አፈፃፀም ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ በእራሱ አማካኝነት ወደ ተግባር የሚለውጥበት ሥርዓት ነው፡፡ ስለፍርድ አፈፃፀም የተደነገጉትን ድንጋጌዎች በመከተል ፍርድን በተግባር መተርጎም እንደመሆኑ መጠን የማስፈፀሚያ ሥርዓቱ በጥቅሉ የፍ/ብ/ሥ/ሥ ህጉን መሠረታዊ ዓላማ ተከትሎ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲፈፀም በሚያስችል አኳኋን የተዋቀረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር እንደሚታየው ክስ አቅርቦ ለማስፈረድ ከሚወሰደው ውጭ ጊዜና ጉልበት ባልተናነሰ ሁኔታ የተፈረደን ፍርድ ለማስፈፀም የሚጠይቀው ወጭና ጊዜ በልጦ የሚታይበት ጊዜ ይከሰታል፡፡ ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው፡፡

ከነዚህም ጥቂቶቹ፡-

በአጠቃላይ ፍርድን በማስፈፀም በኩል ለሚከሰተው መጓተት ዓበይት የሆኑትን ምክንያቶች በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

ይኸውም፡-

  1. ህጉ በሚያዘው መሠረት ያለመመራት፣ በህጉ እና በልምድ መካከል ያለው ልዩነት፣
  2. ድንጋጌው በእራሱ ግልፅ ያለመሆን ወይም ሁሉን ሁኔታ ያለመሸፈን፣
  3. ረቂቁ ከተዘጋጀበት ቋንቋ ወደ አማርኛ ሲተረጎም የተፈጠረው የትርጉም ስህተት (ክፍተት) በዋነኛነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ከላይ የተመለከቱት ዓበይት ችግሮች ከማታይባቸው ድንጋጌዎች ጥቂቶቹን ለመመልከት ያህል፡-

በሕጉ ያለመመራት ሁኔታ

የፍርድ ባለመብት ፍርድ እንዲፈፀምለት በቁጥር 378 መሠረት ማመልከቻ ሲያቀርብ አፈፃፀሙን የያዘው ፍርድ ቤት በቁጥር 386 መሠረት እንደፍርዱ የማይፈፅምበት ምክንያት ካለው ያስረዳ ዘንድ የማመልከቻው ግልባጭ ከመጥሪያ ጋር ይላክለታል፡፡

በቀነ ቀጠሮውም በቀረበ ጊዜ ፍርድ ቤቱና የፍርድ ባለገንዘቡ ለሚያቀርቡለት ጥያቄ በመሃላ ቃል የተደገፈ መልስ ይሰጣል፡፡ በማለት በቁጥር 386(1) እና (2) ተደንግጓል፡፡ በዚህ አኳኋን መፈፀም ሲገባው የፍርድ ባለዕዳው ለቀረበበት የአፈፃፀም ክስ መልሱን ይዞ እንዲቀርብ፤ ይዞ በቀረበ ጊዜም የፍርድ ባለመብቱ የመልስ መልሱን እንዲያቀርብ ተከታታይ ቀጠሮ የመስጠቱ አሠራር በህግ ያልተደገፈ እና አላስፈላጊ ተግባር ነው፡፡ በአፈፃፀም ምክንያት የሚነሳው ክርክር አጭርና ግልፅ ነው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 375፣396፣397፣398 መሠረት ዕዳውን ከፍሎ ከሆነ፣ የፍርድ ባለዕዳነቱን ግዴታ ፈፅሞ ከሆነ፣ የመቻቻል ጥያቄ ካለው ይህንኑ ለማረጋገጥ እና ፍርዱ የሚፈፀምበትን መንገድ የሚያሳይ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ሌላ የፅሑፍ ክርክርን የሚጋብዝበት ሁኔታ አይታይም፡፡ ይህም ከላይ ከፍ ሲል እንደተገለፀው የፍርድ ባለዕዳው በአካል በተገኘበት ጊዜ በመሃላ ሥር ሆኖ የሚያረጋግጠው ተግባር ነው፡፡

በዚህ አኳኋን ፍርዱ እንዳይፈፀም የሚቃወምበትን ምክንያት ቀርቦ ካላስረዳ ወይንም ያልቀረበ እንደሆነ በቁጥር 386(3) እና 392(1) መሠረት ፍ/ቤቱ ውሳኔው እንዲፈፀም ወዲያውኑ ትዕዛዝ መስጠት አለበት፡፡

የፍርድ ባለዕዳው በመጥሪያው መሠረት ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ታስሮ እንዲቀርብና ለሚደረግለት ጥያቄ ወይም ምርመራ መልስ እንዲስጥ የሚታዘዘው ገንዘብ እንዲከፍል የተፈረደን ፍርድ ለማስፈፀም እንደሆነ ከዚሁ ድንጋጌ ንዑስ ቁጥር 3 እና 4 መገንዘብ ይቻላል፡፡

እንደዚሁም የፍርድ ባለዕዳው ፍርዱ እንዲፈፀም መሰናክል በመፍጠር ወይም የፍርዱን አፈፃፀም ለማዘግየት ንብረቱን ከፍርድ ቤቱ ሥልጣን ክልል ውጭ ለማሸሽ ወይም ራሱ ከፍርድ ቤቱ ሥልጣን ክልል ውጭ ለመውጣት፣ ለመሸሽና ለመሰወር ያቀደ መሆኑን የሚያረጋግጥ በቃለ መሃላ የተደገፈ ማመልከቻ የቀረበለት እንደሆነ በቁጥር 386(1) መሠረት መጥሪያ ማስተላለፍ ሳያስፈልግ በቀጥታ ታስሮ እንዲቀርብ እና እንደፍርዱ የማይፈፀምበትን ምክንያት እንዲያስረዳ ፍ/ቤቱ ማዘዝ እንደሚችልም በቁጥር 387 ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም በመጀመሪያው ቀነ ቀጠሮ በዚህ አኳኋን እንደ ህጉ አነጋገር የአፈፃፀም ሥርዓቱ ከተከናወነ አፈፃፀምን ሳይንዛዛ መምራት እና በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ያስችላል፡፡

