በተሻሻለው የኢትዮጲያ የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 1 መሰረት ህጋዊ ጋብቻ በተለያዩ ሰነ-ስረዓቶች ሊፈፀም ይችላል፡፡ እነሱም በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣በሐይማኖት እና በባህል መሰረት የሚፈፀሙ የጋብቻ አይነቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ጋብቻ ከላይ በተጠቀሱት በአንዳቸው ስነ-ስርዓቶች ቢፈፀም እንኳን ውጤቱም አንድ መሆኑን የዚሁ ህግ አንቀፅ 40 ያትታል፡፡ ህጋዊ ጋብቻ በተጋቢዎቹ ላይ ሁለት ዓይነት ውጤት ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው በተጋቢዎች ግለዊ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ውጤት ሲሆን፤ በስሩም የመከባበር ፣ የመተጋገዝና የመደጋገፍ ግዴታ ፣ ቤተሰብን በጋራ የመስተዳደር እና በጋራ አንድ ላይ የመኖር ግዴታዎችን ያቅፋል፡፡ ሁለተኛው ውጤት ደግሞ ጋብቻ በተጋቢዎች ንብረት ላይ የሚኖረው ውጤት ነው፡፡ ይህም ተጋቢዎች  ጋብቻቸውን በሚፈፅሙበት ጊዜ በግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ እና በስጦታ በየግላቸው ያገኙዋቸው ንብረቶች የግል ንበረታቸው ሆነው ሲቀሩ ከዚህ ውጪ ያሉ ንብረቶች በሙሉ የጋራ  ንብረት ይሆናሉ፡፡

ከጥንት ጀምሮ በወነዶችና በሴቶች መካከል ከነበሩ ማህበራዊ ግንኙነቶች መካከል ጋብቻ ሳይፈፀሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር አንዱ ነው፡፡ የዚህ አይነት ግንኙነት ምንም እንኳን ለቤተሰብ መመስረት ምክንያት  ቢሆንም በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻ ሟሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎችን ያላሟላ ስርዓት ነው፡፡ በሀገራችን እንደ ፍትሃ ነገስት ያሉ ጥንታዊ ጋብቻ ህጎች ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖሩን ቢያወግዝም የፍትሐብሔር ህግ እና በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አስፈላጊነቱን በማመን ከለላ አድረግውታል፡፡

  1. አንድምታዎቹ

የተሸሻለው የኢትዮጲያ የቤተሰብ ህግ በአንቀፅ 98 ስር እንደሚያትተው ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ማለት አንድ ወንድ እና አንድ ሴት በህግ በሚፀና አኳኋን ጋብቻ ሳይፈፀሙ በትዳር መልክ የኖሩ ሲሆን ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ግንኙነት በህግ አግባብ  ከሚደረጉ ጋብቻ ጋር ተቃራኒ ነው ተብሎ ሰለሚታሰብ እንደ “ፍተሃ ነገስት” ያሉ ጥንታዊ ህጎች እንደ ሃጥያት በመቁጠር ያወግዙት ነበር፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ  በዓለማችን ከትዳር ውጪ የሚወለዱ ልጆችና የፍቺ መጠን ፍጥነት እየጨመረ ሲመጣ በተቃራኒው ደግሞ ከትዳር ውጪ አብሮ መኖር እየተለመደና እየበዛ መጥቷል፡፡ ይህም ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖርን ከለላ መስጠት አስፈላጊ እና የማይታለፍ መሆኑን ህጉ ተቀብሎታል::  እንደምክንያትነትም የኢትዮጲያ ህግ መንግስት አንቀፅ 34 ለቤተሰብ የሚሰጠው ከለላ ይነሳል፤ ይህም ልክ በህግ እንደሚደረግ ጋብቻ ሁሉ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖርም ቤተሰብን ይመሰረታል፡፡

ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ህጋዊ እንዲሆን ወይም ተገቢነት እንዲኖረው በህግ አግባብ የሚፈፀም ጋብቻ ማሟላት የሚገበውን ሁኔታዎች እና ስርዓቶች መፈፀም አይጠበቅበትም:: የዚህ ስርዐት ዋናው አስፈላጊ ነገር የሁለቱ ወገኖች ነፃ ፍቃድ እና ስምምነት ነው፡፡

የተሻሻለው የኢትዩጲያ የቤተሰብ ህግ በአንቀፅ 99 ባስቀመጠው ማብራሪያ መሰረት፤ጋብቻ ሳይፈፀሙ እንደባልና ሚስት አብረው ኖሩ ማለት ወንድየውና ሴትየዋ የሚያሳዩት ሁኔታ በህግ እንደተጋቡ ሰዎች አይነት መሆኑ አስፈላጊና በቂ ነው፡፡ በተጨማሪም የዚህ ስርዓት ካሉት ልዩ ባህሪያት አንዱ ሁለቱ ወገኖች ለሶስተኛ ወገኖች እንደተጋቡ ሆነው መቅረብ አስፈላጊ አይደለም:: በሌላ በኩል አንድ ወንድና አንዲት ሴት በታወቀና በተደጋገመ ሁኔታ የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት መፈፀማቸው ብቻ በሁለቱ መካከል ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት ግንኙነት አላቸው ለማለት በቂ ምክንያት አይደለም፡፡

ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብረው መኖር የሚያስገኘውን የህግ ከለላ ለማግኝት ለምን ያህል ጊዜ አብረው መቆየት አለባቸው የሚለው ነትብ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው? ጊዜን በተመለከተ የተሸሻለው የቤተሰብ ህግ ያስቀመጠው ገደብ የለም ነገር ግን በአንቀፅ 99 ንኡስ አንቀፅ 3 ስር ከላይ አንደጠቀስነው ተደጋጋሚ ሩካቤ ስጋ መፈፀም ብቻ ጋብቻ ሳይፈፀሙ እንደባልና ሚስት ግንኙነት አላቸው እንደማያስብል አይተናል:: ስለዚህ ከዚህ የምንረዳው የዚህን ስርዓት የህግ ከለላ ለማግኘት ከጊዜ ይልቅ በህግ አግባብ ጋብቻ እንደፈፀሙ ተጋቢዎች አይነት በህሪ ማሳያት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- መከባበርና መተጋገዝ ፣መደጋገፍ ፣ ቤተሰብን በጋራ መምራት ፣ መተማመን  ወ.ዘ.ተ በመካከላቸው ካለ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት አለ ማለት ይቻላል::

ከዚህ  በመቀጠል ደግሞ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር የሚያስከትላቸውን የህግ ውጤቶችን እንዳስሳለን፡፡

  1. የጋብቻ ዝምድናን አያስከትልም፡- ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር በወንድየውና በሴቲቱ የስጋ ዘመዶች መካከል እንዲሁም በሴትየዋና በወንድየው የስጋ ዘመዶች መካከል አንዳችም የጋብቻ የጋብቻ ዝምድናና አያስከትልም፡፡

ነገር ግን የተሸሻለው ቤተሰብ ህግ አንቀፅ 100 ንዕስ አንቀፅ 2 ስር እንደተደነገገው “ሆኖም የጋብቻ ዝምድና ባለ ጊዜ፤ ጋብቻን የሚከለክሉ ድንጋጌዎች፣ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ባለ ጊዜም ተፈፃሚ ይሆናሉ” በማለት አትቷል፡፡ ይህም ማለት ምንም እንኳን ህግ ይህንን ስርዓት ለማስቀረት እና በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻን ለማበረታታት ሲል የጋብቻ ዝምድናን አይፈጥርም ቢልም በተገላቢጦሽ በሁለቱ ሰዎች ቤተሰቦች መካከል ጋብቻ እንዳይፈፀም ይከልክላል በተጨማሪም ይህ የሚያመላክተው በህግ አግባብ  የሚደረግ ጋብቻ በሁለቱ ተጋቢዎች ቤተሰቦች ላይ የጋብቻ ዝምድና እንደሚፈጠር ሁሉ የተሸሻለው የቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 9 ለጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብረው ለሚኖሩ ሰዎችም ይሰራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የጋብቻ ዝምድናን ያስከትላል፡፡

  1. የጋራ ወጪዎችን በጋራ መሸፈን፡- ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ኑሮአቸውን ወጪ ለመሸፈን እያንዳንዳቸው እንደየአቅማቸው እና ችሎታቸው አስተዋፆ ማድረግ አለባቸው፡፡ የቤተሰብ ህጉ በአንቀፅ 101 ስር የጋራ ወጪዎችን በጋራ መሸፈን አለባቸው ሲል ያትታል፡፡
  2. ጋብቻ ሳይፈፀሙ እንደባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ሰዎች ከሶስት ዓመት ላላነሰ ጊዜ አብረው ከኖሩ፤ በግንኙነት ውስጥ እያሉ ያፈሩዋቸው ንብረቶች የጋራ ሀብቶች ይሆናሉ፡፡ በተጨማሪም የሚገቧቸው እዳዎች አብረው በሚኖሩበት ጊዜ ለጋራ ኑሮአቸው ወይም ከግንኙነቱ የተወለዱ ልጆችን መሰረታዊ ፍለጎቶች ለሟሟላት ሲባል የተገቡ ዕዳዎች ሲሆኑ ለዕዳዎቹ አከፋፈል ሁለቱም በአንድነትና በነጠላ ኃላፊዎች ይሆናሉ፡፡
  3. ጋብቻ ሳይፈፅም እንደ ባልና ሚስት አብረው ከሚኖሩ ወንድና ሴት የሚወለዱ ልጆችን ተወላጅነታቸው የሚረጋገጠው ልክ በትዳር ውስጥ እንደተወለዱ ልጆች “እውነት ነው ተብሎ በሚገመት” ሳይሆን ስለ መወለድ በሚባል አካሄድ ነው፡፡ ይህ አካሄድም በተሸሻለው የቤተሰብ ህግ ምዕራፍ 9 ስር ተደንግጓል፡፡

ከዚህ በማስቀጠል ደግሞ ግንኙነቱ የሚቋረጥባቸውን መንገዶች እና ለግንኝነቱ መኖር እንደ ማስረጃ የሚቀርቡ ሁኔታዎችን እንመለከታለን፡፡

የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ በአንቀፅ 105 ስር እንደደነገገው ጋብቻ ሳይፈፅሙ እነደ ባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ወንድና ሴት በማንኛውም ጊዜ ግንኙነታቸውን ማቋረጥ ይችላሉ:: በተጨማሪም ግንኙነቱ እንዲቋረጥ ያደረገው ወገን እንደ ዝሙት ያለ ጥፋት ካልፈፀመ በስተቀር ካሳ እንዲከፍል አይገደድም፡፡ ይህ የሚያመላክተው ወደ ግንኙነቱ ሲገባ ምንም ሁኔታዎች ማሟላት እንደማይጠበቅባቸው ሁሉ ግንኙነቱን ለማቋረጥም ምንም ቅድም ሁኔታ ሳያስፈልግ ማቆም ይቻላሉ ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል የግንኙነቱን መኖር ማስረጃ በተመለከተ አንድ ወንድና ሴት ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብረው ይኖራሉ የሚባለው ምንም እንኳን በህግ የተጋቡ ባይሆንም የተጋቡ ሰዎችን ሁኔታ ሲያሳዩና ቤተዘመዶቻቸውና ማህበረሰቡ እንደተጋቡ ሰዎች የሚኖሩ ናቸው  ብለው ሲገምቷቸው ነው፡፡ ይህም በተሸሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 106 ስር በግልፅ እንደተደነገገው “የግንኙነቱ ሁኔታ መኖሩን በማጋገጥ” ማስረዳት ይቻላል፡፡

  1. ተግዳሮቶች

ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ያሉበትን ተግዳሮቶች ለማየት ከህግ አግባብ ከሚፈፀም ህጋዊ ጋብቻ ጋር በማነፃፀር እንደሚከተለው እናያለን፡-

  1. መደምደሚያ

ስለ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ምንነት፤ አንድምታዎቹ እና ተግዳሮቶቹን ተመልክተናል፡፡ በዚህ አይነት ግንኙነት ውስጥ ያሉ የማህበረሰባችን ክፍሎች ከህጋዊ ጋብቻ ይልቅ ይህንን ግንኙነት ለመምረጣቸው እንደምክንያትነት ከሚያስቀምጧቸው ነገሮች መካከል፤ለምሳሌ፡ በህግ ወይም በዕድሜ ጋብቻን ለመፈፀም አቅም ማጣት፣ትዳር ውስጥ ከመግባት በፊት እንደሙከራ፣የሰርግ ወጪን ለመቀነስ ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡ ከዚ ጋር አያይዘንም ስለባህሪያቶቹ፣ መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች፣ ህጋዊ ውጤቶቹን እና የሚቋረጥባቸውን መንገዶች ከህግ ማእቀፎቹ ጋር በማያያዝ የዳሰሰን ሲሆን፤ ተግዳሮቶቹን ደግሞ በህግ አግባብ ከሚደረግ ጋብቻ ጋር በማነፃፀር አይተናል፡፡

ከላይ በተዘረዘሩት ፅንሰ ሀሳቦች መሰረት በማድረግ ምንም እንኳን ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር በተሸሻለው ቤተሰብ ህግ ከለላ ቢደረገለትም፤ማህበረሰባችን ግን በህግ አግባብ የሚደረግ ጋብቻን ከሶስቱ አንዱን ስርዓት በመምረጥ ቢፈፅሙ እና የተሟላ ቤተሰብ ቢመሰርቱ መልካም ነው በማለት እዚህ ላይ እንቋጫለሁ፡፡ ሰላም!!!