Font size: +
11 minutes reading time (2268 words)

የሰበር ዓላማ ወጥነትን ማስፈን ወይስ ሕገ-ወጥነትን ማስፋፋት?

ጊዜው እ.ኤ.አ 1954 ነው፡፡ ለአለም ሀገራት የዲሞክራሲ አርአያና መምህር ነኝ ብላ በምትደሰኩር በአሜሪካ ሀገር ነጭና ጥቁር ተማሪ በአንድ ላይ አይማርም ነበር አሉ፤ ምክንያቱም ጥቁር ተማሪ ከነጭ ተማሪ ጋር በአንድ ላይ እንዲማር መፍቀድ ማለት በነጭ ተማሪዎች ሞራልና ክብር መቀለድ ነው ብላ ታምን ነበር፤ አሜሪካ፡፡ በመሆኑም ጥቁሮችና ነጮች ተለያይተው ይማሩ ነበር ማለት ነው፡፡ በዚሁ አይን ያወጣ አድልዎ የተበሳጨው ብራውን የተባለው ግለሰብ በአሜሪካ ሀገር የካንሳስ ክልል የትምህርት ጉዳይ ቦርድን በፍርድ ቤት ገተረው፡፡ ሚስተር ብራውን ለጥቁሮች ሽንጡን ገትሮ ከተከራከረ በኃላ ጥቁሮችን አንገት የሚያቀና ፍርድ አስፈረደ፡፡ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥቁርና ነጭ ተማሪዎች ተለያይተው እንዲማሩ ማድረግ የሰው ልጆች በተፈጥሮ እኩል ሆኖው የመፈጠር መብትን የሚቃረን በተለይም ደግሞ የጥቁሮች ክብርና ሞራል የሚነካ እኩል የትምህርት እድል የሚነፍግ ህገ ወጥ ድርጊት በመሆኑ ከተፈጥሮ ሕግና የአሜሪካ ህገ መንግስት ጋር የሚጣረስ ነው ሲል ለሰው ልጆች እኩልነት የሚያረጋግጥ ፍርድ ሰጠ፡፡ ጥቁሮች ከነጮች ጋር ያለአድልዎና ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩል የትምህርት እድል የማግኘትና የመማር መብት አላቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ተደረሰ፡፡ በዚሁ ውሳኔ የተበሳጨው "ጆርጅያ ኩሪዬር" የተባለ ጋዜጣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ዳኞችን እንዲህ ሲል ገለፃቸው፡፡

“No man knows today what his rights are in this country. No man today has any liberties left. His rights and his liberties are in the laps of the nine crazy men who sit on the Supreme Court bench. And the lord only knows what these crazy men will do next. Today they are most dangerous tyrants that ever existed. Like Hitler, Mussolini, and the other modern day tyrants, they are mentally deranged. They are crazed with a desire to serve a minority for political purposes. Their insanity has made them unscrupulous in the methods they have employed to do the bidding of this minority. They are mentally deranged tyrants ruling as unscrupulously as any tyrant in all of history. The members of this court must be curbed or they must be removed from the bench.”

ትችቱ ወደ አማርኛ ስንመልሰው በዚች ሀገር መብቱን እና ነፃነቱን የሚያውቅ ሰው የለም፡፡ ነፃነቱንና መብቱን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንበር ቁጭ ባሉ በእነዚህ  ዘጠኝ ያበዱ ዳኞች እጅ ላይ ነው፤በቀጣይም እነዚህ እብድ ዳኞች የሚሰሩት ነገር ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ አሁን በዘመናችን አይተነው በማናውቅ ሁኔታ እነዚህ ዳኞች አደገኛ አምባገነኖች ናቸው፤እንደ እነ ሂትለር፣ሙሶሎኒና ሌሎች ዘመናዊ አምባገነኖች በጭካኔ ያበዱ ናቸው፤ለፖሊቲካ አላማ ሲባል አናሳ ማህበረሰብን ለማገልገል አብደዋል፡፡ እብደታቸውን አናሳውን ለማገልገል ይሉኝታ እንኳን ሊገድበው አልቻለም፤እነዚህ ሰዎች ሊወገዱ ይገባል ለማለት ነው፡፡ (ትርጉም የራሴ)

