በኢትዮጵያ የብድር ሕግ "አበደረ" ማለት የብድሩን ገንዘብ ሰጠ ማለት ይሆን?

ብድር የሰው ልጅ እና ጎደሎው ከተገናኙበት ሩቅ ዘመን ጀምሮ የነበረ ሰዋዊ ድርጊት ነው፡፡ የብድር መሰረቶቹ መቀራረብ ፣ እዝነት እና መተማመን ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን እነዚህ መሰረቶቹ እየተናጉ የብድርን ህልውና ሲፈታተኑት ይስተዋላል፡፡ በርካታ ሰዎችም ብድርን መሰረት ላደረጉ ክርክሮች ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡

ከእነዚህ በርካታ ብድር ነክ ክርክሮች አንዱ በውሉ ላይ ተበዳሪ ተብለው የተሰየሙ ሰዎች የብድሩን ገንዘብ አልተቀበልኩም በማለት የሚያነሱት ክርክር ነው፡፡ ተበዳሪው በውሉ ላይ ተበድሬአለሁ ብሎ የፈረመ ቢሆንም ውሉ ፍ/ቤት ሲመጣ ግን ተበድሬአለሁ ብዬ ፈርሜአለሁ ግን የብድሩን ገንዘብ አልተቀበልኩም ማለት ይከራከራል፡፡

ይህ አይነቱ ክርክር በዋናነት መበደር እና መቀበል ምንና ምን ናቸው የሚለውን ጠንካራ የሕግ ጥያቄ የሚያስነሳ ፣ በቀላሉ መታለፍ የማይገባው እና ሰፊ ምርምራ ሊደረግበት የሚገባ ክርክር ቢሆንም አንዳንድ ችሎቶች ለክርክሩ ክብደት ሲሰጡትም ሆነ ትኩረት ሰጥተው ሲመረምሩት አይስተዋልም፡፡ ይህም በዋናነት ተበድሬአለሁ ማለት ገንዘቡን ወስጃለሁ ማለት ነው ከሚል አረዳድ የሚነጭ ሲሆን በተለይ ውሉ በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት የተደረገ በሚሆን ጊዜ ፍ/ቤቶቻችን ከጅምሩ ክርክሩን ተቀባይነት የሌለው እና ሊነሳ እንደማይገባ ክርክር በመቁጠር ሲያልፉት ይስተዋላል፡፡

ይሁን እንጅ እንዲሁ በተፈጥሮ ጸባይ ሲታይም አበደርኩ ተበደርኩ ብሎ ውል ያደረገ ሰው ሁሉ የብድሩን ገንዘብ ውሉ በተደረገበት ቀን ተቀባብሏል ለማለት አይቻልም፡፡ ይህ እንዳይሆን የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ዳኞች ከራሳቸው እውቀት እና ግምት ተጽዕኖ ነጻ በመሆን እንዲህ ዓይነት በግራ ቀኙ የሚቀርቡ ክርክሮችን ጉዳዩን ከሚገዙ ህጎች እና ማስረጃዎች ጋር በማገናዘብ እየመረመሩ ውሳኔ ሊሰጡባቸው ሲገባ ከጅምሩ ትኩረት መንፈጋቸው ተገቢነት ያለው አይመስልም፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ዓላማም በኢትዮጵያ የብድር ህግ ተበደርኩ ማለት የብድሩን ገንዘብ መስጠትን ፤ አበደርኩ ማለትም የብድሩን ገንዘብ መስጠትን ያሳያሉ ወይስ አያሳዩም በሚለው ጭብጥ ላይ አንዳንድ የግል ምልከታዎችን ማስቀመጥ ነው፡፡

ገብታችኋል - መልካም ንባብ

 

1. በብድር ውሉ ላይ አበደርኩ/ተበደርኩ መባሉ የብድሩ ገንዘብ የተሰጠ መሆኑን ያሳያልን?

