(‘ደረሰኝ የማይሰጥ ከሆነ አይክፈሉ')

ደረሰኝ  ምን ማለት ነው?

የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 19፣120 እና 131(1)(ለ) እንዲሁም የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 82 ላይ የተደነገጉ ድንጋጌዎችን ጣምራዊ ንባብ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ሕጎች  መሠረት በማድረግ የደረሰኝ ትርጉም እና ምንነት፣ የደረሰኞች ዓይነቶች እና ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ግብር ከፋዮችን እነማን እነደሆኑ እንዲሁም ደረሰኝ መሰጠት ያለበት መች እንደሆነ በወፍ በረር መልኩ ለመዳሰስ እሞክራለሁኝ፡፡

ደረሰኝ ማለት የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ማንኛውም ታክስ ከፋይ ከደንበኞቹ ጋር ለሚያከናውነው ግብይትና ለሚሰበስበው ገንዘብ እውቅና የሚሰጥ ሕጋዊ ሰነድ ለደንበኞቹ ቆርጦ በመስጠት በመንግስት የተጣለበትን ግብር የማስከፈል እና የመክፈል ግዴታው የተወጣ ስለ መሆኑ የሚረጋገጥበት  የማረጋገጫ ወረቀት ነው፡፡ የሽያጭ መመዝገብያ መሣርያዎች ስለመጠቀም ለመደንገግ በሚኒስትሮች ምክርቤት የወጣ ደንብ ቁጥር 139/2007 አንቀጽ 2(3) ላይም ደረሰኝ (Receipt) ማለት የጥሬ ገንዘብ ሽያጭ ሲሆን፣ የዱቤ ሽያጭ ኢንቮይስና ያለክፍያ የሚሰጥ እቃ ወይም የአገልግሎት ማስተላለፍያ ደረሰኝን ይጨምራል በማለት ይደነግጋል፡፡በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008  አንቀጽ 19(3) መሠረት የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ማንኛውም ግብር ከፋይ ደረሰኝ እንዲሰጥ ይገደዳል፡፡የደረሰኙ አይነት በህግ መሠረት የሚወሰን ሆኖ ማንኛውም ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለበት ግብር ከፋይ ካለደረሰኝ ግብይት ካከናወነ እንደየሁኔታው በአንቀጽ 120 ወይም በአንቀጽ 131(1)(ለ) መሠረት በወንጀል ይጠየቃል፡፡

የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ማን ነው? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ በመሆኑ መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 82(1) እና (2) ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው የንግድ ስራ ገቢ የመክፈል ሃላፊነት ያለባቸው የደረጃ ‘ሀ’ እና ‘ለ’ ግብር ከፋዮች በፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ መሠረት የተዘጋጁ የሂሳብ መዝገቦችን የመያዝ ግዴታ አለባቸው፡፡ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮችን በተመለከተ ግን የሚኒስትሮች ምክርቤት በሚያወጣው ደንብ በሚወሰነው መሠረት ጠቅላላ የሽያጭ ገቢያቸውን የሚያሳይ ወይም ሌላ አስፈላጊ መዝገብ ሊይዙ እንደሚችሉ ተጠቃሹ የአዋጁ ድንጋጌ በንኡስ አንቀጽ 3 ላይ ይደነግጋል፡፡በሌላ አገላለጽ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ እንዲይዙ የሚገደዱበት የህግ አግባብ የለም ማለት ነው፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ እና በተግባር ላይም በህግ ባለሙያዎች መካከል ልዩነት እየፈጠረ የሚገኘው አንድ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋይ በፍላጎቱ የሂሳብ መዝገብ መያዝ የጀመረ እና የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ያስገባ ከመሳርያው በሚወጣ ደረሰኝ ወይም ካለደረሰኝ ከተገበያየ በወንጀል ይጠየቃል ወይስ አይጠየቅም የሚለው ሲሆን የታክስ አስተዳደር አዋጁም በግልጽ ያልመለሰው ጉዳይ በመሆኑ  በአሰራር ላይ ወጥነት እና ተገማችነት ያለው ውሳኔ ያለመሰጠት ችግር ይስተዋላል፡፡

