሎት እነዚህን ድንጋጌዎች አግባብነት ካላቸው ውርስን ከሚመለከቱ የፍትሐብሔር ሕጉ ሌሎች ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ በመተርጎም የፍ//.973 እና 974 ድንጋጌዎች ተናዛዡ ካደረገው የውርስ ሀብት ድልድል ጋር ተያይዞ የሟች ወራሾች ኑዛዜው አይጸናም የሚሉባቸውን ምክንያቶች መሰረት በማድረግ ተቃውሞ ለማቅረብ የሚችሉበትን የጊዜ ገደብ የሚያመለክቱ እንጂ በቁጥር 938 እና 939 ድንጋጌዎች ጥበቃ የተደረገለትን ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ከውርስ ያለመነቀል መብት፣ኑዛዜው የተደረገበት ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል የተናዛዡ አለመሆኑን እና መሰል መብቶችን መሰረት በማድረግ ኑዛዜው እንዲፈርስ ወይም እንዲቀነስ በሚቀርቡ ክሶች ጉዳይ ተፈጻሚነት የላቸዉም። የእነዚህ ዓይነቶቹ ክሶች የሚቀርቡበትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ ተፈጻሚነት ያለው ቀደም ሲል በመ..15974 እና በሌሎች መዝገቦችም በተሰጠው የህግ ትርጉም መሰረት በፍ...1000 የተመለከተው የይርጋ ዘመን ስለመሆኑ በመ..70292 እና በመ..93501 ላይ አስገዳጅነት ያለው የሕግ ትርጉም ሰጥቶአል።

ከውርስ መንቀል ከጅምሩ የሚነሳው ኑዛዜ መኖርን ታሳቢ በማድረግ በመሆኑ ከኑዛዜ ተነቅያለሁኝ በሚል ኑዛዜው እንዲፈርስ የሚጠየቀው ክርክር የሚደረገው በወራሾች መካከል በመሆኑ የይርጋው ጊዜ ሟች ከሞተበት ጀምሮ 3 ዓመት ጊዜ ውስጥ መሆኑ ያለበት ሲሆን 3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ክሱ ካልቀረበ ጉዳዩ በይርጋ የሚታገድ ይሆናል፡፡

5.      የሟች የኑዛዜ ወራሽ የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ጊዜ

ወራሾች የኑዛዜ እና የሕግ ወራሾች ሊሆኑ እንደሚችሉ ከላይ በዝርዝር አይተናል፡፡ በክርክር ሂደት ይርጋ መቃዎሚያ ሲነሳ የትኛው ድንጋጌ ተፈጻሚነት እንዳለው ለመለየት ክስ ያቀረበው ከሳሽ የሕግ ወራሽ ወይስ የኑዛዜ ወራሽ ነው የሚለውን መለየት የግድ የሚል ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ//.98517 በሆነ መዝገብ በቀን 26/01/2008 . በሆኑ መዝገብ ላይ የኑዛዜ ወራሽ ሆነ ሰው በኑዛዜ ያገኘውሁትን ቤት ይለቀቅልኝ በሚል የሚያቀርበው ክስ 10 ዓመት የይርጋ ጊዜ የሚታገድ ለመሆኑ የሚከተለውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡

የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1062 ውርሱ በተጣራ ጊዜ በማናቸውም ጊዜ ቢሆን እያንዳንዱ የጋራ ወራሾች ውርሱን እንከፋፈል ብለው ለመጠየቅ እንደሚችሉ የሚደነግግ ነው። ድንጋጌው የቁጥር 1060 እና 1061 ድንጋጌዎች ተከታይ በመሆኑ ከእነዚሁ ድንጋጌዎች ጋር ተገናዝቦ መታየት የሚገባው ነው። ከድንጋጌው አነጋገር በግልጽ መገንዘብ እንደሚቻለው ድንጋጌው ተፈጻሚነት የሚኖረው ውርሱ ከተጣራ በኋላ አንደኛው ወይም የተወሰኑት ወራሾች ውርሱን ለመከፋፈል በሌላኛው ወይም በሌለኞቹ ወራሾች ላይ በሚያቀርቡት የክፍፍል ጥያቄ ላይ ነው እንጂ ዉርሱ ብዙ አመታትን ማለትም የይርጋዉን ጊዜ ካለፈ በኋላ በሚጣራ ጊዜም አይደለም።

በወራሾች መካከል ሳይሆን ወራሽ በሆነ እና ወራሽ ባልሆነ ሰው መካከል ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ በፍትሐብሔር ሕግ በተመለከቱት መደበኛ የይርጋ ድንጋጌዎች መሰረት የሚገዛ ከሚሆን በቀር የቁጥር 1062 ድንጋጌ ለጉዳዩ ተፈጻሚ ሊደረግ የሚችልበት የሕግ አግባብ አይኖርም።

በመሆኑም በዉርስ ማጣራት ሂደት ተካፋይ ያልሆኑ ፤የሟች ወራሽ ያልሆነ ሰዉ ፤የሟች የኑዛዜ ወራሽ ነኝ በሚል ሟች ከሞቱ 10 ዓመት በኋላ በውርስ ያገኘሁትን ቤት የያዘዉ አካል ይልቀቅልኝ በሚል የሚቀርብ ክስ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1677 (1) እና 1845 ድንጋጌዎች መሰረት በአስር ዓመት ይርጋ የሚታገድ ነዉ።

የኑዘዜ ወራሹ የወራሽነት መብቱን ሳያረጋግጥ ወይም የውርስ ሃብቱን ሳያጣራ ከቆየ እና የውርስ ሃብት ይገባኛል ክስ ወራሽ ባልሆነ ሰው ላይ ክስ የሚያቀርብ ከሆነ የይርጋው ጊዜ 10 ዓመት ሲሆን ክስ የሚያቀርበው ግን ንብረቱን በያዘበት የሟች የኑዛዜ ወራሽ ወይም የሕግ ወራሽ ከሆነ የይርጋው ጊዜ 3 ዓመት ይሆናል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ፍቺ ከፍርድ ቤት ውጭ - የሰበር ሰሚ ችሎት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎች...
በፍርድ ቤት አወዛጋቢ የሆኑ የውርስ ጉዳዮች እና መፍትሔዎቻቸው

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 11 September 2024