አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 እየተሰራበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ስለኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 67/2013 ጸድቆ ከጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በመመሪያው አንቀጽ 38 ላይ በጨው ላይ የሚከፈል የኤክሳይዝ ታክስን በተመለከተ የሰፈረውን ድንጋጌ ከአዋጁ አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ አንጻር በጥቂቱ ለመዳሰስ ነው፡፡

 1. በጨው ምርትና ግብይት ላይ ወሳኝ ባለድርሻ አካላት

የንግድ ሚኒስቴር በደብዳቤ ቁጥር 011.36/7898፤ ህዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም የጥሬ ጨው አምራቾች በማምረቻ ቦታ እና በፋብሪካ የተቀነባበረ አዮዲን ያለው ጨው እስከ ተጠቃሚው ድረስ የዋጋ ግንባታ እና የገበያ ሰንሰለት በሚል ባመወጣው የመግለጫ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው ጨው ከማምረቻ ቦታ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ተጠቃሚ እስኪደርስ ድረስ በርካታ ባለድርሻ አካለት ከፍተኛ ሚናና ተሳትፎ ያላቸው ቢሆንም የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት ጥሬ ጨው አምራቾች /Salt Producers/  እና አዮዲን ያለው ጨው እና የታጠበ ጥሬ ጨው አምራች ፋብሪካዎች /Salt Manufacturers/ ናቸው፡፡ 

ጥሬ ጨው አምራቾች /Salt Producers/ ማለት ምንም እሴት ሳይጨምሩ ከባህላዊ ፈቃድ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ ፈቃድ በማውጣት ጥሬ ጨውን በማሳ (በማምረቻ ቦታ) ላይ የሚያመርቱ አምራች ገበሬዎች ናቸው፡፡ የማዕድን ሥራዎች አዋጅ ቁጥር 678/2002 (እንደተሸሻለ) እና ደንብ ቁጥር 423/2010 ጨውን ጨምሮ በሌሎች የማዕድን ሥራዎች ላይ ገዥ ህጎች ናቸው፡፡ የጨው አምራች ለመሆን የፈለገ ሰው በእነዚህ ህጎች ላይ በተደነገገው መሰረት ፈቃድ የማውጣትና የማደስ፤ የሮያሊቲና የመሬት ኪራይ የመክፈልና ሌሎች መብትና ግዴታዎች ተካተው ይገኛሉ፡፡

በሌላ መልኩ ጨው አምራች ፋብሪካዎች /Salt Manufacturers/ ማለት ከጥሬ ጨው አምራቾች ላይ ጥሬ ጨውን በመግዛት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በዘመናዊ መልኩ እሴት በመጨመር አዮዲን ያለው ጨው እና የታጠበ ጨውን በማምረት ለተለየ ዓላማ እንዲውል የሚያደርጉ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ ይህ ማለት እነዚህ ጨው አምራች ፋብሪካዎች 2 ሥራዎችን ያከናውናሉ ይህም፤ የምግብ ጨው ማቀነባበር እና ጥሬ ጨውን በፋብሪካ አጥቦ ለገበያ ማቅረብ ነው፡፡

በመሆኑም በጨው ምርትና ግብይት ላይ የአንበሳውን ድርሻ ከያዙት ከእነዚህ ሁለት ወሳኝ ባለድርሻ አካላት መካከል የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ስለኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ አፈፃፀም ባወጣው መመሪያ ቁጥር 67/2013 ከታች እንደተመለከተው በአንቀጽ 38 ላይ የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታን በጥሬ ጨው አምራቾች ላይ/Salt Producers/ እንዲጣል አድርጎ፤ ጨው አምራች ፋብሪካዎችን /Salt Manufacturers/ ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ ያደረገበትን አግባብ ከአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 ድንጋጌዎች አንጻር ይዳሰሳል፡፡

አንቀጽ 38.   በጨው ላይ የሚከፈል የኤክሳይዝ ታክስ

 

2. የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለው በምን ላይ ነው፤ (What?)

በአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 አንቀጽ 5 መሰረት ታክሱ የተጣለው በ3 ነገሮች ላይ ነው፡፡

ከላይ በተራ ቁጥር 1 ላይ ከሰፈረው ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ ሁሉም ዕቃዎች/ምርቶች/ ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ያልተጣለባቸው ስለመሆኑ፤ ሆኖም ሕጉ ለይቶ የኤክሳይዝ ታክስ በጣለባቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈቀደለት አምራች የሚመረቱ ዕቃዎች/ምርቶች/ ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ይከፈልባቸዋል ማለት ነው፡፡

በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 1186/2012 መሰረት ጨው 25% የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልበት ዕቃ/ምርት/ በመሆኑ፤ ለምሳሌ አንድ የተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) በኢትዮጵያ ውስጥ ጨው ቢያመርት፤ ይህ የተፈቀደለት አምራች ባመረተው የጨው ምርት ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ይከፍልበታል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መመሪያ ቁጥር 67/2013 በአንቀጽ 38(1) ላይ ጨው የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልበት ምርት እንደሆነ መደንገጉ ከአዋጁ ጋር የሚጣጣምና ተቀባይነት ያለው ነው፡፡

 

3. የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለው በማን ላይ ነው፤ (Who?)

በኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 አንቀጽ 6 መሰረት የኤክሳይዝ ታክስ በተጣለባቸው ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ታክሱን የመክፈል የሕግ ግዴታ የተጣለው በአዋጁ አንቀጽ 5 እንደተቀመጠው ቅደም ተከተል: 1) የተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer)፤ 2) አስመጪው (Importer) እና 3) አገልግሎቱን ለመስጠት የተመዘገበው ሰው ነው፡፡   

በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ የኤክሳይዝ ታክስ በተጣለባቸው ዕቃዎች ላይ በአዋጁ መሰረት ታክሱን የመክፈል የሕግ ግዴታ የተጣለው የተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) እንደሆነ በግልጽና በማያሻማ መልኩ ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ከላይ እንደተመለከተው መመሪያው በአንቀጽ 38 ላይ በአዋጁ በተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) ላይ የተጣለውን የኤክሳይዝ ታክስ በተጻረረ መልኩ ታክሱን የመክፈል ግዴታን በጥሬ ጨው አምራች /Salt Producer/ ላይ እንዲጣል አድርጎ፤ ለተለየ ዓላማ በፋብሪካ የሚመረት ጨው ታክሱ አይከፈልም በሚል ጨው አምራች ፋብሪካዎችን /Salt Manufacturers/ ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ ያደረገበት ድንጋጌ የአዋጁን አንቀጽ 6 የተጻረረ ነው፡፡  ምክንያቱም በአዋጁ አንቀጽ 6 መሰረት የኤክሳይዝ ታክስ በተጣለባቸው ምርቶች ላይ ታክሱን የመክፈል ግዴታ የተጣለው በተፈቀደለት አምራች ላይ በመሆኑ፤ በጨው ላይ የተጣለውን የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታ ያለበት የተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) እንጂ፤ የሚያመርት ሰው /Producer/ አይደለም፡፡

በአዋጁ በተሰጠው ትርጉምና ድንጋጌዎች መሰረት የተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) እና የሚያመርት ሰው /Producer/ ማለት የየቅል በመሆናቸው፤ በጸሃፊው እምነት በመመሪያው አንቀጽ 38(1) ላይ...በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያመርት ሰው…...በሚል የሰፈረው ሃረግ፤….በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈቀደለት አምራች….. በሚል መቀመጥ ሲገባው እንደዋዛ የሚያመርት ሰው ተብሎ በመመሪያው የተቀመጠው ድንጋጌ ከአዋጁ የተለየ ትርጉም የሚሰጥ እና መመሪያው ታክሱን የመክፈል ግዴታ ከተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) አንስቶ ወደ የሚያመርት ሰው /Producer/  የሚጥል በመሆኑ፤ በመመሪያው በአንቀጽ 38 የሰፈረው ድንጋጌ ከአዋጁ ጋር ፈጽሞ የተጻረረ ነው፡፡

 

4. የተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) ማን ነው?

በኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 አንቀጽ 2(20) መሰረት “የተፈቀደለት አምራች” (Licensed manufacturer) ማለት፡ የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ዕቃዎችን የሚያመርት በአዋጁ አንቀጽ 17 መሰረት ፈቃድ የተሰጠው ሰው ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ በመመሪያው አንቀጽ 2(መ) መሰረት “የተፈቀደለት አምራች” ማለት፡ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ዕቃዎች ለማምረት ፈቃድ የተሰጠው በኢትዮጵያ ውስጥ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ዕቃዎች የሚያመርት ሰው ነው፡፡

በመሆኑም በአዋጁም ሆነ በመመሪያው ትርጉም መሠረት “የተፈቀደለት አምራች” ለመሆን ከታች የተመለከቱትን 2 የማይነጣጠሉ መስፈርቶችን አሟልቶ መገኘት የግድ ነው፡፡ እነዚህም፡-

