Font size: +
18 minutes reading time (3578 words)

ሐሰተኛ ደረሰኝ - ገቢዎች ሚኒስቴር እራሱ በድሎ እራሱ አለቀሰ !

“In the Judgment alone is to be found the law in its living form.”

“ሕግ ህያው በሆነ ቅርጹ የሚገኘው በፍርዶች ውስጥ ብቻ ነው”  Marcel Planiol

መታሰቢያነቱ. ይህ ጽሑፍ መታሰቢያነቱ ለማከብረው፣ ለሕግ ሥርዓቱ ዕድገት ላበረከተው አስተዋጽኦ ማመስገን ለምፈለገው እና ሁሌም በሥራዎቹ ለምማረው፣ ዕንቁ ለነበረው የሀገራችን የሕግ ምሁር ዩሐንስ ኅሩይ ይሁንልኝ!!!

መነሻ ክስተት

የኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ድርጅት የሆነውን ተቋም እና ሥራ-አስኪያጁን ከ2003-2005 በነበረው የግብር ዘመን ድርጅቱ ሊከፍል ከሚገባው የግብር መጠን እንዲቀንስለት እና መክፈል የሚገባው የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲቀንስ በማሰብ በሌሎች ግለሰቦች ስም የተዘጋጁ እና ግዢ ያልተፈጸመባቸው ሕገ-ወጥ እና ሐሰተኛ ደረሰኞችን በማቅረብ ወጪን እና የግብዓት ታክስ በማናር ወንጀል ፈጽመዋል በማለት በገቢ ግብር አዋጅ 286/94 አ.ቁ 96፣ 97፣ 49፣ 102 እና በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁ 285/94 አ.ቁ 49 እና 50ድንጋጌዎችን ጠቅሶ በ7 የወንጀል ዓይነቶች ክስ በማቅረቡ ነው፡፡

ተፈጽሟል በማለት ላቀረበው የወንጀል ድርጊትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሁለት ኦዲተሮቹን በምስክርነት አስቀርቦ የተወሰኑ ደረሰኞች ሐሰተኝነት ስለመሆናቸው ያስመሰከረ ሲሆን የተቀሩት ደረሰኞች ደግሞ ተሰጡ የተባሉት በግብር ወንጀል ጥፈተኛ ተብለው እየተፈለጉ ካሉ ግለሰብ በመሆኑ የሰዎቹን ወንጀለኝነት የኮንስትራክሽን ድርጅቱም ማወቅ እየተገባው በቸልተኝነት ያደረገው ድርጊት በመሆኑ ደረሰኞቹ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደ ሕገ-ወጥ የሚቆጠሩ መሆናቸውን አስመስክሯል፡፡ በተመሳሳይም ደረሰኙ በስማቸው ተሰራ የተባሉ ግለሰቦች የዐቃቤ-ሕግ ምስክር በመሆን የተሰማሩበት ሞያ እና በስማቸው የቀረበው ደረሰኝ የተለያየ መሆኑን፣ ከተከሳሽ ድርጅት ጋር ግብይት ያልፈጸሙ ስለመሆኑ እና ደረሰኞቹም የእነርሱ አለመሆኑን በማስረጃነት ቀርበው አስረድተዋል፡፡

በተከሳሽ ድርጅት የቀረቡት ምስክሮች ደረሰኞቹን በዓመታዊ የግብር ዘመን በ2003-2005ዓ.ም ወቅት ያስረከቡ መሆኑን በጊዜው የእነዚህን ደረሰኞች ሐሰተኛ እና ሕገ-ወጥነት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ስላለመግለጹ በተለይም ደግሞ ከእነዚህ ሐሰተኛ ከተባሉ ደረሰኞች የተሰበሰቡ የተጨማሪ እሴት ግብር ክፍያዎችን መንግሥት ክፍያ የተቀበለ ሆኖ ሳለ ገንዘቡን ተጠቅሞ ጥፋቱን ወደ ድርጅቱ ማምጣቱ አግባብ አለመሆኑ ፣ ድርጅቱ ደረሰኞቹ ሐሰተኛ እና ሕገ-ወጥ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚችልበት ምንም ዓይነት የተዘረጋ ሥርዓት አለመኖሩን በመጥቀስ እና በደረሰኙ ግብይት ተፈጸመ የተባለባቸውን ዕቃዎች በግብዓትነት በግንባታው የተጠቀማቸው መሆኑን በሰነድ ማስረጃ አረጋግጦ እና ምስክሮች አቅርቦ ተከራክሯል፡፡

ጉዳዩን ሲመረምረው የነበረው ፍ/ቤትም በኮንስትራክሽን ደርጅቱ የቀረቡት ደረሰኞች ሐሰተኛ እና ሕገ-ወጥ መሆናቸው ተረጋግጧል ሲል በድርጅቱ ላይ የገንዘብ ቅጣት እና በሥራ-አስኪያጁ ላይ ደግሞ የእሥራት ቅጣት እንዲፈጸም ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

 

መግቢያ

የግማሽ ክፍለ ዘመን የሕግ እና የግብር ሥርዓት መሻሻል ውጤት የሆነው የኢትዮጵያ “ዘመናዊው የግብር ሕግ” መነሻ/መጀመሪያ ተደርጎ የሚወሰደው በ1933ዓ.ምበዋናነት በመሬትና በቀንድ ከብቶች ላይ ሲጣል የነበረው የግብር ሥርዓት ላይ ለውጥ መደረጉ ነው፡፡ (ዓለማየሁገዳ ”Reading on the Ethiopian Economy” AAU Press,2011,pp.189)በተጨማሪምበሀገሪቷየተከሰቱት የመንግሥታት መለዋወጥ፣ የመንግሥት የገቢ ፍላጎት መናር እና ዓለማቀፋዊ የኢኮኖሚ ሁኔታና የገንዘብ ተቋማት መመስረት ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የግብር ሥርዓት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡ (ታደሰ ሌንጮ “The Ethiopian Tax System: Cutting Through the Labyrinth and Padding the Gaps” PP.57 Journal of Ethiopian Law Spetmber,2011 Vol.XXV No.1”

 ያም ቢሆንም ግን ይህ ዘመናዊ የተሰኘው የግብር ሕጋችን ዛሬም ቢሆን እንደሌሎቹ ዘመናዊ የሀገራችን ሕጎች በተደረጀ እና ወጥ በሆነ መልኩ ያልተሰደሩ እና በተለያዩ አዋጆች፣መመሪያዎች እና ደንቦች ተበታትኖ የሚገኙ ናቸው፡፡ይህን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ጊዜ እንኳ እስከ 67 የሚደርሱ መመሪያዎች በትግበራ ላይ አሉ፡፡ (ወ/ሮመሰረትማናስቦ፡በገቢዎችሚኒስቴርየደረሰኝአስተዳደርቡድንአስተባባሪ)ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ የሚወጡት የግብር አዋጆች በበቂ የፖሊሲ ጥናት እና ብቁ ባለሙያዎች ምሪት የማይዘጋጁ በመሆኑ እና መንግሥት የገጠመውን የገንዘብ ችግሩን ወይም ያለበትን የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ለመቅረፍ እንዲያስችለው ገንዘብ መሰብሰብን ብቻ ዓላማ አድርገው የሚዘጋጁና ሕጎችበመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ (እሸቱ ጮሌ ” Towards a History of the Fiscal Policy of the Pre-Revolutionary Ethiopian State: 1941-1974 pp63 under development in Ethiopia, Organization for Social Science Research in Eastern and Southern Africa,2004)

