Font size: +
7 minutes reading time (1461 words)

‘ኮማንድ ፖስት’ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተሰጠ ልዋጭ ስም?

በሀገራችን ኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ሲከሰት መንግሥት በሕግ የተቀመጠለትን መደበኛውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም ፈንታ በስም የተለየ ነገር ግን በአተገባበር ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተመሳሳይነት ያለውን የሕግ ማስከበር መንገድ ‘ኮማንድ ፖስት’ በሚል ስያሜ እያዘወተረ እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ ከዚህም በመነሳት ህብረተሰቡም ይህንኑ ኮማንድ ፖስት የተባለውን ስያሜ እኩል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር አገናኝቶ ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ኮማንድ ፖስት መንግሥት በመደበኛ የሕግ ማስከበር መንገድ ሕግን ማስከበር ሲቸገር እየተጠቀመው የሚገኝና በተግባርም የግለሰቦችን መብት የሚገድቡ ክልከላዎችን ጭምር በማውጣት በተግባር ተጠያቂ እያደረገ በመስተዋሉ ነው፡፡ ብዙን ጊዜ ይህንን አዋጅ ሲያውጅ የሚስተዋለው በፌደራል ደረጃ የተዋቀረ ‘ብሔራዊ የፀጥታ ም/ቤት’ የሚባል አካል እነደሆነ ይደመጣል፡፡ ይህ አካል አዋጁን ያውጅ ዘንድ በሕገ-መንግሥቱ ሥልጣን የተሰጠው አካል እንዳይደለ መረዳትም ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል እየተዘወተረ የመጣው የክልሎች የጸጥታ መደፍረስን ምክንያት በማድረግ ‘ኮማንድ ፖስት’ እያወጁ የግለሰቦችን መብት መገደብ በብዛት እየተስተዋለ የመጣ ሲሆን ይህ ስልጣን በህገ-መንግስቱ ለነርሱ ያልተሰጠ ሆኖ ሳለ ይኸው ‘ኮማንድ ፖስት’ የተባለው ሲያሜ ምቹ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው እንመለከታለን፡፡

በዚህ ጽሑፍ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምንነት፤ ለምን እንደሚታወጅ፤ ማን እንደሚያውጀው እና ሲታወጅም ይሁን ከታወጀ በኃላ አዋጁንና አፈፃፀሙን በሚመለከት ሊሟሉ የሚገባቸው ይዘታዊም ሆኑ ሥነ-ሥርዓታዊ የሕግ መጠይቆችን እንመለከታለን፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘንም ከላይ ያተትነው ኮማንድ ፖስት የተባለው አዋጅን ከመደበኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጽንሰ ሃሳብ ጋር አገናኝተን እንመለከትና በዚሁ ኢ-መደበኛ አዋጅ ያሉትን ችግሮች ነቅሰን በማውጣት መሆን አለበት የምንላቸውን መፍትሔዎች እናስቀምጣለን፡፡

መግቢያ

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማለት መንግሥት በመደበኛ ሕግና የሕግ አስከባሪ አካላት ሕግን የማስከበር አቅሙ ጥያቄ ውስጥ ሲገባ የሚታወጅ የግለሰቦችን መብት የመገደቢያና የተፈጠረን ችግርን ለመፍታት የሚሰራበት የሕግ ስሪት መንገድ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች ምንጫቸው ተፈጥሮአዊ (ለምሳሌ፡- የመሬት መደርመስ /መንሸራተት/፤ ያልተጠበቀ ጎርፍ እና የህዘብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተላላፊ በሽታዎች መከሰት ወይም ሰው ሰራሽ (ለምሳሌ፡- የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፤ አመጽ፤ መፈንቅለ መንግሥትና የመሳሰሉት….) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ይህ አዋጅ በባህሪው በህገ መንግሥትና ሀገሪቷ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፋዊም ሆነ አህጉራዊ ሰብዓዊ መብት ሕግጋት ሰነዶች የተረጋገጡ መብቶችን የሚገድብ ነው፡፡ በመሰረቱ ይህ አዋጅ በሕግ መሰረት የሚያውጀውን መንግሥት ጉልበት ለጊዜው የሚያፈረጥም በተቃራኒው ደግሞ ኀብረተሰቡን ‘መብቴ ነው’ በሚል ያደርግ ከነበረው እንቅስቃሴው የተፈቀደለለትንና የተከለለትን መብት በመለየት እነዲንቀሳቀስ የሚያስገድድ እግዶቹን ተላልፎ ሲገኝም የሚቀጣ በጊዜያዊነት መብትን ለመገደብ የሚወጣ ጊዜያዊ አዋጅ መሆኑን እንረዳለን፡፡ አዋጁን የማወጅ ስልጣንም በሀገሪቷ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኩል ወይም የዚህን ም/ቤት ይሁንታ በኃላ ላይ የሚጠየቅ ሆኖ በሕግ አስፈፃሚው አካል ሊታወጅ ይችላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓለም ላይ የሀገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅን ልምድ ስንመለከት ባብዛኛው ሶስተኛው የዓለም ሀገራት የሚባሉና የዴሞክራሲ ባህላቸውም ኃላ ቀር የሚባሉ ሀገራት በብዛት እንደሚጠቀሙበት የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ የሀገራት ግዴታ የማክበር፤ የማስከበር እና የማሟላት በመሆኑ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶችን በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ ብዙን ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እንደ መጨረሻ አማራጭ (last resort) እንዲጠቀሙ ይጠበቃል፡፡ አዋጁ ሲታወጅ እንዲሁ በአቦሰጥ የሚታወጅ ሳይሆን ስለ ጉዳዩ በሚያትት የህገ-መንግሥት ክፍል የተቀመጡ አዋጁን የሚመሩ ይዘታዊ (substantive) እና ሥነ-ሥርአታዊ (procedural) የሕግ ማዕቀፎች የሚከተል ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ በዴሞክራሲ በዳበሩ ማህበረሰቦች ዘንድ ባለው ልምድ እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በጣልያኗ የሲራኩሳ ከተማ በ1984 እ.ኤ.አ የተሰባሰቡ የሕግ ሊኀቃን ገደቦቹ ሲጣሉ ሊሟሉ በሚገባቸው ነገሮች ላይ የሚከተሉትን ቅደም ተከተሎችን ለተሻለ የሰብዓዊ መብት አተገባበር ሀገራት እንዲጠቀሙ አስቀምጠው እናገኛለን፡፡ (Siracusa Principles on the Limitation and Derogation of Provisions in the International Covenant on Civil and Political Rights Annex, UN Doc E/CN.4/1984/4 (1984) ይመልከቱ))፡፡ እነዚህ መጠይቆች ቢተነተኑ ጥልቅ ሲሆኑ ለጽሁፋችን ግብዓት በሚሆን መልኩ ብቻ እንደሚከተለው አሳጥረን እንመለከታለን፡፡ ይኸውም፡- 1) የሚገደበው መብት በግልፅ በሕግ ሊታገድ ይገባል፡፡ ይህም ማለት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚታወጀው አዋጅ የተከለከለውና ያልተከለከለው ተለይቶ ሊቀመጥ ይገባል፡፡ ይህም (requirement of legality) ተብሎ ይጠራል፡፡ 2) የገደቡ መጣል አስገዳጅና አሳማኝ የሆኑ ምክንያቶችን መያዝ አለበት፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለተባለ ብቻ የግለሰቦች መብት በምክንያት ሳይደገፍ እንዲሁ ሊገደብ አይገባም፡፡ ይህም (requirement of legitimate aim) ተብሎ ይጠራል፡፡ 3) ክልከላውን ተከትሎ የሚጣለው ገደብ ተመጣጣኝ የሆነና ከላይ የተገለፀውን አስገዳጅና አሳማኝ ምክንያቶችን ብቻ ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆን አለበት ይህም (test of proportionality) የምንለው ነው:: 4) የሚጣለው ገደብ የተፈጠረውን ችግር የሚመለከት አስፈላጊ የሆነው ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ (test of necessity) ነው፡፡ እና 5) ገደቦቹ ያለ አድሎ የተጣሉና