Font size: +
10 minutes reading time (2017 words)

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሕገ-መንግሥታዊነት

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መንግሥት የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን የሚያቋቁም አዋጅ ማፅደቁ ይታወቃል፡፡ አዋጁ በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የጦፈ ክርክርን አስነስቶ በ33 ተቃውሞ እና በ4 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ቢፀድቅም በፓርላማ ውስጥ ለአዋጁ ድምፅ ከነፈጉ የሕዝብ ተወካዮች ጀምሮ እስከ ክልል መንግሥታት ድረስ ሰፊ ተቃውሞን አስተናግዷል፡፡ ለተቃውሞው መነሻ የሆነው ዋነው ጉዳይ የማንነትም ሆነ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን መፍታት የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የክልሎች ሥልጣን ሆኖ ሳለ ሌላ ተቋም የማቋቋም አስፈላጊነት እና ሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ ነው፡፡

ለእነዚህ ጉዳዮች በሕግ አግባብ መልስ ለመስጠት ሁለት ጉዳዮችን በጥልቀት ማገናዘብ ይጠይቃል፡፡ አንደኛው እና መሠረታዊው ጉዳይ በሕገመንግሥቱ እና በሥራ ላይ በነበሩ ሕጎች  መሠረት የማንነት እና ራስን የማስተዳደር ጥያቄዎች እንዲሁም በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች የሚፈቱበት ሥርዓት ምን እንደሆነ መፈተሸ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለኮሚሽኑ የተሰጠውን ሥልጣን እና ተግባር ከሕገ-መንግሥቱ ጋር በንፅፅር አይቶ ሕገ መንግሥታዊነቱን መመርመር ነው፡፡

የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች

በሕገ መንግሥቱ መሠረት የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን የመፍታተት ሥልጣን በመሰረታዊነት የተሰጠው ለክልሎች (ምክር ቤት) ነው፡፡ ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ከመደንገጉም በላይ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 እንደተቀመጠው ክልሎች ለቀረበላቸው ጥያቄ በአንድ ዓመት ውስጥ አጥጋቢ መልስ ካልሰጡ ጥያቄው በይግባኝ መልክ ለፌዴሬሽ ምክር ቤት ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ማግኘት ይችላል፡፡

በመሠረቱ በማንነት እና ራስን በራስ በማስተዳደር ጥያቄዎች መሀል ምን ልዩነት እና አንድነት እንዳለ በግልፅ ያስቀመጠ ሕግ የለም፡፡ በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎችም ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እንጂ ‹የማንነት ጥያቄ› በሚል አገላለፅ የተቀመጠ መብትም ሆነ ሥርዓት የለም፡፡ ከዚህ ባለፈም በአንዳንዶች ዘንድ በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን አለመግባባቶች እና በማንነት ጥያቄዎች መካከል ያለውን ልዩነት ያለመረዳት ስህተት ይስተዋላል፡፡ በዚህ ላይ የሚነሱ ክፍተቶች እና አከራካሪ ጉዳዮች በሌላ ሰፊ ጽሑፍ ቢታዩ ተመራጭ ስለሆነ ዝርዝሩን በመተው ወደ ቀጣዩ ጉዳይ እናልፋለን፡፡

በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን አለመግባባቶች የሚፈቱበት አሠራር

በሁሉም የፌደራል ሥርዓት በሚከተሉ ሀገራት እንደተለመደው በክልሎች መካከል የሚነሱ ማንኛውም አለመግባባቶች የሚፈቱት ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮችን እንዲዳኝ ሥልጣን በተሰጠው አካል በኩል ነው፡፡ በዚህም አብዛኞቹ ፌደራላዊ ሀገራት በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የሚፈቱት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ወይም በሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች በኩል ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ፌደራላዊ አገራት ይህን ሥልጣን (በተጓዳኝ ወይም በዋናነት) ከፍርድ ቤት ውጪ ለሆኑ ተቋማት ሲሰጡ ይስተዋላለል፡፡ ለዚህ ዋና ምሳሌ ሊሆን የሚችለው የሕገ መንግሥት ክርክሮችንም ሆነ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በላይኛው (የፌዴሬሽን) ምክር ቤት እንዲወሰኑ ያደረገው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ነው፡፡ ሆኖም እንደ ህንድ እና ስዊዘርላንድ ያሉ ፌዴሬሽኖችም ጠቅላይ ፍርድ ቤቶቻቸው ካላቸው የዳኝነት ሥልጣን በተጓዳኝ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች በግልግል ችሎቶች እና በድንበር ኮሚሽኖች የሚፈቱበትን ሥርዓት ዘርግተዋል፡፡ ይህም አለመግባባቶቹ በመደበኛ የፍርድ ሂደት ሲዳኙ በክልሎች መካከል ጠላትነት እና ፉክክር እንዳይፈጠር በማሰብ ጉዳዮቹን በስምምነት ለመፍታት የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡

ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ደግሞ ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮችን ለመዳኘት ስልጠን የተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የመፍታት ኃላፊነትም ተጥሎበታል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62/6 ምክር ቤቱ ማንኛውንም ዓይነት በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የሚፈታበትን ሥልጣን ሲሰጠው አንቀጽ 48 ደግሞ በተለየ መልኩ በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን (የድንበር) አለመግባባቶችን እንዲዳኝ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ (በሌሎች ፌዴሬሽኖች በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች በወሰን ምክንያት ብቻ ሳይሆን በግብር አሰባሰብ እና እንደ ወንዝ ባሉ የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም ዙሪያም ሊነሱ ይችላሉ)፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ የሚኖርበት ጉዳይ በአንቀጽ 48 መሠረት ምክር ቤቱ የወሰን አለመግባባቶችን የሚያየው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክልሎች አለመግባባቱን በስምምነት መፍታት ካልቻሉ ብቻ ነው፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን አለመግባባቶችን የሚወስነው የሕዝብ አሰፋፈርን እና ፍላጎት መሠረት አድርጎ እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ቅድሚያ የሚሰጠው መስፈርት የሕዝብ ፍላጎት ይሁን የአሰፋፈር ሁኔታ በግልፅ አልተቀመጠም፡፡ ሆኖም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር እና ሥልጣን እና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 28 ላይ እንደተቀመጠው ምክር ቤቱ የሕዝብ ፍላጎትን ከግምት የሚያስገባው የሕዝብ አሰፋፈርን በማጥናት አከራካሪው አከባቢ ወዴት መካለል እንዳለበት መወሰን ያልተቻለ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ የህዝቡ ፍላጎት የሚታወቀው በህዝበ ውሳኔ መሠረት መሆኑን ይህ አዋጅ ያስቀመጠ ሲሆን አከራካሪው አከባቢ  አብላጫው ሕዝብ ድምፅ ወደሰጠበት ክልል ወሰን ይካለላል፡፡ ይህ አሰራር መሰረታዊ የዴሞክራሲ መርሆችን ያገናዘበ ቢሆንም የታሪክ ማስረጃዎን ያማከል ውሰኔ ለመስጠት ባለማስቻሉ ወቀሳ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡

በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጠው ሥርዓት በተጨማሪ በ1994 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 256/1994 የተቋቋመው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች የሚፈቱባቸውን ሁኔታዎች እንዲያመቻች ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ እና ከሌሎች የተቋሙ ኃላፊነቶች ለመረዳት እንደሚቻለው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በክልሎች መካከል ያለውን የበይነ-መንግሥታት ግንኙነትት (Inter-Governmental Relations) የሚያሳልጥ ተቋም እንዲሆን የተቋቋመ ነው፡፡ ይህ ተቋም አሁን ሰላም ሚኒስቴር በሚል እንደ አዲስ የተዋቀረ ሲሆን በዚህ ረገድ የነበረው ሥልጣን እንዳለ ቀጥሏል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር ያለው ሥልጣን በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን መፍታት ወይም መወሰን ሳይሆን አለመግባባቶቹ የሚፈቱባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት (Facilitate ማድረግ) በመሆኑ በሕገ መንግሥቱ ለክልሎች እና ፌዴሬሽ ምክር ቤት ከተሰጠው ሥልጣን ጋር አይጣረስም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የማመቻቸት ሥራ ምን እንደሆነ ትርጉም የሚሰጥም ሆነ ተቋሙ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ምን አይነት የሥራ ግንኙነት እንደሚኖረው በግልፅ የሚያስቀምጥ ሕግ የለም፡፡ (አሁን የተቋቋመው የወሰን ኮሚሽን ግን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ የመፍትሔ ሃሳቦችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለሚያቀርብበት አሠራር በግልፅ መደንገጉን ልብ ይሏል)

