Font size: +
7 minutes reading time (1451 words)

ስምና ድንጋጌዎቹ በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ

ስም ሰዎችን ለመለየት የምንጠቀምበት ሁነኛ ዘዴ ነው፡፡ ይህም አንድን ሰው ከሌላ ሰው ለመለየት ለሰዎቹ ስያሜ በመስጠት በቀላሉ መለየት ይቻላል፡፡ የአገራችን ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 36 (1) (ለ) ስምን የመሰየም የሁሉም ህጻናት መብት ነው ሲል ያትታል፡፡ በተጨማሪም ICCPR አንቀጽ 24 (2) እንደሚደነግገው ሁሉም ህጻናት እንደተወለዱ ወዲያውኑ እንዲመዘገቡ እና ስም እንዲወጣላቸው ያዛል፡፡

በጥልቀት የሀገራችንን ህጎች ስንመለከት የፍትሐብሔር ሕጉ ስምን የሚያስተዳድሩ ዝርዝር ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፤ እነሱም ከአንቀጽ 32 እስከ 46 እና ከአንቀጽ 3358 እስከ 3360 ድረስ የተደነገጉት ናቸው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ ማንኛውም ሰው የቤተ ዘመድ ስም፣ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የግል ስሞች እና የአባት ስም በዚሁ ቅደም ተከተል በሁሉም አስተዳደራዊ ሰነዶች ላይ እንዲሰፍር ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን ይህ ድንጋጌ የሚሰራው የፍትሐብሔር ሕጉ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው፤ ይህም ሕጉ ከመስከረም 11 ቀን 1960 በፊት የነበሩ ሰዎች ላይ ተግባራዊ አይሆንም፡፡

2. ስምና አይነቶቹ በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ

2.1 የቤተ ዘመድ ስም

የቤተ ዘመድ ስም በማንኛውም ጊዜ በህጋዊ ሰነዶች ላይ ቀድሞ ይጻፋል፡፡ የቤተዘመድ ስም ዋነኛ ጥቅሙ ቤተሰቦችን አንድ የቤተዘመድ ስያሜ በመስጠት ቤተሰባዊ አንድነትን እና ቀላል መለያ መፍጠር ነው፡፡ በፍትሐብሔር ሕጉ መሰረት ከመስከረም 11 ቀን 1960 ወይም የፍትሐብሄር ሕጉ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የሚወለዱ ሰዎች በሚከተለው አካኋን የቤተዘመድ ስም ሊኖራቸው ይገባል፤

  1. የእናት ባል የታወቀ ከሆነ፣ እንዲሁም ልጁን ካልካደ እና የቤተ ዘመድ ስም ካለው፤ የዛኔ የልጁ የቤተ ዘመድ ስም የእናቱ ባል የቤተ ዘመድ ስም ይሆናል ሲል አንቀጽ 3359 እና 33 ያትታል፡፡
  2. የልጁ አባት የታወቀ ከሆነ፣ ልጁንም ካልካዱ፣ ነገር ግን አባትየው የቤተዘመድ ስም ከሌለው የልጁ የቤተዘመድ ስም የአባቱን አባት (አያቱን) የግል ስም ይሆናል ሲል አንቀጽ 3359 (2) እና 36 (1) ይደነግጋል፡፡
  3. የልጁ አባት የማይታወቅ ከሆነ ወይም ልጁን የካደ እንደሆነ፤ በዚህ ሁናቴ የልጁ የቤተዘመድ ስም የእናቱ የቤተዘመድ ስም ይሆናል፡፡ ነገር ግን እናቱ የቤተዘመድ ስም ከሌላት ልጁ የእናቱን አባት ስም እንደ ቤተዘመድ ስም ይወስዳል ሲል አንቀጽ 3359 (3) እና 33(2) ያትታል፡፡ በሌላ በኩል ከላይ የተጠቀሱት አንቀጾች የልጁ አባትነት በፍርድ ቤት ውሳኔ የተረጋገጠ ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም ሲል አንቀጽ 33(3) ይደነግጋል፡፡ በዚህ ጊዜም ልጁ የቤተዘመድ ስሙ ወደ አባቱ እስኪቀየር ድረስ የእናቱን የቤተዘመድ ስም እንደያዘ ይቆያል ሲል አንቀጽ 42 ያትታል፡፡
  4. የልጁ ወላጆች ማለትም እናትና አባቱ የማይታወቁ ወይም የሌሉ ከሆነ፤ የልጁ የቤተዘመድ ስም በክብር መዝገብ ሹም አማካኝነት የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ስሙም በአካባቢው ከሚገኙ ልማዳዊ ስሞች መካከል ይመረጥለታል ሲል አንቀጽ 39 ይደነግጋል፡፡

በሌላ በኩል የፍትሐብሔር ሕጉ ከመደንገጉ በፊት የነበሩ ስሞችን በተመለከተ የቤተዘመድ ስም መኖር በምርጫቸው ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ነገር ግን በገዛ ፍቃዳቸው የቤተዘመድ ስም እንዲኖራቸው ከወሰኑ በሚከተለው አኳኋን የቤተዘመድ ስም ይሰጣቸዋል፤

  • የልጁ አባት የታወቀ ከሆነ እና ልጁን ያልካደ ከሆነ እንዲሁም የአባቱ ወደ ላይ የሚቆጠሩ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ወላጆች በመስከረም 11 ቀን 1960 ላይ በህይወት ካሉ፤ ልጁ የአባቱን አያት ስም እንደ በተዘመድስም ይወስዳል በማለት አንቀጽ 3358 ይደነግጋል፡፡
  • የልጁ አባት የታወቀ ከሆነ እና ልጁን ያልካደ ከሆነ ነገር ግን በመስከረም 11 ቀን 1960 ዓ.ም ላይ ወደላይ የሚቆጠሩ የአባቱ ወላጆች የሌሉ እንደሆነ፤ ልጁ የአባቱን አባት ስም እንደ ቤተዘመድ ስም ይወስዳል ሲል አንቀጽ 3358 (2) ያትታል፡፡
  • በአንቀጽ 3358 (3) መሰረት የልጁ አባት ያልታወቀ ከሆነ ወይም ልጁን የካደ ከሆነ፤ የዛኔ የልጁ የእናቱን አባት ስም እንደቤተዘመድ ስም ይወስዳል፡፡
  • የልጁ እናትና አባት የማይታወቁ ከሆነ የፍትሐብሔር ሕጉ የሽግግር ድንጋጌዎች ምንም ያስቀመጡት ነገር ስለሌለ፣ ምስለትን በመጠቀም አንቀጽ 39 ተግባራዊ ይሆናል፡፡

2.1.1 የቤተዘመድ ስም የሚለወጥባቸው መንገዶች

በመሰረቱ ለአንድ ሰው የቤተዘመድ ስም ከተሰጠው በኋላ ሊቀየር አይችልም፡፡ ነገር ግን ለሚከተሉት ወጣ ላሉ ሁነቶች ብቻ የቤተዘመድ ስም ሊቀየር ይችላል፡፡ እነሱም፤

   ሀ. የመጀመሪያው በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 40 ስር የተደነገገው አንድ ሴት ጋብቻ ስትፈጽም የቤተዘመድ ስሟን ልትቀይር ትችላለች የሚለው ነው፡፡ በመሰረቱ ሴቲቷ የቀድሞውን የቤተዘመድ ስሟን ይዛ መቀጠል ትችላለች፡፡ ነገር ግን ከጋብቻ በኋላ ሚስት ቀድሜ የነበሩትን የቤተ ዘመድ ስም ወደ ባሏ የቤተዘመድ ስም መቀየር ትችላለች፡፡ ይህ አዲሱ የቤተዘመድ ስሟ በጋብቻ ውስጥ እስከቆች ወይም ጋብቻው በመቶ ወይም በመጥፋት ውሳኔ ከተቋረጠ እና ሌላ ሳታገባ ከኖረች የቤተዘመድ ስሟ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

