Font size: +
14 minutes reading time (2872 words)

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ-መንግሥት መተርጎም ላይ ያለው ሚና እና በጉባዔው አዋጅ ላይ የተደረገ አጭር ምልከታ

ሁሉም ሕጎች በራሳቸው ምሉዕ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ሕጎችን በተገቢው የአተረጓጎም ሥርዓት መሠረት ተርጉሞ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ አጠቃላይ መርሆዎችን የደነገጉ ሕጎችን የያዙ እንደ ሕገ-መንግሥት ዓይነት ሕጎች በከፍተኛ ጥንቃቄ መሠረታዊ የአተረጓጎም መርሆዎችን በተከተለ ሁኔታ ፍጹም ገለልተኛና ብዘሀኑን በሚወክል ብቃት ባለው ሕገ-መንግሥት ተርጓሚ ሊተረጎም ይገባዋል፡፡ ይህም በመሆኑ ብዙ ሐገራት ሕገ-መንግሥት የሚተረጉም ራሱን የቻለ ተቋማትን አቋቁመዋል፡፡

ሐገራችን ኢትዮጵያም እንደሌሎች ሐገራት የሕገ-መንገስት ትርጉም ጥያቄ ሲቀርብ ጉዳዩን ተቀብሎ ተገቢውን ውሳኔ የሚሰጡ ተቋማትን አቋቁማለች፡፡ የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት የሕገ-መንግስታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ ጥያቄው እንዴት መልስ ያገኛል ለሚለው ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 62 ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ የሕገ-መንግስታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ያገኛል በማለት ደንግጓል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤቱም የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርብለት ሕገ- መንግስታዊ ጉዳይ ላይ በሠላሳ ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም በሚሰጥበት ጊዜ ሞያዊ ዕገዛ የሚሰጠው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሥልጣንና ተግባር በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 84 ላይ ተዘርዝሮ ተቀምጧል፡፡

በዚህ አጭር ጽሑፍ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሕገ-መንግስቱ የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባሩን እንደዚሁም ጉባዔውን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በድጋሚ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 798/2005 መሠረት በማድረግ በሕጉ ረገድ ያሉትን ጥሩና ደካማ ጎኖች እንዲሁም የጉባዔውን አሰራሮች በመጠኑ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡  በቅድሚያ ግን የሕገ-መንገስት ትርጉም ስንል ምን ማለታችን ነው የሚለውን ለማየት እንሞክር፡-

     የሕገ-መንግሥት ትርጉም ምንነት

ሕገ-መንግሥት እንደ ማንኛውም መደበኛ ሕግ (ordinary law) አይደለም፡፡ ይልቁንም ልዩ ዓይነት ሕግ (special law) ነው፡፡ ልዩ የሚሆንበትም ምክንያት በውስጡ ሕግ፣ ፖሊቲካ፣ ባህልና ታሪክ ጠባያትን የያዘ እንደዚሁም ደግሞ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ተብሎ የሚታሰብ ከሁሉም ሕጎች የበላይ የሆነ ሕግ በመሆኑ ነው፡፡ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ስንል አንድና ወጥ የሆነ ትርጉም አናገኝለትም፡፡ ለምሳሌም በዚህ መንገድ ተተርጉሟል፡፡

Constitutional interpretation can be defined as ‘the activity aimed at extracting from a written constitution the general normative content and specific meaning of its provisions’

በአጭሩ ግን የሕግ ትርጉም ስንል ሕግ ተርጓሚው በሕጉ ውስጥ ያሉትን ቃላት ትክክለኛ ሐሳባቸውን፣ ዓላማቸውን፣ ግባቸውን የሚፈልግበት ሒደት ነው፡፡በተለይም ሕገ-መንግሥት ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ሰነድ በመሆኑና የሕግ አውጪውን ሐሳብ ብቻ በመያዝ ትርጉም መስጠት የሚቻልበት ባለመሆኑና የብዙዎችም ፍላጎት ያለበት ስለሆነ የትርጉም ስራውን አዳጋች ያደርገዋል፡፡

ሕገ-መንግሥትን መተርጉም ለምን ያስፈልጋል?

ማንኛውም ሕግ በራሱ ምሉዕ ሆኖ ራሱን ችሎ ያለምንም ትርጉም አስፈላጊነት ተፈጻሚ እንዲሆን ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን እንደ ሕገ-መንግሥት ዓይነት ሕጎች መደበኛ ሕጎችን (substantive laws) ብቻ ሳይሆኑ የፖለቲካ ዶክመንትም ስለሆኑ ራሳቸውን ችለው (self-executing) ያለ ትርጉም ተፈጻሚ ለማድረግ የሚከብዱ ናቸው፡፡

የሕገ-መንግሥት ሕጎቹ ሰፊ፣ አሻሚ፣አከራካሪ፣ ወይም ደግሞ ጸጥ ያሉ (silent) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ መሠረታዊ የአተረጓጎም መርሆችን በጠበቀ መልኩ ትርጉም መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ሕገ-መንግስቱን ያወጣው አካል ፈጽሞ ያላያቸውና ሊያያዋቸው የማይችላቸው ሁኔታዎች ወይም ሕገ-መንግስቱ በወጣበት ጊዜ ያልነበሩና ሊኖሩም የማይችሉ ከጊዜ በኃላ የመጡ አዲስ ነገሮች አንዳንዴም አርቃቂዎቹ ከቃላት እጥረት ወይም ከፅንሰ ሐሳብ አዲስነት በግልጽ ቃላት የማያስቀመጡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ሕገ-መንግሥትን መተርጎም ግድ ይላል፡፡

በሐገራችን ያለው ብንመለከት በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 9/1 ላይ ሕገ-መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ-መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም ይላል፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ተቋማት የሚያወጧቸው ሕጎች፣ አሰራሮች፣ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ከሕገ-መንግስቱ ጋር መቃረን የሌለባቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ተቃራኒ ሆነው ከተገኙ ግን ሕገ-መንግሥት ተርጓሚው (የፌደሬሽን ምክር ቤት) እነዚህን ከሕገ-መንግሥቱ ተቃራኒ የሆኑ ሕጎች፣አሰራሮችና ውሳኔዎች ሕጋዊ ውጤት እዳይኖራቸው ሕገ-መንግሥቱን በመተርጎም ውሳኔ ይኖርበታል፡፡

የሕገ-መንግሥት ትርጉም ካልተሰጠ ደግሞ መሠረታዊ የሆኑ የሰዎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውና ነጻነቶች ሊከበሩ አይችሉም ይልቁንም ሊጣሱ የሚችሉበት ዕድል ይሰፋል፡፡

የተለያዩ ሐገራት ሕገ-መንግሥት የመተርጎም ልምድ

በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት ሕገ-መንግሥት የመተርጎም የሕግ ሥርዓት አለ፡፡ የመጀመሪያው የተማከለ (centralized model) የሚባለው ሥርዓት ሲሆን ይህም በአውሮፓና በተወሰኑ ሐገራት የሚተገበር አሰራር ነው፡፡ የተማከለ ወይም ማዕከላዊ የሆነ የተባለበትም ምክንያት ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን ለአንድ ተቋም ብቻ ተላይቶ ተጠቅሎ (monopolization) የሚሰጥ በመሆኑ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ያልተማከለ (Decentralized model) ሥርዓት ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ የፍርድ ቤቶቹን የሥልጣን ደረጃ ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ሁሉም መደበኛ ፍርድ ቤቶች (ordinary courts) ሕገ-መንግሥት እንዲተረጉሙ ስልጣን የሚሰጥ አሰራር ነው፡፡ ያልተማከለ የተባለበትም ምክንያት ስልጣኑ ለሁሉም ፍርድ ቤቶች የተከፋፈለ በመሆኑ ነው፡፡

ከላይ የገለጽነውን ዓይነት አሰራር ሥርዓት ያላቸውን የተወሰኑ ሐገራትን በምሳሌነት በመጥቀስ የሕገ-መንግሥት ትርጉም አሰጣጥ ስርዓታቸውን ለማየት እንሞክር፡-

 

1. የአሜሪካን ሞዴል (Decentralized model)

 ሕጎች ከሕገ-መንግስቱ ጋር የተጣጣሙ መሆን አለመሆናቸውን በፍርድ ቤት እንዲታይና ትርጉም እንዲሰጥባቸው ካደረጉ ሐገራት መካከል አሜሪካ ቀዳሚዋ ሐገር ናት፡፡ አሜሪካኖች ሕገ-መንግሥት በፍርድ ቤት ሊዳኝ የሚችል ሕጋዊ ሰነድ (legal document) ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በዩናትድ ስቴትስ ማንኛውም ፍርድ ቤት አንድን ሕግ ሕገ መንግስታዊ አይደለም ብሎ ሊወስን ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

በአጠቃላይ በዩናይትድ ስቴትስ የሕጎችን ሕገ-መንግስታዊነት ለመመርመር ለአንድ አካል ተጠቅሎ የተሰጠ ስልጣን ሳይሆን ለሁሉም ፍርድ ቤቶች ባልተማከለ (Decentralized) ሁኔታ የተሰጠ ስልጣን ነው፡፡

