የአካል ነጻነት መብት በኢፌዲሪ ህገ መንግስት እውቅና ከተሰጣቸው የሰብአዊ መብቶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይኸውም የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 17 ድንጋጌ በግልጽ ማንም ሰው በህግ ከተደነገገው ስርአት ውጪ ሊያዝ እንዲሁም ክስ ሳይቀርብበት እና ሳይፈረድበት ሊታሰር የማይችል ስለመሆኑ ያስቀምጣል፡፡ በእርግጥ ይህ መብት በዚሁ ሕገ መንግስት መሰረት የሀገሪቱ የህግ አካል የሆኑ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነነት ሰነዶችም ቢሆን እውቅና ከተሰጧቸው የሰብአዊ መብቶች መካከል አንዱ ስለመሆኑ እሙን ነው፡፡ 

ይሁን እና የዚህ አጭር ጽሁፍ ዋነኛ አላማ የዚህን መብት መሰረታዊ  ነጥቦችን ወይም ወሰኑን ለማብራራት ሳይሆን አንድ የአካል ነጻነት መብቴ ተገፏል የሚል ሰው ይህ መብቱን ፍ/ቤት እንዲያስከብርለት አቤቱታ ቢያቀርብ ክርክሩ ከመደበኛው የፍታብሄር ጉዳዮች ክርክር የሚለይበትን ዋና ዋና የሥነ-ሥርዓት  ነጥቦች ለማብራራት ነው፡፡

እንደሚታወቀው የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በልዩ ሁኔታ ሥነ-ሥርዓት ካበጀላቸው ክርክሮች መካከል አንዱ ተገዶ የመያዝን ሕጋዊነት ለማጣራት ወይም የአካል ነጻነትን ለማስከበር የሚቀርብ ክርክር አንዱ ነው፡፡ ይህ ሕግ ከቁጥር 177 እስከ 179 ባሉት ድንጋጌዎቹ ክርክሩ የሚመራበትን መሰረታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ዘርግቶ እናገኛለን፡፡  ድንጋጌዎቹ ምንም  እንኳ ከሌሎቹ ልዩ ሥነ-ሥርዓት ከተሰራላቸው ጉዳዮች አንጻር ጥቂት ቢሆኑም ይሁን እና በውስጣቸው ትልልቅ ሥነ-ስርዓቶችን ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህም መሰረት ይህ ክርክር ከመደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክር የሚለያይባቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ጽሁፉ እንደሚከተለው ተመልክቷቸዋል፡፡

  1. ከመብት ጥቅም አኳያ

እንደሚታወቀው የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በቁጥር 33 ላይ ከሳሽ የመሆንን ችሎታ ያስቀምጣል፡፡ ይኸውም በዚህ ሕግ መሰረት አንድ ሰው ከሳሽ የመሆን ችሎታ አለው የሚባለው ክስ ባቀረበበት ነገር ላይ እና ክስ ባቀረበበት ሰው ላይ የሚጠይቀው መብት እንዳለው አረጋግጦ በቀረበ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም በሕጉ መሰረት ከሳሽ ለመሆን ክስ በቀረበበት ነገር እና በተከሳሽነት ከተጠራው ሰው ላይ የሚጠየቅ መብት ወይም ጥቅም ሊኖር ይገባል ማለት ነው፡፡

ከተያዘው ጉዳይ ጋር ስንመልሰው ደግሞ እንደዚህ ድንጋጌ አገላለጽ የአካል ነጻነት መብቱን በ ፍ/ቤት ለማማረጋገጥ ክስ ለማቅረብ የሚችለው ሰው እራሱ የአካል ነጻነት መብቱ የተጣሰበት ሰው ወይም ሕጋዊ ወኪሉ ሲሆኑ ክሱም የሚቀርበው ይህንን መብት በተጋፋው ሰው ላይ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እና ይህ ጉዳይ ከላይ የተጠቀሱት የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች ልዩ ሁኔታዎችን ካስቀመጡበት አንዱ የሥነ-ሥርዓት ክፍል ነው፡፡

ይኸውም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 177(3) ስንመለከተው የአካል ነጻነትን መብትን ለማስከበር የሚቀርብ ክስ ወይም አቤቱታ የግድ መብቱ በተገፋበት ሰው ወይም በሕጋዊ ወኪሉ ብቻ የሚቀርብ እንዳልሆነ ያስገነዝበናል፡፡ ሕጉ ይህንን እውነት በቃለ መኃላ ለማረጋገጥ የሚችል ማንም ሰው መብቱ በተገፋበት ሰው ፈንታ የዛ ሰው ወኪል ባይሆን እንኳ ክሱን ለማቅረብ ችሎታ እንዳለው ያስቀምጣል፡፡ ይህም ማለት ክሱ በማንም ሰው ለፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚችል መሆኑን የሚያስገነዝበን ሲሆን በተለይም ማንኛውም ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ በተለየ ሁኔታ መብቱ ወይም ጥቅሙ የተጎዳበት ባይሆንም ክሱን ለማቅረብ ግን በኽጉ ልዩ ችሎታ የተሰጠው ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡

ይሁን እና ሕጉ ለሁሉም ሰው ክሱን ለማቅረብ መብት ሰጥቷል ሲባል ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ለፍ/ቤቶች በዘፈቀደ ክሱን ያቀርባል ማለትም አይደለም፡፡ ሕጉ ለሁሉም ሰው ክስን የማቅረብ መብት ሲሰጥ ከቅድመ ሁኔታዎች ጋር ስለመሆኑ በተለይም የዚሁ ሕግ አንቀጽ 33(1) እና 177 (3) ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህም ሕጉ በዋነኛነት ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠ ሲሆን እነዚህም አቤቱታ አቅራቢው ሰው እራሱ ክሱን ለማቅረብ በሕግ ችሎታ ያለው መሆኑ ማለትም ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው መሆን እንዳለበት እና ያልተከለከለ ሰው ሊሆን እንደሚገባ የሚያስቀምጥ ሲሆን በተጨማሪም ይህ ሰው መብቱ የተገፋበት ሰው አቤቱታውን በራሱ ሊያቀርብ እንደማይችል በቃለ መኃላ ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ናቸው፡፡ ስለዚህ የሕግ ችሎታ እና መብቱ የተገፋበት ሰው አቤቱታውን በቃለ በራሱ ሊያቀርብ የማይችል መሆኑ ቅድመሁኔታዎች ተደርገው ተቀምጠዋል፡፡ 

