የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ዙሪያ የቀረበ መነሻ የሆነ አጭር የሕግ ማስታወሻ
"In Claris non fit interpretation." (When the text is clear, no interpretation is needed.")
መግቢያ
በዚህ አጭር መነሻ የሆነ የሕግ ማስታወሻ ላይ በተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ዙርያ የቀረበ ሲሆን፤ በተለይም በዚህ ድንጋጌ ስር ስለተመለከተው የዋስትና መብት እና የዋስትና ክልከላ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ያልተያዙ ሰዎችና የተያዙ ሰዎች ላይ የሚተገበርበትን ሁኔታ የመጀመሪያ ምልከታ ለማድረግ ተሞክሯል። ይህንን የሕግ ማስታወሻ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋና ጉዳይ አንድ ደንበኛዬ የሆነ ሰው በሙስና ወንጀል ክስ የቀረበበት መሆኑን ከሌላ ሰው ከሰማ በኋላ ጉዳዩን አጣርቶ የሙስና ወንጀል ክሱ የቀረበበት የሙስና ወንጀል ችሎት ዘንድ ባልተያዘበት ሁኔታ በገዛ ፍቃዱ በቀረበ ጊዜ ችሎቱ የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌን መሠረት በማድረግ በቂሊንጦ ማረፍያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ሲል በቅርቡ የሰጠው ትእዛዝ ነው።
ዋስትና እና የዋስትና ክልከላ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ያልተያዙ ሰዎችና የተያዙ ሰዎች ላይ ስለሚተገበርበት ሕጋዊ ሁኔታ፣
የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ እንዲህ ይነበባል:-
"በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፤ ሆኖም የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መለቀቅ አይችልም። ከአራት ዓመት በላይ እና ከአስር ዓመት በታች የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲኖሩም እየተደመሩ ከአስር ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትና ይከለከላል።"
ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ላይ በግልጽ የተመለከተዉ "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው" የሚለው የድንጋጌው ሐረግ የሚያመለክተዉ ድንጋጌዉ የሚናገረው በሙስና ወንጀል ምክንያት በሕጋዊ መንገድ "የተያዙ ሰዎችን" ብቻ በተመለከተ መሆኑን ነው። የአዋጁ አንቀጽ 3(1) መሠረት "የተያዘ ሰው" ማለት ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 881/2007 ላይ በተመለከተ በማናቸውም የሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በሕግ አስከባሪ አካላት በኩል በሕጋዊ መንገድ የመንቀሳቀስ ነጻነቱ ተነፍጎ/ተገድቦ የተያዘ/በቁጥጥር ስር የዋለና ወደ እስር ቤት/በማረፍያ ቤት የተወሰደ ሰው ማለት ነው።
በዚህ ድንጋጌ ላይ የተቀመጠው ድርብ ነጠላ ሰረዝ(፤) የሚያመለክተው "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል" መርሕ መሆኑን ነው። ከድርስ ነጠላ ሰርዙ(፤) በኋላ የተመለከተው "ሆኖም የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መለቀቅ አይችልም።" አረፍተ ነገር ደግሞ ልዩ ሁኔታው መሆኑን፣ ያመለክታል። በዚህ መንገድ ሁለቱ ዓረፍተ ነገሮች ሎጂካሊ በዐውደ ጽሁፉ ውስጥ የተያያዙና ተዛማጅ የሆኑ ነገሮች መሆናቸውን የሚያሳይ ሆኖ በምትኩ አራት ነጥብን በመጠቀም ሊከሰት የሚችለውን አሻሚነት ለማስወገድ የገባ አስተሳሳሪ ወይም አገናኝ/አያያዥ ሥርዓተ ነጥብ ነው።