ተለምዷዊውን የብድር ውል አቀራረጽ ወይም አጻጻፍ በምንመለከትበት ጊዜ አብዘሃኛዎቹ የብድር ውሎች "አበዳሪው አበደረ ፤ ተበዳሪው ተበደረ" ከሚለው አገላለጽ በተጨማሪ ተበዳሪው የብድሩን ገንዘብ በዚህ ውል ደረሰኝነት ተቀብሎ ወስዷል የሚል ዓረፍተ ነገር ሲያስቀምጡ በርከት የሚሉ የብድር ውሎች ደግሞ አበዳሪ አበደረ ተበዳሪ ተበደረ የሚል ዓረፍተ ነገር ብቻ ሲወሰኑ ይስተዋላል፡፡ በዋናነት ይህ የመበደር እና የመቀበል ክርክር ትርጉም ባለው መልኩ የሚነሳው በእነዚህ ስለመቀበል ምንም ሳይሉ "አበደረ ተበደረ" ብቻ በሚሉ የብድር ውሎች ላይ ነው፡፡

አበዳሪው እንደዚህ ዓይነቱን ውል መሰረት አድርጎ ያበደርኩት ይመለስልኝ ሲል በውሉ ላይ ተበዳሪ የተባለው ግለሰብ ደግሞ የብድር ውሉን ተፈራርመን የነበረ ቢሆንም አበዳሪው የብድሩን ገንዘብ አልሰጠኝም የሚል ክርክር ያነሳል፡፡ ለዚህ ክርክር ዕልባት ለመስጠት ማበደር እና መበደር የሚሉ የብድር ውል ቃላት ግራ ቀኙ ተዋዋዮች የብድሩን ገንዘብ በተግባር የተቀባበሉ መሆኑን ያሳያሉ ወይስ አየሣዩም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ለዚህም ምላሽ ለማግኘት የብድርግ ሕጉን ድንጋጌዎች መመርመር ያስፈልጋል፡

 በፍ/ትሃብሔር ህጋችን ውስጥ ተካትቶ የሚገኘው የሀገራችን የብድር ሕግ በዋናነት ከአንቀጽ 2471 እስከ አንቀጽ 2489 ድረስ ተዘርገቶ የሚገኝ ሲሆን በዋናነት የብድርን ትርጉም ፣ የግራ ቀኙን ግዴታዎች እና የውሉን አፈጻጸም የተመለከቱ ድንጋጌዎች አካትቶ ይገኛል፡፡ ይህንን በእጃችን ላይ ያለውን ጥያቄ ከእነዚህ የሕጉ ክፍሎች ውስጥ ከተካከቱ ድንጋጎች አንጻር በቀደም ተከተል መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡

 ሀ. የብድር ሕጉ ለብድር ከሰጠው ትርጉም አንጻር

 የሚያልቅ ነገር ብድር ውልን ትርጓሜ የሚያስቀምጠው የፍ/ሕ/ቁ.2471 እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

የሚያልቅ ነገር ብድር ማለት ከተዋዋዮቹ አንዱ ወገን አበዳሪው ሌላውን ተበዳሪ ሰው የተበደረውን ነገር በዐይነት ለመመለስ ተገዳጅ በማድረግ ገንዘብ ወይም በመገልገል የሚያልቅ ሌላ ነገር ለተበዳሪው ለመስጠትና ሀብትነቱን ለማስተላለፍ የሚገደድበት ውል ነው፡

ይህ በሕግ የተቀመጠው የብድር ውል ትርጉም መበደር እና መቀበል ወይም ማበደር እና መስጠት ለሚሉት ቃላት የሚሰጠውን ቦታ ለመረዳት ለግራ ቀኙ ተዋዋይ ወገኖች የሰጠውን ስያሜ ፣ ለብድር ውል ያስቀመጠውን አድማስ እና ለግራ ቀኙ የሰጣቸውን ግዴታዎች መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡

የብድር ውል የሚያደርጉ ተዋዋይ ወገኖች "አበዳሪ" እና "ተበዳሪ" ተብለው እንደሚጠሩ እና በውሉም ላይ በዚሁ መጠሪያ የሚሰየሙ መሆኑን ከዚህ ትርጓሜ ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህም መሰረት እነዚህ ስያሜዎች ከጅመሩ የብድር ውል ግዴታ ለሚገቡ ሰዎች የሚሰጡ መጠሪያዎች መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል፡፡

በትርጉሙ ውስጥ የተቀመጠውን የብድር ውልን አድማስ እና በአድማሱ ውስጥ የተቀመጡትን የግራ ቀኙን ግዴታዎች ስንመለከት ደግሞ በውሉ የሚቋቋሙ ሁለት በቀደም ተከተል የሚመጡ ተገዳጅነቶችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያ በተበዳሪው ላይ የተጣለው የተበደረውን ነገር የመመለስ ግዴታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአበዳሪው ላይ የተጣለው ገንዘቡን ለተበዳሪው የመስጠት ግዴታ ነው፡፡ ይህም በመጀመሪያ የብድር ውል አድማስ በግራ ቀኙ መካከል ግዴታዎችን ከማስቀመጥ የማይሰፋ የግዴታዎችን አፈጻጸም የማያካትት መሆኑን ያሳያል፡፡ በዚህም መሰረት በውሉ ላይ "አበዳሪ" ተብሎ የተሰየመው ተዋዋይ "አበድሬአለሁ" በማለት አበድሬአለሁ ያለውን ገንዘብ ለመስጠት የወደፊት ግዴታ የሚገባበት ውል እንጅ ገንዘቡን በመስጠት ግዴታውን መፈጸሙን የሚያሳይበት ውል አለመሆኑን የተበዳሪው ገንዘብ የመመለስ ግዴታ የሚመነጨው የብድር ውል ከመደረጉ ሳይሆን አበዳሪው የብድሩን ገዝብ በመስጠት የውል ግዴታውን ከመወጣቱ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡

ለ. በህጉ ላይ ከተቀመጠው የግራ ቀኙ ግዴታ አንጻር

ከላይ በትርጉሙ ውስጥ የተቀመጠውን የውሉን አድማስ በተመለከትንበት ጊዜ በግራ ቀኙ ላይ የተጣሉትን ግዴታዎች በጠቅላላው ያየን ቢሆንም ከትርጉሙ ከፍል ውጪ ባሉት የሕጉ ድንጋጌዎች የተቀመጡትን የግራ ቀኙን ዝርዝር ግዴታዎች ማየቱ ጉዳዩን በቅጡ ለመረዳት የሚጠቅም ነው ፡፡ በዋናነት የአበዳሪውን ግዴታ የሚያስቀምጠው የብድር ህጉ አንቀጽ 2474 ሲሆን የዚህ ድንጋጌ 1ኛ ንዑስ አንቀጽ በሽያጭ ውል ምዕራፍ የተነገሩት የሻጭን ግዴታዎች የሚመለከቱ ደንቦች በአበዳሪው ላይ የሚፈጸሙ ይሆናሉ በማለት የሻጭን ግዴታ አሻግሮ የአበዳሪ ግዴታ አድርጎታል፡፡

ወደ ሽጭ ህጉ በመሄድ የአበዳሪም ናቸው የተባሉትን የሻጭን ግዴታዎች ለማየት ከመመኮራችን በፊት ከዚህ የግዴታ ሽግግር ድንጋጌ ጀርባ ያለውን የህግ አውጭውን ሀሳብ መመርመር ጉዳዩን ለመረዳት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የሽያጭ ውልን ተለምዷዊ አቀራረጽ እና አተረጓጎም ስንመከት በውሉ የሚለከተው "ሸጫለታለሁ" የሚለው የውል ቃል መብት ያተላለፈ መሆኑን እንጅ ሻጩ በሸጥ መብት ያስተላለፈለትን ነገር ያስረከበ ወይም የሰጠ መሆኑን እንደማያሳይ ሁሉ ገዥም ገዛሁ ብሎ መፈረሙ እንደዚሁ መብት የተላለፈለት መሆኑን እንጅ የገዛውን ነገር የተቀበለ ወይም የተረከበ መሆኑን ሊያስረዳ አይችልም፡፡ የብድር ውልም መብቶችን ማስተላለፍን የሚመለከቱ ውሎች በሚለው የፍትሃ ብሔር ሕጉ 5ኛ መጽሀፍ 15ኛ አንቀጽ ስር ከሽያጭ ውል ጋር አብሮ የሚገኝ በመሆኑ ይህንን የሽያጭን ውል መብት የማስተላለፍ ጸባይ የሚጋራ ነው፡፡ ይህንን መሰረት አድርገን ስንመለከት ከዚህ የሻጭ ግዴታ የአበዳሪ ግዴታ ነው ከሚለው መሸጋገሪያ ድንጋጌ ጀርባ "አበደርኩ" ማለት ሰጠሁ "ተበደርኩ" ማለትም ተቀበልኩ አይደለም የሚል የሕግ አውጭ ሀሳብ እንዳለ እንረዳለን፡፡

አሻጋሪ ድንጋጌውን ተከትለን ወደ ሽያጭ ሕጉ ስንሄድ ደግሞ የሻጭን ግዴታዎች የሚያስቀምጡትን የሽያጭ ህጉን አንቀጽ 2273 ፣ 2274 ፣ 2287 እና 2288 እናገኛለን፡፡ ዋናው የሻጭን ግዴታ የሚያስቀምጠው ድንጋጌ አንቀጽ 2273 ሲሆን ሻጭ የሸጠውን ነገር የማስረከብ ግዴታ እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ማስረከብ ማለት ደግሞ በውሉ ውስጥ የተመለከተውን ነገር በውሉ ልክ መስጠት ማለት እንደሆነ የዚሁ ሕግ አንቀጽ 2274 በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ያስረከበው ወይም የሰጠው ነገር በውሉ የተገለጸው ለመሆኑም ሻጩ ዋስ የመሆን ግዴታ እንዳለበትም በአንቀጽ 2287 ስር በግልጽ ተቀምጧል፡፡