በመሆኑም ይህ የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌ ምንም እንኳ በጉዳዩ ላይ በቀጥታ መብቱ የተጎዳበት ሰው ባይሆንም እንኳ ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሟላ ማንኛውም ሰው በጉዳዩ ላይ ክስ የማቅረብን መብት የሚያጎናጽፍ ሲሆን ይህም ከመደበኛው የፍትሐ ብሔር ሕጉ የክስ አቀራረብ ችሎታ  የሚለይበት አንዱ ልዩ ሁኔታ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

  1. ክስን በውክልና ከማቅረብ አኳያ

በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ በመደበኛ የፍትሐ ብሔር ክርክር ጉዳይ ላይ በውክልና ክስ የሚቀርብበትን ሥነ-ሥርዓት ልዩ ሁኔታም ሆኖም እናየዋለን፡፡ ምክንያቱም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 57 እና ተከታዮቹን ድንጋጌዎች ስንመለከታቸው አንድ ሰው በራሱ ወይም በወከለው ሰው አማካይነት ክስ ለማቅረብ የሚችል ስለመሆኑ ያስቀምጣሉ፡፡  ይሁን እና ይህ የሚወከለው ሰው ክርክሩን ግለሰቡን ወክሎ ለማቅረብ ፍቃድ የተሰጠው ባለሙያ(ጠበቃ) አልያም ህጉ በልዩ ሁኔታ ባለሙያ ባይሆኑ እንኳ ክርክርን በውክልና እንዲያደርጉ ከፈቀደላቸው የቤተሰቦች አባላት መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚገባ ያስቀምጣሉ፡፡ (የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 58(2) እና 63) ላይ ተመልክቷል፡፡

ይሁን እና ለክርክሩ መነሻ የሆነው ጉዳይ ግን የአካል ነጻነትን ለማስረከብ የቀረበ ክስ በሆነ ጊዜ አንድ ሰው መብቱ ከተገፋበት ሰው ጋር ቤተሰብ ባይሆን ወይም ክርክሩን ፍ/ቤት ለማቅረብ የተሰጠው የሙያ ፈቃድ ባይኖር እንኳ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟላ ድረስ ክሱን አቅርቦ በፍ/ቤት ፊት ቀርቦ እንዲከራከር የተፈቀደለት መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ከክስ አቀራረብ እና ክርክር አመራር አንጻር ይህ ሁኔታ ሌላኛው የአካል ነጻነት መብትን በፍ/ቤት ለማስከበር ለሚቀርብ ክስ ልዩ ስነስርአት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

እዚህ ጋር አንድ መታየት ያለበት ነጥብ ግን ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሟላ ማንኛውም ሰው ክሱን ሲያቀርብ የሚያቀርበው በራሱ ስም ነው? ወይስ መብቱ በተገፋበት ሰው ስም የሚለው ነው፡፡ በእርግጥ ህጉን ስንመለከተው በግልጽ ማንኛውም የተባለውን ቅድመ ሁኔታ የሚያሟላ ሰው ክሱን ሊያቀርብ ይችላል እንጂ በማን ስም ክሱን ሊያቀረብ እንደሚችል የሚያስቀምጠው ነገር የለም፡፡ በዘርፉ ያሉ አንዳንድ ባለሙያዎች ክሱ መብቱ በተገፋበት ሰው ስም ሊቀርብ ይገባል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ክሱን በክስ አቅራቢው ሰው ስም ሊቀርብ ይገባል ይላሉ፡፡

እንደዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ግን ይህን ጥያቄ ለመመለስ በዋናነት መታየት ያለበት ነገር ለምን ማንኛውም ሰው ክሱን እንዲያቀርብ ሕጉ ልዩ ችሎታ ሰጠው? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ይህንንም ከዚሁ ሕግ አንቀጽ 177(3) ድንጋጌ ይዘት መረዳት የሚቻል ሲሆን ህጉ በግልጽ መብቱ የተገፋበት ሰው በማንኛውም ምክንያት ክሱን በራሱ ሊያቀርብ ባልቻለ ጊዜ ብቻ ሌላ ሰው እሱን ተክቶ እንዲያቀርብለት የሚፈቅድ ስለመሆኑ ነው፡፡

ይህ ማንኛውም ሁኔታ የተባለው ደግሞ መብቱ የተገፋበት ሰው በዛን ወቅት ያለበትን ያለመንቀሳቀስ ሁኔታ እና የሕግ ችሎታውን የሚጨምር መሆኑን ለመረዳት የሚቻል ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ክሱ መብቱ በተጎዳበት ሰው ስም እንዳይቀርብ በተለየ ከልካይ ሁኔታዎች አይደሉም፡፡ በመደበኛውም የሙግት ሥነ-ሥርዓትም ቢሆን የአንድ አካለ መጠን ያልደረሰን ሰው መብት በፍ/ቤት ለማስከበር ሰውየው በራሱ ክስ ለማቅረብ ባይችልም በሞግዚቶቹ በኩል በስሙ ክሱ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ ስለመሆኑ የምናየው ነው፡፡

በዚህም ጉዳይ ቢሆን መብቱ የተገፋበት ሰው ተገዶ መያዙን ተከትሎ ፍ/ቤት ቀርቦ የራሱን ክስ ሊያቀርብ ስለማይችል ማንም ሰው እሱን ተክቶ ክሱን እንዲያቀርብ ሕጉ የፈቀደ ቢሆንም ይህ ተገዶ መያዙ ብቻውን ግን ክሱ በስሙ እንዳይቀርብ ልዩ ከልካይ ሁኔታ ተደርጎ የሚወሰድበት አግባብ ያለ አይመስልም፡፡ ስለሆነም ክሱ መቅረብ ያለበት መብቱ በተገፋበት ሰው ስም ሆኖ አቤቱታው ያቀረበው ሰው ግን መብቱ የተገፋበት ሰው ክሱን በራሱ ሊያቀርበው አለመቻሉን በቃለ መኃላ ካረጋገጠ የሚበቃ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