2. የአውሮፓ ሞዴል (centralized model)

በአውሮፓ እና በተወሰኑ ሐገራት ደግሞ ከሕገ-መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ ሕጎችን ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም ለመስጠት የሕገ-መንግሥት ጉዳዮችን የሚመለከቱ ልዩ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች (special constitutional courts) ተቋቁመዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮችን የመተርጎም አሰራር በአንድ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮችን የሚተረጉም ወይም ለዚህ ተብሎ በተቋቋመ ልዩ በሆነ ፍርድ ቤት ሥልጣን ስር የተጠቃለለ በመሆኑ የተማከለ (centralization) የሆነ አሰራር እንደሚከተሉ መረዳት ይቻላል፡፡

3. የላቲን አሜሪካ ሞዴል

የሕገ-መንግሥት ትርጉም መስጠትን በተመለከተ በላቲን አሜሪካ ለየት ያለ ሥርዓትን የሚከተሉ ሐገራት አሉ፡፡ ይኸውም ሕገ-መንግሥት ትርጉም በፍርድ ቤት እና በሕገ-መንግስታዊ ልዩ ፍርድ ቤቶች (mixed system) አማካይነት እንዲሰጥ የሚፈቅድ ሥርዓት ይከተላሉ፡፡  

በአጠቃላይ ሐገራት ሕገ-መንግሥትን መተርጎም በተመለከተ የየራሳቸው ሥርዓት ዘርገተዋል፡፡ አሜሪካ፣ ሕንድ፣ አውስትራሊያ የመሳሰሉ ሐገራት ፍርድ ቤቶች ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮችን እንዲያዩ ስልጣን የሰጡ ሲሆን፣ አውሮፓ ደግሞ ልዩ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮችን የሚያዩ ፍርድ ቤቶችን አደራጅተዋል፣ ቻይና ብሔራዊ ሕዝባዊ ኮንግረስ ቋሚ ኪሚቴ በተባለውን አካል የሕገ-መንግሥት መተርጎም ስራዎችን ስትሰራ ስዊዘርላንድ ደግሞ ሪፈረንደም በማድረግ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ይሰጣሉ፡፡

ሕገ-መንግሥትን መተርጎም በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የሕገ-መንግሥት መተርጎም ሥልጣን የተሰጠው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ከላይ በዝርዝር ለማየት ከሞከርናቸው የተለያዩ ሐገራት ሕገ-መንግሥት አተረጓጎም ሥርዓት (system) አንጻር የኢትዮጵያ በጣም የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ስልጣን እንደሌሎች ሐገራት ለፍርድ ቤቶች ወይም ሕገ-መንግሥት ለመተርጉም ለተቋቋመ ልዩ ፍርድ ቤት የተሰጠ ሳይሆን የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች ተወካዮች ላሉበት ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት ደግሞ የፖሊቲካ ቻምበር (political chamber) ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መተርጎም እንደ ሌሎች ሐገራት ለፍርድ ቤት ወይም ለልዩ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች የተሰጠ ባለመሆኑና በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 83/1 ላይ የሕገ-መንግሥታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ በፌደሬሽኑ ምክር ቤት ውሳኔ ያገኛል በሚል የተደነገገ በመሆኑ ስልጣኑ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ብቻ ተለይቶ የተሰጠ ነው በሚል የህግ ምሁራን ኢትዮጵያ የተማከለ (centralized) የሚባለውን ሕገ-መንግሥት መተርጎም ሥርዓት ተከታይ ናት ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን የሕገ-መንግሥት መተርጎም ሥርዓት በተመለከተ በሕግ ምሁራን ዘንድ የተለያየ አቋም አለ፡፡ ለምሳሌ የተወሰኑ ምሁራን የፌደራል ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ-መንግስቱን የመተርጎሙን ሥራ ከማርዘምና ከማንዘዛት የተለየ ፋይዳ የለውም ስለሆነም ተቋሙ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ሌሎች ደግሞ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአብዛኛው የሕግ ባለሞያዎች ያሉበት እንደዚሁም ከተለያዩ ክፍሎች ላይ የተውጣጡ በመሆናቸው የብዙሃኑን ውክልና የያዙ ስለሆነ ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ሙሉ ስልጣን ሊሰጠው ይገባል ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍርድ ቤቶች ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም ምንም ዓይነት ሚና እንዳይኖራቸው ማድረግ ተገቢ አይደለም ምክንያቱም ሕገ-መንግሥት ፖለቲካዊ ሰነድ ብቻ ሳይሆን ሕጎችን ደንግጎ የያዘ ስለሆነ በተወሰነ መልኩ ፍርድ ቤቶች የሕገ-መንግሥት ትርጉም እንዲሰጡ ሊደረግ ይገባል የሚሉ አመለካከቶች አሉ፡፡