ሆኖም ግን የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 120 እና 131(1)(ለ) በዚሁ ኣዋጅ ተደንግጎ ከሚገኘው አንቀጽ 19 (3) እና ከፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 82(1) - (3) ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች ጋር በጣምራ አገናዝበን ካልተረጎምነው በስተቀር ፍትሃዊ፣ ሚዛናዊ እና የህጋዊነትን መርህ መሠረት ያደረገ  ውሳኔ መስጠት አንችልም፡፡ እነዚህ ግብር ከፋዮች( የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች) በፍላጎታቸው እና በራሳቸው ተነሳሽነት የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ አስገብተው ሲያበቁ የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው ላለመጠቀም የሚያስችል ምንም አይነት አስገዳጅ ሁኔታ ሳይገጥማቸው ከሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው በሚወጣው ደረሰኝ መሠረት ካልተገበያዩ ወይም  ከነአካቴው ካለደረሰኝ ግብይት ከፈጸሙ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 በአንቀጽ 120 ወይም 131(1)(ለ) መሠረት ሊጠየቁ ይገባል የሚል ጽኑ አቋም በመያዝ የሚከራከሩ የህግ ባለሙያዎች ቢኖሩም ከድንጋጌዎቹ ይዘት፣መንፈስ  እና አላማ አንጻር ስናየው ግን ውሃ የሚቋጥር ክርክር ነው ብየ ኣላምንም፡፡

በእርግጥ እነዚህ ግብር ከፋዮች በፍላጎታቸው የሂሳብ መዝገብ ከያዙና የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ቢጠቀሙ  የሚበረታታና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የታክስ አሰባሰብ መርህን ስኬታማ የሚያደርግ ከመሆኑ በተጨማሪ ጊዜ እና ጉልበት ቆጣቢ በመሆኑም ጠቀሜታው እጅግ በጣም የላቀ ነው፡፡  ይህን የውዴታ ሃላፊነታቸው ካልተወጡ ግን በአመታዊ የሽያጭ መጠን ላይ የተመሰረተ የግምት መደበኛ  የቁርጥ ግብር ወይም በሌላ የቁርጥ ግብር ዘዴዎች ግብር  እንዲከፍሉ ከማድረግ ውጪ ደረሰኝ ባለመቁረጣቸው ምክንያት ብቻ በወንጀል ሃላፊነት እንዲጠየቁ የሚያደርግ ግልጽ የሆነ የህግ መሠረት የለም፡፡ምክንያቱም የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 82(3) እና የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 19፣120 እና 131(1)(ለ) ጣምራዊ ንባብ የሚሰጠን ትርጉም የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ እንዲይዙ ሆነ ድረሰኝ እንዲሰጡ ሊገደዱ እንደማይችሉ ነው፡፡   

የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ሁለት ዓይነት ደረሰኞችን በግልጽ እውቅና ሰጥቷል፡፡ እነሱም፡-

1) የእጅ በእጅ ደረሰኝ፡-

የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ለመጠቀም ያልተመዘገቡ ወይም ተመዝግበው ነገር ግን በተለያዩ አስገዳጅ እና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሊጠቀሙበት ያልቻሉ   ነጋዴዎች የእጅ በእጅ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ይህ ግዴታ ሳይወጡ ከቀሩ ግን በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 120 መሠረት በወንጀል ይጠየቃሉ፡፡የዚህ አንቀጽ ርእስ ስናየውም ከደረሰኝ ጋር የተያያዙ ጠቅላላ ወንጀሎች በማለት ያስቀምጧል፡፡ህጉ በዚሀ መልኩ የተቀረጸው ማንኛውም የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ግብር ከፋይ ሆኖ የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ለመጠቀም ያልተመዘገበ ወይም ተመዝግቦ መሳርያው ግን በበቂ ምክንያት ሊገለገልበት ባለመቻሉ ምክንያት የእጅ በእጅ ደረሰኝ እንዲሰጥ ለማስገድድ እና ይህ ግዴታውን ወደ ጎን በመተው ያለደረሰኝ ግብይት ሲያከናውን ከተገኘ ግን በዚሁ አንቀጽ መሠረት በወንጀል እንዲጠየቅ በማሰብ  የተቀረጸ የህግ ማእቀፍ ነው፡፡

2) በሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ የታተመ ደረሰኝ፡-

 የሽያጭ መመዝገበያ መሳርያው አገልግሎት መስጠት እየቻለ ግብር ከፋዩ ከዚህ ውጭ በታተመ ደረሰኝ መስጠት አይችልም፤ካለደረሰኝ ግብይትም ማከናወን አይችልም፡፡ይህን ክልከላ በመተላለፍ ከሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ውጭ በታተመ ደረሰኝ ወይም ካለምንም ደረሰኝ ግብይት ያከናወነ ማንኛውም ከሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ የወጣ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለበት ግብር ከፋይ በአንቀጽ 131(1)(ለ) መሠረት በወንጀል ይጠየቃል፡፡

ክርክሬን ይበልጥ ለማጠናከር በመጀመርያ ደረጃ የአንቀጽ 131(1)(ለ) ዋና አላማ ምንድን ነው የሚል መሰረታዊ ጥያቄ መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡የዚሁ አንቀጽ ዋና አላማ አንድን ነጋዴ ታክስ ለመክፈል ወይም ለማስከፈል የተሰጠውን የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ በንግድቤቱ ለይስሙላ ብቻ በማስቀመጥ ወይም በአግባቡ ጥቅም ላይ ላለማዋል አስቦ ከመሳርያው ከወጣው ደረሰኝ ውጪ ወይም ካለምንም ደረሰኝ ግብይት ሲያከናውን ለመቅጣት ነው፡፡ ይህ ማለት የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው ላለመጠቀም የሚያስችል አስገዳጅ ሁኔታ ካልገጠመህ በስተቀር ሌላ ምትክ ደረሰኝ መስጠትም ሆነ ከነጭራሽ ደረሰኝ አለመስጠት አትችልም የሚል  ግልጽ ክልክላ ያስቀምጣል፡፡ የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው በስራ ላይ እያለ በመሳርያው ከታተመው ደረሰኝ ውጪ ሌላ(ምትክ) ደረሰኝ በመስጠት ግብይት የማከናወን ተግባር በዚህ አንቀጽ እንደሚያስቀጣ በማያሻማ ሁኔታ የተቀመጠ በመሆኑ ብዙ የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም፤በተግባር ላይም  በአቃብያነ ህግ ሆነ በዳኞች ወጥነት ባለው ሁኔታ እየተተገበረ ስለሚገኝ የፍትሃዊነት እና የእኩልነት ጥያቄ ያስነሣል የሚል ስጋት የለኝም፡፡በዚህ አንቀጽ ላይ በህግ ባለሙያዎች መካከል የአተረጓጎም ልዩነት እየፈጠረ ያለውም ‘ከሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ  ከታተመ ደረሰኝ ውጭ’ የምትለዋ ሃረግ ሳይሆን ከዚች ሃረግ ቀጥላ በኣማራጭነት የተቀመጠችው ‘ያለደረሰኝ ግብይት ማከናወን’ የምትለዋ ሃረግ በመሆኑ ከህጉ ይዘት፣ አጠቃላይ አላማ እና   አቀራረጽ አንጻር የራሴ አስተያየት ለመስጠት እሞክራለሁኝ፡፡ የድንጋጌው ይዘት ቃል በቃል እንደሚከተለው አሰፍረዋለሁኝ ፡

.