እኔ ደግሞ እላለሁኝ፡፡ ያበዱት ዳኞቹ ሳይሆን ጋዜጣውን ያወጣው ፀኃፊ ራሱ ነው፡፡ ይህ ጋዜጣ በወቅቱ ይዞት የወጣ ትችት ብሽቅ እና በዘረኝነት የተነዳ ከአንድ ዲሞክራሲያዊት ሀገር ፈፅሞ የማይጠበቅ ነው፡፡ የእብደት እብደት፡፡ ይህ ማለት ከፍትህ እና ከእኩልነት አንፃር የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ከትክክልም በላይ ነበር፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን ይህ ፅሁፍ ጎርጉሬ ወደዚህ ያመጣሁበት ዋና አላማ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ለመተቸትም ለማድነቅም አይደለም፡፡ ነገር ግን የአንድ ሀገር ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ በአወንታዊም በአሉታዊም ምን ያህል በሰዎች ላይ ተፅእኖ መፍጠር እንደሚችል ለማሳየት ስለፈለግኩኝ ነው፡፡ በአንድ ሀገር የፍትህ የመጨረሻ ስፍራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ እንደየሀገራቱ የፍትህ ሥርዓት አቀራረፅና የፍርድ ቤቶች አወቃቀር የሚለያይ ቢሆንም የአንድ ሀገር ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመጀመርያ ደረጃ ፣በይግባኝ እንዲሁም በሰበር ሰልጣን አይቶና መርምሮ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ ወይም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የስልጣኑ መነሻ ምንም ይሁን ምን ይህ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት ይኖረዋል፡፡

በመሆኑም ማንኛውም ሰው በስር ፍርድ ቤቶች ሂወቱን እንዲያጣ ሲወሰንበት ሂወቱን ለማትረፍ ከሞት ጋር አንገት ለአንገት ትግል ገጥሞ ለመጨረሻ ጊዜ አቤት የሚልበት ቦታ ጠቅላይ ሚኒስተር  ወይም ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት እንደማይሆን ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡ “የ ፍትህ ያለህ” ብሎ የሚሄድበት የመጨረሻ ቦታው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡ አለአግባብ ንብረቱን የተነጠቀ ሰው የንብረት መብቱን የሚያስከብርበት፤ሊገደል አፋፍ ላይ ያለ ሰው ሂወቱን ሊያስምልሰበት፤ባርያ ነህ፣ከሰው በታች ነህ የሚል ዘመቻ ተከፍቶበት በአድልዎ ሲሰቃይ የነበረ ሰው ሁሉ ባርነቱን እንዳይቀጥል ወይም ነፃ እንዲወጣ መጠየቅ የሚችለው የአንድ ሀገር ኮንግረስን፣ፌደረሽን ምክር ቤትን ወይም ፓርላማን አይደለም፡፡ በአጭሩ የመጨረሻ የፍርድ ደወል የሚገኘው በመጀመርያ፣ በይግባኝ ወይም በሰበር ስልጣኑ ለማየት በሚሰየምበት በዚሁ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው፡፡

በብዙ የአለም ሀገራት በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጡ ውሳኔዎችን በማስተካከል ወጥነትና እኩል የህጎች ተፈፃሚነት እንዲኖር የሚሰራ የሰበር ሰሚ ችሎት ሲያቋቁሙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ሰበር የሚለው ቃል ካሳሲዮን ከሚለው የፈረንሰይኛ ቃል የመጣ ሆኖ ቀጥተኛ ትርጉሙም መሰበር ማለት ነው፡፡ መሰበር/ሰበር ከቃሉ ራሱ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ጉዳይ በሕግ ስልጣን በተሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ሰጪ አካል የመጨረሻ ፍርድ ተሰጥቶ ከተዘጋና ካበቃለት በኃላ ውሳኔው መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈፅሞበታል ተብሎ ውሳኔው እንዲሰበር በመጠየቅ አቤቱታ የሚቀርብበት ስነ ስርአታዊ ሂደት ነው፡፡ የሰበር ሥርዓት የተጀመረው እንደ ኢሮፓውያን አቆጣጠር በ 1960 አከባቢ ሲሆን መደበኛ የይግባኝ መጠየቂያ(Le Cour de Cassation) ሳይሆን የተወሰኑ ጉዳዮች በመጨረሻ ፍርድ ውሳኔው የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል ብሎ ሲያምንበት ብቻ ይህን ጉዳይ ለማከናወን ስልጠን የተሰጠው አካል ተቀብሎ የሚሰማ ነበር፡፡

