Font size: +
3 minutes reading time (526 words)

ጠበቆች ሊለይዋቸው የሚገቡ አራት የደንበኛ ዓይነቶች - “ጀማሪ” ደንበኛ

ጠበቆች ከደንበኞቻቸው፣ ከፍርድ ቤት፣ ከፍትሕ ሥርዓት እና ከሌሎች የሥራ ባልደረቦች(ጠበቆች) ጋር ያላቸው ግንኙነት ለጥብቅና ሙያ ሥነ-ምግባር መሠረት ሲሆኑ እነዚህን ግንኙነቶች ጠንቅቆ መረዳት የጥብቅና ሙያ ኃላፊነትን በአግባቡ ለመረዳት ይረዳል።

ይህ ጽሑፍ ጠበቆች ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለመረዳት የሚያስችል ስለደንበኞች ዓይነቶች ለመጠቆም የተዘጋጀ ነው። በዚህ ጽሑፍ የምድብ አንድ የደንበኛ ዓይነት “ጀማሪ ደንበኛ/ባለጉዳይ” የሚለውን ለማየት እንሞክራለን። ምንም እንኳን ሁሉም ደንበኞች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አራት ምድቦች ውስጥ በትክክል የሚገጣጠሙ ባይሆንም ደንበኞች ከሚያሳዩት ጸባይ እና ተነሳሽነት ደንበኞችን በአራት መመደብ ይችላል።

የጠበቃ እና የደንበኛ ግንኙነት የሚመሰረተው ጠበቃ የጠበቃ አገልግሎትን ለሚፈልግ ሰው የሕግ እርዳታ ለመስጠት ሲስማማ ነው። የጠበቃ-ደንበኛ ግንኙነት ብዙ ገፅታዎች ያሉት ሲሆን ደንበኞችን አስመልክቶ ሁለቱ መሠረታዊ የጠበቃ ግዴታዎች ብቃት ያለው የሙያ አገልግሎት መስጠትና እና ይህንን ተግባር በትጋት የመሥራት ኃላፊነት ናቸው።

ጠበቆች የደንበኛ ዓይነቶችን መረዳታቸው ለደንበኞች አያያዝ እና አስተዳደር ጠቃሚ ችሎታን ይጨምርላቸዋል። የተለያዩ ደንበኞችን ጸባይን መረዳት ዓመታትን ሊወስድ ይችላል፣ ስለዚህ ከተለመዱ ደንበኞች በስተጀርባ ያሉትን መሠረታዊ ነገሮች ማወቅ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

  1. ጀማሪደንበኛ

ይህ ባለጉዳይ ከጠበቆች ጋር ልምድ የሌለው ነው፤ በመሆኑም ስለሕግ፣ ስለሚጠይቀው ወይም ስለሚጠየቀው ጉዳይ፣ ስለፍርድ ቤት፣ ስለጠበቃና ደንበኛ ግንኙነት የሚየውቀው ነገር የለም። በአጠቃላይ ይህ ባለጉዳይ ለሕግ ዘርፉ አዲስ ነው። በዚህም ምክንያት ሕግ እና ለሕግ ሥነ-ሥርዓት ፍርሐት አላቸው። በጉዳዩ በደረጃው ሁሉ ሁሉንም ነገር ማየት እና መጠየቅ ይፈልጋሉ፤ በትንሽ ነገር ይደሰታሉ፤ በጥቃቅን ነገር ይበሳጫሉ።

እንዲህ ዓይነቱን ባለጉዳይ መረዳት አስፈላጊ ነው። ጉዳያቸው ቀላል እና አስደሳች ቢሆን እንኳን እነዚህ ባለጉዳዮች በጣም አድካሚና አሰልቺዎች ናቸው። እንደዚህ ዓይነት ደንበኞችን ለመርዳት ምርጡ መንገድ ሁሉንም ነገር በዝርዝር ማብራራት ነው። ለሕጻን ልጅ እንደማስረዳት ሁሉንም ነገር ማስረዳት ተገቢ ነው። ለዚህ ነው እንደዚህ ዓይነት ደንበኞች አድካሚና አሰልቺዎች የሚሆኑት። በእያንዳንዱ ደረጃ በትዕግስት ነገሮችን ማብራራት ያስፈልጋል፤ በዚህ ደረጃ ነገሮችን ካላብራሩ ስለጉዳዩ መሠረታዊ የሆነ መረጃ እንኳን ለማግኘት ይቸገራሉ፤ እና ለጉዳይዎ ተጨማሪ መረጃ የሚያመጡልዎትን ጥያቄዎችን ለማንሳት እድሉን የሚያገኙት በየደረጃው በሚደረግ ማብራሪያ ነው። ይህንን ማብራሪያ የማያደርጉ ከሆነ እንደ ደካማ ጠበቃ ይቆጠራሉ።