  1. የተከራካሪዎች ፍ/ቤት አለመቅረብ እና ውጤቱ

በመደበኛው የፍትሐ ብሔር የሙግት ስነ-ሥርዓት አንድ ክስ ያቀረበ ሰው ከላይ እንደተገለጸው እራሱ በአካል ካልሆነም በተወከለው ሰው አማካኝነት ፍ/ቤት በመቅረብ ሊከራከር ይችላል፡፡ ይኸውም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 65(1) ድንጋጌ ተከራካሪዎች በራሳቸው ወይም በወኪላቸው አማካይነት ፍ/ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡ ይህም ማለት በፍትሐ ብሔር ክርክር ጉዳይ ተከራካሪዎች የግድ በአካል ፍ/ቤት እንዲቀርቡ በሕጉ አይገደዱም፡፡ ወኪላቸውን በመላክ ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁል ጊዜም ላይሆን ይችላል፡፡ ይኸውም ፍ/ቤቱ ተከራካሪዎች በራሳቸው በአካል እንዲቀርቡ ባዘዘ ጊዜ ግን በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክር ጉዳይ ላይም ቢሆን በአካል መቅረብ ግዴታ ነው፡፡ ፍ/ቤት እንደዚህ አይነት ትእዛዞች መቼ እና በምን ሁኔታ ይሰጣል የሚለው ጉዳይ የዚህ ጽሁፍ አላማ ጋር የሚገናኝ ስላልሆነ መመልከቱ አላስፈለገም፡፡ ስለዚህም በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክር ጉዳይ በመርህ ደረጃ ፍ/ቤት በአካል መቅረብ አስገዳጅ ባይሆንም በልዩ ሁኔታ ግን መቅረብ ግዴታ ነው፡፡

ክርክሩ የአካል ነጻነት መብትን ለማስከበር የቀረበ በሆነ ጊዜ ግን ይህ ሁኔታ በተቃራኒው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይኸውም የሥነ-ስርዓት ሕጉ 178(1) ድንጋጌን ስንመለከተው በተለይም የአካል ነጻነት መብቱ የተገፋበት ሰው እና መብቱን ገፍቷል ተብሎ በተከሳሽነት የተጠራው ሰው የግድ በአካል ፍ/ቤት ሊቀርቡ እንደሚገባ ያስረዳናል፡፡ እንደዚህ ድንጋጌ አገላለጽ ‹አሳሪው የያዘውን(የአሰረውን) ሰው ፍ/ቤት በአካል ይዞት እንዲቀርብ እና የእስሩንም ሁኔታም እንዲያስረዳ› የሚገደድ መሆኑን ከዚህ ሕግ ድንጋጌ መረዳት የሚቻል ነው፡፡  ይህም ክርክሩ የአካል ነጻነት መብትን ለማስረከብ በሆነ ጊዜ ከሳሽ እና ተከሳሽ የግድ ፍ/ቤት በአካል እንዲቀርቡ የሚገደዱ መሆኑን ሲሆን በተለይም ከሳሽ (ታሳሪው) በአካል፤ ተከሳሽ(አሳሪው) ደግሞ በአካል ወይም በወኪሉ አማካይነት ሊቀርቡ የሚገባ መሆኑን ከድንጋጌው ይዘት መረዳት የሚቻል ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ሁኔታ ክርክሩን ከመደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክር ሥነ-ስርዓት ልዩ ሁኔታ ያደርገዋል፡፡

እንደሚታወቀው በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክር ተከራካሪዎች ፍ/ቤት ባልቀረቡ ጊዜ የራሱ ውጤት አለው፡፡ ይኸውም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 69 እና ተከታዮ ድንጋጌዎች ላይ የተመለከተው ሲሆን ከሳሽ የሆነ ሰው ባልቀረበ ጊዜ ተከሳሽ ክርክሩን እስካላመነ ድረስ መዝገቡ የሚዘጋ መሆኑን የዚሁ ሕግ ቁጥር 73 ና 74 ድንጋጌዎች የሚያስቀምጡ ሲሆን ተከሳሹ ባልቀረበ ጊዜ ደግሞ ጉዳዩ በሌለመበት የሚታይ ስለመሆኑ በተመሳሳይ የዚሁ ሕግ ቁጥር 70(ሀ) ያስቀምጣል፡፡

ክርክሩ የአካል ነጻነት መብትን ለማስከበር በሆነ ጊዜ እነዚህ የተከራካሪዎች አለመቅረብ የተጠቀሰው ውጤት አለው ወይ? የሚለውን ነጥብ ስንመለከት  በእርግጥ ይህንን ጉዳይ የሚመራው ከላይ የተገለጸው ልዩው ሕግ ከሳሹ ወይም ታሳሪው እና አሳሪው በአካል ፍ/ቤት መቅረብ ያለባቸው መሆኑን እንጂ ባልቀረቡ ጊዜ ውጤቱ ምን ይሆናል ስለሚለው ነገር ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡

ከዚህ ጋር በተገናኘ ከላይ እንደተገለጸው ሁለት ተቃራኒ ክርክሮች በዘርፉ ባሉ ባለሙያዎች የሚነሱ ሲሆን አንደኛው ወገን ክርክሩ ከፍትሐ ብሔር ክርክሮች መካከል አንዱ ስለሆነ የተከራካሪዎች አለመቅረብ ከላይ የተገለጸው ውጤት አለው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉ ሥነ-ሥርዓቶች እንደአግባብነቱ ታይተው ከሚተረጎሙ በቀር የጠቅላላውን የፍትሐ ብሔር ክርክር ላይ ያሉ የተከራካሪዎች አለመቅረብ ውጤት ለዚህ ጉዳይ ተፈጻሚ ማድረጉ የክርክሩን ልዩ ባህሪ ያገናዘበ አይደለም ይላሉ፡፡