የሚፈጸሙ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ (Test of non-discrimination) ብለን የምንገልፀው ነው፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ጊዜ ሰብዓዊ መብቶች ሲገደቡም ሆነ (limitations) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የግለሰቦችን መብት በጊዜያዊነት ሲገደብ (derogations) ሀገራት እነዚህን መጠይቆችን አሟልተው እንዲተገብሩ ይጠበቃሉ፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰብዓዊ መብቶች መገደብ ጊዜያዊ ሲሆን ይህም ኖሮ በማንኛውም ጊዜ (አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ) ወቅትም ቢሆን ፍፁም የማይገደቡ መብቶች እንዳሉ ከዓለም አቀፍ እስከ ሀገር አቀፍ ያሉ ሕግጋት ያስቀምጣሉ፡፡ የዚህ ፅሁፍ ጭብጥ እነዚህን መብቶች ከዓለም አቀፍ እስከ ሀገር ውስጥ ሕግጋት ያላቸውን ልዩነት ማተት ባለመሆኑ በአዋቂ ወግ ልናልፍ እንገደዳለን፡፡ ይሁን እንጂ በንስር ዓይን የኢትዮጵያን ህገ-መንግሥት በገረፍታ ዳሶ ለማለፍ ያህል - ለምሳሌ፡- በኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት መሰረት አንቀፅ 1 (የሀገሪቱ መንግስታዊ ሥያሜ) አንቀፅ 18 (ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ስለ መከልከሉ) አንቀፅ 25 (የእኩልነት መብት) እና አንቀፅ 39 (1) እና (2) (የብሄር ብሄሮችና የህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወስን መብት) በተመለከተ በአስቸኳይ ጊዜ እንኳ ከማይገደቡ መብቶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህ ውስጥ የምናስተውለው የኛ ህገ-መንገስት ከሌሎች ሀገራት ህገ መንግስቶችም ሆነ ሀገሪቱ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያላካተታቸው መብቶች እንዳሉ አንባቢው ልብ ይሏል፡፡

ወደ ጽሁፋችን ፍሬ ነገር ስንገባ በሀገራችን ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁኔታ ስንመለከት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከህገ መንግስቱ አገላለፅ ባፈነገጠ መልኩ የአዋጆቹ ስም ‘በኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ስር’ የሚልና የሚያውጀውም አካል የፀጥታና የደህንነት ም/ቤት የሚባል በአስፈፃሚው የመንግሥት አካል የተደራጀ ም/ቤት ሆኖ እንደሚገኝ እያየን ነው፡፡ ይህም በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 93(1) (ሀ) መሰረት አዋጁን የማወጅ ስልጣን የሀገሪቷን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይሁንታ በኃላ ላይ የሚጠየቅ ሆኖ በሕግ አስፈፃሚው አካል (የሚንስትሮች ም/ቤት) እንደሆነ ህገ-መንግስቱ በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ከላይ የተገለጸው ም/ቤት የሚንስተሮች ም/ቤት ካለመሆኑም ባሻገር በሚንስተሮች ም/ቤት በኩል የተደራጀ እንደሆነ ግን መገመት ይቻላል፡፡ ለዚህም ግምት ማስረጃው በጠቅላይ ሚንስትሩ መመራቱ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ሆኖም ሳለ ግን ህገ-መንግስቱ ቀጥታ የሚንስተሮች ም/ቤት በሚል በግልፅ ማስቀመጡ ያለምክንያት አለመሆኑን የምንረዳው ሆኖ በተግባርም አንዳንዶቹ የዚህ ም/ቤት አባል የሆኑት አካላት የሚንስተሮች ም/ቤት አባል ያልሆኑ ፈፃሚ ባለድረሻዎች እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ ባጠቃላይም በባህሪው በጊዜያዊነትም ቢሆን መንግሥትን ይበልጥ ጉልበታም ባይለስልጣን የሚያደርግ ይህ ስልጣን ቢያንስ ሊታወጅ የሚገባው የሀገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ሕግ የሆነው ህገ-መንግስቱ ባሰለጥነው መሰረት በሚንስተሮች ም/ቤት እንጂ በአስፈፃሚው አካል ፍላጎት በተደራጀ ‘ም/ቤት’ ሊሆን አይሀገባም፡፡ ምክንያቱም ይህ በህገ-መንግሰቱ እንዲህ መሆኑ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተል እና እንደአስፈላጊነቱም የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ያስችለው ዘንድ መሆኑ እሙን ስለሆነ በቀጥታ ስልጣን በግላጭ በተሰጠው አካል በኩል አዋጁ ሊታወጅ ይገባል፡፡