ለ) መሳርያው በጥገና ላይ ባለበት ጊዜ ወይም በሌላ በቂ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር  በሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ከታተመ ደረሰኝ ውጪ ወይም ያለደረሰኝ ግብይት ካከናወነ ፣ከሁለት አመት በማያንስ እና ከአምስት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል በማለት ደንግጓል፡፡

በዚሁ አንቀፅ መሠረት የሚቋቋም የወንጀል ተግባር እንዲኖር መጀመርያ የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው በስራ ላይ የመኖር ጉዳይ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች መሳርያው አገልግሎት መስጠት የማይችል ከሆነ ግን ይህ የህግ ድንጋጌ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው አንቀጹ በግልባጩ ስናነበው የምንገነዘበው ይሆናል፡፡ (ካልሆነ በስተቀር የሚለው ሀረግ አጠቃላይ ከህጉ የአረፍተ ነገር ሙሉ ይዘት ጋር አያይዘን በተገላቢጦሽ አንብበን በሚሰጠን ትርጉም መሠረት የዚህ ህግ ድንጋጌ ተፈፃሚ የሚሆነው የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው አገልግሎት መስጠት እየቻለ ነጋዴው በአግባቡ ሊጠቀምበት ሳይፈልግ ሲቀር ብቻ ይሆናል ማለት ነው፤ነጋዴው ከአቅሙ በላይ የሆነ ክስተት አጋጥሞት መሳርያው ከአገልግሎት ውጪ በመሆኑ ምክንያት ደረሰኝ ሳይሰጥ ከቀረ ግን በዚሁ አንቀጽ ሊጠየቅ አይችልም)፡፡የአንቀጽ  131 አጠቃላይ ይዘት እና አቀራረጽ  ከርእሱ  ጀምሮ ሲታይም ‘ከሽያጭ መመዝገብያ መሳርያዎች ጋር በተገናኘ የሚፈጸሙ ወንጀሎች’ ያለበት የራሱ የሆነ አላማ ስላለው ነው፤ይህ አንቀጽ አገልግሎት መስጠት የሚችለው ደረሰኞችን ለማውጣት ወይም አገልግሎት ለመስጠት የሚችል ማሽን እያለ ከማሽኑ ባልወጣ ደረሰኝ መስጠት ወይም ከነጭራሽ ደረሰኝ ያለመስጠት ተግባር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ስለሆነም ’ካለደረሰኝ ግብይት’ የምትለው ሀረግ ከአንቀጹ ሙሉ ይዘት እና አላማ ጋር አያይዘን መተርጎም ካልቻልን ከሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ውጪ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ከሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ጋር ተያያዘው ከሚፈጸሙ ወንጀሎችን በአግባቡ መለየት ሆነ መተግበር አንችልም፡፡      

በሌላ አገላለጽ በአንቀጽ 131(1) (ለ) መሠረት አንድ ወንጀል የሚቋቋመው የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው በስራ ላይ እያለ እና ከዚሁ መሳርያ የሚወጣው ደረሰኝ መስጠት እየተገባው በሌላ መንገድ ደረሰኝ መስጠት ወይም ከነአካቴው ደረሰኝ ያለመስጠት ሁኔታ ሲኖር ብቻ መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም ማንኛውም ነጋዴ በታክስ አስተዳደር አዋጅ አንቀጽ 131 (1) (ለ) መሠረት ሊቀጣ የሚችለው የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው በስራ ላይ እያለ ወይም አክቲቭ ሆኖ እያለ፡-

