በኮሮና ወረርሽኝ ፍርድ ቤቶችን እንዴት ማስቀጠል ይቻላል?

እርግጥ ነው አሁን ያለንበት የኮሮና ቫይርስ ወረርሽኝ ወቅት እጅግ ፈታኝ፣ ፈጣን አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመስጠት የሚከብድበት የቱ ትክክልየቱ ስህተት እንደሆነ ለማመዛዘን የሚቸግር ጊዜ ነው፡፡ በተለይም በወረርሽኙ ምክንያት የሰዎች ህይወት አደጋ ላይ መውደቁ ሲታይ አሳሳቢና አስጨናቂ ነው፡፡

በዛው መጠን ደግሞ በማዕበሉ ወቅትም ቢሆን ህዝብና የመንግሥት አስተዳደር ይቀጥላል፡፡ ፍርድ ቤቶች ደግሞ እጅግ በጣም አስፈላጊና ወሳኝየህዝብ አገልግሎት ሰጪ አካላት መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ሐቅነው፡፡ ፍ/ቤቶች ከሶስቱ የመንግሥት አካላት (the three organs of Government/state) አንደኛው ቅርንጫፍ/አካል ናቸው፡፡ ሌሎቹ የመንግሥት አካላት(አስፈፃሚውና ሕግ አውጪው) ሥራቸውን እያስኬዱ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም በወረርሽኙ ምክንያት የሰውን ህይወት ለአደጋ በማያጋልጥና በጥንቃቄ ሥራቸውን የሚያስኬዱበት መንገድ ሊፈተሸ ይገባል፡፡

በጣም የሚያስደነግጠው ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ‹‹የኮሮና ቫይረስ ለማጥፋት በርካታ ዓመታት ሊወስድ ይችላል፡፡ የሚጠፋበት ጊዜ ቅርብ አይደለም እንደውም እንደ ኤች.አይ.ቪ ላይጠፋ ይችላል›› የሚል መግለጫን አውጥቷል፡፡

ስለዚህ ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች ወሳኝ አገልግሎት ሰጪ አካላት በቀጣይ ከቫይረሱ ጋር በጥንቃቄ ህይወት የሚቀጥልበትን መንገድ ሊያስቡበት ግድ ይላቸዋል ማለት ነው፡፡ እጅን አጣጥፎ ‹‹ጥሩ ቀን ቶሎ ና›› እያሉ ብቻ መጠበቅ አያስኬድም አያዋጣም፡፡

እጅግ ብዙ የሕግ ክፍተት ላለባት፣ ሕግን ለማስከበር የአሠራር ማነቆዎች በሞሉበት፣ የፍትሕ ጥማት ላለባት ሀገር መንግሥትም እነዚህን ጎዶሎዎች ለመሙላት ደፋ ቀና በሚልበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የፍ/ቤቶች ሚናና አገልግሎት እንደ ህዝብ ከመቀጠል አለመቀጠል ከመኖርና አለመኖርጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው፡፡

እስቲ አስቡት በእጁ የፍርድ ቤት ውሳኔ አንከርፍፎ ግን ውሳኔውን ማስፈፀም ባለመቻሉ ቤተሰቡ በችግሩ ምክንያት ሊበተን መሆኑን ሲነገርህ፤ ሠራተኛ ደመወዙን ተከልክሎ ወይም ከሥራው ተሰናብቶ ክስ አቅርቦ መብቱን ሊያስከበር ሲያስብ አሁን መዝገብ መክፈት አትችልም ጠብቅ ተብሎ ሲመለስ፤ በጥሩ የሥራ ግንኙነት ወቅት ወይም በደህና ጊዜ ገንዘቡን አበድሮ ዛሬ የሚበላ የሚቀመስ ሲያጣ የአገልግሎቱን ወይም ያበደረውን ገንዘብ እንዲሰጠው ሲጠይቅ በብልጣብልጥ/ክፉ ባላጋራው ገንዘቡን የተከለከለ ግለሰብ ለጊዜው ክስ መስርተህ መዘግብ ከፍተህ መጠየቅ አትችልም ሲባል፤ ቤቱን፣ ይዞታውን ወይም መሬቱን የተነጠቀ ዜጋ ሜዳ ላይ ወድቂያለሁ ብሎ ሲያማክር አሁን ክስ ማቅረብ አትችልም መጠበቅ አለብህ የሚል መልስ ሲሰጠው፤ እነዚህ ዜጎች ከኢኮኖሚ ጉዳታቸው ባሻገር ውስጣቸው የሚሰማቸውን የተስፋ ማጣት ስነ-ልቦና ማየት ይሰቀጥጣል፡፡ እንዲሁም አሁን ያለው የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በቫይረሱ ወረርሽኝ ምክንያት በእጅጉ እንደተጎዳ ግልፅ ነው፡፡ በዚህ ጉዳት ላይ የአንዳንድ ተንኮለኛ ግለሰቦች/ድርጅቶች የተዛባ የንግድና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው ተጨምሮበት በፍርድ ቤቶች የሕግ ማስከበር ሂደት ሃይ ካልተባሉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ ነው የሚሆነው እንዴት ሊዘለቅ ነው ምን ልንሆን ነው ያስብላል ብዙ ጥያቄም ያጭራል፡፡የሕግ የበላይነትም በእጅጉ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል፡፡