ህገ-መንግሰቱ ሀገሪቱ የፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ስርዓት የምትከተል ሀገር መሆኗን ባከበረ መልኩ ለክልል መንግስታትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ስልጣንን በተወሰነ መልኩ ይሰጣቸዋል፡፡ በመሆኑም የክልል መስተዳድሮች የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ በማለት ያስቀምጣል የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 93 (1) (ለ)፡፡ ከዚህም የምንረዳው ከፀጥታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የማወጅ ስልጣኑ ለፌዴራሉ ሚንስትሮች ም/ቤት ስልጣን ስር የሚያድር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይሁን እንጂ በአመዛኙ ክልሎች ያለ ስልጣናቸው በስራቸው በሚገኙ በተለያዩ የአስተዳደር መዋቅሮች በፀጥታ ምክንያት ኮማንድ ፖስት በሚል ሲያሜ ሲያውጁ ተስተውለዋል፡፡ ለማሳያነትም በደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ በ2008 ዓ/ም በኮንሶ የዞንነት ጥያቄ ምክንያት በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት የክልሉ መንግሥት ኮማንድ ፖስት በሚል ሲያሜ የግለሰቦችን መብት የሚገድብ አዋጅ አውጆ የነበረ ሲሆን በተመሳሳይም በቀድሞው የሰገን ዞን እና በአማሮና በቡርጂ ወረዳዎች ከላይ በተጠቀሰው ሲያሜ ፀጥታን ምክንያት ያደረጉ አዋጆችን ማወጁ ይታወቃል፡፡ ለማሳያነት የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ ተጠቀምን እንጂ በሌሎችም የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች እየተዘወተረ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይም በህገ-መንግስታዊ ቋንቋ ፀጥታን በሚመለከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚችለው የፌዴራሉ ሚንስትሮች ም/ቤት ሲሆን ክልሎች ይህንን ሊያደርጉ እንደማይችሉ እንረዳለን፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ በየከባቢው (በዞኖችና በየወረዳዎቹ) በክልል መንግስታት የሚታወጁ ኮማንድ ፖስቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ እጅግ የሚገርመው ለነዚህ አዋጆች መነሻ ችግሩ የመንግሥት የራሱን ስራ በአግባቡ አለመስራት (የመልካም አስተዳደር ችግሮች) እና የህዝብን ጥያቄ በአግባቡና በሕግ መሰረት አለመመለስ ሆኖ እናገኛለን፡፡ ለዚህም ይመስላል የሚታወጁት አዋጆች በአመዛኙ ችግሮችን የማዳፈን እንጂ የማረምና የማረቅ አቅም የላቸውም የሚሉ ትችቶች በተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ሲሰነዘሩ የሚደመጠው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኮማንድ ፖስት ተቀፅላ መተግበሩ ያላውን ተፅእኖዎችን ስንመለከት፡- ኮማንድ ፖስቶቹ ህገ መንግስቱ ያስቀመጠውን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሊወሰድ የሚገባቸውን መጠይቆች ያላሟላ በመሆኑ የግለሰቦችን መብቶች በእጅጉ የሚጥሱ ተግባራት እንዲፈፀሙ ዕድልን ይፈጥራል፡፡ ለምስሌ በስመ ኮማንድ ፖስት የሚታወጁ አዋጆች የተከለከሉ እና የተፈቀዱ ተግባራት በግልፅ የማይገለፅባቸው፤ በአተገባሩ ላይም የሚኖሩ ግድፈቶችን የሚከታተል መርማሪ ቦርድ የሌለው መሆኑ፤ በኮማንድ ፖስቱ ምክንያት የታሰሩ ሰዎችን ይፋ የማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎችን ኢ-ሰብዓዊነታቸው የማይታወቅበት እና በአፈፃፀሙ የሚታዩትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚከታተል ህጋዊ አካል የሌለው መሆኑ እጅግ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው፡፡ ምንም እንኳ ህገ-መንግስታችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከከለከሉና ያልተከለከሉ ድርጊቶች በተለያዩ ማሰራጭ መንገዶች ለህዝብ ተደራሽ እነዲሆን የሚያውጀውን አካል የሚያስገድድ አንቀፅ ባይኖረውም ኢትዮጵያ ፈራሚ የሆነችበት የዓለም አቀፉ ሲቪል እና ፖለቲካል መብቶች ኮንቨንሽን በአንቀፅ (4) ላይ የማሳወቅ ግዴታን በሀገራት ላይ የሚጥል በመሆኑና በህገ መንግስቱ አንቀፅ 13(2) መሰረት በዚህ መልኩ ተተርጉሞ በሚያውጀው አካል ላይ ግዴታ ሊጣልበት ይገባል፡፡ ነገር ግን በነዚህ ኮማንድ ፖስቶች የሚታወጁ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚገድቡ ክልከላዎች ለህዝቡ ግልፅ ሲደረጉ በአብዛኛው አይስተወሉም፡፡ አይደለም ለመላው የሀገሪቱ ዜጎች ለታወጀበት አካባቢ ስንኳ በአግባቡ እንደማይገለፅ በብዛት ይተቻል፡፡ ይህም አለመሆኑ ግለሰቦች ማድረግ ያለበቸውን ጥንቃቄ ካለማስገንዘቡም በላይ ቅድመ ማስጠንቀቅያን የመስጠትና ጥፋተኛን ባወቀበት የመቅጣት መሰረታዊ የሕግን መርህ የሚጥስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በመሰረቱ በተወሰነ አካባቢ የታወጀ አስቸኳይ አዋጅም ቢሆን ለሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ማሳወቅ እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ምክንያቱም በሌላ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው ዜጋ ህገ-መንግስታዊ የመንቀሳቀስና የመስራት መበቱን ተጠቅሞ ወደዚያ አዋጁ ወደታወጀበት አካባቢ ሊሄድ ስለሚችልና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚደረገውን ነገር የማወቅ መብት ያላቸው ስለሆነ መንግሥት እንዲያሳውቅ ይገደዳል፡፡

በመጨረሻም የዚህ ፅህፍ መደምደሚያ በስመ ኮማንድ ፖሰት የሚደረጉ አዋጆች መደበኛውን የህገ-መንግስቱን ስያሜና እና አንድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያሟላ ይገባዋል በማለት ህገ-መንግስቱ የሚያስቀምጣቸውን መሰረታዊ መጠይቆች በጠበቀ መልኩ ቢሆን የተሻለ ይሆናል የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ህገ-መንግስቱ እነዚህን መሰረታዊ መጠይቆች ያስቀመጠበት ዋናው ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የግለሰቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አላስፈላጊና ተገቢ ባልሆነ መልኩ እንዳይጣሱና የታወጀውም አዋጅ የተፈጠረውን ችግር የመፍታት ዓላማ ብቻ እነዲኖረው የሚያስችል እንዲሆን መሆኑን በመረዳት ተገቢው ዕርምት ሊወሰድ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አዋጁ የዜጎችን መብት መንጠቂያና መደፍጠጫ መሳሪያ መሆኑ የማይቀር ሃቅ ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Effect of Irregularities in Public Contract Awardi...
ወደኋላ ሄዶ ተግባራዊ የሚያደርጉ የታክስና ጉምሩክ ሕግ ድንጋጌዎች ሕገ መንግሥታ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 19 July 2024