ሕገ-መንግሥትን በመተርጎም ላይ የተቋማት ሚና

1. የፌደሬሽን ምክር ቤት

የፌደሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግስቱ ከተቋቋሙ ሁለቱ ምክር ቤቶች አንዱ ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት እንደሌሎች ሐገራት ሁለተኛ ምክር ቤት ሳይሆን ሕግ አውጪ ያልሆነ (non-legslative council) ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱ የተለያዩ ስልጣንና ተግባራት የተሰጡት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ አንዱ ሕገ-መንግስቱን መተርጎም ነው፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት በፌደራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች የሚልኩዋቸው አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው፡፡

2. ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ

የፌደሬሽን ምክር ቤቱ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ሲሰጥ ሞያዊ ድጋፍ እንዲሰጥ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እንዲቋቋም ተድርጓል፡፡ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ በሚያደርገው ማጣራት መሠረት ሕገ-መንግስቱ መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌደሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል፡፡  የመጨረሻውን ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ነው፡፡ ለሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ከራሱ ከፌደሬሽን ምክር ቤት፣ ከክልል ሕግ አውጪ አካላት፣ ከሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ ከፍርድ ቤቶችና ከማንኛውም የሚመለከተው ግለሰብ ጥያቄው ሊቀርብለት ይችላል፡፡

የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አባላትን ስንመለከት የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በሰብሳቢነትና በምክትል ሰብሳቢነት እንደዚሁም በፌደሬሽን ምክር ቤት አቅራቢነት በሐገሪቱ ርዕሰ ብሔር ፕሬዚዳንቱ የሚሾሙ በሕግ ዕውቀታቸውና ስነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ ስድስት የሕግ ባለሞያዎች እና ሦስት የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት በጠቅላላ አስራ አንድ አባላት አሉት፡፡

በክልሎች በኩል ያሉትን ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪዎች ስንመለከት በአንዳንድ ክልሎች የተቋቋሙ ቢሆንም በአግባቡ አልተደራጁም በሚጠበቅባቸው ደረጃም ሥራ እየሰሩም አይደለም፡፡ በአጠቃላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት እና የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሕገ-መንግሥት መተርጎም ላይ ከፍተኛ የሆነ ሚና አላቸው፡፡

የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ስልጣንና ተግባራት እንደዚሁም በሕጉ ላይ ያሉ ክፍተቶች አጭር ምልከታ

በሕገ-መንግሥት ትርጉም ሒደት ላይ ሕገ-መንግስቱን እንዲተረጉም ስልጣን ለተሰጠው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ሞያዊ ዕገዛ እንዲሰጥ በሚል የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ተቋቁሟል፡፡

ይህንን የሕ-መንግስቱን ድንጋጌ ተከትሎ የፌደራሉ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአዋጅ ቁጥር 250/1993 የታወጀ ቢሆንም ይህ አዋጅ ለአስር ዓመታት ያክል ጊዜ ሲያገለግል ቆይቶ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በሚል በድጋሚ በወጣ በአዋጅ ቁጥር 798/2005 ተተክቷል፡፡

አጣሪ ጉባዔው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የቀረበለትን የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ መርምሮ ትርጉም አያስፈልገውም ብሎ ካመነ ለባለጉዳዩ ወይም ከፍርድ ቤት የመጣ ከሆነ ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ተመላሽ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ብሎ ካመነ ደግሞ የራሱን የውሳኔ ሐሳብ አስቀምጦ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ለመጨረሻ ውሳኔ ይልካል፡፡ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ሲቀርብለት ከአቤቱታ አቀራረብ አንስቶ እስከ ውሳኔ አሰጣጥ ድረስ ያለውን አሰራር ከሕጉ ጋር በማገናዘብ ለማየት እንሞክር፡-

 

1. የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ አቤቱታ አቀራረብ ሥነ-ሥርዓት

ማንኛውም ባለጉዳይ ወይም ፍርድ ቤት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ለአጣሪ ጉባዔው ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ ሲሆን ባለጉዳዩ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ለአጣሪ ጉባዔው እንዲልክለት መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ያልተቀበለ እንደሆነ ባለጉዳዩ ውሳኔውን እንዳወቀ በ 90 ቀናት ውስጥ ለአጣሪ ጉባዔው ማቅረብ ይኖርበታል፡፡  በአጣሪ ጉባዔው ቅር የተሰኘ ባለጉዳይ ቅሬታውን በይግባኝ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡

የሕገ-መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥለት ማንኛውም የሚመለከተው ባለጉዳይ በተወካይ አማካይነት ጥያቄውን ለማቅረብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ውክልናው በፍ/ብ/ሕ/ሥነ-ሥርዓት ሕግ መሠረት ነው ወይንስ በምን አግባብ የሚለው በሕጉ ላይ በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ምናልባትም ጉባዔው የሚያወጣው የአቤቱታ አቀራረብ መመሪያው የሚደነግገው ይሆናል፡፡

ለሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አቤቱታ የሚቀርበው ያለ ክፍያ በነጻ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አጣሪ ጉባዔው በዋናነት ስራውን የሚሰራው ለሕዝብ ጥቅም (pubic interest) ነው ተብሎ ስለታሰበ ነው፡፡

በአዋጁ ላይ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ በአቤቱታው ላይ ምን ምን ነገሮችን መጥቀስ አለበት የሚለው በዝርዝር አልተቀመጠም፡፡ የጥያቄው አቀራረብ በሚወጣው መመሪያ መሠረት እንደሚሆን በአዋጁ አንቀጽ 7/1 ላይ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን መመሪያው ለብዙ ጊዜ ሳይወጣ በመቅረቱ ምክንያት ባለጉዳዮች አቤቱታቸውን በምን መልኩ ማቅረብ እንዳለባቸው ችግር ሲገጥማቸው ተስተውሏል፡፡

የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ በምን በምን ጉዳዮች ላይ ሊቀርብ ይችላል የሚለውን በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ 3/1 ላይ አጣሪ ጉባዔው ማንኛውንም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ ወይም የመንግሥት አካል ውሳኔ ወይም የባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገ-መንግስቱ ጋር ይቃረናል የሚል ጥያቄ በጽሑፍ ሲቀርብለት ያጣራል በማለት ደንግጓል፡፡

ለጉባዔው የሚቀርቡት አቤቱታዎች ብዙዎቹ ወይም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ ሰዎች እንደ መጨረሻ አማራጭ ለአጣሪ ጉባዔው አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ አቤቱታዎች የሕገ-መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ውድቅ ይደረጋሉ፡፡ ለጉባዔው የሚቀርቡ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጉዳዮች ምንነትና ይዘት በሕጉ ላይ ግልጽ ሆነው ተዘርዝረው የተደነገጉ ባለመሆኑ በጉባዔው ስራ ላይ ከባድ ፈተና ሆኗል፡፡ አንዳንድ ሐገራት ለሕገ-መንግሥት ትርጉም የሚቀርቡ ጉዳዮች ምን ምን ናቸው የሚለውን በሕጋቸው ላይ ዘርዝረው አስቀምጠዋል፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ ለሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮችን በሕጓ ላይ ለይታ ዘርዝራለች፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች ደግሞ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ሊቀርብባቸው አይችልም በሚል ክልከላ አስቀምጣለች፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ  ሊታይ የሚገባው ነጥብ ከፍርድ ቤት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ሊነሳ የሚችለው በፌደራሉ መንግሥትም ሆነ በክልል ሕግ አውጪ አካላት የሚወጡ ሕጎች ከሕገ-መንግሥት ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ብቻ ሲነሳ ነው ይህም ከሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 84/2 ላይ መረዳት ይቻላል የሚል አመለካከት አለ፡፡ ስለሆነም የፌደራሉም ሆነ የክልል ፍርድ ቤቶች የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሊያነሱ ይችላሉ? ወይንስ አይችሉም? የሚለው ጥያቄ በደንብ ሊታይ የሚገባው ነጥብ ነው፡፡

ሌላው ጉባዔው ለሚቀረቡለት ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም ጥያቄዎች የውሳኔ ሐሳብ በሚሰጥበት ጊዜ የውሳኔ ሐሳብ ለመስጠት የሚረዱ መሠረታዊ የአተረጓጎም መርሆዎችን መከተል ይኖርበታል፡፡ ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም ለመስጠት በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 13/2 መሠረት ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን የጉባዔውን የውሳኔ ሐሳቦችን ስንመለከት መሠረታዊ የአተረጓጎም መርሆች (principles of interpretation) ወይም በሙከራ የዳበር ልምድ የጎደላቸው ናቸው፡፡ 