እና መፍትሔ ምንድነው? መላ ምቱ እስቲ? ፍርድ ቤቶች እንዴት ይቀጥሉ?

WHO ቫይረሱ ከእኛ ጋር ለዘላለም ሊቆይ ይችላል የሚል መግለጫ ከሰጠ መቼም ቫይረሱ እስኪጠፋ ፍርድ ቤቶቻችን ተዘግተው ይቆያሉ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ በሆነ መንገድ የፍትሕ መርከቧ ጉዞዋን መቀጠል አለባት፡፡ የጤና ባለሙያዎች ምክራቸው ወሳኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እንዲሁም የፍ/ቤት ኃላፊዎች የመፍትሔ ሀሳብ እንዳላቸውና እየተዘጋጁበት እንደሆነ ባምንም ፍ/ቤቶች በቀጣይ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዴት ሥራቸውን ማስቀጠል ይችላሉ የሚለውን በተመለከተ እንደ አንድ ቅን ዜጋና የሕግ ባለሙያ እይታ ተከታዩን የመፍትሔ አቅጣጫዎች ማሳየትና ሀሳቤን መግለፅ እፈልጋለሁ፡-

1ኛ. መዝገቦችን ዘርዘር አድርጎ መቅጠርና case flow management በተመለከተ፡-

  • ፍርድ ቤቶች ተዘግተው ይቆዩ ተብሎ የተወሰነበት ዋናው ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ባለጉዳዮች በአንድ ጊዜ የሚሰተናገዱበት የሚጨናነቅና ንክኪ የሚበዛበት ቦታ ስለሆኑና ይህም ለቫይረሱ መሰራጨት ምክንያት ይሆናል ከሚል ግንዛቤ ነው፡፡ ትክክልም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በፍርድ ቤቶች እና በእያንዳንዱ ችሎት በቀን የሚስተናገደውን የመዝገብ ብዛት መቀነስ አንዱ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡

ቀድሞም ቢሆን ፍርድ ቤቶቻችን(በተለይ ፌዴራል ፍ/ቤቶች) ከፍተኛ የሆነ የሥራ ጫና እንዲሁም ከፍተኛ የመዝገብ ፍሰት እንዳለበቻው የታወቀ ነው፡፡ የፌዴራል ፍ/ቤቶች እስከ ግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በከፊል ዝግ ሆነው እንደሚቆዩ የተወሰነ ሲሆን፣ የወደፊቱን ማንም እርግጠኛ አይደለም ሆኖም ሰኔ 01 ቀን 2012 ዓ.ም ፍርድ ቤቶቹ ተከፍተው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሎ ቢገመት እንኳን ከተዘጉ ሦስት ወራት ቆይታ በኃላበድጋሚ ሲከፈቱ የሚኖረውን የመዝገብ ፍሰት እና አዲስ የሚከፈተው መዝገብ ብዛት ሲታሰብ ይጨንቃል ጎርፍ ነው የሚሆነው፡፡ይህም ሊታሰበብበት ይገባል፣ ምናልባትም ለተወሰነ ጊዜ በፊደል ቅደምተከተል መዝገብ መክፈቻ ቀን በመለየት ፍሰቱን መቀነስያስፈልግ ይሆናል፡፡ የቀድሞውን የመዝገብ ፍሰት ስንመለከት እንደኔ እይታ በአንድ ችሎት በቀን ከ15-20 የሚሆን መዝገብ ያስተናግዳል፡፡ ከዛም በላይ ቁጥር ያለው መዝገብ የሚያስተናግዱ ችሎቶች ይኖራሉ፡፡ በአንድ ችሎት በቀን በአማካይ 20 መዝገብይስተናገድ ነበር ብለን እንያዝ፡፡ በተለመደው አሠራር ከሳሽ ተከሳሽ ኖሮት ጠበቃ ካለና ባለጉዳዩም አብሮት ካለ በአንድ መዝገብ በአማካይ አራት ሰው ይመጣል ብለን ብንገምት፣ በአንድ ችሎት በቀን 80 ሰውይመጣ/ይስተናገድ ነበር ማለት ነው፡፡ በአንድ ምድብ ላይ 20 ችሎቶች ቢኖሩ ደግሞ በአንድ ምድብ በአንድ ቀን ብቻ (80*20) 1600 ሰው ይስተናገድ ነበር ማለት ነው:: ይህም ስሌት መደበኛ ቀጠሮ ያለውን ባለጉዳይ ብቻ እንጂ አዲስ መዝገብ ሊከፍት የሚመጣውን፣ ከመደበኛ ቀጠሮ ውጪ አቤቱታ ሊያስገባ የሚመጣውን፣ጉዳይ አስፈፃሚውን እንዲሁም የራሱ ጉዳይ ሳይኖረው የቤተሰቡን ወይም የወዳጁን ጉዳይ ለመታዘብ፣ ለትምህርት ወይም በሌላ ምክንያት ወደ ፍ/ቤት የሚመጣውን ሰው ሳንቆጥር ነው፡፡ ይህን ቁጥር በእጅጉ በሚቀንስ መልኩ መዝገቦች እንዲቀጠሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ችሎት በቀን ቢበዛ ከአሥር ያልበለጠ መዝገብ መቅጠር፡፡ ይህም ብዛት ያላቸውን ምስክር፣ በአንድ መዝገብ ቁጥራቸው ከፍ ያለ ባለጉዳይ ያላቸውን መዘገቦችን ከግንዛቤ በማስገባት ጭምር ማለት ነው፡፡ የምርመራ ቀንና የአቤቱታ ቀንተብለው የሚቀነሱ የሥራ ቀናት ሲታሰቡ በፍ/ቤት የሚሠራው የመዝገብ ብዛት እጅጉን የተገደበና ተገልጋዩን ላያረካ ይችላል ሆኖም ይህንን የዳኞችና የረዳት ዳኞች ቁጥር በመጨመር ከተቻለም የሥራ ሰዓትን በማራዘም ማካካስ ይቻል ይሆናል፡፡