በኢትዮጵያ ትልልቅ የተባሉት የግብር ሥርዓት ለውጦች የተከሰቱት የንጉሱን ከስደት መመለስ ተከትሎ ፤ በወታደራዊ ጁንታ ‘ደርግ’ የተመራው እና በ1967ዓ.ም የፈነዳውን የኢትዮጵያ አብዮት ተከትሎ፤የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በ1983ዓ.ም ሥርዓተ-መንግሥቱን መያዙን ተከትሎ እና በ1994 ዓ.ም “የተጨማሪ እሴት ታክስ” የተባለ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የግብር ዓይነትን በሀገራችን መተዋቁን ተከትሎ የወጡ ሕጎች ናቸው፡፡ (ታደሰ ሌንጮ “The Ethiopian Tax System: Cutting Through the Labyrinth and Padding the Gaps” PP.58 Journal of Ethiopian Law Spetmber,2011 Vol.XXV No.1”)

በመሆኑም ይህ ለሀገሪቷ በዓይነቱ ልዩ የሆነው የተጨማሪ እሴት ታክስ (ከዚህ በኃላ “ተ.እ.ታ” ተብሎ ይገለጻል) አዋጅ ቁ.285/94 በአ.ቁ 64 ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንዲያወጣ በሰጠው ስልጣን መሰረት እና ይህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁ.139/99 አንቀጽ 22 መሰረት ይህን ስልጣኑን ለገቢዎች ሚኒስትር አሳልፎ የሰጠ ሲሆን ገቢዎች ሚኒስትርም በመመሪያ ቁ 46/1999 የሽያጭ ምዝገባ መሳሪያን  የመጠቀም ግዴታን አውጇል፡፡ በተጨማሪም የተ.እ.ታ አዋጅ ቁ.285/94 አንቀጽ 22 (1) እና በማሻሻያው አዎጅ 609/2001 አ.ቁ50 (ለ-1) መሰረት የተ.እ.ታ ተመዝጋቢው ነጋዴ ለሚያከናውናቸው እያንዳንዱ ሽያጮች በሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያው ደረሰኝ እንዲቆርጥ እና ተገልጋዩም ነጋዴው ደረሰኝ ካልተቆረጠለት ክፍያ እንዳይፈጽም ጥብቅ ትዕዛዝ ይዞ ነበር ወደ ሥራ የገባው፡፡

ግና በመዲናችን አዲስ አበባ መኃል መርካቶ አይደለም በወረቀት የተዘጋጀ ቀላል ደረሰኝ ይቅርና ሰውን አመሳስሎ ለመሥራት ጥቂት የቀራቸው ብሩህ አዕምሮና ክፉ ልቦና ያላቸው ወገኖቻችን ደረሰኝን አመሳስሎ በመሥራት ለስግብግብ ነጋዴው ሲያከፋፍሉ ይህ ስግብግብ ነጋዴ ደግሞ በመንግሰት በተፈቀደላቸው ደረሰኝ ቁጥሮች ሌሎች ደረሰኞችን አመሳስሎ በማሰራት በአንድ ደረሰኝ ቁጥር አራት እና አምስት ግብይት እየፈጸሙ ትርፍ ማጋበሳቸው ፤ በተቃራኒው በምንም ድርጊት ያልተሳተፈው ንጹህ ተገልጋዩ ዕቃ የሸመተባቸውን እነዚህን ደረሰኞቹን አያይዞ ወጪውን ለባለስልጣኑ ሪፖርት በሚያደርግበት ጊዜ ሐሰተኛ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ በማቅረብ ግብር ለማጭበርበር ሞክረሀል ወይም አጭበርብረሀል ተብሎ በየእስር እና እንግልት መዳረጉ የአደባባይ ሀቅ ነው ፡፡

ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ድረስ እንኳ በሀገራችን በሐሰተኛና ሕገ-ወጥደረሰኞች የተፈጸሙ የግብይቶች የገንዘብ መጠን ብር 20,000,000,000 (ሀያ ቢሊየን) የደረሱ ሲሆን እነዚህ ደረሰኞችም ለህትመት የበቁት የእዕምሮ ህመምተኛ፣ህጻናት፣ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ሴተኛ አዳሪዎች፣…ከሆኑ ሰዎች ውክልና በመውሰድና የንግድ ፍቃድ በማውጣት በንግድ ሥራ ላይ በተሰማሩ ግለሰቦችም ጭምር ነው፡፡ (አቶ ሲሳይ ገዙ ለታ፡ በኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር)

ይህን ድርጊት ያስቀራል፣ ስግብግብ ነጋዴውንም በፍትህ አደባባይ ይቀጣል፣ የሐሰተኛ/የተጭበረበረ ደረሰኝ ገፈት ቀማሽንጹህ ተገልጋዩን ይታደጋል ተብሎ የተዘረጋው የሕግ ሥርዓት ታማኙን ከአጥፊው፣ ንጹሁን ከአጭበርባሪው የሚለይበት እና በዚህም አጥፊውን በፍትህ አደባባይ ለመቅጣት በሚያደርገው የፍትህ ጉዞ ከተ.እ.ታ ሐሰተኛ ወይም ሕገ-ወጥ ደረሰኝ መመዘኛ አኳያ ብቻ በዚህ ጽሑፍ ይቃኛሉ፡፡

 

የጽሑፍ ዓላማ

ይህ ጹሁፍም ዓላማው ከላይ የተመለከተውን ንባራዊ ሁኔታዎች መሰረት በማድረግ  ከተ.እ.ታ አዋጅ አኳያ ለመመለስ የሚሞክራቸው ጥያቄዎቹ ፡-

  • ሐሰተኛ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ ማለት ምን ማለት ነው?
  • የደረሰኝን ሐሰተኝነት የማረጋገጥ ግዴታ የማን ነው?
  • ግለሰቦች እና የግል ተቋማት በግብይት ጊዜ የደረሰኞችን ሐሰተኝነት ማረጋገጥ የሚችሉበት ሁኔታዎች አሉ?
  • በፍ/ቤቶቻችንስ ያለው ትግበራ ምን ይመስላል?

የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ የግብር ሕግ የሚባሉት የታክስ አስተዳደር አዋጅ፣ የገቢ ግብር አዋጅ፣ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ፣ የተርን ኦቨር ታክስ አዎጅ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ፣ የቴምብር ቀረጥ አዋጅ፣ የጉምሩክ አዋጅ፣ ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡

በእነዚህ የግብር ሕጎቻችን እና የሀገራችን የበላይ ሕግ በሆነው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥትን ጨምሮ“ግብር”፣ “ቀረጥ” እና “ታክስ” የሚሏቸው ቃላቶች ሰፍረው የሚገኙ ሲሆኑ ትርጉማቸው ግን እንደ ሕጉ ዓላማና የተፈጻሚነት ወሰን ልዩ ልዩ ሆኖ ተዘርዝሯል፡፡ ሆኖም የፌደራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ በሆነበት (የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አ.ቁ 5 (2)) እና “ታክስ” ለሚለው የእንግሊዘኛቃል አቻ የሆነ የአማርኛ ትርጉም ያለው “ግብር”የሚለው ቃል ባለበት ሁናቴ የእንግሊዘኛውን “ታክስ” የሚለውን ቃል በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎች ውስጥ ሳይቀር (ከአ.ቁ 96-100 )መጠቀሙ ግልጽ አይደለም፡፡ እንደዚሁም የሕግ አውጪውና ሕግ አስፈጻሚው የእንግሊዘኛ ቃል የሆነውን “ታክስ” እንደ ወረደ በግብር ሕጎቻችን ላይ ከመጠቀም አልፎ የሕጎቹ ስያሜ አድርጎ መጠቀሙ ግርታን እንደፈጠረ አለ፡፡

ከእነዚህ የእንግሊዘኛው “ታክስ” የሚለው ቃል መጠሪያቸው ከሆነው የግብር አዋጆች መካከል አንዱ በሰኔ 27 ቀን 1994 ዓ.ም የጸደቀው አዋጅ ቁ.285/94 ‘የተጨማሪ እሴት ታክስ’ እና ይህን አዋጅ ለማሻሻል ተከታትለው የወጡትአዋጆች ቁ.609/2001 እና 1159/2002 ናቸው፡፡ ለመሆኑ ተ.እ.ታ ማለት ምን ማለት ነው?

 

1. ተጨማሪ እሴታ ታክስ (ተ.እ.ታ)

 

ተ.እ.ታ ማለት በፍጆታ ዕቃ ወይም በተጠቃሚ ወጪ ላይ የተመሰረተ ታክስ ሲሆን የሚሰበሰበውም ምርት ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ወይም ማንኛውም ታክሱ የሚከፈልበት ዕቃና አገልግሎት ግብይት ሲካሄድበት፤በታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት  ወይም በገቢዎች ሚኒስቴር የሚሰበሰብ የታክስ ዓይነት ነው፡፡ (ዳንኤል ታደሰ፡ ከኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር የኢንትርኔት ድህረ ገጽ ላይ የተለጠፈ)

ተ.እ.ታ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች ተብለው ከሚታወቁት የታክስ ዓይነቶች አንዱ ሲሆን በፍጆታ ላይ የሚጣል የታክስ ዓይነት ነው፡፡ ከስሙም መረዳት እንደሚቻለው በግብይት ሂደት በየደረጃው በሚፈጠር ተጨማሪ እሴት ላይ በፍጆታ የሚጣል ታክስ/የግብር ነው፡፡ ( ሳሙኤልታደሰ፡ ‘ተጨማሪ እሴት ታክስ በኢትዮጵያ’፡ ግንቦት 2004 ዓ.ም ገጽ፡ 16) በመሆኑም የተ.እ.ታ አዋጅ 285/94 እና ማሻሻያዎቹ ወደ ሥራ የገቡት በተ.እ.ታ ከፈይነት የተመዘገበ ማንኛውም ነጋዴ ላይ“ደረሰኝ የማይሰጥ ከሆነ አይክፈሉ” የሚል ጽሑፍ በግልጽ በሚታይ ቦታ ላይ ማስታወቂያ በመለጠፍ  በሚያደርገው ግብይት ላይ ይህንን የተ.እ.ታ ተፈጻሚ እንዲያደርግ እና ለዚህም ማረጋገጫ ክፍያ ከመቀበሉ በፊት የተ.እ.ታ ደረሰኝ በመቁረጥ እና ሽያጩ እንደተከናወነ ወዲያውኑየቆረጠውን የተ.እ.ታ ደረሰኙን መስጠት እንዳለበት በተ.እ.ታ አዋጅ 285/94 አ.ቁ 22 (1) እና በማሻሻያው አዋጅ ቁ. 609/2001 አ.ቁ 47 ሀ (9) (ሐ) እና 50 (ለ-1) ግዴታ በማስቀመጥ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የተ.እ.ታ ግብር ሥርዓት በሀገራችን ከተዘረጋ በኃላ የሀገሪቱ የገቢ መጠንን በ39% ያሳደገ ቢሆንም አሁን ያለበት ደረጃ ግን ከ20% በታች ዝቅ ብሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክንያቱ የደረሰኝ አጠቃቀምና ቁጥጥር ሥርዓቱ ነው፡፡ በመሆኑም የተ.እ.ታ ደረሰኝ ጉዳይ የግብር አስተዳደር ሥርዓቱ ቀዳሚውና ዋናው ማነቆ እንደሆነበት አሁንም አለ፡፡ ( አቶ ሲሳይ ገዙ ለታ፡ በኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር)

ለመሆኑ የተ.እ.ታ ደረሰኝ ምንድን ነው?

 

2. የተ.እ.ታ ደረሰኝ

 

“ደረሰኝ” ማለት የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ማንኛውም ታክስ ከፋይ ከደንበኞቹ ጋር ለሚያከናውነው ግብይትና ለሚሰበስበው ገንዘብ ዕውቅና የሚሰጥ ህጋዊ ሰነድ ለደንበኞቹ ቆርጦ በመስጠት በመንግሥት የተጣለበትን ግብር የማስከፈል እና የመክፈል ግዴታውን የተወጣ ስለመሆኑ የሚያረጋገጥበት የማረጋገጫ ወረቀት ነው፡፡ ( ገብረእግዚአብሔር ወልደገብርኤል፡ ደረሰኝ አለመቁረጥና የወንጀል ተጠያቂነት፡ ABYSSINIALAW)ከዚህም አኳያየተ.እ.ታ ደረሰኝከሚቆረጥበት ዓላማ አንጻር“የሽያጭ” እና “ገንዘብ መሰብሰቢያ”ደረሰኝ ተብለው ለሁለት መከፈል የሚችል ሲሆን ይህ ደረሰኝ እንደተሰጠበት ማረጋገጫ ሁኔታ ደግሞ “የእጅ በእጅ” (በተለምዶ ማኑዋል የምንለው) እና “በሽያጭ መመዝቢያ የታተመ/የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝ” በማለት ልንከፍው እንችላለን፡፡