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉ ከተዘረዘሩት ድንጋጌዎች መካከል ግልፅ ያልሆነ ወይም ሁሉን ሁኔታዎች የማይሸፍኑ ወይም በትርጉም ስራ ምክንያት በተፈጠረው ክፍተት ለጉዳዩ መጓተት ምክንያት የሆኑትን ድንጋጌዎች ለአብነት ለመጥቀስ ያህል፡-

ፍርዱን እንዲያስፈፅም የታዘዘ ፍ/ቤት ስላለው ሥልጣን በሚደነግገገው በቁጥር 347(1)“…ስለፍርድ አፈፃፀም የሚሰጠው ትዕዛዝና በትዕዛዙም ላይ ይግባኝ ስለሚባልበት ሁኔታ ያለው ሥልጣን ዋናውን ፍርድ ከወሰነው ፍርድ ፍ/ቤት ሥልጣን ጋር እኩል ሆኖ ይቆጠራል፡፡” በማለት በመደንገጉ አፈፃፀሙን በሚመለከት የይግባኝ አቤቱታ ለየትኛው ፍ/ቤት ይቀርባል? ለሚለው ጥያቄ አሳሳች ምላሽ የሚሰጥ ድንጋጌ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ፍርዱን የሰጠው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ቢሆንና ፍርዱን እንዲያስፈፅም የተወከለው ደግሞ የወረዳው ፍ/ቤት ቢሆን ከወረዳው ፍ/ቤት ይግባኝ ስለሚባልበት ሁኔታ ያለው ሥልጣን ከከፍተኛው ፍ/ቤት ሥልጣን ጋር እኩል ሆኖ ይቆጠራል በማለት በቁጥር 374(1) የተቀመጠ ስለሆነ በአፈፃፀሙ ጉዳይ የወረዳው ፍ/ቤት በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ይግባኙ ለጠቅላይ ፍ/ቤት ይቀርባል ወደ ሚለው መደምደሚያ የሚያደርስ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከዚሁ ድንጋጌ የእንግሊዘኛ ግልባጭ ጋር ተገናዝቦ ሲታይ እኩል ሆኖ የሚቆጠረው በማስፈፀም ረገድ ያለውን ሥልጣን በሚመለከት እንጂ ይግባኝ በተባለ ጊዜ እራሱ የተወከለው ፍ/ቤት በሚሰጠው ፍርድ ይግባኝ ሲባል ይግባኙን ለሚያየው ፍ/ቤት ነው በማለት ደንግጓል፡፡

የፍርድ አፈፃፀምን በተወከለው ፍ/ቤት ለጊዜው አግዶ ስለማቆየት በሚደነግገው ቁጥር 376 (1) ‹‹… እንዲሁም ፍርድ እንዲታገድለት ወይም ስለፍርዱ ወይም ስለውሳኔው አፈፃፀም ጉዳይ ለፈረደው ፍ/ቤት ሲያመለክት ፍርድ ቤቱ ፍርዱን እንደሚያስፈፅመው ፍ/ቤት ሆኖ ነገሩን ይመለከታል፡፡›› የሚለውን ከዚሁ ድንጋጌ የመጀመሪያ ክፍል ጋር አቆራኝተን ስንመለከተው ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሆኖም ከእንግሊዝኛው ግልባጭ ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ለአስፈፃሚው ፍ/ቤት በቂ ምክንያት የቀረበ እንደሆነ ፍርዱን የፈረደው ፍ/ቤት አፈፃፀሙን እንዲያግድለት ወይም ደግሞ እራሱ ፍርዱን የፈረደው ፍ/ቤት አፈፃፀሙን ይዞት ቢሆን ኖሮ ስለአፈፃፀሙ መስጠት ይችል የነበረውን ማናቸውም ትዕዛዝ መስጠት እንዲችል የፍርድ ባለዕዳው ውሳኔውን ለሰጠው ፍ/ቤት ማመልከት እንዲችል በቂ ሆኖ ለሚገመት ጊዜ ብቻ ውሳኔው ከመፈፀሙ ታግዶ እንዲቆይ ያደርግለታል የሚለውን ለማስተላለፍ ታስቦ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ይህም ፍርዱን የፈረደው ፍ/ቤት ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ አለማስተላለፉንና አስፈፃሚው ፍ/ቤትም ለዘለቄታው ማገድ የማይችል መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ድንጋጌው በእራሱ ግልፅ ባለመሆኑ የተነሣ አሻሚ ትርጉም ሊሰጥ በመቻሉ ለክርክር መራዘም ምክንያት ከሆኑ ድንጋጌዎች አንዱ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 337 የተመለከተው ነው፡፡ ቁጥር 377 "ፍርድ በተፈረደለት በማናቸወም ሰው ላይ ፍርድ የተፈረደበት ወገን ክስ ያቀረበበት እንደሆነ ፍ/ቤቱ ተገቢ መስሎ የገመተውን በቂ ዋስትና ወይም መያዣ እንዲሰጥ ካደረገ በኃላ ለክርክሩ ውሳኔ እስኪሰጠው ድረስ ፍርዱ ከመፈፀሙ ታግዶ እንዲቆይ ለማዘዝ ይችላል፡፡" በሚል በመቀረፁ አፈፃፀሙ ታይቶ እንዲቆይ ትዕዛዝ የሚሰጠው የትኛው ፍ/ቤት ነው? የፍርድ ባለዕዳው በፍርድ ባለገንዘቡ ላይ ያቀረበውን ክስ እያየ ያለው ፍ/ቤት ወይስ አፈፃፀሙን የያዘው ፍ/ቤት? ለሚለው ጥያቄ ድንጋጌው ለብቻው ሲታይ አሻሚ ነው፡፡