 አንድ ነጋዴ በንግድ ቤቱ ስም የሽያጭ መመዝገብያ  መሳርያ አስገብቶ ሲያበቃ በበቂ ምክንያት(ለምሳሌ፡-መብራት ባለመኖሩ፣ብልሽት ገጥሞት ለጥገና በመላኩ ወዘተ…) የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው ሊጠቀምበት ባለመቻሉ ከመሳርያው የወጣ ደረሰኝ ሆነ የእጅ ከእጅ ደረሰኝ ሳይሰጥ ግብይት ካከናወነ በምን እንጠይቀው የሚል መሰረታዊ ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ሆኖም አንድ ነጋዴ የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ተመዝጋቢ ሆኖ እያለ ከመሳርያው በወጣ ደረሰኝ ብቻ አልተገበያየም ወይም ካለ ደረሰኝ ግብይት ፈጽሟል በማለት  በታክስ አስተዳደር አዋጅ አንቀጽ 131(1)(ለ) መሠረት ከመጠየቃችን በፊት የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያው አገልግሎት መስጠት ይችል ነበር ወይስ አይችልም ነበር የሚለው መሰረታዊ ነጥብ አስቀድመን ማጣራት ይጠበቅብናል፡፡ እርግጥ ነው! በምንም መልኩ ቢሆንም ደረሰኝ መስጠት ግዴታ ያለበት ማንኛውም ነጋዴ ካለደረሰኝ የተገበያየ እንደሆነ በወንጀል ይጠየቃል፡፡ይህ አጠቃላይ መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤የእጅ በእጅ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለበት ነጋዴ እና ከሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ የሚወጣ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለበት ነጋዴ የሚፈጸምባቸው የህግ ድንጋጌና የሚጣልባቸው የቅጣት መጠን የተለያየ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል ፡፡

 በዚሁ መሠረት አንድ የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ያስገባ ነጋዴ መሳርያው አገልግሎት የማይሰጥ ከሆነ በመሳርያው መሠረት የወጣ ደረሰኝ እንዲሰጥ የሚጠበቅበት ሁኔታ እንደማይኖር ግልፅ ቢሆንም የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ሳያስገቡ በመቅረታቸው ምክንያት የእጅ ከእጅ ደረሰኝ የመስጠት ህጋዊ ግዴታ ካለባቸው ነጋዴዎች ጋር በእኩል ይህ ነጋዴም የእጅ ከእጅ ደረሰኝ እንዲሰጥ በታክስ አስተዳደር አዋጅ አንቀፅ 120 መሠረት ይገደዳል፤ግዴታው ካልተወጣም በዚሁ ድንጋጌ መሠረት ሊቀጣ ይገባል፡፡

በመሰረቱ አገልግሎት የማይሰጥ የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ያላቸው ነጋዴዎች እና ከመጀመርያውንም የሽያጭ መመዝገብያ መሳርያ ያላስገቡ ነገር ግን የእጅ በእጅ ደረሰኝ ለመስጠት የሚገደዱ ነጋዴዎች ካለደረሰኝ ግብይት ሲያከናውኑ ከተያዙ በተመሳሳይ የህግ ድንጋጌ ሊከሰሱ እና ሊቀጡ ይገባል፡፡ አንደኛ የሁለቱም ድርጊቶች ፍጹም ተመሳሳይ በመሆናቸው በተመሳሳይ የህግ ድንጋጌዎች በእኩል አይን እንዲዳኙ ማድረግ የእኩልነት መርህን ማክበር ነው፤ሁለተኛ የድንጋጌዎቹ አቀራረጽ እና ይዘት በዚሁ መልኩ የተቃኙ ይመስላል፡፡

              ደረሰኝ መሰጠት ያለበት መቼ ነው?