በእርግጥ ሕጉ ግራ ቀኙ ፍ/ቤት እንዲቀርቡ አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ሥነ-ሥርዓት ሲዘረጋ ዋነኛ ዓላማው አሳሪው ያሰረውን ሰው ፍ/ቤት ይዞ እንዲያቀርበው ለማድረግ ስለመሆኑ የዚሁ ሕግ አንቀጽ 178 ድንጋጌ ሙሉ ይዘት ያስቀምጣል፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በሚቀጥለው ርእስ ስር በዝርዝር የምናየው ሆኖ  በዋነኛነት ግን ፍ/ቤቱ እስሩ ህገወጥ መሆኑን ካረጋገጠ አመልካቹን ያለ ተጨማሪ የአፈጻጸም ትእዛዝ ከእስር እንዲፈታ ለማስቻል ነው፡፡

በዚህም ተከሳሹ ባይቀርብ ውጤቱን በተመለከተ ምንም እንኳ ይህ ልዩ ድንጋጌ በግልጽ ምንም ነገር ባይል አቤቱታውን ከመመርመር አኳያ ግን ፍ/ቤቱ  የአመልካቹን ምስክሮች ሰምቶ ውሳኔ በነገሩ ላይ ሊሰጥ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ የሚያስቀምጥ ድንጋጌ አለው፡፡ ይኸውም የዚሁ ከላይ የተጠቀሰው ድንጋጌ  ንዑስ ቁጥር 2 ስንመለከተው ፍ/ቤቱ እስሩን በተመለከተ እንደ አስፈላጊነቱ ምስክሮችን ሰምቶ በጉዳዩ ላይ ሊወስን ይችላል በማለት ያስቀምጣል፡፡

እነዚህ ምስክሮች የአካል ነጻነት መብቱን ለማስከበር በሚቀርበው አቤቱታ ላይ የተጠቀሱ ምስክሮች ስለመሆናቸው ይኸው ድንጋጌው ያሳያል፡፡ አቤቱታዉም የአመልካቹ መሆኑም የሚሰሙት ምስክሮች የአመልካች እንደሆኑ መረዳት ያስችላል፡፡

ምስክሮች በሁለት የተለያዩ ምክንያቶች ሊሰሙ የሚችሉ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡ አንድም ተከሳሹ ቀርቦ እስሩ ሕጋዊ ነው ብሎ በተከራከረ ጊዜ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተከሳሹ ቀርቦ ስለ እስሩ ሁኔታ ክርክር ባላቀረበ ጊዜ ፍ/ቤቱ የእስሩን ሕጋዊነት ወይም ሕገወጥነት ለመለየት እንዲችል የአመልካቹን ምስክሮች ሊሰማ የሚችልበት ሁኔታዎች ናቸው፡፡

እንግዲ ፍ/ቤቱ የአመልካቹን ምስክሮች ሰምቶ የእስሩን ሕጋዊነት እና ሕገወጥነት ለማጣራት ልዩ ሕጉ የሚፈቅድለት ከሆነ ተከሳሽ መጥርያ ደርሶት ባይቀርብ እንደተባለው ጉዳዩን በሌለበት በማየት ሊወስን የሚችል ስለመሆኑ አመላካች ነው፡፡ ይህም የተከሳሽ መጥርያ ደርሶት ፍ/ቤት አለመቅረብ በዚህም ጉዳይ እንደ መደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክር ተመሳሳይ ውጤት እንዳለው የሚያስረዳን ነው፡፡ ማለትም ተከሳሽ ባይቀርብም ጉዳዩን በሌለበት በማየት ውሳኔ ሊሰጥ የሚገባዉ ይሆናል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ትንሽ ሊያወሳስበው የሚችለው ተከሳሽ ወይም አሳሪው ፍ/ቤት ቀርቦ አመልካቹን አላሰርኩም ወይም በእኔ እጅ የለም፤ ፍ/ቤት ላቀርበው አልችልም በማለት አመልካቹን  ይዞ ባልቀረበ ጊዜ ያለው ሁኔታ ነው፡፡  ይህ ጉዳይ በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክር ቢሆን ኖሮ ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ እየካደ ስለሆነ እና ከሳሽም ፍ/ቤት ስላልቀረበ ፍ/ቤቱ  ከላይ እንደተገለጸው መዝገቡን ሊዘጋው የሚገባ ነው፡፡

ይሁን እንጅ ይህ ክርክር ግን የአካል ነጻነትን ለማስከበር የቀረበ እንደመሆኑ መጠን ከሳሽ ሳይቀርብ ተከሳሽ ከቀረበ ፍ/ቤቱ የተከሳሽን ክርክር ሰምቶ መዝገቡን ሊዘጋው ይገባል ብሎ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ አያምንም፡፡ ምክንያቱም በመጀመርያ ደረጃ መብቱ የተገፋበት ሰው ፍ/ቤት ባይቀርብም ስለእሱ ሆኖ ክሱን ያቀረበው ሰው ፍ/ቤት የሚቀርብ ስለሆነ ከሳሽ የሆነው ሰው ፍ/ቤት ስላልቀረበ ብቻ የሕጉ መስፈርት አልተሟላም በሚል ሰበብ ብቻ መዝገቡ ሊዘጋ የሚችል አይደለም፡፡ በተጨማሪም  አመልካቹ ወይም ከሳሹ ፍ/ቤት እንዲቀርብ ያስፈለገበት ምክንያት ከላይ እንደተገለጸው በልዩ ምክንያት ስለሆነ (ከውሳኔው አፈጻጸም ጋር የተያያዘ ስለሆነ)  እና ፍ/ቤቱም የአመልካቹን ምስክር ከሚሰማባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ተከሳሹ አመልካቹን በሕገወጥ መንገድ ማሰር አለማሰሩን ለማጣራት ስለሆነ እንዲህ ባለው ሁኔታ አመልካች ባይቀርብም ምስክሩ ተሰምቶ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዳይሰጥ ከልካይ ሁኔታ የለም፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ እንደሚታወቀው ፍርድ ቤቶች እንደ አንድ የመንግስት አካል በሕገ-መንግስቱ  እውቅና የተሰጣቸውን የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የማክበር እና የማስከበር ሕገ መንግስታዊ ግዴታ በአንቀጽ 13(1) መሰረት አለባቸው፡፡ ከዚህ ከፍርድ ቤቶች ግዴታ ጋር በተገናኘም  የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት  በሰ/መ/ቁ 230167 ሀምሌ 28 ቀን 2014 ዓ/ም በሰጠውን አስገዳጅ ውሳኔም ፍርድ ቤቶች ያለባቸዉ ግዴታ ተፈጥሯዊ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ይህም ማለት ፍ/ቤቶች ከተቋቋሙበት አላማ መካከል የሰብዓዊ መብቶችን ማክበር እና ማስከበር አንዱ ነው ማለት ስለመሆኑ እሙን ነው፡፡