በህግ አተረጓጎም መርህ መሠረት ህጉ አሻሚ መስሎ በታዩ ጊዜ ድንጋጌዎችን እርስ በእርሳቸው አስተሳስረን ልንተረጉም ይገባል፡፡ ይኸው ድንጋጌ የሚገኝበት ክፍል አፈፃፀምን ስለሚያስፈፅሙ ፍ/ቤቶች እና ስላላቸው ሥልጣን የሚገልፅ በመሆኑ በዚሁ ድንጋጌ "... ፍርድ ቤቱ... " የሚለው ሀረግ አፈፃፀሙን የያዘው ፍ/ቤት መሆኑን እንረዳለን ከዚህም በቀር ክስ የቀረበለት ፍ/ቤት የዕግድ ትዕዛዝ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 154-159 በተመለከቱት ሁኔታዎች በመሆኑና የተጀመረን አፈፃፀምም አግዶ የሚያቆየው በዚሁ ህግ  በቁጥር 332-335 በተመለከተው መሠረት የይግባኝ ክርክሩን የሚያየው ፍ/ቤት በመሆኑ በማናቸውም መንገድ ቢሆን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 377 ድንጋጌ የፍርድ ባለዕዳው በፍርድ ባለመብቱ ላይ ክስ በማቅረቡ ምክንያት ክሱን እያየ ያለው ፍ/ቤት በሌላ ፍ/ቤት በፍርድ ባለዕዳው ላይ የተጀመረን የአፈፃፀም ክስ አግዶ ለማቆየት ሥልጣን የሚሰጥ አይደለም፡፡

ፍርድ እንዲፈፀም የሚቀርብ ማመልከቻ በጊዜ የተገደበ ለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 384 ተመልክቷል፡፡ በቁጥር 385(1) "ፍርድ እንዲፈፀም የሚቀርበው ማመልከቻ ከዚህ በላይ ባሉት ቁጥሮች የተነገሩትን ግዴታዎችና ሥርዓቶች አሟልቶ የያዘ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ አለበት፡፡" በማለት በመደንገጉና የይርጋ ጊዜው ሁኔታ ከቁጥር 385 በፊት የተቀመጠ በመሆኑ ጊዜው ያለፈበት የአፈፃፀም ጥያቄ ከሆነ  እንደሌሎች የይርጋ ክርክሮች በተከራካሪ ወገን ብቻ እንዲቀርብ የተተወ ሳይሆን ፍ/ቤቱ በእራሱ አነሳሽነት ሊያነሳው የሚገባ ጉደይ ነው፡፡ የጊዜውም መነሻ የሚታሰበው እንዲፈፀም የሚጠይቀው ነገር በፍርዱ ከተወሰነበት ቀንና ዓመተ ምህረት ጀምሮ ነው በሚል ተቀምጧል፡፡ ፍርድ ሲባል በመጀሪያ ደረጃ የተሰጠን ፍርድ ወይም በይግባኝ የተሰጠን ፍርድ ያጠቃላል የሚለውንም  ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡

የፍርድ አፈፃፀም መሠረታዊ ታሳቢዎችንና በአፈፃፀም ጊዜ የሚከሰቱ ችግሮች ምክንያቶቹ  ምንድን ናቸው ለሚለው ጥያቄ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ጠቋሚዎች ሲሆኑ ቀሪውን ክፍል ደግሞ ከሚከተሉት ርዕሰ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የምናያቸው ይሆናል፡፡

ከፍርድ በፊት እና በፍርድ ማስፈጸም ሒደት ስለሚሰጡ የዕግድ ትዕዛዞች

ለጊዜው የሚሰጥ የማገድ ትዕዛዝ (temporary junction) ክርክሩ ተጀምሮ ነገሩ በፍርድ እስኪወሰን ወይም የተለየ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ያሉትን ሁኔታዎች በነበሩበት አèኃን ጠብቆ ለማቆየት ሲባል ከሚሰጡት ጊዜያዊ ትዕዛዞች አንዱ ነው፡፡ ንብረት እንዳለ እንዲቆይ፣ ከመጥፋት እንዲድን፣ እንዳይበላሽ፣ ለሌላ ስው ተላልፎ እንዳይሰጥ ወደ ሌላ ስፍራ እንዳይዛወር እንዳይባክን ለማድረግ ሲሆን ዓላማውም ክርክሩ ተጠናቆ የሚሰጥ ፍርድ ለአፈፃፀሙ ዋስትና እንዲኖረው፤ ውጤት እንዲያገኝ ለማስቻል ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ ትዕዛዝ የሚሰጠውም ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ ተቀብሎ በሚያየው ፍ/ቤት ሲሆን ትዕዛዙ በሁለት ምክንያቶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

አንደኛው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 154(ለ) እንደተጠቀሰው ጊዜያዊ የማገጃ ተዕዛዝ የሚሰጠው በክርክሩ ምክንያት በሆነው ንብረት ላይ ሆኖ ይኸው ክርክር የተነሣበት ንብረት የሚጠፋ፣ የሚበላሽ ወይም ተከሳሹ በማናቸውም ምክንያት ለሌላ አሳልፎ ለመስጠት ያቀደ መሆኑ በቃሉ መሃላ ሲረጋገጥ ሲሆን፤

ሁለተኛው ደግሞ ጊዜያዊ የዕግድ ትዕዛዝ ይሰጥበት የሚባለው ንብረት የክርክሩ ምክንያት (መነሻ) ባይሆንም ተከሳሹ የባለመብቶችን ጥቅም ለመጉዳት ሲል ንብረቱን ለማጥፋት፣ ለሌላ ሰው አሳልፎ ለመስጠት ያቀደ የዛተ ወይም ያሰበ መሆኑ የተረጋገጠ እንደሆነ ነው፡፡

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 157 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ ጊዜያዊ የዕግድ ትዕዛዝ ከሳሹ በቃለመሃላ በሚያረጋግጠው አቤቱታ መነሻ በመሆኑ ተከሳሹ በቃለ መሃላ የተዘረዘሩት ፍሬ ነገሮች በእውነት ላይ የተመረኮዙ አይደለም በማለት የሚያስተባብል ከሆነ አስቅድሞ የተሰጠውን የዕግድ ትዕዛዝ ማስነሳት የሚቻልበት ሥርዓትም በቁጥር 158 ተቀምጧል፡፡

በፍርድ ማስፈፀም ሂደት ንብረት ስለማስከበር

ፍርድ የተፈረደበት ወገን በቁጥር 386 እንደተደነገገው እንድ ፍርዱ የማይፈፀምበትን ምክንያት ካላስረዳ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 386(3) እና 392(1) መሠረት ፍርዱ እንዲፈፀም ወዲያውኑ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡

ፍርድ የሚፈፀመውም የፍርድ ባለዕዳውን ንብረት በማስከበርና በማሸጥ ነው፡፡

የፍርድ ባለገንዘቡም በዚህ አኳኋን ይፈፀምለት ዘንድ ከላይ እንዳየነው ከፍርዱ በፊት ያሳገደውንም ሆነ ለፍርድ አፈፃፀም ሊውል ይችላል የሚለውን የፍርድ ባለዕዳ ንብረት ዝርዝር ያቀርባል፡፡

በፍርድ አፈፃፀም ሂደት መጓተት እንዳያስከትል እንዲያዝና እንዲሸጥ ተብሎ የቀረበው የንብረት ዝርዝር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 404 ከተመለከቱት ውጭ መሆናቸውንና በእርግጥም በፍርድ ባለዕዳው ባለቤትነት የሚገኙ ስለመሆናቸው በሚቻለው መንገድ ሁሉ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

በፍርድ አፈፃፀም ምክንያት ንብረት እንዲያዝና እንዲከበር የማድረጉ ተግባር አፈፃፀሙን በያዘው ፍ/ቤት ብቻ ሣይሆን በሌሎች ፍ/ቤቶችም ተይዞ እና ተከብሮ የተገኘ እንደሆነ ጉዳዩ በምን አኳኋን እንደሚታይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 413 ተመልክቷል፡፡ ቁጥር 413 “… ንብረቱ የተያዘው በፍ/ቤት የሆነ እንደሆነ ሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ይህንኑ ንብረት አስቀድመን አስይዘናል፤ አስከብረናል በማለት የቀዳሚነት መብት አለን በማለት ክርክር ያነሱ እንደሆነ ክርክሩ የሚወሰነው ንብረቱን ይዞ በሚገኘው ፍርድ ቤት ነው፡፡” በማለት ደንግጓል፡፡

አንድ ንብረት አስቀድሞ በፍ/ቤት በመከበሩ ምክንያት የተፈረደ ፍርድ ሳይፈፀም ይቀራል ማለት እንዳልሆነ ይኸው ድንጋጌ አስረጂ ቢሆንም፤ ክርክሩ በየትኛው ፍ/ቤት ይታያል ለሚለው ግን ሁሉንም ጉዳይ የሸፈነ አይደለም፡፡

በመጀመሪያ ንብረቱን የያዘው የከፍተኛው ፍ/ቤና ሆኖ በተለያየ ምክንያት አፈፃፀሙ በመጓተቱ የተነሣ በወረዳው ፍ/ቤት ውሣኔ መሠረት እንዲፈፀም የተከበረ መሆኑ ቢታወቅ እንደ ቁጥር 413 ድንጋጌ ይዘት በባለገንዘቦች መካከል የሚነሳው የቀዳሚነት መብት ክርክር በወረዳው ፍ/ቤት ይታያል እንደማለት ነው፡፡

በእርግጥ ይህ አይነቱ ክርክር እንዳይከሰት በቁጥር 378/መ/ መሠረት አፈፃፀሙን ለከፍተኛው ፍ/ቤት ቢመራው የተመረጠ ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ድንጋጌው ቀጥተኛ ምላሽ አይሰጥም፡፡

ፍ/ቤቶቹ አቻ ከሆኑ ችግር የሚያስከትል መስሎ አይታይም፡፡ ላይና ታች ከሆኑ ግን ድንጋጌው ትርጉም ያሻዋል፡፡ ይኸው ድንጋጌ የተወሰደው ከህንድ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 63 እንደሆነ ከይዘቱ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚሁ የህንድ ድንጋጌ የአቻነት ሥልጣን ባላቸው ፍ/ቤቶች ንብረቱ ተከብሮ በሚገኝበት ጊዜ ቀድሞ ንብረቱን ባስከበረው ፍ/ቤት፤ የሥልጣን ደረጃቸው እኩል ባልሆነ ፍ/ቤቶች ንብረቱ ተከብሮ በሚገኝበት ጊዜ ደግሞ ሥልጣኑ ከሁሉም ከፍ ብሎ በሚገኘው ፍ/ቤት ክርክራቸው ታይቶ እንደሚወሰን ተመልክቷል፡፡ የቁጥር 413 ድንጋጌ በዚህ መሠረት ተብራርቶ የተቀረፁ ባለመሆኑ ላላስፈላጊ ሙግቶች በር ከፋች ነው፡፡

ክርክሩን አይቶ ለመወሰን የሚችለው ፍ/ቤት የትኛው እንደሆነ ከተለየ በኋላ ጉዳዩ ታይቶ የሚወሰነው በፍ/ብ/ሥ/ሕ/ቁ 403 መሠረት ነው፡፡

የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 403 በአንድ የፍርድ ባለዕዳ ላይ ቁጥራቸው ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ የፍርድ ባለገንዘቦች በቀረቡ ጊዜ እና የሁሉንም ገንዘብ ጠያቂዎች ፍላጐት ይኸው የፍርድ ባለዕዳው ንብረት/ገንዘብ የማይሸፍን ሆኖ በተገኘ ጊዜ የፍርድ ባለዕዳን ሃብት እንዴት ማከፋፈል እንደሚቻል የሚሸፍን ክፍል ነው፡፡

የድንጋጌው ዓላማም ሁለት ገፅታ አለው፡፡

1ኛ/ አላስፈላጊ የሆነና የተነጣጠለን የአፈፃፀም ክስን ለማስቀረት፣

2ኛ/ ሁሉንም ገንዘብ ጠያቂዎች በእኩል ደረጃ በማስቀመጥ ፍትሃዊ የንብረት

    ክፍፍል ለማድረግ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በተለያዩ የሕግ ክፍሎች እንደተደነገገው ሁሉም ገንዘብ ጠያቂ በእኩል ደረጃ ይገኛል ማለት አይደለም፡፡