አንድ ነጋዴ ላከናወነው ግብይት ደረሰኝ መስጠት ያለበት መች ነው የሚለው ሌላ መመለስ ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 22(1) በአዋጅ ቁጥር 609/2001 እንደተሻሻለው እና ስለ ንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ የወጣ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 17 (1) ስር ግብይቱ እንደተከናወነ ወድያውኑ ደረሰኝ መሰጠት አለበት በማለት የደነገጉ ቢሆንም ‘ወድያውኑ’ ማለት መች ነው የሚለውን ጥያቄ በግልጽ እና በማያሻማ ሁኔታ አልገለጹም፡፡ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀፅ 120 እና 131(1)(ለ) ቢሆኑም ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለበት ማንኛውም ታክስ ከፋይ እቃዎቹን ለሚገዛው ሰው ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ እንዳለበትና ግዴታውን ሳይወጣ ሲቅርም ሊጣል የሚችለውን ቅጣት ከመደንገግ ውጪ ደረሰኙ የሚሰጥበት ጊዜ አስመልክቶ መች እንደሆነ ግን በግልጽ ያስቀመጠው መርህ የለም፡፡ይህ የህግ ክፍተት በቀላሉ ሊታለፍ የማይገባ እና ወጥነት እና ተገማችነት ያለው ውሳኔ ለመስጠት ቀላል የማይባል እንቅፋት በመፍጠር ረገድ የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በነጋዴዎች በኩልም  ደረሰኝ ቆርጠን ነገር ግን እቃ ገዢው ተጣድፎ ደረሰኙን ጥሎ በመሄዱ ምክንያት ወድያውኑ ደረሰኝ አልቆረጣችሁም ተብሎ በወንጀል የምንጠየቅበት አግባብ ትክክል አይደለም የሚሉ አቤቱታዎች እንዲቀርቡ ምክንያት ሆኗል ብዬ አስባለሁኝ፡፡ በተለይም ከጉምሩክ ባለስልጣን መስርያ ቤት በአንዳንድ ንግድ ቤቶች በጥናት (Operation) ተመድበው በየንግድቤቱ እየዞሩ ግብይት በመፈጸም የንግድ ቤቱ ባለቤት ወይም አስተናጋጆችን በማጣደፍ የገዙትን እቃ ይዘው በመውጣት ከደቂቃዎች ቆይታ በኃላ ተመልሰው ሲመጡ ደረሰኙ ተቆርጦና ተዘጋጅቶ ቢያገኙትም ከወንጀል ተጠያቂነት አያድንም፡፡

በሌላ በኩል መንግስት ማግኘት ያለበትን ግብር እስካገኘ ድረስ ደረሰኙ መቼም ይቆረጥ መች በወንጀል ሊያስጠይቅ አይገባም የሚል ክርክርም ይነሳል፤ይህ ክርክር ግን ውሃ የሚያነሳ ክርክር አይሆንም፡፡ የህጉ አላማም የሚያሳካ አይደለም፡፡ምክንያቱም ሽያጩ ሲከናወን ወድያውኑ እቃውን ለገዛ ግለሰብ ደረሰኝ በቀጥታ ካልተሰጠው ነጋዴው ደረሰኙን ሳይቆርጥ በመቅረት መንግስትን የማጭበርበር እድሉ ሰፊ ከመሆኑ በተጨማሪ ለተጠቀመው የፍጆታ እቃ ወይም አገልግሎት ከኪሱ ለመንግስት በተዘዋዋሪ ግብር የሚገብር ሰውም የከፈለውን ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ሳይሆን በነጋዴዎች ኪስ እንዳይቀር ለመብቱንም ለግዴታውንም በሃላፊነት የሚታገል እና መንግስትን የሚተባበር ዜጋ በመፍጠር  ግብር የመክፈል ግዴታ የሚረጋገጠው ወድያውኑ ለገዢው ደረሰኝ ተቆርጦ ከተሰጠው ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ደረሰኝ ለገዢው መሰጠት ያለበት ሽያጭ ሲከናወን ወድያውኑ መሆን አለበት፡፡ መሰጠት ያለበትም በቀጥታ እና ወድያውኑ ግዢውን ላከናወነ የነጋዴው ደንበኛ ለሆነው ገዢ እንጂ ደረሰኝ በድብቅ ወይም ገዢው ከወጣ በኃላ ተቆርጦ ከነጋዴው ጋር እንዲቀመጥ አይደለም፡፡