ይህ በመሆኑ ምክንያት የቀድሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በአሁን አጠራሩ ደግሞ የሰላም ሚኒስቴር፤ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ ያለው ድርሻ ከፌዴሬሽ ምክር ቤት ጋር ተደራራቢ ነው ወይስ ተመጋጋቢ? የሚለው ጥያቄ ቢያንስ ከሕግ አንፃር በቂ መልስ የለውም፡፡ በተግባር ግን ሚኒስቴሩ ሦስት ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ አንደኛው ግጭት መከላከል እና ማስተዳደር ሲሆን ሁለተኛው በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል ውሳኔ ያገኙ የወሰን አከላለሎችን ማስፈፀም ነው፡፡ ሶስተኛው እና የመጨረሻው ደግሞ በክክሎች መካከል የተነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት ክልልች በራሳቸው የሚያደርጉትን ድርድር እና ስምምነት ማሳለጥ ነው፡፡

ተቋሙ በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን አለመግባባቶችን በተመለከተ ሰፋ ያሉ የታሪክ ማስረጃዎችን እና የማህበረሰብ አሰፋፈር ባህሪዎችን ያካተቱ ጥናቶችን ለተከራካሪ ክልሎች በማቅረብ ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከመድረሱ በፊት መግባት ላይ የሚደርሱበትን ምክረ ሀሳብ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተከራካሪ ክልሎችውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፉ የጋራ ምክር ቤቶችን መማቋቋም ድርደሩ ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲኖረው እና ስምነቶቹም ቅቡልነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ተቋሙ ይህን ተግባሩን ሲያከናውን ብዙ ቅሬታዎች ተነስተውበት የሚያውቅ ቢሆንም ተቋሙ ካለው የባለሙያ ስብጥር እና ግጭቶችን ለመፍታት ከሚከተላቸው መርሆች አንፃር ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሸለ ውጤታማነት እንዳለው ይታመናል፡፡ እስከ አሁንም ሦስት በክልሎች መካከል የተነሱ የወሰን ውዝግቦችን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከመቅረባቸው በፊት በስምምነት (እና በፖለቲካዊ መግባባት) እንዲፈቱ አአድርጓል፡፡

ይህ አሰራር ባለበት ሁኔታ ነው እንግዲህ መንግሥት የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ያቋቋመው፡፡ ይህም በክልሎች መካለከል የሚነሱ የወሰን አለመግባባቶችን የሚመለከት ሥልጣን ያላቸውን የፌደራል ተቋማት ቁጥር ወደ ሦስት ያሳድገዋል፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ሰላም ሚኒሰስቴር እና አዲስ የተቋቋመው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን፡፡

የኮሚሽኑ አስፈላጊነት

ኮሚሽኑ በተቋቋመበት ከአዋጅ ቁጥር 1101/2011 መግቢያ ለመረዳት እንደሚቻለው መንግሥት ኮሚሽኑን ማቋቋም የፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ላሉ የወሰን ይገባኛል እና የማንነት ጥያቄዎችን ‹ገለልተኛ በሆነ ተቋም በማያዳግም እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ ማፈላለግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ› ነው፡፡ ከፓርላማ አባላት እና ከሌሎች የሕግ ባለሙያዎች የተነሳው የመጀመሪያ ተቃውሞ ‹ጉዳዩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የክልሎች ሥልጣን ሆኖ ሳለ ተጨማሪ ተቋም ያስፈለገበት ምክንያት ምንድ ነው?› የሚል ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ከሌሎች የምክር ቤት አባላት የተሰጡት ምላሾች ‹በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን ውዝግቦች እና የማንነት ጥያቄዎች ለብዙ ደም መፋሰስ እና ሰብአዊ ቀውስ መነሻ በመሆናቸው መንስኤያቸውን በሳይንሳዊ መንገድ በመተንተን እና በማጥናት አማራጭ ሃሳቦችን ለፌዴሬሽ ምክር ቤት የሚያቀርብ ተቋም ያስፈልጋል› የሚል ነው፡፡