ከዚህ በቀር የቀዳሚነት መብት አለን የሚሉ ወገኖች በቀረቡ ጊዜ ከላይ እንደተመለከተው ጉዳዩ የሚታየው አግባብነት ባላቸው ድንጋጌዎች መሠረት ይሆናል፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 167 “በቅጥር ላይ ከተመሠረተ የሥራ ግንኙነት የሚመነጭ ማንኛውም የሠራተኞች የክፍያ ጥያቄ ከማናቸውም የክፍያ ወይም የዕዳ ጥያቄ ቅድሚያ ይኖረዋል፡፡” በማለት የዕዳ ክፍያ ቅድሚያነቱን የደነገገ በመሆኑ እንደ ሕጉ አነጋገር ከሌሎች ገንዘብ ጠያቂዎች ቀድሞ እንደ ፍርድ እንዲፈፀም የማድረግ መብት አለው፡፡

የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 80/1/ “ዋስትና የተሰጣቸው የሌሎች አበዳሪዎች የቅድሚያ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ አዋጅ መሠረት ግብር ተከፋይ ከሚሆንበት ቀን አንስቶ ተከፍሎ እስካለቀበት ጊዜ ድረስ ግብር የመክፈል ግዴታ ባለበት ሰው ሃብት ላይ ባለሥልጣኑ ከማናቸውም ሌሎች ዕዳዎች የቀደምትነት መብት ይኖረዋል፡፡” በማለት የተደነገገ በመሆኑ በመያዣ ምክንያት በፍ/ብሔር ሕጉ ከቁጥር 3059 እና ተከታዮች የተሰጠው የቀዳሚነት መብት የተጠበቀ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ስለሆነም ባለመያዣ የሆነው የፍርድ ባለመብት በግብር ምክንያት ባለመብት ከሆነው ከመንግስት ቀድሞ ዕዳውን የመሰብሰብ መብት ያለው መሆኑን ያስረዳል፡፡ የአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ ጥቅል አባባል የያዘ 80 “… ለማናቸውም ሌሎች ዕዳዎች …” የሚል ጥቅል አባባል የያዘ ሐረግ ስለሰፈረበት በአዋጅ ቁጥር 377/96 ቁጥር 167 ጋር ይቃረናል፡፡ እንደዚህ በሆነ ጊዜ በዕኩል ደረጃ የሚገኙ ሕጐች አንድን ጉዳይ በተለያየ መንገድ ደንግገው በተገኙ ጊዜ በዚህም የተነሣ ሕጐቹ እርስ በእርሳቸው ከተቃረኑ በኋላ የወጣው ሕግ ከበፊተኛው በልጦ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡ በሚለው የሕግ አተረጓጐም መርህ መሠረት በአሠሪና  ሠራተኞች ጉዳይ የሚጠየቀው የዕዳ ክፍያ ጥያቄ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡

ስለማይከበሩና በፍርድ አፈፃፀም ምክንያት ስለማይወሰዱ ሀብቶች

ፍርድ የሚፈፀመው የባለዕዳውን ንብረት በማስከበርና በማሸጥ ቢሆንም ፍርድን ለማስፈፀም ሲባል የማይከበሩና በፍርድ አፈፃፀም ምክንያት ሊወሰዱ የማይችሉት ንብረቶች ዓይነትና መጠን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 404 ሥር ተዘርዝረዋል፡፡ ከሚከተሉት ሁለት ንዑስ አንቀጾች በስተቀር ድንጋጌው በእራሱ ግልፅ በመሆኑ ማብራሪያ የሚያስፈልገው መስሎ አይታይም፡፡

በቁጥር 404/ለ/ “ለዕለት ሞያ ሥራዎቹ አገልግሎት ለንግድ ሥራው ማከናወኛ ተገቢ የሆኑ ዕቃዎች ከሚለው ድንጋጌ “ዕቃዎች” የሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም ሊያሰጥ በሚችል አኳኋን ይጠቀስ እንጂ የዚሁ ግልባጭ ከሆነው የእንግሊጨኛ ንባብ ጋር አጣቅሰን ካየነው ተገቢ የሆኑ የመገልገያ መሣሪያዎች ለማለት ተፈልጐ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በንዑስ ፊደል ሠ “ለጡረታው የሚከፈለው ገንዘብ ...” የሚለውን ድንጋጌ ስለጡረታ ጉዳይ ከደነገገው የጡረታ ሕግ አዋጅ ቁጥር 345/95 አንቀጽ 45 ጋር ተገናዝቦ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡

ለጡረታው የሚከፈለው ገንዘብ እንደማይከበር በፍርድ አፈፃፀም ምክንያት እንደማይያዝ በቁጥር 404 የተገለፀ ቢሆንም በመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 345/95 አንቀጽ 45 ላይ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ተደንግጓል፡፡ ይኸውም በአንቀጽ 45 ከጡረታ አበሉ እንዲከፈል የተጠየቀው ዕዳ ለመንግስት ገቢ የሚሆን መቀጮ፣ ግብር ወይም ቀረጥ ለመክፈል ወይም አግባብ ባላቸው የፍ/ብሔር ድንጋጌዎች መሠረት የተወሰነ ቀለብ የመስጠት ግዴታ ለመወጣት በፍርድ ቤት የታዘዘ እንደሆነ የጡረታ አበሉ ሊከበር እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

የጡረታ አበል በዕዳ ምክንያት ሊከበር እና ሊያዝ የሚችል የመሆኑና የአለመሆኑ ጉዳይ በተለያዩ ሕጐች በተለያዩ ሁኔታ ተደንግጐ ከተገኘ በሕግ አተረጓጐም ዘዴ መሠረት ስለጡረታ ጉዳይ በተለይ የሚደነግገው የጡረታ አዋጁ በመሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉ በልጦ ተፈፃደሚነት ሊኖረው የሚችል ከመሆኑም በላይ በኋላ የወጣ እንደመሆኑ ተፈፃሚነት የሚኖረው ይኸው የጡረታ ሕግ ነው ወደ ሚለው መደምደሚያ ሊያደርሰን ይችላል፡፡