ስለ ንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ የወጣ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 17 (1) ስንመለከተውም ማንኛውም ነጋዴ ለሸጠው እቃ ወይም አገልግሎት ለሸማቹ ወድያውኑ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ አለበት በማለት ይደነግጋል፡፡በዚህ የህግ ድንጋጌም ወድያውኑ የሚባለው መች ነው የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ የማይቀር ነው! ይህ ጥያቄ ለመመለስ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 609/2001 47ሀ(9)(ሐ) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ማየቱ እጅጉን ይጠቅመናል፡፡ ማንኛውም ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ ያለበት ግብር ከፋይ ‘ደረሰኝ የማይሰጥ ከሆነ አይክፈሉ’ የሚል ጽሁፍ ያለበት ማስታወቅያ  በግልጽ እና በሚታይ ቦታ  ለጥፎ ካልተገኘ ብር  አንድ ሺህ ይቀጣል በማለት ደንግጓል፡፡ይህን ማስታወቅያ አለመለጠፉ ብቻ አንድ  ሺህ ብር እንደሚቀጣ በሚገባ የሚያውቅ ነጋዴ ደረሰኝ ሳይቆርጥ ለገዢው እቃውን አስረክቦና ታክስን ጨምሮ ሂሳብ ተቀብሎ ከተለያዩ በኃላ  ገዢውም ከደቂቃዎች  ቆይታ በኃላ እንደገና ተመልሶ ሲመጣ ደረሰኝ ተቆርጦ ስላገኘ ብቻ ነጋዴው ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ መሆን አለበት የሚለው ክርክር ጠቅላላ የህጉን አላማ የሚስት እና የታክስ ቁጥጥር ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ምክንያቱም ግብይቱ ሲከናወን ወድያውኑ ደረሰኝ ያልቆረጠ ነጋዴ ተመልሰው  እንዳይመጡብኝ በሚል ጥርጣሬ  እና ፍርሃት ምክንያት ከግብይት በኃላ ደረሰኝ መቁረጥ የህጉ አላማ አይደለም፡፡ ህግ ህግ ነው ፤ሊከበር እና ሊሰራበት ይገባል፡፡ነጋዴው እና ሸማች(ገዢ) በመጀመሪያ ደረጃ መቀያየር ያለባቸው ደረሰኝ እና ገንዘብ መሆን አለበት፤ የእቃ (የአገልግሎት) እና የገንዘብ መቀያየር ከደረሰኙ በፊት ቀድሞ ከመጣ ግን ደረሰኝ ያለመቁረጥ እቅድን መከላከል አይቻልም ፤መንግስትን የማጭበርበር እድልም በሰፊው ይጨምራል፡፡ህጉ ይህን ለመከላከል ሲል ማንኛውም ነጋዴ ሂሳብ ከመቀበሉ በፊት ደረሰኝ እንዲቆርጥ ያስገድዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ግብይቱ(ሽያጩ) እንደተከናወነ ወድያውኑ ደረሰኝ መሰጠት እንዳለበት የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 22(1) በአዋጅ ቁጥር 609/2001 የተሻሻለው  የአንቀጹ ድንጋጌ ያስገድዳል፡፡ ሽያጭ ተከናወነ የሚባለው መች እንደሆነም የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 11(1) እና(2) በግልጽ  የደነገገ ሲሆን እነሱም፡-

ከነዚህ ድንጋጌዎች ጋር በማያያዝ ስለ ሽያጭ ክንዋኔ እና ደረሰኝ አሰጣጥ አስመልክቶ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቅጽ 15 ሰበር መዝገብ ቁጥር 86672 ላይ የሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም ስንመለከትም፡-

በመርህ ደረጃ ሽያጭ ተከናወነ የሚባለው ደረሰኝ ሲሰጥ መሆኑና እቃዎቹ ለተረካቢው ዝግጁ ሆነው ሲቀመጡ፣ የእቃዎቹ ርክክብ ሽያጭ መፈጸም ወይም አገልግሎት መስጠት አንዲሁም እንደየሁኔታው የእቃዎችን ርክክብ ማጓጓዝን የሚያካትት ስለመሆኑ፤ ይልቁንስ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ   ለተከናወነው ግብይት ሂሳብ መከፈሉ ወይም አለመከፈሉ እንደ ቅድመ ሁኔታ ሊወሰድ እንደማይችል በግልፅ ወስኗል፡፡