ስለጉዳዩ በዝርዝር የሚጠየቁትን ትተን የሚከተሉትን አሰልቺ ጥያቄዎች ለመመለስ መዘጋጀት አለብዎት፦

ክሱ ለምን እዚህኛው ፍርድ ቤት ሆነ? ለምን የዳኝነት ይከፈላል? ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለማየት እንደጠበቃ ገንዘብ ይቀባለል? አይቀንስም? ይህንን ክፍያ በኋላ ፍርድ ቤቱ ይመልስልኛል? ስንት ዳኞችና ናቸው ጉዳዩን የሚያዩት? በስንት ጊዜ ውሳኔ ይሰጣሉ? ውሳኔ የሚሰጥበት ቁርጥ ያለ ጊዜ ልትነግረን ትችላለህ? ከዳኞችም ሱፍ ለምን አይለብሱም? ለምን ዳኛው ቢሮ ውስጥ ጠራህ/አስተናገደህ? ፍርድ ቤቶች ሽንት ቤት የላቸውም? ፍርድ ቤቱ የቀጠረን ሰዓት ለምን አያከብርም? ለምርመራ ምን ማለት ነው? አሁንም ቀጠሮ? ቃል ክርክር ምን ማለት ነው? አዲስ ማስረጃ ማስገባት አይቻለም? ለምን ዳኛው ጋር ሔደን በዝርዝር ጉዳዩን እንዲረዳ አናደርገውም? ጉዳዩን የሚያየው አንድ ዳኛ ብቻ ነው? ለምን ሌሎች ዳኞች አላዩትም? ችሎት ጸሐፊ ምንድነው? ሬጂስትራርስ? አቤቱታ ምንድነው? የአቤቱታ ቀን ለምን ሁሉ ጊዜ አይሆንም? ጠበቆች ለምን ፕሮቶኮል አይጠብቁም? ጠበቆችም እንደባለጉዳይ ነው ሚታዩት? ጠበቃዬ እስከሆንክ ለምን ይህንንም ጉዳይ አታማክረኝም? ከተከራካሪ ወገን ጠበቃ ጋር ለምን ትነጋገራለህ? ጉዳዩን ለምን በዝርዝር ለፍርድ ቤቱ አልተናገርክም? ሌላኛው ጠበቃ ሁለቴ ተናግሮ አንተ አንድ ጊዜ ብቻ ለምን ተናገርክ? ስልክህን ለምን አታነሳም? በፈለኩህ ጊዜ ላገኝህ አልቻልኩም፥ ምን ይሻላል? ………. ወዘተ

እነዚህና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እየመለስክ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ባለጉዳዩንም ስለሕግ እና ስለሥነ-ሥርዓት እያሰለጠንክ ካልሔድክ መጨረሻህ አያምርም። ጀማሪ ደንበኞች/ባለጉዳዮች ከላይ የተመለከተው አንድ የሚያደርጋቸው ጸባይ ቢኖርም የተለያዩ ዓይነቶች ናቸው። ለምሳሌ፦ እርግጠኛ ያልሆኑ ባለጉዳዮች፣ አጣዳፊ ባለጉዳዮች፣ ምላሽ የማይሰጡ ባለጉዳዮች፣ ከእውነት የራቁ ባለጉዳዮች፣ ስሜታዊ ባለጉዳዮች፣ ስለወጪ በጣም የሚጨነቁ ባለጉዳዮች፣ ስራዎን በቅርበት የሚከታተሉ ባለጉዳዮች፣ ቆራጥ ወይም አጋዥ ባለጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ።

በመሆኑም ባለጉዳይዎ ጀማሪ መሆኑን የተረዱ እንደሆነ በዋናው ጉዳይ ላይ ከሚያጠፉት ጊዜ በላይ እንደባለጉዳዩ ዐይነት ዝርዝር ምላሽ መስጠት እና ባለጉዳዩን መያዝ እንዴት እንዳለበዎት መረዳት ያስፈልጋል።

ሁለተኛ ዐይነት ደንበኞችን በቀጣይ ጽሑፍ አቀርባለሁ። 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥትን በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ለማሻሻል ብቸኛው መንገድ፡- ...
ጋብቻ በሚፈርስበት ወቅት የባልና ሚስት የንብረት ክፍፍል ሥነ-ሥርዓት ከሰበር ው...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Monday, 24 June 2024