የጡረታ አበል በፍርድ ምክንያት ሊያዝ አይገባውም የተባለው መተዳደሪያው በመሆኑ ነው፡፡ ለመተዳደሪያው ሲል ለሕይወቱ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ሲል ባመጣው ዕዳ ምክንያት ፍርድ አርፎበት ከተገኘ ይህንኑ ዕዳ ለማስፈፀም የጡረታ አበልን ማስከበር ምን ይከለክላል? የቁጥር 404/ሠ/ ድንጋጌ ይህን ጉዳይ ሊሸፍን የሚችል አይደለም የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ በተለይም ይህንኑ ጥያቄ ለአብነት ያህል ከተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አዋጁ ቁጥር 213/92 አንቀጽ 205/3/ “. . . ለቀለብ ተቀባዩ ኑሮ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለማግኘት ሲባል የመጣ ዕዳ መሆኑ ከተረጋገጠ የቀለብ ገንዘብ ሊተላለፍና ሊያዝ እንደሚችል ከተደነገገው ጋር ተገናዝቦ ከታየ የቀለብ ገንዘብ ማለት ለጡረታ የሚከፈል ገንዘብ እስከሆነ ድረስ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 404/ሠ/ ገዳቢ የሆነ ድንጋጌ መስሎ አይታይም፡፡

በተከበረ ንብረት ላይ የሚቀርብን አቤቱታ ስለመመርመር /418 – 421/

ለአፈፃፀም ክስ መዘግየት ዐበይት ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ በአፈፃፀም ምክንያት ንብረት እንዳይያዝ ወይም እንዳይከበር በሚቀርበው አቤቱታ መነሻ የሚደረገው ክርክር ነው፡፡

ይኸው አቤቱታ ያለበቂ ምክንያት ሳይዘገይ ከቀረበ እና ተቃዋሚው ወይም መብት አለኝ ባዩ በተያዘው ወይም በተከበረው ንብረት ላይ ያለውን የቀዳሚነት መብት ወይም ባለይዞታነቱን የሚያረጋግጥ የፅሑፍ ማስረጃ አያይዞ ማቅረቡ ከተረጋገጠ አፈፃፀሙን የያዘው ፍ/ቤት ጉዳዩን ይመረምራል፡፡ በአቤቱታው መነሻ ጉዳዩ ሊመረመር ይገባል ከተባለ የተከበረው ንብረት የማን ነው? የፍርድ ባለዕዳው ወይስ መቃወሚያ ያቀረበው ነው? ወደ ሚለው ክርክር ማምራቱ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህም ነው አቤቱታ አቅራቢው ወይም ተቃዋሚው በመጀመሪያው ክስ ተካፋይ እንደሆነ በመቁጠር አፈፃፀሙን የያዘው ፍ/ቤት ጉዳዩን መመርመር አለበት በሚል የተቀመጠው፡፡

በዚህ ረገድ ጐልተው ከሚታዩት ክርክሮች መካከል የፍርድ ባለዕዳው ሚስት/ባል ለፍርድ ምክንያት የሆነው ተግባር የተፈፀመው ወይም ዕዳው የመጣው እኔ ሳላውቀው በመሆኑ ለጉዳዩ አግባብነት ባለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት አንደኛው ተጋቢ በግሉ በመጣው ዕዳ ምክንያት በጋራ ሃብታችን ላይ አፈፃፀም ሊቀጥል አይገባም፡፡ ይህ እንኳ ቢታለፍ ድርሻ ሃብቴ ሊነካብኝ አይገባም በሚል የሚቀርበው አቤቱታ ነው፡፡

ለዚሁ ዓይነት ክርክር አግባብነት ያለው የቤተሰብ ሕግ በአንድ በኩል የሰለጠ የሥራ/የንግድ እንቅስቃሴ /Business transaction/ እንዲኖር በመፈለግ፤ በሌላ በኩል በትዳር ምክንያት የተፈጠረን የጋራ ሃብት ላይ ጥበቃ በማድረግ ረገድ ያለውን ሚዛን በማጣጣም የተቀረፀ መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 418 መሠረት አቤቱታ የሚያቀርቡት ወገኖች የተከራካሪ ወገኖችን ማንነት በመለየት የክርክርን አድማስ በመወሰን በኩል በተቀመጡት ድንጋጌዎች /በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 41, 42, 358 . . ./ መሠረት የክርክሩ ተካፋይ መሆን የሚገባቸው ወገኖች ከሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 418 መሠረት ገብተው በመከራከር መብት አላቸው ወይስ የላቸውም? የሚለው ጥያቄ ትኩረት የሚያሻው ነው፡፡

የሐራጅ ሽያጭ ሥነ - ሥርዓት

በቀጥታ ወይም በተለዋዋጭ ገንዘብ እንዲከፈል የተሰጠ ማናቸውም ፍርድ ወይም ውሣኔ የሚፈፀመው የባለዕዳውን ንብረት በማስከበርና በማሸጥ ሲሆን፤ ማናቸውም ሃብት ወይም ንብረት የሚሸጠውም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 422/3/፣ 427 እና 439 የተመለከቱት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው የሐራጅ ሽያጭ በማድረግ ነው፡፡

ለፍርድ ማስፈፀሚያ ተብሎ የሚሸጠውም ንብረት በቁጥር 394/2/ እና 422/1/ እንደተደነገገው ከሚፈለገው የዕዳ መጠን ጋር በተቻለ መጠን ተመጣጣኝ መሆኑን ማረጋገጥ በተከታዩ እንደምናየው ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 428/2/ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር ለማስቀረት ይረዳል፡፡

ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 428 ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚታዩ ችግሮች

ይኸው ድንጋጌ ለትርጉም በር በሚከፍት ሁኔታ የተቀረፀ ከመሆኑ የተነሣ ድንጋጌውን በሥራ ላይ በማዋል ረገድ ከፍርድ ቤት ፍርድ ቤት አልፎ አልፎም በአንድ ፍ/ቤት በሚገኙ የተለያዩ ችሎቶች ለድንጋጌው የተለያዩ ትርጉም በመስጠት በተመሣሣይ ጉዳይ የተለያዩ ውሣኔ ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡

ለዚህም ወጥ ያልሆነ አሠራር እንደ ምክንያትነት የሚወሰደው በቁጥር 428/1/ “በዚህ ሕግ በቁጥር 423/2/ በተመለከተው መሠረት በሚሰጠው ማስታወቂያ የተገለፀውን የዋጋ ግምት የሚከፍል ገዥ ያልተገኘ እንደሆነ ድጋሚ ማስታወቂያ በማውጣት ሁለተኛ ጨረታ ይደረጋል፡፡” ከሚለው ፓራግራፍ “በማስታወቂያ የገለፀውን የዋጋ ግምት የሚከፍል ገዥ ያልተገኘ እንደሆነ . . .” የሚለው አባባል ለመግዛት ተጫራƒች ቀርበው ነገር ግን የግምቱን መነሻ ዋጋ ባለመጥራታቸው ነው? ወይስ ጭራሹኑ የሐራጅ ሽያጩ በሚደረግበት ጊዜና ቦታ ተጫራች ባለመገኙቱ? ለሚለው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ የማይሰጥ በመሆኑ ነው፡፡

በተለይም የመጀመሪያ ደረጃ ሽያጭ ተደርጐ ገዥ አልተገኘም ከሚል መደምደሚያ ላይ ከተደረሰ በሁለተኛ ሐራጅ ሽያጭ ጊዜ ንብረቱ የሚሸጠው ከግምቱ ዋጋ በታች ቢሆንም ከፍተኛ ዋጋ ላቀረበው ገዥ በመሆኑ ከላይ የተቀመጠውን ጥያቄ ይበልጥ የተወሳሰበ ያደርገዋል፡፡

“. . . Where the highest bid at a sale by auction . . .” የሚለው የእንግሊዘኛ ግልባጭ በሐራጅ ሽያጭ ጊዜ በጨረታ የተገኘው ከፍተኛ ዋጋ በማለት የተቀመጠ በመሆኑ በመጀመሪያው የሐራጅ ሽያጭ ጊዜ ገዥዎች ቀርበው ውድድር ያደረጉ መሆኑን ነገር ግን ከግምቱ መነሻ በታች የሆነ የግዥ ዋጋ በማቅረባቸው ምክንያት ሽያጩ ሊከናወን ያልቻለ መሆኑን የሚያመለክት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ለተለያዩ አተረጓገም ምክንያት ሆኖ ይገኛል፡፡

የ1958ቱ ዓ.ም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ከመውጣቱ በፊት በነበረው የሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር 176/45 አንቀጽ 22 ደግሞ “በዚህ ደንብ እንደተመለከተው በአደባባይ በሚደረገው የሐራጅ ሽያጭ ጊዜ ተጫራƒች ያቀረቡት ከፍተኛ ዋጋ በመሐንዲሱ ወይም ግምት አዋቂው ሰው ወይም ጉባኤው ከገመተው ዋጋ ያነሰ እንደሆነ . . . የሽያጩ ማስታወቂያ እንደገና ይደገማል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በድጋሚው የሐራጅ ሽያጭ ጊዜ በጨረታ የቀረበው ከፍተኛ ዋጋ ከግምቱ ቢያንስም በዚያው በቀረበው ዋጋ ይሸጣል፡፡” በሚል ተደንግጐ የነበረና ይህም የበፊተኛው ሕግ ይዘት አሁን በሥራ ላይ ካለው ሕግ የእንግሊዘኛ ግልባጭ /version/ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ መገኘቱ /የአማርኛው ግልባጭ ገዥነት ያለው ድንጋጌ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ድንጋጌው ትርጉም የሚያሻው መሆኑን አመላካች ነው፡፡

በመሆኑም ከትርጉም ሥራ የተነሣ ሊነሱ የሚችሉትን የክርክር መስመሮች /የመከራከሪያ ሐሳቦች/ እንመልከት፡፡

አንደኛው፡- በቁጥር 423/2/ በተመለከተው መሠረት በሚሰጠው ማስታወቂያ የተገለፀውን የዋጋ ግምት የሚከፍል ገዥ ካልተኘ ድጋሚ ማስታወቂያ በማውጣት ሁለተኛ ጨረታ እንደሚደረግና ንብረቱም የሚሸጠው በሁለተኛ ጨረታ ጊዜ ከፍተኛ ዋጋ ለሚያቀርብ ተጫራች እንደሆነ በግልፅ ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም “ . . . የሚከፍል ገዥ ያልተገኘ እንደሆነ . . .” የሚለው አባባል በመጀመሪያው ሐራጅ ጊዜ ተጫራች የግድ መቅረብ እንዳለበት የሚያመለክት አይደለም፡፡

በተደረገው ጥሪ መሠረት በዋጋው መነሻ ንብረቱን የሚገዛ ተጫራች በግንባር ካልቀረበ የመጀመሪያ ሐራጅ እንደተደረገ መቆጠር አለበት፡፡ አለበለዚያ የመጀመሪያ ሐራጅ ተደርጓል ለማለት ተወዳዳሪ ቀርቦ ፉክክር ከተደረገ በኋላ በማስታወቂያው ላይ የተገለፀውን የዋጋ ግምት የሚከፍል ገዥ ያልተገኘ እንደሆነ ብቻ ነው የምንል ከሆነ ተወዳዳሪ እስከሚቀርብ ድረስ ለምን ያህል ጊዜ ነው፡ የመጀመሪያ ማስታወቂያ እያልን ተከታታይ ትዕዛዝ የምንሰጠው? መዳረሻውስ የት ነው? ባለዕዳ ዕዳውን እንዲከፍል ባለገንዘቡም ገንዘቡን እንዲያገኝ ማድረግ ይቻል ዘንድ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ዓላማስ አንፃር ይኸው አካሄድ ይደገፋል ወይ? በመጀመሪያው የሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያ የሚደረገው የሽያጭ ግብዣ በቁጥር 423/2//ሀ/ መሠረት በተቀመጠው የዋጋ መነሻ እስከሆነ ድረስ ከዚህ ዋጋ በታች ለመጥራት ሲሉ የሚቀርቡት ተጫራƒች ከእነ አካቴው /ጭራሹኑ/ ካልቀረቡትስ በምን ይለያሉ፡፡ በመሆኑም በመጀመሪያው የጨረታ ማስታወቂያ መሠረት ተወዳዳሪ ቀርቦ በማስታወቂያው ላይ የተገለፀውን የዋጋ ግምት ሊከፍል አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን በማስታወቂያው በተገለፀው ጊዜና ቦታ ጭራሹኑ ገዥ ካልተገኘ የመጀመሪያ ሐራጅ እንደተደረገ በመቁጥር ድጋሚ የጨረታ ማስታወቂያ በማውጣት ሁለተኛ ጨረታ መደረግ አለበት፡፡ ንብረቱም የሚሸጠው ከንብረቱ ግምት ዋጋ በታች ቢሆንም ከፍተኛ ዋጋ ላቀረበው ተጫራች ነው የሚለው ነው፡፡