  • መዝገቦችን በሰዓት ለያይቶ መቅጠር፡፡ ይህ አሠራር በአጠቃላይ ለፍትሕ አሰጣቱ እጅግ ወሳኝ የሆነና ቀድሞም ቢሆን በአግባቡ ሊሠራበት ይገባ የነበረና ለመተግበርም ብዙም አስቸጋሪ ባይሆንም እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው በጥቂቱ እየተጀመረ ብቻ የሚተው ከጥቂት ችሎቶች በስተቀር ሲተገበር የማይታይ ጉዳይ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ case flow management በተመለከተ ችሎቶች በሰዓት እንዲቀጥሩ መመሪያ እየተዘጋጀ እንደሆነ የተነገረ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ያን ያህል ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለጉዳዮችና ጠበቆች የራሳችን ችግር እንዳለብን እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ቅድሚያ ዳኞች ችሎቱን በአግባቡ መምራት(Manage ማድረግ) አለባቸው፡፡ በሀገሪቷ ትልቁ ፍ/ቤት ከጠዋቱ 2፡30 ላይ ድረስ ተብለህ ተቀጥረህ ቀኑን ሙሉ ልትውልም ትችላለህ፡፡ ዳኞች ችሎት ከመግባታቸው በፊት በፅ/ቤቶቻቸው እየሠሩ እንደሆነ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ባለጉዳዩን የሚያስተናግዱበት ልከኛ ሰዓት ማሳወቁና በተባለው ሰዓትም ማስተናገዱ ግድ ይላል፡፡በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ችግር ለመቅረፍ አልተቻለም፡፡ የፍ/ቤቶቻችን Achilles Heel ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን በዚህ ወቅት በጣም ወሳኝ የሆነ መፍትሔ በመሆኑ በቁርጠኝነት መተግበር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ከላይ በተራ ቁጥር 1.1 ላይ የተገለፀውን ስሌት ይዘን በአንድ ችሎት በቀን 10 መዝገብ የሚስተናገድ ቢሆን በሦስት፣አራት፣አምስት ሰዓት ጠዋት እንዲሁም 8፣9 እና 10 ሰዓት ከቀጥር በኃላ እየተባለ በሰዓት ከፋፍሎ ቢቀጠር በየሰዓቱ 1.66 መዝገብ ብቻ ይስተናገዳል ማለት ነው፣ የባለጉዳይ ፍሰቱንም በዛው መጠን እጅግ ይቀንሰዋል፡፡
  • ቀድሞ ውሳኔ አግኝተው የይግባኝ እግድ የሌለባቸውን ወይም የመጨረሻ ፍርድ ያገኘቱን ለአፈፃፀም የደረሱ ጉዳዮችን፣ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮች፣ የቤተሰብ ጉዳዮች(የህፃናትና ባልና ሚስት)፣ የመሳሰሉ ብዙም ውስብስብነት የሌላቸውንና ቅድሚያ መፍተሔ ሰጥቶ መሸኘት የሚቻሉ ጉዳዮችን ለይቶ በተቻለ መጠን ቅድሚያ ሰጥቶ መፍትሔ መስጠት፡፡
  • እንደጉዳዩ ክብደትና አስፈላጊነት በቅድሚያ የሚስተናገደው እንደተጠበቀ ሆኖ ሲንከበላሉና ውሳኔ ሳይሰጣቸው የቆዩ(Backlogs) መዝገቦችን በቅድሚያ መፍትሔ ለመስጠት መሞከር፡፡
  • ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱት ሁኔታዎች በየደረጃው ባሉ ፍ/ቤቶች፣ በየምድብ ችሎቱ እና በየችሎቱ ነባራዊ ሁኔታና የሚያስተናግደው የጉዳይ ዓይነት አንፃር እየታየ ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ፡፡

2ኛ. የባለጉዳይ መስተንግዶና የፍ/ቤቶችን ቦታዎች በአግባቡ መጠቀም (Spatial utilization) በተመለከተ፡-

2.1. አብዛኞቻችን የፍርድ ቤቶች ጥበትና የኮሪደራቸው መጨናነቅ ያሳስበናል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በደንብ ከታሰበበት አሁን ባለው ሁኔታ አብዛኞቹ የፌዴራል ፍ/ቤቶች ሰፋፊ ግቢ ያላቸው በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ባለጉዳዮቻቸውን እያስተናገዱ ከሚገኙት ተቋማት ለምሳሌ ከሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ፅ/ቤቶች፣ ከገቢዎች ፅ/ቤት፣ ከወረዳ ፅ/ቤቶች እንዲሁም ከአብዛኞቹ መንግሥታዊ ቦታዎች በተሻለ ባለጉዳዮችን እርቀታቸውን በጠበቀ መልኩ ለማስተናገድ አመቺ ቦታ አላቸው ወይም ሁኔታዎችንም መፍጠር ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ በፍ/ቤቶች ግቢ ውስጥ ከዝናብና ከፀሐይ የሚከላከሉ መጠለያ ተሰርቶ ወይም ካልተቻለም በአራቱም አቅጣጫ ክፍት የሆኑ ጥሩ ዳስ/ድንኳን በመጣል ባለጉዳዮች በዳኞች እስኪጠሩና ተራቸው እስኪደርስ ድረስ የፍ/ቤቱ ህንፃ ውስጥ ወይም ዳኛ ፅ/ቤት መግባት ሳያስፈልጋቸው ርቀታቸውን ጠብቀው ዘርዘር ብለው የሚጠብቁበት ቦታ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ምድብ ችሎቶች ብንመለከት የቂርቆስ ምድብ፣ ልደታ፣ የካ ፣ን/ስ/ላፍቶ እና አቃቂ/ቃ ምድብ ችሎቶች እንዲሁም ፌ/ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ዋናው ግቢ፣ ፌ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ግቢ ጊዜያዊ መጠለያዎችን መሥሪያ ቦታዎች አሏቸው ወይም ደግሞ ቀድሞም የተሠሩ መጠለያዎች አሏቸው፡፡ በእነዚህ መጠለያዎች ውስጥ ባለጉዳዮች ርቀታቸውን ጠብቀው ወደ ህንፃ ወይም ዳኞች ፅ/ቤት መግባት ሳይጠበቅባቸው ተራቸው እስኪድርስ የሚቆዩበት ማረፊያ ቦታቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህም ተገቢው ርቀት በጠበቀ መልኩ ባለጉዳይ ማስተናገድ ይቻላል፡፡