ከዚህም ጋር በተያያዘ፣ "በዋስ እንዲለቀቅ" የሚለው የድንጋጌው ሐረግም የሚያመለክተው ድንጋጌው ተፈጻሚነት ያለው በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ማመልከቻ ባቀረበ ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆን መሆኑን ነው። ምክንያቱም "እንዲለቀቅ" የሚለው ቃል ቀደም ብሎ መያዝን ወይም በቁጥጥር ስር መዋልን ታሳቢ የሚያደርግ በመሆኑ ነው። የሚለቀቀውም ከመያዝ ወይም ከእስር እንጂ ከሌላ ነገር አይደለም።
በተለይም እስር ከሌለ፣ መለቀቅ ብሎ ነገር አይኖርም። መያዝ (Arrest) ከቅድመ ትሪያል እስር/ከቅድመ ፍርድ እስር (pretrial detention) ይቀድማል። በሌላ አነጋገርም፤ መያዝ ሳይኖር ቅድመ ትሪያል እስር/ከቅድመ ፍርድ እስር ሊኖር አይችልም። ሲጠቃለል መያዝ ከሌለ፤ ቅድመ ትሪያል እስር/ከቅድመ ፍርድ እስር ብሎ ነገር አይኖርም። በመሆኑም መያዝ ከእስር (detention) በፊት ይመጣል፤ ይህም በወንጀል ሕግ መሠረት (አንቀጽ 54) እና በፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት (አንቀጽ 17) የተጠበቀ መርህ ነው። በ882/2015 አባባል አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ላይ የዋስትና ክልከላ የተደረገው በሙስና ወንጀል ተጠርጠረው ለተያዙ ወይም ለታሰሩ ሰዎች ብቻ ነው።
እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ነገር ቢኖር በተያዙ ሰዎች እና በተከሰሱ ሰዎች መካከል ያለውን ሕጋዊ ልዩነት በተመለከተ በፌደራሉ ሕገ መንግስት አንቀጽ 19ና 20 ድንጋጌዎች ላይ የተመለከተ ስለመሆኑ ነው። በሕገ መንግሥት አንቀጽ 19(6) ድንጋጌ ላይ የዋስትና መብት የተረጋገጠለት በማናቸውም ወንጀል ተጠርጥረው "ለተያዙ ሰዎች" ብቻ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ያልተያዘ ሰው ባልተያዘበት ሁኔታ ልለቀቅ ብሎ ዋስትና የሚጠይቅበት የህግ አግባብ ባለመኖሩ ነው። የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 2(3) ድንጋጌ መተግበር የሚኖርበት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 19/6/ ስር የተረጋገጠውን የተያዙ ሰዎችን ሕገ መንግስታዊ የዋስትና መብት ባገናዘበ መልኩ ነው። ከዚህ በላይ በተመለከቱት ሁኔታዎች መሠረት የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተፈፃሚ የሚሆነው በማንኛውም የሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ማመልከቻ ሲያቀርብ ነው።
እንዲሁም የድንጋጌዉ አርዕስትም የሚለው "በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ ስለተያዙ ሰዎች በዋስትና የመፈታት መብት" ("The Right to Bail of Arrested persons on Corruption Offences") የሚል ሲሆን ከዚህ የድንጋጌው አርዕስት ላይ መገንዘብ እንደሚቻለው ድንጋጌው የሚናገረው በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ የተያዙ ሰዎች በዋስ/በዋስትና ስለሚፈቱበት/ስለሚለቀቁበት እና ስለማይፈቱበት/ስለማይለቀቁበት ሁኔታ/የሕግ አግባብ ነው።
በተጨማሪም፣ በድንጋጌዉ ስር "[....] በዋስትና መለቀቅ/መልቀቅ አይችልም።" የሚለዉ ሐረግም የሚያመለክተዉ አስቀድሞ መያዝ መኖሩን ነዉ። ምክንያቱም መልቀቅ/መለቀቅ አስቀድሞ መያዝን ወይም መታሰርን ታሳቢ ያደርጋልና። በሌላ አነጋገርም፣ "በዋስትና መለቀቅ አይችልም" የሚለው ሐረግ በእርግጠኝነት "ከእስር ነፃ መዉጣት" (Release from custody) የሚል ፅንሰ-ሀሳብ ያዘለ ነው። ይህም ጽንሰ ሃሳብ በድንጋጌው ስር ዋስትና የሚከለከለው ሰው ቀድሞ በአካል ተይዞ በቁጥጥር ስር የሚገኝ መሆኑን ያመለክታል። በአጠቃላይ የድንጋጌው ይዘት በግልጽ በዋስ "መለቀቅ" ላይ ያተኮረ ሲሆን በዋስ ለመለቀቅ ደግሞ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እና በጸረ ሙስና ልዩ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ መሠረት አስቀድሞ በሚመለከተው ፖሊስ ወይም በፍርድ ቤት በኩል መያዝና መታሰርን ይጠይቃል።