እዚህ ጋር በዋናነት መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ቅርፅ ይዛ እንደ አዲስ ስትዋቀር በሌሎች የፌደራል አገራት እንደሚደረገው የአባል ክልሎቹን ወሰን በወረቀት እና በስምምነት የማስቀመጥ (delimitation) እና መሬት ላይ የማካለል (demarcation) ሥራ አልተሰራም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለሚነሱ የወሰን አለመግባባቶች ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደውም ፌዴሬሽኑ ሲመሠረት የወሰን ማካለል ሥራ በበቂ ሁኔታ አለመደረጉ ነው፡፡

ይህ የማካለል ሥራ ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊት ተጠናቆ የሕገ መንግሥቱ አካል መሆን የሚገባው ሲሆን ደቡብ አፍሪካ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ ሆኖም ሕገ መንግሥታቸው ከፀደቀ በኋላም ቢሆን ይህን የማካለል እና ዳግም የማዋቀር ሥራ ያከናወኑ እንደ ህንድ፣ ናሚቢያ እና ናይጄሪያ ያሉ ሀገራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመዋሃድ ፌዴሬሽኖች (Coming-Together Federations) የሚደረግ የክልሎችን ወሰን የማካለል ሥራ ብዙ ችግር ሲያመጣ አይታይም፡፡ ሆኖም ቀድሞ አዋዳዊ ሥርዓት ይከተሉ የነበሩ ሀገራት ወደ ፌዴሬሽን ሲለወጡ (Holding-Together Federations) በክልሎቹ መካከል አዲስ ወሰን ማስመርም ሆነ ማካለል ውስብስብ ችግሮች ይፈጥራል፡፡ ለዚህም ሕዝብን እና ገለልተኛ ባለሙያዎችን የሚያሳትፉ የወሰን አካላይ ኮሚሽኖችን ማቋቋም ሌሎች አገራት በስፋት የተከተሉት የተለመደ አካሄድ ነው፡፡

በመግባባት ላይ በተመሰረተው የፖለቲካ ስርአቱ የሚወደሰው ስዊዘርላንድ ፌዴሬሽን በክልሎቹ (በካንቶኖቹ) መካከል የወሰን አለመግባባት ሲኖር ጉዳዩ በፖለቲካ ስምነት እና ክልሎቹ በሚመርጡት ገለልተኛ ኮሚቴ እንደሚፈታ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይህ ልማድ ፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ሉአላዊነት ላይ ጣልቃ እንዲገባ እድል አይፈጥርለትም ጠቅላይ ፍርድቤቱ በዚህ ረገድ የተሰጠውንም ሥልጣን አያሳጣውም፡፡ ይህ ከመሆኑ አንፃር አሁን በኢትዮጵያ መንግሥት የአስተዳደር ወሰን ኮሚሽን መቋቋሙ ከመሰረታዊ የፌደራሊዝም መርሆች ጋር የሚጣጣም ከመሆኑም በላይ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡

ሕገ-መንግሥታዊነት

ሌላው በኮሚሽኑ መቋቋም ላይ የተነሳው አከራካሪ ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊነቱ ነው፡፡ የኮሚሽኑን መቋቋም የተቃወሙ የፓርላማው አባላት እና የትግራይ ክልል መንግሥት፤ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ የሕገመንግሥቱን አንቀጽ 39፣ 47፣ 48፣ 62/3፣ 62/6 እና ሌሎች አንቀፆችን ይጥሳል፤ ለክልሎ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠውን ሥልጣንም ይጋፋል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የኮሚሽኑ ሥልጣን እና ተግባር በዝርዝር ሲፈተሽ አስተዳደራዊ ወሰኖች በቀጣይነት የሚወሰኑበትንና የሚለወጡበትን መንገድ በተመለከተ ሕገ-መንግሥታዊ መርህዎች ያገናዘበ፣ ግልጽና ቀልጣፋ ስርዓት ወይም የሕግ ማሻሻያ እንዲዘረጋ ሙያዊ ጥናት አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት የማቅረብ እንጂ በጉዳዮቹ ላይ የመወሰን ሥልጣን የለውም፡፡ በተጨማሪም በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በፌዴራል መንግሥት የሚመሩለትን የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግቦችን መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የማቅረብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይህም በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ የሆነ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ያለው የፌዴሬሽ ምክር ቤት ውሳኔ ላይ ለመድረስ የባለሙያ አስተያየት እና ሙያዊ ድጋፍ የሚያገኝበትን ሥርዓት የሚዘረጋ ነው፡፡ የፌደራሉ መንግሥት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለወሰን ውዝግቦች ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ወይም ችግሩን ከመሰረቱ ለማስቀረት የሚረዳ ፖሊሲ ማውጣት ቢያስፈልጋቸው ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ተቋም በመሆን ሊያገለግል ይችላል፡፡