2.2. የባለጉዳይ ስምና መዝገብ ቁጥር የያዘ የቀጠሮ እና ተራ ማሳወቂያ(print) ከሳምንት በፊት በደህና የማስታወቂያ ቦርድ ላይ ከፍ/ቤት ቅጥር ግቢ ወይም ህንፃ ውጪ እንዲለጠፍ ማድረግና ይህንንም የተራ ማሳወቂያ ግልባጭ ለፍ/ቤቱ ጥበቃ ወይም ሠራተኛ መስጠት፡፡

2.3. መጨናነቅን ለመቀነስ ከቀጠሮ ሰዓታቸው አንድ ሰዓት ወይም 30 ደቂቃ አስቀድመው የሚመጡ ባለጉዳዮችን ወደ ፍ/ቤት ቅጥር ግቢ አለማስገባትና ሰዓታቸውን እንዲጠብቁ ማሳወቅ፡፡ ለዚህም ለፍ/ቤቶች ጥበቃ ተገቢውን መመሪያ መስጠትና የጥበቃ አካሉምበአግባቡ ስለመፈፀሙ ክትትል ማድረግ፡፡

2.4. ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ በፍ/ቤት ቀጠሮ ያለውን ባለጉዳይ ብቻ ማስተናገድ፡፡ ለዚህም አፈፃፀም ጠበቆች ተገቢውን ውክልና እና ጥብቅና ፍቃዳቸውን፣ ባለጉዳዮች መታወቂያቸውን፣ ምስክሮች መታወቂያቸውንና መጥሪያ እንዲይዙ አስቀድሞ ማሳወቅና ማስጠንቀቅ፡፡ ባለጉዳይ ለማጀብ፣ እንዲሁ ለመታዘብ፣ ለትምህርት ወይም ለሌላ ምክንያት የሚመጣን ሰው ወቅቱ እንደማይፈቅድና ቦታ እንደሌለ ማሳወቅና መመለስ፡፡

2.5. አዛውንት፣ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና በልዩ ልዩ ምክንያት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ዜጎችን ቀድሞ በመለየትና በማወቅ ቅድሚያ ሰጥቶ ማስተናገድ፡፡