ፍ/ቤቶች ከሌሎች ጉዳዮች በተለየ በሕገ-መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸውን ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ እና እንዲያስከብሩ ግዴታ ያለባቸው መሆኑ ደግሞ ጉዳዩ መብቱ የተገፋበት ሰው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አንዱ የሕግ የበላይነት በሀገሪቱ መኖሩ ማረጋገጫ (የሁሉም ጉዳይ) ስለመሆኑ ያሳየናል፡፡ ስለሆነም ከሳሽ ፍርድ ቤት ስላልቀረበ ብቻ መዝገቡ በተከሳሽ ክርክር ላይ ተመስርቶ ወድያው የሚዘጋ ከሆነ ጉዳዩ የከሳሽ ጉዳይ ብቻ ከማድረጉም በላይ ፍ/ቤቶች ይህ ከላይ የጠቀስነውን ሕገ መንግስታዊ ግዴታቸውን እንይወጡ የሚያደርጋቸዉ ይሆናል፡፡

ፍ/ቤቱ የአመልካችን ምስክሮች ሰምቶ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ጉዳዩን የሚመራው ልዩ የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ክፍል መፍቀዱ እና ከላይ በዝርዝር ከተጠቀሱት ምክንያቶች  በጋራ ስንመለከታቸው ከሳሽ ሕጉ ባስቀመጠው መልኩ ፍ/ቤት ባይቀርብ እንኳ ፍ/ቤቱ አቤቱታው እስከቀረበለት ድረስ በእርግጥም ተከሳሹ አመልካቹን ማሰር አለማሰሩን እንዲሁም አስሯል የሚባል ከሆነ እስሩም ሕጋዊ ወይም ሕገወጥ መሆኑን በማጣራት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሊሰጥበት የሚገባ መሆኑ ሊታመንበት ይገባል፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሌላው በዋናነት መታየት ያለበት ነጥብ ፍ/ቤቶች ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር እና የማስከበር ግዴታ አለባቸው ሲባል  አቤቱታው (ክሱ) ባይቀርብም ፍ/ቤቶች ሕገወጥ እስር መኖሩን ባረጋገጡ በማንኛውም ጊዜ( ማለትም በሌላ የክርክር ሂድት ሕገወጥ እስር መኖሩን በተረዱ ጊዜ ሁሉ)  ይህን ጉዳይ በራሳቸው ተነሳሽነት በመመልከት ውሳኔ ሊሰጡበት ይችላሉ ማለት ነው ወይ? የሚለው ነጥብ ሲሆን ይህንን ነጥብ በተመለከተ አንባቢው የራሱን አቋም እንዲይዝበት የምተወው ይሆናል፡፡ ይሁንና አንድ በመሰረታዊነት ሊታወቅ የሚገባዉ  ጉዳይ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርም ሆነ የማስከበር ጉዳይ የፍርድ ቤቶች ሥነ-ሥርዓታዊ ግዴታ መሆኑን ነው፡፡  የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ክርክሩ የሚመራበትን ልዩ ሥርዓት መዘርጋቱም የጉዳዩን ሥነ-ስርዓታዊነት ያረጋግጣል፡፡ ይህም ሌላኛው የዚህ ክርክር ከመደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክሮች የሚለይበት ልዩ ሥነ-ሥርዓት መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት የሚችል ነው፡፡

  1. የአፈጻጸም ክስ የሌለው መሆኑ

እንደሚታወቀው በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት አልፈው ፍርድ ያረፈባቸው ጉዳዮች ሊፈጸሙ የሚችሉት በሕጉ መሰረት የአፈጻጸም ክስ ሲቀርብባቸው ብቻ ነው፡፡ ይኸውም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 371 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎችን ስንመለከታቸው አንድ በፍትሐ ብሔር ክርክር ፍርድ የተሰጠው ሰው የፍርድ ባለዕዳው እንደ ውሳኔው ሊፈጽምለት ያልፈቀደ ከሆነ ፍርዱን ለሰጠው ፍ/ቤት የአፈጻጸም ክስ በማቅረብ ሊያስፈጽም እንደሚችል ያስቀምጣሉ፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች  የፍርድ ባለእዳው ፈቃደኛ ሆኖ ፍርዱን ከፍርድ ቤት ወጪ እስካልፈጸመ ድረስ ፍርድ ሊፈጸም የሚችለው የአፈጻጸም ክስ ሲቀርብ ብቻ መሆኑን የሚያስቀምጡ ናቸው፡፡

ይህ ጉዳይ ግን የአካል ነጻነት መብትን ለማረጋገጥ ለፍ/ቤት በሚቀርቡ የፍትሐ ብሔር ክርክሮች ላይ በሚሰጡ ፍርዶች ላይ ተፈጻሚነት ያለው አይደለም፡፡ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 179(2) ላይ ይህ ፍርድ ያለ ተጨማሪ ትእዛዝ የሚፈጸም ስለመሆኑ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ይህም ማለት ፍርድ ቤቱ በክርክሩ ሂደት በእርግጥም ተከሳሽ አመልካቹን ሕገወጥ በሆነ መንገድ ማሰሩን ካረጋገጠ እና አመልካቹ ከእስር ሊፈታ ይገባል ብሎ ውሳኔ ከሰጠ አሳሪው በዚሁ ውሳኔ መሰረት አመልካቹን ወድያውኑ እንዲፈታው ይገደዳል ማለት ነው፡፡