“የሽያጭ ደረሰኝ” ማለት እጅ በእጅ ወይም በዱቤ ዕቃ ወይም አገልግሎት ስለመሸጡ የሚሰጥ ማረጋገጫ ማለት ሲሆን ፤ የ”ገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ” ማለት ደግሞ ከሽያጭ የተገኘ ገቢ ቢሆንም ባይሆንም ማንኛውም በጥሬ ገንዘብ ወይም በቼክ ስለመከፈሉ ወይም ገቢ ስለመደረጉ የሚሰጥ ማረጋገጫ ማለት ስለመሆናቸው የገቢዎች ሚኒስቴር ስለደረሰኝ አያያዝ፣አጠቃቀምና ቁጥጥር ባወጣው በመመሪያ ቁጥር 28/2001 አንቀጽ 2 (1) እና (2) እና በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 አ.ቁ 12 እና 13 ላይ ተገልጻል፡፡

በተጨማሪም በገዢው ተይዞ ሰለሚከፈል የተ.እ.ታ አፈጻጸም የወጣ መመሪያ ቁጥር 27/2002በአንቀጽ ቁጥር 5 እናበታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 አ.ቁ 2 (6) መሰረት ደረሰኝ ማለት “ታክሱን ቀንሰው የሚያስቀሩ ወኪሎች በኢትዮጵያ ገቢዋች ጉምሩክ ባለስልጣን ዕውቅና የሚያሳትሙት እና ታክሱ ተቀንሶ ለመቅረቱ ማረጋገጫ እንዲሆን የሚሰጡት፣ የተያዘውን ታክስ መጠን የሚያሳይ ሰነድ ነው”ሲል ትርጉም የሚሰጠው ሲሆን የዚህ ደረሰኝ ተፈጻሚነት ግን ከመንግሥታዊ ተቋም ጋር ለሚደረግ ግብይት ብቻ ስለመሆኑ ጨምሮ ያሳስባል፡፡

“የሽያጭ” እና “የገንዘብ መሰብሰቢያ” የተ.እ.ታ ደረሰኞች ከሌሎች ደረሰኞች የምንለይበት ብቸኛው መንገድ ደረሰኞቹ በውስጣቸው በሚይዙት መረጃ መሰረት ብቻ ስለመሆኑ ባለስልጣኑ ገቢዎች ሚኒስቴር በመመሪያ ቀ.28/2001 አ.ቁ 4 (1) እና (2) እና በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 ላይ ገልጾታል፡፡ በዚህም መሰረት የተ.እ.ታ ደረሰኞች በውስጣቸው ሊይዟቸው የሚገቡት በመረጃዎች በተ.እ.ታ አዋጅ ቁ 285/94 አ.ቁ22 (2) እና በሚኒስቴሩ መመሪያ ቁ 28/2001 አ.ቁ 4 (1) እና በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 አ.ቁ 6 (2) ላይ የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህም፡-

 ሀ/ የግብር ከፋዩን ሙሉ ስም ፣አድራሻ እና የተመዘገበ የንግድ ስም፣

ለ/ የግብር ከፋዩን የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ምዝገባ ሰርፊኬትቁጥርና የተሰጠበት ቀን፣

ሐ/ የገዢውን ሙሉ ስም ህጋዊ መጠሪያው የተለየ ከሆነ የተመዘገበውን ሰው የንግድ ስም ፣አድራሻና የግብር መክፈያ መለያ ቁጥር፣

መ/ ተከታታይ የሆነ የደረሰኝ ቁጥር፣

ሠ/ የደረሰኙን አታሚ ድርጅት ስምና የታተመበት ቀን፣

ረ/ የተጓጓዘው ወይም የተሸጠው ዕቃ ወይም የተሰጠው አገልግሎት ዓይነት መጠን እና ታክስ የሚጣልበት ግብይት ላይ የሚፈለገውን የተጨማሪ እሴት ታክስ መጠን፣

ሰ/ ግብይቱ የተፈጸመበት ዕቃ የኤክሳይዥ ታክስ የተከፈለበት ሲሆን የኤክሳይዝታክሱን መጠን፣

ሸ/ በፊደል እና በአሃዝ የተጻፋ የሽያጭ ወይም ታክስ የሚከፈልበትግብይት ዋጋ፣

ቀ/ ደረሰኙ የተሰጠበት ቀን ፣

በ/ ደረሰኙን ያዘጋጀውና ገንዘቡን የተቀበለው ሰራተኛ ስምና ፊርማ እና

ተ/ ደረሰኙ እንዲታተም ባለስልጣኑ የፈቀደበትን ደብዳቤ ቁጥርና ቀን ነው፡፡

 

3. ሐሰተኛ/የተጭበረበረ ደረሰኝ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ

 

የታክስ ወንጀሎች ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ በደረሰኝ ላይ የሚፈጸም ወንጀል አንዱ ስለመሆኑ የታክስ አስተዳደርአዎጅ (ከዚህ በኃላ “ታ.አ.አ” ይባላል) ቁ 983/2008 አ.ቁ 119፣120 እና 122 ላይ ተገልጾል፡፡ ባለስልጣኑ የገቢዎች ሚኒስቴርም የግብር አስተዳደር ሥርዓቱ ዋናችግር የሆነበት ይህ ሐሰተኛ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ ነው፡፡ በግብር ሕጎቻችን ሐሰተኛ ደረሰኝ ወይምሕገ-ወጥ ደረሰኝ ምን ማለት ስለመሆኑ ወይም በሐሰተኛ ደረሰኝ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ መካከል ያለው ግልጽ ልዩነትን በግልጽ ዘርዝሮ አላስቀመጠም፡፡ በባለስልጣኑ ገቢዎች ሚኒስቴርም ያለው መረዳት በሐሰተኛ/በተጭበረበረ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ መካከል ልዩነት የሌለ ስለመሆኑ ነው፡፡ (አቶ ተሾመ ወልዴ: በገቢዎች ሚኒስቴር የፍትሐብሄር ጉዳዮች ክትትል ቡድን መሪ)

ነገር ግን በወንጀል ሕጋችን አንድ ድርጊትን እንደ ወንጀል ቆጥሮ ለመቅጣት ሊሟሉ የሚገባቸው ሦስት ፍሬ-ነገሮች ህጋዊነት (legal)፣ ግዙፋዊ (material) እና ሞራላዊ (moral)ስለመሆናቸው እና በተለይም በህጋዊነት ፍሬ-ነገር ስር በ1997ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕጋችን በአ.ቁ 2 እ 23 (1) ላይ ወንጀል የተባለው ድርጊት በዝርዝር በግልጽ ወንጀል ስለመሆኑ ሊደነገግ ወይም ሊገለጽ የሚገባ ስመሆኑ ግዴታ ያስቀምጣል፡፡ ስለሆነም በሐሰተኝነት/በተጭበረበ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ ስም የወንጀል ክስ ለማቅረብም ሆነ በወንጀል ሕጉ መሰረት ከመቅጣታችን በፊት በደረሰኞቹ መካከል ያለ ልዩነት ወይም አንድነት በግልጽ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፡፡