በወንጀል ሕግ አተረጓጎም መርሆች መሠረት ጥብቅ የሆነ የወንጀል ህግ አተረጓጎም መርህ (Nullum Crimen Sine Lege) ማንኛውም የዋስትና ክልከላ ወይም ገደብ በግልፅና የማያሻማ ሆኖ እንዲገለፅ እና በሕጉ ቃል ላይ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ከተገለፀው ቃል በላይ ተለጥጦ በስፋት እንዲተረጎምና እንዲተገበር አይፈቅድም። ከዚህም አንጻር፣ "መለቀቅ"/መልቀቅ የሚለው ግስ ከማንኛውም እስራት ወይም ቁጥጥር ነጻ መዉጣት/መፈታት ማለት ነው። በድንጋጌዉ ላይ "በዋስትና መለቀቅ አይችልም።" የሚለዉ ሐረግ አስቀድሞ መያዝና መታሰርን ታሳቢ ያደርጋል። ያልተያዘ የተከሰሰ ሰዉ "መለቀቅ" የሚለውን ሂደት ስለማይጠቅስ፣ የዋስትና ክልከላው በእርሱ ላይ ተፈፃሚነት የለዉም። ስለዚህ ይህ ቃል በቀጥታ አስቀድሞ "ተይዟል" የሚል እውነታ እንዳለ ያሳያል።
በዚህም መሠረት በድንጋጌው ስር የተመለከተው የዋስትና ክልከላው ተፈጻሚነት ያለው የሙስና ወንጀል ክሱ ከመቅረቡ በፊት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ ወይም/እና በልዩ ሕጉ መሠረት በአካል ለተያዙ ሰዎች ወይም በፖሊስ ተይዘው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት ለቀረቡ የተያዙ ሰዎች ብቻ ነው። ይህም ማለት ድንጋጌው በአካል ባልተያዘ በሙስና ወንጀል በተከሰሰ ማናቸውም ሰዉ ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም ማለት ነው። ስለዚህም ይህ የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ስር የተመለከተዉ የዋስትና ክልከላ ባልተያዘ በሙስና ወንጀል በተከሰሰ ማናቸውም ሰዉ ላይ ተፈጻሚነት የለውም። እንዲሁም የሙስና ወንጀል ተከሰሰዉ ሰዉ በቁጥጥር ስር ሳይውል ወይም ሳይያዝ የሙስና ወንጀል ክስ እንደቀረበበት እንደሰማ በራሱ ፍቃደኛነት ከውጭ ጉዳዩ የቀረበበት ፍርድ ቤት ዘንድ የቀረበ እንደሆነ የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በእርሱ ላይ ተፈፃሚነት የለውም።
ሆኖም ግን ጠበቆችና ዐቃቤ ሕጎችን ጨምሮ እንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የሕግ አውጪው ሀሳብ እንደዚህ አይደለም ወይም በተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ እንዲወሰን አይደለም ብለው ተቃራኒ ሙግት ሊያነሱ ይችላሉ። የሕግ አውጪው ሀሳብ አግባብ ባለው አካል ባይያዙም ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ በሚችል የሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎችንም እንዲጨምር ነው ብለው ክርክር ሊያነሱ ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሕግ አውጪው ሃሳብ ቀዳሚና ዋና ምንጭ ደግሞ የሕጉ ቋንቋ/ቃላትና ሐረግ (Verba legis) ናቸው። የሕግ አረዳድ/ትርጉም የሚጀመረውም ሆነ የሚደመደመውም በሕጉ ቋንቋ/ቃላትና ሐረግ/ (Language/wording of the law) ላይ ነው። ሕጉ ግልጽና የማያሻማ እስከሆነ ድረስ ፍርድ ቤቶች ከሕጉ ቋንቋ/ቃላት በላይ መመልከት የለባቸውም። በሌላ አገላለጽ፣ ሕጉ አሻሚ ካልሆነ በስተቀር ፍርድ ቤቶች ከሕጉ ቃላት ውጪ መመልከት የለባቸውም።
