በዓለማችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን እየተስፋፋ በመምጣቱ ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ እሲያ ከአውስትራሊያ እስከ ደቡብ አሜሪካ መንግስታት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች አነስተኞቹን ጨምሮ እንቅስቃሴያቸው እየተናጋ፤ ህልውናቸው ፈተና ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ይህ ወረርሽን ማብቂያው እና መወገጃው በግልጽ ያልታወቀ እና ሊተነበይም ያልቻለ በመሆኑ በተለይም የግል የንግድ ድርጅቶች ቀጥረው የሚያሰሯቸው ሠራተኞች ላይ ሊወስዱ ስለሚችሉት እርምጃ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም የቫይረሱ መግባት ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ መንግስት ትምህርት ቤቶችን እንዲዘጉ አድርጓል፡፡ በመቀጠልም ፍርድ ቤቶች በከፊል እንዲሁም የመንግስት ተቋማት በፈረቃ የሚሰሩበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ በሌሎች የንግድ ድርጅቶች ላይ በመንግስት ደረጃ የተሰጠ ትዕዛዝ ባይኖርም የንግድ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዙ እንዲሁም ግለሰቦች በተቻላቸው አቅም ከቤት እንዳይወጡ እየተመከረ በመሆኑ ሥራ በአግባቡ እየተሰራ እና ድርጅቶች በፊት ያገኙ የነበረውን ገቢ እያስቀጠሉ ነው ለማለት አዳጋች ነው፡፡
በመሆኑም የግል የንግድ ተቋማት በተለይ በእንደዚህ አይነት አስገዳጅ የሆነ ሥራን ማሰራት፣ ገቢንም መሰብሰብ በማይቻልበት ወቅት ምን አይነት ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ? በሕጉ ላይ የተቀመጡ አማራጮች ምንድን ናቸው? አማራጮቹን ለመጠቀምስ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችስ ምን ምን ናቸው? የሚሉትን ነጥቦች ከአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 (አዋጁ) ድንጋጌዎች አንጻር በመቃኘት አሠሪዎች በሠራተኞቻቸው ላይ አላስፈላጊ እርምጃ እንዳይወስዱ፤ ሠራተኞችም የሥራ ዋስትናቸው እስከምን ድረስ ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበው የራሳቸውን መብት እንዲያስከብሩ እና አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማሰብ ይህን ጽሑፍ ተዘጋጅቷል፡፡
ከአቅም በላይ የሆኑ ከሥራ ውል የሚመነጩ መብትና ግዴታዎች እንዲታገዱ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎች፡-