3ኛ. የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና እገዛን በተመለከተ፡-

 3.1. ይሄ እጅግ በጣም በጣም ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ ቀድመን ጠንክረን ሰርተንበት በሰፊው ተዘጋጅተንበት ቢሆን ኖሮ በዚህ ፈታኝና አካላዊ ቅርርብ በማይፈለግበት ወቅት ቴክኖሎጂውን ተጠቅመን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሥውን ማስኬድ እንችል ነበር ወይ ብዬ እፀፀታለሁ፡፡ በጣም በጣም ወደኃላ ቀርተናል፡፡ ደግነቱ አሁንም አልረፈደም፡፡ It is never too late እንደሚለው ፈረንጅ፡፡ ቴክኖሎጂን መጠቀም አሁን ላለንበት ችግር ብቻ ሳይሆን ከጊዜው ጋር ለመጓዝ ወደፊትም ቢሆን ክፍተት ያለበትን ሕግ በማሻሻል ህብረተሰቡን ከቴክኖሎጂ ጋር በማላመድና በመተግበር ጉዳዮችን መፈጸም መቻል አለብን፡፡ በዚህ ረገድም በእጅጉ ፈጥነን መራመድ አለብን፡፡ በእርግጥ በፌ/ፍ/ቤት ካለተሳሳትኩ ከ1998/99 ጀምሮ ያዝ ለቀቅ ወጣ ገባ እያለም ቢሆንፕላዝማ፣ ተችስክሪን፣ ስካኒንግ፣ ኤሌክትሮኒክ ፋይሊንግ፣ 992፣ የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ሲተገበሩ ቆይተዋል፣ በተለይ በፌ/ጠ/ፍ/ቤት ደረጃ በጥሩ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ልምዶች ለአሁኑ አስቸጋሪ ወቅት ጥሩ ተሞክሮ ይሆናሉ ባይ ነኝ፡፡ ነገር ግን በዚሁ ወቅት ፍርድ ቤቶቻችን የአይቲ ባለሙያዎችንና ሶፍት ዌር አበልፃጊ ባለሙያዎችን የቀኝ እጅ በማድረግ የጉዳዮች ፍሰት በቴክኖሎጂዎች በታገዘና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በሁሉም ችሎቶች በአስቸኳይ ሊተገብሩት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እንዴት? ለሚለው ለመነሻ ያህል ከዚህ በታች በተገለፀው መልኩ ብንሞክረውስ?

3.2. እያንዳንዱ ፍርድ ቤት/ምድብ ችሎት የራሱ የሆነ የታወቀ(Official) ድህረ ገፅ ይኖረዋል፡፡ አዲስ የሚከፈቱ መዝገቦች በዚህ ድረገጽ አማካኝነት በe-filing ሲስተም ባለጉዳዩ አዲስ ክስ እንዲመሰርት ይደረጋል፡፡ በዚህ ክስ ላይ የክሱ ይዘትና ማሰረጃ ዝርዝር መግለጫ በቂ ይሆናል፡፡ ሆኖም ከሳሹ የስካኒን ቴክኖሎጂ ካለው የሰነድ ማስረጃውንም አርጂናሉንስካን አድርጎ ከክሱ ጋር ሊልክ ይችላል፡፡ በክሱ አድራሻ ላይ ከመኖሪያው በተጨማሪ የስልክና የኢ-ሜይል አድራሻ እንዲያሰፍር ይደረጋል፡፡ በፍርድ ቤቱ ሬጅስትራርና በዳኛ በኩል የክሱ የቴክኒክና ሕጋዊ ብቃት ታይቶ የታተመው/printed/ የክስ ወረቀት ከተሟላ ማስረጃው ጋር ይዞ የሚቀርብበትን፣ መዝገብ የሚከፍተበትንና መጥሪያ የሚወስድበትን ቀጠሮ ቀንና ሰዓት በአድራሻው ላይ ባስቀመጠው ኢ-ሜይልና የስልክ ቴክስትይላክለታል በፍ/ቤቱ ድህረ ገፅ ላይም ቀጠሮ ይመዘገብለታል ከሳሹም መዝገብ ቁጥሩን እንደ ይለፍ ቃል/ፓስወርድ ተጠቅሞ የተሰጠውን ትዕዛዝና ቀጠሮ ሊከታተልበት ይችላል፡፡ ለተከሳሹም በከሳሽ አግባብ የፍ/ቤቱን ድህረ ገፅ ተጠቅሞ መልስና ማስረጃውን የሚያስገባበት ቀጠሮ ይመቻቻል፡፡ የቃል ክርክር የሚደረግበትን ቀጠሮና ሰዓት በድህረ-ገፅ፣ በኢ-ሜይል እና በቴክስት ለተከራካሪዎች ይገለጽላቸዋል፡፡

በዚህ ሁኔታና ሌሎችንም የቴክኖሎጂ አሠራሮችን በመተግበር እርቀትን በጠበቀና በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ፍርድ ቤቶቻችን የፍትሕ ስርዓቱን መርከብ ማስጓዝ መቻል አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ የአይቲ ባለሙያዎች እገዛ በተለይም ድህረ-ገፁን ማበልፀግ የድህረ-ገፁን ደህንነትና ሚስጥራዊነት ከማስጠበቅ አኳያ እንዲሁም ሌሎች የፍ/ቤት አሰራሮችን የማዘመን ፕሮግራሞችን በመፍጠር በኩል የሚወጡት ሚና እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በሥነ- ሥርዓት ሕግ ላይ ያለው ክፍተትም ከዚሁ አንፃር ተቃኝቶ በፍጥነት መሻሻል ያለበት ክፍል ሊሻሻል ይገባል፡፡ የሌሎች አገራትን ልምድ ማጥናትና ማየት፣ ጠቃሚውንና ለአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ተስማሚ የሚሆነውን መጠቀም ይቻላል፡፡

4ኛ. የንፅህና አጠባበቅን በተመለከተ፡-

በዚህ ረገድ እንኳን ብዙ ማለት አይቻልም፡፡ አብዛኛው ሕብረተሰብ ወረርሽኙን ለመከላከል እንዲፈፅም የሚጠበቅበት የንፅህና አጠባበቅ ማለትም እንደ ማስክ ማድረግ፣ እጅን በደንብ መታጠብ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም፣ ጓንት ማድረግ፣ ቢሮዎችን የተናፈሱ ማድረግ፣ ርቀትን መጠበቅ የመሳሰሉትን በፍርድ አካባቢም በአግባቡ መፈፀም አለበት፡፡ በፍርድ ቤት ለየት የሚያደርገው ከፍተኛ የሆነ የወረቀት(መዝገቡ፣ ማስረጃው፣ ሌሎች ሰነዶችም) ከአንድ ግለሰብ ወደ ሌላ መቀባበልና መነካካት ስለሚኖር እንዲሁም የመጠጋጋት ሪስኩ ከፍተኛ ስለሚሆን የንፀህና አጠባበቁ በተለይም ማስክና ጓንት ማድረግ እንዲሁም እጅን መታጠብ ቢሮዎችን የተናፈሱ ማድረግ፣ በአንድ ቢሮ ከአንድ በላይ የሚቀመጡትን ዳኞችና ሠራተኞች ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ማመቻቸትና በበጥብቅ ሊፈፀሙት ይገባል፡፡ እንደውም ማስክ አድርጎ መምጣት የእጅ መታጠብ ለባለጉዳይ እንዲሁም ከእጅ መታጠብና ከማስክ በተጨማሪ ጓንት ማድረግ ደግሞ ለፍ/ቤት ሠራተኞች አስገዳጅ መሆን አለበት፡፡ ባለጉዳዮችም ከዳኞችና ሠራተኞች ርቀታቸውን ጠብቀው መስተናገድ አለባቸው፡፡ ለዚሁ አፈጻፀም ሠራተኛውን በአግባቡ ማሰልጠንና የጤና ባለሙያው እንደአስፈላጊነቱ በምድብ ደረጃ መቅጠርና መመደብ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የጤና ባለሙያዎች ከፍ/ቤት ኃላፊዎች ጋር ብዙ ሊመክሩበት ይችላሉ፡፡

በመጨረሻም መግለፅ የምወደው ከላይ ያቀረብኩት ፅሁፍ በጥልቅ ጥናት ላይ የተመሠረተ ላይሆን ይችላል፡፡ ሙሉ የሆነ (Complete) ዝርዝር መፍትሔ የያዘም አይደለም፡፡ ሆኖም ካለው ወቅታዊ ችግር ጋር ተያይዞ ፍርድ ቤቶች ሥራቸውን እንዴት ሊቀጥሉ ይችላሉ ለሚለው ለመነሻ የሚሆኑ ሀሳቦችን ያካተተ ነው፡፡ የፍርድ ቤት ኃላፊዎችን፣ ዳኞችና ሠራተኞችን እንዲሁም የሙያ አጋሮቼን ሊያነቃቃ የሚችል (stimulating) ፅሁፍ እንደሚሆን ግምቴ ነው እላለሁ፡፡ አመሰግናለሁ!!

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

አንዳንድ ጉዳዮች ስለ ሕገ-መንግሥት እና ፍርድ (ትርጉም)
PROBLEMS WITH THE ‘GENEROUS DIRECTIVE’: DIRECTIVE ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 26 April 2024