የታ.አ.አ ቁ.983/2008 አ.ቁ 119፣120 እና 122 ድንጋጌዎችን በጥልቅና በቅርብ (with deep and close reading of the provisions) በምንመለከትበት ጊዜ ከዚህ በታች የተመለከቱትን ልዩነቶች እና ተመሳሳይነት በሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ መካከል እናገኛለን፡፡

ሀ/ ተመሳሳይነት/similarity/

ሐሰተኛ/የተጭበረበረ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኞች የሚያመሳስላቸው መሰረታዊ ነገሮች ሁለት ሲሆኑ እነዚህም፡-

  • ደረሰኞቹ በሕግ በግልጽ የተከለከሉና እንደ ወንጀል የሚቆጠሩ መሆናቸው እና
  • በግብይት ውስጥ በብዛት የሚውሉት በእጅ በእጅ ወይም በተለምዶ በማኑዋል ደረሰኞች ላይ መሆኑ ነው፡፡ ( በተሰረቀ የካሽ ሬጂስትር ማሽን የሚፈጸሙ የሕገ-ወጥ ደረሰኞች ግብይት እንዳሉ ልብ ይሏል) ( አቶጌትነትአበባው፤የገቢዎችሚኒስቴርየሽያጭመመዝገቢያመሳሪያቴክኖሎጂቡድንአስተባባሪ)

ለ/ ልዩነት/difference/

  • ሐሰተኛ/የተጭበረበረ ደረሰኝ በማለት በታ.አ.አ ቁ983/2008 አ.ቁ 119 (1) (ሀ) እና (3) ላይ ትርጉም የተሰጠው ከባለስልጣኑ የሚኒስቴር መ/ቤት ፍቃድ እና ዕውቅና ውጪየታተመደረሰኝ ወይም በባለስልጣኑ ፍቃድና ዕውቅና የታተሙ ደረሰኞችን በማመሳሰል የተሰራ ደረሰኝ ማለት ነው፡፡
  • ሕገ-ወጥ ደረሰኝ ማለት ደረሰኙ በባለስልጣኑ ፍቃድ እና ዕውቅና የታተመ ህጋዊ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ደረሰኙ የዋለበት ግብይት ሕገ-ወጥ በሚሆንበት ጊዜ ነው ለምሳሌደረሰኙ የተቆረጠው ግብይት ሳይፈጸም (አ.ቁ 120 (4) እና በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 አ.ቁ 25 (2))፣ ለአንድ ግብይት በዋሉ ተመሳሳይ ደረሰኞች ላይ የተለያየ ዋጋ ያሰፈሩ (አ.ቁ 120 (2) እና በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 አ.ቁ) 22 (3)፣ በባለስልጣኑ አካል በጋዜጣና በኢንትርኔት መረብ ላይ ግብይት እንዳይፈጸም ስማቸውን ከዘረዘራቸው ግለሰብና የንግድ ተቋም ጋር ግብይት ተፈጽሞ የቀረቡ ደረሰኞች (ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ድረስ በባለስልጣኑ የኢንተርኔት መረብ ላይ 162 ደረሰኞች ተዘርዝረዋል)፣ለአንድ ግብይት ጥቅም ላይ የዋለን ደረሰኝ ለሌላ ግብይት ሲጠቀሙ (በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 አ.ቁ22 (2)፣የደረሰኝ ህትመቱን ከተፈቀደለት ታክስ ከፈይ ውጪ ለሌላ ታክስ ከፈይ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ፣ የተ.እ.ታ ደረሰኝ ሊይዘው ከሚገባው አስገዳጅ የመረጃ ዝርዝር ውስጥ አጉድሎ መጠቀሙ (በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 አ.ቁ 22 (10)፣ በባለስልጣኑ እንዲሰረዝ ውሳኔ በተሰጠበት ደረሰኝ መጠቀም (በታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 አ.ቁ 22 (9)፣ በኮንትሮባንድ የገባ ዕቃ ላይ ግብይት የተፈጸመበት ደረሰኝ (አቶ ሲሳይ ገዙ ለታ፡ በኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር) እና ወ.ዘ.ተ፡፡

 ለመሆኑ እነዚህን ሐሰተኛ/የተጭበረበረ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኞች ከህጋዊ ደረሰኞች እንዴት መለየት ይቻላል?

 

4. ሐሰተኛ/ የተጭበረበረ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ የመለየትና የመቆጣጠር ግዴታ የማን ነው?

 

በግብይት ውስጥ የሚውሉ ሐሰተኛ ደረሰኞችን እና ከዚህ በፊት ግብይት የተፈጸመባቸው ሕገ-ወጥ ደረሰኞችን፣ በሚኒስቴት መ/ቤቱ በተሰረዙ ደረሰኞች የሚፈጸሙ ግብይቶችን፣ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በድረ-ገጹ ወይም በመገናኛ ብዙሃን ካላሳወቀው ነገር ግን በፍ/ቤት በማጭበርበር ድርታቸው ጥፈተኛ በተባሉ ሰዎች የታተመን ሕገ-ወጥ ደረሰኝን ብቻ መሰረት በማድረግ እነዚህን ደረሰኞች በግብይት ሥርዓት ውስጥ እንዳይውሉ የማድረግ ግዴታው በማን ላይ እንደሆነ በየደረጃው ከዚህ በታች ተዘርዝሯል፡፡

 

ገቢዎች ሚኒስቴር ግዴታ

 

ህዳር 20 ቀን 2011ዓ.ም10 የሚኒስቴር መሥሪያቤቶችን አቋቁሞ የጸደቀው የኢፌዲሪ የፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 በአንቀጽ ቁጥር9 (19) ላይ የገቢዎች ሚኒስቴርን ሲያቋቁም ስልጣኑንም ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተሰጡት ስልጣን ለገቢዎች ሚኒስቴር የተሰጠ መሆኑን በአንቀጽ ቁጥር 31 ላይ በመግለጽ ነው፡፡በመሆኑም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንን ያቋቋመው አዋጅ ቁጥር 587/2000 የባለስልጣኑን ስልጣን በአንቀጽ ቄጥር 5 (3) ላይ ሲዘረዝር “የታክስ ማጭበርበርና ስወራን በመከላከልና በመቆጣጠር የታክስና የጉምሩክ ሕግጋትን ማስከበር” መሆኑን የሚደነግግ በመሆኑ የገቢዎች ሚኒስቴርም ከተቋቋመበትና ዋና ዋና ዓላማዋች መካከል ይህ የታክስ ማጭበርበርን መከላከል ቀዳሚውና ዋናው ተግበሩ ይሆናል፡፡ 

በዚህም መሰረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ግዴታውን እንዴት እየተወጣ ስለመሆኑ ከዚህ ጹሁፍ ጻፊ ለቀረበላቸው ጥያቁዎች መልስ ሲሰጡ የሰጡት መልስ፡-