    ለ. ሁለተኛው ደግሞ በጉዲፈቻ ስምምነት ወቅት ልጁ የቀድሞ የቤተዘመድ ስሙን በመተው ወደ ጉዲፈቻ አድራጊው ቤተሰብ የቤተዘመድ ስም ይቀይራል ሲል አንቀጽ 41 ያትታል፡፡

   ሐ. ሶስተኛው ሁናቴ ደግሞ በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 39 (3) እና የተቀመጠው ነው፡፡ ይህም የልጁ ወላጆች የማይታወቅ ወይም የሌሉ እንደሆነ፤ ልጁ የቤተዘመድ ስም የሚሰጠው በክብር መዝገብ ሹም ነው፡፡ ነገር ግን ማንኛውም የህሊና ወይም የሞራል ጥቅም ያለው ሰው ወይም ያገባኛል የሚል ሰው ልጁ አምስት አመት ሳይሞላው በፊት ለፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረብ የልጁን የቤተዘመድ ስም መቀየር ይችላል፡፡

   መ. በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 42 መሰረት የቤተዘመድ ስም ለመለወጥ ጥያቄ ሲቀርብ በቂ ምክንያት የተገኘ እንደሆነ በሰውየው ጠያቂነት የቤተዘመድ ስሙ እንዲለወጥ ዳኞች ሊፈቅዱ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ዳኞቹ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመረምሩ የስሙ መለወጥ ጉዳይ በሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ላይ አንዳችም ጉዳት እንደማያስከትል ያረጋግጣል፡፡

2.1.2 የቤተዘመድ ስም ልዩ ባህሪያት

በመጀመሪያ የቤተዘመድ ስም ዋነኛ ጥቅሙና አስፈላጊነቱ አንድን ቤተሰብ በአንድ የቤተዘመድ ስያሜ አንድ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም የአንድ ሰውን ወደታች የሚቆጠሩ ልጆችና የልጅ ልጆች በአንድ የቤተዘመድ ስም መሰየም ከሌሎች በቀላሉ ለመለየት እንዲቻል ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በጋብቻ እና በጉዲፈቻ የቤተዘመድ ስሙን ሊቀይር ይችላል፡፡ በተጨማሪም አንድ ሰው ተመሳሳይ የቤተዘመድ ስም የሚጠቀሙ ዘመዶቹ በህይወት እያሉ ከመሬት ተነስቶ የቤተዘመድ ስሙን ሊቀይር አይችልም፤ መቀየር በፈለገ ጊዜ ፍ/ቤቱ በቂ ምክንያት ማቅረቡንና ሶስተኛ ወገኖች ላይ ጉዳት አለማድረሱን ካጤነ በኋላ ሊፈቅድ ይችላል፡፡

በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 44 መሰረት ስለ ስም የሚደረግ ማንኛውም ውል በሕግ ረገድ ዋጋ የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው የቤተዘመድ ስሙን ለሌላ ሊሰጥ፣ ሊያከራይ፣ ሊሸጥ እንዲሁም ሊያበድር አይችልም፡፡ ነገር ግን የንግድ ስምን በሚመለከት የንግድ ሕጉ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 45 እንደሚያትተው አንድ ሰው የሙያ ስራውን በሚያከናውንበት ሁኔታ ውስጥ በገዛ ስሙ የመገልገል ጉዳይ በይመስላል ከሚደርሰው መዘባረቅ ይነሳ በሌላው ሰው ክብርና ገናናነት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ግብ ወይም ውጤት የሚያስከትል ነገር ሊኖው አይገባም፡፡ በተጨማሪም አስፈላጊ መሆኑ በተገመተ ጊዜ በእንደዚህ ያለው አጋጣሚ ጉዳይ ያለአግባብ የመወዳደርና የስም ማጥፋት ደንቦች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል በሌላው ስም ያለአግባብ መገልገልን በተመለከተ የፍትሀብሔር ሕጉ አንቀጽ 46 የቤተዘመድ ስም ያለው ሰው በዚሁ በመሰል ስሙ ምክንያት ሌላው ሰው ያለአግባብ በመገልገሉ ግዙፍና የህሊና (የሞራል) ጉዳት የሚያጋጥመው የሆነ እንደሆነ ይህን የቤተዘመድ ስሙን ሌላ ሰው ያለአግባብ እንዳይገለገልበት መቃወም ይችላል፡፡ በተጨማሪም ባለስሙ ከሞተ ወይም ፈቃዱን ለመግለጽ ችሎታ ባጣ ጊዜ ይህን ስም የማይጠራበት ቢሆንም እንኳ የሟቹ ሚት ወይም ባል እና ተወላጆቹ ይህን የመቃወም መብት ይኖራቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ይህ በስም ያለአግባብ የመገልገል ጉዳይ እንዲታገድ ተጠይቆ ሳይታገድ የቀረበ እንደሆነ እንደ ስም ማጥፋት ተቆጥሮ የህሊና ወይም የሞራል ጉዳት ካሳ እንዲከፈል ሊወሰን ይችላል፡፡