ኮሚሽኑ የክልሎችንም ሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የመወሰን ሥልጣን እስካልተጋፋ ድረስ ጥናቶችን አድርጎ የመፍትሔ ሃሳቦችን ማቅረቡ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ነው ሊባል የሚችልበት ምንም መሠረት የለም፡፡ ይልቁኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት የፖለቲካ ተወካዮች ከመሆናቸው አኳያ ያለባቸውን የሙያ (expertise) ክፍተት የሚደግፍ እና የሚያጠናክር ደጋፊ ተቋም መሆን ይችላል፡፡ የባለሙያዎች አጥኚ ቡድን ማቋቋም የየትኛውም አስፈፃሚ አካል ተፈጥሮአዊ ሥልጣን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የፌደራሊዝም እና የሕግ ጥናት እና ምርምር ተቋማት በዚህ ረገድ ያደረጓቸውን ጥናቶች፤ አስፈፃሚው አካል ለፖሊሲ አቅጣጫዎቹ፤ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ለአሰራር እና ውሳኔዎቹ እንደ ግብአት እንዳይጠቀሙ የሚያግዳቸው ምንም የሕገ መንግሥት መርህ እንደሌለ ሁሉ ጊዜአዊ ኮሚሽን አቋቁሞ የባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ መጠቀም በሕገ መንግሥት ስም የሚወገዝበት ምንም ህጋዊና ምክንያታዊ መሠረት የለም፡፡

ሌላው ጉዳይ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 5፤ ‹ኮሚሽኑ የተሰጡት ኃላፊነቶች ተግባራዊ ሚሆኑት የሕገ መንግሥቱ የተለያዩ አንቀፆች በዚህ ረገድ ያስቀመጧቸው ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው› መሆኑን በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ በተመሳሳይ በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 13/1/አ የሰላም ሚኒስቴር ‹‹የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 እና 62(6) ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች የሚፈቱባቸውን ሁኔታዎች ያመቻቻል›› የሚል ተመሳሳይ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ተቋም በ1994 የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተብሎ ሲቋቋምም ሆነ በያዝነው አመት በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 የሰላም ሚኒስቴር ተብሎ ሲደራጅ የሕገመንግሥታዊነት ጥያቄ ቀርቦበት አያውቅም፡፡

ከዚህ ቀደም ሌላ ተቋም በተመሳሳይ ሥልጣን ሲቋቋም ያልተነሳ የሕገመንግሥታዊነት ጥያቄ አሁን ላይ መነሳቱ ጥያቄው ህጋዊነቱ ሳይሆን ፖለቲካዊ እንደምታው የጎላ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በተመለከተ ሰላም ሚኒስቴር እስከዛሬ ድረስ ሰፋ ያሉ ጥናቶችን አድርጎ ተከራካሪ ክልሎችን ካስማማ በኋላ ስምምነቶቹ ለፌዴሬሽን ምከር ቤት ቀርበው መፀድቃቸው ይታወቃል፡፡ አዲስ የተቋቋመው ኮሚሽን ሕገ መንግሥታዊ የማይሆን ከሆነ የሰላም ሚኒስቴር ባለፉት 18 አመታት በዚህ ረገድ የከናወናቸው ተግባራትም ኢ-ሓገ መንግሥታዊ ሆነው መቆጠር ይኖርባቸዋል፡፡