ሀ/ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በድህረ-ገጽ እና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ላይ ሐሰተኛ እና ሕገ-ወጥ የሚሏቸውን ደረሰኞችን እና በማጭበርበር ተግባር የተሳተፍ ግለሰቦችን እና የንግድ ተቋማትን ስም በመዘርዘር ተገልጋዩ ከእነዚህ ግለሰቦች ጋር ግብይት እንዳይፈጽም በማሳወቅ (ታ.አ.አ ቁጥር 983/2008 አ.ቁ 133) ፣

ለ/ ከተገልጋዮች በሚደርሳቸው ጥቆማ እና ለሚሰጠው ተጨባጭ መረጃ ሽልማት በመስጠት (ታ.አ.አ ቁጥር 983/2008 አ.ቁ 134 (1))

ሐ/ መ/ቤቱ የተ.እ.ታ ተመዝጋቢውን ሰነዶች ኦዲት በማድረግ እና

መ/ መ/ቤት በራሱ ጥርጣሬ ተነስቶ በሚያደርገው ፍተሻ ስለመሆኑ ገልጾል፡፡

 

ሌሎች የመንግሥት አካላት ግዴታ

 

ማናቸውም የፌደራል እና የክልል መንግሥት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ ኤጀንሲ ወይም ሌላ አካል፣ የአካባቢ አስተዳደሮች፣ ማህበራት፣ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የታክስ ሕጎችን በማስፈፀም ረገድ ከባለሥልጣኑ ጋር የመተባበር ግዴታ አለባቸው፡፡ (ታ.አ.አ ቁጥር 983/2008 አ.ቁ 7)

 

በግብይት የተሳተፋው የተ.እ.ታ ግብር ከፋይ ግዴታ

 

ሀ/ በግብይቱ የሚሳተፈው የተ.እ.ታ ተመዝጋቢ የሚሰጠው ደረሰኝ በተ.እ.ታ ሕጎች ላይ ደረሰኝ ሊይዛቸው የሚገቡ መረጃዎችን አሟልቶ የያዘ መሆኑን በማየት፣

ለ/ የንግድ ፍቃድ እና የታክስ መለያ ቁጥሩን በደረሰኙ ላይ ከተጠቀሰው ቁጥሮች ጋር በማገናዘብ፣

ሐ/ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ በየወሩ በሚያደርጋቸው የታክስ ሪፖርት ጊዜ እና ለኦዲት ሰነዶችን በሚያቀርብበት ጊዜ ሐሰተኛ ደረሰኞችና እና ሰነዶችን ያለማቅረብ (የተ.እ.ታ አዋጅ 285/94 አ.ቁ 49 እና 50)፣

መ/ ለሚያደርጋቸው ማንኛውም ግብይት ደረሰኞችን እና ሰነዶችን በአግባቡ ሰድሮ መያዝና በተጠየቁ ጊዜ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ማቅረብ (ታ.አ.አ ቁጥር 983/2008 አ.ቁ 17)፣

ሠ/ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በተጠየቁ ጊዜ ግብይት የተፈጸመባቸው ዕቃዎችን ወይም የተገዙት ዕቃዎች ለአገልግሎት የዋሉበትን እሴት በማሳየት እና

ረ/ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በተጠየቁ ጊዜ ግብይት የፈጸሙባቸውን የሽያጭ መደብሮች ማሳየት ናቸው፡፡

 

የሶስተኛ ወገኖች ግዴታ

 

በታክስ ሕጉ መሰረት ግዴታውን እየተወጣ እና በማጣራትና በምርመራ ላይ ያለን የታክስ ሰራተኛ ያደናቀፈ ወይም ለማደናቀፍ የሞከረ ማንኛውም ሰው በወንጀል የሚቀጣ ስለመሆኑ በታ.አ.አ ቁጥር 983/2008 አ.ቁ 126 (1) ላይ የተደነገገ በመሆኑ የታክስ ሰራተኛው ሥራውን ሲሰራ ወይም ሲያጣራ ያለማደናቀፍ የሁሉም ሰው ግዴታ ነው፡፡

 

ግለሰቦች እና የግል ተቋማት በግብይት ጊዜ ደረሰኞችን ሐሰተኝነት ማረጋገጥ የሚችሉበት ሁኔታዎች አሉ?

ከላይ በዝርዝር ለመግለጽ እንደተሞከረው ሐሰተኛ/የተጭበረበሩ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኞች በግብይት ውስጥ እንዳይውሉ ቁጥጥር በማድረግ ለመከላከልና ንጹህ ተገልጋይን የዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ገፋት ቀማሽ እንዳይሆን ለማድረግ መንግሥት በሚኒስቴር ደረጃ “የገቢዎች ሚኒስቴርን” በማቋቋም በተጨማሪም ማንኛውም የመንግሥት አካላቶች ይህ የሚኒስቴሩን ሥራ በመተባበር ሊሳተፍ እንዲገባ ግዴታ በመጣል አብዛኛውን ግዴታ በሚኒስትር መ/ቤቱና በመንግሥት ተቋሞች ላይ አድርጓል፡፡

ግለሰቦችና የግል ተቋማት በሚፈጽሙት ግብይት ሐሰተኛ/የተጭበረበረው ደረሰኝን እና ሀገ-ወጥ ደረሰኞችን ለመለየት የሚችሉበት መንገድ ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነዚህም፡-

  • ይህም አንድ የተ.እ.ታ ደረሰኝ ሊይዝ የሚገባቸውን መረጃዎችን በማወቅና በግብይት ሂደት የሚቀርብላቸው ደረሰኝ በሕግ የተ.እ.ታ ሊይዝ የሚገባውን መረጃ መያዝ አለመያዙን በማረጋገጥ እና
  • የሻጭን የታክስ መክያ ቁጥርና ንግድ ፍቃድ ከሚቀርብላቸው ጋር በማመሳከር ብቻ ነው፡፡

በሚኒስቴር መ/ቤት በተንቀሳቀሽ ስልክ ላይ በሚዘረጋ የስልክ አፕሊኬሽን የአንድ ግብይት ተገልጋይ በግብይት የሚቀበለውን ደረሰኝ ቁጥር በማስገባት የደረሰኙን ትክክለኛነት በቀጥታ ከሚኒስቴሩ  የሚያጣራበት ሥርዓት ታስቦ የነበረ ቢሆነም እስካሁን ድረስ ግን ተፈጻሚ ሊደረግ አልቻለም፡፡ ( አቶጌትነትአበባው፤የገቢዎችሚኒስቴርየሽያጭመመዝገቢያመሳሪያቴክኖሎጂቡድንአስተባባሪ)