የሰበር ባሕርይ በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት

በሰበር ችሎት የተሰጠ ማንኛውም አይነት ውሳኔ ውጤቱ ምንድን ነው? ኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት የሚከተሉ የአለም አገራት በቀደምት ውሳኔዎች መርጋት (Stare Decisis) ሥርዓት የሚከተሉ ሲሆን ይህ ማለት በበላይ ፍርድ ቤቶች የተሰጡ ውሳኔዎች የበታች ፍርድ ቤቶች ተቀብለው የመተግበርና የመፈፀም ግዴታ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል የሲቭል ሎው የሕግ ሥርዓት የሚከተሉ ሀገራት የበላይ ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች የበታች ፍርድ ቤቶች እንዲከተሉዋቸው አይገደዱም፡፡

ኢትዮጵያ የምትከተለው የሕግ ሥርዓት ቅይጥነት ባሕርይ ያለው ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የተፃፋ ህጎች ያሏትና በተለይም ደግሞ መሰረታዊ ህጎቿ የሲቭል ሎው የሕግ ሥርዓት ከሚከተሉ ሀገራት የተቀዱ በመሆናቸው በዚሁ ረገድ የሲቭል ሎው የሕግ ሥርዓት ተከታይ ነች ማለት ቢቻልም  በወንጀል ክርክርና ማስረጃ አቀራረብ ረገድ ስንመለከተው ግን ኮመን ሎው የሕግ ሥርዓት ሚዛን የሚደፋ መሆኑን ከተለያዩ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን በመርህ ደረጃ የበታች ፍርድ ቤቶች በበላይ ፍርድ ቤቶች የተሰጡ የቀደምት ውሳኔዎችን የመተግበር ሆነ የመፈፀም ግዴታ የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ፡- በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ከተከራካሪ ወገኖች አንዱ ይግባኝ በመጠየቅ ውሳኔውን ካስገለበጠው ውጤቱ ተፈፃሚነት የሚኖረው በተያዘው ጉዳይ እና በተከራካሪ ወገኖች ብቻ ነው፡፡ የስር ፍርድ ቤቶች በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ ቢሆንም በሌላ ተከራካሪ ወገኖች የሚቀርብ ክርክርን እልባት ለመስጠት ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔና ፍርድ እንዲፈፅሙ ወይም እንደ ማጣቀሻ እንዲገለገሉበት አይገደዱም፡፡ ይህ ማለት  በይግባኝ የተለወጠ ውሳኔ የጎንዮሽ ተፈፃሚነት የለውም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ እንዲፈፀም የሚያስገድድ ሕግ የለም፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት መሰረት የሰበር ሥርዓት ተራ ይግባኝ አይደለም፣በተከራካሪ ወገኖች የመብት ደረጃ ብቻ ታጥሮ የሚቀርም አይደለም፡፡ ከላይ እንደተገለፀው የሰበር ሥርዓት የህጋዊነት መርህ፣የህጎች አፈፃፀም አንድነትና ወጥነት በማረጋገጥ ሕግን የማቅናትና ፍትህን የማስፈን ስራ የሚከናወንበት የመጨረሻ የመፍትሄ መንገድ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ የሰበር ሥርዓት እንደ አንድ አዲስና ተጨማሪ የይግባኝ ደረጃ እንዲሁም የተከራካሪ ወገኖችን መብት ማስከበርያ ተደርጎ የሚታይ ሳይሆን የህጎች እኩል ተፈፃሚነት የሚመረመርበት በመሆኑ የመጨረሻ ፍትህ ሰጪ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጥ ማንኛውም አይነት የሕግ ትርጉም በኢትዮጵያ በሚገኙ በማናቸውም ፍርድ ቤቶች ላይ ተፈፃሚነት ስላለው በዚሁ ረገድ የኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት በቀደምት ውሳኔዎች መርጋት የሚከተል ነው ማለት ይቻላል፡፡

