በማያ ጋዜጣ ሐምሌ የታተመ በሰሞኑ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የችሎት ውሎዎች በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የጋራ የወንጀል ሕጉን የማስፈጸም ተግባር ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የተለያዩ መንግስታዊ መሥሪያ ቤቶች ዳይሬክተሮችን ጨምሮ በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪነት ተይዘው የጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀባቸው የሚገኙት እስከ ሣምንቱ አጋማሽ ድረስ ቁራቸው 45 የደረሱ ተጠርጣሪዎች በእሥር ላይ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የሕግ እርምጃው ቀጣይነት ያለው መሆኑንም በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በኢቢሲ መግለጫ ተነግሯል፡፡ የተጠርጣሪዎችን በእሥር ላይ መዋል ተከትሎ በመንግስትም ሆነ በግል መገናኛ ብዙሃን ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመውታል ተብሎ ስለተጠረጠሩበት ወንጀል ዝርዝር የገንዘቡን መጠን ጨምሮ በስፋት ሲዘገብ እየተመለከትንና በጋዜጦች እያነበብን ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎቹን በሕግ መሠረት በቁጥጥር ሥር አውሎ፣ ክስ አቅርቦ ጥፋተኝነታቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸውን በህጉ መሠረት እንዲቀጡ ማድረግ መሰረታዊ የህግ ዓላማ እንዲሁም አንደኛው የሕግ አስፈጻሚዎች ሥልጣንና ተግባር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በእሥር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪ እሥረኞችን ሕገመንግሥታዊ መብቶችን የማክበሩ ጉዳይም ከተጠያቂነቱና የወንጀል ህጉን ከማስፈጸሙ እኩል ጎን ለጎን ትኩረትን የሚሻ ነው፡፡ የሰዎች መብቶችና ግዴታዎች ሁል ጊዜ ጎን ለጎን በትይዩ የሚፈጸሙ መሆናቸው መሠረታዊ የህግ መርህ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ተጠርጣሪዎችን ጨምሮ ካሁን በፊት በሙስናም ሆነ በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው በእሥር ቤት/ በማረሚያ ቤት በሚገኙ ተከሳሾች የፍርድ ቤት ችሎት ውሎዎች የታሰሩ ሰዎችን መብቶች በተመለከተ የሚነሱ ዘርፈ ብዙ የመብት ጥያቄዎች፣ የመብት ጥሰት አቤቱታዎችና ክርክሮች ተደጋግመው ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ የዛሬው የጽሁፋችን ርእስና ጭብጥ ሆኖ የተመረጠው ይህንኑ የእስረኞችን መብት ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡ በኢፌዲሪ ሕገመንግስት ከአንቀጽ 13 እስከ 44 ስለ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከተደነገጉት መካከል በአንቀጽ 21 ሥር በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት ከሰብአዊ መብቶች መካከል አንደኛው ሕገመንግስታዊ መብት መሆኑን ተደንግጓል፡፡
የሕገመንግስቱ አንቀጽ 21 ሁለት ንዑሳን ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ይነበባሉ፡-
(1) በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡
(2) ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው፡፡
ለመሆኑ የታሰሩ ሰዎች ምን መብት አላቸው? መብቶቻቸውስ በየትኞቹ የሀገራችን ህግጋት ጥበቃ ተደርጎላቸዋል? የመብት ጥበቃውስ ከማን ነው? ጠባቂውስ ማን ነው? የት፣ መቼና እንዴትስ ይጠበቃል? ጽሁፉ እንዚህንና ተያያዥ ጭብጦችን ይዳስሳል፡፡