ይሁን እንጂ በሕግ ሐሰተኛ አና ሕገ-ወጥ ደረሰኞች በግብይት እንዳይውሉ የመጠበቅና የመከላከል ግዴታ በአብዛኛው በሚኒስቴር መ/ቤቱ ላይ የተጣለ ሆኖ ሳለ በተግባር ግን በተቃራኒው ሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ አቅርባቹሀል፡፡ የደረሰኞችን ሐሰተኛነት እና ሕገ-ወጥነት ግብይት ከመፈጸማችሁ በፊት ልታውቁ ሲገባ ይህን በቸልተኝነት አላደረጋችሁም በማለት ገቢዎች ሚኒስቴር የራሱን ግዴታ ሳይወጣ የሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኝን የማወቅ አቅም የሌላቸውን ግለሰቦችና ድርጅቶች በወንጀል ይከሳል፡፡ ይበልጥ ጉዳዩን የሚያሳዝነው ተከሳሽ ድርጅቶች ግብይት ስለመፈጸማቸው የገዙትን ዕቃ በማስረጃነት ቢያቀርቡ እንኳ በደረሰኙ የፈጸሙት ግብይት 65%ብቻ ተቀባይነት በማድረግ ሌላው ወጪያቸው እንደ ወጪ አይያዝላቸውም፡፡ (አቶ ሲሳይ ገዙ ለታ፡በኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር)

 

በፍ/ቤቶቻችንስ ያለው ትግበራ ምን ይመስላል?

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ክስተት ስለመሆኑ በዚህ ጽሑፍ በቅድሚያ የተገለጸውን ጉዳይ መሰረት በማድረግ ሐሰተኛ/የተጭበረበሩ ደረሰኝን አስመልከቶ እና ሚኒስቴር መ/ቤቱ በድረ-ገጹ ወይም በመገናኛ ብዙሃን ካላሳወቀው ነገር ግን በፍ/ቤት በማጭበርበር ድርጊታቸው ጥፈተኛ በተባሉ ሰዎች የታተመን ሕገ-ወጥ ደረሰኝን ብቻ መሰረት በማድረግ በፍ/ቤቱ የተሰጠው ውሳኔ እና የፍርድ ሂደት በዚህ የፍ/ቤቶች ትግበራ ይቃኛል፡፡

በዚህ ጉዳይ በገቢዎች ሚኒስቴር ተከሳሽ የሆነው ድርጅት የተከሰሰው ለባለስልጣኑ መሥሪያ ቤት ሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኞችን ሪፓርት በማድረግ ሐሰተኛ ሰነድ አቅርበኃል በሚል ነው፡፡ ለዚህም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በክሱ በማስረጃነት ያያዛቸው ደረሰኞችን ሕገ-ወጥነት እና ሐሰተኝነት እንደሚከተለው አስረድቷል፡፡

ሕገ-ወጥ ያላቸው ደረሰኞች፡- ደረሰኞቹ በባለስልጣኑ ፍቃድ የታተሙ ቢሆኑም ያሳተሙት ግለሰቦች በግብር ማጭበርበር ድርጊት በፍ/ቤት ጥፈተኛ የተባሉ በመሆናቸው ተከሳሽ ድርጅት ከእነዚህ ግለሰብ ጋር ግብይት ሊያከናውን እንደማይገባው እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ግብይት ፈጽሜያለሁ በማለት ያቀረባቸው ደረሰኞች ሕገ-ወጦች ናቸው በማለት ነው (በማስረጃነትም የፍ/ቤት የጥፈተኝነት ውሳኔን አያይዟል)፡፡ ሀተሰኛ ደረሰኞች፡- የተባሉት በሌሎች ግለሰቦችና ድርጅቶች ስም ሐሰተኛ ደረሰኝ አመሳስሎ በማሳተም ለግብይት የዋሉ ደረሰኞች መሆናቸውን በመጥቀስ ነው ( ለማስረጃነትም ደረሰኝ በስማቸውና በድርጅታቸው የተሰራባቸው ግለሰቦችን በምስክርነት አስቀርቦ ደረሰኙ የነሱ ስላለመሆኑ አስመስክሯል)፡፡

የተከሳሽ ድርጅት መከራከሪያ ደግሞ በቀዳሚነት የእነዚህን ደረሰኞች ሐሰተኛነት እና ሕገ-ወጥነት ማወቅ የምችልበት ሁኔታ የለም፣ደረሰኞቹ በሕግ ሊይዙ የሚገባቸውን መረጃዎች በሙሉ የያዙ እና ከንግድ ፍቃድና የግብር መለያ ቁጥር ጋር አገናዝቤ የተረከብኩት ነው፣ሐሰተኛና ሕገ-ወጥ በተባሉት ደረሰኞች ግዢ ስለመፈጸሜና የገዛዋቸው የግንባታ ዕቃዎችን ግንባታ ላይ ማወሌን የሚያስረዳልኝ ግንባታና የግንባታው ውል የዋጋ ዝርዝር (Bill of Quantities) አለ በማለት ነው፡፡

በተጨማሪም በገቢዎች ሚኒስቴር የባለሙያምስክር አድርጎ ያቀረባቸው የባለስልጣኑ ኦዲተር ከተከሳሽ ድርጅት ለቀረበለት መስቀለኛ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ተከሳሽ ድርጅት እነዚህ ደረሰኞች ሐሰተኛም ሆነ ሕገ-ወጥ ስለመሆናቸው ሊያውቅ የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡ በባለስልጣን መ/ቤቱም ተገልጋዮች በግብይት ሂደት ይህን እንዲያውቁ የሚያስችላቸው ሥርዓት እስካሁን አልተዘረጋም፡፡ ተከሳሽ ድርጅትን ጨምሮ ተገልጋዮችን ከሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ድርጊት መጠበቅና መከላከል ግዴታው የሚኒስቴር መ/ቤቱ ነው በማለት አስረድቷል፡፡

 ይሁን እንጂ ጉዳዩን የመረመረው ፍ/ቤት በጭብጥነት “የደረሰኞቹን ሐሰተኝነት እና ሕገ-ወጥነት “ ብቻ በመመርመር በሰውና በሰነድ ማስረጃ የቀረበውን መዝኜ ድምዳሜ ላይ የደረስኩት በተከሳሽ ድርጅት ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የቀረቡት ደረሰኞች “ሐሰተኛ/የተጭበረበሩ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኞች“መሆናቸውን ነው በማለት የጥፈተኝነት ውሳኔ እና የገንዘብና የእስር ቅጣት በድርጅቱና በሥራ-አስኪያጁ ላይ እንዲፈጸም አዟል፡፡

በዚህም ፍ/ቤቱሊያጣራ የሚገባቸውንመሰረታዊ ጉዮዳዮችን ማለትም፡-

1ኛ/ ተከሳሽ ድርጅት ሐሰተኛ እና ሕገ-ወጥ ደረሰኞችን ለመለየት የሚያስችለውን መንገድ ሁሉ ተጠቅሞል ወይስ አልተጠቀም?

2ኛ/ በተከሳሽ ድርጅት ሊለይ የሚችል የደረሰኝ ማጭበርበር ነው የተፈጸመው ወይስ አይደለም?