2.2 የግል ስም

አንድ ሰው በመሰረቱ አንድ የቤተዘመድ እና የአባት ስም ሊኖረው፤ አንድ ወይ ሁለት የግል ስሞች ይኖሩታል፡፡ በማለት የፍትሐብሔ ሕጉ አንቀጽ 32(2) ያትታል፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 34 እና 35 መሰረት የግል ስም አሰጣጥን በዚህ አካሄድ እንዲሆን ይደነግጋል፤

  • የአንድን ልጅ የግል ስም የሚመርጠው አባቱ ነው፡፡ አባቱ በሌለ ጊዜ የአባቱ ቤተዘመዶች ይመርጣሉ፡፡
  • ለልጁ ሁለተኛ የግል ስም እናቱ ወይም እርሷ የሌለች እንደሆነ የእናቱ ቤተዘመዶች መርጠው ሊያወጡለት ይችላሉ፡፡
  • የልጁ አባት ያልታወቀ በሆነ ጊዜ ወይም የልጁ አባት ወገን የሆኑ ቤተዘመዶች የሌሉት የሆነ እንደሆነ የልጁ እናት ወይም እርሷ ባትኖር የእናቱ ቤተዘመዶች ለልጁ ሁለት የግል ስም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩል ከላይ የተጠቀሱት ቤተሰቦች በሌሉበት ወቅት ለልጁ በጣም ቅርብ የሆነ ወደ ላይ የሚቆጠር ወላጅ ወይም የጎን ዝምድና ያለው ሰው የቤተዘመድ እንደራ በመሆን የግል ስም ሊያወጡለት ይችላሉ፡፡ በአጋጣሚም በቤተዘመድ እንደራሴዎች እንደራ በመሆን የዝምድና ደረጃ እኩል በሚሆኑበት ጊዜ የልጁን የግል ስም የሚመርጠው በእድሜ ከፍ ያለው ወደላይ የሚቆጠር ወይም የጎን ዝምድና ያለው ሊሆን ይችላል፡፡

በመጨረሻም ከላይ የተጠቀሱ ሰዎች በሙሉ የሌሉ እንደሆነ በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 39 መሰረት ከልጁ የግል ስም የክብር መዝገብ ሹም መኮንን በአካባቢው ከሚገኙ ልማዳዊ ስሞች መካከል መርጦ ይሰጠዋል፡፡ በሌላ በኩል በአንቀጽ 41 መሰረት በጉዲፈቻ ስምምነት ወቅት አንድ የግል ስም ሊሰጠውና የጉዲፈቻ አድራጊው የግል ስም እንደ አባት ስም ሊሆነው ይችላል፡፡

የፍትሐብሔር ሕጉ በአንቀጽ ሕጉ በአንቀጽ 38 ስር የተከለከል የግል ስምን አስቀምጧል፡፡ በዚህ መሰረት ማንኛውም ልጅ የአባቱን ወይም የእናቱ ወይም ደግሞ በህይወት ካሉት እህቶቹና ወንድሞቹ የአንደኛው የግል ስም ሊሰጠው አይችልም፡፡ በዚህ ጊዜ ከነዚህ ሰዎች የሚለየው አንድ ሌላ ስም ሊኖረው ይገባል፡፡

