Font size: +
5 minutes reading time (1069 words)

የተሻረው እና አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ድንጋጌዎች ንጽጽር በተለይም በጨው ምርት ላይ

በሀገራችን የኤክሳይዝ ታክስን በተመለከተ በሥራ ላይ የነበረው አዋጅ ቁጥር 307/2002 (እንደተሻሻለ) ተሽሮ በአዲስ የኤክሳይዝ አዋጅ ቁጥር 1186/2020 የተተካ ስለመሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ይህ ጽሁፍ ሁለቱ አዋጆች የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ዕቃዎችን፤ ታክሱን የመክፈል ግዴታን እና ታክሱ ስለሚሰላበት ስሌትን በተመለከተ ያስቀመጡትን ድንጋጌዎች ከጨው ምርት ጋር በተያያዘ በወፍ በረር ለማነጻጽር ነው፡፡

1. በተሻረው እና በአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ መሰረት ታክሱ የተጣለባቸው ዕቃዎች፤ ታክሱን የመክፈል ግዴታ እና ታክሱ የሚሰላበት ስሌት፤

1.1 የተሻረው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ፤

በቀድሞ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/2002 (እንደተሻሻለ) አንቀጽ 4 መሰረት የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ዕቃዎች በአገር ውስጥ ሲመረቱ (When produced locally) ወይም ከውጭ ወደሀገር ውስጥ ሲገቡ (When imported) የኤክሳይዝ ታክስ እንደሚከፈልባቸው የሚደነግግ ሲሆን፤ ታክሱን የመክፈል ግዴታ በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ 6 መሰረት በአገር ውስጥ በሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታ የተጣለው በአምራቹ (by the Producer) ላይ ሲሆን ወደ አገር ውስጥ በገቡ ዕቃዎች ላይ ደግሞ የመክፈል ግዴታ የተጣለው በአስመጭው (by the importer) ነው፡፡

በተሻረው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ የቃል ትርጉም ላይ ለአምራች የተሰጠው ትርጉም ባይኖርም ከአዋጁ ጠቅላላ ድንጋጌ አምራች ማለት የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸውን ዕቃዎችን የሚያመርት/Producer/ እንጂ፤ የሚፈበርክ/Manufacturer/ ማለት እንዳልሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ Producer ተብሎ በተሻረው አዋጅ ለተጠቀሰውም ሆነ Manufacturer ተብሎ በአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ላይ ለተጠቀሰው የኢንግሊዘኛ ቃል የተሰጠው የአማረኛ አቻ ትርጉም አምራች ቢሆንም Producer and Manufacturer የተለያዩ ትርጉም ያለቸው ቃላቶች ናቸው፡፡ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2016 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 14 መሰረት “Manufacturing” includes any formulation, alteration, assembling or processing…or operation activity carried out by using industry ማለት ነው፡፡

ይህ የቃል ትርጉም በአዋጁ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 13 ለኢንዱስትሪ ከተሰጠው ትርጉም ጣምራ ንባብ መደራት የሚቻለው Manufacturing ማለት ኢንዱስትሪን በመጠቀም በሞተር ኃይል የመቀመም፤ የመለወጥ፤ የመገጣጠም፤ የማሰናዳት ወይም የማምረት ሥራን ማከናወን ማለት ነው፡፡  ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በተሻረው አዋጅ መሰረት በጨው ላይ 30% የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለው በአምራቹ (Producer) በመሆኑ በጨው መሸጫና መግዥ የዋጋ ግንባታ ላይ 30% የኤክሳይዝ ታክስ የተካተተው በጥሬ ጨው አምራች ገበሬዎች የመሸጫ ዋጋ ብር 257.95 ላይ እንጂ፤ ኢንዱስትሪን በመጠቀም ጥሬ-ጨው በማሰናዳትና በማቀነባበር /Processing/ ለምግብ ወይም ለሌላ ጥቅም በሚፈበርኩ /Manufacturer/ ፋብሪካዎች የመሸጫ ዋጋ ብር 529.68 ላይ የኤክሳይዝ ታክስ አልተካተተም፡፡  

 