በዚህም መሠረት ስንመለከተው፣ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ላይ የተገለጸው የሕግ አውጪው ቋንቋ/ቃላት ደግሞ ከላይ በጥቅስ ውስጥ የተቀመጠው ሲሆን የሕግ አውጪው ይፋዊ ሃሳብ በዋናነት የተገለጸውም ከዚህ በላይ በተመለከቱት የድንጋጌው ቃላትና ሐረጎች ውስጥ ነው። በድንጋጌው ላይ "መለቀቅ" የሚለው ቃል ታሳቢ የሚያደርገው የቀደመ መያዝን ሲሆን መልቀቅ የሚለው ቃል የሚያመለክተው የተያዘ ሰው መኖሩን ነው። በመሆኑም በድንጋጌው ላይ "በዋስትና መለቀቅ አይችልም" የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው አስቀድሞ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው ሳይኖር በዋስትና መለቀቅ/መልቀቅ ብሎ ነገር የለም። በመሆኑም ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ በሚችል የሙስና ወንጀል እስከተከሰሱ ድረስ የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3/1/ ድንጋጌ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ላልተያዙ የተከሰሱ ሰዎችም ጭምር ተፈጻሚነት አለው በማለት የሚቀርብ መከራከሪያ ሕጋዊ መሠረት ያለው አሳማኝ የሆነ ክርክር መስሎ አይታየኝም።
እንደዚውም ዋስትና መከልከል መርሕ (Principle) ሳይሆን ልዩ ሁኔታ (An exception) ወይም ልዩ የሥነ ሥርዓት ሁኔታ(ድንጋጌ) በመሆኑ ጥብቅ የሆነ የወንጀል ህግ አተረጓጎም መርህ (Nullum Crimen Sine Lege) መሰረት የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3/1/ ድንጋጌ በጣም በጠባቡ መተርጎም እንዳለበት ከግንዛቤ ማስገባት ይገባል፡፡
ለማጠቃለል በመርሕ ደረጃ የሕጉ የሕግ አውጪው ሃሳብ በዋናነት የሚገለጸው በድንጋጌው/በሕጉ ውስጥ በሚጠቀማቸው የተመረጡ ቃላትና ሐረግ ውስጥ ነው። ከዚህ አንጻር፣ በድንጋጌው ስር "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው"፣ "በዋስ እንዲለቀቅ"፣ "በዋስትና መለቀቅ አይችልም"፣ እና "በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዉ ስለተያዙ ሰዎች በዋስትና የመፈታት መብት" የሚሉት አነጋገሮች/ሐረጎች ላይ የሕግ አውጪው ሀሳብ እንደተገለጸው/እንደተመለከተው ድንጋጌው በፖሊስ ወይም በፍርድ ቤት በተሰጠ የመያዥያ ትእዛዝ መሠረት አስቀድሞ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በአካል የተያዘ ሰዉን ብቻ ያካትታል።
ስለዚህም የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ሰር የተደነገገው የዋስትና ክልከላ የሚተገበረው በሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በሕጋዊ መንገድ በአካል የተያዘ/ በቁጥጥር ስር የወደቀ፣ በአዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 4(2) መሠረት በመርማሪው በዋስትና ያልተለቀቀ የተያዘ ሰው፣ እና በአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) መሠረት በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በአካል የተያዘው ሰዉ በዋስ እንዲለቀቅ የዋስትና ማመልከቻ ለፍርድ ቤት ሲያቀርብ ብቻ ነው። በዚህም አግባብ በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ያልተያዘ ሰው ላይ ግን ይህ የዋስትና ክልከላ ሊተገበርበት አይችልም።