ሕጉ ፍ/ቤቱ አመልካቹ እንዲለቀቅ ወድያውኑ ትእዛዝ የሚሰጥ መሆኑን የሚያስቀምጥ ሲሆን ጉዳዩ እንደ መደበኛ ፍትሐ ብሔር ክርክር ቢታይ ኖሮ አመልካቹ ይህንን ውሳኔ ለማስፈጸም በአዲስ ፋይል የአፈጻጸም ክስ ሊያቀርብ በተገባ ነበር፡፡ ይሁንና ሕጉ በግልጽ ሌላ ተጨማሪ ትእዛዝ ሳያስፈልግ ተከሳሹ አመልካቹን እንዲፈታው ይገደዳል ማለቱ በራሱ በግልጽ ለዚህ ጉዳይ የሥነ-ሥርዓት ሕጉ 371 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት እንደሌላቸው የሚያሳየን ነው፡፡ ስለሆነም የተሰጠው ውሳኔ ወድያው የሚፈጸም መሆኑ ደግሞ  ይርክሩ ሌላኛው ልዩ ሁኔታ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

  1. ክሱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 205 መሰረት በቃለ መኃላ ተረጋግጦ ሊቀርብ የሚገባው ስለመሆኑ

በመደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክር መሰረት የሚቀርቡ ክሶች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 92 መሰረት በክሱ ላይ የተጠቀሰው ፍሬ ነገር እውነት ስለመሆኑ በሚመለከተው ሰው እንዲረጋገጡ እንጂ ክሱ በራሱ በቃለ መኃላ ተረጋግጦ እንዲቀርብ ሕግ አያስገድድም፡፡ በእርግጥ ይህ አንዱ የመደበኛው የፍትሐ ብሔር ክርክሮች የክስ አቀራረብ ፎርም ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ይሁንና ክሱ የአካል ነጻነት መብትን ለማስከበር የሚቀርብ ክስ በሆነ ጊዜ ሕጉ በክሱ ላይ የተጠቀሰው ነገር እውነት ስለመሆኑ እንዲረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ክሱ ተገቢው ቃለ መኃላ ተፈጽሞበት የሚቀርብ ስለመሆኑ ያስቀምጣል፡፡ ይኸውም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 177(2) ድንጋጌ በግልጽ ማመልከቻው በመኃላ ቃል የተደገፈ ሊሆን የሚገባ ስለመሆኑ ማስቀመጡ አንዱ የክርክሩ ልዩ ሁኔታ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

  1. መብቱን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር ተያይዞ እየታዩ ካሉ አንዳንድ ነጥቦች አኳያ

ሀ፡- በወንጀል ተጠርጥረው በፍ/ቤት ዋስትና የተፈቀደላቸው ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ፤ የአካል ነጻነት መብታቸው እንዲከበር አዲስ የፍትሐ ብሐየር ክስ ሊያቀርቡ የሚገባ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ

እንደሚታወቀው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርዓት አንቀጽ 59 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎችን መሰረት አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ሰው የወንጀል ምርመራው እስኪደረግ ድረስ በፍርድ ቤቶች ትእዛዝ በእስር እንዲቆይ ይገደዳል፡፡ በዚህ የወንጀል ምርመራ ሂደት ፍ/ቤቱ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ መስጠት ባላስፈለገ ጊዜ ወይም ደግሞ ምርመራው እንዲደረግ ተጠርጣሪው የግድ በእስር እንዲሆን ያስፈልጋል ብሎ ባላመነ ጊዜ ተጠርጣሪውን በዋስትና እንዲፈታ ለማዘዝ የሚችል ስለመሆኑ እነዚሁ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ያስቀምጣሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ሊታይ የሚገባው ነጥብ ተጠርጣሪው ዋስትናውን አሟልቶ አቅርቦ እያለ የወንጀል ምርመራውን እያጣራ ያለው የፖሊስ አካል  ከእስር ሊለቀው ፍቃደኛ ባይሆን ውጤቱ ምን ይሆናል? የሚለው ነጥብ ነው፡፡ 

ከዚህ ጋር ተያይዞም  ከላይ እንደተገለጸው በዚህም ጉዳይ ላይ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች በዘርፉ ባሉት ባለሙያዎች ይነሳሉ፡፡ የመጀመርያው ሀሳብ ተጠርጣሪው ከእስር እንዲፈታ የግድ የአካል ነጻነት መብቱ እንዲከበር  ክስ ሊያቀርብ አያስፈልገውም፡፡ ይልቁንም  ትእዛዙን ለሰጠው ፍ/ቤት ትእዛዙ አለመከበሩን ገልጾ አቤቱታ ማቅረብ አለበት ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠርጣሪው ፖሊስ ከእስር ሊለቀው ካልፈቀደ  የአካል ነጻነቱን ለማስከበር  የፍትሐ ብሔር ክርክር ሊያቀርብ ይገባል ይላሉ፡፡

በእርግጥ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ፍ/ቤቶች በተለይም የፍትሐ ብሔር ክርክሮች አስመልክቶ ዳኝነት ሊሰጡ የሚችሉት ክስ ወይም አቤቱታ ቀርቦ ዳኝነት ሲጠየቁ ብቻ ስለመሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የፍ/ቤቶች አንድን ጉዳይ በሕጉ አግባብ ተመልክተው የሚሰጡት ትእዛዝ ወይም ውሳኔ  ደግሞ መከበር ያለበት እስካልተሻረም ሆነ እስካልተለወጠ ድረስ ተፈጻሚነት እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በመሰረቱ ይህ አባባል ብቻ ሳይሆን የፌድራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1234/2013  በአንቀጽ 51(1) ላይ ያስቀመጠው ሕጋዊ ግዴታ ሲሆን ድንጋጌው በግልጽ ማንም ሰው እንዲሁም  በየትኛውም አገሪቱ ክልል ውስጥ የሚገኝ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም  የፍ/ቤቶችን ትእዛዝ ሊያከብር የሚገባው ስለመሆኑ የሚያስቀምጠው ነው፡፡  አዋጁ የፍ/ቤቶችን ትእዛዝ እና ውሳኔዎችን የማክበርን ነገር በግዴታነት ከማስቀመጡም በላይ ትእዛዙን አለማክበር የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ስለመሆኑም በአንቀጽ 52 ድንጋጌው ላይ በግልጽ አስቀምጦት እናገኛለን፡፡

ከዚህም ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ተጠርጣሪ ፍ/ቤቱ የፈቀደለትን ዋስትና እስካሟላ ድረስ ከእስር ሊፈታ የሚገባው መሆኑን ሲሆን አሳሪው አካልም ቢሆን ይህንኑ ተመልክቶ ታሳሪውን ከእስር በመልቀቅ የፍ/ቤቱን ትእዛዝ ሊያከብር እንደሚገባ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ አሳሪው አካል ይህንን ካላደረገ ደግሞ የፍ/ቤቱን ትእዛዝ እያከበረ አለመሆኑን ማሳያ ይሆናል፡፡

