የንግድ እቃን ማከማቸት፣ መደበቅ፣ ዋጋ ጨምሮ መሸጥ እና የኮረና ወረርሽኝ ከኢትዮጵያ ሕግ አንፃር

በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ ሲከሰት የሰዎች ህይወትን ከመቅሰፉ በተጨማሪ የንግድ እንቅስቃሴዎችንም አደጋ ላይ ይጥላል። ንግድ የተሳለጠ እና ለሁሉ ተደራሽ የሚሆነው የተረጋጋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ሲኖር ብቻ ነው። በንግድ ዓለም ውስጥ የነጋዴዎች ዋነኛ ግብ ተደርጎ የሚወሰደው በአጭር ጊዜ ወይም በረጅም ጊዜ ውስጥ ትርፋማ መሆን ነው። ነገር ግን ይህ ትርፋመነታቸውን የሚያሳኩት ሕግ እና ሥርዓትን በአከበረ መንገድ በሚደረግ እንቅስቃሴ ሊሆን ይገባል። ከሕግ እና ሥርዓት ውጭ ትርፍ ለማጋበስ የሚንቀሳቀስ ነጋዴ የተመሰረተበት አላማ ማትረፍ ስለሆነ በሚል ተልካሻ ምክንያት ዝም ተብሎ ሊታለፍ አይገባም። ይህንም መሰረት ለማስያዝ ሕግ እና ሥርዓት አስፈፃሚ አካላት ትልቅ ድርሻ አላቸው። ትርፍ ለማግኘት ከሚደረጉ ጥረቶች ጎን ለጎን ማህበራዊ ሀላፊነትን መወጣትንም መዘንጋት አይገባም። የነጋዴዎች ትርፍን ለማሳደግ የሚያርጉት እሩጫ ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር ከተቋቋመ አካል ጋር በጥብቅ ከሚካረሩባቸው ወቅቶች አንዱ ወረርሺኝ የሚከሰትበት ወቅት ነው። ወረርሽኝ በሚከሰትበት ወቅት ሁሉም ከወረርሽኙ ለመዳን በሚያደርገው እሩጫ ወቅቱ የሚፈልጋቸው እቃዎች እና አገልግሎቶች እጥረት ሊከሰት ይችላል።

በዚህ ጊዜ ማህበራዊ ሀላፊነትታቸውን ለመወጣት ደፋ ቀና የሚሉ ነጋዴዎች የሚኖሩትን ያክል አጋጣሚውን ተጠቅመው ሀብት ለማካበት እና ከችግር ለማትረፍ የሚሯሯጡም አሉ። እነዚህ ከችግር ለማትረፍ የሚሯሯጡ ነጋዴዎች ከሚተገብሯቸው ነገሮች መካከል እጥረት ያለበትን እቃ ማከማቸት እና በተፈላጊ እቃዎች ላይ አለአግባብ ዋጋ መጨመር ይገኙበታል። እነዚህ ተግባራት በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ከቀላል እስከ ከባድ አደጋዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ሀገራት የሸመቾች ጥበቃ ሕግን በማውጣት ሸማቹን ማህበረሰብ ከእንደዚህ አይነት ችግር ለመጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ  ይስተዋላል። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ለሸማቾች መብት ጥበቃ ልዩ ትኩረትን የሰጠች ሲሆን በመካከልም ሁለት ህጎችን አርቅቃለች። አሁን ላይ በስራ ላይ ያለው የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ትኩረት ከሰጣቸው ነገሮች መካከል እጥረት ያለባቸውን እቃዎች ማከማቸት እና ተፈላጊ እቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኙበታል። በሀገራችን ዓለም አቀፍ የሆነው የኮረና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ከወረርሽኙ እኩል በሚባል ደረጃ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት የሳበው ጉዳይ የነጋዴዎች እጥረት ያለባቸውን እቃዎች ማከማቸት ተግባር እና የተፈላጊ እቃዎችን ዋጋ  ጨምሮ መሸጥ ይገኙበታል። የዚች አጭር ፅሁፍ አላማም እነዚህን የነጋዴው ማህበረሰብ ተግባራት ከኢትዮጵያ የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ አንፃር መተንተን እና መወሰድ ያለባቸውን ተግባራት መጠቆም ነው።

  1. የኮረና ወረርሽኝ እና እጥረት የተከሰተባቸው እቃዎች