ይህም ሲባል የአዋጁ ድንጋጌ ይዘት ላይ "በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው" የሚለው ሐረግም ሆነ ሌሎች ቃላቶች ግልጽና የማያሻሙ በመሆናቸው የድንጋጌው ይዘት ግልጽነት ያለው ስለሆነ የሕግ ትርጉም አያሻውም። በዚህም ምክንያት ግልጽ ይዘት ያለው ድንጋጌ ደግሞ ትርጉም ሳያስፈልገው በቀጥታ ተግባራዊ ሊሆን የሚገባው ነው። ከዚህም አኳያ፣ በአጠቃላይ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ አግባብነት ባለው አካል ያልተያዘ በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ማናቸውም ሰው በዚህ የአዋጁ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ስር የዋስትና ክልከላ አይደረግበትም። ስለሆነም የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ስር የተመለከተዉ የዋስትና ክልከላ በሙስና ወንጀል በአካል የተያዙ እና ፍርድ ቤት ፊት የቀረቡ ሰዎችን ብቻ የሚመለከት ነዉ።
በሌላ በኩል፣ በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ድንጋጌ መነሻ የጽኑ እስራት ቅጣት ከአሥር ዓመት በታችና ጣሪያው ደግሞ ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ስር በተመለከተዉ መሠረት ዋስትና ለመከልከል የሚወሰደነው የድንጋጌው መነሻ የጽኑ እስራት ቅጣትን ወይንስ የጽኑ እስራት ቅጣት ጣሪያውን መሆን አለመሆኑን በተመለከተ፣ አንድ በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት ወንጀል መፈጸሙ በዐቃቤ ሕግ ማስረጃ በፍርድ ቤት ቢረጋገጥና ሰውየውም በማስተባበል መከላከል አለመቻሉ ተረጋግጦ ጥፋተኛ ቢባል ሊቀጣ የሚችለው በሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 ስር በተከሰሰበት የወንጀል ድንጋጌ ስር በተቀመጠው ቅጣት እና ቅጣትን ለመወሰን፣ የቅጣት አወሳሰንን ትክክለኛነትና አንድ ወጥነት ለማረጋገጥ ሲባል የወጣው የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሠረት የወንጀሉን ደረጃና የእስራት ቅጣት መነሻ እርከን በማውጣት በሚወሰነው ነው፡፡
ሆኖም ለዋስትና ዓላማ የሚወሰደነው የድንጋጌው መነሻ የጽኑ እስራት ቅጣትን ወይንስ የጽኑ እስራት ቅጣት ጣሪያውን መሆን አለመሆኑን በሚመለከት በድንጋጌው ስር "[....] ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ" የሚለው ሐረግ ላይ እንደተመለከተው የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተፈጻሚ የሚሆነው የተያዘው ሰው የተከሰሰበት ወንጀል ጣሪያ ከአስር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ከላይ ይዘቱ የተጠቀሰዉ የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 2(3) ድንጋጌ ለብቻው ሲታይ በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው ዋስትና ሊከለከል የሚችለው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ ብቻ ነው የሚል ግልጽ ይዘት ያለው ድንጋጌ በመሆኑ የሕግ ትርጉም ሳያስፈልገው በቀጥታ ተግባራዊ ሊሆን የሚገባው ድንጋጌ ነው።
ሕግ አዉጪዉ ምክር ቤትም የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌን በመደንገግ አቋም ሲወስድ የተያዘ ሰው ዋስትና የሚከለከልባቸውን የሙስና ወንጀል ዓይነቶችን ማለትም የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 ላይ መነሻ ቅጣታቸው ከአስር ዓመት በላይ በሆነ የጽኑ እስራት የሙስና የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ዉስን መሆናቸዉን እና አብዛኛዎቹ የሙስና የወንጀል ጉዳዮች የተያዘው ሰው በዋስትና ሆኖ የሚታዩ እንደሆኑ እያወቀ ነዉ፡፡ ሕግ አዉጪዉ ምክር ቤት እንዲህ አይነት አቋም የያዘዉ ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የተያዙ ሰዎች ከፍርድ ሂደት ተሰዉረዉ የወንጀለ ተጎጂዎች ፍትህ የማግኘት መብት እንዳይጣስ ብልም የወንጀል ሕጉ ዓላማ ከግብ ሳይደርስ ቀርቶ ጠቅላላዉ ሕብረተሰብ ተገጂ እንዳይሆን ማድረግ እንደሚቻል በማመን ነዉ፡፡ እንዲሁም ከፍርድ በፊት ያለመታሰር መብት ሕገ መንግስታዊ መርሕ በመሆኑ እና ዋስትና መከልከል ደግሞ ልዩ ሁኔታ በመሆኑ ልዩ ሁኔታ የደነገገው የአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ በጣም በጠባቡ መተርጎምና መተግበር ይኖርበታል፡፡