እንዲሚታወቀው አንድ የፍ/ቤት ትእዛዝ መከበር አለመከበሩን ደግሞ ሊመረምር እና ተገቢው ውሳኔ ሊሰጥበት  የሚገባው ትእዛዙን በሰጠው ፍ/ቤት መሆኑን የምንረዳው ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ሲታይ ፍ/ቤት በዋስ የለቀቀውን ሰው የአካል ነጻነትህ እንዲከበር አዲስ የፍትሐ ብሔር ክርክር አቅርበህ የአካል ነጻነት መብትህን አስከብር የሚባል ከሆነ ፍ/ቤቱ እራሱ የሰጠው ትእዛዝ በሌሎች ተቋማት እንዳይከበር ተባባሪ ከመሆን ያለፈ ሌላ ትርጉም የሚሰጠዉ አይሆንም፡፡

በመሰረቱ የፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉን አንቀጽ 177 (1) ድንጋጌን ስንመለከተው የአካል ነጻነት መብት ክርክር በወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የነበረን ተጠርጣሪ የማይመለከተው መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ሕጉ በግልጽ ክሱን ማን ያቀርበዋል የሚለውን ለይቶ ያስቀመጠ ሲሆን ይኸውም በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ መሰረት ፍ/ቤት ሳይወስንበት ወይም ሳይፈርድበት የአካል ነጻነት መብቱ የተገደበበት ሰው የአካል ነጻነት መብቱ እንዲከበር ክስ ያቀርባል በማለት ያስቀምጣል፡፡

ይህ ሕግ እና ሕግ አውጪው አካል ሰዎች ለወንጀል ምርመራ ተብሎ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሰርዓት ሕጉ መሰረት በፍ/ቤት ትእዛዝ  በእስር እንዲቆዩ የሚገደዱ መሆኑ ይጠፋዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሕጉ በዚሁ አግባብ ሰዎች ሊታሰሩ እንደሚችል እያወቀ ግን ደግሞ ክርክሩን ማቅረብ ያለባቸው በወንጀለኛ መቅጫ  ሕጉ መሰረት ፍ/ቤት ሳይወስንባቸው የመዘዋወር መብታቸው የተገደበባቸው ሰዎች ናቸው  በማለት ለይቶ ማስቀመጡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት ዋስትና የተከበረላቸው ሰዎች ይህንን ክርክር ማቅረብ ሳያስፈልጋቸዉ ሊፈቱ ይገባል ብሎ ስላመነ ስለመሆኑ እሙን ነው፡፡ ምክንያቱም ህግ አውጪው አካል እነዚህ ሰዎች ይህንን ክርክር እንዲያቀርቡ ቢፈልግ ኖሮ አቤቱታውን እንዲያቀርቡ ከለያቸው ሰዎች መካከል በግልጽ ለይቶ ያስቀምጣቸው ነበር፡፡ ስለሆነም አለመካተታቸው በራሱ የአካል ነጻነት መብታቸው ዋስትናውን በፈቀደላቸው የጊዜ ቀጠሮ ፍ/ቤት ይረጋገጣል ብሎ ያመነ መሆኑን ያሳየናል፡፡

በመሆኑም ሕጉ ፍ/ቤቶች የሰጡት ትእዛዝ በሁሉም ተቋማት እንዲከበር በማስገደድ ያስቀመጠ በመሆኑ እና በተለይም የአካል ነጻነት መብት እንዲከበር ክስ የሚያቀርቡ ሰዎች በመን ሁኔታ ታስረዉ የሚገኙ  እንደሆኑ በሕግ ተለይቶ የተቀመጠ መሆኑ ሲታይ በወንጀል ተጠርጥረው በፍ/ቤት ዋስትና የተፈቀደላቸው ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ የግድ አዲስ የፍትሐ ብሔር ክርክር ሊያቀርቡ ይገባል ብዬ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ አላምን፡፡  

ይህ ክርክር በወንጀል ተጠርጥረው ዋስትና የተፈቀደላቸውን ሰዎች ካልተመለከተ ታድያ ማንን ነው የሚመለከተው  የሚል ነጥብ መነሳቱ አይቀርም፡፡ እንደሚታወቀው ከመያዝ ጋር ተያይዞ ሕጉ አንድን በወንጀል የተጠረጠረን ሰው እንዲይዝ የሚፈቅድለት ለፖሊስ ተቋም ብቻ ሳይሆን ለግለሰቦችም ጭምር ነው፡፡ ይኸውም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ-ሥርኣት በአንቀጽ 50 ላይ የእጅ ከፍንጅ ወንጀል ሲፈጽም የተገኘን ሰው እንዲይዝ ለፖሊስ ተቋም ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ግለሰቦች መብት የሚሰጥ ስለመሆኑ የድንጋጌው ንዑስ አንቀጽ (1) ያስቀምጣል፡፡  ይሁንና ይህ ሰው ወንጀል ሲፈጽም ያገኘውን ሰው ለፈለገው ጊዜ ያህል ይዞ ሊያቆየው አይችልም፡፡ ሕጉ ግለሰቦች ወንጀል ሲፈጽሙ ያገኟቸውን ሰዎችን የመያዝ መብት የሰጠ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች የያዟቸውን ሰዎች በእጃቸው ሊያቆዩ የሚችሉበትንም ጊዜ ያስቀመጠ ስለመሆኑ ከድንጋጌው ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡

እነዚህ ሰዎች በሕጉ ላይ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ የያዟቸውን ሰዎች ለሚመለከተው የሕግ አካል የማያስተላልፉ ከሆነ ድርጊታቸው ሕገወጥ ስለመሆኑ መረዳት የሚቻል ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተያዙ ሰዎች የአካል ነጻነት መብታቸው እንዲከበር ለፍ/ቤት ሊያመለክቱ የሚችሉ ሲሆን ይህም አንዱ የአካል ነጻነት መብት ክርክር የሚቀርብበት ሁኔታ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በሌላ በኩል በወንጀል ተጠርጥረው በሚመለከተው የመንግስት አካል የተያዙ ነገር ግን ለጊዜ ቀጠሮም ቢሆን ፍ/ቤት እየቀረቡ ያልሆኑ ሰዎችም ካሉ ይህም እስር ሕገወጥ በመሆኑ እነዚህም ሰዎች የአካል ነጻነት መብታቸው እንዲከበር የተባለውን የፍትሐ ብሔር ክርክሩን ሊያቀርቡ የሚችሉ ናቸው፡፡