የኮረና ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። የዓለም ጤና ድርጅት በሰጠው መመሪያ መሰረት ሀገራት ሊከተሏቸው ከሚገቡ የመከላከያ መንገዶች አካላዊ እርቀት፣ ማስክ መጠቀም ፣አለመጨባበጥ እና እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ዋነኞቹ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ማስክ መጠቀም የማስክ አቅርቦትን እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ደግሞ የሳሙና እና የሳኒታይዘር አቅርቦትን ይጠይቃሉ። በአሁኑ ሰዓት በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እነዚህ በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ እቃዎች እጥረት የመንግስታት እና የህዝብ ጭንቀት ከሆኑ ውሎ አድሯል። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህን እጥረት ያለባቸውን ቁሳቁስ በአገኙት አጋጣሚ የሚሰበስቡ እና በውድ ለመሸጥ የሚያከማቹ ነጋዴዎች እንዲሁም ከእራሳቸው እና ከቤተሰባቸው ፍጆታ በላይ የሚገዙ ግለሰቦች መበራከት ሌላ ትልቅ የእራስ ምታት ሆኗል። ከህክምና ቁሳቁሶች በተጨመሪ ለእለት ፍጆታ የሚውሉ እቃዎችም ለዚሁ ችግር ሰለባ ሆነዋል። መንግስት የሚያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ዜጎች እቤት ውስጥ ለመቀመጥ ከሚገዙት ከመጠን ያለፈ የምግብ እቃዎች በተጨማሪ ወደፊት የዋጋ ጭማሪ ሊከሰት እንደሚችል በመተንበይ ዜጎች ሊገዙ የሚፈልጉአቸውን እቃዎች አከማችቶ የለም iማለት ወይም አላግባብ ዋጋ በመጨመር የሸማቹን የመግዛት አቅም የመቀነስ ተግባር በነጋዴው ማህበረሰብ ዘንድ ይስተዋላል። እነዚህ ተግባራት በወቅቱ ተገቢ የሆነ ህጋዊ እርምጃ ካልተወሰደባቸው በጊዜ ሂደት የሚያስከትሉት አደጋ በጣም ከባድ ይሆናል። የህክምና ቁሳቁሶች ላይም ሆነ የእለት ፍጆታ እቃዎች ላይ የሚደረገው የማከማት እና ሰው ሰራሽ የእቃ እጥረት ችግር ሸማቹን ማህብረሰብ ለርሀብ ብሎም ለሞት የሚዳርግ ችግር ውስጥ ሊከተው ይችላል። ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ እቃዎች በአግባቡ እንዲሰራጩ ከአልተደረገ ከእለት ወደ እለት ወረርሽኙ እየተስፋፋ ከሚያስከትለው ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ የእለት ከእለት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በመገደብ ሀገርን ከባድ የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ሊከት ይችላል። የእለት ፍጆታ አቅርቦቶችን መገደብም በእራሱ ዜጎችን ለርሀበ እና ሲቃይ በመዳረግ ወረርሽኙ ሊያስከትል ከሚችለው አደጋ የበለጠ ችግር ሊያመጣ ይችላል። እነዚህን ከባድ ችግሮች መቋቋም የሚቻለው ሕግን መሰረት አድርጎ በእንደዚህ አይነት ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላትን ማስተካከል እና አስፈላጊ እርምጃዎች ሲወሰዱ ብቻ ነው።

  1. የንግድ እቃን ማከማቸት እና ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር በኢትዮጵያ ሕግ

እቃን ማከማቸት እና ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር የገቢያ አለመረጋጋት እና የዋጋ ንረትን ከሚያስከትሉ ተግባራት መካከል የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች የእቃውን በገቢያ ላይ ያለውን ተፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአቅርቦት ችግር በሌለበት ሁኔታ የአቅርቦት ችግር ያለ በማስመሰል በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ ሊያከማቹ እና ሰው ሰራሽ እጥረት ፈጥረው በትልቅ ዋጋ የመሸጥ ተግባር ሊፈፅሙ ይችላሉ። ነጋዴዎች እቃውን አከማችተው የሚያስቀጡበት ዋነኛ አላማቸው ጊዜውን ጠብቆ ከተገቢው በላይ ትርፍን ለማጋበስ ነው። ከነጋዴው ማህበረሰብ በተጨማሪ የሸማቹ ማህበረሰብም በእንደዚህ አይነት ተግባራት ተሰማርቶ ሊገኝ ይችላል። የሸማቹ ማህበረሰብ በዋነኝነት እንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ የሚሰማራው እቃው ከገቢያ ላይ ይጠፋል የሚል ፍራቻ ሲያድርበት ነው። ይህ የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ የሸማቹ የማከማቸት ተግባር በዜጎች ላይ ወይም እንደ አጠቃላይ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ በጣም ከባድ የሆነ ነው። ይህንም ተግባር ለመከላከል ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 እቃን ስለማከማቸት እና ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠርን አስመልክቶ ድንጋጌዎችን የአካተተ ሲሆን የማስፈፀም ሀላፊነቱንም ለንግድ ሚኒስትር፤ ለንግድ ዉድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን እና ለንግድ ቢሮዎች ሰጥቷል።

በአዋጁ አንቀፅ 24 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት አንድ ነጋዴ  ከመደበኛ የግብይት ስርዐት ውጭ ወይም ነጋዴ ያልሆነ ሰው ለግል ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ከሚውል መጠን በላይ በንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስተር በገቢያ ላይ እጥረት ያለበት መሆኑ በሚኒስተሩ በወጣ የህዝብ ማስታወቂያ የተገለፀ የንግድ እቃን ማከማቸት ወይም መደበቅ ክልክል ነው። እዚህ ላይ በመጀመሪያ ደረጃ የንግድ ሚኒስተር እጥረት ያለበትን እቃ በዝርዝር በህዝብ ማስታወቂያ የማሳወቅ ሀላፊነት ያለበት ሲሆን ይህንም ተከትሎ ነጋዴዎች እና ለግል ወይም የቤተሰብ ፍጆታ የሚሸምቱ ግለሰቦች ከመደበኛ መጠን ያለፈ እቃን ማከማቸት ወይም መደበቅ አይችሉም። ነጋዴውን ማህበረሰብ ወይም ሌሎችን ግለሰቦች ከእነዚህ ተግባሮች እንዲቆጠቡ ለማድረግ ሚኒስተሩ በመጀመሪያ የራሱን ሀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ መገንዘብ ይገባል። የህዝብ ማስታወቂያዎች ለህዝቡ ተደራሽ በሆኑ የብሮድካስት ወይም የህትመት ሚዲያዎች እንዲሁም የህዝብ ማስታወቂያ መለጠፊያ ቦርዶችን እንደአግባብነቱ በመጠቀም ሊገለፅ ይችላል።  በተመሳሳይ አንቀጽ ላይ አዋጁ የአስፈፃሚ አካላት ሕግን የማስከበር ስራ በሚሰሩበት ወቅት ችግር እንዳይፈጠር እንዲሁም የትርጉም ክፍተቶችን በመቀነስ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለማስቻል በንዑስ አንቀፅ ሁለት ላይ ከመደበኛ የግብይት አሰራር ውጭ እቃ ተከማችቷል ወይም ተደብቋል የሚያስብሉ መስፈርቶችን አስቀምጧል። መጀመሪያ ላይ የሰፈረው ነጋዴውን ማህበረሰብ የተመለከተ ሲሆን አንድ ነጋዴ ግምቱ ከነጋዴው ካፒታል 25% የማያንስ እቃ ከውጭ የመጣ ሲሆን አስመጭው ራሱ ለቀጣይ የምርት ሂደት በጥሬ እቃነት ወይም በግብይት የሚጠቀምበት ካልሆነ በስተቀር የጉምሩክ ፎርማሊቲ ከተጠናቀቀለት በኋላ በሶስት ወራት ውስጥ፤ በሀገር ውስጥ የተመረተ የንግድ እቃ ሲሆን በተመሳሳይ አምራቹ ለእራሱ የምርት ግብዐት ካልተጠቀመበት በሁለት ወራት ውስጥ ወይም በጅምላ ሻጭ እና በችርቻሮ ሻጭ የተገዛ እቃ ሲሆን ከተገዛበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ ለሽያጭ ካልቀረበ ነጋዴው እጥረት ያለበትን እቃ የማከማቸት እና የመደበቅ ክልከላን እንደጣሰ ይቆጠራል። እነዚህ መስፈርቶች ባይሟሉም እንኳ በማንኛቸውም መጓጓዣ  ከተፈቀደው የስርጭት መስመር ውጭ ሲጓጓዝ የተገኘ እቃ እንደ ተከማቸ እና አንደተደበቀ ይቆጠራል። ይህ ድንጋጌ ለነጋዴው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ከንግድ ውጭ ላሉ ማህበረሰቦች ተፈፃሚነት አለው። እንደፃፊው አረዳድ የተፈቀደ የጉዞ መስመር የሚለውን ሀረግ የሚያመላክተው የጉምሩክ መመሪያን መሰረት የአደረገ እንቅስቃሴን አለመከተል ወይም የእቃ እጥረት ማጋጠሚን ተከትሎ በመንግስት የሚወጡ የጉዞ መስመር መመሪያዎችን የተመለከተ ሊሆን ይችላል። ከነጋዴ ማህበረሰቦች ውጭ ያሉትን ግለሰቦች በተመለከተ ተቀባይነት ያለውን የግል ወይም የቤተሰብ ፍጆታ ሁኔታዎችን ታሳቢ አድርጎ እንዲወስን ለንግድ ሚኒስትር በአዋጁ ስልጣን ተሰጦታል። የማከማቸት እንዲሁም የመደበቅ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን በተመለከተ የአዋጁ አንቀፅ 43 ንዑስ አንቀፅ 4 እና 5 ላይ የተቀመጡ ድንጋጋጌዎች የተከማቸውን እቃ እንዲሁም ማጎጓዣን መውረስን ጨምሮ እስከ አምስት አመት የሚደርስ ፅኑ እስራትን እና የገንዘብ ቅጣቶችን አስቀምጠዋል። የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ባለስልጣን በአንቀፅ 36 ንዑስ አንቀፅ 1(ለ) መሰረት በአዲስአበባ እና በድሬደዋ ከተማ የሚፈጠሩ እቃ የማከማቸት ወይም የመደበቅ ወንጀሎችን የመመርመር እና ክስ የማቅረብ ስልጣን የተሰጠው ሲሆን በክልልሎች የሚፈጠሩ ችግሮችን በተመለከተ በአንቀፅ 23(5) መሰረት ለክልል የንግድ ቢሮዎች ስልጣን ተሰጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም በአንቀፅ 23(5) መሰረት አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በተመለከተ ለባለስልጣኑ አዋጁ በግልፅ ስልጣን ስላልሰጠው የእቃ ማከማቸት እና መደበቅን በተመለከተ የሚያስፈልጉ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን የመውሰድ ስልጣንም በንግድ ሚኒስተር እና ቢሮዎች ስር የሚወድቅ ይሆናል።

 ይህ የንግድ እቃን ማከማቸት እና መደበቅን የተመለከተ ድንጋጌ በተወሰነ ጊዜ ወይም ሁኔታ የተገደበ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስተር የእቃ እጥረት መከሰቱን ሲረዳ ሊከተለው እና ሊያስፈፅመው የሚገባ ድንጋጌ ነው። በማንኛውም ጊዜ አስፈላጊ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሀገር ለከባድ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋ(በሽታ ወረርሽኝን ጨምሮ) ስትጋለጥ አስፈላጊነቱ ከምንም በላይ ይሆናል። በዚህ ወቅትም ዓለም በኮረና ወረርሽኝ አደጋ በተጨነቀችበት ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል iA´Xu} ከምንጠቀምባቸው ህጎች መካከል የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ላይ የተቀመጠው ይህ የንግድ እቃወችን ማከማቸት እና መደበቅን መቆጣጠሪያ ድንጋጌ አንዱ እና ዋነኛው ነው። ይህንንም ለማድረግ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ እጥረት የተከሰተባቸውን የእቃ አይነቶች የንግድ ሚኒስትር በተከታታይ ይፋ ሊያደርግ እና የተቀመጡ ሂደቶችን ተከትሎ ሊቆጣጠር ይገባል። ሌሎች በአዋጁ ሀላፊነት የተሰጣቸው  የክልል እና የፌደራል መስሪያቤቶችም ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል። አሁን ከተከሰተው የኮረና ወረርሽ አደጋ አንፃር የአዋጁን ድንጋጌዎች ከአየናቸው ግን አንዳንድ ክፍተቶችን መገንዘብ እንችላለን። በአዋጁ አንቀፅ 24 ላይ እንደተመለከተው ከተፈቀደ መስመር ውጭ ሲጓጓዙ የተያዙ እና በግለሰቦች እጅ የተከማቹ እቃዎች ውጭ ያሉ ሁሉም የማከማቸት እና የመደበቅ ድርጊቶች በየደረጃው ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወር የሚደርስ የእፎይታ ጊዜን ተሰጦአቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የንግድ እቃዎችን በተመለከተ አንድ ነጋዴ እስከ 25% ካፒታሉ ድረስ የማከማቸት ስልጣን መሰጠቱን ከወቅቱ የኮረና ወረርሽኝ አጣዳፊነት አንፃር ስንመለከተው አዋጁ ታሳቢ ያደረገው በመደበኛ ጊዜ የሚፈጠር እጥረትን ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። እስከ 3 ወር የሚደርስ እፎይታን እና አስከ 25% ካፒታሉ የሚደርስ እቃን የማከማቸት መብት ለነጋዴው የምንሰጥ ከሆነ እቃው በተሎ ለገቢያ መድረስ እየቻለ የህጉን ክፍተት ተጠቅሞ እንዲያከማች ለነጋዴው እድል እየሰጠነው እና በመካከል ብዙ የሰብዓዊ ኪሳራ እንዲያጋጥም እያደረግን ነው። ስለዚህ  ይህ ክፍተት ወቅቱን ታሳቢ አድርጎ የሚሞላበትን አቅጣጫ መጠቆም አስፈላጊ ይሆናል። በፀሃፊው አረዳድ ይህን ክፍተት መሙላት የሚቻለው በህገመንግስቱ መንግስት መደበኛውን የሕግ አሰራር ወደ ጎን በመተው ነገሮችን እንዲያስተካክል የሚፈቅድለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ስልጣን መጠቀም ነው። በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 93(4) መሰረት በሀገር ደረጃ ወይም በክልልሎች የወረርሽኝ በሽታ በሚከሰትበት ወቅት የፌደራል መንግስት ወይም የክልል መንግስታት እንደተዋረዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት በመደበኛ የሕግ ስርዐቱ ማስፈፀም ያልቻሉአቸውን ጉዳዮች እንዲያስፈፅሙ እና ዜጎችን ከመጣው ወረርሽኝ እንዲከላከሉ ስልጣን ሰጧቸውአል። ይህንንም ተከትሎ የኮረና ቫይረስ ወርሽኝ የሚያመጣቸውን ችግሮች ከመደበኛው የሕግ ሥርዓት በተለየ መልኩ ተንቀሳቅሶ በሚገባ ለመመከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012ን አወጥቷል። ከላይ እንደገለፅኩት በትክክለኛው የሕግ አሰራር የኮረና ወረርሽኝን ተከትሎ መንግስት ሊያስፈፅማቸው ከማይችላቸው ነገሮች መካከል እስከ 25% ካፒታላቸው ያከማቹ ነጋዴዎችን ምርታቸውን ወደ ገቢያ እንዲያወጡ ማድረግ እና ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወር የሚደርሱ በየደረጃው የተሰጡ የእፎይታ ጊዜዎችን በመጣስ ነጋዴዎች ያላቸውን ምርት ለገቢያ እንዲያቀርቡ ማስገደድ ይገኙበታል። እነዚህ ደግሞ በአንፃሩ የነጋዴውን ማህበረሰብ የማከማቸት እና የመደበቅ ተግባር የሚያግዙ እና የመንግስትን ወረርሽኙን የመመከት እንቅስቃሴ የሚጎዱ የሕግ ክፍተቶች ናቸው። ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ክልከላዎችን እንዲያስፈፅም ስልጣን የተሰጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሽታውን ለመቆጣጠር ያግዘው ዘንድ እነዚህን የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ የሕግ ክፍተቶች የሚሞላ ድንጋጌን ቢያወጣ የተሻለ አፈፃፀም ይኖረዋል።

  1. ማጠቃለያ

በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወረርሽኝ አደጋ ሲከሰት በሀገራት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርሰው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም። አሁን ላይ አለማችን ያጋጠማት እና በሀገራችን መከሰቱ የተረጋገጠው የኮረና ወረርሽኝም ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ሀገራት ላይ እያደረሰው ያለው ሰብዓዊ እና ማህበራዊ ኪሳራም በጣም ከፍተኛ ነው። እንደዚህ አይነት አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት በጣም ፈታኝ እና እልህ አስጨራሽ ከሚሆኑ ህገወጥ ተግባራት መካከል የነጋዴዎች ከአደጋ የማትረፍ እሩጫ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ይህ የነጋዴው ማህበረሰብ ኢሞራላዊ እና ህገወጥ እንቅስቃሴ በሀገር ላይ በተለይ ደሞ በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሰው ሰብዓዊ እና ማህበራዊ ቀውስ በጣም ከባድ ነው። ይህንን ቀውስ ለመከላከል ወይም ለመቀነስ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጠንካራ የሕግ ሥርዓት መዘርጋት ትልቁን ድርሻ ይወስደዋል። ሀገራት  እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመቀነስ የሸማቾች ጥበቃ ሕግን  በብዛት ሲጠቀሙ ይስተዋላል። ኢትዮጵያም ለሸማቾች ጥበቃ ልዪ ትኩረት መስጠት ከጀመረችበት 2002 ዓ.ም ጀምሮ ሁለት የሸማቾች ጥበቃን የሚመለከቱ ህጎችን ያወጣች ሲሆን አሁን በስራ ላይ ያለው የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ከአካተታቸው ድንጋጌዎች መካከል የንግድ እቃዎችን ማከማቸት እና መደበቅን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኙበታል። የአዋጁ አንቀፅ 24 ለነጋዴዎች በገቢያ ላይ ከተለመደው መጠን ውጭ እንዲሁም ነጋዴ ላልሆኑ ግለሰቦች ለግል ወይም የቤተሰብ ፍጆታ ከሚያስፈልግ በላይ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስተር እጥረት እንዳለበት የተገለፀን እቃ ይዞ መገኘት የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል። ነጋዴዎችን በተመለከተ አዋጁ የመጠን እና የጊዜ መስፈርት የአስቀመጠ ሲሆን ከነጋዴ ውጭ የሆኑ ግለሰቦችን በተመለከተ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የመወሰን ስልጣን ተሰጦታል። ከተፈቀደ መስመር ውጭ ሲጓጓዝ የተገኘ እቃም ምንም እንኳ መስፈርቶችን ባያሟላም እንደ ተከማቸ እቃ እንደሚቆጠር አዋጁ ያስቀምጣል። የአዋጁን ድንጋጌዎች ጥሶ እቃ አከማችቶ የተገኘ ነጋዴም እቃ የመወረስ፣የገንዘብ እና የስር ቅጣቶች ይጠብቁታል። አሁን በዓለም ላይ እንዲሁም በሀገራችን የተከሰተውን ኮረና ወረርሽኝ አደጋን ተከትሎ እየተስተዋሉ ያሉ የነጋዴዎች እንቅስቃሴን ከመግታት አንፃር የዚህን ሕግ ጥንካሬ ስንገመግም በተለይ የተቀመጡት የመጠን መነሻ መስፈርቶች እና የእፎይታ ጊዜዎች የነጋዴውን ማህበረሰብ የአልተገባ እንቅስቃሴ የሚደግፉ እና ህዝብን ለከባድ ችግር የሚያጋልጡ ስለሆኑ ማስተካከያ ሊደረግባቸው እና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሚያስችል መንገድ ሊቃኙ ይገባል። ይህንም ለማድረግ ወረርሽኙን ለመከላከል የፌደራል መንግስቱ የአወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 መሰረት አድርጎ እነዚህን ገደቦች የሚያነሳ መመሪያ ማውጣት ያስፈልጋል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የመፈንቅለ መንግሥት ጽንሰ ሃሳብ እና መገለጫዎች
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ-መንግሥት መተርጎም ላይ ያለው ሚና እና...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 25 April 2024