ነገር ግን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሕግን ከመተርጎም ወጥቶ ሕግን ወደ ማውጣት ስራ ላይ ከተሰማራ  የቁጥጥርና ሚዛናዊነት መርህን(Principle of Check and Balance) የሚንድ ኢ-ህገ መንግስታዊ ተግባር በመሆኑ በፌደረሽን ምክርቤት የህገ-መንግስት ትርጉም መሰረት ሊሻር የሚችል መሆኑን እንደተጠበቀ ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ ፅሁፍ ወሰን (Delimitation) የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ የሚያስነሳ ምክንያት ሳይኖራቸው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረት አፈፃፀማቸውን በመጠባበቅ ላይ በሚገኙ ውሳኔዎችን ብቻ የሚመለከት መሆኑን አንባቢው እንዲገነዘብ እፈልጋለሁኝ፡፡   

 የሰበር ሥርዓት በኢፌድሪ ህገ መንግሰት አንቀፅ 80(3)(ሀ) ስር ሽፋን ያገኘ ፅንሰ ሀሳብ ሲሆን በዚሁ መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም የሰበር ችሎት የማየት ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ይህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ዝርዝሩ በሌላ ሕግ እንደሚወሰን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 10 እና ይህን አዋጅ ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀፅ 10(4) ስር በግልፅ እንደተመለከተው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልል ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ በሀገሪቷ ክፍል በሚገኙ ማናቸውንም የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡዋቸውን ማንኛውም አይነት ውሳኔዎች  መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለባቸው መሆኑን ከተረጋገጠ በሰበር አይቶ የማረምና የማስተካከል ስልጣን አለው፡፡

 በሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰየሙ ዳኞች በልምድ፣በእውቀትና በክህሎት የተሻሉ በመሆናቸው በሕግ አተረጓጎም ረገድ  ስህተት ይሰራሉ ተብሎ ሳይሆን ስህተትን ያርማሉ ተብለው የሚታመንባቸው ነው፤የሚሰጡዋቸው ውሳኔዎችም በተናጠል ሳይሆን በጋራና በውይይት በመሆኑ የተሻለና ለሁሉም የሚያሳምን የሕግ ትርጉም ይሰጣሉ ተብሎ ይታመናል። ስለሆነም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከአምስት ባላነሱ ዳኞች ተሰይመውበት የሰጠው ማንኛውም አይነት የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌደራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ የአስገዳጅነት ባሕርይይ ያለው መሆኑን የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን ለማሻሻል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 454/97 በግልፅ ደንግጓል፡፡ በኢትዮጵያ የዳኝነት ሰርአት ሰበር የሚባለውም ይህን ነው፡፡ ነገር ግን የሀገራችን ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች ተቀራራቢ እና ወጥነት ያላቸውን የህጎች ተፈፃሚነት እንዲኖር እየሰራ ነው የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱ አይደለም እላለሁኝ፡፡ ችግሩ ከሕግ የሚመነጭ ሆኖ በተግባርም የተዘበራረቀ፣ወጥነት የሌለው፣የእኩልነት መብትን ጥያቄ ውስጥ የሚከት በአንድ ጭብጥ ላይ በየጊዜው እንደ እስስት የሚቀያየር ውሳኔ ሲሰጥ ማየት የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ ስለሆነም  ችግሩ ከተግባር ብቻ የመነጨ ሳይሆን የሕግ ትእዛዝ ያለበት የሚመስል ሕግን የሚንድ ሕግ በመውጣቱም ጭምር ነው፡፡

  • የሕግ መዘውር

የሰበር ሥርዓት መዘርጋቱ በሀገሪቷ ፍርድ ቤቶችና የፍርድ ቤት ስራ የሚሰሩ መሰል ፍርድ ቤቶች በአንድ ጭብጥ የተለያየ ውሳኔ በመስጠት የተዘበራረቀና ወጥነት የሌለው የህጎች ተፈፃሚነት እንዳይኖር በመከላከል ረገድ ሊተካ የማይችል ሚና እንደሚጫወት የሚያስማማን ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የፍርድ ቤቶች አዋጅ ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀፅ 10(4) ስር በግልፅ እንደተመለከተው  ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም ሊሰጥ እንደሚችል ያልተገራና ሊሸከመው የማይችል ስድ ስልጣን ይሰጠዋል፡፡ እንግዲህ ይህ አንቀፅ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ የፍትህ መዛባት፣የሕጎች መናድና መናወጥ በተለይም ደግሞ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ልቅና መረን የለቀቀ የዘፈቀደ አካሄድ ከበሮ መቺና የምስራች ነጋሪ ድንጋጌ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ሕግ አውጪ ቀደም ሲል ያወጣውን ሕግ መሻር እና ማሻሻል እንደሚችል ሁሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ቀደም ሲል የሰጠውን ውሳኔ እንዲገለብጠው፣እንዲያሻሽለው ወይም እንዲሽረው ከሕግ አውጪ አካል ጋር እኩልና የትይዩ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በመሰረቱ ይህ አይነት የትይዩ ስልጣን በተለይም ደግሞ ከዚህ ቀደም የሰጠውን የሕግ ትርጉም ሙሉ በሙሉ በመቀየር ሌላ አዲስ ትርጉም እንዲሰጥበት መፍቀድ ማለት ሕግ እንዲያወጣ ከመፍቀድ የሚተናነስ ስልጣን አይሆንም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሰበር ሰሚ ችሎት በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ የተለየ ትርጉም መስጠት ይችላል ከተባለ ወጥነትን እያሰፈነ ነው ወይስ ሕገ-ወጥነትን እያስፋፋ ነው የሚለው ጥያቄ ለመመለስ እምብዛም የሕግ ፍልስፍና የሚጠይቅ አይደለም፡፡ በመሰረቱ በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ የተለየ ትርጉም ወይም ውሳኔ ይሰጣል ሲባል ካለምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ነው፤ለምን አለማ እንደሆነም ድንጋጌው አያስቀምጥም፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎት በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ የተለየ ትርጉም እንዲሰጥ ካለምንም አይነት ገደብ ስልጣን ሲሰጠው በአላማ ያልተገደበ ካለመሆኑም በላይ የጊዜ ገደብ ራሱ አላስቀመጠም፡፡ ስለሆነም በየቀኑ በአንድ ጭብጥ ላይ የተለያየ ትርጉም በመስጠት የህጎች እኩል ተፈፃሚነትና ወጥነትን መናድ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ የተለያየ ትርጉም የመስጠት ተፈጥሮአዊ  ኃይልም አለው ማለት ነው፡፡ በተግባር እየታየ ያለውም ይኸው ነው፡፡

ከአላማ አንፃር ስንመለከተውም በአንድ ተመሳሳይ ጭብጥ የተለያየ ትርጉም መስጠት የሚችለው ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ ስለሚረዳው ነው?ለርትእ ሲባል ነው? ተቀራራቢ ወይም ወጥነት ያለው የህጎች ተፈፃሚነት ለማስፈን ነው?ለሙስና እና ለግል ጥቅም አላማ ነው? ከቶ ግልፅ አይደለም፡፡ ዳኞች የሚመሩበት ሕግ ግልፅና ግልፅ አላማ ያነገበ መሆን አለበት፡፡ ህጋችን በደፈናው የሰበር ሰሚ ችሎት ዳኞች በአንድ ተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም መስጠት ይችላሉ በማለት ለሌብነትና፣ለአድሎዎነት ብሎም ለሙስና በር የሚከፍት አደገኛ ድንጋጌ መሆኑን ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሰኞ የሰጠው ውሳኔን ማክሰኞ የሚሽር ዳኛ እንዲበራከት ጥሩንባ የሚነፋ ድንጋጌ ነው፤ድንጋጌው አስገራሚ ነው፡፡ በሕግ ሳይሆን በግል ፍላጎት የሚጋለብ የፍትህ ሥርዓት እንዳይኖር የምንከላከልበት የሕግ ተቋም ከመገንባት ይልቅ በዳኞች ፈላጭ ቆራጭነት የሚሽከረከር የፍትህ ሥርዓት መገንባት አደጋው ከፍተኛ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህገ መንግስታዊ እውቅና ያገኘ የእኩልነት መብትን የሚያናውጥ ነው፡፡ ለምሳሌ:–በአንድ ወቅት አንድ ተከራካሪ ወገን ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከዚህ ቀደም የሕግ ትርጉም የሰጠበትን ጨብጥ አንስቶ ቢከራከርም ችሎቱ ራሱ ከዚህ ቀደም በሰጠው ውሳኔ እንደማይገደድና ይህን ከተከራካሪ ወገን የተነሳ ክርክር ተቀባይነት እንደሌለው ወስኗል፡፡ ራስሽ ታመጪው ራስሽ ታሮጪው ማለት እንዲህ ነው እንግዲህ፡፡

ከተግባር አንፃር

ለማሳያ ያህል ሰበር ሰሚ ችሎቱ በራሱ ያመነባቸውን የተወሰኑ ተቃርኖዎችን እንመልከት፡፡

 

  • ማሳያ አንድ፡-ስለ ዳግም ዳኝነት በማስመልከት የተሰጠ ውሳኔ

 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 16624 መሰረት ጉዳዩን በመጀመርያ ደረጃ ተቀብሎ የመጨረሻ ውሳኔ በሰጠው የስር ፍርድ ቤት ዳግም ዳኝነት እንዲታይለት ማመልከቻ ያቀረበ ሰው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 6(1) መሰረት ተቀባይነት የሚያገኘው የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም ወደ በላይ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ ከማቅረቡ በፊት ብቻ ሆኖ ይግባኝ ካቀረበ በኃላ ከሆነ ግን ተቀባይነት አይኖረውም የሚል አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡  

በሌላ በኩል ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 43821  የሰጠውን ውሳኔ ስንመለከት ሀሰተኛ ማስረጃ መሰረት በማድረግ የመጨረሻ ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ ይግባኝ ተጠይቆበት በክርክር ላይ እያለ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሃሰተኛ ማስረጃውን ተመርኩዞ የሰጠው ውሳኔ እንደነበር የሚያረጋግጥ እውነተኛ ማስረጃ ቢገኝ ይግባኙን እንዲቋረጥ ተደርጎ ዳግም ዳኝነት እንዲታይ ማመልከት እንደሚቻል እና ፍርድ ቤቱም ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ጉዳዩን ተቀብሎ ዳግም ማየት እንዳለበት ሌላ አስገዳጅ ውሳኔ ወስኗል፡፡

 

  • ማሳያ ሁለት፡- ይርጋን በማስመልከት የሰጠው ውሳኔ

 

ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 16648 በሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ መሰረት ማንኛውም ሰው ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን ስልጣን ወደሌለው የዳኝነት አካል ክስ ቢያቀርብ የይርጋ ጊዜ መቆጠርን አያቋርጠውም በማለት የወሰነ ሲሆን በሌላ በኩል  ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 36730 በሰጠው ውሳኔ መሰረት ስልጣን ለሌለው የዳኝነት አካል ክስ ማቅረብና ክርክር ማካሄድ የይርጋ ጊዜን የሚያቋርጥ እንደሆነ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡

 

  • ማሳያ ሶስት፡- ሀሰተኛ ሰነድን በመገልገል የሚፈፀሙ የማታለል ወንጀሎች በማስመልከት የሰጠው ውሳኔ

 

ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 104715 መሰረት ስለተደራራቢ ወንጀሎችን የሕግ ትርጉም ሲሰጥ አንድ ወንጀል ከመስራት የሚመነጩ የተለያዩ ድርጊቶች አንድ ወንጀል ከመስራት የሚመነጩ ናቸው በማለት ተጠቃልለው ሊታዩ እንደማይገባ በመግለፅ ማንኛውም ሰው ሀሰተኛ የፍቺ ምስክር ወረቀት ላሰራልህ በማለት የገንዘብ ጥቅምን ተቀብሎ ሌላ ሰውን ያታለለ እንደሆነ  በኢፌድሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 699 መሰረት በሀሰተኛ ሰነድ መገልገልና በማታለል ወንጀል ሊጠየቅ እንደሚችል አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 104637 በወሰነው መሰረት ማንኛውም ሰው የማታለል ወንጀልን ለመፈፀም ሲል የሀሰት ሰነድ የተገለገለ እንደሆነ የመጨረሻ ግቡን የማታለል ወንጀል ለመፈፀም ሲል የሀሰት ሰነዱን በመገልገሉ በተደራራቢ ወንጀል ሊጠየቅ አይችልም በማለት ቀደም ሲል የሰጠውን ውሳኔ በራሱ ሽሮታል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በዚሁ ጉዳይ ለሶስተኛ ጊዜ በሰጠው ውሳኔ መሰረት መጀመርያ ወደ ሰጠው ውሳኔ ተመልሶ አዲስ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ችሎቱ ሀሰተኛ ሰነድን በመገልገል የሚፈፀም የማታለል ወንጀል በተደራራቢ የሚያስቀጣ የወንጀል ጥፋት እንደሆነ የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ አንቀፅ 699 በመጥቀስ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ይህ ውሳኔ በቅርቡ የተሰጠና ያልታተመ ሲሆን ለጊዜው መዝገብ ቁጥሩን ላስታውሰው ወይም ላገኘው አልቻልኩም፡፡

ይህ ሶስተኛ ማሳያ ከሌሎች ውሳኔዎች የባሰ እና የተለየ ነው፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሶስት ጊዜ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የተሰጠውን የተሳሳተ ትርጉም በመቀየር በአንድ ጭብጥ ላይ የተለየ ትርጉም መስጠት ችግር ላይኖረው ይችላል፤ስህተትን አንዴ ከታረመ በኃላ እንደገና ዙረህ ወደ ሌላ ሶስተኛ ስህትት ውስጥ መግባት ግን ሕገ-ወጥነት ነው፡፡ በስህተት ዙርያ ሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ መሽከርከር ከሰበር ሰሚ ችሎት ፈፅሞ የማይጠበቅ ነው፡፡

መደምደሚያ

ሰበር ሰሚ ችሎት የሕግ ስህተትን መስበር ትቶ ፍትህን እየሰበረ ነው፡፡ የሕግ ስህተትን ይሰብርልናል ብለን በህገ መንግስት መሰረት ያቋቋምነው ሰበር ሰሚ ችሎት ፍትህን እየሰበረ ሲውል ማየት ኢ-ፍትኃዊም ኢ–ህጋዊም ነው፡፡ በመሰረቱ ዳኞች ስልጣናቸውን በአግባቡ ሊያውቁና ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውስጥ በአምስት ወይም ሰባት ወንበሮች ላይ ቁጭ ብለው የሚውሉት ዳኞች መሰረታዊ የሕግ ስህተትን ለማረም እንጂ ወጥነት የሌለው፣እኩልነትን የሚንድ፣ሕግን የሚያናውጥና ፍትህን የሚያጣምም ፍርድ ለመስጠት አይደለም፡፡ ችሎቱ ሕግ አውጪ ሳይሆን ሕግ ተርጓሚ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በየቀኑ በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ትርጉሞች እንዲሰጥ ልጓም አልባ ስልጣን የሰጠው አዋጅ ሊሻሻል ይገባል፤አዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀፅ 10(4)፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ስለወለድ እና የወለድ ወለድ አስተሳሰብ ደንቦች በጨረፍታ
በኢትዮጵያ የሲቪክ ምህዳር መብቶች ጥበቃ እና የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 03 October 2024