2.3 የአባት ስም

በተለምዶ የአባት ስም የምንለው የአባት የግል ስምን ሲሆን በህጋዊ ሰነዶች ላይ መጨረሻ ላይ የሚጻፈው ነው፡፡ በተጨማሪም የአባት ስም ሁልጊዜ የአባት የግል ስም ሲሆን ከእናት ስም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም በሌላ በኩል በጉዲፈቻ ውል ጊዜ ልጁ የጉዲፈቻ አድራጊውን የግል ስም እንደ አባት ስም ሊወሰድ እንደሚችል የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 41 (2) ይደነግጋል፡፡

በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 36 መሰረት ለልጁ የአባት ስም የሚሆነው የአባቱ የግል ስም ነው፡፡ ነገር ግን የልጁ አባት ባልታወቀ ጊዜ ልጁ የአባት ስም አይኖረውም፡፡ በተጨማሪም በአስተዳደር ክፍል ወይም በአድሚኒስትራዮን ጽሁፎች ውስጥ የአባት ስም ከቤተዘመድ ስም ጋር አንድ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ የአባት ስም አይጻፍም፡፡

በመሰረቱ የአባት ስም ሊቀየር አይችልም፤ ነገር ግን የልጁ እናት ተደፍራ ከሆነ ወይም ከአንድ በላይ ወንዶች ጋር ግንኙነት መስርታ ከሆነ እና የአባትነት ግጭት ከተነሳ፤ በፍርድ ቤት አባት ተደርጎ የሚወሰንለት ሰው የግል ስም የልጁ አባት ስም ተድርጎ ይቀየራል፡፡ ይህንንም በተመለከተ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ከአንቀጽ 123 – 179 ስር ያሉት ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡ በመጨረሻም ልጁ በተወለደበት ቀበሌ ወይም አጥቢያ ለሚገኘው የክብር መዝገብ ጽ/ቤት ሹም የልጁን መወለድ መግለጫ ሊሰጥ የሚገባው ሰው ልጁ ከተወለደበት ቀን አንስቶ ባለው በተከታዩ 90 ቀን ውስጥ ለተወለደው ልጅ የተሰጠውን የግል ስም ማቅረብ አለበት ሲል የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 37 ይደነግጋል፡፡

3. ማጠቃለያ

በአለማችን የሚገኝ አብዛኛው ያደጉ አገራት የቤተዘመድ ስምን በአግባቡ እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ በዚህም ረገድ አንድን ቤተሰብ ከሌላ ቤተሰብ ለመለየት ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ በአገራችን ስምን በተመለከተ የፍትሐብሔር ሕጉ እሰከሚረቅ ድረስ ምን አይነት ደንብ ያልነበረ ሲሆን ከመስከረም 11 ቀን 1960 ዓ.ም በኋላ ግን በፍትሐብሔር ሕጉ ታቅፎ ስምን በሶስት ማእዘናት ከፍሎ ያስቀመጠ ሲሆን፤ ከሶስቱ የስም አይነቶች አንዱ የሆነው የቤተዘመድ ስም ነው፡፡ ሕጉ እንደሚደነግገውም ሁሉም ኢትዮጵያ የቤተዘመድ ስም ሊኖረው እንደሚገባ እንዲሁም ያገቡ ሴቶች እና የጉዲፈቻ ልጆችም የቤተዘመድ ስማቸውን ሊለውጡ እንደሚችሉ ያትታል፡፡ ነገር ግን በተግባር ከአንድ አንድ ህጋዊ ሰነዶች ለምሳሌ ፓስፖርት በስተቀር የቤተዘመድ ስምን ማህበረሰባችን እየተጠቀመው አይገኝም፤ በዚህ ረገድ በሕጉና በተፈጻሚነቱ መካከል ተግዳሮት ሆኖ ይገኛል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ቀለብ የመስጠጥ ግዴታ ፅንሰ ሀሳብ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ
የፍርድ አፈፃፀም መሠረታዊ ታሳቢዎችና ያጋጠሙ ችግሮች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 11 September 2024