ሁለተኛው የክርክር መስመር ደግሞ፡-

በድንጋጌው የእንግሊዘኛ ግልባጭ “በጨረታ የተገኘው ከፍተኛ ዋጋ . . .” የሚለውን ሐረግና የመጀመሪያ ጨረታ ተደርጓል ካልን የሚያስከትለውን ውጤት መነሻ የሚያደርግ ነው፡፡

 “. . . በጨረታ የተገኘው ከፍተኛ ዋጋ . . .” የሚለው አነጋገር ተወዳዳሪ ቀርቦ ጨረታ የተከናወነ መሆኑን ነገር ግን አሸናፊው የግምቱን መነሻ ዋጋ የሚከፍል ሆኖ አለመገኘቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለሆነም ንብረቱን በሐራጅ ለማሸጥ ማስታወቂያ በመጣበት ቀን አንድም ተጫራች ሳይቀርብ ቢቀር ንብረቱ በሐራጅ እንደሚሸጥ ለሕዝብ በማስታወቂያ መግለፅ ብቻውን የመጀመሪያ ጨረታ እንደተደረገ አያስቆጥርም፡፡ የመጀመሪያ ጨረታ ሳይኖር ሁለተኛ ጨረታ ለማለት አይቻልም፡፡ በመጀመሪያው የሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያ ላይ በተገለፀው ጊዜና ቦታ ተጫራች ሳይቀርብ ቀርቶ በድጋሚ ማስታወቂያ መሠረት ተጫራች ቢቀርብ ጨረታው የመጀመሪያ ነው ከሚባል በስተቀር ሁለተኛ ጨረታ ሊባል አይችልም፡፡ በዚህ ጊዜ ንብረቱም የሚሸጠው የዋጋውን ግምት መነሻ በማድረግ ነው፡፡

በሁለተኛው ጨረታ ማስታወቂያ ላይ በተወሰነው ቀን ተጫራች ያልቀረበ እንደሆነ ማናቸውም ተቃራኒ ድንጋጌ ቢኖርም እንኳ ይህን ንብረት የፍርድ ባለገንዘቡ ተረክቦ እንዳይዝ ማድረግ እንደሚቻልና ይህም በሆነ ጊዜ እንደነገሩ አካባቢ ሁኔታ ዕዳው በሙሉ ወይም በከፊል እንደተፈፀመ እንደሚቆጠር በቁጥር 428 ንዑስ ቁጥር 2 ውጤቱ ተቀምጧል፡፡ በቁጥር 423/1/ መሠረት የሚሸጠው ንብረት የሚጠየቀውን ዕዳ ለመሸፈን የሚያስችለውን ክፍል መሆኑን በማረጋገጥ፤ ወይም ደግሞ በቁጥር 394/2/ መሠረት በአፈፃፀም እንዲሸጥ የተባለው ንብረት በተቻለ መጠን በፍርዱ ላይ ከተገለፀው የገንዘብ ልክ ጋር ተመዛዛኝ መሆኑን በማየት የአሻሻጥ ሥርዓቱን የምንከተል ከሆነ በቁጥር 428/2/ መሠረት እንዲፈፀም የማድረጉ ተግባር ተከታይ ችግር ሊያስከትል አይችልም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህንኑ ሥርዓት ካልተከተልንና የንብረቱ ግምት በልጦ የሚፈለገው ዕዳ አነስተኛ ከሆነ ስለዕዳው ባለገንዘቡ ንብረቱን እንዲረከበው የማድረጉ አሠራር በባለዕዳው ዘንድ ፍትህን ያጓድላል፡፡ በንብረቱ ግምት እና በሚፈለገው ዕዳ መጠን መካከል ያለውን ልዩነት የፍርድ ባለመብቱ በጥሬ ገንዘብ ለባለዕደው ይከፈለው እንዳይባል ባለገንዘቡ ያስፈረደውን በገንዘብ መሰብሰብ እንጂ ከፈቃዱ ውጭ ግዥ ለመፈፀም የቀረበ ባለመሆኑ ላልታሰበ ዕዳ ሊዳርገው በሚችል አኳኋን ያልፈለገውን ንብረት ተረክቦ እንደገና ገንዘብ እንዲመልስ ማድረጉም ፍትሃዊ አይሆንም ስለሆነም እንደዚህ ዓይነት ችግር እንዳይከተል የአሻሸጥ ሥርዓቱን መነሻ እንደህጉ አነጋገር መስመር ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ታልፎ ከዚህ ደረጃ የምንደርስ ከሆነ ግን ከተቻለ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 439 መሠረት እንዲፈፀም ማድረግ፤ ይህ የማይሆን ከሆነ በቁጥር 428/2/ የተመለከተው ድንጋጌ ፈቃጅ እንጂ አስገዳጅ ባለመሆኑ በፍ/ቤቱ አስተያየት ሌሎች አማራጮችን ከመፈለግ በስተቀር እንደ ቁጥር 428/2/ የግድ መፈፀም አለበት ወደ ሚለው መደምደሚያ የሚያደርሰን መስሎ አይታይም፡፡

ምንጭ

ይህ ጽሑፍ በፍትህ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠና ማዕከል ለወረዳ ዳኞችና ዐቃብያነ -ህግ የቀድመ ሥራ ሥልጠና ከተዘጋጀ ሰነድ የተወሰደ ሲሆን ጸሐፊው ተሻገር ገ/ሥላሴ ነው፡፡