Font size: +
9 minutes reading time (1724 words)

የወራሽነት ማረጋገጫ፣ መቃወሚያ እና ልጅነት፡- ክፍተተ ወሕግ ወአሰራር እና መፍትሔዎቻቸው

የርዕሰ መዲናዋን አስተዳደር ለመመስረት በቻርተር ደረጃ የወጣው አዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 41(1) (ሸ) እና ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 408/96 አንቀጽ 2 የወራሽነት ማረጋገጫን ጨምሮ ሌሎች ምስክር ወረቀቶች የመስጠት የስረ ነገር ስልጣንን ለአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች ሰጥቷል። በዚህም መሰረት ከሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አምስት ዓመተ ምህረት ጀምሮ እስካሁን ድረስ እነዚህ ፍ/ቤቶች እገሌ የእገሌ ወራሽ ነው፣ አንቺ የእንትና ሚስት ነበርሽ፣ አንተ ደግሞ የእገሊት አበዋራ ነበርክ …….. ወዘተ እያሉ በሕግ ዓይን ህያው ይሆን ዘንድ በሞት የፈረሰን የዓይነ ስጋ ዝምድና በወረቀት ማረጋገጫ ሲቀጥሉ ኖረዋል።

በመንገድ ላይ

በዚህ ሃያ ዓመት በደፈነ ረጅም የአገልግሎት ዘመን በእነዚህ አገልግሎቶች ላይ ተጣብቀው የቀጠሉ ብዙ ስንክሳሮች፣ ህጸጾች እና ጉድለቶች አገልግሎቱን ወጥነት የሌለው እና የዕድሜውን ያህል ያልጎለመሰ በዳዴ ተጓዥ ሚጢጢ ህጻን አድርገውታል። ለአብነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወራሽነት ማረጋገጫ ለመውሰድ የልደት እና የሞት ምስክር ወረቀቶችን እንዲቀርብ መጠየቅ ከመጀመሩ በፊት አመልካቹ የእገሌ ወራሽ ነኝ ብሎ በሚያቀርበው ቃለ መሃላ ብቻ የወራሽነት ማረጋገጫ ይሰጥ የነበረ መሆኑ እንደ ትልቅ ችግር ሊጠቀስ ይችላል። በዚህ አሰራርም በርካታ ወራሽ መባል ያልነበረባቸው ግን የውርስ ሀብት ያማለላቸው ሰዎች በፍ/ቤት ጠረንጴዛዎች ላይ የተቀመጡ ቅዱሳን መጸሐፍትን እየመቱ ባቀረቧቸው ቃለ መሃላዎች ብቻ ወራሽ በመባላቸው ምክንያት ፍ/ቤቶች በበርካታ የተቃውሞ አቤቱታዎች ሲጥለቀለቁ ኖረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤት ምድብ ችሎቶች ብሎም በችሎቶች መካከል የሚስተዋለው የአሰራር ልዩነትም ሌላው አሁንም ድረስ የዘለቀ ችግር ነው። ለአብነት ያህል አስቀድሞ በተሰጠ የወራሸነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ላይ የተቃውሞ አቤቱታ በሚቀርበበት ጊዜ በችሎቶች መካከል የሚስተዋለውን የአሰራር ልዩነት መጥቀስ ይቻላል። የተወሰኑ ችሎቶች ጉዳዩ ልጅነትን የሚመለከት በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ስልጣን የለኝም በማለት የመቃወም አመልካቹ ወራሽነቱ በተረጋገጠለት ሰው ላይ ስልጣን ባለው ፍ/ቤት የመካድ ክስ አቅርቦ ልጅ አለመሆኑን አረጋግጦ ይቅረብ በማለት መዝገቡን ይዘጋሉ ። የተወሰኑት ችሎቶች የወራሽነት ማረጋገጫ የተሰጠው ግለሰብ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ልጅነቱን አረጋግጦ ይቅረብ በማለት መዝገቡን ሲዘጉ ቀሪዎቹ ውስን ችሎቶች ደግሞ ጉዳዩ ላይ ስልጣን አለኝ በማለት የወራሽት ማረጋገጫው ሊሻር ይገባዋል ወይስ አይገባውም የሚለው ላይ አከራክረው ሲወስኑ ይስተዋላል።

