በሀገራችን በቅርብ ጊዜየቶች ውስጥ በተደጋጋሚ እየተነሱ ከሚገኙ ጉዳዮች እና የሕግ እና የፓለቲካ ተዋንያንን እያነጋገር ያለው አንዱ ጉዳይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከአዲስ አበባ ከተማ ሊኖረው ይገባል በሚል በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 49 (5) የተቀመጠውን ልዩ ጥቅም የተመለከተው ድንጋጌ ነው፡፡በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን ድንጋጌ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያነሱት በሀገሪቷ ውስጥ ያሉትን ሰለማዊ የሆኑ ህዝቦች አብረው ሲኖሩ የነበሩትን ግንኙነት ለማበላሸት እና ልዩነትን ለማጉላት በሚል የተቀመጠ ድንጋጌ አድርገው የሚመለከቱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ይህ ድንጋጌ በሀገሪቷ ውስጥ የነበረውን ተጨባጭ የህዝቦች ችግር ለመፍታት በሚል የገባ ችግር ፈቺ እና ምክንያቲያው ድንጋጌ እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል፡፡ በዚህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ ሕገ-መንግሥቱ ለሕገ-መንግሥት አርቃቂ ጉባኤ ቀርቦ በሚታይበት ወቅትም ቢሆን የተለያዩ ሀሳቦች የተነሰቡት እና በሃላም ላይ ድንጋጌው ተቀባይነት አግኝቶ የጸደቀበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተደነገገው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ አለው የሚለው ድንጋጌ ይዘት ላይ ምን እንደሆነ እና ምን እንዳልሆነ፤ እነዚህን ልዩ ጥቅሞች በስራ ላይ ለማዋል በሚታሰብበት ውቅት ታሳቢ ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች በመግለጽ ለውይይት የሚሆን መነሻ ሀሳብ ማቅረብ ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ የብዙ ሺህ ዘመናት አኩሪ ታሪክ ያለው፤ ዘመናው የዲሞክራሲ እሴቶች የሆኑ የመንግሥት አመራር እና አስተዳደር የነበራቸው፤ የራሱ የዘመናት አቆጣጠር፤ አኩሪ ባህላዊ እሴቶች ያሉት ህዝብ ነው፡፡ይህ ህዝብ እንደማናኛውም ህዝብ የነበረው ስልጣኔ እየወደቀ እየተነሳ፤ ከሌሎች ጎረቤት ህዝቦች ጋር ሰላማዊ የሆነ ተቻችሎ የመኖር ባህሪያቶችን ይዞ የኖረ እና እየኖረ የሚገኝ ህዝብ ነው ቢሆንም የራሱን ባህል፤ ቋንቋ ታሪክ እና ሌሎች የማንነት መገለጫዎች እንደ ሃላ ቀር በመቅጠር በፊት የነበሩት የንጉሳዊያን አስተዳደሮች በህዝቡ ላይ እጅግ አሳዛኝ እና ታሪክ ሊረሳው የማይችል ድርጊት ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ሕዝቡ ሲፈጸሙበት የነበሩትን ድርጊቶች አንዳንዴ በተደራጃ እና በአብዛኛው በተበታተነ መልኩ ሲታገል እና ሲቃወም ቆይቶ ራሱ በላካቸው ወኪሎቹ መሰረት በ1987 ዓ.ም የጸደቀውን የኢፌደሪ ሕገ-መንግሥት የክልል ባለቤት ሊሆን ችሎዋል፡፡ ህዝቡ የራሱ የሆነ ክልል እንዲኖረው ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች እና የተለያዩ ክልላዊ አስተዳደሮች ጋር ሊኖረው ስለሚገባው ግንኙት ምን መምሰል እንዳበት በሕገ-መንግሥቱ ላይ ደንግጎዋል፡፡ በዚህ አግባብ በሕገ-መንግሥቱ ላይ ከተቀመጡት መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ ክልሉ ከአዲስ አበባ ከተማ ላይ ልዩ ጥቅም ሊኖረው የሚገባ እንደሆነ የሚያስቀምጠው ድንጋጌ አንዱ ነው፡፡በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠው ፌደራላዊ ስርዓት መሰረታዊ እምነቱ ብዙሀነትን ማዕከል ያደረግ አንድነትን መፍጠር እንደሆነ በመግቢያው ላይ ደንግጎዋል፡፡
ሕገ-መንግሥቱ ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ አለው የሚለው ድንጋጌ ልዩ ጥቅም የሚባሉ ሊጠበቅላቸው/ሊንጸባረቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምን እንደሆነ ያመለከተ እንጅ ልዩ ጥቅም ለሚለው ሀረግ የሰጠው ትርጉም የለም፡፡ ልዩ ጥቅም የሚለውን ሀረግ ሲታይ ልዩ የሚለው ቃል ከአንድ ነገር ጋር የተያያዘ እና ከተለመደው ወጣ ያለ የሚለውን ሁኔታ የሚገልጽ ሲሆን ጥቅም የሚለው ደግሞ ህጋዊ ተቀባይነት ያለው አንድ ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችለውን መብት የሚመለክት እንደሆነ ሊወሰድ ይችላል፡፡ስለሆነም ክልላዊ መንግሥቱ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለው ሲባል ተለይቶ የሚታወቅ ሕገ-መንግሥታዊ መብት የሚያጎናጽፍ ጥቅም አለው ተብሎ ይወሰዳል፡፡
ሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 49 ላይ ለክልሉ መንግሥት ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ እንዲጠበቅ የፈለገበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሕገ-መንግሥቱ ሲዘጋጅ በአንቀጹ ላይ ከተካሄዱ ወይይቶች፤ ከፌደራል ስርዓቱ መሰረታዊ ባህሪያት እና መነሻ ምክንያቶች አንጻር የሚከተሉት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይወሰዳል፡፡