ሲጠቃለል በወንጀል ተጠርጥረው ተይዘው የነበሩ በኋላም በፍርድ ቤት ዋስትና የተፈቀደላቸው ሰዎች ዋስትናውን አሟልተው እስከቀረቡ ድረስ የፍ/ቤቱ ትእዛዝ ተከብሮ ከእስር ሊፈቱ የሚገባ ሲሆን ይህ ባልሆነ ጊዜ ግን ግለሰቦቹ አዲስ የፍትሐ ብሔር ክርክር ማቅረብ ሳያስፈልጋቸው ዋስትና ለፈቀደላቸው ፍ/ቤት ጉዳዩን አመልክተው ትዕዛዙ እንዲፈፀም ሊደረግ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡

     

 ለ፡-  ከፍርድ ቤት የሥረ- ነገር ስልጣን አኳያ

የአካል ነጻነት መብት አንዱ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 17 ላይ እውቅና የተሰጠው መብት ስለመሆኑ ከላይ የተገለጸ ነው፡፡ ይህ የሕገ-መንግስቱ ድንጋጌ ደግሞ በዚሁ ሕገ- መንግስት በምዕራፍ ሶስት ውስጥ የሚካተት ስለመሆኑ ሕገ-መንግስቱን በመመልከት ለማረጋገጥ የሚቻል ነው፡፡ እንደሚታወቀው የፍርድ ቤቶች ስረነገር ስልጣን ደግሞ የሚወሰነው በሕግ መሰረት ሲሆን እነዚህ የሕገ-መንግስቱን ምዕራፍ ሶስት ላይ የተቀመጡ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብት ድንጋጌዎችን የመተላለፍን ጉዳይ በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 11(3) መሰረት የማከራከር የሥረ-ነገር ስልጣኑ የፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡

ይሁንና የአካል ነጻነት መብትን በተመለከተ ግን  የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ  230167 ሀምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም በሰጠው የሕግ ትርም ጉዳዩን አከራክሮ የመወሰን የሥረ-ነገር ስልጣኑ የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍ/ቤት ነው ብሏል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠውን ውሳኔ ስንመለከተው በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተመለከቱ በፍርድ ቤት ታይተዉ ሊወሰኑ የሚችሉ መብቶች ጋር በተገናኘ የሚቀርብ ክስ በፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 11(3) መሰረት  የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ  ቤት ስልጣን ቢሆንም ተገዶ መያዝን ለማጣራት የሚቀርብ ክስ በአዋጁ በአንቀጽ 11(1) ላይ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በግልጽ የሥረ- ነገር ስልጣን ከሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል ተዘርዝሮ አለመካተቱ ሕግ አውጪው ጉዳዩ በቀድሞውን አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 25/88 መሰረት ጉዳዩ በፌደራል የመጀመሪ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታይ መፈለጉን ያሳያል በማለት ተገዶ የመያዝን ሕጋዊነት ለማጣራት የሚቀርቡ ክሶችን አከራክሮ የመወሰን የሥረ-ነገር ስልጣኑ የፌደራል መጀመሪ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው በማለት ውሳኔውን መስጠቱ ከውሳኔው ይዘት መረዳት የሚቻል ነው፡፡

ይሁን እና የአዋጁ በአንቀጽ 11(5) ድንጋጌ ስንመለከተው በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት የተመላከቱ መብት እና ነጻነትን የተመለከቱ ክርክሮችን በከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲታዩ ሲቀርቡ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ሲመለከት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 176-179 ያሉ ድንጋጌዎችን እንደ አስፈላጊነቱ ተግባራዊ ያደርጋል በማለት አስቀምጧል፡፡ ይህ ደግሞ አዋጁ ተገዶ የመያዝን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ የሚቀርብ ክስ እንደ አንድ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት ውስጥ እንደተካተተ የሰብዓዊ መብት  በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይታያል ማለቱ አልነበረም ወይ የሚል ጥያቄን የሚፈጥር ቢሆንም ነገር ግን ይህ የሰበር ሰሚ  ፍ/ቤቱ ውሳኔ በየትኛውም የሀገሪቱ ፍ/ቤቶች ላይ ገዢነት ያለው እንደመሆኑ መጠን በውሳኔው መሰረት ጉዳዩን የማከራከር ስልጣኑ የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍ/ቤት በክልሎች ሲሆን ደግሞ ተገቢው ህገ መንግስታዊ የፌድራል ፍርድ ቤቶች ህገመንግስታዊ ስልጣን ያለው የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሲጠቃለል ለፍርድ ቤቶች ቀርበው ክርክር ከሚደረግባቸው የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነዉ የአካል ነጻነት መብትን ለማስከበር (ተገዶ የመያዝን ሕጋዊነት ለማጣራት)   የሚቀርብ የፍትሐ ብሔር ክርክር ሲሆን ከሌሎቹ የመደበኛ የፍትሐ ብሔር ክርክሮች ክሱ ከሚቀርብበት፣ክርክሩ ከሚመራበት እና ዉሳኔዉ የሚፈፀምበት ሥርዓት ከላይ የተገለጹ የተለዩ ሂደትን የሚከተል ነዉ፡፡ ሂደቱም ፍርድ ቤቶች በሕገ-መንግስቱ የተቀመጡ ሰብዓዊ መብት እና ነፃነቶችን በማስከበር ረገድ ከፍተኛ የሆነ ሚና እንዳላቸዉ የሚያሳይ ሲሆን የእነዚህ መብቶች መከበርም ከፍርድ ቤቶች ህገመንግስታዊ እና ሥነ-ሥርዓታዊ ግዴታ ጋር የተገናኘ መሆኑን የሚያሳየን ነው።