ለሻጭ የተነገረው ግዴታ ደግሞ የአበዳሪም ግዴታ መሆኑ በሕግ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ አበዳሪም ያበደረውን ነገር በውሉ ልክ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት እና የሰጠው ነገር በውሉ የተገለጸው ለመሆኑም ዋስ የመሆን ግዴታ ያለበት መሆኑን ጭምር ከፍ/ሕ/ቁ. 2474 ፣ 2273 2274 እና 2287 ድንጋጌዎች የጋራ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ማለት ማበደር እና መስጠት እጅግ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን በገልጽ የሚያሳይ ነው፡፡

 

ሐ. ከሌሎች የብድር ሕጉ ድንጋጌዎች አንጻርስ?

ከላይ ባየናቸው አንቀጾች መሰረት ያበደረውን ነገር የመስጠት ግዴታ የተጣለበት አበዳሪ ውሉን ከፈረመ በኋላ የውል ግዴታውን አልወጣም ማለት የሚችልበት መብት በፍ/ሕ/ቁ.2475 ስር እንደሚከተለው በግልጽ ተቀምጦለታል፡፡

ውሉ ከተደረገ በኋላ ተበዳሪው የመክፈል ችሎታ ማጣት የደረሰበት እንደሆነ አበዳሪው በብድር ሊሰጠው ቃል የገባለትን ነገር ለመከልከል ይችላል፡፡ ይህ መክፈል አለመቻሉ ውሉ ከመደረጉ በፊት ደርሶ እንደ ሆነና አበዳሪው ውሉ ከተደረገ በኋላ ነገሩን ቢያውቅም እንኳን አልሰጥም የማለት መብት አለው፡፡

በአንቀጽ 2471 ስር ከተተረጎመው ውጪ በብድር ህጉ ውስጥ የተቀመጠ ሌላ ልዩ የብደር ውል አይነት ባለመኖሩ ምክንያት ይህ ድንጋጌው የሚያወራው በአንቀጽ 2471 ስር ስለተተረጎመው የብድር ውል ነው፡፡ በመሆኑም "ውሉ ከተደረገ በኋላ …." የሚለው የብድር ውሉ ከተደረገ በኋላ ተብሎ መነበብ ይኖርበታል፡፡

ወደ ድንጋጌው ይዘት ስንለመስ ድንጋጌው የብድር ውል ከተደረገ በኋላ የሚፈጠርን ወይም የሚታወቅን የተበዳሪውን የመክፈል ችሎታ ማጣት የሚመለከት ሲሆን የብድር ውል በማድረግ በተበዳሪው የብድሩን ገንዘብ ስጠኝ ጥያቄ ለቀረበለት አበዳሪ የብድር ገንዘቡን ለመስጠት ግዴታ ብገባም ግዴታ ከገባሁ በኋላ የመክፈል ችሎታ ማጣት የደረሰብህ መሆኑን ስላወቅሁ እና በዚህም ምክንያት ገንዘቡን ትመልስልኛለህ ብዬ ስለማላምን የብድሩን ገንዘብ አልሰጥህም በማለት ከግዴታው ነጻ የመሆን መብት የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ የብድር ውል ማለት አበዳሪ የተገለጸውን ገንዘብ ለመስጠት ግዴታ የገባበት እንጅ ገንዘቡ የመስጠት ግዴታውን የተወጣበት ወይም ግዴታውን መወጣቱን የሚያሳይለት ሰነድ አለመሆኑን ፤ በሌላ አገላለጽ በውሉ ላይ "አበደርኩ" ማለቱ መስጠትን "ተበደርኩ" ማለቱ ደግሞ መቀበልን የማያሳይ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ 

ሌላው ከዚህ ነጥብ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት የብድር ሕጉ አንቀጽ 2477(2) ድንጋጌ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

የተበደረው ነገር የጠፋ ወይም የተበላሸ እንደሆነ ከተቀበለበት ጊዜአንስቶ

በነገሩ የሚደርሰውን የጥፋት ወይም የመበላሸት አደጋ የሚችለው እርሱ

ይሆናል ፡፡

በአጭሩ "የተበደረው ነገር የጠፋ እንደሆነ ከተቀበለበት ጊዜ አንስቶ…." የሚለው የዚህ ድንጋጌ አገላለጽም መበደርና መቀበል የተላያዩና ምናልባትም በአንድ ጊዜም የማይከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ይህም ከላይ የተቀመጠውን ትርጉም በሚገባ የሚያጠናክር ነው፡፡