3ኛ/ ሚኒስቴር መ/ቤቱስ ይህ ግብይት እንዳይፈጸም ሊወጣ የሚገባውን ግዴታ ተወጥቷል ወይስ አልተወጣም?

የሚሉትን ጭብጦች በመዝለል በቀጥታ የደረሰኞቹን ሐሰተኝነት እና ሕገ-ወጥነት ብቻ በጭብጥነት በመያዝ ውሳኔ ላይ መድረሱ አግባብ ካለመሆኑም በላይ ሕጉ ሊደርስበት ካሰበው ዓላማ ጋር እያራራቀው፣ የተ.እ.ታ ከፈዩ ነጋዴንና ግብይት ፈጻሚን በስጋት እንዲኖር አድርጎታል፡፡ በተለይም ደግሞ የሚኒስትሩ መ/ቤት ግዴታ በፍ/ቤት አለመመርመሩ መ/ቤቱ ግዴታውን ከመፈጸም ቸል እንዲልና ሀላፊነቱን ሁሉ በዜጎቹ ላይ ጥሎ በበቂ ሁናቴ እንዳይሰራ በር ከፍቷል፡፡ በዚህም ግዑዝ በሆኑት አዎጆቻች ተጽፈው የሚገለጹት ሕጎች ህይወት የሚዘሩት ተግባራዊ እንዲደረጉ እና ከለላ በሚደረግላቸው ፍ/ቤቶች ውስጥ ቢሆንም ከላይ በተገለጸው መልኩ በፍ/ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎች ግን በግዑዝ ሰነዱ ላይ ያሉትን ሕጎች የሚቀብሩ ናቸው እንጂ ህይወት የሚዘሩበት አይደለም፡፡ በእርግጥ ይህን አንድ አንድ ጉዳይ ብቻ መሰረት በማድረግ በአጠቃላይ ያለው የፍ/ቤት ትግበራ ይሄ ነው ማለት ስህተት (hasty generalization) ቢሆንም የጻፊው ዓላማው ያጋጠመውን ጉዳይ በማካፈል በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በፍ/ቤቶች እየተሰሩ ያሉትን ጉዳዮች ሌሎች ባለሙያዎች እንዲያካፍሉ እና እንድንማማርበት ለማነሳሳት ያህል ነው፡፡

 

ማጠቃለያ

 

በሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኞች በግብይት ሥራ ላይ በስፋት ለመዋላቸው ዋናው ምክንያት ሀገራችን ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለችው የደረሰኝ ሥርዓት አጠቃቀምና ቁጥጥር ስለመሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤት ሰራተኞችም ሆነ ነጋዴዎች ይስማሙበታል፡፡ ከኃላችን ተነስታ የተ.እ.ታ የግብር ሥርዓትን የዘረጋችው ኬንያ የኤሌክትሮኒከስ ደረሰኝ (e-invoice) በመጠቀም ደረሰኝን ተከትሎ የሚከሰቱ ችግሮችን አስቀርታለች፡፡ ይሁን እንጂ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ዛሬም ቢሆን ይህን መሰል በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓትን በመዘርጋት በደረሰኝ ምክንያት እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለማስወገድ ጥረት ሲያደርግ አይታይም፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር በሕግ የተጣለበትን ሀላፊነት በአግባቡ እየተወጣ ስለመሆኑ ሊጠይቁና ሊቆጣጠሩት (check-balance) ከሚገቡት አካላት መካከል የሆነው ሕግ አውጪው የህዝብ ተወካዮች/እንደራሴዎች ምክር ቤት ሚኒስቴር መ/ቤቱን በዓመት ግብር በመሰብሰብ ያስገኘውን የገንዘብ መጠን በመቁጠር ከመገምገም ባለፈ በደረሰኝ ቁጥጥርና ጥበቃ ላይ ይሄ ነው የሚባል ግምገማ አከናውኖበት አያውቅም፡፡ ሕግ ተርጓሚው ፍ/ቤትም ይህ የመቆጣጠር ስልጣኑን አስመልክቶ በገቢዎች ሚኒስቴር ከሳሽነት በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ባለስልጣኑ ሀላፊነቱን በመወጣት ሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ በግብይት እንዳይውል ያደረገውን ተግባር ሳይመዝን ውሳኔ መስጠቱ አግባብ ያልሆነና ሊታረም የሚገባው ነው፡፡ (ጻፊው የገጠመውን ጉዳይ ብቻ መሰረት በማድረግ ስለመሆኑ ልብ ይሏል)

የገቢዎች ሚኒስቴር የተቋቋመበትን ዓላማ ላይ ለመድረስ የተሰጠውን ሀላፊነት በተገቢው ደረጃ ባልፈጸመበት ሁናቴ፤ ግለሰብና ድርጅቶችን ከሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ የመከላከልና የመጠበቅ ግዴታውን በበቂ ሁናቴ ሳይወጣ፤ በከተማው እና በሀገሩ በሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ የተፈጸመው የግብይት መጠን እስከ ብር 20,000,000,000 (ሀያ ቢሊየን) ደርሷል በማለት በእሪሪታ እያለቀሰበተቃራኒው በግብይት ሂደት የሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ ተጠቂ የሆኑ ግለሰብና ድርጅቶችን በወርኃዊና ዓመታዊ ሪፖርት ጊዜ ሐሰተኛና ሕገ-ወጥ ደረሰኝ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ አቅርባቹኃል በማለት የወንጀል ክስ በማቅረብ ሥራ-አስኪያጆችን ለእስር የንግድ ድርጅቶችን እስከ ማዘጋት በሚያደርስ መልኩእየበደለ ይገኛል፡፡ታዲያ ይህ የባለስልጣኑ ገቢዎች ሚኒስቴር ተግባር “እራሱ በድሎ እራሱ አለቀሰ”አያስብልም ወዳጆቼ?

በመጨረሻም በቅንነት ላስተናገዳችሁኝ እና ቃለ-መጠየቅ ለሰጣችሁኝ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ሰራተኞች

- አቶ ሲሳይ ገዙ ለታ፡ በኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ  ማጭበርበር ምርመራ ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር፤

- አቶ ተሾመ ወልዴ :በገቢዎች ሚኒስቴር የፍትሐብሄር ጉዳዮች ክትትል ቡድን መሪ፤

- አቶ ጌትነት አበባው፤የገቢዎች ሚኒስቴር የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ቴክኖሎጂ ቡድን አስተባባሪ

- ወ/ሮመሰረት ማናስቦ፡ በገቢዎች ሚኒስቴር የደረሰኝ አስተዳደር ቡድን አስተባባሪ፤

- እንዲሁም የተፈቀደለት የሂሳብ ባለሙያና ኦዲተር፡ አቶ ተገኝ ለገሠ

ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

A Brief Note on Ethiopia’s Tax Privileges to ease ...
የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ትኩረት ያልሰጠበት የገበያዉ ሁኔታ እና አተገባበሩ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 05 November 2024