አቤቱታው ከቀረበ በኃላ የአጣሪ ጉባዔው ሰብሳቢ በቀረቡ ጉዳዮች ላይ የሙያ አስተያየት እንዲዘጋጅ ለንዑስ አጣሪ ኮሚቴ አባላት ወይም ለጽሕፈት ቤቱ ባለሞያዎች በቅድሚያ ይመራል፡፡ ንዑስ አጣሪ ኮሚቴው ምንም እንኳን በሕገ-መንግስቱ እውቅና ባይኖረውም ለጉባዔው ስራ እንዲመች በሚል የተደራጀ ነው፡፡ ነገር ግን በአዋጁ አንቀጽ 24 ላይ ንዑስ አጣሪ ኮሚቴው ተጠሪነቱ ለአጣሪ ጉባዔው የሆነ በአጣሪ ጉባዔው የሚሰየሙ አባላት እንዳሉት ቢገልጽም በአዋጁ አንቀጽ 2/7 ላይ ግን ንዑስ አጣሪ ኮሚቴ ማለት ከአጣሪ ጉባዔ አባላት መካከል ከሶስት የማያንሱ አባላትን ያካተተ ኮሚቴ ነው በማለት ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ይህም ንዑስ ኮሚቴው ከአጣሪ ጉባዔ አባላት መካከል የሚመረጡ ናቸው ወይንስ በአጣሪ ጉባዔው የሚሰየሙ ለሚለው ግልጽነት የጎደለው የሚያምታታ የትርጉም አገላለጽ በመሆኑ ስህተቱ ሊታረም ይገባል፡፡

የአጣሪ ጉባዔው ሰብሳቢ ከቀረቡት ጉዳዮች በተለየ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲታይ ብሎ ካመነ በቅድሚያ ከሚታዩ ጉዳዮች በቀር ጉዳዮች የሚታዩት እንደ ቅደም ተከተላቸው ነው፡፡ በተግባር ያለው አሰራር ከፍርድ ቤት ተመርተው የመጡ በተለይም ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው የሚከታተሉ፣ ዕግድ የተጠቀባቸው ጉዳዮች ፣የሕጻናት ጉዳዮች የመሳሰሉት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየታዩ ይገኛሉ፡፡

ሌላው የሥነ-ሥርዓት ጉዳይ አጣሪ ጉባዔው የያዘውን ጉዳይ የሚያይበት መንገድ ነው፡፡ ይህም በአዋጁ አንቀጽ 10/4 መሠረት ጉባዔው ጉዳዮችን በግልጽ እንደሚያይ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን በተግባር ጉባዔው ጉዳዮችን ግልጽ በሆነ መንገድ እያየ አይደለም፡፡ ማንኛውም ባለጉዳይ አጣሪ ጉባዔው ጉዳዩን ሲመለከት የሚያይበት፣ የሚከታተልበት አሰራር የለም፡፡ ይህም አሰራር ከሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 12 እንደዚሁም ጉባዔው ከተቋቋመበት አዋጅ ውጪ የሆነ አሰራር ከመሆኑ ባለፈ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት እንዳይኖር የሚያደርግ ለማይገባ አሰራር መንገድ የሚከፍት ነው፡፡ 

በአዋጁ ላይ የሕገ-መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥለት ከሚያቀርበው ባለጉዳይ ውጪ ሌላኛው ተከራካሪ ወገን በጉዳዩ ላይ የራሱን መከራከሪያ ለጉባዔው የሚያቀርብበት ዕድል የለም በተግባርም እየተሰራበት አይደለም፡፡ ይህ አሰራር የአንደኛውን ወገን የመከላከል ዕድል የሚያሳጣ ከመሆኑም በላይ ጉባዔው ትክክለኛ የሆነ የውሳኔ ሐሳብ ላይ እንዳይደርስ የሚያደርገው በመሆኑ ይህ ዓይነቱ አሰራር መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ ለሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሚቀርብ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ በምን ያክል ጊዜ ውስጥ መቅረብ እንዳለበት በአዋጁ ላይ የተቀመጠ የይርጋ ጊዜ የለም፡፡ ነገር ግን ይርጋ ማለት በአጭሩ ጊዜ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በጊዜ የተገደበ ነው፡፡

ስለሆነም የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የሚቀርብበት የይርጋ ጊዜ በሕጉላ ሊገለጽ ይገባዋል፡፡ ወይም ደግሞ የይርጋ ጊዜ የሌላቸው ጉዳዮች ካሉም  በአዋጁ ወይም በመመሪያው ላይ ተዘርዝረው ሊቀመጡ ይገባል፡፡