 

መ. የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት

ፀሀፊው እስከሚያውቀው ድረስ ሰበር ችሎቱ እስከሁን ድረስ አበደረ ተበደረ ማለት ሰጠ ተቀበለ ማለት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በቀጥታ በመያዝ የሕግ ትርጉም አልሰጠም፡፡ ይህም የሆነው አጣሪ ችሎቶች ይህን ክርክር እንደመሰረታዊ የሕግ ጉዳይ በማየት ለሰበር ችሎት ስለማያስቀርቡት ነው የሚል ግምት አለኝ፡፡ ለሰበር አጣሪ ችሎቱ በመሳሳይ ጭብጥ የቀረበ ነገር ግን አያስቀርብም በመባሉ ምክንያት በሰበር የመተርጎም ዕድል ያጣ ጉዳይ ጸሃፊው በግል ገጥሞታል፡፡

ከላይ እንደተገለጸው ምንም እንኳን ጸሃፊው በቀጥታ በዚህ ጭብጥ ላይ የተሰጠ የሰበር ትርጉም ባያገኝም ሰበር ችሎቱ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ክርክሮች በቀረቡባቸው የሰ/መ/ቁ. 78398(14) እና የሰ.መ.ቁ.59882 (12) በሆኑ ሁለት መዛግብቶች ላይ የብድር ክርክሮችን አይቶ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ችሎቱ በብድር ውሉ ላይ ተበዳሪው የብድሩን ገንዘብ የተቀበለ መሆኑ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት እና ይህ ካልሆነ ግን ገንዘቡን አልተቀበልኩም ማለት እንደሚችል የሚያሳይ የፍርድ ሀተታ በውሳኔዎቹ ላይ አስቀምጧል፡፡ ይህም በተወሰነ ደረጃ ሰበር ችሎቱ መበደር እና መቀበል የተለያዩ መሆናቸው ላይ ያንጸባረቀውን አቋም ያመላክታል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

2. የብድር ውሉ አደራረግ (በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት መደረጉ) በዚህ ትርጓሜ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል?

 ሀ. የፍትሃ ብሔር ሕጉ እና የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ማቋቋሚያ አዋጅ

ከብር 500.00 (አምስት መቶ ብር) ከፍ ያለ መጠን ያለውን ገንዘብ ለማበደር የተደረገን ውል ማስረዳት የሚቻለው በጽሁፍ በተደረገ ውል ነው ከሚለው የፍ/ሕ/ቁ.2472 ድንጋጌ ውጪ የብድር ውል በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት መደረግ አለበትም ሆነ መመዝገብ አለበት የሚል ሕግ የለም፡፡ በዚህም መሰረት በመንደር የሚደረጉ የብድር ውሎችም የሕጉን መስፈርቶች አሟልተው እስከተደረጉ ድረስ ህጋዊ እና የብድር ውል መኖርን የሚያስረዱ ውሎች ናቸው፡፡

ይሁን እንጅ ፍ/ቤቶች በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት ለተደረጉ ውሎች ይሰጣሉ ከሚባለው ከፍተኛ ተዓማኒነት ለመጠቀም ሲባል ብዙ ሰዎች የብድር ውሎችን በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ፍ/ቤቶቹም ለእነዚህ በጽ/ቤቱ ለሚደረጉ ውሎች በሕግ ካገኙት ደረጃ በላይ የሆነ መለኮታዊ እምነት ሲሰጧቸው ይታያሉ፡፡ በተለይም የገንዘብ መቀበል አለመቀበልን አስመልከቶ በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት የሚደረጉ ብድር ውሎች ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎችን ለመመርመር ፍላጎት ሲያሳዩም አይስተዋሉም፡፡ ይህንን እምነት በማየትም ፍ/ቤቶች ሕግ ከመተርጎም ስልጣናቸው የተወሰነውን ቀንሰው ለጽ/ቤቱ ሰጥተዋል የሚሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ፍ/ቤቶች ለእነዚህ ሰነዶች የሚሰጡት እምነት ተገቢነት በራሱ ልዩ ትኩረት እና ዳሰሳ የሚሻ በመሆኑ እና ከዚህ ጽሁፍ አድማስ የሚሰፋ በመሆኑ እያየነው ካለው ነጥብ ጋር የሚገናኘውን ብቻ ነጥለን መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡

 በጽ/ቤቱ የሚደረጉ ውሎችን የእምነት ምንጭ ከማየታችን በፊት በጽ/ቤቱ የሚከናወነው የማረጋገጥ እና የመመዝገብ ስራ ምንድነው የሚለውን ማየቱ ጉዳዩን ከመሰረቱ ለመረዳት ይጠቅማል፡፡ በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 922/08 አንቀጽ 2(2) እና 2(3) ስር በግልጽ እንደተመለከተው ሰነድ ማረጋገጥ ማለት ሰነዱ በሚመለከታቸው ሰዎች መፈረሙን ማየት እና ይኽው መፈጸሙን በማረጋገጥ በሰነዱ ላይ መፈረም እና ማህተም ማድረግ ሲሆን ሰነድ መመዝገብ ማለት ደግሞ በዚህ አግባብ የተረጋገጠውን ሰነድ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጄ መዝገብ መለያ ቁጥር እየሰጡ መመዝገብ እና ማስቀመጥ ነው።

በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት ለሚደረጉ (ተረጋግጠው ለሚመዘገቡ) ውሎች የመታመን ጉልበት የሚሰጠው የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 23 ሲሆን ድንጋጌው እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

በዚህ አዋጅ መሠረት የተረጋገጠ ሰነድ በውስጡ ስለሚገኘው ይዘት ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ተረጋግጦ የተመዘገበን ሰነድ በክርክር ሂደት ውስጥ መቃወም የሚቻለው ፍርድ ቤት በበቂ ምክንያት ሲፈቅድ ብቻ ነው፡፡

በዚህም መሰረት በጽ/ቤቱ የእነዚህ ውሎች ተዓማኒነት የሚመነጨው ተረጋግጠው ከመመዝገባቸው ሲሆን እምነቱም በሰነዶቹ ውስጥ በሚገኘው ይዘት ብቻ የሚወሰን ነው፡፡ የፍ/ሕ/ቁ.2005 እና ተከታዮቹን ድንጋጌዎች ስንመለከት ደግሞ የብድር ውሉ ተረጋግጦ ባይመዘገብም የሕጉን መስፈርቶች አሟልቶ በጽሁፍ እስከተደረገ ድረስ በላዩ ላይ ስለሚገኘው የስምምነት ቃል ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ነው ፡፡ በመሆኑም በዋናነት በሕግ ተዓማኒነት የተሰጠው ለብድር ውሉ መረጋገጥ ሳይሆን በብድር ውሉ ላይ በግልጽ ለተቀመጠው የውሉ ይዘት መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁ.2472 እና 2005 እንዲሁም ከአዋጁ አንቀጽ 23 መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህም መሰረት በተረጋገጠው ሰነድ ይዘት ላይ በግልጽ ያልተቀመጠ ወይም ያልተመላከተ ፍሬ ነገር ተረጋግጧልም ሆነ የሕግ እምነት ተጥሎበታል ሊባል አይቻልም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሰነዱን መሰረት አድርጎ በቀረበ ክስ ላይ ይህንን ከሰነዱ ይዘት ውጪ የሆነ ነገር መሰረት በማድረግ ክርክር ማንሳት ይቻላል፡፡

ወደያዝነው ጉዳይ ስንምለስ ፤ ከላይ ባሉ ክፍሎች በግልጽ እንደተመለከትነው በብድር ሕጋችን መሰረት አበደረ ማለት የብድሩን ገንዘብ ሰጠ ማለት አይደለም፡፡ ተበደረ ማለትም የብድሩን ገንዘብ ወሰደ ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት በተደረገ የብድር ውል ውስጥ የተገለጸው አበደረ ተበደረ የሚል ቃል ብቻ ከሆነ እና የመስጠት እና የመቀበል ነገር በግልጽ ካልተቀመጠ የብድሩን ገንዘብ መስጠትን እና አለመስጠትን የተመለከተው ነገር በሰነዱ ይዘት ላይ የተካተተ የውሉ ይዘት ነው ማለት አይቻልም፡፡ በዚህም መሰረት በጽ/ቤቱ ለተደረገው ሰነድ የሚሰጠው እምነት በሰነዱ ይዘት ላይ ላልተካተተው ለእንዲህ ዓይነቱ ፍሬ ነገር አይሰጥም፡፡ በመሆኑም ፍ/ቤቶች በተከራካሪዎች የሚቀርበውን እንዲህ ዓይነቱን ክርክር ከውሉ ይዘት ጋር ማገናዘብ እና ከሕጉም ጋር አገናኝተው መወሰን ይጠበቅባቸዋል እንጅ ውሉ ሰነዶች ማረጋገጫ የተደረገ ነው በማለት ብቻ በጉዳዩ ላይ የሚቀርቡ ክርክሮችን ሳይመረምሩ ውድቅ ማድረጋቸው ተገቢነት የለውም፡፡

