ፍርድ ቤት የበደል ስር የሚቆረጥበት ፤ ተበዳይ የሚካስበት፤ አጥፊ የሚቀጣበትና መንግስት ከህግ በታች መሆኑ የሚረጋገጥበት መድረክ ነው፡፡ ፍርድ ቤት ፍትህ ከረቂቅነት ከፍ ብላ የምትታይ ፣ የምትሰማ እና የምትዳሰስ ህልው መሆኗ የሚታወቅበት አደባባይ ነው፡፡ ፍርድ ቤት የሰለጠነ ህዝብ የኔ የሚለውን ህግ የሚያስከብርበት መሳሪያ ነው፡፡ ህይወቱ ፣ ንብረቱና የኔ የሚላቸው እሴቶቹ ሁሉ ጥበቃ ያላቸው ስለመሆኑ የሚተማመንበት ዋሱ ነው ፍርድ ቤት፡፡
የምትታሰረው ፣ የምትፈታው፣ ከአታላዮች ገንዘብህን የምታስመልስው፣ ስሜ አስጠላኝ ልቀይር ፣ ትዳር ከበደኝ ልፋታ ካልክ መሄጃህ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ሞት የሚፈርደብህ፣ ቀሪ ዘመንህን በአንድ የተከለለ የቆርቆሮ ግቢ ውስጥ በጥበቃ ስር ሆነህ እንድታሳልፍ የምትገደደውም በፍርድ ቤት ነው፡፡ ተበድያለሁ ልካስ ፣ በድሏል ይቀጣ ፣ የመናገር ነፃነቴ ይከበር ፣ የመዘዋወር መብቴ ተገደበ ብለህ የምትጮህውም ፍርድ ቤት ነው፡፡ ክብሬ ተንክቷል ልከበር ፣ ስሜ ጠፍቷል ይታደስ ፣ ገንዘቤ ተወስዷል ይመለስ ማለት የምትችለውም በዚያው ነው፡፡ አርእስቱን የተቀኘው ባለቅኔም በፍርድ ከሄደች ብዙ ዋጋ ከምታወጣው በቅሎው ይልቅ ያለፍርድ የሄደችው በሳንቲም የምትተመነው ጭብጦው የቆጨችው ያለፍርድ በዘፈቀደ የሚደረግ ድርጊት የፍትህ መዛባት የፍርድ መጓደል አድርጎ ስለሚመለከተው ነው፡፡
ታዲያ ይህን ሁሉ ማድረግ የሚችሉት ፍርድ ቤቶቻችን እነዚህን ጉዳዮች በጊዜው ፣ በእኩል እና ያለአድሎ ለመፈጸም በሚያስችላቸው ቁመና ላይ ይገኛሉ? በርግጥስ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታመን ሲቀጣም ሲፈታም ልክ ነው የሚባል ፍርድ ቤት ገንብተናል? ፍትህ ለሁሉም በግዜው ተደራሽ ሆኗል?
ፀሃፊው ለጥያቄዎቹ የሚሰጠው ምላሽ ከፁሁፉ አርእስት ጋር አንድ እና ያው ነው፡፡ ይህ ፅሁፉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ክብርት ፕሬዝዳንቷ ከመሾማቸው ቀደም ብሎ ለንባብ ለማብቃት ታስቦ በመሃል ክብርት ፕሬዝዳንቷ በመመረጣቸው የፅሁፉ ፋይዳ ከትችት ወደ ቸግር ተቋሚነት ከፍ ብሏል፡፡ የትላንቱ የፍርድ ቤት ዘመን አጥፍቶም ሆነ አልምቶ አልፏል፡፡ ለለውጥ የተሾሙት እና የሚሾሙት አዲስ ሀይሎች የትላንቱን ችግር መፍትሄ ማፈላለጊያ በማድረግ አዲስ ዘመን እንደሚያነጉ ይታመናል፡፡
ይህ ፅሁፍ መንግስት ለፍርድ ቤቶች ትኩረት ከመንፈጉ የተነሳ፣ በተበላሸ አስተዳደር ምክንያት ፣ ለሙግት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች ፍርድ ቤቶችን በማጨናነቃቸው ሳቢያ ፣ ለነሱም ትኩረት እና ምስጋና ሳይቸራቸው በሚቻላቸው መጠን በችግሮቹ መሀል ያላቸውን የሰጡ ለሀቅ እና ለፍትህ የቆሙ ዳኞችን አይመለከትም፡፡ ይልቁንስ በዚህ ችግር መሃል የቻሉትን አድርገዋል እና ምስጋናየ ይድረሰቻው፡፡ ይልቁንም ፅሁፉ ለችግሮቹ ዋና ምክንያት የሆኑትን የትኩረት ማጣት፣ የአስተዳደር ብልሽት እና ስሁት የሆኑ የፖሊሲ ጉዳዬች ላይ ያተኩራል፡፡
ዳኛ መሆን የሚገባው ማን ነው፡፡