በተሻረው አዋጅ አንቀጽ 5 መሰረት በአገር ውስጥ ለተመረቱ ዕቃዎች የኤክሳይዝ ታክስ ስሌት የሚሰላው ከማምረቻ ወጪ (cost of production) ዋጋ ላይ ሲሆን፤ በአዋጅ አንቀጽ 2(8) መሰረት የማምረቻ ወጪ ማለት፡-ለምርት ተግባር በቀጥታ የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችና የጉልበት ዋጋ፤ ቀጥተኛ ያልሆኑ ግብዓቶች ወጪ እና ኦቨር ሄድ ወጪ ያካትታል፡፡ ለምሳሌ የቀድሞ የንግድ ሚኒስቴር ህዳር/2009 ዓ.ም የጥሬ ጨው አምራቾች በማምረቻ ቦታ እና በፋብሪካ የተቀነባበረ አዮዲን ያለው ጨው እስከ ተጠቃሚው ድረስ የዋጋ ግንባታ እና የገበያ ሰንሰለት በሚል በማወጣውና ተግባራዊ በመሆን በሚገኘው ሰነድ ውስጥ በተራ ቁጥር 12 ላይ አንድ ኩንታል ጥሬ ጨው ለማምረት የተያዘው የማምረቻ ወጪ ብር 95.12 ነው፡፡ ይህ ማለት በተሻረው አዋጅ ጨው 30% የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልበት ዕቃ/ምርት/ በመሆኑ የጨው አምራች የሆነ ገበሬ ኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታ ያለበት ሲሆን፤  ይህ አምራች ገበሬ የኤክሳይዝ ታክሱን የሚከፍለው ለማምረቻ ወጪ ተብሎ ከተያዘው ብር 95.12 በመሆኑ በኩንታል ሊከፍል የሚገደደው 30% × 95.12 = ብር 28.54 ነው፡፡

ማስታወሻ

የተሻረው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ የኤክሳይዝ ታክስ ስሌት እንዲሰላ ግዴታ ሲጥል የነበረው ከማምረቻ ወጪ (cost of production) ዋጋ በመሆኑ፤ የቀድሞ የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስቴር ህዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር 011.36/7879 የጥሬ ጨው አምራቾች በማምረቻ ቦታ እና በፋብሪካ የተቀነባበረ አዮዲን ያለው ጨው እስከ ተጠቃሚው ድረስ የመግዥና መሸጫ ዋጋ እና የገበያ ሰንሰለት ተግባራዊ እንዲሆን ባስተላለፈው ሰርኩላር ደብዳቤ ላይ 30% የኤክሳይዝ ታክስ ተካቶ የሚገኘው በጥሬ ጨው አምራቾች የመሸጫ ዋጋ ብር 257.95 ላይ እንጂ በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ ብር 529.68 ላይ የኤክሳይዝ ታክስ አልተካተተም፡፡

 

2. አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ፤

 

በሌላ በኩል በአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2020 አንቀጽ 5 መሰረት የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለው በ3 ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ይህም፡- a) በተፈቀደለት አምራች በኢትዮጵያ ውስጥ በሚመረቱ ዕቃዎች (Manufactured in Ethiopia by a licensed manufacturer); b) ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ዕቃዎች; እና c) በተፈቀደለት አገልግሎት ሰጪ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጡ የአክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው አገልግሎቶች ናቸው፡፡

በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 6 መሰረት የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታ የተጣለው ከላይ ከa እስከ c በተጠቀሰው ቅደም ተከተል መሰረት የተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) አስመጪው እና አገልግሎቱን ለመስጠት የተመዘገበው ሰው ናቸው፡፡ የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታ ከተጣለባቸው 3 አካላት መካከል ጸሃፊው በተፈቀደለት አምራች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጓል፡፡

በአዋጅ አንቀጽ 2(20) መሰረት የተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) ማለት የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ዕቃዎችን የሚያመርት በአዋጁ አንቀጽ 17 መሰረት ፈቃድ የተሰጠው ሰው ማለት ነው፡፡ በአዋጁ በአንቀጽ 18(2) መሰረት የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ዕቃዎች ለሚያመርት ሰው የሚሰጥ ፈቃድ የሚከተሉትን መያዝ አለበት፡-

  1. አምራቹ አንዲያመርት የተፈቀደለት ዕቃ ምድብ እና
  2. አምራቹ ምርቶችን እንዲያመርት የተፈቀደለትን ፋብሪካ ናቸው፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 18/3ና4/ መሰረት ፈቃድ የተሰጠው አምራች፡ በተሰጠው ፈቃድ የተመለከተው ፋብሪካ ማምረት የሚችለው በፈቃዱ የተመለከተውን ዕቃ ምድብ ብቻ እንደሆነ እና በተሰጠው ፈቃድ የተመለከተው ፋብሪካ ማምረት የሚችለው በፈቃዱ ላይ አምራች በሚል የተመለከተው ሰው ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡

በፈቃድ የተመለከተ ዕቃ ምድብ ማለት የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስቴር በ2012 ዓ.ም ባሳተመው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደቦች መመሪያ መሰረት በንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ ላይ የተመለከተ የሥራ መደብ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አምራች በፈቃዱ ላይ የተመለከተው ዕቃ ምደብ የምግብ ጨው ማምረት ከሆነ ይህ ባለፈቃድ በፋብሪካው ማምረት የሚችለው የምግብ ጨው ብቻ ሲሆን ባለፈቃዱ በፈቃዱ ላይ አምራች መባል አለበት፡፡ በሌላ አገላለጽ አምራች ተብሎ ባልተገለጸ ፈቃድ እና በፈቃዱ ላይ ያልተገለጸን ዕቃ ምድብ ማምረት ክልክል ነው፡፡

በአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 2(20) መሰረት ፋብሪካ/Factory/:- ማለት ፈቃድ የተሰጠው አምራች የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸውን ዕቃዎች የሚያመርትበት ወይም የሚያከማችበት ሥፍራ ሲሆን፤ የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸውን ዕቃዎች ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ለገበያ የሚቀርቡበትን ማናቸውንም የአምራቹን የሥራ ቦታ አይጨምርም፡፡ ይህ ማለት ባለፈቃዱ ያመረታቸውን ዕቃዎች ለምሳሌ የምግብ ጨው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል መጋዘን ወይም ሱቅ በማከማቸት ለተጠቃሚዎች የሚያቀርብበት ቦታ እንደ ፋብሪካ ሊቆጠር አይችልም፡፡ 

በመሆኑም በጸሃፊው እምነት በተሻረው አዋጅ መሰረት በአገር ውስጥ በሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የኤክሳይዝ ታክሱ የተጣለው በአምራቹ (Producer) በመሆኑ በጨው መሸጫና መግዥ የዋጋ ግንባታ ላይ 30% የኤክሳይዝ ታክስ የተካተተው በጥሬ ጨው አምራች ገበሬዎች የመሸጫ ዋጋ ብር 257.95 ላይ በመሆኑ፤ በተመሳሳይ በአዲሱ አዋጅ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚመረቱ ዕቃዎች መካከል በጨው ላይ 25% የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታ የተጣለው በተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) በመሆኑ ታክሱ የሚመለከተው አምራች ፋብሪካዎችን እንጂ፤ ጨው አምራች (Producer) ገበሬዎችን  አይመለከትም፡፡

ከላይ እንደተመለከተው በተሻረው አዋጅ አንቀጽ 6 መሰረት በአገር ውስጥ በሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታ የተጣለው በአምራቹ (by the Producer) በመሆኑ እና በአዋጁ አንቀጽ 5 መሰረት አምራቹ የሚከፍለው የኤክሳይዝ ታክስ ስሌት የሚሰላው ከማምረቻ ወጪ (cost of production) ዋጋ ላይ በመሆኑ፤ 30% የኤክሳይዝ ታክስ ተካቶ የሚገኘው በአምራች ገበሬዎች የመሸጫ ዋጋ ብር 257.95 ላይ እንጂ በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ ብር 529.68 ላይ የኤክሳይዝ ታክስ አልተካተተም፡፡

3. ማጠቃለያ

የቀደም የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ በአዲስ አንዲተካ ከተደረገበት ምክንያቶች መካከል በዋናነት በአዋጅ ቁጥር 1186/2020 መግቢያ/Preamble/ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው በማምረቻ ወጪ ላይ ሲሰላ የነበረውን የኤክሳይዝ ታክስ፤ በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ እንዲተካ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ በመሆኑ በጸሃፊው እምነት አዲሱ አዋጅ ሲሰራበት የቆየውን የኤክሳይዝ ታክስ ስሌት ከማምረቻ ወጪ ወደ ፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ እንዲተካ ያደረገ በመሆኑ በጨው ላይ የተጣለውን 25% የኤክሳይዝ ታክስ ክፍያ መካተት ያለበት በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ ብር 529.68 እንጂ፤ በጨው አምራች ገበሬዎች የመሸጫ ዋጋ ላይ ባለመሆኑ፤ ቀደም ሲል በጨው አምራች ገበሬዎች የመሸጫ ዋጋ ላይ ብር 257.95 ተካቶ የነበረው የኤክሳይዝ ታክስ በአዲሱ አዋጅ ተነስቷል፡፡  

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

አዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 ምን አዲስ ነገር ይዟል - በ...
የኑሮ ውድነት እና የሸማቾች መብት ጥበቃ በኢትዮጵያ ሕግ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Monday, 24 June 2024