ለ. ከጽ/ቤቱን አሰራር አንጻር

የጽ/ቤቱን አሰራር በምንመለከትበት ጊዜም ጽ/ቤቱ ሰራተኞቹ ስራቸውን የሚሰሩበት ነባር የሰነድ ማረጋገጥ እና መመዝገብ አገልግሎት አሰጣጥ የአሰራር ማንዋል ያለው ሲሆን የብርድ ውልን ለማረጋገጥ መከናወን ያለባቸው ተግባራት በሕግ አግባብ የተዘጋጄ የብድር ውል መቅረቡን ማረጋገጥ ፣ የተዋዋዮቹን መታወቂያ በመቀበል ማንነታቸውን እና ስልጣናቸውን ማረጋገጥ እና የትዳር ሁኔታቸውን ማስረጃ በማየት ማረጋገጥ መሆናቸው በዚህ ማንዋል ክፍል 4.2 ስር በግልጽ ተቀምጠዋል፡፡ ይህ ማንዋል ሰነድ አረጋጋጩ ከእነዚህ ተግባራት ውጪ ግራ ቀኙ የብድሩን ገንዘብ መቀባበላቸውን እንዲያረጋግጥ የጣለበት ኃላፊነት የለም፡፡ በተግበርም የጽ/ቤቱ አረጋጋጮች የሚያረጋግጡት እነዚህን በማንዋሉ የተቀመጡትን ተግባራት ሲሆን ተመዝግቦ በጽ/ቤቱ ቀሪ በሚሆነው የውሉ ቅጅ ላይም አረጋገጥን ብለው በእጅ ጽሁፍ የሚመዘግቡት እነዚህን ተግባራት ብቻ መሆኑን ጸሃፊው ተመልክቷል፡፡

በቅርብም ሀገሪቱ የገንዘብ ኖት መቀየሯን ተከትሎ ሌሎች ውሎችን ጨምሮ የብድር ውል ሊያደርጉ የሚቀርቡ ተዋዋዮች የብድሩን ገንዘብ የተቀባበሉበትን የባንክ ደረሰኝ ይዘው ሊቅርቡ ይገባል የሚል መመሪያ ወጥቷል፡፡ ይህ መመሪያ የወጣው በዋናነት ሰዎች የማይሰጡትን ገንዘብ አበደርን በማለት ብድርን እንደ አንድ ህጋዊ የገንዘብ ማሸሻ መንገድ አንዳይጠቀሙበት ለመከላከል ነው፡፡ ይህ ለመመሪያው መውጣት ምክንያት የሆነ ስጋት ከመመሪያው በፊት በነበረው የጽ/ቤቱ አሰራር ተዋዋዮች በጽ/ቤቱ ቀርበው ውል ከተመፈራረም ባለፈ በጽ/ቤቱ ገንዘብ የማይቀባበሉ መሆኑን እና የጽ/ቤቱም የብድር ውል የማረጋገጥ እና የመመዝገብ ስራ ገንዘብ መቀባበልን ማረጋገጥን እንደማይጨምር በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 5 ዓመት ሳይሞላ እንዳይሸጥ የሕግ ክልከላ የተደረገበትን የኮንዶሚኒየም ቤት የሚሻሻጡ ሰዎች የሽያጭ ውሉን በመንደር ካደረጉ በኋላ ለዋስትና ይሆን ዘንድ ሻጭ የሆነው ወገን ከፍ ያለ ገንዘብ እንደተበደረ ተደርጎ የተዘጋጄ የብድር ውል በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት እንደሚያደርጉ እና እንደሚያረጋግጡ የአደባባይ እውነት ነው፡፡ ይህም የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት የብድር ገንዘብ ቅብብልን የማረጋገጥ የቀደመ አሰራር እንደሌለው የሚያረጋግጥ ተጨማሪ አሰራር ነው፡፡