ከዚህ አንጻር፣ የተያዘው ሰው ዋስትና ሊከለከል የሚችለው የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል መሆን አለመሆኑን ለዋስትና ዓላማ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 ላይ የተመለከተውን መሠረት በማድረግ ሊተረጎም አይገባም፡፡ በመሆኑም የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 2(3) ድንጋጌ ስር የተመለከተው "ከአስር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ" የሚለው የሕጉ ሐረግ መታየት ያለበት ጣሪያው ሳይሆን መነሻ ቅጣቱ ነው፡፡ ይህም የሕግ አተረጓጎም በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 14፣ 17(1)-(2)፣ 19(3)(6)፣ 20(3) እና 22 ድንጋጌዎች ስር የተረጋገጡትን ሕገ መንግስታዊ የሆኑ መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶች መሠረት ያደረገ ትርጉም ነው፡፡ እንደዚውም ዋስትና መከልከል ልዩ ሁኔታ በመሆኑ ልዩ ሁኔታ ደግሞ በጣም በጠባቡ መተርጎምና መተግበር አለበት የሚለውን የሕግ አተረጋጎም መርሕ መሠረት ያደረገ ትርጓሜ ነው፡፡ ድንጋጌው በጠባቡ ሲተረጎም ለዋስትና ክርክር ውሳኔ አሰጣጥ ሲባል የሚወሰደው የቅጣቱ ጣሪያ ሳይሆን መነሻ ቅጣቱ ነው፡፡
ሆኖም ግን በድንጋጌው መሠረት ለዋስትና ጉዳይ አዋሳሰን ሲባል የሚወሰደነው የድንጋጌው መነሻ የጽኑ እስራት ቅጣትን ወይንስ የጽኑ እስራት ቅጣት ጣሪያውን መሆን አለመሆኑን አሻሚነት ያለው ነው የሚባልም ከሆነ፣ በወንጀል ሕግ አተረጓጎም መርሆች አግባብ በጥብቅ የአተረጓጎም መርሕ መሠረት መተርጎም ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሠረት በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው ዋስትና ሊከለከል የሚችለው በወ/ሕ/አ 88(2) መሠረት የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ድንጋጌ ስር የተቀመጠውን የጽኑ እስራት ቅጣት አማካኝ ቅጣት በማውጣትና አማካኙ የጽኑ እስራት ቅጣት ከአሥር ዓመት በላይ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
አልያም የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 2(3) ድንጋጌ የተያዘው ሰው የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል የሚያስቀጣው ጽኑ እስራት መነሻ ቅጣት ከአሥር ዓመት በታች ሆኖ የጽኑ እስራት ጣሪያው ከከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ተፈጻሚነት አለው ወይ? ካለው እንዴት ይፈጸማል? የሚለው ጉዳይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 231732 ስር ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም በሰጠው ከሰጠው ገዢ የሆነ የሕግ ትርጉም አንጻር፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘው ሰው ዋስትና ሊከለከል የሚችለው የተጠሪጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል "ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል" መሆን አለመሆኑን ለዋስትና ዓላማ መወሰን የሚገባው የተያዘው ሰው የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል ድንጋጌ ስር የተቀመጠውን ቅጣት፣ እና ቅጣትን ለመወሰን፣ የቅጣት አወሳሰንን ትክክለኛነትና አንድ ወጥነት ለማረጋገጥ ሲባል የወጣው በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሠረት የወንጀሉን ደረጃና የእስራት ቅጣት መነሻ እርከን በማውጣት በመወሰን መሆን ይኖርበታል ብሎ ለመከራከር ይቻላል፡፡