2. የአጣሪ ጉባዔው ውሳኔና የውሳኔ ሐሳብ አሰጣጥ

የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ውሳኔ አሰጣጥ በተመለከተ ከጉባዔው ሁለት ሦስተኛ አባላት ከተገኙ ጉባዔው ይካሄዳል፡፡ የጉባዔውም ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ ይወሰናል፡፡ በውሳኔው ላይ የጉባዔው አባላት ስም ዝርዝር እንደዚሁም በጉዳዩ ላይ የተሰጡትን አስተያየቶች ያካተተ መሆን እንዳለበት አዋጁ ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መስከረም 2011 ዓ/ም ላይ አሳትሞ ባወጣው የጉባዔው የውሳኔ ሐሳቦችን የያዘ ጆርናል ላይ የጉባዔው አባላት ስም ዝርዝር አልተጠቀሰም፡፡

የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በቀበረው ጥያቄ ላይ የሕገ-መንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም በማለት ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ቅር የተሰኘ ወገን ይግባኙን ለምክር ቤት ማቅረብ ይችላል ፡፡

አጣሪ ጉባዔው ስራውን ለመስራት በወር አንድ ቀን እንደሚሰበሰብ በአዋጁ ላይ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ለጉባዔው ከሚቀርቡ መዝገቦች ብዛት አንጻር በወር አንድ ቀን ብቻ ጉባዔው ስብሰባ ማድረጉ ፈጽሞ አግባብነት የለውም፡፡ ምክንያቱም በየቀኑ በርካታ አዳዲስ ፋይሎች ይከፈታሉ ብዙ ሺ ፋይሎችም ወረፋ እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡  በተጨማሪ ደግሞ የዕግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙም በርካታ ፋይሎች አሉ፡፡ ለጉባዔው ከቀረቡ ፋይሎች ውስጥ እስከአሁን ድረስ መቶ የማይሞሉ ጉዳዮች ላይ ብቻ የውሳኔ ሐሳብ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደተሰጠ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም ስራውን ከጀመረ ከአስራ አምስት ዓመት በላይ ለሆነው ተቋም እጅግ አነስተኛ የሆነ የስራ አፈጻጸም መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ስለሆነም ጉባዔው በየወሩ ስብሰባ ያደርጋል በሚል መደንገጉ ካለው የፋይል ፍሰት ብዛት አንጻር ፈጽሞ የማይመጣጠን በመሆኑ ጉባዔው በየቀኑ የሚሰበሰብበት አሰራር በአስቸኳይ መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል፡፡

የአጣሪ ጉባዔው ተቋማዊ አደረጃጀትና የአሰራር ችግሮች

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ጉባዔው አስራ አንድ አባላት አሉት፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት በጉባዔው ውስጥ በሰብሳቢነት እና በምክትል ሰብሳቢነት ይሰራሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱና ምክትል ፕሬዚዳንቱ በጉባዔው ውስጥ በሰብሳቢነትና በምክትል ሰብሳቢነት መስራታቸው የስልጣን መከፋፈል (separation of power) የሌለው መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ ምክንያቱም በሁለቱም ቦታ ተመሳሳይ ሰዎች ሆነው (Double membership) መስራታቸው ገለልተኛነት የሌለው አሰራር ይሆናል፡፡ ይህንንም ደግሞ ሕገ-መንግስቱም ሆነ አዋጁ ክልከላ አላደረጉበትም፡፡

ባለጉዳዮች የፌደራል ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ በፌደራሉ ፍርድ ቤት ያዩትን ጉዳይ መልሰው በጉባዔው ላይ ሊመለከቱ አይገባም በሚል ተቃውሞ ቢያቀርቡም የፍርድ ቤቱ ስራና ኃላፊነት ከጉባዔው ስራና ኃላፊነት ጋር የተለያየ ነው በሚል ምክንያት የአመልካቾች ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል፡፡

የአጣሪ ጉባዔው ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ የስልጣን ቆይታ ጊዜ በፌደራል ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዚደንት እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ ሲሆን ከፌደሬሽን ምክር ቤት የተሾሙት ደግሞ በፌደሬሽን ምክር ቤቱ የስራ ቆይታ አምስት ዓመት ድረስ ነው፡፡ እንደዚሁም በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የተሾሙት ደግሞ እንደ ፕሬዚዳንቱ የስልጣን ቆይታ ጊዜ ስድስት ዓመት ነው፡፡  ነገር ግን የጉባዔው አባላት የስራ ዘመን በጊዜ መገደቡ በሥራቸው ላይ ለሚኖራቸው ነጻነት (independence) የራሱ የሆነ ጎጂ ጎን ይኖረዋል፡፡

ሌላው የጉባዔው አባላት አመራረጥን በተመለከተ የስራ ልምድ፣ ዕውቀት፣ እድሜ የመሳሰለው ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባዋል፡፡ አብዛኞቹ የጉባዔው አባላት የሕግ ባለሞያዎች ቢሆኑም ከፌደሬሽን ምክር ቤት ተመርጠው የሚመጡት ሦስት አባላት ግን በሕጉ ላይ የሕግ ባለሞያ መሆን አለባቸው ስለማይል ባለሞያዎች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡

ይልቁንም በፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ሕገ-መንግሥት ሕግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሰነድ ስለሆነ መተርጎም ያለበት በሕግ ባለሞያዎች ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ሰዎች ጭምር ነው የሚል አቋም ቢኖርም የጉባዔው አባላት ከማንም ተጽእኖ ገለልተኛ ሆነው ሊሰሩ የሚገባቸው በመሆኑ በዚህ ረገድ የተቋሙን ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡

የአጣሪ ጉባዔው አባላት ከኃላፊነት ስለሚነሱበት ሥርዓት በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ 19/3 በተዘረዘሩት ምክንያቶች ከዋና ሰብሳቢውና ከምክትል ሰብሳቢው በቀር ሌሎች አባላት ከአባልነታቸው ሊነሱ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ሰብሳቢውና ምክትል ሰብሳቢው የዲሰፕሊን ጉድለት ወይም የስራ ላይ ብቃት ማነስ ቢያሳዩ እንዴት ከኃላፊነት ሊነሱ እንደሚችሉ ግልጽ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የጉባዔው አባላት ከባለጉዳዩ ጋር ዝምድና ቢኖራቸው ወይም ጉዳዩን ቀደም ሲል በሽምግልና ወይም በእርቅ አይተው ቢሆን መልሰው በጉባዔው ላይ ጉዳዩን ማየት ይገባቸዋል? ወይስ አይገባቸውም? የሚለውን አዋጁ ምንም መልስ አይሰጥም፡፡

በአጠቃላይ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከአዋጁ ጀምሮ አተገባበሩና በአጠቃላይ አደረጃጀቱንም በተመለከተ በርካታ ችግሮችና ጉድለቶች ያሉበት በመሆኑ ብዙ ማሻሻያዎችና ማስተካከያዎች ሊደረጉለት ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ሲነሳ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ውሳኔ የመወሰን እንደዚሁም የውሳኔ ሐሳብ ለፌደሬሽን ምክር ቤት በመስጠት ረገድ ትልቅ ሚና አለው፡፡ በተለይም በሕገ-መንግስቱ የተረጋገጡ የዜጎችን መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶችን በሚመለከት መብታቸው እንዳይጓደል  ለማስጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡

ነገር ግን ከላይ በጽሑፉ በዝርዝር ለማየት እንደተሞከረው ጉባዔው ስልጣንና ተግባሩን በሚገባ የሚወጣበት አስተማማኝ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እና የተስተካከለ ተቋማዊ አደረጃጀት የለውም፡፡ ስለሆነም በአዋጁ ላይ መሠረታዊ የሆኑ በርካታ ማሻሻያና ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም በቅድሚያ በጊዜያዊነት ሊወሰድ የሚገባው ማስተካከያ አሁን በስራ ላይ ያለውን የአጣሪ ጉባዔውን አዋጅ ጉድለቶችን በቂ ጥናትና ምርምር አድርጎ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ጉባዔው ስራውን የሚመራበትን መመሪያ ከአዋጁ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማሻሻያ በጊዜያዊነት ሊወሰድ የሚገባው ነው፡፡

በቀጣይነት ግን በሕገ-መንግስቱ ላይ አስፈላጊውን ጥናትና ምርምር እንዲሁም የሌሎችን ሐገራት ልምድ በመውሰድ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ በማድረግ የፌደሬሽን ምክር ቤት እና የአጣሪ ጉባዔውን ስልጣን በማስቀረት የሕገ-መንግሰት ትርጉም በልዩ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤት እንዲሰጥ ቢደረግ የተሻለ ነው፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ሁሉም መንግስታዊ አካላት ሕገ-መንግስቱ ላይ የተደነገጉትን  መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶችን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ስላለባቸው መደበኛ ፍርድ ቤቶችም ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም የተወሰነ ስልጣን እንዲኖራቸው በማድረግ ሐገሪቱ የተቀበለቻቸውን ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋትንና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሠረት ባደረገ መልኩ ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም እንዲሰጡ ቢደረግ ለዜጎች መብት መጠበቅና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓተ-መንግሥት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

 

{phocadownload view=file|id=1855|text=Download this Article with full citation|target=s}

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የንግድ እቃን ማከማቸት፣ መደበቅ፣ ዋጋ ጨምሮ መሸጥ እና የኮረና ወረርሽኝ ከኢት...
የኮቪድ 19 ወረርሸኝና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 19 July 2024