በዚህም መሰረት ውሉ በግልጽ የብድር ገንዘቡን አበዳሪው መስጠቱን እና ተበዳሪው መቀበሉን ካላሰፈረ በስተቀር የብድር ውሉ በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽ/ቤት መደረጉ የብድር ውሉን መደረግ መቃወምን ከሚከለክል በስተቀር የብድር ውል የቀረበበት ሰው የብድር ውል ገንዘቡን አልተቀበልኩም በማለት እንዳይቃወም አይከለክለውም፡፡ የፍ/ህ/ቁ/2005 ም ሆነ የጽ/ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ይህንን አይከለክልም፡፡ በመሆኑም የውሉ በሰነዶች ማረጋገጫ እና መዝገባ ጽ/ቤት መደረጉም በዚህ የሕግ አተረጓጎም ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡

3. ማጠቃለያ

በሀገራችን የብድር ህግ መሰረት የብድር ውል አበዳሪው ገንዘብ በብድር ለመስጠት ግዴታ የሚገባበት ተበዳሪውም ይህንን በብድር የሚሰጠውን ገንዘብ ለመመለስ ተገዳጅ የሚሆንበት ውል ነው፡፡ ግራ ቀኙ ይህንን የውል ግዴታቸውን ይወጡ ዘንድም በውሉ ተገዳጅ ይሆናሉ፡፡

አበዳሪው ለመስጠት ግዴታ የገባበትን ገንዘብ ውሉ በሚደረግበት ጊዜ ወይም ደግሞ ከዚያ በኋላ በሆነ ጊዜ በመስጠት ግዴታውን ሊፈጽም ይገባል። ይህንን ግዴታ ካልተወጣም ተበዳሪው በአበዳሪው ላይ የውል ይፈጸምልኝ ክስ አቅርቦ የመጠየቅ እና እንዲበደር ያስገደደው ችግር አልፎ ይህንን ማድረግ ሳይፈልግ ቀርቶ ውሉ ሳይፈጸም በቀረበት አበዳሪው በተለያየ ምክንያት ያልሰጠውን ገንዘብ መልስልኝ የሚል ክስ ቢያቀርብበት የብድሩን ገንዘብ አልሰጠኽኝም ብሎ የመከራከር ተፈጥሯዊ መብት አለው፡፡

በዚህ አግባብ የገንዘቡን መሰጠት አለመሰጠት አስመልክቶ ክርክር በተነሳ ጊዜም በውሉ ላይ የገንዘቡ መሰጠት በግልፅ ካልተመላከተ በስተቀር አበዳሪው የተባለውን ገንዘብ ለተበዳሪው የሰጠ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ ማቅረብ ከሚኖርበት በስተቀር በውሉ ላይ አበደርኩ ማለቱ ወይም ተበዳሪው ተበደርኩ ማለቱ አበዳሪው የመስጠት ግዴታውን መወጣቱን ሊያሳይ የሚችልበት የህግ መሰረት የለም፡፡ ሰነዱ የተረጋገጠ እና የተመዘገበ ቢሆንም እንኳን ተከሳሹ የብድሩን ገንዘብ አልተቀበልኩም የሚል የተቃውሞ ክርክር እንዳያቀርብ ያደርገውም፡፡

በመሆኑም ችሎቶች ተከሳሹ ገንዘቡን አልተቀበልኩም የሚል ክርክር ሲያነሳ ውሉ በጽሁፍ መሆኑንም ሆነ ተረጋግጦ መመዝገቡን መሰረት በማድረግ ውድቅ ከማድረጋቸው በፊት መቃወሚያው የቀረበው በውሉ ይዘት በተካተተ የስምምነት ቃል ላይ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ነጥብ በአንክሮ መመርምር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ውሉ ሲታይ አበደርሬአለሁ ተበድሬአለሁ ብቻ የሚል ከሆነ እና አበዳሪው አበድሬአለሁ ያለውን የብድሩን ገንዘብ ለተበዳሪው የሰጠ መሆኑ በውሉ ላይ በግልጽ ያልሰፈረ ከሆነ ተከሳሹ ገንዘቡን አልተቀበልኩም በማለት ያቀረበውን ክርክር በመቀበል ከሳሹ በቅድሚያ ገንዘቡን የሰጠ መሆኑን እንዲያስረዳ መጠየቅ ይገባል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ግለሰቦች ያልተቀበሉትን ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚያስገድዱ እጅግ ኢፍትሐዊ የሆኑ ውሳኔዎች የሚሰጡበት ዕድል ይፈጠራል፡፡

እርስዎስ ምን ይመስልዎታል?

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የወራሽነት ማረጋገጫ፣ መቃወሚያ እና ልጅነት፡- ክፍተተ ወሕግ ወአሰራር እና መፍ...
The legality of Levying Income Tax on Illegal Amou...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 29 March 2024