ለምሳሌ አንድ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ የኤክሳይዝ ታክስ ከሚከፈልባቸውን ዕቃዎች መካከል አንዱን የሚያመርት ሆኖ ነገር ግን ይህ ሰው እያመረተ በሚገኘው ዕቃ/ምርት/ ላይ በአዋጁ በተሰጠው የፈቃድ ትርጉምና ድንጋጌ መሰረት ከታክስ ባለሥልጣኑ ፈቃድ ካልተሰጠው “የተፈቀደለት አምራች” ሊባል አይችልም፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 15 መሠረት ማንኛውም ሰው ከታክስ ባለሥልጣኑ ፈቃድ ካላገኘ በስተቀር በኢትዮጵያ ውስጥ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ዕቃዎች የማምረት ሥራ መስራት እንደማይችል በግልጽና በማያሻማ መልኩ ተደንግጓል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2(29) መሠረት “የታክስ ባለሥልጣን” ማለት፡ የገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም የየክልሉ እና የከተማ አስተዳደሮች የገቢ ሰብሳቢ አካላት ማለት በመሆኑ፤ ከእነዚህ አካላት ፈቃድ ሳይሰጥ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ዕቃዎች የሚያመርት ሰው “የተፈቀደለት አምራች” ሊባል አይችልም፡፡

በመሆኑም “የተፈቀደለት አምራች” ለመባል ከፌዴራል ወይም ከክልል የገቢ ሰብሳቢ አካላት በአዋጁ በተመለከተው የፈቃድ አሰጣጥና የፈቃድ ቅርጽ መሰረት ፈቃድ የማግኘት ጉዳይ ቀደሚ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም በጨው ላይ የተጣለውን የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታ ያለበት ከታክስ ባለሥልጣኑ ፈቃድ የተሰጠው የተፈቀደለት አምራች ሆኖ እያለ፤ መመሪያው በአንቀጽ 38(1) ላይ በአዋጅ ስለ ተፈቀደለት አምራች የተሰጠውን ትርጉምና ድንጋጌ በተጻረረ መልኩ፤ በጨው ላይ የተጣለውን የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታን በተፈቀደለት አምራች ላይ ሳይሆን፤ በሚያመርት ሰው ላይ በመጣል ታክሱን የመክፈል ግዴታን በጥሬ ጨው አምራቾች ላይ አድርጎ፤ ጨው አምራች ፋብሪካዎችን ከታክሱ ነጻ በማድረግ ያሰፈረበት አግባብ ከአዋጁ ጋር የሚጻረር ነው፡፡

 

5. ከታክስ ባለሥልጣን የሚሰጥ ፈቃድ እና ቅርጽ

በአዋጅ ቁጥር 1186/2012 አንቀጽ 2(18) መሰረት “ፈቃድ” ማለት……የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸውን ዕቃዎች በሚመለከት እነዚህን ዕቃዎች ለማምረት በአዋጁ አንቀጽ 17 መሠረት የሚሰጥ ፈቃድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ዕቃዎች ለማምረት የፈለገ ሰው በአዋጁ አንቀጽ 15 መሠረት ፈቃድ እንዲሰጠው ለታክስ ባለሥልጣኑ ማመልከቻ ማቅረብ ያለበት ሲሆን፤ በአዋጁ አንቀጽ 17 መሠረት የታክስ ባለሥልጣኑ የቀረበውን የፈቃድ ማመልከቻ በመመርመር ፈቃዱን ሊሰጥ ወይም ሊከለክል ይችላል፡፡

አዋጁ የታክስ ባለሥልጣኑ ፈቃድ ሊሰጥ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ከመዘርዘር ይልቅ በአንቀጽ 17 (2) ላይ የታክስ ባለሥልጣኑ ፈቃድ ሊከለክል የሚችልባቸውን ሁኔታዎች አሟጦ ሳይሆን ለማሳያነት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ዝርዝር ሁኔታዎች ውስጥ በአዋጁ በአንቀጽ 17 (2) (መ) እንደተቀመጠው አመልካቹ ያቀረበው የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ምርቶች ለማምረት ከሆነ በማመልከቻው የተመለከተው ፋብሪካ፤ ማምረቻ፤ መሣሪያ (the factory, plant or equipment) ምርቱን ለማምረት በቂ ካልሆነ ነው፡፡

በመሆኑም በአዋጁ በአንቀጽ 17 (2) (መ) የተዘረዘሩት መስፈርቶችና ሁኔታዎች የሚያመለክቱት ስለ አምራች ፋብሪካዎች /Salt Manufacturers/ እንጂ፤ ጥሬ ጨው አምራች/Salt Producers/ ባለመሆኑ፤ ለታክስ ባለሥልጣኑ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን የጨው ምርት ለማምረት ፈቃድ እንዲሰጠው ማመልከቻ ማቅረብ ያለበት እና በማመልከቻው ላይ የተመለከተው የጨው ፋብሪካ የምግብ ጨው ወይም የታጠበ ጥሬ ጨው ለማምረት በቂ መሆኑን የማስረደት ግዴታ ያለባቸው ጥሬ ጨው አምራች /Salt Producers/ ሳይሆኑ፤ አምራች ፋብሪካዎች /Salt Manufacturers/ ናቸው፡፡