እነዚህ የአሰራር ልዩነቶች በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ወጥ የሆነ የሕግ አተረጓጎም እንዳይኖር እና ተመሳሳይ ክርክር ያላቸው ዜጎች በተመሳሳይ ሁኔታ እና ሕግ እንዳይዳኙ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በተለይም በወራሽነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ላይ ተቃውሞ ያቀረቡ ወገኖች የመካድ ክስ እንዲያቀርቡ የሚሰጡ ትዕዛዞች በመቃወም አመልካቹ ላይ ብሎም በፍትህ ሚዛን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እና መዛነፍ የሚያስከትሉ በመሆናቸው በቀጣይ ክፍሎች በእነዚህ ትእዛዞች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚያስከትሏቸውን ችግሮች እና መፍትሔዎቻቸውን በዝርዝር ለማየት ተሞክሯል።

የከፋው ገጽታ

የወራሽነት ማረጋገጫ ም/ወረቀት የተሰጠው ያለአግባብ ነው በማለት በመዝገቡ ላይ በመቃወም አመልካችነት የቀረበው ወገን ስልጣን ባለው ፍ/ቤት የመካድ ክስ አቅርቦ ወራሽ የተባለውን ሰው ልጅ አለመሆን አረጋግጦ እንዲቀርብ የሚወስኑ ችሎቶች በርከት ያሉት ናቸው። ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው ይህኛው የችሎቶቹ አቋም በርካታ ችግሮችን ሲያከትል የነበረ እና እያስከተለ የሚገኝ ነው።

  • የመጀመሪያው ችግር

የመጀመሪያው ችግር ችሎቶቹ የመካድ ክስ እንዲቀርብ የሚያዙት የተረጋገጠ የሚካድ ልጅነት በሌለበት መሆኑ ነው። አብዘሃኛውን ጊዜ በሚባል ደረጃ የወራሽነት መቃወሚያዎች ሲቀርቡ የሚስተዋለው ከትዳር ውጪ ባለ የሕግ እውቅና ባላገኘ ግንኙነት ውስጥ ተወለድኩ በማለት የወራሽነት ማረጋገጫ በሚያወጡ ግለሰቦች ላይ ነው። የወራሽት ተቃውሞው የሚርበውም እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ በሀገራችን የቤተሰብ ሕግ ልጅነት ከሚረጋገጥባቸው የሕግ ግምት፣ የአባት መቀበል እና የፍርድ ቤት ውሳኔ በአንዱም ልጅነታቸው ያልተገመተ ወይም ልጅነታቸውን ያላረጋገጡ ስለሚሆኑ ነው። ከእነዚህ በሕግ ከተቀመጡ መንደጎች በአንዱ እንኳን ልጅነት የሕግ ግምት ካላገኘ ወይም ካልተረጋገጠ ደግሞ የሚካድ መወለድ ስለማይኖር የመካድ ክስ ሊቀርብ አይችልም።

እነዚህ ችሎቶች የመካድ ክስ እንዲቀርብ ትዕዛዝ የሚሰጡት ወራሽ የተባለው እና መቃወሚያ የቀረበበት ግለሰብ ልጅ መሆኔን ያሳዩልኛል በማለት ያቀረባቸውን ማስረጃዎች በማየት ልጅ ነው የሚል ግምት ወስደው ነው እንዳይባል እንኳን ይህ ድምዳሜ ልጅነትን የማረጋገጥ ውጤት ያለው በመሆኑና እነዚህ የከተማ ፍ/ቤት ችሎቶች ደግሞ ልጅነትን የማረጋገጥ ስልጣን የሌላቸው በመሆኑ ይህንን ማድረግ አይችሉም። በመሆኑም ይህኛው የተገመተ ወይም የተረጋገጠ ልጅነት በሌበለበት የመካድ ክስ መቅረብ አለበት የሚል አተረጓጎም ከፈረሱ ጋሪው እንዲቀድም የሚያደርግ ተገቢነት የሌለው አተረጓጎም ነው።

  • ሁለተኛው እና ከመጀመሪያው የከፋው ችግር

ሁለተኛው ችግር ደግሞ ይህ በሌለ ልጅነት ላይ የመካድ ክስ እንዲያቀርብ የሚገደደው የመቃወም አመልካች በቤተሰብ ሕጉ ላይ ለመካድ ክስ ከተቀመጡ እጅግ ጥብቅ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ወይም መስፈርቶች ጋር መላተሙ ነው። የመካድ ክስ የፍ/ቤት ፈቃድ፣ ጊዜ እና የማስረጃ ጥንካሬ ደረጃ በቅድመ ሁኔታነት የተቀመጡለት ልዩ የክስ ዓይነት ነው። የመካድ ክስ ፍ/ቤት ካልፈቀደ በስተቀር ሊቀርብ እንደማይችል የቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 171 ሲደነግግ ክሱ የልጁ መወለድ ከታወቀበት ወይም ሊታወቅ ከሚገባበት ጊዜ ጀምሮ 6 ወራት ካለፉ በኋላ ሊቀርብ እንደማይችል ደግሞ በዚሁ ህግ አንቀጽ 171 ስር መቀመጡን ማስተዋል ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ለመካድ ክስ መቅረብ ያለበት ማስረጃ በማያጠራጥር ሁኔታ (beyond reasonable doubt) የማስረዳት አቅም ያለው መሆኑን በዚሁ ህግ አንቀጽ 170 ስር በግልጽ ተቀምጧል።

ምናልባትም ከተወለደ ብዙ ዘመን ባለፈው እና የወራሽነት ማረጋገጫ ይዞ በመምጣቱ ብቻ ባወቀው ሰው ላይ የመካድ ክስ እንዲያቀርብ የተገደደው የመቃወም አመልካች እነዚህን ጥብቅ የመካድ ክስ ቅድመ መስፈርቶች ማሟላት ይከብደዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤት ችሎቶች የመካድ ክስ እንዲቀርብ በማለት የሰጧቸውን ትዕዛዞች የሚካደው ሰው ልጅነት የተረጋገጠባቸው ትዕዛዞች አድርገው የሚወስዱት የፌ/ፍ/ቤቶች ልጅ አለመሆንን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ አልቀረበም በማለት የሚቀርቡላቸውን አብዘሃኛዎቹን የመካድ ክስ ማስፈቀጃዎች አቤቱታዎች ውድቅ ይስተዋላላል። በውስን ሁኔታዎች የፍ/ቤት ፈቃድ ቢገኝ እንኳን ቀጥሎ በመቃወሚያነት የሚቀርበውን የጊዜ ገደብ ማለፍ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል።

ይህም በአንድ በኩል በመቃወም አመልካቹ መብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተቃውሞ የቀረበበትን የወራሽት ማረጋገጫ ም/ወረቀት ያገኙ ሰዎች በሕግ የልጅነት ግምት ላገኙ ወይም ልጅነታቸውን ላረጋገጡ ተወላጆች የተቀመጠውን ጥብቅ የመካድ ክስ ቅድመ ሁኔታ ከለላ እንዲያገኙ በማድረግ ልጅ መሆን አለመሆናቸው ሕግ እና ማስረጃን መሰረት አድርጎ ሳይመረመር እና ውሳኔ ሳይሰጥበት በአቋራጭ ልጅ መባል የሚችሉበት ጥቁር ቀዳዳ የሚከፍት እና በድምሩ በፍትሕ አሰራር ላይ መሰናክል የሚፈጥር ነው።

ሰበር ችሎት ያስቀመጠው መፍትሔ

ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ ነጥለን እያየነው ባለነው የወራሽነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ላይ እና በሌሎች ማረጋገጫ ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ መቃወሚያዎችን የሚመለከቱ በርካታ ጉዳዮች ደረጃቸውን ጠብቀው ለፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርቡ ይስተዋላል። ሰበር ችሎቱም ለበርካታ ዓመታት በቅጡ ያልተናበቡ ልዩ ልዩ አቋሞችን ሲይዝ ከቆዬ በኋላ በመጨረሻ በሰ.መ.ቁ.17106፣ 199769፣ 195227፣ 196567 እና 216496 በሰጣቸው የሕግ ትርጉሞች "የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች የወራሽነት ማረጋገጫን ጨምሮ ሌሎች በሕግ የተቀመጡ ምስክር ወረቀቶችን በተመለከተ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ትክክለኛነት እና ህጋዊነት በማረጋጥ በማስረጃነት ውሳኔ (declaratory judgment) ከመስጠት ውጪ ማስረጃው የተሰጠበት ውሳኔ ላይ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.358 መሰረት የሚቀርብን የተቃውሞ አቤቱታ ተቀብሎ የማየት ስልጣን የላቸውም" የሚል ግልጽ አቋም ይዟል። በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤት የተሰጡ የወራሽት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቶች ላይ የሚቀርቡ የመቃወሚያ አቤቱታዎች የግዛት ክልል ስልጣን ባላቸው የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ችሎቶች በሚከፈቱ አዳዳስ መዛግብት እየቀረቡ በመታየት ላይ ይገኛሉ። ይህም በልጅነት ይረጋገጥልኝ እና በመካድ ክስ ላይ የሚጨመር 3ኛ ወደ ልጅነት ክርክር መግቢያ በር የፈጠረ ሆኗል።

ይህ የሰበር ችሎቱ አቋም የስልጣን ገደብ ሳይገታው ወራሽ ተብሎ ማስረጃ የተሰጠው ሰው ተገቢ ወራሽ መሆን አለመሆን ሕግን እና ማስረጃን መሰረት በማድረግ ተመርምሮ ትክክለኛ ፍትሕ እንዲሰጥበት የሚያደረግ ተገቢ መፍትሔ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይሁን እንጅ መፍትሔው የወራሽነት ማረጋገጫ ውሳኔውን በአዲስ አበባ ፍ/ቤት እየተሰጠ በውሳኔው ላይ የሚቀርበው መቃወሚያ ደግሞ በፌዴራል ፍ/ቤት እንዲታይ የሚያደርግ መሆኑ የአንድ ጉዳይ ሂደቶች የሆኑ ንዑሳን ጉዳዮችን የተለያየ የስልጣን መዋቅር ላላቸው የአዲስ አበባ ከተማ እና የፌደራል ፍ/ቤት የሚሰጥ በመሆኑ የስልጣን መደበላለቅ የሚፈጥር፣ እና በባለጉዳዮች ላይ እንግልት የሚያበዛ እና የጉዳዩን አወሳሰን የሚያወሳስብ ነው። በመሆኑም ሌላ ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ አስፈላጊ ነው።

የፀሐፊው የመፍትሔ ሀሳብ

 

  • የችግሩ ዋነኛ ምንጭ

እያየነው ያለነው የወራሽነት ማረጋገጫ ጉዳይ በዋናነት በውርስ ሕጉ በልዩነት ደግሞ በሕጉ የውርስ ማጣራት ክፍል የሚካተት ነው። ወራሽ ለመሆን ተወላጅነት ወይም ልጅነት መሰረት ሆኖ ስለሚነሳ ጉዳዩ የልጅነት ሕግ የተደነገገበትን የቤተሰብ ሕጉንም ይመለከታል። በመሆኑም የወራሽነት ማረጋገጫ ውሳኔ መስጠትም ሆነ በውሳኔው ላይ የሚቀርብን መቃወሚያ አከራክሮ የመወሰን ጉዳይ በውርስ ሕግ ከሚመራው የውርስ ማጣራት እና በቤተሰብ ህጉ ከሚመራው የልጅነት ጉዳይ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። በዚህም መሰረት የወራሽነት ማረጋገጫ ጉዳይ ላይ ለሚነሱ ክርክሮች የተሟላ ዕልባት ለመስጠት የውርስ እና የቤተሰብ ጉዳይን የማየት ስልጣን ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው የቤተሰብ እና ውርስ ጉዳዮች በፌ/ፍ/ቤቶች ስልጣን ስር የሚወድቁ ናቸው። አከራካሪ የነበረው ውርስ አጣሪ የመሾም ስልጣንም የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ.35657 (ቅጽ 9 ላይ እንደታተመ) በሰጠው ውሳኔ የፌ/ፍ/ቤቶች ስልጣን መሆኑ ተረጋግጧል። የወራሽነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመስጠት ስልጣን ግን ከላይ በመጀመሪያው ክፍል እንደተቀመጠው ከውርስ እና ከቤተሰብ ጉዳዮች ተነጥሎ በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር አዋጅ ለአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤት ተሰጥቷል።

የዚህ ምስክር ወረቀት ምንነት እና የሚሰጥበት ሁኔታ ከውርስ ህጉ ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ደግሞ ምስክር ወረቀቱ በልዩነት በፍ/ብሔር ሕጋችን ከአንቀጽ 996 እስከ አንቀጽ 998 ባሉት ድንጋጌዎች የሚገዛ ሲሆን እነዚህ ድንጋጌዎች ደግሞ ስለ ውርስ ማጣራት በሚያወራው የውርስ ህጉ 2ኛ ምዕራፍ ስር ተካተው የሚገኙ ናቸው። በዚህም መሰረት የወራሽነት ምስክር ወረቀት የውርስ ማጣራት ሂደት አካል መሆኑን እና ወራሾች የውርስ አጣሪው በአንቀጽ 856 እና 994 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ወራሾችን፣ የውርስ ሀብቱን፣ የወራሾችን ድርሻ እና ሌሎች ነገሮችን ካጣራ በኋላ በፍ/ሕ/ቁ.960(1) መሰረት የሚያቀርብላቸውን የስራ ክንውን ሪፖር (የውርስ አጣሪ ሪፖርት) በማስረጃነት በማቅረብ ፍ/ቤቱ ወራሽ መሆናቸውን እና የውርስ ድርሻውን የሚገልጽ ምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት የሚሰጥ የውርስ ማጣራት ውጤት መሆኑን መረዳት እንችላለን።

በዚህም መሰረት ለሁሉም ችግሮች ምክንያት የሆነው ይህን የውርስ ማጣራት ሂደት የሆነ የወራሽነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የማግኘት ጉዳይ ከውርስ ጉዳይ እና ከውርስ ማጣራት ሂደት ተነጥሎ እንዲታይ እና በሌላ ፍ/ቤት ስልጣን ስር እንዲወድቅ መደረጉ ነው የሚል እምነት አለኝ ። በሌላ በኩል ከሕጉ ጽንሰ ሀሳብ እና አወቀቀር ውጪ ውርስ ሳይጣራ የወራሽነት ምስክር ወረቀት በአቋራጭ ለብቻው እንዲሰጥ መደረጉ የውርስ ማጣራት ስራ በሕጉ መተቀመጠለት አጭር ጊዜ ውስጥ እንዳይከናወን እና በዚህም ምክንያት በስራው ላይ የበዙ መጓተቶች፣ የመብት ማጣቶች እና የማስረጃ መጥፋቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።

መፍትሔው

በመሆኑም ለዚህ ችግር አስተማማኝ ዕልባት ለመስጠት የወራሽት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመስጠት ስልጣንን መልሶ ወደ ውርስ ጉዳይ በመመለስ አጠቃሎ የማየቱን ስልጣን ለአንድ ፍ/ቤት መስጠት ዘላቂ መፍትሔ ነው የሚል እምነት አለኝ ። ስልጣኑ ለየትኛው ፍ/ቤት ሊሰጥ ይገባል ለአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤት ወይስ ለፌ/ፍ/ቤት የሚለው ደግሞ ቀጥሎ መታየት የሚገባው ነው። ከላይ እንደተገለጸው በውርስ እና በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ ባለርስቶቹ የፌ/ፍ/ቤቶች ናቸው። ርስቱ ሲከፋፈል ጉዳዩ በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ቅጥር ውስጥ የወደቀ ነው። በመሆኑም በመጀመሪያ ተነጥሎ ለከተማ ፍ/ቤት የተሰጠውን የወራሽነት ማረጋገጫ የመስጠት ስልጣን የውርስ ጉዳይን የማየት ስልጣን ወዳላቸው የፌ/ፍ/ቤቶች በመመለስ ጉዳዩን ማስተካከል ይቻላል። በሌላ በኩልም ሙሉ የውርስ ጉዳይ ስልጣኑን ለአዲስ አበባ ፍ/ቤቶች መስጠትን እንደአማራጭ መፍትሔ አድርጎ የሚያቀርብ አይጠፋም።

ይሁን እንጅ የከተማዋ ፍ/ቤቶች ምንም እንኳን የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ.75560፣ 172282፣ 171061 161650፣ 199769፣ 195227፣ 196567 እና 216496 በሰጣቸው ውሳኔዎች የመስመር ስር ንባብ የተወሰደባቸው ሰፊ እና ውስብስብ ጉዳዮችን የማየት አቅም የላቸውም የሚል ግምት ሰፊ እና ውስብስብ ጉዳዮችን ለማየት የሚያስችል ተጨማሪ ስልጣን በሰጣቸው አዋጅ ቁጥር 1234/13 የተነሳላቸው ቢመስልም ከማስቻያ ስፍራ እጥረት፣ ከችሎት አወቃቀር ድክመት፣ ከሰራተኛ ማነስ እና ከጠቅላላ የበጀት እና የቁሳቁስ አቅርቦት ችግሮቻቸው አንጻር እና የተጨመረላቸውን ተጨማሪ ስልጣን ለማስተናገድ የሚያስችል ምንም ዓይነት ለውጥ ካለማድረጋቸው አንጻር ሲታይ ግን የሰበር ችሎቱን ግምት አምነው የተቀበሉ ይመስላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የቤተሰብ እና የውርስ ጉዳዮች የፌ/ፍ/ቤቶችን አብዘሃኛውን የመዛግብት ቁጥር የሚሸፍኑ ግዙፍ ጉዳዮች በመሆናቸው የከተማ ፍ/ቤቶች አሁን ባሉበት ሁኔታ ለከተማ ፍ/ቤት መስጠት የሚታሰብ ባለመሆኑ ስልጣኑን ለአዲስ አበባ ፍ/ቤቶች መስጠት የሚለው የመፍትሔ አማራጭ ውሃ የሚቋጥር አይደለም።

ሲጠቃለልም በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር ላይ እና በፌ/ፍ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጆች ላይ ማሻሻያ በማድረግ የወራሽነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመስጠት ስልጣንን ከአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች ወስዶ ለፌ/ፍ/ቤቶች (የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት) መስጠት ለችግሩ የተሻለ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሰጥ አምናለሁ። በግልጽ ባይቀመጥም አዲስ በወጣው የፌ/ፍ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 5(1) (ደ) ላይ በቻርተሩ ለከተማ ፍ/ቤት ተሰጥተው ከነበሩት ስልጣኖች መካከል የወራሽነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መስጠትን የተመለከተው ስልጣን ወደ ፌደራል ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን የተካተተ ይመስላል። በመሆኑም አሁን ላይ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 5(1) (ደ) እና 57(2) ን ከአዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 41 እና ከማሻሻው አዋጅ ቁጥር 408/96 አንቀጽ 2 ድንጋጌዎች ጋር በማናበብ የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶች የወራሽነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመስጠት ስልጣን የላቸውም በማለት የሚቀርብ ክርክር የሕግም ሆነ የአመክንዮ መሰረት የለውም ሊባል አይችልም።

ይህ በሕግ ማሻሻም ሆነ በሕግ ትርጉም ሊመጣ የሚችለው ሙሉ ስልጣኑን ለፌ/ፍ/ቤቶች የመስጠት መፍትሔ በፍ/ሕ/ቁ.998 ስር በተቀመጠው አግባብ ችሎቶች ራሳቸው በሰጡት የወራሽነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ላይ የሚቀርብን መቃወሚያ ራሳቸው አይተው እንዲወስኑ የሚያስችል እና ችግሩን በዘላቂነት እና በአስተማመኝነት የሚፈታ መስሎ ይታየኛል።

እርስዎስ ምን መስሎ ይታይዎታል ወዳጄ ?

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ተገዶ የመያዝን ሕጋዊነት ለማጣራት የሚቀርብ ክስ (Habeas corpus) እና ...
በኢትዮጵያ የብድር ሕግ "አበደረ" ማለት የብድሩን ገንዘብ ሰጠ ማለት ይሆን?

Related Posts

 

Comments 2

Abyssinia Law | Making Law Accessible! on Friday, 11 November 2022 19:58

ሰላም ፈቃዱ
ጽሑፍህን ስላካፈልከን እናመሰግናለን። በርታልን።

ሰላም ፈቃዱ ጽሑፍህን ስላካፈልከን እናመሰግናለን። በርታልን።
Abebe
Guest - yonas on Saturday, 12 November 2022 21:42

በጣም ጥሩ ሃሳቦችን አቅርበሃል። ፅሁፉ በተለይ የመቃወም ማመልከቻ አቅራቢው ወገን ላይ ያለውን ጫና አሳይተሃል። አሁን ባለው የከተማ ነክ ፍርድ ቤት አሰራር ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ወራሽነት አረጋግጦ ባለመብት መሆን ይችላል። ይህን ማሻር ደሞ በጣም ከባድ ነው።

በጣም ጥሩ ሃሳቦችን አቅርበሃል። ፅሁፉ በተለይ የመቃወም ማመልከቻ አቅራቢው ወገን ላይ ያለውን ጫና አሳይተሃል። አሁን ባለው የከተማ ነክ ፍርድ ቤት አሰራር ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ወራሽነት አረጋግጦ ባለመብት መሆን ይችላል። ይህን ማሻር ደሞ በጣም ከባድ ነው።
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 11 September 2024