ይህንንም አማራጭ መከራከሪያ የሚያጠናክረው ቅጣት የእያንዳንዱን ግለሰብ ግላዊ ሁኔታዎች ጭምር ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የሚወሰን መሆኑ ነው፡፡ በተለይም ድንጋጌው የሚለው የተጠሪጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ድንጋጌ ሳይሆን "የተከሰሰበት ወይም የተጠሪጠረበት የሙስና ወንጀል" በመሆኑ ለዋስትና ክርክር ውሳኔ አሰጣጥም ቢሆን አንድ ሰው "የተከሰሰበት ወይም የተጠሪጠረበት የሙስና ወንጀል" መነሻነት ቅጣት የሚወሰንበት በተከሰሰበት የሙስና ወንጀል አንቀጽና ድንጋጌ ስር በተቀመጠው ቅጣት መሠረት በማድረግ ብቻ ሳይሆን ቅጣትን ለመወሰን፣ የቅጣት አወሳሰንን ትክክለኛነትና አንድ ወጥነት ለማረጋገጥ ሲባል የወጣው በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 እና በወንጀል ሕጉ ስር በተመለከቱት ጠቅላላና ልዩ ሁኔታዎችን እግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጭምር በመሆኑ አማካኙ መወሰዱ ድንጋጌውን ተፈጻሚ የሚያደርግ የሁለቱንም ወገኖች ፍላጎት የሚያጣጥምና የሚያስታርቅ አሳማኝ ጊዜያዊ መፍትሄ መስሎ ይታያል፡፡
ይሁን እንጂ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 63344 ቅጽ 12 ስር በሰጠው ፍርድ ላይ ፍርድ ቤቶች በሙስና ወንጀል የተያዘው ሰው የተጠረጠረበት ወይም የተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ድንጋጌ ቅጣት ጣሪያን መሠረት በማድረግ ውሳኔ ሊሰጡ እንደሚገባ አስገዳጅ የሆነ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡ ሆኖም በሰበር መዝገብ ቁጥር 182050 ስር ታሕሳስ 24 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ፍርድ ላይ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል ብሎ ለመናገር ይቻላል፡፡
መደምደሚያ፣
ፍርድ ቤቶች የሕጉን ግልጽ ቋንቋ/ቃላት በማይቃረን መልኩ መተግበር አለባቸው፡፡ ሕጉ ግልጽ ከሆነ፣ ከሕጉ ቃላት በላይ ማስፋት የለባቸውም፡፡ የተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ ተፈጻሚነት ያለው በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በተያዙ ሰዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ ሕጉ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በተያዙ ሰዎች ላይ የዋስትና ክልከላ ማድረግ የሕጉ አቋም አይደለም፡፡ ፍርድ ቤቶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ያልተያዙ ሰዎች ወይም ከአሥር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ በሚችል ያልተያዙ ሆነው በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ላይ ድንጋጌውን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችላቸው ምንም የሕግ መሠረት የለም፡፡ በሌላ በኩል፣ ለዋስትና ክርክር ውሳኔ አሰጣጥ ሲባል አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 3(1) ድንጋጌ መሠረት የሚወሰደው የቅጣቱ ጣሪያ ሳይሆን መነሻ ቅጣቱ ነው፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments