Font size: +
5 minutes reading time (998 words)

ቀለብ የመስጠጥ ግዴታ ፅንሰ ሀሳብ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ

ግዴታ ህጋዊ ግንኙነት ሲሆን መሰረታዊ መርሁም የሚያካተው አንድ ዕዳ ያለበት ሰው ወይም ባለዕዳ ለአበዳሪው ዕዳውን የሚፈጽምበት ሂደት ነው፡፡ በዚህ ግንኙነት ውስጥ ባለዕዳው ለአበዳሪው አንድን ነገር ለማድረግ ፣ ለመስጠት ወይም ላለማድረግና ላለመስጠት የሚያደርገው ህጋዊ ግዴታ ነው፤ በተቃራኒው ደግሞ አበዳሪው ከባለዕዳው የሚገባውን እና በሕግ የተፈቀደለትን ጥቅም የሚያገኝበት ሁነት ነው፡፡ ግዴታዎች ከሁለት ምንጮች ይቀዳሉ፤ የመጀመሪያው ከውል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሕግ ነው፡፡ ከውል የሚመነጭ የግዴታ አይነት በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ላይ የሚመሰረት ሲሆን ስምምነቱም በተዋዋይ ወገኖቹ ላይ እንደ ሕግ እንደሚያገለግል የፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 1731 ያትታል፡፡ ሁለተኛው የግዴታ ምንጭ ደግሞ ከሕግ የሚመዘዝ ነው፤ የዚህ አይነት ግዴታዎች በቀጥታ ከሕግ  የሚመነጩ ሲሆን ግዴታውም በባለዕዳው እና አበዳሪ ሰዎች ሊቀየር ፣ ሊሻሻል እንዲሁም ሊቀር አይችልም፡፡

ቤተሰብ የአንድ ማህበረሰብ በጣም ጠቃሚ እና መሰረት የሆነ አካል ነው፡፡ ቤተሰብ አንድ ግለሰብን ከአጠቃላይ ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኝ ታላቅ ድልድይ ነው፡፡ እንዲሁም ተፈጥሮዊ ኢኮነሚያዊ እና ማህበረሰባዊ ጥቅም አለው፡፡ ቀለብ የመስጠት ግዴታ በአብዛኛው በቤተሰብ መካከል የሚገኝ ሲሆን ተገላቢጦሽ ባህሪ አለው፡፡ ይህም ወላጆች ለልጆቻቸው ለሚያደርጉላቸው እንክብካቤ እና ለማሳደግ ላለባቸው ግዴታ ልጆችም በተራቸው ለቤተሰቦቻቸው በዕርጅና ወቅት፣ በችግር ላይ ላሉ ወንድም እና እህት እና ለሚወልዷቸው ልጆች ቀለብ የመስጠት ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ዋንኛ ምንጩ ከሕግ ቢሆንም በስምምነት ግዴታውን መመስረት ግን በግልጽ በሕግ አልተከለከለም፡፡ ይህ የሆነውም ቀለብ የመስጠት ግዴታ መሰረቱ በቤተሰብ መካከል የሚገኝን ግብረገባዊ ወይም ስነ-ምግባራዊ የመተጋገዝ ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ተግባር ስለሆነ ነው፡፡    

 

2. ቀለብ የመስጠት ግዴታ ልዩ ባህሪያት

ቀለብ የመስጠት ግዴታ በሕግ የታቀፈ እንደመሆኑ እንዲሁም የሀገር ፖሊሲ ከመሆኑ አንፃር በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ጥሩ ቤተሰባዊ እሴቶች እና መመሪያዎች ከመንደፍና ከማስተግበር አንፃር ሰፊ ተቀባይነት እንዲኖረው ይፈለጋል፡፡ ቀለብ የመስጠት ግዴታ በዋነኝነት የሚጣለው ባለዕዳ(ቀለብ የመስጠት ግዴታ የተጣለባቸው) ሰዎች ላይ ሲሆን አበዳሪዎች ደግሞ በሕግ የተለዩ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ የምንረዳው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ጥብቅ በሆነ ሁኔታ ግላዊ ነው፤ ይህም ግዴታው ከባለዕዳው እና አበዳሪው ውጭ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡  

ቀለብ የመስጠት ግዴታ ከሌሎች የፍትሐብሔር ግዴታዎች አንፃር ልዩ ሲሆን ይህም ግዴታው ለማይንቀሳቀስ ንብረት እንድማስያዣ ሊሆን አይችልም፤ በባለዕዳው እና አበዳሪው መካከል የቀደመ ዕዳ ማቻቻያ ሊሆን አይችልም፤ አበዳሪው ከግዴታው የሚገኘውን ጥቅም ለሌላ ሶስተኛ ወገን ሊያስተላልፈው አይችልም፤ እንዲሁም በፍርድ ቤት እንደ ዕዳ ማካካሻ ሊያዝ አይችልም፡፡ በተጨማሪም አበዳሪው ባለዕዳ ለሚሆንላቸው ሌሎች አበዳሪዎች መብቱን ሊያዘዋውር አይችልም፡፡ ይህም ቀለብ የመስጠት ግዴታ በባለዕዳ ግለሰብ የሚፈፀም የአበዳሪ መብት ሲሆን፤ በሁለቱ ግለሰቦች መካከል ሌላ የዕዳ ወይም ጥቅማ ጥቅም ግንኙነት ቢኖር ራሱ፤ ዕዳው ሊጠየቅ የሚችለው በሌላ ራሱን በቻለ ግንኙነት ሊፈፀም ይችላል እንጂ ከቀለብ የመስጠት ግዴታ ጋር በፍጹም ሊጣመር አይችልም፡፡

ቀለብ የመስጠት ግዴታ ካለው ግላዊ ባህሪ አንፃር ግዴታውም መብቱም ከሁለቱ ወገኖች ጋር አብሮ የሚሞት ሲሆን ለሌሎች ሰዎች በውርስ አይተላለፍም፡፡ ይህም ማለት ባለዕዳው ከሞተ አበዳሪው ከባለዕዳው ወራሾች ግዴታው እንዲፈፀምለት ሊጠይቅ አይችልም፤ በተመሳሳይ ሁኔታ አበዳሪው ከሞተ የባለዕዳው ግዴታ ወደ አበዳሪው ወራሾች አይተላለፍም፡፡ ነገር ግን ፅንሰ ሀሳቡ አበዳሪ ሲሞት ወዲያውኑ ግዴታው ይቋረጣል ማለት አይደለም፤ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 213 ንዑስ አንቅጽ አንድ እና ሁለት እንደሚያትተው ባለዕዳው ለአበዳሪ ቀብር ማስፈፀሚያ ወጪ እንዲከፍል ይግድዳል፡፡ በተጨማሪም ይህን የቀብር ማስፈፀሚያ ወጪ ሌላ ሦስተኛ ወገን ከከፈለ ደግሞ በአበዳሪው ቦታ ራሱን በመተካት ባለዕዳው ወጪውን እንዲተካለት መጠየቅ ይችላል፡፡

ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ሰው ወይም ባለዕዳው እንደ ኑሮው ሁኔታ እና እንደ አካባቢው ልማድ የሚስማማውን በመከተል ለቀለብ ተቀባዩ ወይም አበዳሪው ምግብ፣ ልብስ፣ ጤናውን የሚጠብቅበትና እንደሁኔታው ለትምህርት አስፈላጊ የሆነውን ነገር መስጠት አለበት፡፡ ውድ አድማጮቻችን ከዚህ በማስቀጠል ቀለብ የመስጠት ግዴታ እንዲኖር መሟላት ያለቧቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እንዳስሳለን!!!

 

4. ቀለብ የመስጠት ግዴታ እንዲኖር መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 49 እና 198(1 እና 2) መሰረት ቀለብ የመስጠት ግዴታ የሚኖረው፤

  • በቀጥታ ወላጆችና ተወላጆች ወይም
  • በቀጥታ ጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ፣
  • በወንድማማቾች እና እህትማማቾች መካከል እና
  • በባልና ሚስት መካከል ነው፡፡

በተያያዘም አንቀጽ 199 በጋብቻ ለሚፈጠር ቀለብ የመስጠት ግዴታ የሚቀርበትን ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ ይህም ጋብቻው የፈረሰው በሞት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር፤ በጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ያለው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ቀሪ ይሆናል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ተፈፃሚ የሚሆነው ቀለብ ጠያቂው ሠርቶ ለኑሮው አስፈላጊ የሆነ ገቢ ለማግኘት አቅም የሌለው በችግር ላይ የወደቀ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል የጉዲፈቻ ግንኙነት በሚኖር ጊዜ በመሰረቱ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 212(1) እንደሚያትተው የጉዲፈቻ ልጅ ባል ወይም ሚስትና የቀጥታ ጋብቻ ተወላጆች የጉዲፈቻ አድራጊው ቤተዘመዶች ቀለቡን መስጠት በማይችሉበት ሁኔታ ካልተገኙ በስተቀር፤ የሥር ወላጆቹን ቤተዘመዶች ቀለብ መጠየቅ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ንዑስ አንቀጽ ሁለት የቀደምት ቤተሰቦቹ ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆች ቀለብ ለማግኘት ከዘመዶቻቸው አንዱን ለመጠየቅ የማይችሉ ካልሆነ በስተቀር በጉዲፈቻ የሰጡትን ልጅ ቀለብ ሊጠይቁት አይችሉም በማለት ያትታል፡፡

በተጨማሪም አንቀጽ 210 የቀለብ ሰጪዎች ተራ ቅደም ተከተል አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት ቀለብ የመስጠት ግዴታ  ያለባቸው ሰዎች ቅደም ተከተል፤

  1. ባል ወይም ሚስት
  2. ተወላጆች እንደየደረጃቸው
  3. ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆች እንደየደረጃቸው
  4. ወንድማማችና እህትማማቾች
  5. የጋብቻ ተወላጆች እንደየደረጃቸው
  6. የጋብቻ ወደላይ የሚቆጠሩ ወላጆች እንደየደረጃቸው ናቸው፡፡

 

5. ቀለብ የመስጠት ግዴታ የሚፈፀምባቸው መንገዶች

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 202 እንደሚያትተው በመሰረቱ ቀለብ የመስጠት ግዴታ የሚፈጸመው ቀለብ ሰጪው ለቀለብ ተቀባዩ የቀለቡን ገንዘብ በመስጠት ነው፡፡ በተጨማሪም የቀለቡ መጠን የሚወሰነው ቀለብ ጠያቂው ያለበትን ችግር እና የቀለብ ሰጪውን አቅም በማመዛዘን ነው፡፡ በሌላ በኩል ቀለቡ የሚከፈልበት ቦታን በተመለከተ  አንቀጽ 204 የሚያትተው ቀለቡ የሚከፈለው በተቻለ መጠን ለቀለብ ተቀባዩ በሚያመቸው ቦታ ይሆናል፤ እንዲሁም በአንቀጽ 203 መሰረት ቀለብ ሰጪው ወይም ተቀባዩ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት ስለቀለቡ መጠን ወይም ስለ ቀለብ ተቀባዩ መኖሪያ የተሰጠውን ውሳኔ በማናቸውም ጊዜ ማሻሻል ይችላሉ፡፡

የቀለብ ገንዘብ ሊተላለፍ ፣ ሊያዝ እና ሊጠራቀም አይችልም፤ እንዲሁም ቀለብ ተቀባዩ ለኑሮው አስፈላጊ መሆኑን ካላረጋገጠ በስተቀር፤ የቀለቡን ገንዘብ መቀበል ካለበት ቀን ጀምሮ በተከታታዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ያልተቀበለው ወይም ሳይጠይቀው የቀረ እንደሆነ የተጠራቀመው ቀለብ እንዲሰጠው መጠየቅ አይችልም፡፡ ይህም በአንቀጽ 205 እና 206 ስር ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ቀለብ ተቀባዩን በቀለብ ሰጪው ቤት በማኖር የቀለብ ግዴታን ማስቀረት እንደሚቻል አንቀጽ 207 ያትታል፡፡

ለቀለብ ተቀባዩ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ሰዎች ብዙ የሆኑ እንደሆነ ቀለብ ተቀባዩ ከእነርሱ መካከል አንዱ ቀለቡን እንዲሰጠው ሊጠይቀው ይችላል፡፡ ነገር ግን ቀለብ የመስጠት ግዴታ ካለባቸው ሰዎች አንዱ ሙሉውን የከፈለ እንደሆነ፤ ከፋዩ ራሱን በቀለብ ተቀባዩ ቦታ በመተካት ቀሪ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለባቸውን ሰዎች ወጪውን እንዲተኩለት መጠየቅ ይችላል ሲል የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 208 እና 209 ያትታል፡፡

በመጨረሻም የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 200 ቀለብ ተቀባዩ መብቱን ስለሚያጣበት ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ ይህም ቀለብ ተቀባዩ በቀለብ ሰጪው ወይም በዚህ ሰው ወደላይና ወደታች በሚቆጠሩ ወላጆች ወይም ተወላጆች ወይም ባልና ሚስት ሕይወት ወይም ንብረት ላይ የወንጀል ተግባር የፈፀመ ወይም ለመፈፀም የሞከረ እንደሆነ ቀለብ የመቀበል መብቱን ያጣል፡፡

6. መደምደሚያ

ግዴታ ከሁለት የተለያዩ ምንጮች ይፈጠራል፤ እነሱም ከውል እና ከሕግ ናቸው፡፡ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ከሕግ የሚመነጭ ግዴታ ቢሆንም፤ በስምምነት ከመፈጠር የሚያግደው ወይም የሚከለክለው ሕግ የለም፡፡ ይህ የሆነውም ቀለብ የመስጠት ግዴታ መሰረቱ በቤተሰብ መካከል የሚገኝን ግብረገባዊ ወይም ስነ-ምግባራዊ የመተጋገዝ ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ተግባር ስለሆነ ነው፡፡

ቀለብ የመስጠት ግዴታ ያለበት ሰው ወይም ባለዕዳው እንደ ኑሮው ሁኔታ እና እንደ አካባቢው ልማድ የሚስማማውን በመከተል ለቀለብ ተቀባዩ ወይም አበዳሪው ምግብ፣ ልብስ፣ ጤናውን የሚጠብቅበትና እንደሁኔታው ለትምህርት አስፈላጊ የሆነውን ነገር መስጠት አለበት፡፡ 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት በተሰጠ የፍርድ ውሳኔ ላይ የሚቀርብ የአፈጻጸም ...
ስምና ድንጋጌዎቹ በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 16 July 2024