ቅቡልነት

ከኮሚሽኑ አስፈላጊነት እና ሕገ መንግሥታዊነት በተጨማሪ መታየት ያለበት ሌላው ጉዳይ የኮሚሽኑ ቅቡልነት ነው፡፡ የፓርላማ አባለቱ ካነሷቸወች ነጥቦች መካከልም የኮሚሽኑን መቋቋም በተመለከተ የሚመለከታቸው አካላት በቂ ውይይት አለማድረጋቸው ነው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እና በክክሎች መካከል የሚነሱ የወሰን አለመግባባቶች ከምንም በላይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው እና ለብዙት የደም መፋሰስ እና መጠነ ሰፊ ማህበራዊ ቀውሶች ምክንያት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ጉዳዩን የሚመለከቱ አካላት ህዝባዊ እና ፖለቲካዊ ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸው እንዲሁም ለጉዳዩ የሚሰጠውን መፍትሄ አሳታፊ ማድረግ ለችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ከማበጀት አንፃር ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ክልሎች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የማህበረሰብ ተወካዮች በዚህ ረገድ ውይይት አድርገው እስከ አሁን እነዚህን ችግሮች በመፍታት ረገድ የነበረው ክፍተት ምን እንደሆነ ስምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ኮሚሽኑም ከመቋቋሙ በፊት እንደዚህ አይነት ምክክሮች እና ድርድሮች ተደርገው ቢሆን የኮሚሽኑን ቅቡልነት ማረጋገጥ ይቻል ነበር፡፡

መደምደሚያ

በስፋት እየተከሰቱ ላሉ የአስተዳደር ወሰን ውዝግቦች እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የጉዳዮቹ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መንስኤ ማጥናት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በሆኑ ፖለቲከኞች የሙያ ክህሎት ሊፈፀም እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡ ለዚም ሲባል የባለሙያዎች አጥኚ ብድን (ኮሚሽን) ማቋቋም ከሌሎች ፌዴሬሽች የምንማረው አይነተኛ መፍትሄ ነው፡፡ የኮሚሽኑ አላማም ሆነ የተሰጠው ኃላፊነት ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት የሚደግፍ ፌደራላዊ ስርአቱንም መልክ የሚያሲዝ እንጂ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ሊባል አይችልም፡፡ ሆኖም የኮሚሽኑ መቋቋም ጥርጣሬ ያሳደረባቸው አካላት ያሳዩት ፅኑ ተቀዋውሞ ኮሚሽኑ የሚኖረውን ህዝባዊ ቅቡልነት ሊሸረሽረው ይችላል፡፡ ይህን ያህል ተቀዋውሞ እንደሚያቀርብበት ታውቆ ከነበረ ኮሚሽኑን ከማቋቋም ይልቅ ቀድሞውኑ ተመሳሳይ ኃላፊነት የተሰጠው ሰላም ሚኒስቴር የኮሚሽኑን ተግባራት እንዲፈፅም በሚያስችለውን ሁኔታ ማመቻቸት ተቀባይነት ያለው እና ስልታዊ የፖለቲካ መፍትሔ መሆን ይችል ነበር፡፡ 

አሁንም ቢሆን ኮሚሽኑ ከሰላም ሚኒሰቴር ጋር የሚኖረው ግንኙነት እና ሰላም ሚኒስቴር በዚህ ረገድ የተሰጠው ኃላፊነት ቀጣይነት ምን እንሚሆን አልታወቀም፡፡ በሰላም ሚኒስቴር ስር ያለው የአስተዳደር የወሰን ጉዳዮችን የሚከታተለው ዳይሬክቶሬት እጣ ፋንታም ግልፅ አይደለም፡፡ ነገር ግን በሚኒስቴሩ ስር ያሉ ከሀያ ዓመት በላይ በሀገሪቱ ውስጥ የሚነሱ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎችን በቅርበት ሲከታተሉ የኖሩ ከፍተኛ ባለሙያዎች አዲስ ለተቋቋመው ኮሚሽን ግብአት የሚሆኑበት መንገድ መመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ኮሚሽኑም የተራራቀ ፅንፍ በያዙ የክልል አስዳደሮች እና በጎረቤት ህዝቦች መካከል መግባባት የሚፈጥር፤ የፉክክር እና የጠላትነት ስሜትን የሚያስወገድ፤ የታሪክ እውነታዎችን በማጣራት አሁን ካለው የህዝቦች አሰፋፈር እና ፍላጎት ጋር በተጣጣመ መልኩ ሕዝብን ያሳተፈ የሥራ ሂደት መከተል ይኖርበታል፡፡ ከምንም በላይ ኮሚሽኑ ውሳኔ ሰጪ አካላት ፍትሕ እና ርትዕ ላይ መድረስ የሚችሉበትን ግብአት እና ምክረ ሃሳብ ማመንጨት ከቻለ በርግጥም የተቋቋመለትን አላማ ማሳካት ይቻለዋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Rocks of Hope: Interrogating PM DR Abiy Ahmed’s Re...
በኢትዮጵያ በኢንተርኔት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እና ገደቡ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 16 July 2024