በአዋጁ በአንቀጽ 18(2) መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸውን ዕቃዎች ለማምረት የፈለገ ሰው ያቀረበውን የፈቃድ ማመልከቻ የታክስ ባለስልጣኑ ማመልከቻውን መርምሮ ፈቃድ የሚሰጥ ከሆነ የፈቃዱ ቅርጽ የሚከተሉትን መያዝ አለበት፡-

ይህ ማለት ለምሳሌ ጨው የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልበት ዕቃ/ምርት/ በመሆኑ ይህንን ምርት ለማምረት የፈቃድ ማመልከቻ አቅርቦ የታክስ ባለስልጣኑ ፈቃድ የሰጠው ከሆነ፤ አምራቹ በሚሰጠው ፈቃድ ላይ እንዲያመርት የተፈቀደለት የዕቃ ምድብ ጨው መባል ያለበት ሲሆን፤ እንዲያመርት የተፈቀደለት ፋብሪካ ደግሞ የጨው ፋብሪካ ተብሎ በፈቃዱ ላይ መገለጽ አለበት ማለት ነው፡፡

 

6. ማጠቃለያ

አንድ መመሪያ የሚወጣው በአዋጅ ወይም በደንብ ላይ የተደነገጉ የሕግ ድንጋጌዎችን መሰረት አድርጎ ለአፈጻጸም አመች በሆነ መልኩ በዝርዝር ለማብራራት እንጂ፤ በአዋጁ ወይም በደንቡ ላይ ከሰፈረው ድንጋጌዎች ጋር የሚጣረስ ወይም አዲስ ድንጋጌ ለማውጣት አይደለም፤ ይህ ሆኖ ከተገኘ እንኳን መመሪያው ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡  

የቀደም የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 307/2002(እንደተሻሻለ) በአዲስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 አንዲተካ የተደረገበት ዋና ምክንያት በአዋጁ መግቢያ ምዕራፍ 2 ላይ በግልጽ እንደተመለከተው በማምረቻ ወጪ (production cost) ላይ ሲሰላ የነበረውን የኤክሳይዝ ታክስ፤ በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ (by ex-factory price) እንዲተካ ስለታመነበት እንደሆነ በማያሻማ መልኩ ይደነግጋል፡፡ WHEREAS, it is believed that replacement of the current excise tax which was assessed on production cost by ex-factory price……

 

በመሆኑም በአዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 አንቀጽ 6 መሰረት በተፈቀደለት አምራች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ የኤክሳይዝ ታክስ በተጣለባቸው ዕቃዎች ላይ ታክሱን የመክፈል የሕግ ግዴታ የተጣለው በተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) ላይ በመሆኑ፤ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ስለኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ አፈፃፀም ባወጣው መመሪያ በጨው ላይ የተጣለውን የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታን በተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) ላይ ማድረግ ሲገባው፤ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በመመሪያ ቁጥር 67/2013 በአንቀጽ 38 ላይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እነደዋዛ.…በሚያመርት ሰው /Producer/ በማለት ታክሱን የመክፈል ግዴታን በጥሬ ጨው አምራቾች ላይ እንዲጣል አድርጎ፤ ጨው ለተለየ ዓላማ እንዲውል ለማድረግ ጨውን በፋብሪካ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን የኤክሳይዝ ታክስ እንዳይከፍሉ ማድረጉ ከላይ በዝርዝር እንደተመለከተው በመመሪያው አንቀጽ 38 የሰፈረው ድንጋጌ ከአዋጁ ድንጋጌዎች ጋር የሚቃረን ነው፡፡

በመሆኑም በአዋጁ አንቀጽ 6 መሰረት የኤክሳይዝ ታክስ የመክፈል ግዴታ የተጣለው በኢትዮጵያ ውስጥ  የተፈቀደለት አምራች (Licensed manufacturer) ላይ እንጂ፤ በሚያመርት ሰው /Producer/ ላይ የተጣለ ግዴታ ባለመኖሩ፤ በጸሃፊው እምነት በመመሪያው አንቀጽ 38 ላይ በጨው ላይ የሚከፈል የኤክሳይዝ ታክስን በተመለከተ የሰፈረው ድንጋጌ ከአዋጁ ጋር በተጣጣመ መልኩ መሻሻል ይገባዋል፡፡